በሳምንቱ ማብቂያ በተለያዩ አገራት በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባለድል ሲሆኑ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ለሁለት አስርት ዓመታት በሌሎች አትሌቶች ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን የግሉ ማድረግ ችሎበታል። ዮሚፍ በሳምንቱ መጨረሻ በአሜሪካ ቦስተን በተደረገ የአንድ ማይል የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊ ከመሆኑም በላይ ለሁለት አስርት ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰንም የግሉ ማድረግ ችሏል። አትሌቱ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ሰዓት 3ደቂቃ 47 ሰከንድ 1ማይክሮ ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቧል።
የውድድሩ ክብረ ወሰን እኤአ1997 በሞሮኮው አትሌትሂሻል ኤልግሩዥ 3:48.45 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የ21 ዓመቱ ዮሚፍ ይህን ክብረ ወሰን አንድ ደቂቃ ከአርባ አራት ሰከንድ በማሻሻል አዲስ ታሪክ መፃፍ ችሏል። በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ሶስተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው ዮሚፍ፤ ከዚህ ቀደም በበርሚንግሃም በተካሄደውና ሳሙኤል ተፈራ ቀዳሚ ሆኖ ባጠናቀቀበት ውድድር ላይ ክብረ ወሰን ለማሻሻል ተቃርቦ እንደነበር ይታወሳል።
ከ19 ቀናተ በፊት በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ላይ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ 3 ደቂቃ፣ ከ31 ሰከንድ፣ ከ04 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት የዓለም የፈጣኑ ሰዓት ባለቤት መሆን መቻሉ ይታወሳል። አትሌቱ ይህ ታሪክ መስራት የቻለው እኤአ በ1997 በሞሮኳዊው አትሌት ሂሻል ኤልግሩዥ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በ23 ሰከንድ በማሻሻል ነው።
ከፈረንጆቹ 2019 ወዲህ ኢትዮጵያውያኑ የሂሻል ኤልግሩዥን ክብረ ወሰን ለሁለተኛ ጊዜ መስበራቸውና በተለያዩ አገራት በሚካሄዱ ውድድር በአስደናቂ ብቃት አሸናፊ እየሆኑ መታየታቸው የብዙዎችን አድናቆት እያጎረፈላቸው ይገኛል። ከዚህ ውድድር በተጓዳኝ በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደውና በዓለም ዓቀፉ አትሌቲክስ ማህበር የወርቅ ደረጃ በሚሰጠው የቶኪዮ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ድል ቀንቷቸዋል። በሴቶች መካካል የተካሄደውን ውድድር አትሌት ሩታ አጋ አሻንፋለች። 2:20.40 ደግሞ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የወሰደባት ጊዜ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ በውድድርታሪክም ሶስተኛው ፈጣን ሰዓት መሆኑ ታውቋል።
ባለፉት ሶስት የበርሊን ማራቶን ውድድሮች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዛ መፈፀም የቻለችው ሩቲ አጋ በተለይም ባለፈው ዓመት በጀርመን የበርሊን ማራቶን 2፤18፤34 የሆነ ሰዓት ማስመዝገቧ በርቀቱ ታሪክ ስድስተኛዋ ፈጣን አትሌት እንድትሆን እንዳስቻላት ይታወሳል። አትሌቷ ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየትም፤ የአየር ፀባዩ በተለይ በመሮጫ መንገዷ ላይ የተንጣለለው ውሃ ውድደሩን ከባድ ቢያደርግባትም የኋላ ኋላ ውጤታማ መሆን መቻሏን ተናግራለች። ሩታን ተከትለው ሌላኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሄለን ቶላ ሹሬ ደምሴም ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ተከታትለውን ገብተዋል። ይህም በቶኪዮ ማራቶን ታሪክ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝገቧል። በወንዶች መካከል የተካሄደውን ውድድር አትሌት ብርሐኑ ለገሰ በቀዳሚነት አጠናቋል።
የ24 ዓመቱ አትሌት ውድድሩን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜም፤ 2፡04.48 ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ሰዓትም እኤአ በ 2017 ኬንያዊው አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ በቶኪዮ ማራቶን ካስመዘገበው ሰዓት ቀጥሎ ፈጣኑ ሰዓት ሆኖ ተመዘግቧል። አትሌት ብርሐኑ ባሳለፍነው ዓመት ዱባይ ማራቶን፤ ሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ 48ሰከንድ አሸናፊ መሆኑም ይታወሳል። አትሌቱ ውድድሩን በቀዳሚነት ካጠናቀቀ በኋላ በሰጠው አስተያየትም፤ በውጤቱ በጣም መደሰቱንና በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ማራቶን ይህን ድሉን እንደሚደግም ባለሙሉ ተስፋ መሆኑን ተናግሯል። በቶኪዮ ማራቶን ብርሃኑን በመከተል፤ ኬንያዊያኑ ቤዳን ካሮጊና ዲክሰን ቹምባ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። የገቡበት ሰዓትም እንደ ቅድም ተከተላቸው2:6:48 እንዲሆን 2:08.44 ሆኗል።
በተለይ የአምናውን ጨምሮ የመድረኩ የሁለት ጊዜ ሻምፒዮኖ ቹምባ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁም ብዙዎች ያልጠበቁት ውጤት ሆኖም ታይቷል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ከዓመት ዓመት የበላይ መሆናቸው በማስመስከር ላይ ሲገኙ ካለፉት ስምንት ውድድሮች መካከልም በስድስቱ በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችለዋል። በዘንድሮው የጃፓን ማራቶን ከ37 ሺ በላይ አትሌቶች መሳተፋቸው የታወቀ ሲሆን፤የ2012 የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ጃፓናዊውን ሳይንቲስት ሺኒያ ያማናካን መድረኩን አድምቀውታል።
አዲስ ዘመን የካቲት26/2011
በታምራት ተስፋዬ