የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበትን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮን ሺፕ /ቻን/ እኤአ በ2020 ለማስተናገድ ከካፍ ኃላፊነቱን ከተረከበ ዓመታት አልፈዋል። ፌዴሬሽኑ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ውድድር ለማሰናዳት ለካፍ ሲያመለክት አገሪቱ ቀደም ሲል የአፍሪካ ዋንጫን በብቃት ማስተናገዷን ጠቅሷል፤ ይህ ብቻም አይደለም በየክልሉ የተገነቡትን እና እየተገነቡ ያሉትን ስታድየሞችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማስረጃነት በማቅረብም ፍላጎት ብቻም ሳይሆን አቅሙም እንዳለው ለማሳየት ሞክሯል።
የካፍ ፕሬዚዳንት ማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ ወደ ተመረጡባት ኢትዮጵያ ብቅ ባሉበት ወቅትም አገሪቱ በስፖርት መሰረተ ልማት በተለይ ለእግር ኳሱ እድገት ከፍተኛ ወጪ በመመደብ እያከናወነች የምትገኛቸው የተለያዩ ተግባራት በማድነቅ፤አህጉራዊ ውድድሮች የማዘጋጀት ፍላጎቷንም በስኬት የማድመቅ ተስፋ እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል።
በእርግጥም አገሪቱ የአፍሪካ ዋንጫን ጨምሮ ሌሎችም አህጉራዊ ውድድሮችን ለማስተናግድ ፅኑ ፍላጎት አላት።ይህን የማድረግ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አቅምም እንዳላት ለማሳየት ታዲያ ቻንን ለማዘጋጀት የተቀበለችውን አደራ በብቃት መወጣት ግድ ይላታል። ይሁንና ሀገሪቱ ለመስተንግዶ የምታደርገው ዝግጅት ሲፈተሽ ግን በቂ ፍጥነት እንደሌለው በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው።አሁንም ቢሆን ስራዎች በበቂ መልኩ ሲከወኑም አይታይም።ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም የሚሰሩ ስራዎች ደካማ ሆነው ይስተዋላሉ።
በእነዚህ ምክንያቶችም የአገሪቱ የቻን ዋንጫ ዝግጅት በምን ዓይነት ቁመና ላይ እንደሚገኝ በቅጡ አይታወቅም።የመሰናዶ ዝግጅት ለመገምገም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የካፍ ልዑካን ቡድንም፤መሰረታዊ ግንባታዎች እስከ ውድድሩ መቃረቢያ ወቅት መጠናቀቅእንዳለባቸው ማሳሰቡ ይታወሳል።
ይሁንና አሁን ባለው የኢትዮጵያ ስቴዲየሞች የግንባታና መሰናዶ አካሔድ በተለይ በክልሎች የሚገኙና ግንባታቸው የተጀመሩ ስታዲየሞች የካፍን መስፈርት አሟልተው በወቅቱ ስለመድረሳቸው ማረጋገጫ ለማግኘት ከባድ ሆኗል።ከስታድየሞቹ የውጭ ገፅታም በላይ ውስጣዊ ሙሉነታቸው ከሙሉው ይልቅ ጎዶሎው ቀድሞ የሚታይ ነው።ይህ መሆኑም አገሪቱ አዘጋጅነቷን የመነጠቅ ዕጣ ፋንታ እንዳይደርስባት የሚሰጉ እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል።
በዚህ ረገድ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች በአንፃሩ፤አዘጋጅነቱን መነጠቅና አሳልፎ መስጠት ከሚያደርሰው ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኪሳራ ለመዳን ሊከናወኑስለሚገባቸው አብይት ተግባራት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ ሲያምረኝ በርሄ የአህጉራዊ የእግር ኳስ ውድድሮችን ለማሰናዳት ጥያቄ ስታቀርብ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ያሉ ውድድሮችን ለማሰናዳት ቻንን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበትና አቅሟን ማሳየት ይገባታል»ይላሉ። ይሁንና በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበትን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮን ሺፕ /ቻን/ ውድድር የሚሰጠው አመለካከት የተዛባ መሆኑን የሚያስገነዝቡት አቶ ሲያምረኝ፤ከሁሉም በላይ ውድድሩን ዝቅ አድርጎ የመመልከት ከፍተኛ የተሳሳተ አመለካከትመኖሩንም ይገልፃሉ።
እንደ አቶ ሲያምረኝ ገለፃ፤ቻን ከአፍሪካ ታላላቅ የእግር ኳስ ውድድሮች አንዱና እውቅና ያለው ነው።በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት እንደመሆኑ ለወጣት የነገ ተተኪዎች እድል የሚፈጥርና ጎልተው እንዲታዩ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።በአሁኑ ወቅትም የላቀ ትኩረት አግኝቷል። የምዕራባውያን መልማዮች አይን ማረፊያ ከሆነም ቆይቷል፡፡ «ውድድሩ በዚህ ረገድ የላቀ ግምት የሚሰጠው እንደመሆኑም አዘጋጅ አገራት፤የማስተናገድ እድል ሲያገኙ የሚጠቀሙት ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትሩፋት ከፍተኛ ነው»የሚሉት አቶ ሲያምረኝ፥በውድድሩ የቆይታ ጊዜ የመላአፍሪካና ዓለም አይን በአገሪቱ ላይ እንደመሆኑ በገፅታ ግንባታ ረገድ የሚኖረው አበርክቶም የላቀ መሆኑንም ይገልጻሉ።
በብሄራዊ ቡድን ደረጃም ቢሆን፤ውድድሮችን በማስፋት በቂ ልምድ እንደሚያስገኝ ይናገራሉ፡፡ በስፖርት ቱሪዝሙም የሚገኘው ገቢም ለረጅም ዓመታት ተሰርቶ የማይገኝ ስለመሆኑ ያመላክታሉ። በስንት ተማጽኖ ተጠይቆ የሚገኝ አዘጋጅነት መነጠቅ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያስቀርም አቶ ሲያምረኝ ያስገነዝባሉ፡፡
‹‹መሰል ውድድሮችን ለማሰናዳት አሁን በእጅ የተያዘውን አጋጣሚ መጠቀሙ እንደ ቀላል ነገር መታየቱ መቆም ይኖርበታል፤ለመስተንግዶ ስኬት የሚመለከታቸው አካላት በተለይም ከመስተንግዶው ተጠቃሚ የሚሆኑ ባለሃብቶች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸውም ይላሉ። ውድድሩን ለማስተናገድ ከሚቀረው ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ ውስጥ በመላ አገሪቱ የተገነቡ ዘመናዊ ስታዲየሞችና ለእንግዶች መስተንግዶ ግልጋሎት የሚሰጡ ግንባታዎን ማቀላጠፍን ጨምሮ አስፈላጊውን ዝግጅት መቋጨት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ ታደሰ እንደሚሉት፤ውድድሩን ለማዘጋጀት መብቃት ከስፖርቱ ጨዋታ ባሻገር በተለይ የአገር ገፅታን በመገንባት ፖለቲካዊ፤ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፤የአገር ውስጥ እግር ኳስ አፍቃሪዎችም የውጭ ተጫዋቾችን በመመልከት ይበልጥ የሚነቃቁበት አጋጣሚ ይፈጥራል። የውድድሩ ፋይዳ ይህ እስከሆነ ድረስ በመስተንግዶ ረገድ በቂ ዝግጅት ማድረግና አህጉራዊ ውድድሮች የማስተናገድ በቂ አቅም እንዳለ ማስመሰከር የግድ እንደሚል የሚገልፁት ረዳት ፐሮፌሰር ወንድሙ፤ በተለይ በሁሉም ክልልከተሞች ውስጥ ግንባታቸው ተጀምሮ ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቁትን ስቴዲየሞች፤ የማጠናቀቅ፣በተለይም ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ማስጠበቅ የግድ እንደሚል ነው ያመለከቱት፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ፤«አገሪቱ ውድድሩን ከማሰናዳት ባሻገር ለመድረኩ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን በማዘጋጀት ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ እንዳለባት መዘንጋት የለበትም» የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤መወዳደር ብቻም ሳይሆን ውጤታማ ለመሆን ከወዲሁ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ይገልጻሉ። ይህ ካልሆነም ገና በመጀመሪያው ዙር መባረር እንደሚከተል፣ይህ ሲሆንም ስታዲየም ተገኝቶ ጨዋታዎችን የሚመለከት ተመልካችም እንደማይገኝ፣ ውጤቱም ግዙፍ ኪሳራ እንደሚያስከትል ማወቅ ይገባል ይላሉ፡፡ ከውድድሩ መስተንግዶ ባሻገር ጠንካራ ቡድን ይዞ ለመቅረብ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አፅዕኖት ተናግረዋል። የስፖርት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሰ ፤ ኢትዮጵያ የቻን ዋንጫን እኤአ በ2020 ለማስተናገድ ከካፍ ኃላፊነቱን ከተረከበች ዓመታት ማለፋቸውን ያስታውሳሉ።
«በአሁኑ ወቅትም ይህን የዝግጅት አደራ በስኬት ለመወጣት እቅድ ወጥቶ ወደ ስራ ተገብቷል፤ዝግጅቱን ለመገምገም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የካፍ ልዑካን ቡድን በሰጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት ክልሎችም የሀዋሳ፤ የባህር ዳር፤የመቀሌ ስታዲየሞችን የማዘጋጀት ተግባር እያከናወኑ ናቸው»ያሉት አቶ ናስር፤ኮሚሽኑም የስታዲየሞቹ ግንባታ ሂደት በተሻለ ፍጥነት ጥራቱን ጠብቆ ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ያብራራሉ።
አገሪቱ አደራዋን በስኬት ለመወጣት እየተንቀ ሳቀሰች እንደሆነ ቢገለፅም፣ ውድድሩ እየተቃረበ በመጣበት በዚህ ወቅት የመስተንግዶ ዝግጅት ፍጥነት ሲፈተሽ መጓተት እንደሚስተዋል በግልፅ ይታያል ፤በዚህ ላይ ምን ይላሉ በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ አቶ ናስር ሲመልሱም፤መስተንግዶው በቂ ፍጥነት እንደሌለው አልሽሸጉም። «ቻንን የመሰለ ታላቅ አህጉራዊ ውድድር ለማስተናገድ አስቀድሞ መዘጋጀት የሚገባ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው ዝግጅት ግን በሚፈለገው ልክ እየተጓዘ አይደለም»ያሉት አቶ ናስር፤ውድድሩ እየተቃረበ ሲመጣ በርካታ ተግባራት መልክ መልክ እንደሚይዙና እንደሚሳኩ እምነታቸው መሆኑን ነው ያብራሩት።
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
በታምራት ተስፋዬ