ከቀድሞ የአየር ኃይል አባላት አንዱ ናቸው። የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም ያደጉትም ሆነ የተማሩት በአዳማ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ቁጥር ሶስት በተባለ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አፄ ገላውዲዮስ ተምረዋል። ሀገራቸውን በውትድርና የማገልገል ፍላጎት ስለነበራቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በ1970ዎቹ አጋማሽ ተቀላቀሉ።
ለሦስት ዓመታት ያህል በበረራ ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ከሰለጠኑ በኋላ በቀጥታ አየር ኃይሉን ተቀላቅለው በመላ አገሪቱ እየተዘዋወሩ አገለገሉ። በ1981 ዓ.ም በሀገሪቱ ተካሂዶ በነበረው መፈንቅለ መንግሥት ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ጀነራሎች በወታደራዊ መንግሥቱ መገደላቸውን ተከትሎ አብዛኛው አባል ኩርፊያና ማጉረምረም ውስጥ ገባ። ጥቂት የማይባለውም የሚያበረውን አውሮፕላን ይዞ እስከመጥፋት ድረስ በመንግሥት ላይ ያለውን ተቋውሞ አሰማ። የዛሬው የዘመን እንግዳችንም መንግሥትን ተቃውሞው አውሮፕላን ይዘው የመን ከገቡት አባላት መካከል አንዱ ናቸው። ለሁለት ዓመታት በየመን በስደት ከቆዩ በኋላም የአሜሪካ መንግሥትን ጥገኝነት ጠይቀው አሜሪካ ገብተዋል።
ከ30 ዓመታት በላይ ኑሯቸውን በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ በግል ሥራ ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እኚሁ ሰው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ሀገራቸው መጥተውም ነበር። ሆኖም በሀገሪቱ የነበረው አፋኝ ስርዓት አላምር ይላቸዋል፤ የነበረው የዲሞክራሲ ብልጭታም ጭራሹን እየጠፋ መሆኑን በመገንዘባቸው ተመልሰው ወደ መጡበት አገር ሄደዋል። በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረው ግፍና በደል እየበረተ በመምጣቱ ምክንያት የትህነግን መንግሥት ለ20 ዓመታት ሲታገሉ ቆይተዋል። የለውጡን መምጣት ተከትሎ የሚወዷት አገርን ዳግም ለማየት ችለዋል። በተለይም የለውጡ መንግሥት እየፈጠረ ባለው ምቹ ምህዳር በመደሰታቸው ይህ ስርዓት ከዚህ በላይ ያብብ ዘንድ ለማገዝ በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አራት ጊዜ እየተመላለሱ አጋርነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት በአምባገነኑ የትህነግ መንግሥት አላግባብ መበተንና መጎሳቀል ጉዳይ የሚያንገበግባቸው እኚሁ እንግዳችን በአሜሪካ ቆይታቸው ታዲያ ሥርዓቱን እያማረሩ ብቻ ዝም ብለው አልተቀመጡም። ከዛሬ 29 ዓመታት በፊት የቀድሞ አየር ኃይል ማህበርን በማቋቋም በስደትና በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ያሉ አባላት የሚደገፉበት ሁኔታ ፈጠሩ። የነበረውን ስርዓት ተቃውመው ከአገር የተሰደዱ አባላትን በመቀበልና ህጋዊ የሆነ የጥገኝነት ሰነድና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድም የዛሬው የዘመን እንግዳችን ሚና የላቀ እንደነበር ይወሳል።
‹‹በህብረት ችግሮችን መፍታት ይቻላል›› የሚል ፅኑ የህይወት መርህ ያላቸው እኚሁ ሰው የናዝሬት ልጆች ማህበር የሚባል አንጋፋ ማህበርንም በማቋቋም ይታወቃሉ። ከታማኝ በየነ እና ነዓምን ዘለቀ ጋር በመሆንም ‹‹የጀግኖች ምሽት›› የተባለ አስተባባሪ ኮሚቴም በመመስረት ለሀገራቸው ታላላቅ ሥራዎችን የሰሩ የአገር ባለውለታዎችን እውቅና እና ሽልማት የሚሰጥ መርሐ ግብር በተከታታይ ለአራት ጊዜ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በቅርቡ ደግሞ የማህበሩን አባላት በማስተባበር አሸባሪውን ለማስወገድ በሚደረገው ዘመቻ አጋርነታቸውን በተግባር ለማስመስከር ሲሉ ወደ ሀገራቸው ገብተዋል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በዚህና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከቀድሞው አየር ኃይል ማህበር መስራችና ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ሞላ ጋር ውይይት አድርጓል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው አየር ኃይል አባላት ማህበር ከተመሰረተ ወዲህ የሰራቸውን ሥራዎች በጥቂቱ ያንሱልንና ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ ብርሃኑ፡– ይህ ማህበር ከሰራቸው ዋና ዋና ሥራዎች ጎልቶ የሚጠቀሰው የተሰደዱ አባላትን ህይወት የመታደጉ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ግፈኛው የወያኔ ስርዓት ሲገባ አየር ኃይሉ እንዳለ ሲበተን በአብዛኛው ወደ ጅቡቲ ነው የተሰደደው። ወደተለያዩ የአፍሪካ አገሮችም የሄዱ አሉ። ግን ደግሞ በአብዛኛው የሄደው ጅቡቲ ስለነበር የእኛ ማህበር ቀድሞ ተቋቁሞ ስለነበር ሜዳ ላይ የተበተኑ አባላትን ህይወት ለመታደግ ብዙ አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥረናል። ብዙ ለሀገር የሰሩ የእኛ ጓደኞች ጅቡቲ በርሃ ላይ ሜዳ ላይ ነበር የሚተኙት። ያንን ችግር በሚመለከት እነሱን የመታደጉ ሁኔታ ቅድሚያ ሰጥተን ነው የመጀመሪያ እርምጃ የወሰድነው። እ.ኤ.አ በ1995 ዓ.ም ካቶሊክ ሪሊፍ ሶሳይቲ ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር አንድ ኮንቴነር ሙሉ ለስደተኛ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን እስከ መቶ ሺ ዶላር በማውጣት ድጋፍ አድርገናል። ከዚያ በተጨማሪም በዓል በደረሰ ቁጥር ልብሶችን እየሰበሰብን ወደአሉበት አገር እንልክ ነበር።
በዚህ ማህበር አማካኝነት የጀግኖች ምሽት ወይም ክብረ በዓል ኮሚቴ አቋቁመናል። ይህም ማለት ከአየር ኃይል ባሻገር ከምድር ጦር ፤ ከባህር ኃይል፤ እንዲሁም እንደታማኝ በየነ እና ነዓምን ዘለቀ ያሉ አገር ወዳድ ዜጎችን በማስተባበር በርካታ ጀግኖችን ሸልመናል። ወያኔ እነዚያን ጀግኖች አዋርዶ ሲጥላቸው እኛ ደግሞ አንስተን ጀግንነታቸውን እናከበር ነበር። በዚያ ሂደት ውስጥ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የእውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብሩ የተካሄደ ሲሆን በመጀመሪያ ዓመት ጀነራል ለገሰ ተፈራን ሸልመናል። እሳቸው በተለይም በ1965 ዓ.ም ከሱማሌ ጋር በተካሄደው ጦርነት ትልቁን ሥራ የሰሩ እና የሱማሌን አምስት ጀቶች አየር በአየር ውጊያ የጣሉ ጀግና ናቸው። ሱማሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘልቃ እንዳትገባ ብዙ ታድገዋል። እኚህ ሰው ታዲያ መንግሥት ሲቀየር እንደማንኛውም አልባሌ እቃ ተጥለው ነበር። በመሆኑም እኚህን ጀግና መሸለማችን ለእሳቸውም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ የሞራል ብርታት ሰጥቷል ብዬ ነው የማምነው።
በመቀጠልም ጀነራል ካሳዬ ጨመዳን፤ ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያምን ፤ ሚሊሻ አሊ በርጌን እንዲሁም በህይወት ከሌሉት ውስጥ ደግሞ የአየር ኃይሉን ጀነራል ፋንታ በላይን፤ ጀነራል አመሃ ደስታን ልጆቻቸውን ጠርተን ሸልመናል፤ አበረታተናል። እ.ኤ.አ 2010 ዓ.ም በተካሄደው መርሐ ግብር ደግሞ ጀነራል ጃካማ ኬሎን አሳክመን ሸልመናቸዋል። እንዲሁም የኮሪያውን ጀግና ሻምበል ማሞ ሃብተወልድ በተመሳሳይ መልኩ እውቅና እንዲሰጣቸው ተደርጓል። ከአራት ዓመት በፊት ባካሄድነው የሽልማት መርሐ-ግብር ላይ ደግሞ ጀነራል መርዳሳ ሌሊሳ ፤ ጀነራል አሸናፊ ገብረፃድቅ ፤ ከዚያ ደግሞ ኮሎኔል ካሳ ገብረ ማርያም ናቅፋ ላይ ጀብዱ ሰርተው ቢሞቱም ልጃቸውን አሜሪካ ድረስ አምጥተን ሸልመናል። በምፅዋው ጦርነት የተሰውትን ሁሉ በዚያ መርሐግብር ላይ እንዲሸለሙ አድርገናል። ይህም በቤተሰቦቻቸው ላይ ብዙ መነቃቃትን ፈጥሯል። በአጠቃላይ ይሄ ማህበር ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ወገኖቹን ለመታደግ ብዙ ሥራ ሰርቷል።
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው ሰራዊት ያለአግባብ በሕወሓት መበተን በሀገር ላይ ምን አይነት ጉዳት አድርሷል ብለው ያምናሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- በአጠቃላይ በቀድሞ ጦር ላይ የተፈፀመውን ግፍ መቼም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀዋል ብዬ እገምታለሁ። የአገር መከላከያን ሙሉ ለሙሉ ማፍረስና ደማቸውን ያፈሰሱ እና አጥንታቸውን የገበሩ አባላትን ያለጡረታ ሜዳ ላይ መበተኑ በእውነት የግፍ ግፍ ነው። ይህ ሰራዊት ቤተሰብ አለው፤ ልጆች አሉት፤ ግን ያለአግባብ ሲበትኑት ማዕረጉን መንገድ ላይ አንጥፎ ይለምን ነበር። ይህም በእያንዳንዳችን ላይ ትልቅ ቁጭት ፈጥሯል። ምክንያቱም የሰለጠነ ኃይል ነው የበተኑት። በተለይም የአየር ኃይሉ ሲሰለጥን ብዙ ገንዘብ የወጣበት ባለሙያ የሆኑ ሰዎች ስብስብ ነበር ሜዳ ላይ እንዲወድቅ የተደረገው። የአንድ አገር አየር ኃይል እንደአዲስ መጀመር ከባድ ነው። ግን ደግሞ እንደእርሾ ሆነው ያገለገሉት እነሱ ናቸው። ወያኔ ከጫካ ሲመጣ አይደለም ስለአየር ኃይል ይቅርና ስለወታደራዊ ሳይንስ የሚያውቀው ነገር የለም። እናም ያንን የሰለጠ ኃይል ከበተኑ በኋላ ነው አንዳንዶችን መርጠው እንደእርሾ አድርገው እንደገና የተጠቀሙባቸው።
ወያኔዎቹ አየር ኃይሉን የበተኑት በቂም በቀል ነው። ምክንያቱም አየር ኃይሉ ብዙ አጥቅቷቸዋል። ብዙ ግንባሮች ላይ አየር ኃይሉ ነው የደመሰሳቸው። የምድር ጦሩ ሚና ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም አየር ኃይሉ በማያስቡት ሁኔታ እየደመሰሰ ቡዙዎቹን አጥፍቷቸዋል። በዚያ ቂም መሰረት ነው የተበቀሉት እና ተቋሙን ሙሉ ለሙሉ ያፈረሱት። ንብረቶቹንም ብዙዎቹን አግዘዋል፤ ዘርፈዋል። አሁንም ይበልጥ አዳክመውት ነው የሄዱት። እናም ያ ቁጭት ፈጥሮብን ነው እኛም በማህበር ተደራጅተን ይህንን ስርዓት መታገል አለብን ብለን የተነሳነው። እነኚህ የተገፉትን ወገኖቻችንን ደግሞ በምንችለው አቅም መደገፍ አለብን ብለን ነው ስንቀሳቀስ የነበረው። ትልቁ ነገር እነኚህ ሰዎች ለአገርም ሆነ ለማንም የማይጠቅሙ መሆናቸውን መገንዘባችን ነው። እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን ሊያስተዳደሩ ሳይሆን ሊዘርፉ ነው የመጡት።
ሲጀመርም እድል ገጥሟቸው እንጂ ትግራይን የመገንጠል እቅድ ይዘው ነበር ሲታገሉ የነበሩት። ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ጦር በእነሱ ተሸንፎ አይደለም እነሱ አገሪቱን የተቆጣጠሩት። ግን በነበረው የአስተዳደር ችግር ምክንያት የጦሩ ሞራል ያዘነበለበት ወቅት ነበር። ያም ቢሆን ግን አገር ወዳድ የሆነ መንግሥት ነው የነበረን። ግን እንዳልኩሽ አስተዳደራዊ ችግሮች ስለነበሩ ጦሩ አካባቢ የነበረው መንፈስ የተዳከመበት ወቅት ስለነበር ነው። በዚያ ምክንያት ፊት ለፊት ከመዋጋት ይልቅ እጁን የሚሰጥ ወታደር ነበር። በወሬ የሚፈታበት ሁኔታም ነበር።
ያቺን አጋጣሚ ተጠቅመው ነው ከመቀሌ አልፈው አዲስ አበባ የገቡት እንጂ የኢትዮጵያን ሰራዊት አሸንፈው አይደለም። እነሱ ከስማቸው ጀምሮ ነፃ አውጪዎች እንጂ ኢትዮጵያዊ ስሜት ያላቸው አልነበሩም። በአጠቃላይ ሳይፈልጉ ነው 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት። ምክንያቱም የሚያስተዳደሩትን አገር ‹‹ኢትዮጵያ›› ብለው ለመጥራት የማይደፍሩ ሰዎች ነበሩ።
አዲስ ዘመን፡- አየር ኃይሉንም ሆነ በአጠቃላይ የመከላከያ ሰራዊቱ በአንድ ብሔር የበላይነት የነገሰበት እንዲሆን ማድረጋቸው ህዝቡ በሰራዊቱ ላይ እምነት እንዲያጣና የኔነት ስሜት እንዳይኖረው አድርጎታል ብለው የሚያነሱ ሰዎች አሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- አዎ፤ እንግዲህ አየር ኃይሉን እንኳን ብናይ፤ እነሱ ያዋቀሩት ኃይል በአንድ ብሔር የተደራጀ ነው። መጨረሻ አካባቢ ለይስሙላ በእነሱ አስተሳሰብ የተሞሉ አንዳንድ ሰዎች አስገብተው ነው ህብረ-ብሔራዊ ለማድረግ ሙከራ ያደረጉት። በአብዛኛው ከአስተዳደሩም ጀምሮ እስከ ተራ ባለሙያ ድረስ የአንድ ብሔር የበላይነት የነገሰበት ነበር። ያ በዘረኝነት የተዋቀረ አየር ኃይል ደግሞ አገራችን ላይ ትልቅ ጉዳት ፈጥሯል ባይ ነኝ። ጉዳትም አድርሷል። በአጋጣሚ እንኳን ከትምህርት ቤት የገቡ ወጣት ባለሙያዎች ቢኖሩ ይደረግላቸው በነበረው የዘር መድሎ ብዙ ስቃያቸውን አይተው መጨረሻ ላይ ጥለው ለመጥፋት ተገደዋል።
የሚችለው አውሮፕን ይዞ የኮበለለም አለ። ያ የሚያሳየው በዘር የተዋቀረው አስተዳደር ምን ያህል ጫና እንዳሳደረባቸው ነው። ምክንያቱም በአንድ ዘር ተዋቅሮ የትም ሊደርስ አይችልም። ምክንያቱም ከዚህ በፊት የነበረው አየር ኃይል ህብረ-ብሄራዊ መሆኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲኖር አድርጓል ባይ ነኝ። ይሄ ግን በራሳቸው ምስል ቀርፀው የሰሩት አየር ኃይል ነበር። በዚያ ምክንያት ብዙዎቹ አኩርፈው አገር ለቀው ወጥተዋል። የሚገርምሽ ወያኔ አየር ኃይሉን በመራባቸው ዓመታት ከ50 ያላነሱ ባለሙያዎች አገር ጥለው ወጥተው የእኛ ማህበር ታድጓቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ በዲያስፖራው መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር በመሰራቱ በአገር ገፅታ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ነበረው ብለው ያምናሉ?
አቶ ብርሃኑ፡– ትክክለኛ ሃሳብ ነው ያነሳሽው፤ እኛ እንዳውም ኤምባሲ እንዳለን ቆጥረን አናውቅም ነበር። እኔ በግሌ በታሪክ ኤምባሲ ገብቼ አላውቅም። አሁን ዶክተር ዐቢይ ሲመጡ ነው ኤምባሲ የገባነው። በዚያም አጋጣሚ እንዳውም የዶክተር ዐቢይ የአሜሪካ አቀባበል ኮሚቴ ውስጥ ነበርኩኝ። በዚያ ምክንያት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ኤምባሲውን ያየሁት። ከዚያ በፊት የሚያስኬደኝ ጉዳይም የለኝም፤ ቢኖረኝም የመሄድ ፍላጎት አልነበረኝም። ምክንያቱም የእኔነት ስሜት የለኝም ነበርና ነው። ኤምባሲው ራሱ በዘር የተደራጀ ነው። የሚሰበሰቡት የአንድ ብሔር አባላት ብቻ ነበሩ። የሚገርምሽ ኤምባሲው ውስጥ የየግላቸውን ፓርቲ ያዘጋጁበት ነበር። ዲያስፖራው አካባቢ ዘረኝነቱን ለማስፋፋት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። ግን ዲያስፖራው በቀላሉ የሚፈታ ህዝብ አይደለም። ምክንያቱም ተፅዕኖው በቀጥታ አያገኘውም። እነሱ ግን የተለያዩ መደለያዎችን በመስጠት በመካከላችን ልዩነት ለመፍጠር ይሞክሩ ነበር።
አዲስ ዘመን ፡- ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ብርሃኑ፡- ለምሳሌ መሬት በመስጠት ዲያስ ፖራውን ለማታለል ይሞክራሉ። በተለይም በሚሊ ኒየም በዓል ምክንያት በማድረግ ብዙዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ አድርገው መሬት የሰጧቸው አሉ። ይህ ማለት የመጡት ሁሉ ለእነሱ አጎብድደዋል ማለት አይደለም። የተወሰኑትን በጥቅም ማርከዋል። እነዚህ ሰዎች ናቸው እስከመጨረሻው ለእነሱ እየታገሉ ያሉት። ግን ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ የሆነ ሆድ አደሮችን ነው እንጂ ሁሉንም ማለቴ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። አብዛኛው ዲያስፖራ 27 ዓመታት ሲታገላቸውና የተቃውሞ ሰልፍ ሲያዘጋጅ ነው የኖረው። ብርድና ፀሐይ እየተፈራረቀበት የወያኔን ትክክለኛ ማንነት ለዓለም ህብረተሰብ ሲያስ ተዋውቅ ነው የኖረው። በዲያስፖራው የተደረገው ትግል ቀላል አይደለም።
ግን ኤምባሲን በሚመለከት የአንድ ብሔር ስብስቦች ብቻ ሙሉ ለሙሉ የግላቸው መኖሪያ ያህል የፈለጉትን የሚያደርጉበት ነበር። በዓል እንኳን ሲሆን የአውሮፕላን ትኬት በ500 ዶላር እየገዙ ነበር የሚመጡት። ይህ በሌላ መንግሥት ተደርጎ አያውቅም። የወያኔ የምስረታ በዓል ሲከበር ብዙዎች ወደ አገር እንዲገቡ ይገፋፉ ነበር። ሲመጡ ደግሞ መሬት ይሰጣቸው ነበር። ዛሬ የብዙ ፎቅ ባለቤቶች ናቸው እኮ እዛ ሆነው የሚታገሉላቸው። እነሱ ድሮ ከነበረው መንግሥት ጋር አብሯል ያሉትን ሁሉ ሲበቀሉ አሁን ያለው የእኛ መንግሥት ግን መልካም በመሆኑ በየዓለም አደባባዩ የሚንከባለሉት የወያኔ አጫፋሪዎችን ሀብት አልነካም።እነሱ ቢሆኑ እዚህ ያለውን ንብረት ይወርሱ ነበር። በዚህ ዙሪያ ምንም የተደረገ ነገር የለም። ግን ህዝቡ በንቃት ሊያየው የሚገባው ጉዳይ ዛሬ ዓለም እያመሱ ያሉት ኢትዮጵያን በየሚዲያው እያብጠለጠሉ ያሉት በሙሉ እዚህ የንብረት ባለቤቶች መሆናቸውን ነው። የጥቅም ተካፋይ ስለነበሩና በዚያ ወቅት ብዙ ነገር የተደረገላቸው ሰዎች ናቸው አሁንም ኢትዮጵያን እያብጠለጠሉ ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- ዲያስፖራው በያለበት ስለአገሩ እያደረገ ያለው ትግል አፍሪካዊ ይዘት እየያዘ ቢመጣም ምዕራባውያኑ ለኢትዮጵያ ጆሮ ለመስጠት አልወደዱም። የዚህ ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ብርሃኑ፡– እንግዲህ ምዕራባውያኑ ችግሩን ሳያውቁት ቀርተዋል ብዬ አላስብም። በደንብ ያውቁታል። ግን እውነታውን ማየት አይፈልጉም። እነሱ የሚፈልጉት ለእነሱ የሚንበረከክላቸውን መንግሥት ነው። የእኛ መንግሥት ግን ሊንበረከክላቸው አልቻለም። በመሆኑም ለዚህ ነው እነሱ ከእውነታው ባፈነገጠ መልኩ ለወያኔ ድጋፍ እየሰጡ ያሉት። ወያኔ የሚሰራው ነገር ስህተት እንደሆነ አሳምረው ያውቁታል። አሁን ላይ አንዳንዶቹ የሚያውቁት የወያኔን ማንነት ማውጣት ጀምረዋል። አማራና አፋር ክልል የተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በገሃድ እያዩ ነው ያሉት። በፊት ከነበራቸው የከረረ አቋም እየተለሳለሱ የመጡት በወያኔ ላይ የነበራቸው ተስፋ እየተመናመነ በመምጣቱና እንደማያሸንፍ ስለተገነዘቡት ነው። በአጠቃላይ ግን ምዕራባውያኑ ወዲያም አሉ ወዲህ፤ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚከበርበትን ሁኔታ ነው የሚፈልጉት።
በዚህ ረገድ ወያኔ ላይ የነበራቸው ተስፋ እየጨለመ ሲመጣ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀበል እየተገደዱ ነው ያሉት። ግን ትልቁ ችግራቸው ለእነሱ አሻንጉሊት የሆነ መንግሥት ማቋቋም ብቻ ነው። በተለይም አሜሪካኖቹ ይሄ መንግሥት ደግሞ አልበገር ስላላቸው ከወያኔ ጋር በመሆን ምዕራባውያኑን በሙሉ አስተባብረው ተነስተውብን ነበር። በዚያ ምክንያትም ነው እኛ ዛሬ ተሰባስበን አገራችንን ለመርዳት የመጣነው። ኢትዮጵያ ያለችበት ችግር ከፍተኛ ቢሆንም የምዕራባውያኑም የተቀናጀ ዘመቻ ከባድ ቢሆንም ኢትዮጵያ አትበተንም ብለን ነው ከወገኖቻችን ጎን የቆምነው። ለሌሎች አርዓያ በመሆን እና በሙያችን ልናግዝ ወስነን ነው የመጣነው።
እንዳልሽው ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ላይ የተነሱበት መንገድ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ ግን ኢትዮጵያ ሲፈልጉ የሚያቆሟት ሳይፈልጉ የሚያፈርሷት በጭቃ ተጠፍጥፋ የተሰራች አገር አይደለችም። ያ አለመሆኑንም የኢትዮጵያ ህዝብ በጀግንነት አስመስክሯል። አሁን ላይ ዲያስፖራው ላይ የምናየው ትልቅ ቁጭት የወለደው ነው። አሁን ላይ መንግሥት ያቀረበውን ወደ አገር የመግባት ጥሪ ከተጠበቀው በላይ ይመጣል ብዬ ነው የማምነው። ግን ያንን ሁሉ ዲያስፖራ ሊያስተናግድ የሚችል አቅም መኖሩ ላይ ትንሽ ስጋት አለኝ። በአሁኑ ሰዓት እንኳን በረራ ሙሉ ነው፤ ከፍተኛ የሆነ እጥረት አለ።
አንድ ጊዜ የሚደረገው በረራ አሁን ሊመጣ ካለው ዲያስፖራ መጠን ጋር የሚመጣጠን አይመስለኝም። ሀገር ለመጥቀም እስከታሰበ ድረስ ዲያስፖራው በሌላ አገር አውሮፕላን መምጣት የለበትም። አስፈላጊ ሁኔታ ከተሟላለት ወደ አገሩ መምጣትና ቁጭቱን መግለፅ የሚፈልግ ብዙ ነው። አሁንም ቢሆን በየአለበት አገር ሆኖ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሰላማዊ ሰልፍ ነው እያካሄደ ያለው። በአጠቃላይ ብዙ የመታገያ ዘዴዎችን እየተጠቀምን ምዕራባውያኑን ወደ እኛ አቋም ማምጣት እንችላለን። ዲያስፖራው አገርና ወገኑን የሚደግፍበት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካና አጋሮቿ በፖለቲካው ከሚያደርጉት ተፅዕኖ ባሻገር የኢኮኖሚ አሻጥር በመስራት ኢትዮጵያን ለማዳከም እየጣሩ ነው ያሉት። ታዲያ ይህንንስ በምን መልኩ ነው መታገል የሚገባው?
አቶ ብርሃኑ፡- እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ባለሙያም ባልሆንም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ከተፅዕኖ ውጭ የመጣ ወይም ራሳችን ሰርተን ልናገኘው የምንችለው ትንሽ ገንዘብ የበለጠ ጠቀሜታ አለው። ዘላቂነቱም አስተማማኝ ነው ብዬ ነው የምገምተው። ምክንያቱም እነሱ በሰጡ ቁጥር ተፅዕኖው አብሮ ነው የሚመጣው። ለምሳሌ አግዋን ብንመለከት ለተወሰነ ጊዜ ኢንዱስትሪዎችና በውስጡ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ተጠቃሚ ሆነዋል። ግን ተያይዞ የመጣው ተፅዕኖ የበለጠ ነው። ለማንበርከክ ሲሉ እንደመሳሪያ ነው የተጠቀሙበት። በመሆኑም ያለችንን ገንዘብ ትንሽም ብትሆን እሷኑ እያሳደግን አገር በቀል በሆነ ሀብት የሀገራችንን ኢኮኖሚ ብናሳድግ የተሻለ ነው የሚሆነው። ይህንን ማድረጋችን በራሱ ከእጅ አዙር ቀኝ ግዛታቸው እንላቀቃለን።
ሌላው በዲያስፖራው ዙሪያ ብናይ በርካታ ኢትዮጵያዊ በየአገሩ አለ። ያ ዲያስፖራ በቁርጠኝነት አገሩን ለመርዳት ካሰበ የውጭ ምንዛሪ በቀጥታ በባንክ ሊልክ ነው የሚገባው። ይህንን ማድረጉ በራሱ አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በእጅጉ ይፈታዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ደግሞም ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ብንወስድ አብዛኞቹ ያደጉት ዲያስፖራዎቻቸው በሚልከው ገንዘብና ድጋፍ ነው። በመሆኑም በየሀገሩ ያለው ዲያስፖራ በታማኝነት አገሩን ከደገፈ በአጭር ጊዜ ውስጥ እድገት ማስመዝገብ እንችላለን። ስለዚህ ሁሉም ሊያስብ የሚገባው የሚልኳት ትንሽ ገንዘብ እዚህ መጥታ ብዙ ልትሰራ እንደምትችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በአግባቡ አልያ ዘችውም የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ብርሃኑ፡– በእኔ እይታ ከማንኛውም አገር ጋር ያለንን ግንኙነት በአግባቡና በጥበብ መያዝ ይገባል። ደግሞም ከሁሉም ተገልለን መኖር አንችልም። ይህ ሲባል ግን ሊኖረን የሚገባው ግንኙነት ንፁህና ቀጥተኛ መሆን አለበት። በተፅዕኖ ውስጥ የሚደረግ ግንኙነት ነው ለአንድ አገር አደጋ ሊሆን የሚችለው። ከዚያ ውጭ የሆነ ጤናማ የሆነ ግንኙነት መፈጠርና መቀጠል እንዳለበት አምናለሁ። ምክንያቱም ሁሉንም በጠላትነት ልንፈርጀው አይገባም።
ከአሜሪካም ጋር በተቻለ መጠን ጥሩ የሆነ እና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ቢፈጠር ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ።ከዚህ ጎን ለጎንም ራሳችን ችለን መቆም የምንችልበት እድል እያሰፋን መሄድ ይጠበቅብናል። በነገራችን ላይ ‹‹በቃ›› የሚለው ዘመቻ የተጀመረው ሙሉ ለሙሉ ምዕራባውያን አያስፈልጉንም ከሚል ሳይሆን እነሱ የሚሰሩት ተፅዕኖ እና በሀገራት ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡበትን ነገር ማስቀረት አለባቸው ከሚል ነው። እንደገና ደግሞ ከዘመናዊ ቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መላቀቅ አለባቸው። ይሁን እንጂ ሙሉ ለሙሉ ጤናማው ግንኙነት ይቅር ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- እንደአንድ የሰራዊት አባል አሸባሪው ቡድን በዜጎች ላይ የሚፈፅመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ከምን የመነጨ ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- በዓለማችን ላይ በርካታ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ከተካሄዱት ጦርነቶች መካከል የቅኝ ግዛት ጦርነቶች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ። ለምሳሌ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ፋሽስቱ ኃይል በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረገው ግፍ እስከዛሬ ስንቆጭበት የነበረ ነው። ግን ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ወያኔ በንፁሃን ላይ እየፈፀመ ያለው ግፍ የጣሊያንን ሥራ አስንቆታል ወይም ቀንሶታል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ከጣሊያን የባሰ በጣም ብዙ ግፎች በአሸባሪው ቡድን እየተፈፀመ በመሆኑ ነው። ከሰው አልፎ እንስሳትን ያለምንም ጥፋታቸው የሚጨፈጭፍ ነውረኛ ቡድን ነው የተፈጠረው። ለሰው አዕምሮ በሚከብድ መልኩ እነዚህ አውሬዎች በር ዘግተው ንፁሃንን አቃጥለዋል። ጣሊያን ይህንን አላደረገም። ቢያደርገው እንኳን ሊገዛ የመጣ የውጭ ኃይል በመሆኑ ከዚህ በጋራ ሚዛን ላይ ስናስቀምጠው ይሄኛው እየበለጠ ነው ያለው።
ከሁሉ በላይ በራሳችን ወገን ይሄ ሁሉ ድርጊት መፈፀሙ ለመናገርም የሚያሳቅቅ ነው። እኔ የትግራይ ህዝብ ይሄነው ብዬ አልገምትም። ከእነሱ አብራክ የወጡ ናቸው ለማለትም ይከብደኛል። ምክንያቱም በሥራ አጋጣሚ የትግራይን ህዝብ አውቀዋለሁ። እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ነው። ያለችውን ቡና አፍልቶ ቁርስ አድርጎ የሚጋብዝሽ ህዝብ ነው። ከዚያ ህዝብ የወጡ እነዚህ ሰዎች ለወጡበት ማህበረሰብ ጤና አልፈጠሩለትም ፤ኢትዮጵያንም እንዲህ እያመሱ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት እየፈፀሙ ነው ያሉት። ስለሆነም ወያኔ ከጣሊያን ጋር ሳይሆን ምንአልባት ከሂትለር ጋር ሊወዳደሩ ይችላል የሚል እምነት ነው ያለኝ። እኔ በጣም ጭካኔ የሰሩ እንደመሆናቸው ሰው ናቸው ለማለት እንኳን ይከብደኛል። ከዚህ በኋላ የሚፈጠር የልጅ ልጅም ቢሆን ሊታረቅና ይቅር ለማለት የማይችልበት ሁኔታ ነው የፈጠሩት።
አዲስ ዘመን፡- አያይዘው ለዚህ ላልተገባ ጦርነት ልጆቻቸውን ለገበሩ የትግራይ ወላጆች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
አቶ ብርሃኑ፡- አስቀድሜ እንዳልኩሽ የትግራይ ህዝብ በእውነት የሚሰማው ዜና ውስን ስለሆነ በወያኔ መታለሉ ብዙም አይገርምም። ነገር ግን ከትግራይ ውጭ ያለው የትግራይ ክልል ተወላጅ እውነታውን እያየ መንቃት ያልቻለበት ሁኔታ ግን ትክክል ነው ብዬ አላምንም። እነሱን እየበደለና ልጆቻቸውን እያስጨረሰ ያለው ከራሳቸው አብራክ የወጣ አውሬ ነው። በመሆኑም ከዚህ በላይ እንዳይሄድ በቃ ሊሉት ይገባል። ምክንያቱም ከ40 ዓመታት በላይ ነው የትግራይ ህዝብ በወያኔ እየተቀጠቀጠ ያለው። በወያኔ ቁጥር ስፍር የሌለው ወጣት አልቋል። ይህንን ደግሞ የራሳቸው ሰዎች ሳይቀሩ ነው የመሰከሩት። እኔም ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት በቃ ለማለት መሞከር አለባቸው የሚል ነው። ልጆቻችን አይለቁ፤ ኢትዮጵያ አገራችን ናት አትፈርስም ብለው ወያኔን ሊሞግቱ ይገባል። ያ ካልሆነ የመከላከያ ሰራዊት ብቻውን ትግራይን ነፃ ሊያወጣ አይችልም። እነሱም መተባበር መቻል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ጦርነት በተለይ አማራና አፋር ክልል ከፍተኛ የሆነ ውድመት ደርሶባቸዋል። እነዚህ ክልሎች ዳግሞ እንዲያንሰራሩ ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል?
አቶ ብርሃኑ፡- ይሄ በጣም ሰፊ ጉዳይ ነው። መቼም ትልቁ ሥራ ያለው ከጦርነት በኋላ ነው። እነዚህን ክልሎች የማቋቋሙ ሥራ አምስትም ፤ አስርም ከዚያም በላይ ሊፈጅ ይችላል። ምክንያቱም ድሮም ኢኮኖሚያችን ደካማ ነው፤ እንኳን ጦርነት ተጨምሮበት። የደረሰው ውድመት በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ መመለስ ይቻላል ብዬ አልገምትም። እያንዳንዱ ሥራ ጊዜ ይወ ስዳል። ሆኖም ክልሎቹን ዳግሞ የመገንባቱ ሥራ የዲያስፖራውም ሆነ ሀገር ውስጥ ያለው ዜጋ ግዴታ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት አለበት ብዬ ነው የማስበው። ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አማራ ክልልን አጥፍተውታል። ብዙ ፋብሪካዎችንና መኖሪያ ቤቶችን አፍርሰዋል። የግለሰብ ቤት እየገቡ የዘረፉት ነገር ብቻ የሚያመጣው ኪሳራ ቀላል አይደለም። ህዝቡ ተሰዶ ነው ያለው ፤ ተመልሶ ቤቱ ሲገባ ብዙ ነገር ያስፈልገዋል።
እናም ያንን ለማቋቋም የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ መተባበር አለበት ነው የምለው። በተለይም ዲያስፖራው በሚችለው መንገድ ኢትዮጵያን ማቋቋም አለበት። በአንድ ብር ታማኝ ሆኖ መንግሥት በሚያቅዳቸው ነገሮች ሁሉ እገዛ ማድረግ አለበት። እርዳታው የሚቆም አይደለም። ከዚያ ውጭ ለኢትዮጵያ ህልውና መቀጠል ሲሉ በዚህ ጦርነት መስዋዕትነት የከፈሉ የጦር አባላት ልጆችን መደገፍ እና ማቋቋም ያስፈልጋል።
በኛ በኩል የራሳችን ድጋፍ ለማድረግ የጀመርነው እንቅስቃሴ አለ። የሚችል ወስዶ ማሳደግ፤ የማይችል ደግሞ አገር ውስጥ እያሉ መደገፍ የሚቻልበት ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው ያለነው። ምክንያቱም ወላጆቻቸው ዋጋ የከፈሉት ለኢትዮጵያ ነው፤ የእነሱ መሞት ትልቅ ቁጭታችን ሆኖ ሳለ ልጆቻቸው ደግሞ በቁም ሊሞቱ አይገባም። የጀግና ልጆች በመሆናቸው ልንንከባከባቸው ይገባል። መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊሰራ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ እና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ብርሃኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014