ኢትዮጵያ እንዳሰቧትና እንደሚመኙላት ሳይሆን ባልተጠበቀችበት ሁኔታ መገኘቷ አዲሷ አይደለም። ጠላት ‹ላትነሳ ተንኮታኩታለች አበቃላት› ሲል የጠላቷን ምኞት፤ በምኞት ብቻ እንዲቀር የምታደርግ ድንቅ ሀገር ነች።
ዛሬም ያለንበት እውነታ ከዚሁ የተለየ አይደለም። ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ አሸናፊነትን እንጂ ተሸናፊነትን ፈጽሞ አትረዳውም፤ ዜጎቿ ከቃሉ በስተቀር በተግባር መሸነፍን ምን እንደሆነ አያውቁትም። ለዚህ ድግሞ ታሪክ ሕያው ምስክር ነው። ኢትዮጵያ እንደ ምዕራቡ ዓለም ፍላጎት፣ ምኞትና ሟርት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ባልቆየች፤ ዜጎቿም በአንድነት ባልኖሩ ነበር።
እርግጥ ነው አሁን ላይ አገሪቱ ችግር ውስጥ ትሁን እንጂ ከዚህ በታች ችግር የገጠማቸው ሀገራት ግን እንደ አገር መቀጠል ተስኗቸው የምዕራባውያኑ ጉልበት መፈታተሻ ከሆኑ ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል፤ በማስቆጠርም ላይም ይገኛሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት በብዙ ዕጥፍ የሚልቅ ፈተና ገጥሟትም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎቿ እያከናወነች ችግሮቿም ከሰንኮፉ እየነቀለች ዓለምን አጃዒብ ማሰኘቱን ቀጥላለች።
ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እና አገራትም ፍላጎታቸው እንዲሳካ በርካታ መላዎችን በመዘየድ ሲጥሩ የሚስተዋል ሲሆን በተለይም አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ‹ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመግባት ጫፍ ደርሷል› በማለት በምስል በማስደገፍ ‹አዲስ አበባ ተከባለችና በፍጥነት ከተማዋን ለቃችሁ ውጡ።› በማለት እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ ያሉ ሀገራት ዜጎቻቸውን ለማስወጣት በተለያየ መንገድ ውትወታቸውን ቀን ተሌት ሲያደርጉ ቢሰነባብቱም ሰሚ ባለማግኘታቸው እቅዳቸውም ከሽፏል።
እነዚህ አገራትም ከቀረቡት ጥሪ እና ውትወታ በላይ የውጭ ዜጎች ዕምነታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያየለ በመሆኑ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው የዕለት ተዕለት ኑሯቸውንና ሥራቸውን እየመሩ የአዲስ አበባ ንጹህ አየር እየማጉ ዛሬም እየኖሩ ነው።
‹ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች› እንዲል ተረቱ፤ ለወትሮዋ ሠላምና መረጋጋት የተሳናት ጎረቤታችን ሱዳን እንኳን በአቅሟ ዜጎቿ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ጥሪ ማቅረቧ ለስላቅ ዳርጓታል። ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ በዓመት ሁለት ጊዜ መፈንቅ
መንግሥት የተካሄደባት ላለፉት አምስት ዓመታት መረጋጋት ተስኗት በየቀኑ ሰዎች የሚሞቱባትና ጎዳናዎቿ በሰላማዊ ሰልፍ የሚጥለቀለቁ ሆኖ ሳለ ሠላማዊ ኢትዮጵያ ትታችሁ ወደ ሠላም አልባዋ ሱዳን ኑ! ማለቷ አስገራሚም አስደናቂም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሽብር ይፈጠራል እያሉ፤ የሽብር ወሬ ቢነዙም አገሪቱ እንደሚነዛው አሉባልታ ሳይሆን ዛሬም ጎብኚዎች ያልቀሩባት፤ ዛሬም ወዋዕለ ነዋያቸውን ሊያፈሱ የሚመጡ ባለሀብቶች ፍላጎታቸውን የሚያሳዩዋት አገር ሆና ቀጥላለች። በቅርቡም አገሪቱ ከኅዳር 27 እስከ ታህሳስ 03 ቀን 2014 ዓ.ም ያሉትን ቀናት ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት ሰብል ለመሰብሰብ እንዲቻል የትምህርት ማኅበረሰቡን በማሰባሰብ የሰብል ምርት ወደ ደረሱበት የተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች እንደሚያቀኑ በትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሲገለጽ፤ ቢቢሲ ወርልድ የተሰኘው የመገናኛ ብዙኃን አውታር ግን ይህንን መልካም ሥራ ‹አገሪቱ የዕርስ በዕርስ ጦርነቱን ለማባባስ ትምህርት ቤቶቿን ዘጋች› ሲል ነበር የቀጠፈው።
ታዲያ ይህ ቅጥፈት ኃያላን መንግስታትና ሚዲያዎቻቸው ምንኛ ተናበው በኢትዮጵያ ላይ እንደሚዶልቱ ትልቁ ማሳያ ነው። እንደ ሲኤንኤን፣ ቢቢሲ እና አልጀዚራ ያሉ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ ከአሸባሪው ህወሓት ዕኩል በኩል አገር ለማፍረስ፤ ሀገሪቱ በእርስ በእርስ ጦርነት እንድትናጥ ለማድረግ በትጋት በመሥራት ላይ እንደሆኑ መቼም ሁላችን የምናውቀው ነው፤ ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ኤምባሲ እና በእንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ በመገኘት የውሸት ዜና በቃን! ጣልቃገብነት በቃን! በማለት አቋማቸውን እያንጸባረቁ የሚገኙት። በተጨማሪም ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በሚገኙባቸው አገራት ዓደባባይ ላይ በመገኘት ‹በቃን› በማለት ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ያሉት።
ታዲያ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብሎም የኢትዮጵያ ወዳጆች ‹በቃን›› ብለው ከዓለም ጫፍ እስከ ዓለም ጫፍ ላንቃቸው እስኪላጥ ሲጮኹ እውነትን ለዓለም ሲያስተጋቡ እነዚህ መገኛኛ ብዙኃን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል።
በአጠቃይ ማህበራዊ የትስስር ገጾች የኛ ናቸው ያሉ የሚመስሉት ምዕራብያኑ፤ እነርሱ ገጾቹን አሉባልታና የሐሰት ዜና ለማስተጋባት በሚገባ እንደሚጠቀሙበት የሚታወቅ ሲሆን ብርቱ ኢትዮጵያውያን ስለ አገራቸው ያለውን እውነታ ለዓለሙ ማኅበረሰብ በተለያዩ መንገዶች ለማሳወቅ ጥረት ሲያደርጉ ግን አፈና በመፈጸም መረጃ እንዳይሰራጭ በማድረግ ተጠምደው እንደሚገኙ እያየነው ያለው ሀቅ ነው።
አፈናው ይኑር እንጂ ዛሬም ኢትዮጵያ ብዙ ወዳጅ ያሏት በመሆኗ ስለ ኢትዮጵያ እንደሚወራው አሉባልታና የውሸት ዜና ሳይሆን አገሪቱ አሁን ከገባችበት የህልውና ጦርነት በድል ልትወጣ እንደምትችልና ከፊቷም ብዙ ተስፋ የሚጠብቃት እንደሆነ ለዓለሙ ማህበረሰብ በሚገባ የሚያሳውቁ ልጆችና ወዳጆችን ማፍራት ያቻለች መሆኗን መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ነው።
በአሁን ወቅት ከአሸባሪው ቡድን ደጋፊዎች በስተቀር ብዙዎች ‹ነቃ› ብለው የምዕራብያኑን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ‹በቃ› የሚለውን ዘመቻ ዓለም እንዲያውቀው የሚደረገውን ጥረት ጨምሮ፤ በአሁን ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ በሚገኙበት የጦር ግንባር እየተገኙ ባሉ ድሎች፤ የኢትዮጵያ ፀሐይ ልትወጣ የእነርሱ ደግሞ የመጥለቂያ ሰዓቷ እየደረሰ ስለመሆኑ ማሳዎች ናቸው ቢባል ማጋነን አይደለም። እንደሚታወሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአሥር ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር በሚል ሰበብ ማዕቀብ ለመጣል በተለያየ ጊዜ ቢሰበሰብም ጠብ ያለ ነገር ማድረግ ተስኖት ‹ተሰብስቦ ያለ ስምምነት ተለያየ› ከሚል ዜና ውጭ የተለየ ነገር መፈየድ ተስኖታል።
የሀገሬ ሠው ‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል› ብሎ እንደተረተው፤ ኢትዮጵያ ጠል መገናኛ ብዙኃንም ይሁኑ ግለሰቦች ኢትዮጵያን ለመውጋት ቢያሴሩም ከሃዲነታቸው ገሀድ እየወጣ፤ እነርሱ ሲዋረዱና የሀፍረት ካባቸውን ሲከናነቡ፤ ሀገሪቱ ግን ዛሬም ከማስደነቅ ባለፈም ነፃነቷን አሳልፋ ላትሰጥ በድንቅና ለነብሳቸው በማይሳሱ ልጆቿ በመታገዝ ለአፍሪካም እንደቀደመው ታሪኳ የነጻነት ምሳሌ ልትሆን የድል ዋዜማ ላይ ሆና በመገስገስ ትገኛለች።
የምዕራብያኑን ጣልቃ ገብነት፣ የሽብርና የሐሰት ወሬን፤ አገሪቱን ሆነ አህጉሪቱን በቅኝ ለመግዛት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ‹በቃ› በማለት ሁሉም በሚችለውና በፈቀደው ግንባር ዘመቻውን በመቀላቀል ኢትየጵያ ከገባችበት ችግር እንድትወጣ በአንድነት መቆም የግድ ይላል።በማናቸውም ጊዜ እና ሁኔታ ውስጥም በአሉባልታዎች የማይናወጥ ሕዝብ እና አገር መሆናችንንም ማረጋገጥ ይገባል።
በምስጋና ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5/2014