የአምቦ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ መሰረት ፊጡማ ከዘጠኝ ወራት በፊት የዘጠኝ ዓመት ልጇ በድንገት ይታመምባትና በአምቦ ዩኒቨርስቲ ሪፋራል ሆስፒታል ለህክምና እንዳስገባቸው ታስታውሳለች። ልጇ ያጋጠመውን ህመም ማከም ከሆስፒታሉ አቅም በላይ ይሆንና ለከፍተኛ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወስዳ እንድታሳክም ይጻፍላታል፡፡ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም ለዘጠኝ ወራት ያህል ልጇ ህክምናውን ሲከታተል እንደቆየም ወይዘሮ መሰረት ትገልፃለች። ወይዘሮ መሰረት ልጇ ያጋጠመው የህመም አይነት የመቅኔ ማነስ /aplastic anemia/ መሆኑን ይገለጽላታል።
ህክምናውም በውጪ እንጂ በሀገር ውስጥ እንደማይሰጥ በሆስፒታሉ የልጁን ህክምና ጉዳይ ሲከታተል የቆየው የሃኪሞች ቡድን እንዳረጋገጠላት ወይዘሮ መሰረት ታስረዳለች። ለዚህም የህክምና ማስረጃ /medical summary/ እንደተፃፈላት ትገልፃለች። ወይዘሮ መሰረት ልጁን ወደ ውጪ ወስዶ ለማሳከም አቅም ከሌላት ሀገር ውስጥ ያሉ መድሃኒቶችን መውሰድ እንደሚችል ቡድኑ ገልጾላታል። ልጇ በሃኪሞች የታዘዘለትን መድሃኒት መውሰድ ቢጀምርም ህመሙን ሊያስታግስለት አልቻለም።
ወደ ውጪ ሀገር ወስዳ ለማሳከም አቅም አለኝ የምትለው ወይዘሮ መሰረት፤ ህንድ ሃገር ከሚገኝ አንድ ሆስፒታል ልጁ ህክምናውን ማድረግ እንደሚችል የሚያስረዳ መረጃ እንደያዘችና ይህንንም እዛው በህንድ ሃገር የምትኖር ዘመዷ እንዳስጨረሰችላት ትናገራለች። የልጁን ሙሉ የህክምና ወጪ እንደምትሸፍንላትና እርሷም የተወሰነውን ለመሸፈን ዝግጁ መሆኗንም ታስረዳለች።
‹‹የጥቁር አንበሳ የሃኪሞች ቦርድ የሪፈራል ወረቀት እንዲፅፍልኝ ከጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ጥያቄ ባቀርብም›› ምላሽ አላገኘሁም የምትለው ወይዘሮ መሰረት፣ ‹‹የህክምና የቦርድ ሪፈራል ወረቀት ለማግኘት ከአምስት ወራትበላይ መጠበቋንም ነው የምታብራራው። ጥያቄውን በተደጋጋሚ ሳቀርብ የሚሰጠኝ ምላሽ ልጁን ለማሳከም የሚያስችል ትክክለኛ ማስረጃ ከአሳካሚው አካልና ህክምናው ከሚሰጥበት ተቋም ይዤ እንድመጣ ነው ስትል ትናገራለች።
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በውስጥ ደዌ ህክምና ክፍል የልብ ስፔሻሊስት ሃኪምና የተመላላሽ ህክምና ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ደስአለው መኮንን እንደሚገልፁት፣ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሃገሪቱ ከፍተኛው የሪፈራል ሆስፒታል ነው። የሃገሪቱ የህክምና ሥርዓት ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ እኩል ባለመድረሱና ብዙ ህመሞችም ከፍ ያለ ህክምና የሚጠይቁ በመሆናቸው ታካሚዎች ሁሉንም የህክምና አይነቶች በሆስፒታሉ ያገኛሉ ማለት አይቻልም።
በዚህም ምክንያት ታማሚዎች በራሳቸው ወጪ አልያም በድጋፍ ሰጪ አካላት /በስፖንሰር/ ወጪ ወደ ውጪ ሃገር ሄደው ህክምናውን እንዲከታተሉ ይደረጋል። ለዚህም ሆስፒታሉ የሪፈር ወረቀት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። ይህም በአብዛኛው የመንግሥት የአሰራር ሥርአትን ተከትለው ወደ ውጪ ሃገር ለህክምና የሚሄዱ ታማሚዎች ይመለከታል። ይህ ሲባል ግን በግላቸው ወደ ውጪ ሄደው የሚታከሙ ታማሚዎች የሉም ማለት አይደለም።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በሆስፒታሉ የውጪ ህክምና ሪፈራል ውሳኔ የሚሰጠው በቦርድ ሲሆን፣ በቦርዱ ህክምናውን ሲከታተል የቆየው ስፔሻሊስት ሃኪም፣ ሁለት የቦርድ አባላትና የህክምና ክፍሉ ኃላፊ በጋራ ከተፈራረሙበት በኋላ ነው። በዚህ ሂደት ታዲያ አንዳንድ ታካሚዎች የቦርድ ወረቀቱን ያለአግባብ ሲገለገሉበት ይታያሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ወረቀቱን ለልመና ሲጠቀሙበት የሚስተዋሉም እንዳሉ ነው የጠቀሱት። ይህንንም ለመቆጣጠር ለቦርዱ የውጪ ህክምና ውሳኔ የሚያቀርበው ስፔሻሊስት ሃኪም ታካሚው ውጪ ሃገር ሄዶ ለመታከም የሚያስችለው አቅምና በቂ የገንዘብ ድጋፍ ወይም ስፖንሰር እንዳለው ያረጋግጣል ሲሉም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ከተቀባዩ ህክምና ተቋም ታካሚው መታከም እንደሚችልና ህክምናው ስለመኖሩ የሚያረጋገጥ ህጋዊ መልስና ለህክምናው የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ መቅረብ ይኖርበታል። አንዳንዴ ከውጪ የህክምና ተቋማት በኢሜል የሚመጡ መልሶች ቢኖሩም ተቀባይነት የላቸውም። ታካሚዎች ከህክምና ተቋሙ መልስ ማግኘት የሚችሉት መጀመሪያ የህክምና ማስረጃቸውን ውጭ ሀገር ለሚገኘው የህክምና ተቋም ልከው ነው።
በመቀጠልም ተቋሙ የህክምና ማስረጃውን ከተመለከተ በኋላ ተቋሙን በሚገልፅ ደብዳቤ ህጋዊ መልስ ይሰጣል። በዚህም መሰረት ህክምናውን ሲከታተል የነበረው ስፔሻሊስት ሃኪም ምላሹን ለቦርዱ ያቀርባል፤ ቦርዱም ውሳኔ አሳልፎ የቦርድ ሪፈራል ወረቀት ለታካሚው ፅፎ የሚሰጥ ይሆናል። ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል የቦርድ ሪፈራል ውሳኔ ረጅም ሂደት ያልፍ ነበር፤ በሜዲካል ዳይሬክተር ቢሮ ተፈርሞና ፀድቆ የሚወጣም ነበር። ይሁንና ይህ ሂደት በአሁኑ ወቅት የታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ በህክምና ክፍሎች ደረጃ እንዲያልቅ ተደርጓል።
ውጪ ሀገር ሄደው የሚታከሙ ህሙማን ሪፈር ከተፃፈላቸው በኋላ ሆስፒታሉ ለጤና ሚኒስቴር ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት መረጃውን ይልካል። በዚህም መሰረት ታካሚዎች የውጪ ምንዛሬ እንዲያገኙ የጤና ሚኒስቴር ለብሄራዊ ባንክ ደብዳቤ ፅፎ ታማሚዎች ህክምናቸውን በውጭ ሃገራት ያካሂዳሉ።
የቦርድ ውሳኔው ታካሚዎች የተሻለ ህክምና በማግኘት ከህመማቸው እንዲፈወሱ የሚያስችል መሆኑን የሚገልፁት ዶክተር ደስአለው፣ በተለይም ትክክለኛውን አካሄድ ተከትለው ውጪ ሃገር በመሄድ ህክምና ማድረግ ለሚፈልጉ ታካሚዎች ሆስፒታሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፤ የቦርድ ውሳኔ ሂደቱንም ያፋጥናል ሲሉ ያብራራሉ። የህክምና ሪፈራል ቦርድ ወረቀት አሰጣጥ ሂደት ትክክለኛውን ሂደት ተከትሎ ለሚመጣ ታካሚ ቢበዛ አንድ ወር የሚፈጅ ቢሆንም፣ አጣዳፊ በሽታዎች ሲያጋጥሙ ቦርዱም በአስቸኳይ ተስብስቦ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ የሪፈራል ወረቀቱን ይሰጣል።
አንዳንድ ጊዜ ወደ ውጭ ሃገር የማያስኬዱ ጉዳዮች ሲኖሩና ታክመው መዳን የማይችሉ ህመሞች ሲያጋጥሙ የቦርድ ሪፈራል ውሳኔ ላያገኙ ይችላሉ። እንዲያም ሆኖ ታካሚው ህክምናውን ለማግኘት አስከፈለገ ድረስ የህክምና ቦርድ ሪፋራል ወረቀት ይሰጠዋል። ታካሚው የህክምና ቦርድ ሪፈራል ወረቀቱን ይዞ በተለያዩ ምክንያቶች ህክምናውን በውጪ ሀገር ማድረግ ካልቻለና ሶስት ወር ካለፈው የሪፈራል ወረቀቱ የአገልግሎት ጊዜ ስለሚያልፍ እንደ አዲስ ሂደቱን እንዲጀምር ወይም እንዲያሳድስ ይደረጋል።
ልጇን በውጭ ሃገር ለማሳከም የቦርድ ሪፈራል ወረቀት እየተጠባበቀች ስለምትገኘው ወይዘሮ መሰረት ጉዳይ እንደሚያውቁ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የህክምና ማስረጃ እንደተጻፈላትም ይገልጻሉ። ይሁንና ህክምናውን ከሚሰጠው ተቋም ህክምናው ስለመኖሩ የሚያሳይና ለህክምናው የሚያስፈልገው ወጪ ምን ያህል እንደሆነ የሚጠቅስ መልስ በመያዝ የህክምና ጉዳዩን ሲከታተል ለነበረው ሃኪም አላቀረበችም ይላሉ።
ዶክተር ደስአለው፣ ሆስፒታሉ በተደጋጋሚ ድጋፍ ሊያደርግላት የሞከረ ቢሆንም እርዳታ ሊሰጠኝ የሚችል አካል አለ ከማለት ውጪ ከአሳካሚው አካል ማስረጃ ይዛ መቅረብ አልቻለችም ይላሉ። ዳይሬክተሩ አንዳንዴ ከውጪ ሃገር የህክምና ተቋማት መልስ ስለመጣ ብቻ የህክምና ቦርድ ሪፈራል ወረቀት ይሰጣል ማለት አይደለም ይላሉ። ህክምናውን ሲከታተል የቆየው ሃኪምም ተጨማሪ ጊዜ ወስዶ ማየት የሚፈልጋቸው ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያመለክታሉ።
ከዚህ አኳያ የእርሷ/የወይዘሮ መሰረት/ ልጅ ያጋጠመው ህመም የመቅኔ ማነስ /aplastic anemia/ በመሆኑ ከሃኪሙ ጋር በደንብ መነጋገር እና የህክምና ቦርድ ሪፈራል ወረቀት ለማግኘት የሚያስፈልጉ ግብአቶችንም ማሟላትን እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ። ዶክተር ደስአለው እንደሚገልፁት፤ ሰዎች ውጭ ሃገር ሄደው እንዲታከሙ የሚያደርጉ ወይም ሜዲካል ቱሪዝም የሚሰሩ የሃገር ውስጥ ኤጀንቶች አሉ።
ወደነዚህ ኤጀንቶች የህክምና ማስረጃውን በመላክ መልስ ማምጣት ይቻላል፤ ይሁን እንጂ ከነዚህ ኤጀንቶች የሚመጣው መልስ ብቻውን የህክምና ቦርድ ሪፈራል ወረቀት ሊያስገኝ አይችልም፡፡ የእርሷ መልስ በኢሜል የመጣ ከመሆኑ አኳያና የልጁን ህክምና ሲከታተል የቆየው ስፔሻሊስት ሃኪም በሚሰጠው የህክምና አይነት ካላመነና የታካሚው ዝግጁነት ካልታየበት መልሱ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል ሲሉ ዶክተር ደስአለው ያብራራሉ።
ሃኪሞቹ ታካሚዎቻቸውን በደንብ የሚያውቋቸው ከመሆኑ አኳያና በውጭ ሀገር ህክምና ለማድረግ የሚያበቃቸውን ምክንያቶች ስለሚረዱ የህክምና ቦርድ ሪፈራል ወረቀቱ ለማን መሰጠት እንደሚገባው ያውቃሉ። ዶክተር ደስአለው ገለጻ፤ እንዲህ አይነት ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ለመለመኛነት በር ስለሚከፍቱና ስራ ስለሚያስፈቱ ቦርዱ የህክምና ቦርድ ሪፈራል ወረቀት ጥያቄውን ውድቅ ሊያደርገው እንደሚችልም። አስተማማኝ የመንግሥት አካላትና ትላልቅ ኩባንያዎች ታካሚን ወደ ውጪ ሃገር በመውሰድ ህክምና እንዲያገኝ እናደርጋለን የሚሉ ከሆነ ከህክምና ተቋማቱ መልስ እንዲያመጡ አይገደዱም።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ወይዘሮ መሰረት ልጇን በህንድ ሃገር በሚገኘው የህክምና ተቋም ለማሳከም የሚረዳት ሰው እንዳለ ብትጠቅስም ከሚረዳት አካል የድጋፍ /የስፖንሰርሺፕ/ ደብዳቤ ይዛ መቅረብ አልቻለችም። ልጇን በሆስፒታሉ በእርዳታ እያሳከመች መሆኑና ይህም ለሃኪሞቹ አጠራጣሪና ልጇን ለማሳካም አቅም ይኖራታል ተብሎ የማይገመት በመሆኑ የህክምና ቦርድ ሪፈራል ጥያቄዋ እስካሁን መልስ አልተሰጠውም።
በህንድ ሀገር ልጇን ለማሳከም የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግላት የተዘጋጀው አካል ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደብዳቤ መፃፍ የሚችል ከሆነ የቦርድ ህክምና ሪፈራል ወረቀቱን ማግኘት እንደምትችልም ይገልጻሉ። ይህን ዘገባ አጠናክሮ ለአንባቢ ለማቅረብ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከሶስት ሳምንታት በላይ የቆየ ሲሆን ዘገባው እስከተሰራበት ጊዜ ድረስ የወይዘሮ መሰረት የህክምና ቦርድ ሪፈራል ወረቀት ይሰጠኝ ጥያቄ የልጁን የህክምና ጉዳይ ሲከታተል ለነበረው ሃኪም እንደተመራና መልስ ግን እንዳላገኘ ማረጋገጥ ተችሏል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይህን ጉዳይ በቀጣይም ተከታትሎ በሌላ ዘገባ ይመለሳል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
በአስናቀ ፀጋዬ