በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ፊት አውራሪነት የሚመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠላትን ድባቅ እየመታ በወረራ የያዛቸውን በርካታ ስትራቴጂ ቦታዎች እያስለቀቀ ነው። በወታደራዊ ቋንቋ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው የጋሸናን ግንባር በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
ሌሎችም ግንባሮች ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጣፋጭ ድል እያስመዘገበ መቀጠሉ የማይቀር ሃቅ ሆኗል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያውያን ትንሳኤ ቅርብ እንደሆነ ምንም አልጠራጠርም። እንዲህ ጥሎት እግሬ አውጪኝ ማለቱ ለማይቀር በግዜያዊ ድል ልቡ አብጦ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን መሪ በቅርቡ ሲያወድም ለቆየው ንብረት፤ ሲያጠፋ ለነበረው ሕይወት ካሳ መጠየቁን በሰማሁ ግዜ «ጥይት ራሷ መትታ ራሷ ትጮሃለች» የሚሉትን ብሂል አስታውሶኝ ነበር። ዛሬስ ይሄን እብሪቱንና ረዥም ምላሱን ይዘረጋ ይሆን? ወያኔ ከምስረታው አንስቶ ለህዝብ ክብርም ፍቅርም የሌለው በጥላቻ ስሜት የታወሩ፤ በስሜት የሚነዱ ጥቅመኛ ሰዎች ስብስብ ነው።
ወያኔ ዛሬ እንዲህ ደርጅቶ ሀያ ሰባት ዓመት በሥልጣን ዘመኑ የዘረፈውን ሐብትና መሳሪያ ይዞ ይቅርና ድሮም በዘመነ ችግር የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ ለየትኛውም ማህበረሰብ ቀና አስቦ ቀና ሰርቶ አያውቅም።
በቅርቡ በሠ ራዊቱ ክንድ ተደቁሶ የለቀቀባቸውን የአማራና የአፋር ክልል የአርሶ አደር መኖሪያ ቤቶች ምሽግ አድርጎ ሲዋጋ እንደነበር ማየት የአውሬነቱ ቀላል ማሳያ ነው። ጥቂት ተጨማሪ ማሳያዎች ለማንሳት እንሞክር።
ወያኔ የሚፋለምለት ወታደር ባጣበት በዛ በጨለማ ዘመን በተሳሳተ መረጃ ሀውዜን ላይ ቦንብ አስጥሎ በርካታ ቂም ያዘሉ ወጣቶችን ማፍራት ችሏል። ትምህርት ካለ የሚዋጋልን የለም በሚል እሳቤ በተለያዩ የትግራይ ትምህርት ቤቶች ላይ ፈንጂ በማፈንዳትና መምህራንን በመግደል የትግራይ ወጣቶች ካለፍላጎታቸው የሽምቅ ውጊያው ተካፋይ እንዲሆኑ አድርጓል። ይሄን ግብሩን ደግሞ በአማራና በአፋር ክልሎች በሃይል ወርሮ ይዟቸው በነበሩና አሁንም ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች በድጋሜ ተግብሮታል።
ደርግ አብዛኛውን እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረው በተሽከርካሪ በመሆኑ ለማዳከም በሚል ስትራቴጂ ህዝብ የሚገለገልባቸውን ድልድዮችም ሲያፈርስ ነበር።
ይሕን ተግባሩን የዛሬው ትውልድ ቢዘነጋውም በወቅቱ «ድልድይ አፍራሽ» የሚል ቅጽል ስም እስከማሰጠት ያደረሰው ጉዳይ ነበር። የኢትዮጵያ ሠራዊት በቅርቡ በጀመረው የማጥቃት እንቅስቃሴ ባስለቀቃቸው ጭፍራ፣ ካሳጊታ፣ ጋሸናና ሌሎች ግንባሮችም መሠረተ ልማቶችን ማውደሙ ከመረጋገጡም በላይ ማሕበረሰቡን በማስገደድ የኮንክሪት ምሽግ ማሠራቱንና አውሬነቱን በተግባር ማረጋገጡን አስመስክሯል። ቀደም ያለውን የወያኔን የተረገመ ሥራ ያጋለጡት ደግሞ የራሱ ከፍተኛ አመራሮች የሆኑትና ቢዘገዩም ወደ ሕሊናቸው የተመለሱት እነ አብርሃም ያየህ መሆናቸው ጉዳዩ ምን ያህል የሚያም እንደሆነ የሚያመላክት ይመስለኛል።
ዛሬም ከአርባ ሰባት ዓመት በኋላ ከመቶ በላይ እርዳታ የላኩ መኪናዎች በትግራይ ገብተው የውሃ ሽታ ሆነው የቀሩት የጫኑትን እሕል ለሕዝቡ አድርሰው አልነበረም።
በወረራ በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ የአማራንና የአፋርን ገበሬ መከራ ያበዙ አያሌ ግፎችን ፈፅሟል። አሁንም በተሰነዘረበት ከባድ ምት የተደናገጠው ሃይል ከፊቱ ያገኘውን መልካም ነገር ሁሉ እያወደመ እየፈረጠጠ ይገኛል። ይህንን ስናይ ስለ እውነት የግዜ ጉዳይ እንጂ እንኳንስ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአብራኩ የወጣበት ራሱ የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የሚያወራርደው ሂሳብ መኖሩ እንደማይቀር ግልጽ ነው። ምንም እንኳን ሕዝቡ «ላም እሳት ወለደች፤ እዳትልሰው ፈጃት እንዳተወው ልጇ ነው» ሆኖበት በዝምታ ቢቀመጥም።
የሆነው ሆኖ በገባባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ያደረሰው ውድመትና እልቂት በአግባቡ መመዝገብ ይኖርበታል። ያን ግዜ ማን ሂሳብ እንደሚያወራርድና ማን የትኛው አካል ካሳ እንደሚጠይቅ የምንተዛዘብበት ይሆናል። የጥቅም ፍለጋውን ነገር ወደ ጎን ብንተወው እንኳን አሸባሪው በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የቡድኑን አስከፊ ማንነት ለአደባባይ ያበቃ ነው ።
በመሠረቱ የመከላከያ ሠራዊት ከኢትዮ- ኤርትራ ግጭት በኋላ በትግራይ ተራሮች መሽጎ የአንድ ወጣት እድሜ ያሳለፈው የአገር ሉዓላዊነትን ከመጠበቅ ባሻገር ራሱን የትግራይ ሕዝብንና የቡድኑን ባለሥልጣናትን ከጥፋት ለመታደግ ነበር። ወያኔዎች በውድቅት ሌሊት እንደ ትንሳኤ በግ በገመድ እያነቁና እያረዱ ካለሃጢያታቸው ያጠፏቸው ወጣቶች ቤተሰብ ምን የሚሰማቸው ምንስ የሚሉ ይመስላቸዋል? እንደ ናዚ ዘራቸውን ለይተው አውጥተው በሲኖ ትራክ ጎማ ነፍሳቸውን ብቻ ሳይሆን ስጋቸውንም የነጠቋቸው ወጣቶች ተዝካራቸው ሳይወጣ ካሳ ለመጠየቅ የደፈሩ መሆናቸው ትዝ ባለን ግዜ የአውሬነታቸው ጥግ በሰው አእምሮ ሊመዘን የማይችል መሆኑን እንረዳለን። አሁን ሁሉም እየተቀየረ ነው።
እንኳን ካሳ ለመጠየቅ ለራሳቸውም ሕይወት ደሕንነት ምንም ማስተማመኛ የላቸውም። ሠራዊቱ የወንድሞቹን ደም በድል እየገሰገሰ ከመመለሱም በላይ የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ህይወቱን መስዋዕት ለማድረግ ተማምሏል። የዚህን ውጤት ደግሞ በዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ እያየነው ነው። ከምንም በላይ ግን በስሌት የውድመትና የግፍ ቆጠራ ከተጀመረ በባዶ ስድስት ያለቁትን ትግራዋይ ጨምሮ በትግራይ ህዝብ ላይ ራሱ አሸባሪው ሕወሓት የፈጸመው እንኳን ከፍሎ አውርቶ የማይጨርሰው በርካታ የሚወራረድ ሂሳብ አለበት።
ያለፉትን አርባ ዓመታት የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ለተከታተለ (እድሜው ያልደረሰ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ ያነበበና ያዳመጠ አንድ እውነት ይረዳል) ወያኔ በተለያዩ የዳቦ ስሞች ማለትም ተሓህት (ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ) ማሌሊት (ማርክሲስት ሌኒስት ሊግ ትግራይ) ህወሓት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በማለት እንደ እባብ ስሙን እየቀያየረ የሽብር ሥራ ሲከውን የነበረ መሆኑን ነው።
በእነዚህ አካባቢዎች የተጫሩት እሳቶች በሙሉ የእነዚህ የቀትር ጋኔሎች እጅ ያለባቸው ናቸው። ቡድኑ የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ሕዝብ ያሳጣው የዛሬን አያርገውና ልጆቹንና ንብረቱን ብቻ ሳይሆን የእርስ በእርስ ፍቅሩንም ነበር። አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሯል። ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ ሰተት ብሎ ወጥመድ ውስጥ የገባው ሽብርተኛ ቡድኑ በመከላከያ፣ የአማራ ፋኖ፣ ሚኒሻ፣ የአፋር ልዩ ሃይልና በሕዝቡ ደጀንነት እየተደቆሰ ይገኛል።
የአማራና የአፋር ተራራዎች ሂሳብ የሚያወራርድበት ሳይሆን የሚዋረድበትና በማሰው ምሽግ የሚቀበርበት ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሰሙትን የክተት ጥሪ ተከትሎ በየሸጡና በየጉድባው እብሪተኛው ትሕነግ ምሱን አግኝቶ፣ የተማረከው ተማርኮ፣ ቀሪው ተደምስሶ እየተሸኘ ነው። የቀሩት መሪዎችም ሕልማቸው እንደ ጉም እንደበነነ ተረድተው የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተዋል።
ከአሁን በኋላ ይህን ሃይል ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የተጀመረውን እልህ አስጨራሽ ትግል አፋፍሞ ከማስቀጠል ባሻገር በፕሮፖጋንዳውም፣ በተንኮሉም፣ በዛቻውም ሆነ በማስፈራራቱም የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ መንግሥት አንድ እርምጃ እየቀደመ መጫወት ያለበት ይመስለኛል።
በተለይ በጦር ሜዳው ውሎ አላማ መደረግ ያለበት ቦታ ማስለቀቅ አልያም ምርኮኛ መያዝ ሳይሆን መደምሰስ ብቻ ሊሆን ይገባል። ለዚህም ሐይል የሚሰበስቡበትን የእንደራደር ማዘናጊያ የአሜሪካና አንድ አንድ የአውሮፓ ሀገራት ጫና ወደ ጎን በመተው በአጭር ግዜ ግብዓተ መሬታቸውን መፈጸም ይጠበቃል። እየሆነ ያለውም ይሄ ነው። ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዱት ውሳኔና የጋሸና፣ የጭፍራ፣ የካሳጊታ እንዲሁም በርከት ያሉ ድሎችን አስገኝቶልናል። አሁንም ይቀጥላል።
አገር ለማውደምና ለማፍረስ የአማራንና የአፋርን ምድር የወረረው ሽብርተኛ እዚሁ ተቀብሮ እንደሚቀር ደግሞ ምንም ጥርጥር የለውም። ለዚህ ነው የአፋርና የአማራ ምድር ወያኔ ሂሳብ የሚያወራርደው ሳይሆን የሚዋረድበት ነው የምንለው።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7/2014