በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት ኢትዮጵያን መቅረብ እንደሚፈልጉ ሁሉ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከዓለም ካርታ ላይ እንድትፋቅ የሚፈልጉት አያሌ ናቸው። ኢትዮጵያ ታሪኳን፣ ስሟንና ሁለመናዋ ሲሰሙም እንደ ጋለ ብረት የሚያቀልጣቸው እንደ እንዝርት የሚያሾራቸው ሀገራት ጥቂት አይደሉም።
የኢትዮጵያ የቀኝ አልገዛም ባይነትና የጀግንነት ታሪክ ኩራት የሚሰጣቸው በርከት ያሉ ወዳጆች እንዳሉ ሁሉ የዚህ ታሪክ ባለቤት መሆኗ የእግር እሳት የሆነባቸው ሁልቆ መሳፍርት ጠላቶች ያሏት ሀገር ናት።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥ እና ከውጭ ተናበው የሚሰሩ ጡት ነካሾች፣ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እና ሀያላን ሀገራት እንዳሉ ሁሉ በችግሯ ጊዜ ከአጠገቧ የማይጠፉ የቁርጥ ቀን ወዳጆችም ያሏት ቅኔ የሆነች ለጠላትም የእግር እሳት የሆነች ሀገር ናት ። በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያን የገጠማት ፈተና ከዚህ አውድ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።
አሸባሪውን ሕወሓት ከሞት አፋፍ መልሰው እንዲያንሰራራ እና በኢትዮጵያ ምድር ላይ ዳግም የክፋት መርዙን እንዲተክል ሌት ተቀን እየባተቱ ያሉ ሀገራት ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም። ዴሞክራሲ እህል ውሃችን የመኖር ዋስትናችን ነው የሚሉት ምዕራባውያንና ሠብዓዊነትና ዴሞክራሲ መገለጫዬ ነው የምትለው አሜሪካ አሸባሪውን ሕወሓት ከመቃብሩ ቆፍረው አውጥተው እስትንፋስ ሊዘሩበት የሚቻላቸውን አቅም ሁሉ እየተጠቀሙ ነው።
ይህም ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በተፃራሪው በመቆም አደገኛ ቁማር ለመቆመር እየተፈራገጡ ይገኛሉ። ከምኞት የዘለለ ገቢራዊ እንደማይሆን ቢያውቁትም፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ መግለጫዎችን በማውጣት መጠመዳቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው።
እነዚሕ ሀይሎች በአሁኑ ወቅትም ሆነ ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያውያን ላይ የሰራው ግፍና እያደረሰ ያለውን ጥፋት ማየትም መስማትም አይፈልጉም። ዋነኛ የእነርሱ መደራደሪያ ተላላኪ ቡድን መመስረትና የግል ፍላጎታቸውን የሚያሳካ አካል መፍጠር ብቻ ነው። በዚህም የተነሳ ይህ ቡድን ከአፈጣጠሩ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ የሚፈፅመው ህፀፅ ግድ አይሰጣቸውም።
ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ ለተነሳው ቡድን ድጋፍ ከመስጠት ውጪ የመኮነን ሞራል እንኳን አልፈጠረባቸውም። ይልቁንም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትን በመናቅ የራሳቸውን አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት ደፋ ቀና እያሉ ነው።
ጁንታው ከመንበረ ሥልጣን ከተባረረበት 2009 ዓ.ም ጀምሮም ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈትና ዳግም ሀገሪቱን እንደለመደው ለማሰቃየት ሰፊ እቅድ አቅዶ ሲንቀሳቀስ ነበር።
በተለይም አራት ኪሎ ቤተመንግስትን ትቶ ወደ መቐለ ከመሸገ በኋላ ስልጣን የህልም ቅዠት ሆኖበት ያለውን አቅም ሁሉ ለመጠቀም ጥረት አድርጓል። የሀገሪቱን ሃብት በመመዝበር ለክፉ ቀን ይጠቅሙኛል ያላቸውንና ያስተማራቸውን የዕኩይ ዓላማ አስፈፃሚ እና ፈፃሚ ናቸው ያላቸውን ምሁራን ከመላው ዓለም ጥሪ በማድረግ ወደ መቀሌ እንዲመጡ አድርጓል። ሆኖም በዚህ ወቅት እነዚህ ምዕራባውያን አይዞን ብለው ከማበረታት ውጭ ከሀቅ ጎን ለመቆም አልወደዱም።
ቡድኑ ቀደም ሲል በመላው ዓለም የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን ያሰራጭባቸው ለነበሩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ዳጎስ ያለ ገንዘብ በመመደብ የፕሮፓጋንዳ ሥራው ከዓይን ፍጥነት በበለጠ እንዲያቀላጥፉ በሰባቱም አህጉራት አዘጋጅቶም ነበር፤ እውነታውንም በአሁኑ ወቅት እየሆነ ባለው ነገር መረዳት ይቻላል።
ይህ ሁሉ ሲሆን የዴሞክራሲ ጠበቃ ነን ሰብዓዊነት ይቀድማል የሚሉት አካላት ነገሩ ከማማባስ እና የራሳቸውን አጀንዳ ለማስረፅ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በሚዲያ በኩል መላክ እንጂ ከእውነታው መታረቅ አልፈለጉም።
አሸባሪው ሕወሓት በተለያዩ ወቅቶች ለመስኖ ልማት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ናቸው በማለት ድሮን (አነስተኛ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ጥረቶችን ያደረገ ቢሆንም በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እና የሚመለከታቸው አካላት ባደረጓቸው ጥብቅ ክትትሎች ጉዳዩ ከምኞትና የቀን ህልም ከመሆን ያለፈ ውጤታማ አልሆነም። በእርግጥ እንደ ቡድኑ ሃሳብ ቢሆን ኖሮ ይህን ጊዜ ኢትዮጵያ ከመቼውም ሁኔታ በከፋ አደጋ እና ስቃይ ውስጥ በሆነች ነበር።
ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ምዕራባውያን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ነበር። አሁን ነገሮች ፍንትው ብለው ወጥተዋል። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል የለባትም የሚለው የአሸባሪው ሕወሓት እና የምዕራባውያን አጀንዳ አግጦ ወጥቷል።
ኢትዮጵያ ላይ እንዲህ እናደርጋለን እያሉ የሚያሟርቱት ጠላቶች በርካቶች ናቸው። እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ አጀንዳ የለንም እያሉ ነው። ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አለመገዛቷ በእጅጉ ያንገበግባቸዋል። በዓለም ላይ ያሉ ጥቁር ህዝቦች መነቃቃትና ባርነትን ቀንበር እየሰበሩ እንዲወጡ ኢትዮጵያ መሰረት ሆናለች ብለው ስለሚያምኑና እውነታው ይኸው ስለሆነ በተቻላቸው አጋጣሚ ሁሉ የበቀል በትር ሊያሳርፉባት ይዳዳሉ፤ እያደረጉትም ነው።
ግብጽ እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ በውሃ ጥም ልንሞት ነው ሲሉ ሌት ተቀን ይዶልቱባታል። ከምድራችን አፈር፤ ከምንጫችን ደግሞ ውሃ እየወሰዱ እየተጠቀሙ የእኛ ቀና ማለት ያንገበግባቸዋል። ከጥንታዊነታችንና ቀዳሚነታችን የሚቀዱ ታሪኮቻችን የራሥ ምታት እየሆኑባቸው ስለ እኛ ውድቀት ይመኛሉ። ዕዥ እያነባን እንድንኖር ፀረ ሀገር ከሆኑት አካላት ጋር ሁሉ እያበሩና እያስተባበሩ ሲያዳክሙን ኖረዋል፤ አሁንም የዘመናት ሴራቸውን እየሸረቡብን እየነከሱን፤ እያቆሰሉን፤ እያደሙን እና ለእኛ ውድቀት ማፋጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው በሚያስቧቸው ተግባራት ላይ ሁሉ በማተኮር ዛሬም እየተፈታተኑን ነው።
እኛ ጠላቶቻችንን ድባቅ ለመምታት ከመቼውም በበለጠ የምንጠናከርበት የፈተና ወቅት መሆኑን መገንዘብ ይገባናል። እውነታው ጠላቶቻችንን አሳንሶ ማየት፤ አግዝፎም መመልከት የለብንም የሚለው መሆን አለበት። በሁሉም አቅጣጫ በማናቸውም ጊዜ ለጠላት የማንመች ሀሞተ መራራ፤ ልበ ኮስታራ ሆነን መገኘት አለብን።
ምድሪቱን በሙሉ ማጠር አለብን። ኢትዮጵያ ምድር ላይ ቀዳዳዎችን ተጠቅመው መግባት ለሚፈልጉት ሁሉ አሜኬላ እስካልሆን ድረስ ዓላማቸውን ማሳካታቸው አይቀርም። ምንም እንኳ ጠላት የወገንን አሰላለፍና አቅም የሚያስረዱ የሳተላይት መረጃዎችን በቴክኖሎጂ ከመጠቁ ሀገራት የሚያገኙ ቢሆንም ለዚህ ተገዳዳሪ የሚሆንና ሁኔታዎችን ከሚጠበቀውና ከሚገመተው በላይ የሚረዳ ማህበረሰብና ሰራዊት እየፈጠሩ ጠላትንም እየመነጠሩ መሄድ ይገባል።
ለጠላት ምቹ የሚሆኑ ቀጣናዎችንና አካባቢዎችን በሙሉ ማጠር አለብን። ለኢትዮጵያ ምድራዊ አጥር ሆነን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ማስከበር ከአባቶቻችን ታሪክና ደም የወረስነው እንጂ በስሜት ያመጣነው አለመሆኑን ማሳየት ይጠበቅብናል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6/2014