የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በቅርቡ እንደገለጹት፤እንደ ኢህአዴግ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በነፃነት የሚሳተ ፉበት አንድ አገራዊ ፓርቲ ይመሰረታል። ከጥቂት ወራት በኋላ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ ፣ወዘተ ፓርቲ እየተባለ አይሰራም ።
ኢህአዴግ የሚመራው በልማታዊና ዴሞክራ ሲያዊ መስመር ነው።ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመምጣት ካሰበ ይህን መስመር መከተሉን ትቶ ሌላ አማራጭ ሊከተል ይችላል። ገዥው ፓርቲ ከአጋር ፓርቲዎች ጋር አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት እንዲያስችለው የጀመረው ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን ከኢህአዴግ ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃም ያመለክታል።ኢህአዴግ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው እና አቅጣጫም ያስቀመጠው በሀዋሳው 11ኛ ጉባዔው ወቅት እንደነበርም ይታወቃል። አቅጣጫው የዘጠኙንም ክልሎች ፓርቲዎች ያካተተ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችል ነው።
ውሳኔው ሁሉም ዜጎች በእኩልነትና በብቃታቸው በፓርቲው ውስጥ እንዲሳተፉ ዕድል ይፈጥራል። የኢህአዴግ ውሳኔ በአጋር ድርጅቶች ብቻ የሚገደብ እንዳልሆነና ለሌሎችም ፓርቲዎች በሩ ዝግ አለመሆኑን መረጃው ይጠቁማል። አጋር ድርጅቶቹና ኢህአዴግ የሚፈጥሩት ውህደት አባል ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ ፍላጎቱ ካለው በሩ ክፍት መሆኑ ተጠቁሟል። ይህ ሁሉም ሆኖ የሚፈጸመው ውህደት የኢህአዴግ መሰረታዊ ባህሪያትን ሳይለቅ የሚከናወን እንደሆነም ነው የተጠቆመው።
ኢህአዴግ አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዙሪያ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የፖለቲካ ምሁራን እንደተናገሩት፤ አገራዊ ፓርቲ የመመስረቱ ሀሳብ በተለይ አጋር ድርጅቶች ይሰማቸው የነበረውን የባይተዋርነት ስሜት ያስወግዳል፤ድርጅቶቹ በአገራቸው ጉዳይ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆኑበት ዕድልን ያሰፋል። አጋር ድርጅቶቹ የቱንም ያህል ብቃትና ችሎታ ቢኖራቸው የግንባሩ አባል ባለመሆናቸው ብቻ የተነፈጉትን የአገሪቱ መሪ የመሆን ዕድል ያለመልምላቸዋል። ከምንም በላይ በልዩነት ላይ ተመስርቶ የነበረው ግንኙነት እየተወገደ የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ስሜት እያደገ እንዲመጣ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ ፤ አገራዊ ፓርቲ የመመስረቱን ነገር በዋነኝነት ገዥው ፓርቲ ስላነሳው ወቅታዊ ጉዳይ ሆነ እንጂ በሀገሪቱ አገራዊ ፓርቲዎች ስለሌሉ አይደለም ይላሉ።ችግሩ ያለው አገራዊ ፓርቲዎች ደካማዎች መሆናቸው ላይ እንደሆነም ያስረዳሉ። ፓርቲዎቹ ደካማ በመሆናቸውም ጎልተው መታየት አለመቻላቸውን ይገልፃሉ። ዶክተር ሲሳይ፣ ‹‹ባለፉት 27 ዓመታት ብሄር ተኮር ወይም ቋንቋ ተኮር የፖለቲካ እና የክልል አደረጃጀት ሲሰራበት ቆይቷል።
ሁሉም ነገር በዚሁ ዙሪያ ሲሽከረከር ኖሯል፤ጎልቶ የታየው ብሄር ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀትና መዋቅር ነው።›› ሲሉ ያብራራሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ኢህአዴግ ከዚህ አንጻር አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት ፍላጎት ማሳየቱ በራሱ መልካም ነው።ለሌሎቹም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።ኢህአዴግ ግንባር ሆኖ ቆይቷል። አራቱም ብሄራዊ ድርጅቶቹ ብሄር ተኮር ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ብሄር ተኮር ድርጅቶቹ ከስመው አንድ ዓይነት የተዋሃደ ፓርቲ የሚመሰረት ከሆነ ሌሎች ብሄር ተኮር ድርጅቶችም አባል የማይሆኑበት ምክንያት አይኖርም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ አገራዊ ፓርቲው ሲመሰረት አንደኛ አጋር ድርጅቶች በቀጥታ አባል ይሆናሉ ። ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ ዜጋ የኢህአዴግ አባል መሆን አይችልም ነበር። አባል ለመሆን የአራቱ ብሄራዊ ድርጅት ሰው መሆን የግድ ያስፈልጋል። ስለዚህ ይህ የአንድ አገራዊ ፓርቲ መመስረት ማንኛውም ኢትዮጵያ ዜጋ አባል እንዲሆን ያስችላል። ከጋምቤላ ይምጣ ከኦሮሞ ፣ ከቤኒሻንጉል ይምጣ ከትግራይ አባል መሆን የሚችልበትና በማንኛውም ጊዜ ደግሞ በብቃቱና በልምዱ በፓርቲው ወስጥ የሚገባውንም ቦታ መያዝ የሚችልበት ይሆናል። እስከ አሁን ባለው አሰራር ሶማሌ ወይም ሐረሪ ፣ አፋር ወይም ጋምቤላ ‹‹የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እሆናለሁ›› የሚል ህልም አይኖረውም። የግድ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የሚችለው ከአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ውስጥ እንደሆነ ግልፅ ነው።
ዶክተር ሲሳይ እንደሚሉት፤ እስካሁን በአገሪቱ አጠቃላይ ጉዳይ ላይ የሚወስኑት አራቱ ድርጅቶች ብቻ ናቸው። አጋር ፓርቲዎች ታዛቢ ከመሆን ባሻገር በአገሪቱ ጉዳይ ላይ አይወስኑም።ተባብረውና ተደማምጠው ይሰሩ እንደነበር ቢታወቅም፣ያልመሰላቸውን ትክክል አይደለም ብለው መወሰን አይችሉም ነበር። አሁን ለአገሪቱም ሆነ ለዜጎች የሚያዋጣውናጠቃሚው የቱ ነው ከተባለ ሁሉም ክልሎች የሚሳተፉበት አገራዊ ፓርቲ ይሆናል ።ስለ አገራዊ ፓርቲ መታሰቡ ሁሉም ክልሎች በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ሁሉም ህዝቦች የኢህአዴግን ፈቃድ ሳይጠይቁ በፌዴራል መንግሥት መታቀፍ ይችላሉ ። ዶክተር ሲሳይ ለእዚህ አብነት ጠቅሰው እንዳመለከቱት፤ በአሜሪካ ባራክ ሁሴን ኦባማ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ናቸው።
ይህም ጥቁሮቹን በጣም አስድስቷል። በኢትዮጵያም ባለፉት 27 ዓመታት የታየው ሶማሌ ወይም ጋምቤላ ወይም አፋር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ተብሎ ታስቦ አያውቅም።ምክንያቱ ደግሞ ለእዚህ ስፍራ የሚጠበቁት ከአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች መካከል መሆኑ ነው። አሁን ኢህአዴግ እያሰበ ያለው ይህን አይነቱን አካሄድ ያስቀራል።
ዶክተር ሲሳይ የኢህአዴግን ሀሳብ ከዚህ በላይ ትልቅ ፋይዳ የለም ሲሉ ይገልጹታል። እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለጻ፤የውህደቱ ሀሳብ እያንዳንዱ ዜጋ በብቃቴ፣ በልምዱ እንዲሁም በትምህርቴ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር አሊያም ፕሬዚዳንት መሆን እችላለሁ›› ብሎ እንዲያስብና ለአገሩም በኃላፊነት ስሜት ተግቶ እንዲሰራ ያደርገዋል። ሌላው ብሄር ተኮር ድርጅት ሲያደርግ የነበረውና በክልል ላይ ብቻ የተወሰነው አካሄድ እንዲቀር በማድረግ ለተደራጀበት ብሄር ብቻ ሳይሆን ለአገር ጭምር ለማሰብ ዕድል የሚሰጥ ውሳኔ መሆኑን አስታውቀዋል። ዶክተር ሲሳይ ይህን ጉዳይ ሲያብራሩም ባለፉት 27 ዓመታት ህወሓት ለትግራይ በሚጠቅም ሁኔታ የትግራይ ተወላጅ ለሆኑ ሰዎች ስልጣኑንም፣ ኢኮኖሚውንም ማንኛውንምነገር ሲያደርግ እንደነበር ይጠቅሳሉ።አሁን ደግሞ አጭር ጊዜም ቢሆን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ኦሮሞዎችን ወደ ስልጣን የማምጣት እና ለኦሮሞች የሚጠቅም ሥራ የመስራት ምልክቶች እየተስተዋሉ ናቸው ሲሉ ያብራራሉ። የአንድ ፓርቲ መመስረት ይህን ዓይነቱን አሰራር ሁሉ እንደሚያስወግድ ነው ዶክተር ሲሳይ ያብራራት።
የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ስሜት እያደገ ልዩነት ላይ ተመስርቶ የነበረው ግንኙነት እየተዳከመ ወደ ውህደት እንዲመጣ እንዲሁም ሁሉም ለአገሩ ቅድሚያ እንዲሰጥ እና ከአካባቢው ባሻገር ለአገር የሚቆረቆርና አገራዊ ምርጫን የሚያስቀድም እንዲሆን አዲስ መንገድ ይፈጥራል ሲሉ ያብራራሉ ። ለሌሎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አሁን በያዙት መንገድ ሳይቀናጁ ተወዳድረው ማሸነፍ እንደማይችሉ የሚያመላክት መሆኑን በመጥቀስ፣ ፓርቲዎች ሰብሰብ እያሉና ህብረት እየፈጠሩ አንድ ፓርቲ ተጠናክሮ እንዲወጣ ማድረግ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። ሌላው የፖለቲካ ምሁር አቶ ሐሳቡ ደብዩም እስከ አሁን አጋር ድርጅቶች በአገራዊ ውሳኔ ላይ እምብዛም ተሳትፎ አለማድረጋቸውን በመግለጽ የዶክተር ሲሳይን ሃሳብ ያጠናክራሉ።
አቶ ሀሳቡ እንደሚሉት፤ገዥው ፓርቲ (ኢህአዴግ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለው ወንበር አብላጫ እንደመሆኑ የሌሎቹ ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፤ይህም ተሳትፏቸው እምብዛም መሆኑን ይጠቁማል።ኢህአዴግ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሲያሳልፍ የነበረው በራሱ አካሄድ መሆኑም እሙን ነው። የኢህአዴግ የሰሞኑ ውሳኔ ዳር ላይ የነበሩትን ወደ መሃል ለማምጣት አንድ እርምጃ ወደ ፊት የሄደ ያህል ይቆጠራል ሲሉ አቶ ሀሳቡ ይገልጻሉ።
እሳቸውም እንደሚሉት ፤ውሳኔው ወደ አገራዊ አንድነት ለመምጣትም የራሱ ሚና አለው። ወደ መሃል የመምጣት ስሜቱ ለአገራዊ አንድነቱ አሊያም ለሚደረገው ቅንጅት የተጠናከረ ማዕከላዊነትን ከመፍጠር አኳያ ሚናው የጎላ ነው። ማዕከላዊ አስተሳሰብም እንዲኖር ድርሻው ሰፊ ይሆናል። እንደ አቶ ሀሳቡ ገለጻ፤አጋር ፓርቲዎች በአብዛኛው ኢህአዴግ ያለውን ሐሳብ ሲቀበሉ ነበር። በተለይም አገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰቦችና ወሳኝ ጉዳዮችን የሚሹ ነገሮች ሲኖሩ ብዙዎቹ አጋር ድርጅቶች ለኢህአዴግ ድምፃቸውን ነፍገው አያውቁም። በፓርላማ ድምጽ አሰጣጥ ላይ እነርሱም አብረው ይወስናሉ።
አሁን ግን አስፈፃሚ በማቅረብም በኩል የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል። ‹‹ዋናው በስሜት ደረጃ ያለው ጉዳይ ነው። የእኛነት ስሜት ይፈጠራል።በሁሉም ጉዳይ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረጉ ይህ ስሜት እንዲመጣ የራሱ ሚና ይኖረዋል።›› በማለት ያብራራሉ። አቶ ሀሳቡ ፓርቲዎቹ እስከ አሁን ተሳትፎ የሚያደርጉት በክልላቸው ብቻ ተወስነው እንደነበር ጠቅሰው፣አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነው በአብዛኛው ወደ ውሳኔ የሚቀርበው ይላሉ። እነርሱ ግን በታዛቢነት ካልሆነ በስተቀር በድምፅ የሚሳተፉበት አግባብ የለም የሚል እምነት አለኝ ይላሉ። አቶ ሀሳቡ እንዳሉት፤ ውህደቱ የባለቤትነት ስሜት ይፈጥራል። ባለቤት እያንዳንዱን ውሳኔ የሚያሳልፈው በሙሉ ልብና ስሜት ነው።
ከዚህ ውጭ ቀደም ሲል ሲደረግ እንደነበረው ለይስሙላ የሚደረግ አካሄድ ትክክለኛውን ትብብር ለማድረግ መሰናክል ይፈጥራል። የዚያን ያህል ቁርጠኝነቱም ሊኖር አይችልም። ‹‹አጋሮቹ ዞሮ ዞሮ ውህደቱ የኃላፊነት ስሜትም እንዲሰማቸው ያደርጋል። የየክልላቸውን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ፖለቲካ በባለቤትነት ስሜት የሚወጡበት ይሆናል።›› ሲሉ አቶ ሀሳቡ ያመለክታሉ። ስለዚህም ‹‹አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት መታሰቡ የራሱ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፣ይህም ከጫፍ እስከ ጫፍ ማሰሪያ ነው ብዬ አስባለሁ።›› ይላሉ። በእርሳቸው አባባል፤ የተያዘው አጀንዳ አግላ ይነትን የሚያርቅና አካታች ነው።
ከዘጠኝ ክልሎች በአራቱ ብቻ ተወስኖ የቆየውን በሀገር ጉዳይ የመወሰን ሥራ ዘጠኙም ክልል እንዲሳተፉበት የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ክልሎች ዋና ዋና ውሳኔዎች ላይ ሚና እንዲኖራቸው ያስችላል። በመሆኑም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የሚያበረ ታታ ነው። ይህ አካሄድ ለአገሪቷና ለዜጎቿ ይጠቅማል። በተለይ በአገሪቱ ያለውን ትስስር ይበልጥ የሚያጎለብት በመሆኑ ፋይዳው ጉልህ ነው።አቶ ሀሳቡ ውሳኔው አጥሮችን የሚንድም ሆኖ ተሰምቷቸዋል። አቶ ሀሳቡ እንዳሉት፤አጋር ድርጅቶች መገለል ውስጥ ቆይተዋል። እንቅስቃሴያቸውም የታዛቢ ያህል የሚቆጠር ነበር።በአገሪቱ ጉዳይ ላይ የበይ ተመልካች ነበሩ ማለት ያስደፍራል።
ኢህአዴግ እስካሁን 11 ጉባዔዎችን አካሂዷል።ሁሉንም ጉባዔዎች ሲያካሂድ አጋር ፓርቲዎቹ በታዛቢነት እንጂ በውሳኔ ሰጪነትአልተሳተፉም።በጉባዔዎቹ የአገሪቱን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ጉዳዮች መተላለፋቸው እና በርካታ አቅጣጫዎች መቀመጣቸው ይታወቃል። ከእነዚህ አገራዊ ጉዳዮች ውሳኔ ሰጪነት ውጪ መሆን በራሱ የራሱ የሚፈጥርባቸው ባይተዋርነት አለ። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ በርካታ ክፍተቶች ነበሩ ማለትም ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ ያሉ የአጠቃቀም ሁኔታዎች የተለያዩ እንዲሆኑ አድርጓል።
ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ አብዛኛውን መቀመጫ ስለያዘ ሌሎችን እያስገደደ ያስፈጽማል ለማለት ያስደፍራል የሚሉት አቶ ሀሳቡ፣ውሳኔው ከዳር እስከ ዳር አንድ አይነት አስተሳሰብ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር እና ፋይዳው ለአገሪቱም ሰላም ለህዝቦችም አንድነት ከፍ ያለ ነው ይላሉ። የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ሲሳይ ውህደቱ ወይም አንድ ሀገራዊ ፓርቲ የመመስረቱ ሥራ እንዴት ይፈጸማል በሚለው ላይም ሀሳባቸውን ይሰጣሉ። ኢህአዴግ ውህደት የሚያደርገው ከአጋር ፓርቲዎች ጋር ብቻ ላይሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።
በቀጣይ በሚኖረው የኢህአዴግ አካሄድ ግንባሩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለምን ትቶ ሶሻል ዴሞክራሲን ወይም ሊበራል ዴሞክራሲን መሰረት አድርጎ መቀጠል የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር በመጠቆም፣አጋር ፓርቲዎች እስከ አሁን አብዮታዊ ዴሞክራሲን ስለማያሟሉ የግንባሩ አባል መሆን እንዳልቻሉ ይገልጻሉ። ዶክተር ሲሳይ እንደሚሉት፤አሁን ኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎችንም ‹‹የእኛ አባል ትሆናላችሁ›› እያለ መሆኑ ይበል ያሰኛል።
ይህም በሌላ አነጋገር ኢህአዴግ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲን ትቼያለሁ›› እያለ ስለመሆኑ ያመላክታል። ኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከተወ ሶሻል አሊያም ሊበራል ዴሞክራሲን ሊመርጥ ይችላል፤ ምርጫው ከእነዚህ አንዱን ከሆነ በሶሻልና በሊበራ ዴሞክራሲው ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወዲያውኑ ወዳጅ ይሆናል የሚል እምነት ያላቸው ዶክተር ሲሳይ፣ለዚህ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡትም ዓላማቸውና የሚከተሉት ሁሉ አንድ አይነት መሆኑን ነው። ስለዚህ አጋር ድርጅቶችም አሁን ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚባሉትም ከኢህአዴግ ጋር አብረው አንድ አገራዊ ፓርቲ ለማቋቋም ወይም ውህደት ለመፍጠር ይችላሉና ወደዚህ አቅጣጫ ሊመጡ የሚችሉ ወገኖች ይኖራሉ ብሎ መናገር ይቻላል። ከኢህአዴግ በተጓዳኝ ሌሎች ፓርቲዎችም እንዲሁ በአመለካከት ዙሪያ ተሰባስበው አንድ ጠንካራ ፓርቲ ሊመሰርቱ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚኖርም ዶክተር ሲሳይ ይጠቁማሉ።
ሊበራል ዴሞክራሲን ወይም ሶሻል ዴሞክራሲን የሚከ ተልና ራሱን የቻለ አገራዊ ጠንካራ ፓርቲ እንዲፈጠር መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንም ይገልጻሉ። በቀጣይ ሁሉም የኢህአዴግ አባላት አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይከተላሉ ማለት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፣ህወሓትን ለአብነት በመጥቀስም አሁንም አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይዤ እቀጥላለሁ እያለ ነው ይላሉ።
እንደ ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ፤ ህወሃት አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይዞ የሚቀጥል ከሆነ ከኢህአዴግ አካሄድ ይወጣል ማለት ነው። ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች አብዮታዊ ዴሞክራሲን ትተናል ካሉ ልዩነት ይፈጠራል፤ የአብሮነትም ጉዞ ያበቃለታል። የትግራይን ክልል የሚመራው ህዋሃት ተፎካካሪ ፓርቲ ይሆናል ማለት ነው። ‹‹ከአዴፓ ይሁን ወይም ከደኢህዴን ወይ ደግሞ ከኦዴፓ አብዮታዊ ዴሞክራሲን መንገድ እከተላለሁ የሚሉ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ።
ብሄራዊ ድርጅት ሆነን መቀጠል እንፈልጋለን የሚሉ ቡድኖችም ሊቀጥሉ ይችላሉ። ስለዚህ ለሁሉም ክፍት ነው ማለት ነው።›› ሲሉ ያብራራሉ። ዶክተር ሲሳይ በአንድ ፓርቲ ምስረታ ላይ ኢህአዴግ እያካሄደ ያለው ጥናት ውጤት ቀርቦ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ደረጃ የጸደቀ ጉዳይ እንደሌለም ይናገራሉ። ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ የቸኮሉ ይመስለኛል። ፍላጎታቸውን ነው የገለፁት፤እንደ እኔ አመለካከት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደተግባር ይቀየራል የሚል አመለካከት የለኝም።››ሲሉም ያመለክታሉ።
ለዚህ ምክንያቴ ብለው የሚጠቅሱትም ‹‹ህወሓት በራሱ ይህን ጉዳይ አይቀበለውም። ሌሎቹም አዴፓና ኦዴፓም ቢሆኑ እንዲሁም ደኢህዴን በተሟላ መልኩ አምነውበት እየተቀበሉት ነው ወይ የሚለውን ሲወሰን ነው ማረጋገጥ የሚቻለው። ስለዚህ በጉባዔ ወይም በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ውሳኔ ያላገኘን ነገር መሪው ስለፈለገ ብቻ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይሆናል ማለት አይደለም።›› ሲሉ የጉዳዩን ቶሎ አለማለቅ ያመለክታሉ። እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለጻ፤ ለምርጫ ዝግጅት ማድረጊያ ጊዜ አጭር ነው።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህ ውህደት ይፈጠራል ወይ የሚለው ጉዳይ በራሱ አንድ ችግር ሊሆን ይችላል። እንዲያም ሆኖ በሶሻል ፣ ሊበራል ዴሞክራሲ ወይም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብለው ስለሚሰባሰቡ አሁን ኢህአዴጋዊ የሆኑ ድርጅቶች የሚመርጡት ርዕዮተ ዓለም የፖለቲካ ፕሮግራም ይወስነዋል። ‹‹ቀደም ሲል ልገልፅ እንደሞከርኩት አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንደማይቀጥሉ እየነገሩን ነው። ከመካከላቸው ደግሞ ይህን በዚያው የሚቀጥሉ እንዳሉም ግንዛቤው አለ።›› የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፣ በእርግጥ አዴፓና ኦዴፓ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንደማይጠቅም በማወቅ ወደ ውሳኔ መጥተዋል።›› ይላሉ።
‹‹ስለዚህ ይህን መሰረት አድርጎ በቀጣይ ምን ሊከተሉ ይችላሉ የሚለውን ለማየት ሲሞክር በእሳቸው እምነት ፓርቲዎቹ ሶሻል ዴሞክራሲን ሊመርጡ ይችላሉ። እነዚህ ፓርቲዎች ሶሻል ዴሞክራሲን በመምረጥ እና ተፎካካሪ በመሆን ከኢህአዴግ ጋር መደራደራቸው አይቀርም ሲሉም ዶክተር ሲሳይ ያብራራሉ። ‹‹ውህደቱ ከብዙ አቅጣጫ ሊታይ ይችላል። ተመሳሳይ አመለካከት በተመሳሳይ ሁኔታ መዋሃድ ቀላል በመሆኑ ይህን አግባብ የሚከተሉ ይኖራሉ፤ለዚህም ምክንያቴ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም እያራመዱ የተለያዩ ድርጅቶች ሆነው አይቀጥሉም›› ብለዋል። የአገራዊ ፓርቲ መመስረት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው።
መንግስት ፓርቲዎች በሚያግባባቸው አመለካከት ዙሪያ እየተሰባሰቡ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን መስራት እንዳለባቸው ሲያስገነዝብ የነበረው ይበልጥ ተግባራዊ እንዲሆን የራሱን ሚና ይጫወታል። ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን አቀራረብ፣ መጠቃቀምና የቡድን አይነት ፍላጎትን ያስቀራል። በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት እንዲጎላ የሚያደርግ ሲሆን፣በአገሪቱ ሁሉም አካባቢ በእኩል የሚያይ አመራር እንዲኖር ያደርጋል።ከሁሉም በላይ ለሰላምም የራሱን በጎ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ በጥቅሉ ከአግላይነት ወደ አካታችነት የሚመራ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
በአስቴር ኤልያስ