የጽንሰ ሃሳብ ብያኔ፤ ማረጥ (Menopause) ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚያከትመውን ተፈጥሯዊ የሴቶች የወር አበባ ዑደት ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። ዕድሜ በጨመረ ቁጥር በወር አበባ አማካይነት የዘር ዕንቁላል ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ወይንም በራሳቸው ጊዜ ዕንቁላሎቹ እየሟሸሹ ሲጠፉ አንዲት ሴት አረጠች ይባላል።
የሴቶች የማረጫ ዕድሜ ከ40ዎቹ እስከ 60ዎቹ መካከል እንደሆነ የዘርፉ የጥናት ውጤት አረጋግጧል። አልፎ አልፎ ግን ከተሰጠው የዕድሜ ፀጋ ገደብ በታችም ይሁን በላይ ተፈጥሯዊ ክስተቱ ሊቀንስም ሆነ ሊጨምር እንደሚችል ይታመናል።
ሴቲቱ አርጣለች ብሎ ለመደምደም ቢያንስ ለ12 ተከታታይ ወራት የወር አበባዋ መቆሙም መረጋገጥ አለበት። የተለያዩ የጤና እክሎችና የስሜት መዋዠቅ ፈተናዎችም የተፈጥሯዊ ክስተቱ መገለጫዎች ናቸው። ያለበቂ ምክንያት መናደድ፣ ያልተለመዱ የተቆጭነት ባህርያት፣ የቁርጥማትና በርካታ ተያያዥ የድካም ስሜቶችን ማስተናገድ፣ የትኩሳትና የውስጥ አካል ሙቀት መጨመር ዋነኛዎቹ መገለጫዎች ናቸው።
የአሜሪካ ዴሞክራሲ የማረጥ ምልክቶች፤ አሜሪካ ራሷን የዴሞክራሲ “አምራች ማህጸንና ለዓለም ሀገራት ሁሉ ዘሩን በችርቻሮ አከፋፋይ አድርጋ” ማሰብ የጀመረችው ገና ከማለዳው ነው። ይህ ግምቷ ራሷን ሽቅብ አጉና “ከእኔ በላይ ስለ ዴሞክራሲ ለመናገር ለአሳር” በማለትም ለመታበይ ምክንያት ሆኗታል።
ስለ ሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች አጠባበቅ ጉዳይ ሲነሳ ራሷን ዋነኛ ዘበኛ ለማድረግ ስትደሰኩር ብትኖርም በጓዳዋና በደጃፏ የሚፈጸሙትን ጉድፎችና ግፎች ከቁብ ባለመቁጠር ነው። አንድም በዘር አለያም በቀለም ወይንም በሌሎች በርካታ ምክንያቶች በዜጎቿ መካከል በአድልዎ ፈጻሚነት እየታወቀች “እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ!” እንዲል ብሂሉ ወደ ሌሎች ጣቷን የምትቀስረውን ያህል ራሷን ለመፈተሽ አትደፍርም። በርካታ የኮሜዲና የትራዤዲ ትዕይንቶች የሚስተዋልበትን የፖለቲካ ምርጫ ሥርዓቷን ለማሳየት የምትሞክረውም ገለባውን ሳይሆን አላባውን እየሰፈረች ነው።
በአህያና በዝኆን ምልክቶች ከሚፋለሙት አዛውንት የፖለቲካ ፓርቲዎቿ (ዲሞክራቲክና ሪፐብሊካን) ውጭ ሌሎች አናሳ ፓርቲዎች መንበረ ሥልጣኑን እንዳይቆናጠጡ በሯን ከከረቸመች ዘመናት ተቆጥረዋል።
በምርጫ ውድድር ወቅት እንኳን ደፍረው ወደ ምህዳሩ ለመግባት ዳር ዳር የሚሉትን ዐይን አፋር ፓርቲዎች አንዱን “በርግጫ” ሌላውን “በኩምቢ” እያጠቋቸው ከፍልሚያው ሜዳ እንዴት ዘወር እንደሚያድረጓቸው ዓለም በግላጭ እየታዘበ ነው።
በአሜሪካ የፕሬዚዳንቶች ታሪክ ጥቁሩ ባራክ ኦባማ የነጩን ቤተ መንግሥት አጥር በብቃታቸው ጥሰው እስከገቡበት ጊዜ ድረስ “ዕንቁላሉ ቤተ መንግሥት” ነዎሩ እያለ ሲያስተናግዳቸው የኖረው ነጫጮቹን መሪዎች ብቻ እንደነበር አይካድም።
ዛሬስ መች ተለወጠ? ኦባማም ቢሆኑ ብቃታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የብረቱን በር በርግደው ሰተት ብለው የገቡት ምን ያህል ሚሊዮን ረብጣ ዶላሮችን በቅስቀሳ ስም ሆጨጭ አድርገው በማፍሰስ እንደነበር በዜና መዋዕላቸው ውስጥ በሚገባ ተሰንዷል። ይህቺው አሜሪካ ይሏት የጉድ ሀገር ራሷ የጣደችው ድስት (Melting pot) ነኝ ማለቷን ልብ ይሏል፤ ትታ የሌሎችን ሀገር ሉዓላዊነት “ካላማሰልኩ” እያለች ጥልቅ ያለችባቸው ታሪካዊ አጋጣሚዎች ቁጥር ስፍር የላቸውም።
ይሁነኝ ብላ የጫረቻቸውን ጦርነቶችና ፀቦች በማስታወስ እውነቱን ማረጋገጥ ይቻላል። ክርስቶፈር ኬሊ እና ስቱዋርት ሌይኮክ የተባሉ ደራስያን በ2015 ባሳተሙት “All the Countries the Americans Have Invaded” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የዘረዘሯቸው አስደንጋጭ የወረራና የአጥቂነት ታሪኮች የሚከተለውን ይመስላሉ። “…the United States has invaded or fought in 84 of the 193 countries recognized by the United Nations and has been militarily involved with 191 of 193 – a staggering 98 percent.” የአማርኛውን ትርጉም በአጭሩ ለማስቀመጥ፤ “በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ካላቸው 193 አገራት መካከል አንድም በወረሪነት አልያም በጥቃት አድራሽነት አሜሪካ 84 አገራትን ወራለች ወይንም አጥቅታለች።
ከ193 አገራት ውስጥም በ191ዱ አገራት ውስጥ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ተሳትፋለች- ይህ አስደንጋጭ ስሌት የዓለማችን አገራትን 98% እንደሚሸፍን ልብ ይሏል።” ጥናቶች እንደሚጠቁሙት አሜሪካ በወረራ፣ በወታደራዊ ሠፈርነት ወይንም በቀጥታ ጣልቃ ገብነት እስከ ዛሬ በክፉ ዐይን አይታ ያልዞረችባቸው ሀገራት ሦስት ብቻ ሲሆኑ እነርሱም አንዶራ (Andorra)፣ ቡታን (Bhutan) እና ሊችቴንስቲን (Liechtenstein) ናቸው።
እነዚህን ሀገራት በርካታ የዓለማች ዜጎች በሚገባ ስለማወቃቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ለነገሩ እነዚህን ሚጢጢዬ ሀገራት ከመዳፈር የታደጋቸው በዐይን ውሃዋ ልክ ስላልሞሉላት ሊሆን ይችል ይሆናል። አንዶራ የምትገኘው በፈረንሳይና በስፔን መካከል ሲሆን የምትታወቀውም ቅብጥ ባለውና ከቀረጥ ነፃ በሆነው የገበያዋ ሥርዓትና በመዝናኛ ስፍራዎቿ አማካይነት ነው። ምናልባትም አሜሪካ በክፉ ዐይኗ ያልነደፈቻት የሆሊ ውድ ልጆቿ መዝናኛ ስፍራ ስለሆነች ሊሆንም ይችላል። ይህ የጸሐፊው ግምት ነው። የቡታን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ በምሥራቃዊው የሂማሊያ ተራሮች ጠርዝ ላይ ሲሆን መታወቂያዋም የቡድሃ ሃይማኖት ተከታይ መነኮሳት መነኻርያነቷ ነው።
የቡዲህስቶቹ እምነት ዐይኗን ቢያሳውር እንጂ አሜሪካ ከሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ጋር ባላት እንካ ሰላንትያ ምክንያት ይህቺ “ጸሎተኛ ሀገር” በሰላም ባልኖረች ነበር። ሊችቴንስቲን በኦስትሪያና በስዊዘርላንድ መካከል የምትገኝ ብጥሌ ሀገር ናት። ዋነኛ መታወቂያዋም በመካከለኛው ዘመን (ከ5ኛው መቶ እስከ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) የታነጹት ታሪካዊ ሕንጻዎቿ ናቸው።
አሜሪካ ለነባር ታሪኮች ቁብ ስለሌላት ምራታለች ወይንም አልፈለገቻትም። አሜሪካ በቀጥታ በወረራ ከተዳፈረቻቸው ሀገራት መካከል ቪዬትናምን፣ ሱማሊያን፣ ኢራቅን፣ አፍጋኒስታንን እንኳን ለአብነት ብናስታውስ ጦር የሰበቀችበት ምክንያት እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ መረዳት እንችላለን።
በእነዚህ ሀገራት ውስጥም ሆነ ባልተጠቀሱት ሌሎች በርካታ ሀገራት ውስጥ ጡንቻዋን አሳብጣ ወደ ጦርነት ብትገባም ከሁሉም ሀገራት አንገቷን ደፍታ የወጣችው በውርደት እንደነበር የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ እንዴት ከአሜሪካ ጋር ተጣቀሰ ብለው ለሚጠይቁ አንባቢያን በቀድሞዋ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር በኤርትራ፤ አስመራ ከተማ ውስጥ የነበረውን የቃኘው ሻለቃን የጦር ሠፈር ማስታወስ ይቻላል።
ይህ የጦር ሰፈር በኢትዮጵያ ውስጥ የቆየው እ.ኤ.አ ከ1943-1977 ነበር። ገናና ታሪክ ያለው ይህ የጦር ሰፈር ለሦስት አሥርት ዓመታት ሲያከናውን የኖረውን ተልዕኮ በተመለከተ በዝርዝር ለመተረክና ሌሎች በታሪክ የሚታወቁ ጉልህ ጣልቃ ገቦችን ለመተረክ ዐውዱ ስለማይፈቅድ ታሪኩን በይደር አስተላልፎ ማለፉ ይበጃል።
ይህንን መሰሉን ታሪክ አርግዛ የኖረችው አሜሪካ የዴሞክራሲ ጠበቃ ነኝ ብላ ብታደነቁረን ሊጨበጨብላት ይገባል? ደግሞስ “እውነተኛው ዴሞክራሲ በደጃፌ ጎምርቶ ያፈራው ብቻ ነው” ብላ ብታቅራራ “ዘራፍ!” እያለ የሚያግዛት አሟሟቂ ይኖራል? በአጭሩ ለመደምደም የምንችለው የአሜሪካ ዴሞክራሲ ማረጥ ብቻም ሳይሆን ሽሉም ራሱ ጨንግፏል። ማህጸኗም ደርቋል።
መገለጫውም በነጋ በጠባ የሚስተዋሉት የሀገሪቱ ጤና ማጣቶች ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው። ሳይሰስቱ በሚከፍሉት ታክስ በልማትና በርዳታ ስም ለዓለም ሕዝቦች እጃቸውን ለሚዘረጉት ዜጎቿ ምሥጋና ማድረሳችን እንደተጠበቀ ሆኖ አናት ላይ ፊጥ ያሉት የመሪዎቿ ጤንነት ከተቃወሰ ግን ሰነባብቷል። አስተሳሰባቸው ተዛብቷል።
ስሜታቸውም መስከን ተስኖት እንደ አበደ ውሻ እዚህም እዚያም ሀገራትንና መንግሥታትን በመተነኳኮስ እረፍት እየነሷቸው ይገኛሉ። ለአሜሪካ የዴሞክራሲ ማረጥ ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል? ሰሞኑን “Ten Questions for American Democracy” በሚል ርዕስ አንድ የቲንክ ታንክ ቡድን ከ“Chongyang Institute for financial studies, Renmin University of China” የአሜሪካንን ዴሞክራሲ የሚሞግት አንድ ዘርዘር ያለ ሞጋች ጥናት በመላው ዓለም በትኗል።
ጥናቱ ካተኮረባቸው ዐሥር ጥያቄዎች መካከል የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው። የአሜሪካ ዴሞክራሲ ለማን? ለብዙኃን ወይንስ ለጥቂቶች? የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል ወይንስ ለስቃይ ለመዳረግ? ለነፃነት መቆም ወይንስ ለሕዝቦች የማሰናከያ እለት መሆን? ለሰብዓዊ መብቶች ጥብቅና ለመቆም ወይንስ ለጠላትነት? አንድነትን መስበክ ወይንስ ከፋፋይነት? ልማትና ብልጽግናን መደገፍ ወይንስ ለሀገራት የመከራና የስቃይ ምክንያት መሆን? ለዓለም ሰላም ዘብ መቆም ወይንስ የቀውስ ቆስቋሽ መሆን? ወዘተ. ጥናቱ ያተኮረው ለእነዚህ ጥያቄዎች ተጨባጭ መልስ ለመስጠት ተፈልጎ ነው።
ለተዘረዘሩት ዓሠርቱ ጥያቄዎች ሰፊ ትንተና ከተሰጠ በኋላ ግኝቱ የተደመደመው በሚከተለው አስደማሚ ማጠቃለያ ነው። እንዲህ ይነበባል። “Many facets show that, in the name of `democracy` the only ones in the United states that can reflect their will are money-cracy, Guncracy, White-cracy, Media-cracy, Militiacracy, and Drug-cracy…America political practice makes America democracy a “minority democracy,” a “money controlled democracy,” a “corrupted democracy,” a “democracy destroyer,” a “world bully,” and “international rule trampler,” and more.” እናስ ከዚህን መሰሉ ያረጠ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ምን ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ላይ የአሜሪካ ክፉ ዐይን፤ ከየትኞቹም የዓለማችን ሀገራት ይልቅ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ዐይነ ጥላ (evil eye) ክፉኛ የተተከለው በኢትዮጵያ ላይ ይመስላል።
የመገለጫው ዝርዝር ደግሞ የትዬለሌ ነው። እንደ አዶከበሬ ባለዛር በሀገሬ ላይ የሚያስገዝፋቸው ሰበቡ አሸባሪውና ጨካኙ የመጋለቢያ ፈረሳችን ሕወሓት ለምን ተነካብን የሚለው ሰበብ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያን መሰል ታላቅ ሀገር እንድትዳከም ቢሆንላቸውም እንድትበታተን ከዚህ ጉግ ማንጉግ ቡድን ጋር በማበር የማይጠነሰስ የሴራ ዓይነት የለም ማለት ይቻላል።
ይህንን ተግባራቸውን እየፈጸሙ ያሉት ደግሞ በግላጭና በጠራራ ፀሐይ መሆኑ በእጅጉ የሚያስገርም ነው። ሲያሻቸው አሸባሪው ቡድን ያለበት ጎሬ ድረስ በመሄድ፤ አልሆን ሲላቸውም በረቀቀ ስልት፤ ሲዳፈሩም በጦርነቱ መካከል “አለንልህ!” በማለት ወዳጅነታቸውን ለማረጋገጥ ወደ ኋላ አላሉም። በዲፕሎማሲውም መድረክ ላይ “ኢትዮጵያን ካልቀጣናት” እያሉ የሚማማሉት በማን አለብኝነት ትዕቢት ተወጥረው ነው።
በልማትና በተራድኦ ድጋፍ ስም እያስፈራሩ እንድንገብርላቸው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ኢኮኖሚያችን እንዲሽመደመድ ለማድረግ የዘረጉት ወጥመድ ዓይነቱ ብዙ ነው። ምናልባትም እንደዚህ ዘመን የውጭ ኃይላት ተረባርበው ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ያደሙበትና ግምባር የፈጠሩበት ጊዜ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ያዳግታል።
በሕዝብ ድምጽ የተመረጠን መንግሥት ጎትቶ ለማውረድ መሞከር፣ እነርሱ ጠፍጥፈው ለፈጠሯቸው አሻንጉሊት ቡድኖች ኢትዮጵያን አሳልፎ ለመስጠት ማሴር፤ ስንቱ ተዘርዝሮ ይዘለቃል? አልገባቸውም እንጂ እውነቱ ቢበራላቸው ኖሮ ኢትዮጵያን በስም እንጂ የመንፈሷን ጥንካሬ ቢያውቁት ኖሮ እጃቸውን ለአመጽ ባልዘረጉ፣ ሴራቸውንም በአደባባይ ይፋ ባልገለጡ ነበር።
የኢትዮጵያን የብረት አሎሎነት ስላልተረዱት ሊያመነዥጓት ቢሞክሩ አይፈረድባቸውም። ልጆቿም በፈተና ወቅት እጃቸውን ለአለኝታነት፣ ልባቸውን ለአንድነት ለማስተሳሰር ፈጣንና ብርቱ የመሆናቸውን ባህል የተረዱት አይመስልም።
ቤተሰባዊ አታካራችን የጓዳችን ጉዳይ እንጂ የአደባባይ መሃላችን “ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” የሚል መሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገለጸላቸው ስለሆነ እውነቱን ሳይረዱት አልቀሩም። ኢትዮጵያ አንድም በልጆቿ፣ አንድም በጀግኖቿ የሠራዊቷ አባላት፣ አንድም በፈጣሪዋ የተሸመነ የቃል ኪዳን መሃላ ተጎናጽፋ በሦስት ጽኑ ኃይላት እንደተገመደች ማን በነገራቸው? ኦ አሜሪካ! በስመ ዴሞክራሲ ስንት ግፍ ፈጸምሽ!? ሰላም ይሁን!::
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6/2014