በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኛነት የተፈረጀው ሕወሓት በግብርም የጭካኔና የሽብር ጥግ ድረስ ሔዶ ብዙ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋት እያደረሰ እንደሆነ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ድርጅቱ በሽብር የተፈጠረ በሽብር ሲገዛ የኖረና የመጨረሻ እስትንፋሱ እስክትወጣም በሽብር እየሞተ ያለ ነው።
የዚህ መሰሪ ኃይል እኩይ ተግባራት ዛሬ እንደ አዲስ የተጀመሩ ሳይሆን ትናንት የሀገሪቱን መንግስታዊ ሥልጣን ይዞ በቆየባቸው ዓመታት በሕግ ስም ሲተገበሩ የኖሩ ናቸው። በሕዝብ ትግል ከስልጣን ተገፍትሮ ሲወድቅና ወደ መጀመሪያ የሽፍትነት ዘመኑ ሲመለስ የማስመሰያ ጭምብሉን አውልቆ የግድያ፣ የዘረፋና ሀገር የማፍረስ ስራውን በግልጽ ቀጥሎበታል።
በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት የምሞክረው ትህነግ ትናንት በሕግ ስም ሲፈጽማቸው የነበሩ የግድያና የጥፋት ስራዎቹን በማንሳት ያለፈውን በሚገባ ማስታወስ በዛሬው የማወናበጃ ትርክቱ በጥቂቱም ቢሆን ላለመደናገር ይረዳል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። በዓለም ታሪክ እንደታየው እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ ኢ-ሰብዐዊ ድርጊት፣ ማህበራዊ ምስቅልቅል እና ጉዳት በሕዝባቸው ላይ ያደረሱ የፖለቲካ ቡድኖችና መሪዎች በታሪክ መድረክ ላይ ወጥተው ጥቁር ጠባሳ ጥለው አልፈዋል።
የአንደኛው የዓለም ጦርነት ሽንፈታቸውን ለመበቀል በአጉል የዘረኛነትና ከእኔ በላይ የለም ከሚል የእብደት አስተሳሰብ ተነስተው ሀገሮቻቸውን ለውድመት ዳርገው ለሌሎች ሕዝቦችም የእልቂት ምክንያት የሆኑ አዶልፍ ሒትለርና ቤኒቶ ሞሶሊኒ ተጠቃሾች ናቸው። በቅርብ ጊዜ ታሪክ ደግሞ የእራሱን ሕዝብ በጭፍን ኮሚኒስታዊ የጭካኔ እርምጃው የጨረሰው የካምቦዲያ ገዢ የነበረው ፖልፖትና ቡድኑ፤ በዜጎቹ ላይ አሰቃቂ ግድያና አፈና የፈጸመው የቺሊው ወታደራዊ ጁንታ አውግስቶ ፒኖቼ እና የአፍሪካው አራጅ እየተባለ የሚታወቀውን ኢዲአሚን ዳዳን መጥቀስ ይቻላል። በኢትዮጵያ ሀገራችም እንደ አለመታደል ሆኖ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ለሀገራችን ወርቃማ ታሪክና ለሕዝባችን ትልቅነት የማይመጥን ትህነግ የተባለ ጨካኝና መሰሪ የሆነ ሀገር-ጠል ቡድን በመንግስታዊ ስልጣን ላይ ሆኖ የሚጠላቸውን ሀገርና ሕዝብ ሲገዛ ቆይቷል። በታሪክ እንደታዩት አምባገነኖችና ፋሺስቶች ሕወሓትም ከእኔ ውጪ ሀገር ሊመራ የሚገባው ኃይል የለም፣ በደም ያገኘሁትን ስልጣን ለሌላ አሳልፌ አልሰጥም፣ እኔ ሀገር ካልመራሁ ሁሉ ነገር ፍርስርሱ ይውጣ የሚል አጥፊ ዓላማ ይዞ የተነሳ በመሆኑ ያደረሰውና እያደረሰው ያለው ጥፋት ከላይ ካነሳሁዋቸው አምባገነኖች ቢበልጥ እንጂ የሚተናነስ አይሆንም። ይህ ቡድን ዛሬ ላይ የአውሬ ማንነቱ ገሀድ ወጥቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ለአማራ ሕዝብ ስር የሰደደ ጥላቻ ያለው መሆኑን አሳይቷል። ይህንን ጥላቻውንም በደረሰባቸው ቦታዎች ሁሉ ሴቶችን እየደፈረ፣ ሕጻናትንና ሽማግሌዎችን ሳይቀር እየገደለ እያፈናቀለና እየዘረፈ በተግባር እየገለጸ ይገኛል። ይህ ጨካኝ የሽብር ቡድን መንግስታዊ ስልጣኑን በበላይነት ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ዓመታት በሕገመንግስታዊ ስርዓት ስም ተሸፍኖ የሕዝባችንን አንድነት ሲከፋፍል ሲያዳክም ከጫካ ይዞት በመጣው እንደወረደ ሲተገብረው በቆየው እስታሊናዊ የመገነጣጠልና ትናንሽ መንግስታት የመፍጠር ሴራ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለአደጋ አጋልጧል። አሁንም እያጋለጠ ይገኛል። በብዙ መስዋዕትነትና የታሪክ ውጣ ውረድ የተገነባችውን ኢትዮጵያ ለማዳከምና ለማፍረስ ሕዝቦቿን ለመበታተን ደጀን በሆኑት እና የሕዝቦች ስቃይ በሚያስደስታቸው ምዕራባውያን እየተደገፈ የሚችለውን ሁሉ እኩይ ተግባራት ፈጽሟል፣ እየፈጸመም ይገኛል።
የሚከፋው ደግሞ ቡድኑ ባለፉት ዓመታት በአገዛዙና መንግስታዊ የአመራር ዘይቤው የአስመሳይነት የአታላይነትና ብልጣብልጥነት ባህርይ ይዞ መቆየቱ ነው። ቡድኑ በአገዛዝ ዘመኑ በሕግ ስም ተሸፍኖ የፈጸማቸው የጭካኔ ተግባራት ከእርሱ በፊት የነበሩት መንግስታት እንኳ ያልፈጸሟቸው ናቸው ማለት ይቻላል። አጼ ኃይለስላሴ በአገዛዝ ዘመናቸው የሚነቀፉባቸው ነገሮች
የነበሩ ቢሆንም ለሁለት ጊዜያት ባወጧቸው ሕግጋተመንግስት በዲሞክራሲና ሕጋዊነት ጭንብል እራሳቸውን ሳይሸፍኑ በግልጽ ንጉሳዊ ስልጣናቸው ከመለኮት የተሰጠ የማይደፈርና የማይገሰስ እንደሆነ በሕገመንግስት ደንግገው ሀገሪቱን መርተዋል። የንጉሱን ዘውዳዊ ስርዓት የተካው ወታደራዊ መንግስት አምባገነን እንደነበረ አይካድም። በወቅቱ መነሻው ምንም ይሁን በቀይ ሽብር ስም ብዙ ወጣቶች ተገድለዋል። ለሀገራቸው የደከሙ የንጉሱ ባለስልጣናት፣ ምርጥ ወታደራዊ መኮንኖች ምሁራን በግፍ ተረሽነዋል። ይሁን እንጂ የደርግ መንግስትና ያዋቀረው ስርዓት በዘረኛነትና ዝርፊያ ላይ የተመሰረተ አልነበረም።
ሁሉንም ኢትዮጵያውን በእኩል የሚያይ በዘረፋ የማይታማ ባመነበት ርዕዮተ-ዓለም ጠንካራና የበለጸገች ሀገር የመፍጠር ዓላማ ነበረው። ከመነሻው ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን ሀገራዊ መፈክር ይዞ የተነሳው ደርግ እንደ ትህነግ የአስመሳይነት ባህርይ ያልነበረውና የአገዛዝ መልኩን በዲሞክራሲ ጭምብል ሳይሸፍንና ሳይቀባባ በግልጽ በብቸኛው የኢሰፓ መሪነት ለሠርቶ አደሩ የበላይነት የሚታገል እንደሆነ አውጆ ሀገሪቱን የመራ ኃይል ነበር። በተቃዋሚዎቹ ላይ የወሰደው የጭካኔ እርምጃ በታሪክ መኮነን ያለበት ቢሆንም እንደ መሰሪው ትህነግ ቀን ቀን ስለ ዜጎች መብቶች መከበር እያወራ በጨለማ የሚገድል ተንኮለኛ መንግስት ግን አልነበረም።
በአንጻሩ በትህነግ ቁንጮነትና አድራጊ ፈጣሪነት ሲዘወር የነበረው የይስሙላ ፌዴራላዊና ዲሞክራሲያዊ መንግስታዊ አስተዳደር ግን በሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ሽፋን ይፈጽማቸው የነበሩት ሀገር ያወቃቸው ፀሐይ የሞቃቸው ኢ-ሰብዐዊ የማሰቃየት ድርጊቶችና ግድያዎች የሀገርንና ሕዝብን ክብርና ሕልውና ያዋረዱ ተግባራት ሲታዩ ስርዓቱ በጭካኔው አምባገነን ከሚባለው ደርግ ጋር እንኳ ሊወዳደር የሚችል አይደለም።
ከመነሻው የተፈጠረበት በማጥፋት የታጀበው ማርክሳዊ ሌኒናዊ የሆነው የበረሀ ርዕዮተ-ዓለሙ በኋላም ቀባብቶ ያመጣው ግራ አጋቢ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መመሪያው ከጠባብ ብሔረተኛነት ፕሮግራሙ ጋር ተዳቅለው ሌሎችን የማይቀበልና የሚንቅ ለመቻቻል ለሀሳብ የበላይነት ቦታ የማይሰጥ በማጥፋትና እኔ ብቻ በሚል የታወረ ሀሳብ የሚመራ ድርጅት አድርገውታል የሚል እምነት አለኝ። ይህንንም የማጥፋትና ከእርሱ ውጪ ያለውን ሁሉ በጠላትነት የመፈረጅ አባዜ በቅርቡ እንኳ በመስከረም 2013 ዓ.ም ያዘጋጀውና ይፋ ያወጣው ምስጢራዊ ሰነድ ያሳያል።
የተፈጠረበትን ሌሎችን የማጥፋት ዓላማና ተግባር በስፋት አሁንም ቀጥሎበት ይገኛል። በታሪክ አጋጣሚ በቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሚያ ዋዜማ የደርግ አጋሮች የነበሩት የምስራቁ ሶሺያሊስት ጎራ ሀገሮች መዳከምና ድጋፍ መቀነስ የምዕራባውያን ሴራና ጣልቃገብነት ተደማምሮ ይህ ሽብርተኛ ቡድን በለስ ቀንቶት በ1983 ዓ.ም የሀገሪቱን መንግስታዊ ስልጣን ለመቆጣጠር ችሏል። በዚህ ወቅት በብልጣ ብልጥነቱ ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ በመሽከርከር በተፈጥሮው የሌለውንና የማያምንበትን የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጠበቃ የመድብለ-ፓርቲና የፌዴራላዊ ሥርዓት ፊት አውራሪ ሆኖ ሕገመንግስት እንዲጸድቅ አደረገ።
ይሁን እንጂ ከእባብ እንቁላል የእርግብ ጫጩት እንደማይፈለፈል ሁሉ ትህነግ እራሱ ላወጣው ሕገመንግስት የማይገዛ ለሕገመንግስታዊ ድንጋጌዎች መከበር ደንታ ያልነበረው ተግባራቱ ከቃላቱ በእጅጉ የማይገናኙ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው እውነት ነው። የትህነግን አስመሳይነት በሕገመንግስቱ ከተቀመጡ አንዳንድ ድንጋጌዎች አንጻር በተግባር ይፈጸም የነበረውን በማነጻጸር መመልከት ይቻላል። ሕገመንግስቱ ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ድንጋጌዎች የያዘ ቢሆንም የዜጎችንና ቡድኖችን መብቶች ሊያስከብሩና ዋስትና ሊሰጡ የሚችሉ በዛ ያሉ ጠቃሚ ክፍሎችን ይዟል።
በተለይ በሕገመንግስቱ በምዕራፍ ሶስት ስር ከዓለም-ዐቀፍ የሰብዐዊ መብቶች ሕግጋት ስምምነቶችና ዓለም-ዐቀፍ ሰነዶችና መርሆዎች ጋር የሚጣጣሙ የመሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች መደንገጋቸው የሕገመንግስቱ አንዱ ጠንካራ ጎን ነው የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ምዕራፍ ከተደነገጉት ውስጥ በአንቀጽ 15 ዜጎች በሕይወት የመኖር መብት እንዳላቸው ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን እንደማያጣ ተደንግጓል።
ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒ ይፈጸም የነበረው የጭካኔ የግድያ ተግባር በግልጽ ይታወቃል። ለአብነት የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ መሳሪያ ያልያዙ የሕዝብ ድምጽ ይከበር ብለው ለመጮህ ሰልፍ የወጡ ከሁለት መቶ በላይ ወጣቶች በጨካኝ የስርዓቱ ጠባቂዎች ተገድለዋል።
ይህንንም እራሱ በወቅቱ መንግስት ለማስመሰል አቋቁሞት የነበረው የመርማሪ ኮሚሽን ያረጋገጠው ጉዳይ ነው። እንዲሁም በለውጡ ዋዜማ ከ2008-2010 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የወገናቸው ሰቆቃ ግፍና ግድያ ኢ-ፍትሐዊነት እንዲቀር ድምጻቸውን ያሰሙ ወጣቶች በምህረት የለሽ የትህነግ አልሞ ተኳሾች ግንባራቸውን እየተመቱ ተገድለዋል።
የኢሬቻ በዐል ላይ የነበሩ የኦሮሞ ወጣቶች፣ የጋምቤላ አኙዋክ ብሔረሰብ አባላት ጭፍጨፋ፤ በሕገመንግስቱ የተደነገገውን ክልል የመሆን መብት ለመጠየቅ ባዶ እጃቸውን የወጡ የሲዳማ ብሔር ተወላጆች ላይ የደረሰውን ግድያ እናስታውሳለን።
ትህነግ በየዓመቱ ግንቦት ሃያ በመጣ ቁጥር በሚለቅቀው ፊልም የሚያሳያቸው በንጉሱ ዘመን ለሰልፍ የሚወጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንኳ በፖሊስ ዱላ ተደብድበው ወይም በአስለቃሽ ጭስ ይበተናሉ እንጂ የጥይት እራት አይሆኑም ነበር።
በአንድ ወቅት የቀድሞው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ለምን ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት እንደሚተኮስ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ የአስለቃሽ ጭስ መተኮሻ መሳሪያ ስለሌለን ነው የሚል የፌዝ ምላሽ ነበር።
በሕገመንግስቱ አንቀጽ 16 ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት እንዳለው፣ በአንቀጽ 17 ስለነጻነት መብት ሲደነገግ በአንቀጽ 18 ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ኢ-ሰብዐዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት እንዳለው ተደንግጓል።
ይሁን እንጂ በተግባር ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና አንቂዎች በትህነግ መራሹ መንግስት የደህንነት ክፍል ድብቅ የማሰቃያ ስውር ቤቶች ድብደባ ግርፋት ብዙ ስቃይ ደርሶባቸዋል። አካላቸው ጎድሏል። ዜጎች የተለያዩ ስሞች እየተለጠፈባቸው በድብቅ ታፍነው እየተወሰዱ ለዓመታት ለስሙ እንኳን ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ተረስተው ቆይተዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “የታፋኙ ማስታወሻ” በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቁትን መጽሐፍ ያነበበ ሰው ትህነግ ምን ያህል ዜጎችን በማሰቃየትና በማዋረድ የሚደሰት እንደነበረ መረዳት ይቻላል። አሁንም በተግባር እየፈጸመው ያለ ጉዳይ ነው። በአንድ ወቅት በፌዴሬሽን ምክር ቤት በምሰራበት ወቅት ያጋጠመኝን ላነሳ እፈልጋለሁ። የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ተወካዮች ለአቤቱታ ወደ ምክር ቤቱ መጥተው ነበር።
እኔም ከስራዬ ጋር በተገናኘ ከሌላ የስራ ባልደረባዬ ጋር በቢሮ ተቀብለን በምናነጋግርበት ወቅት እኛ የማናውቃቸው የደህንነት መስሪያ ቤት ሰዎች ቢሮአችን አካባቢ ሲያንዣብቡ ቆይተው ተወካዮቹ ሲወጡ ከመስሪያ ቤታችን የመግቢያ በር ላይ አፍነው ወስደዋቸው እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህም የትህነግ የደህንነት ክፍል በሕገመንግስት ለተቋቋሙ አካላት እንኳ ክብር ያልነበረው አሸባሪ ኃይል እንደነበር ማሳያ ነው።
የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ ግፍ ይፈጸም የነበረው ሕገመንግስትና ሌሎች ሕጎች የፍትሕ ተቋማት ባሉበት ሀገር ነበር። በሕገመንግስቱ አንቀጽ 39፤46 እና 52 ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የእራስን እድል በእራስ የመወሰን፤ በቋንቋቸው የመጠቀም፤ ባህላቸውን የማሳደግ፤ የእራሳቸውን ክልላዊ አስተዳደር የማዋቀር መብት እንዳላቸው ተደንግጓል።
በእርግጥ ብሄር ብሄረሰቦረና ሕዝቦች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ክልላዊ አስተዳደሮች መቋቋማቸው፣ በቋንቋቸው መጠቀማቸውና መዳኘት መቻላቸው፣ ባህላቸውን የሚያሳድጉባቸው ሁኔታዎች መመቻቸታቸው፣ በልማት ረገድ ኢ-ፍትሐዊነት የነበረ ቢሆንም የተወሰኑ ስራዎች መሰራታቸው አይካድም። ይሁን እንጂ ሀገረ-መንግስቱን ከላይ እስከታች በአፈናና የስለላ መዋቅሩ ተቆጣጥሮ የነበረው ትህነግ ስለነበር ክልሎች ለስሙ በአካባቢያቸው ሰዎች የሚመሩ ይምሰል እንጂ ከመጋረጃ ጀርባ የክልል አስተዳደሩን ይቆጣጠሩ የነበሩት በትህነግ የተመደቡ ሞግዚቶች ነበሩ።
እራስን በእራስ በማስተዳደር ስም እንደ እነ አብዲ ኢሌ የመሳሰሉ የስርዓቱ የሽብርና የዘረፋ ሸሪኮች ክልል እንዲመሩ ይደረግ የነበረው በትሕነግ መልካም ፈቃድ ነበር። የሶማሌ ክልል ተወላጆች ላይ ኦብነግ፤ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ኦነግ፤ በአማራው ላይ ግንቦት ሰባት የሚል ታርጋ እየተለጠፈ ይደርስባቸው የነበረው ግድያና ኢ-ሰብዐዊ የማሰቃየት ተግባራት እነዚህ ሁሉ ሲታዩ ትህነግ በሕገመንግስት ተሸፍኖ መንግስት የነበረ ቢሆንም በግብሩ በጭካኔው አሁንም በሕዝብና በሀገር ላይ እያደረሰ ባለው ተነግሮ በማያልቅ ጥፋቱ በታሪክ ከታዩት ፋሺስቶችና ነፍሰ ገዳዮች የማይተናነስ እንደነበርና እንደሆነ መመልከት ይቻላል።
ይህ ቡድን ከስልጣን ከተወገደ በኋላም በዚሁ የጥፋትና የሽብር ተግባሩ ቀጥሎበት በግላጭ ለሀገርና ሕዝብ የሕመምና የስቃይ ምክንያት እየሆነ እወክለዋለሁ የሚለውንም ሕዝብ ትውልድ አልባ እያደረገ ነው። የሚገርመው ይህ የትናንትም ሆነ የዛሬው ዐይን ያወጣ ጭካኔው ግድያው ዘረፋው የለየለት የሕዝብ ጠላትና ሀገር አፍራሽ መሆኑን እያሳየ ሕዝብን ለማታለል ጉዳዬ ከብልጽግና፣ ከአሀዳውያንና ከዐቢይ ጋር ነው፣ የምታገለው ለስርዓት ለውጥ ነው እያለ የቁራ ጩሀት ያሰማል።
ደግነቱ ከጭፍን ተከታዮቹ ውጪ ኢትዮጵያውን በሙሉ የቡድኑን ሰይጣናዊ ተግባር ተረድተው ሊፋለሙት ከዳር እስከ ዳር ተነስተዋል። ትናንት ዛሬ አይደለምና። ትህነግ እንጥፍጣፊ ሰብዐዊነት ያልፈጠረበት የገዛ ሀገሩን ለማፍረስ ሕዝብን ለማዋረድ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ከማድረግ የማይመለስ በእኔ እምነት በዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ማሰብ የተሳነው የሽብር ድርጅት ነው።
ይህን ጽሑፌን የምቋጨው ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ተናገረው በተባለው አባባል ነው። ሶቅራጥስ እንደሚለው ማሰብ ሰውን ከእንስሳት የሚለይ ሳይሆን ሰውን ከሰው የሚለይ ነው። ኢትዮጵያዊያንን መተኪያ ስለሌላት ሀገራቸው ስለትውልዳቸው ያስባሉ ይጨነቃሉ። በየግምባሩ እየተጋደሉም ነው። በአንጻሩ ትህነግ ከኢትዮጵያውያን የሚለየው ማሰብ የተሳናቸው የጨካኞች ስብስብ ስለሆነ ነው። በመጨረሻም ሁሉም ዜጋ የቡድኑን ተፈጥሮና ተግባር በማወቅ በሚችለው ሁሉ ለሀገር ማዳን በአንድነት ሊቆም ይገባል እላለሁ።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች
ወልዱ መርኔ /የሕግ ባለሙያ/
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11/2014