በአገራችን አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎች ልጆች እንዳይወለዱ ከተወለዱም እንዳያድጉ የሚያደርግ የርኩስ መንፈስ ውጊያ እንዳለ ያምናሉ። ይህን የእርኩስ መንፈስ ውጊያ ‹‹ሾተላይ›› ብለው ይጠሩታል።
ማህበረሰባችን ሾተላይ ብሎ ስም ያወጣለትን ሳይንስ ሌላ ምክንያት እና ስያሜ ሰጥቶ ይቀበለዋል። ሳይንስም ይሁን ባህል የየራሳቸውን ምክንያት ይስጡ እንጂ አንዳንድ እናቶች በተደጋጋሚ ልጅ እንደሚጨናግፍባቸው ወይም ወልደው በቀናት ውስጥ እንደሚሞትባቸው ይስተዋላል።
ለጊዜው ‹‹ወፍ እንዳ አገሩ…›› ይባላልና የማህበረሰቡን ጉዳይ በማህበረሰቡ አባባል መግለጽ ስለፈለግኩ ሳይንሳዊ እይታውን አቆይቼ ‹‹ሾተላይ›› የእርኩስ መንፈስ ክፉ ግብር ነው የሚለውን ባህላዊ አስተሳሰብ አንዳንድ እውነታዎች ላንሳ። እንደሃይማኖቶች አስተምሮ እርኩስ መንፈስ ወይም ሰይጣን ሥራው ሁሉ መጥፎ ነው፤ ክፋት፣ ግፍ፣ ጭካኔ፣ ምቀኝነት፣ ተንኮል፣ ቅናት፣ ክህደት፣ መግደል፣ ማበላሸት፣ ማውደም፣ ማመንዘር ብቻ አሉታዊ ግብሩ ተዘርዝሮ አያልቅም። ከሁሉም በላይ ለውድቀቱ ምክንያት የሆነበትም ስፍራውን መርሳቱ ነው።
የማህጸናቸውን ፍሬ እንዳያዩ፣ ወልደው እንዳይስሙ፣ ኩለው እንዳያድሩ፣ አርጅተው በልጆቻቸው እንዳይጦሩ ሾተላይ ገና በጠዋቱ ነገሮቻቸውን ያበላሸባቸው እናቶች በርካቶች ናቸው። እንደግለሰብ በየአካባቢያችን በዚህ ችግር የተጠቁ ቤተሰቦችን ልንጠቅስ እንችላለን። እንደማህበረሰብ ካየነው ግን የትግራይ እናቶችን ያህል ልጆቹን በሾተላይ ሲያስነጥቅ የኖረ አለ ማለት አይቻልም።
ሾተላይ የማህጸንን ፍሬ የሚበላ፤ ዘር ወይም ትውልድ እንዳይቀጥል የሚያደርግ በአይን የማያዩት የጠላት ውጊያ ነው ከተባለይህ ባህሪ ከአሸባሪውሕወሓትጋር በእጅጉየሚመሳሰል ነው። ምናልባት ልዩነት አላቸው ከተባለ ማህበረሰቡ ሾተላይ እያለ የሚጠራው ምናባዊ ወይም የማይታይ መንፈስ መሆኑ፤ አሸባሪው ሕወሓት ግን አይኑን አፍጥቶ ጥርሱን አግጥጦ ትውልድን ሲሰለቅጥ የኖረ አውሬ መሆኑ ነው፤ በአፈጣጠሩ የሰው አካል የለበሰ፤ በሰው ቋንቋ የሚናገር፤ የጥቂት ግለሰቦች ሰብስብ መሆኑ ነው።
በየዘመኑ ጦርነት እየፈጠረ የትግራይ ወጣቶችን ደም መጠጣት ምሱ ያደረገ የበረሃ ውላጅ፤ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ሰርቶ ከማግኘት ይልቅ ዘርፎ መብላትን መርሁ ያደረገ፤ እኩልነት የማይመቸው፤ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን የረሳ፤ ለሰው ህይወት ዋጋ የማይሰጥ፤ ህጻናት፣ ሴቶችና አዛውንትን የሚጨፈጭፍ በሰው ልጆች ላይ ግፍ መሥራት የሚያዝናናው፤ በክፉ ድርጊቱ ሰይጣንን ሳይቀር ማስተማር የሚችል ነው። ለዚህግብሩ ታዲያ የትግራይወጣቶችን ከእናቶቻቸውጉያ እየፈለቀቀ በዚህ ርኩስ ተግባር እንዲሰማሩ ሲያደርግ ኖሯል።
አውሬው ልጆቻቸውን እየቀማ እሳት ውስጥ በመማገድ እናቶችን የወላድ መካን አድርጓቸዋል። የትግራይ እናቶች የተጸናወታቸውን ሾተላይ ከጫንቃቸው ላይ የሚያነሳላቸው አጥተው ዘመናቸውን ሙሉ እህህ እያሉ ኖረዋል። ዛሬም ከዚህ የተለየ ህይወት የላቸውም።
የትግራይ ወጣቶች የቡድኑ ንብረት ከሆኑ ከአራት አስርተ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ለፈለገው ዓላማ የማዋል መብት ያለው እርሱ ነው። በትግራይ ምድር የወላጆች ድርሻ ልጅን መውለድና በችግር ተቆራምዶ ማሳደግ ብቻ ነው። ከዚያ ባለፈ በልጆቻቸው ማዘዝ አይችሉም፤ ጎንበስ ቀና ብለው ያሳደጓቸው ህጻናት ለአቅመ አዳምና ሄዋን ሳይደርሱ አፉን ከፍቶ ለሚጠብቃቸው አውሬው እያስረከቡ ያለ ጧሪ መቀመጥን ተላምደውታል። ልጅ ወልዶ መዳርንና ለቁም ነገር የማብቃት ወግን ረስተዋል።
የማህጸናቸውን ፍሬ ለሰው በላው ቡድን ካስረከቡ በኋላ ‹‹ተጋዳላይ፣ መስዋዕቲ›› ከሚለው ስም በስተቀር የሚተርፋቸው ነገር የለም። የትግራይ እናቶች ስቃይ በዚህም አያበቃ፤ አውሬው በሚያከብረው በዓል ላይ እየተገኙ በሾተላዩ የተነጠቃቸውን ልጆች ፎቶ ግራፍ ይዘው አደባባይ እንዲወጡ ይገዳደሉ። ከዚያም ‹‹እንበር›› ተጋዳላይን እያስጨፈሯቸው ሌሎችን ለመቀስቀስ ይጠቀሙባቸዋል።
የያኔው ትህነግ የአሁኑ አሸባሪ ቡድን ከደርግ መንግሥት ጋር ባደረገው የትጥቅ ትግል የትግራይ እናቶች ከስልሳ ሺ በላይ ልጆቻቸውን በትህነግ ምክንያት አጥተዋል። ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በራሱ በድርጅቱ ርምጃ የተወሰደባቸው እንደሆኑ በወቅቱ ታጋይ ከነበሩና ኋላም የቡድኑን እኩይ ሴራ ተረድተው ካፈነገጡ ሰዎች አንደበት ሰምተናል። ቡድኑ በአሜሪካ ሴራ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ በከፍተኛ ስርቆትና ምዘበራ ላይ ተሰማርቶ የሀገር ሀብት እያራቆተ በውጭ ሀገርና በአዲስ አበባ ህንጻዎችን ሲገነባ የተጠቀመባቸውን የጦር ጉዳተኞች ዞር ብሎ አለመመልከቱ ምን ያህል ከሃዲ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
ክራንችና ዊልቸር እንኳን ሊያቀርብላቸው አልፈለገም። እንደውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነበር ከለጋሾች ጋር በመነጋገር በትግራይ ክልል ለሚገኙ በርካታ የጦር ጉዳተኞች የዊልቸር ድጋፍ የተደረገላቸው። አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በለውጥ አመራሩና በወጣቱ ብርቱ ትግል ከስልጣን ከተሰናበተ በኋላ እኔ ያልመራዋት አገር እንደአገር መቀጠል የለባትም በሚል የትግራይ ህዝብን ምሽግ አድርጎ እጁን በማስረዘም ድፍን ኢትዮጵያን ሲያምስ መክረሙ ይታወሳል።
በስልጣን ዘመኑ ዞር ብሎ ባላየው የትግራይ ህዝብ መሐል ተወሽቆ ተወረሃል፤ ተከበሃል በሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ህጻናትን ለጦርነት እየመለመለ አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ እያደረጋቸው ነው። አሁንም የትግራይ ወጣቶችን እሳት ውስጥ እየማገዳቸው እናቶችንም ማቅ እያስለበሳቸው ይገኛል።
እልቂቱ ከዚህም በፊት ከታየው የሚከፋ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ህጻናቱ የስነልቦና ጥንካሬ እንዲያገኙ ጥይት የማያስመታ ድግምት ነው በሚል አንገታቸው ላይ ዘባተሎ እያሰረ፣ ሀሽሽ እያስጨሰና ቀልባቸውን እያሳተ በአሁኖቹ የትግራይ ትውልዶችም ላይ እልቂት እያደረሰ ይገኛል። ዘመኑን ያልዋጀ፤ ያረጀና ያፈጀ የጦርነት ስልት የሚጠቀመው አሸባሪው ቡድን በአንድ ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ጦር ግንባር በመንዳት በጅምላ ማስጨፍጨፉ ሲታይ ለጥቅሙ እንጂ ለትግራይ ህዝብ ዴንታ እንደሌለው ተጨባጭ ማሳያ ነው። አውሬው የኢትዮጵያ ህዝብ አንቅሮ ሲተፋው የትግራይ ህዝብን መደበቂያው ለማድረግ ተገዷል። መደበቁ ባልከፋ፤ ድምጹን አጥፍቶ እንዲቀመጥ የተሰጠውን እድል ትቶ ጭራሽ የትግራይ ታዳጊዎችን እየሰበከ፣ እያባበለ፣ ብዙኋኑንም እያስገደደ ወደ ለየለት የሽብር ሥራ ገብቷል።
አሸባሪ ቡድኑ የሚዋጋው የኢትዮጵያ ህዝብን ለማሸነፍ እንዳልሆነ ጠንቅቆ ያውቀዋል። ምናልባት ከዚህ ጦርነት የሚያተርፈው ነገር ቢኖር በርካታ ወጣቶችን በማስፈጀት የትግራይ እናቶች በሀዘን እንዲጎዱ ማድረግ ነው። ከዚያ ባለፈም የሰይጣን መንፈስ የተጸናወተው በመሆኑ በአማራና አፋር ክልሎች እንዳደረገው ንጹኃንን በመጨፍጨፍ፣ ተቋማትን በማውደም የሚያገኘው እርካታ ሊኖር ይችላል። ከዚያ ውጭ ግን እንዳሰበው ኢትዮጵያን አያፈርሳትም። ቡድኑ የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ብሎ ካመነ የትግራይ ህዝብ እልቂት ምኑም አለመሆኑን የቀደመ ልምዱ ይናገራል።
በግልጽ የሚታወቁትን ብናስታውስ እንኳ በ1977 ዓ.ም የትግራይ ህዝብ በረሃብ አለንጋ ሲገረፍ ህጻናት በእናቶቻቸው ጡት ላይ ተጣብቀው ሲቀሩ፤ ከዓለም የምግብ ድርጅት እርዳታ ተቀብሎ ለመሳሪያ መግዣ ያዋለውን፤የሀውዜን ከተማ ነዋሪዎችን በአውሮፕላን ያስደበደበውን ማስታወስ ይበቃል። የትግራይ እናቶች አሁንም የእርዳታ ስንዴ ለማግኘት ሲሉ ልጆቻቸውን የዚህ ሾተላይ ሰለባ እያደረጉ ነው።
ልጆቻችሁን ለውትድርና ካልሰጣችሁ የእርዳታ ስንዴ አይሰጣችሁም የሚል አስገዳጅ ህግ አውጥቶ በርካታ የትግራይ እናቶች በረሃብ ላለመሞት ሲሉ ልጆቻቸውን ለሞት እየገበሩ ነው። ቡድኑ የሰው ማዕበል አሰልፎ በውጊያ የበላይነት ለማግኘት ድፍን የትግራይ ህዝብን አንዴ ወደ ጦር ግንባር ቢያስገባ ደስታው ወደር አይኖረውም።
የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ልጆች ውጭ ሀገር ተንደላቀው የሚኖሩ እንጂ በጦር ግንባር ተሰልፈው የሚሞቱ ባለመሆኑ የትግራይ እናቶች ቁስል አይሰማውም። አውሬው ተቃውሞ የሚያነሱትን የትግራይ ተወላጆች በሞት የሚቀጣ ነፍሰ በላ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ጸጥ ረጭ ብሎ ይገዛለታል። አሁን ግን የእናቶች ጩኸት እየበረታ መጥቷል። ልጆቻችን የትገቡ ማለት ጀምረዋል።
ይህ የትግራይ እናቶች በጣር የተሞላ ጥያቄ የቡድኑን እድሜ ከማሳጠር ባለፈ የልጆቻችውን ወግና ማእረግ እንዲያዩ አዲስ የታሪክ ምእራፍ መክፈት የሚያስችል በመሆኑ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጥያቄያቸውን ሊያሰሙ ይገባል። መላው ህዝባችንም ለትግራይ እናቶች የሞራል አቅም መሆን ይጠበቅበታል።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11/2014