አቶ ብርሃኑ አሰፋ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው የኢትዮጵያ አየር ኃይልን የተቀላቀሉት በ1970 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነው። መሰረታዊ የውትድርና ትምህርትና የአውሮፕላን ጥገና ትምህርትን ለሶስት ዓመታት ተከታትለዋል።
ከዛም ወደ ዩክሬን በመሄድ ወታደራዊ ኮሌጅ ውስጥ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የተላኩ ሲሆን፤ ወታደራዊ ጋዜጠኝነትና ወታደራዊ ሳይንስን አጣምረው ለሁለት ዓመታት ተምረዋል። በ1975 ዓ.ም በወታደራዊ ጋዜጠኝነት በጦር ሃይሎች ውስጥ በነበረው የሬድዮ ፕሮግራም ላይ ስራ ጀምረዋል። በዚያም ለስምንት ዓመት ያገለገሉ ሲሆን፤ በውትድርና ማዕረግም እስከ ሻምበል ድረስ ለመዝለቅ ችለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጨምሮ በሌሎች የግልና የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ውስጥም በተለያዩ የስራ ሁኔታዎችና የሃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል። በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ሲሰሩ ባገኙት የውጭ እድል ወደ ህንድ ሀገር ሄደው በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተው ተመልሰዋል። በመጨረሻም በስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ተቋም ውስጥ ለዘጠኝ ዓመት ያህል የስነ ምግባር ትምህርትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። እኛም ከአቶ ብርሃኑ አሰፋ ጋር ኢትዮጵያ በምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገን እንዲህ አቅርበንላችኋል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል ?
አቶ ብርሃኑ፦ ኢትዮጵያ ተረጋግታ በሰላም እንዳትኖር የማይሹ በርካታ ጠላቶች ያሏት እንደመሆኑ ሁሌም በየዘመኑ እየተፈተነች ትገኛለች። አሁን ያለችበት ሁኔታም የዚህ የፈተናው አንዱ አካል ሆኖ ነው። በመሆኑም ምን ጊዜም የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገራችን ተረጋግታ ማየት አይፈልጉም። እንደ ሀገር ቆማ እንደነሱ በልጽጋ በልማት በእድገት ወደ ፊት ሄዳ ማየት በፍጹም አይፈልጉም። በዚህ የተነሳ ምን ጊዜም ኢትዮጵያን የሚፈታተኑ ታሪካዊ ጠላቶች አሉ።አሁንም እየሆነ ያለው ይህ ነው።
ሕወሓትም ቢሆን በወገኑ ላይ ጦር ሰብቆ ለእልቂትና ለውድመት የዳረገን የኢትዮጵያን እድገትና ግስጋሴ ከማይፈልጉት ወገኖች መካከል በመሆኑና ከሌሎች ጠላቶቿ ጋር በማበሩ ነው። ከዚህ ነገር የምንወጣበት ጊዜ መቼ ነው ? ብዬ እጠይቃለሁ እንደ ዜጋም አዝናለሁ። ተስፋ ግን አልቆርጥም።ተስፋ ላለመቁረጤ ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ በድል የማጠናቀቋ ምስጢር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ላይ አድገው የኢኮኖሚ አቅማቸው ፈርጥሞ ያሉ አገሮች እዚህ የደረሱት ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ተመቻችቶላቸው አይደለም። አሁን እኛ ያለንበ ትን አይነት ችግር አልፈው ብዙ ተፈትነው እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ከሌሎች ሀይሎች ጋር እልህ አስጨራሽ ጦርነቶችን ተጋፍጠው አልፈው ነው።
እኛም ይህንን ነገር አልፈን የተሻለ ጊዜ የምናይበት ወቅት እየመጣ እንደሆነ አስባለሁ።ይህ አይነት ነገር ተመልሶ የማይመጣበትና ሁሉም ዜጎች በልማት በእድገት ውስጥ አልፈው ዜጎቿም የተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ የሚል ተስፋ አለኝ። በአሁኑ ወቅት የመጣው ለውጥና አመራር ኢትዮጵያን ከችግሮቿ አላቆ ወደ ከፍታ ማማ ለማድረስ ጠንክሮ የሚሰራ ነው። ህዝብም እስከ ዛሬ ድረስ ያሳለፈው ነገር የታከተውና ወደ ተሻለ ነገር ለመሄድ ፍላጎትና ስሜት ያደረገበት ምዕራፍ ላይ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው ሕወሓት እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ መውደም አለባት ብሎ መነሳቱ እርስዎ እንደ ወታደርም እንደ ጋዜጠኛም ምን ይፈጥርቦታል?
አቶ ብርሃኑ ፦ አዎ! ይህ ቡድን ያለፉትን 30 ዓመታት ሀገርን እንዲሁም ክልሌ የሚለውን የትግራይን አካባቢ ሲመራ ነበር። ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ውስጥ የራሱንና የደጋፊዎቹን እንዲሁም የምዕራባውያኑን ጉዳይ ከማስፈጸም በቀር እንደ አገርና ህዝብ የሚጠቅም የሚያሻግር ስራ ሰርቷል የሚል እምነት የለኝም።እንደውም ስልጣን ከያዘ በኋላ የነበሩት ጊዜያት ውስጥ በተለይም ጥቂት የትህነግ ሃይሎች በውስጣቸው ደብቀው ይዘውት የቆዩት ሀገርን የማፍረስ አጀንዳ የነበራቸው ይመስለኛል።ነገር ግን በማስመሰል አገርን ሲመሩ እንደነበሩ አስባለሁ። እነዚህ አሸባሪዎች በተለይም ከላይ ያሉትና አገርን እንደፈለጋቸው ሲያደርጉ የነበሩት ሰዎች ውስጥ ያለ ችግርም ለዚህ አብቅቶናል። እንደውም አብረዋቸው በታችኛው እርከን ላይ ያሉ አመራሮች እንዲሁም መላው የትግራይ ህዝብ ይህንን እኩይ ሴራቸውን ያውቀዋልም ብዬ ለማሰብ በጣም እቸገራለሁ።
እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያን ይፈልጓት የነበረው የራሳቸው ስውር ዐላማ ለማስፈጸም ብሎም እየበዘበዙ እንደልባቸው ለመኖር ነበር። ከልባቸው ተጨንቀው ሀገርና ህዝብን መርተው የሆነ ደረጀ ላይ ለማድረስ አስበው አያውቁም።በዚህ ውስጥ ደግሞ በተለይም ጠላቶቻችን የሚመኙልንን ቀና ብለን እንዳንሄድ የማድረግ ስራን ሲያስተገብሩ ኖረዋል። እንደውም እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን እየጠሉ የሚመሩም ነበሩ። በዚህም ለግል ሃሳባቸውና ለምዕራባውያን ቅጥረኝነታቸው ሲሉ አገር የማፍረስ ህዝብን የመከፋፈል ስራ ላይ ተጠምደው እንደነበር ይሰማኛል።
ይህ ደግሞ በእውነት በጣም የሚያሳዝን ነው። በነገራችን ላይ እነዚህ ሰዎች ይህ እኩይ ተግባራቸው እንዳለ ሆኖ ህዝብን ለመሸወድ የልማት የዴሞክራሲ ኃይል፤ የጭቁኖች መብት ተሟጋች መስለው ለመታየት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።በመሆኑም አሁን ላይ ይህንን መሰል ክህደት በመሩት ህዝብ ላይ መፈጸማቸው ያንን ስውር አላማቸውን እውን ለማድረግ መሆኑ በግልጽ አሳይቶናል።
በመሆኑም ይህ ሁኔታ አሁን ላይ እንዳሉት ወይም እንዳሰቡት ሁሉ አገርን አውድመው ብዙ ደም አፍስሰው ጸረ ልማትና ጸረ ዴሞክራሲ እንዲሁም ምንም ዓይነት ሰውኛ አስተሳሰብ የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል። ወገናቸው ላይ የሚጨክኑ መሆናቸውን አሳይተዋል።አሁን ዳግም እንመራዋለን ብለው የሚያስቡትን ዜጋ በዚህ ልክ ሲበድሉ መሰረተ ልማቱን ሲያወድሙ ማየት እጅግ የሚገርም ቢሆንም እነሱን ግን እያደረጉ ያሉት ከድሮም ጀምሮ በልባቸው የያዙትን ያሴሩትን በተግባር እየገለጹ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሳይቀሩ በተሳተፉበት ጦርነት ብዙ አንጸባራቂ ድሎች እየተመዘገቡ ነው። ይህ አሸባሪ ቡድን ከዚህ ምን ሊማር ይገባል ይላሉ?
አቶ ብርሃኑ፦ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ደብቀው ከነበሩበት ወጥተው በሀገርና ህዝብ ላይ ከፍተኛ ውድመትን አስከትለዋል። ነገር ግን በተለይ ህዝቡ አሁን ላይ ከመሪው ጎን ለመቆም ከመወሰኑም በላይ እኩይ ተግባራቸውን ስለተረዳና እነሱም ይህንን እኩይ ተግባራቸውን መፈጸም ካልቻሉ ሀገርና ህዝብ በአንድ መቆም አይችሉም የሚል አቋም በመያዛቸው እንዲሁም ሀገሪቱን በተቻላቸው መጠን እጃቸው አስገብተው የሚፈልጉትን ለማድረግ የወሰኑ በመሆኑ ህዝቡም አንፈልጋችሁም በሚል ውሳኔውን አሳይቷቸዋል።
በነገራችን ላይ የለውጥ አመራሩ ወደ ስልጣን ሲመጣ ለእነሱም የሚገባቸውን ይቅርታ ለማድረግ ወስኖ ነበር። ህዝቡም የመሪውን ቃል ተቀብሎ በንጹህ ህሊና አብረን እንጓዝ ብሎ የይቅርታ እጁን ዘርግቶላቸው ነበር። ነገር ግን ይቅርታውን ከመግፋታቸውም በላይ አብሯቸው በኖረው የሰሜን እዝ ላይ ያንን ያህል ዘግናኝ ድርጊት ፈጸሙ። በዚህን ጊዜ ህዝቡ ማንነታቸውን በደንብ ከመረዳቱም በላይ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነትን ለማስከበር ከዳር እስከ ዳር ተነስቷል።
አሁንም ይህንን ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ አካል በአንድነት ስሜት እየቀጡት ይገኛሉ። እኔ እንደውም በእነዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ በሃብት በሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በሌሎች ሁኔታዎች እንደ ሀገርና ህዝብ ያጣናቸው ነገሮች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። ነገር ግን ከመጥፎ ነገርም መልካም ነገሮች ይወጣሉና አሁን ካጣናቸው ነገሮች በላይ ያገኘናቸው ነገሮች ብዙ ሆነውልናል።
በተለይም እነሱ በዘርና ሃይማኖት የከፋፈሉት ህዝብ ዛሬ ላይ አንድ ሆኖ የመሪውን ቃል እየሰማ እነሱን ድባቅ ለመምታት እየሄደበት ያለው መንገድ ለዘመናት በእነሱ ምክንያት አጥተነው የቆየነው ነው። እናም ህዝቡ አንድ ሆኖ ይህንን አሸባሪ ኃይል ለመጋፈጥ ከመቻሉም በለይ እነሱን አይዟችሁ እያሉ በጎን የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ላይ ታች የሚሉትንም የውጭ ሃይሎች ተቋቁሞ እዚህ ለመድረስ ችሏል።በመሆኑም አሁን ላይ እነሱ ከፋፍለውት የነበረው ህዝብ ክፍፍሉን ወደጎን ለራሳቸው ትቶላቸው አንድ በመሆን ሀገሩን አስቀድሟል። ይህ አይነቱን ወታደራዊ ድል በአጭር ቀናት ውስጥ ለመመዝገብም ምክንያቱ አንድነት ብቻ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ መሰሉ አንጸባራቂ ድል በዚህ አሸባሪ ቡድን ላይ እንዲመዘገብ ካደረጉ ነገሮች መካከል አሁን አሸባሪው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በማለት አንድ ሆነው በመቆማቸው ነው።በውጭ ያሉት ኢትዮጵያውያንም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አንድ ከመሆናቸውም በላይ ከምንም ነገር በላይ አገራቸውን አስቀድመው መነሳታቸው ለድሉ አንጸባራቂነት የበኩሉን ተወጥቷል ብዬ አስባለሁ።
እንደ ነገርኩሽ ይህ አንድነታችን እና እጅ ለእጅ ተያይዘን የመጣብንን ችግር ለመወጣት ያደረግነው ጥረት እውነት ለመናገር አድዋን እንደደገምነው ይቆጠራል።በአጭር ጊዜ ውስጥ አገሩን ሊከላከል ሊያድን የሚችል ኃይል በመፍጠር በኩልም የታየው ውጤት በጣም ትልቅ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዘመቻውን በተቀላቀሉ ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥም የተመዘገበው ድል በጣም አስገራሚና ደስ የሚል ነው።በዚህ ምክንያት ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት ከአሁን በኋላ አጽሙ የሚቀርበት ሁኔታ እንጂ ስጋ ሊለብስ የሚችልበት አግባብ አለመኖሩን በግላጭ ያሳየ ሆኗል።ኢትዮጵያውያንም ያሳዩት አንድነት ተጠናክሮ ቀጥሎ ችግሩን በአጭር ጊዜ ፈተው ወደ ሰላም እና የልማት ስራ መመለስ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ በተለይም ዓለም አቀፍ ሚዲያ ነን የሚሉ መገናኛ ብዙኃኖች የአገራችንን እውነት በመደበቅና የሃሰት ወሬን በመንዛት የሽብር ቡድኑን በመደገፍ ላይ ናቸው። ይህ ዓላማው ምንድን ነው ይላሉ ?
አቶ ብርሃኑ፦ የመገናኛ ብዙኃኑ ህግ ጠበቅ ያለ ነው። እነሱ ባይተገብሩትም አንድ ጋዜጠኛ ተጨባጭ በማስረጃ የተደገፈ ግልጽ የሆነ መረጃን ለአንባቢና አድማጩ ሊያደርስ ይገባል። ይህ ደግሞ በሙያም በመርህም ደረጃ ቁጭ ብሎ የሚገኝ ነው።ነገር ግን አሁን እኛ ላይ በሚዲያዎች አማካይነት እየተፈጠረ ያለው ጫና እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው።ይህ እኩይ ስራቸው ደግሞ የሚያሳየው ምንም አይነት እውነት ቢኖር እነሱ ከጥቅማቸው ጋር ሸብረክ ማለታቸው አንደማይቀር ያየንበ ት ጊዜ ነው። አንዳንድ ጊዜ ተጨባጭነት፣ ግልጽነት እና እውነታ የሚሉት ነገሮች ከንድፈ ሃሳብ በዘለለ ውጤትን የሚያመጡ አይሆንም። ነገር ግን ይህም ቢሆን የትልልቅ ሀገሮች መገናኛ ብዙኃን በጋዜጠኞች ዘንድ በአርአያነት የሚታዩ ተቋማት በዚህን ያህል ደረጃ ወርደው እና ከእውነት ጋር ተጣልተው ማየት በጣም የሚያሳዝን ነው። በተጨማሪም ቀድሞ ምዕራባውያኑ እነዚህን ሚዲያዎቻቸውን እውነትን ለማውጣት ይጠቀሙባቸዋል ብለን የምናስበውን ሁሉ ገደል የከተተ ነው። በመሆኑም ምዕራባውያን የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ከዳር ለማድረስ የዘረጓቸው የተለያዩ ስርዓቶች አሉ። ይህንን በመጠቀም በዓለም ላይ ያላቸውን ተቀባይነት ለማስፋት ይሰራሉ። ከእዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን መሆኑን በትክክል ተረድተናል።
ጦርነት ሲከፈትብን ብቻውን ጦርነት እንዳልሆነ እንደውም የአስተሳሰብ ጦርነት ሁሉ እንደተከፈተብን እንገነዘባለን። በመሆኑም እነዚህ የውጭ ሚዲያዎች የህዝቡን አስተሳሰብ በሚረብሽ መልኩ የማወናበድ፣ ብዙ ችግሮችን የመፍጠር፣ ህዝብ ተጠራጥሮ የሚጠበቅበትን እንዳይወጣ ለማድረግ የሚሰራ ስራ ነው። ይህ መንገድ ደግሞ የፖለቲካውንም ሆነ ወታደራዊ ተጋድሎውን በዚህ መንገድ እንዲቃኝ አስበው እየሰሩ ነው። በመሆኑም እነዚህ የመገናኛ ብዙኃን የሕወሓትን አፍራሽ አላማ ለመደገፍ ከመጣር ባሻገር ውስጡን ደግሞ የራሳቸውን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ የተጠቀሙበት ያፈጠጠ ጉዳይ ነው።
በዚህ ሁለት ሳምንት በተካሄደ ኦፕሬሽን በሕወሓት ቁጥጥር ስር ወድቀው የነበሩ እነደሴና ኮምቦልቻ እንኳን ተለቀው አሜሪካኖቹ በሚዲያቸው እየታገዙ ዜጎቻቸውን ውጡ እያሉ ነው።እነሱ ይህንን ያህል ጥረት ቢያደርጉም በመሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚረዳው ኢትዮጵያዊ የእነሱም ዜጎች ሳይቀር ውትወታቸውን ወደጎን በመተው መደበኛ ስራቸውን እየሰሩ ኑሯቸውን ቀጥለዋል። አሁን ላይ እነዚህ አሜሪካና ምዕራባውያኑ እያደረጉ ባሉት ነገር የማባባስና የማጋጋል ስራ ነው።
ኢትዮጵያውያን ምርጫ መርጠው ይሆነናል የሚሉትን መንግስት ሾመዋል። እነሱ ግን ጥቅማቸው ስለተነካ ብቻ ይህንን ያህል ርቀት ሄደው አሸባሪ ቡድን እስከመደገፍ ደርሰዋል። ይህ የንቀታቸውን ጥግ ያሳዩበት ይመስለኛል። በመሆኑም እነሱ የሚፈልጉት ነገር ካልመጣ አገር እናፈርሳለን ብለው በሚዲያዎቻቸው ይህንን ያህል በእውር ድንብር ቅዥት ውስጥ እየገቡ መሆናቸው በጣም ያሳፍራል።
ዛሬ ላይ ግን ሁሉም ህዝብ ይህንን ነገር ስለተረዳው ተከታይም ስለማያገኙ እየተሸነፉ ነው። አዲስ ዘመን፦ አሜሪካንም ሆኑ ምዕራባውያን አሸባሪውን ሕወሓትን ደግፈው አገር የማፍረስ ስራቸው ላይ ተጠምደው የነበረ ቢሆንም አገር ደግሞ በውድ ልጆቿ ብርታት እዚህ ደርሳለች። የወደፊቷን ኢትዮጵያ ሲያስቧት ምን ትመስላለች? አቶ ብርሃኑ፦ በአሁኑ ወቅት በተለይም በዚህ አጭር ጊዜ ኢትዮጵያውያን እልህ ውስጥ ገብተዋል። የሚደንቀው ነገር በዚህ የተወሰነች ዓመታት እንኳን ሌላውን ትተን ዴያስፖራውን ብቻ ብናይ በተለያየ መንገድ ተለያይቶ ቤተክርስቲያን ሳይቀር በብሔር ወስኖ ይኖር የነበረው ዛሬ ኢትዮጵያን ለማዳን በአንድነት አብሮ መቆሙ ብቻ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ምን ልትመስል እንደምትችል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።ይህ ደግሞ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንደምንሸጋገር የሚያሳይ ነው።
በዚህ ችግር ወቅት በስንቅ በትጥቅ በገንዘብ በሙያ በሃሳብ እየደገፉ ያሉ ኢትዮጵያውያን አሉ። ይህ አንድነት ደግሞ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነው።በነገራችን ላይ ትህነግ ይህንን ሁሉ ዓመት ሲጫወትብን የነበረው በከፋፋይ አስተዳደሩ ነው። ሌላ ምንም አይደለም፤ አሁን ያ ነገር ተዘጋ። ከውጭም ከውስጥም ያለው ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ አንድ ሆነዋል። ያጣነው ብዙ ነገር አለ። ነገር ግን 27 ዓመት ሙሉ የተሰራብንን ክፋት በዚህ አጋጣሚ እንዲሽር የቀደመው አንድነታችን እንዲጠናከር አደረገ።ይህ አንድነት ደግሞ ትህነግን የምናሸንፍበት ትልቁ ቁልፋችን ነው።
አሁን ኢትዮጵያውያን አንድ ነን። እንደቀደመው ጊዜ ከፋፍለው ሊያባሉን አይችሉም። የውጪዎቹም ቢሆኑ ለእነሱ ሊላላክላቸው የሚችል መንግስትን ከዚህ በኋላ መፍጠር የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንዳሉ አውቀዋል።ይህ አንድነታችን እንደውም ከእኛ አልፎ አብዛኛውን ጥቁር እያሳተፈ ነው። ኢትዮጵያውያን ይህ አንድነታችን ሳይደበዝዝ ልናስብ የሚገባን ነገር አለ። አሁን በአሸባሪው ቡድን እኩይ ተግባር ምክንያት በርካታ ሀብት ንብረቶች ወድመዋል። እነዚህን መሰረተ ልማቶችና ፋብሪካዎች እንዲሁም የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ወደነበሩበት መመለስ ብዙ ሀብትን የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም ይህ የአንድነት ኃይል በተባበረ ክንድ በጀመረው የአንድነት መንገድ መስራት መቀጠል ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፦ የመገናኛ ብዙኃንስ እየተሰራጩብን ያሉ የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በማክሸፍና እውነቱን ለመላው ዓለም በማሳወቅ በኩል ስራዎች እየሰሩ ነው። እርስዎ እንዴት አዩት?
አቶ ብርሃኑ፦ ዋናው አስተሳሰብ ነው። አስተሳሰብ በትክክል ካልተገራ የሚፈለገው ውጤት አይመጣም። በመሆኑም አሁን ላይ ጥሩ መንገድ ይዘናል። ነገር ግን መካከል ላይ ኢትዮጵያን አጉልቶ ከማውጣት ይልቅ በክልል የመታጠር አስተሳሰብ ስላለ ይህንን የመቀየር ኃይሉ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን በመሆኑ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው። አሁን ላይ ህዝቡ ተደፈርን ብሎ ሆ ብሎ እንደተነሳው ሁሉ በቀጣይም የወደሙ ንብረቶችን በመተካት የመሰረተ ልማቶችን እንደገና በማዘጋጀት በኩል በፍቃደኝነት ተነስተቶ ተሳታፊ እንዲሆንም መስራት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ነው።
በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚያስፈልጋት በጣም የተሻለ መከላከያ ሰራዊት ነው።ምክንያቱም ብዙ ጊዜ በልምዳችን እንደምናየው ኢትዮጵያ ልማቱንም ሰላሙንም ያረጋገጠች በሚመስላት ጊዜ በሌሎች ጸረ ሰላም ኃይሎች እይታ ውስጥ ትገባና አሁን እንዳለንበት እናደናቀፋለን። ከመደናቀፍ በተጨማሪ ብዙ ዓመት ወደኋላ የሚጎትቱን ችግሮች ይፈጠራሉ። በመሆኑም የእኛን ሰላም ልማትና ብልጽግና የማይመኙ በርካቶች ያሉብን በመሆኑ እስከ ዛሬ ከነበረን የመከላከያ ሰራዊት የተሻለ ሊኖረን ይገባል።በትጥቁም በምግቡም በዝግጁነቱም በቁጥሩም ሁሉ ቀድሞ ከነበርንበት የተሻለና ጠንካራ ኃይል እንደሚያስፈልገን ይሰማኛል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ብርሃኑ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7/2014