ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ የቦርድ አባልና ምክትል ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ከለውጡ በኋላ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ የስኳር ኮርፖሬሽንና የቀድሞው ሜቴክ ተቋማትን በቦርድ አባልነትና በሰብሳቢነት በማገልገል ድርጅቶቹ ብዙ ለውጥ እንዲያመጡ ያስቻሉ ናቸው፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ተተኪ አርበኛና የምክር ቤቱ አባል በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ተመራማሪና መምህር ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ እንድታመጣ መሠረት ከጣሉ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ አሁንም ለአገራቸው ይሆናል ያሉትን እየሠሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር ዳንኤል ዛሬ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያላቸውን ሃሳብ እንዲያጋሩን አነጋግረናቸው እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሚገኙበት የአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ ከወቅቱ ጋር በተያያዘ ምን ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- የምሁራን መማክርቱ አገራዊ ተልዕኮ ያለውና ስለአገር የሚገደው ነው፡፡ ወሰን ተኮር አይደለም፡፡ በየትኛውም ክልል ላይ ችግር ከተፈጠረ ቀድሞ ይደርሳል፡፡ ከወንድሞቻችን ጋር በመተባበር ለችግሮች መፍትሄ ይሰጣል፡፡ እንዲህ አይነት መማክርት ጉባኤዎች የምሁርነትን ትርጓሜ መያዝ አለባቸው ብሎ የሚሠራ ነው፡፡
ምሁር መሆን ማለት አገርን መውደድና ለሰው ልጅ ሁሉ ወሰን ሳይኖር አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ ዝቅ ብሎ በመሥራት የሚያምንና ራሱን የማይኮፍስ ነው፡፡ ቆሻሻ ካየ ጎንበስ ብሎ የሚያነሳ፤ ከሚመስሉት ጋር ብቻ ሳይሆን ከማይመስሉት ጋርም በመሆን እንዲመለሱ የሚታትር ነው፡፡ ምርጫው ሰው እንጂ ብሔር አይደለም፡፡
ሃይማኖት አይልም፡፡ ከዚህ ውጪ ከሆነ ዶክተርም ይሁን ሌሎች ማዕረጎች ያለው ባለዲግሪ እንጂ ምሁር ሊባል አይችልም፡፡ እናም የምሁራን መማክርት ጉባኤ ይህንን በያዘ መልኩ ከሞላ ጎደል እየሠራ ነው፡፡ ቋንቋ መግባቢያ እንጂ ማንነትን መለኪያ ባለመሆኑ፤ መማክርት ጉባኤው በቋንቋ አያምንም፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ክልልና ብሔር ሳይወስነው ይሰራል፡፡ ምሁርነቱም ኦሮምያ፣ አማራ ወይም ሌላ ክልል በተወለደ ሳይሆን ኢትዮጵያን በማገልገል የተጠበበ ነው፡፡
ሌሎች የመማክርት ጉባኤዎችም በየክልሉ ተመሥርተው ይህንን ዓላማ አድርገው መሥራት እንዲችሉ እመክራለሁ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ኢትዮጵያዊነታችን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ የምንጋራቸው ባህሪያትና አኗኗር አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በእርስዎ እይታ እንዴት ይገልጹታል ፤ በተለይም የውጭ ጫናውንና የሕወሓትን እንቅስቃሴን በሚመለከት ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ደባ በሕወሓት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊትም የነበረ ነው፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለማሸነፍ የቀረጸው ስትራቴጂ አካል ነው፡፡ ጣሊያን ክልሎችን በመከፋፈል ለማስተዳደር ሞክሯል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዳትታሰብ ለማድረግ ተግቷል፡፡
ይሁን እንጂ እንደእነ ራስ አበበ አረጋይ አይነት የአገር ጀግኖች በ1931 ዓ.ም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበርን አቋቁመው ኢትዮጵያ ጥንታዊት መሆኗን ለተተኪው አስተምረው በተራዘመው ጦርነት ውስጥ ብርቱ ትግል በማድረግ ነገሮችን ቀይረዋል፡፡ ማሕበረሰቡም ወደ አንድነት ጎዳናው ተመልሷል፡፡ አሁን ሕወሓት እያደረገ ያለው የጣሊያኖችን ሃሳብ ዳግም ማስፈፀም ነው፡፡
እርሱ እነርሱ የሚፈልጉትን ነገር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁንም ያንኑ እያደረገ ይገኛል፡፡ የብሔር ክፍፍሉ ውጤት በተግባር እንዲውል ብዙ የለፋ ነው፡፡ መሠረቱ ግን ጣሊያኖች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የመጀመሪያው ጣልያን ሲወድቅ ሁለተኛው ጣሊያን (ሕወሓት) በብሔር ውስጥ ብቻ መቀመጥን አስተምሯል፡፡
አገርን አስቦ መሥራትን ጨፍልቋል፡፡ እርሱ ጠቦ አገራችን በራሱ እንደምትጠበን ማመንና ወደ ተግባር መግባት እንዳንችል አድርጎናል፡፡ አፍሪካ ጭምር ለእኛ ትንሽ እንደሆነች እንዳናይም ገድቦናል፡፡ ምክንያቱም እኛ የዓለምን ምህዋር መዘወር የምንችል ሆነን ሳለን ዓይናችንን በብሔር ውስጥ ዘፍቆታል፡፡ በኢትዮጵያዊነታችን በሁሉም አገር ላይ ጎልተን የምንታይና አገራችንን ገናና እንደሆነች የምናስመሰክር እንዳንሆን ጨፍኖናል፡፡
በእኛ ዝና አገራችን እንዳትጠራ፤ ሁሉም አፍሪካውያን የሚወዷትና ምሳሌ የሚያደርጓት ኢትዮጵያ እንዳትሆን ሞክረዋል፡፡ ሕወሓት ድንቁርናን ለማስፋፋት የተጠቀመበት ዋናው መንገድ የትምህርት ሥርዓቱን ማበላሸት ነው፡፡
ዘመኑና የማሕበረሰቡ የአመለካከት ልዕልና ቢቀየርም የትምህርት ሥርዓቱ ዘመኑን ተከትሎ እንዳይቀየር አድርጎታል፡፡ 12ኛ ክፍል ያልተሳካለትና አቅም የሌለው ተማሪ መምህር እንዲሆን መፈቀድ ሲጀምርም ይህ ነገር በሥነልቦና ጭምር እየወደቅን እንድንሄድ አድርጎናል፡፡
በተጓዳኝ ወጣቱ በአደንዛዥ ዕጽ እንዲታወርና ስለ አገሩ ምንም እንዳያስብ ሆኗል። በተለይም ከደርግ ጊዜ ጀምሮ የነበረው ሁኔታ ብዙ ነገሮቻችንን እንዳበላሸብን ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚባል ነገር ጠፍቷል። መምህራን ሳይቀሩ መዋረድ ጀምረዋል፡፡ በዚህም ብቁ ተማሪና ብቁ አስተማሪ ጠፍቷል፡፡ ሰውን የሚያስክብረው ፖለቲከኛ መሆን ብቻ እየሆነ ሄደ፡፡
ለዚያውም ደጋፊ ፖለቲከኛ፡፡ ሰው የሚከበረው በወሬ አቀባይነቱ እንጂ በሥራው መሆኑም ቆሟል፡፡ ሌብነት በአደባባይ የተፋፋመው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ምክንያቱም አትያዝ እንጂ ስረቅ እስከመባል በአደባባይ የተለፈፈበት ነበር፡፡
ቀደም ሲል አይደለም ዋነኛ ሌባው የሌባው ልጅም ይቀጣል፡፡ እንዴት ከተባለ የእከሌ አባት ገንዘብ ጎደለበት ተብለው ከሰሙ ከጓደኞቹ ይገለላል፡፡ በዚህ ዘመን ግን በፊት ለፊት መስረቅም ይበረታታል፡፡ ስንት ትከፍለኛለህም የፊት ለፊት ጥያቄ ነው፡፡ አገርን ከመዝረፍ የበለጠ ምንም አይነት ሌብነት የለምና ሕወሓት ሕዝብን መስረቅ ማለማመዱና አሁንም አገርን ለማጥፋት መነሳቱ አያስገርምም፡፡ ሕወሓት በተቀበለው የውጭ ተልዕኮ የሚሰራ ነው፡፡
በዚህም የፖለቲካ ሴረኝነቱ የበዛ ዋጋ እያስከፈለን ቀጥሏል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ መነሳሳት የተጀመረው ከዚህ የተነሳ ነው። ሕወሓት ወደ ሥልጣንም ሲመጣ ደርግን የጣለው በሴራ እንጂ በውጊያ አይደለም፡፡ አገርን መውደድ በምዕራባውያኑ ዘንድ ስለማይወደድ እርሱም አላደረገውም፡፡
የአገር ጠበቃ የነበሩ የጦር መሪዎችን በተለያየ መንገድ ያስወጋውም ለዚህ ነው፡፡ የባንዳነት ሥራውን ሊሰሩለት የሚችሉ ሰዎችንም አስቀምጦ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ በምዕራባውያኑ ሞገስና መወደድን አስገኝቶለታል፡፡ ለሕወሓት አገር ከሥልጣንና ጥቅም በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ በዚህም ብዙ ነገሮች እንዲያልፉን ሆነናል፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነቱም የመጣው የቀደመ እድላቸውን በመነጠቃቸው የተነሳ ነው፡፡ ጫናውም ቢሆን የሚፈልጉትን መንግሥት መመስረትን አልመው ነው፡፡ ይህ ግን የኢትዮጵያን ማንነት አለመረዳት ይመስለኛል፡፡
የአገሩ ሕዝብ እንጂ የሌላ አገር ጣልቃ ገብቶ መንግሥትን አይመርጥም፤ መርጦም አያውቅም፡፡ አሁንም ኢትዮጵያውያን ይህንን ያስቀጥላሉና ምንም አይነት ጫና ቢያመጡ ውጤቱ ኪሳራ ነው ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት በተለይ በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ የደቀነው አደጋ ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ሁለቱን ክልሎች በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በሥነልቦናና በማሕበራዊ ሕይወቱ ጭምር ጎድቷል፡፡ ለምን ሁለቱን መረጠ? ቡድኑ በዚህ ልክ በሕዝብ ላይ አደጋ የደቀነው ከምን መነሻ ነው?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- ይህንን ሃሳብ የምመልሰው ከማየውና ከማነበው በመነሳት ነው፡፡ ሁለቱ ክልሎች የተመረጡበት ምክንያት በመጀመሪያ የትግራይ ክልል አዋሳኝ በመሆናቸው፣ ሁለተኛም የተለየ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያላቸው ስለሆኑ ነው፡፡
የአፋር እንኳን ሕዝቡ ግመሎቻቸው የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቃሉ ይባል የለ። የሁለቱም ክልል ሕዝቦች ልገንጠልም ብለው አያውቁም ያውስ ከማን ይገነጠላሉ? ትግራይን ጨምሮ ይህንን ጥያቄ ያነሱ ነበሩ፡፡ አልተሳካም እንጂ፡፡ እናም ሞቴም ሕይወቴም ኢትዮጵያ ነች ማለታቸው በምዕራባውያኑ ጥርስ ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡ ሕወሓት ደግሞ የእነርሱ ተላላኪ በመሆኑ ተልዕኮዋቸውን እየፈጸመባቸው ይገኛል፡፡ ሌላው ምክንያታቸው ይህንን ጦርነት ለማሸነፍ በር ስለሚያስፈልጋቸው የሚያደርጉት ነው፡፡ ጅቡቲ አለያም ሱዳን ክፍት ማድረግ እስካልቻሉ ድረስ የፈልጉትን ቡድኑ በዚህ ልክ በሕዝብ ላይ አደጋ የደቀነው ከምን መነሻ ነው? ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- ይህንን ሃሳብ የምመልሰው ከማየውና ከማነበው በመነሳት ነው፡፡ ሁለቱ ክልሎች የተመረጡበት ምክንያት በመጀመሪያ የትግራይ ክልል አዋሳኝ በመሆናቸው፣ ሁለተኛም የተለየ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያላቸው ስለሆኑ ነው፡፡
የአፋር እንኳን ሕዝቡ ግመሎቻቸው የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቃሉ ይባል የለ። የሁለቱም ክልል ሕዝቦች ልገንጠልም ብለው አያውቁም ያውስ ከማን ይገነጠላሉ? ትግራይን ጨምሮ ይህንን ጥያቄ ያነሱ ነበሩ፡፡ አልተሳካም እንጂ፡፡ እናም ሞቴም ሕይወቴም ኢትዮጵያ ነች ማለታቸው በምዕራባውያኑ ጥርስ ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡ ሕወሓት ደግሞ የእነርሱ ተላላኪ በመሆኑ ተልዕኮዋቸውን እየፈጸመባቸው ይገኛል፡፡
ሌላው ምክንያታቸው ይህንን ጦርነት ለማሸነፍ በር ስለሚያስፈልጋቸው የሚያደርጉት ነው፡፡ ጅቡቲ አለያም ሱዳን ክፍት ማድረግ እስካልቻሉ ድረስ የፈልጉትን
አያገኙም። ክልሎቹ ደግሞ አይሆንም ብለው ዘግተውባቸው ድባቅ እየመቷቸው ነው፡፡ ስለዚህም እስከመጨረሻው ሊታገሏቸው ቆርጠዋል፡፡ ዋና ዓላማቸው በጅቡቲ በኩል ገቢ ወጪውን በመዝጋት አዲስ አበባንና ሕዝቦቿን እንዲሁም መንግሥትን ማስጨነቅ ሲሆን፤ በሁመራ (ሱዳን) በኩል ደግሞ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና የውጭ ኃይል በማስገባት ኢትዮጵያን ማተራመስ ነው፡፡ ሆኖም በመከላከያ ሠራዊታችን፣ በልዩ ኃይሉ፣ ፋኖ እንዲሁም በሁለቱ ክልል ሕዝቦች አማካኝነት ሕወሓት ባሰበው ልክ አልሆነለትም፡፡ ፍላጎቱም መክኗል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ለማዳከም የሚያደርጉት ዘመቻ ምንን ታሳቢ ያደረገ ነው፤ የቡድኑ ድርጊት ምንን ያሳያል?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- ማሸነፍንና መልሶ ሥልጣንን መያዝን ያለመ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ እንደነበሩ የሚያገኙትን ጥቅምም መፈለግን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ ነገሩ ህልም ሆነ እንጂ፡፡ ለእነርሱ አገርም ሆነች ዜጋው ምናቸውም አይደለም። ሌላው ቀርቶ የሚተኩሷቸው ጥይቶች እያንዳንዷ ብዙ ዋጋ ያለው ቢሆንም ከአገር የበዘበዘውና ከምዕራባውያኑ የሚደጎመው ስለሆነ ምኑም አይደለም።
በተቃራኒው ለምላሹ የሚጠፋው ሕይወትና ንብረት አያሳስበውም፡፡ ምክንያቱም እርሱ አገራዊ ስሜት የለውም። ስለዚህም ጦርነቱ እንዲራዘምና አገራችን በኢኮኖሚ እንድትዳሽቅ ይሠራል፡፡ ሌላው ኢኮኖሚውን እንዲደቅ ያደረገው ነገር ሰዎችን በማፈናቀል ሲሆን፤ የአንድን ገበሬ በሬዎች በመግደል ብቻ ብዙ ነገሮችን ያዛባል፡፡
በጊዜው ማረስ አይችልም፤ አያመርትም፡፡ በዚህም ለሚቀጥለው ዓመት ገበሬው በችግር ውስጥ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ ሌላ ቦታ ተፈናቅሎ በኑሮ ውድነት ሌላውም እንዲሰቃይ ያደርጋል፡፡ ተፈናቃዩን ለመመገብ ሲባልም መንግሥት ሀብቱን እንዲያዞርና ካዝናው እንዲራቆትም ይሆናል፡፡ በኑሮ ውድነቱ መናርና በጊዜው ድጋፉ አለመድረሱም ሌላው ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያማርር የሚያደርግ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በእርስ በመረዳዳት እና አርቆ በማሰብ እያለፈው ይገኛል፡፡
አሁንም ቢሆን ሥራቸው የቀደመና አገር የማፍረስ ተልኮን ያነገበ በመሆኑ ፈጥነን ካልጨረስነው ዋጋው ብዙ ስለሆነ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ይህንን አስቦ መንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡ ሌላው ኢኮኖሚውን የሚያደቀው ነገር መሰረተ ልማቶችን መውደማቸው ሲሆን አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማውደምም አገልግሎቱን ዳግም ለማስጀመር መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያወጣ ዜጋው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ወራትን በጭንቀትና በችግር ውስጥ እንዲያልፍ ያደርጋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ ቡድኑ ተላላኪነቱን በትክክል እየፈጸመና አገርን ለማፍረስ በትጋት እየሠራ መሆኑን ነው፡፡
ዓላማው ሥልጣን መያዝ ቢሆንም ሰይጣናዊ ድርጊቱ ግን ከዓላማው አስወጥቶታል፡፡ ምክንያቱም ያፈረሳትን አገር እንዴት ሊመራባት ይችላል? በውጭ አገራት መሪነት ዝም ብሎ የሚጓዝና መድረሻውን የማያውቅ መንገደኛም ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት በማይካድራ፣ በንፋስ መውጫ፣ በጭና፣ ወዘተ በደረሰባቸው ስፍራዎች ሁሉ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ሲፈፅም ቆይቷል፤ ቡድኑ እንዲህ አይነት ጭፍጨፋ እያካሄደ የዓለም ማሕበረሰብ ዝምታን መምረጡ ለምንድነው?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- የትግራይ ክልል ከሌላው አካባቢ ብዙ የሚለየው ነገር አለ፡፡ የመስጊዶች፣ ገዳማትና አድባራት መገኛና አማኞች ያሉበት ነው፡፡ ሕዝቡ በዚህ ሥብዕና ውስጥ ሆኖ ሳለ ቡድኑ ግን በሠራው ሰይጣናዊ ሥራ ይህንን ሁሉ ባህልና እምነቱን እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ ይህ ደግሞ የሕወሓት መሪዎች በክፉ መንፈስ ስለታወሩ የማይረባ አዕምሮ ሰፍኖባቸዋል፡፡ ምዕራባውያን ገና ከጅምሩ ሰይጣናዊ የሆነ ስልታዊ አካሄድን ይጠቀማሉ፡፡ እ.ኤ.አ 1884 ላይ በጊዜው የነበሩ የአውሮፓ መሪዎች በርሊን ላይ ቁጭ ብለው መላው አፍሪካን ካርታዋን በጠረጴዛ ላይ ዘርግተው በማስመሪያ ተከፋፍለዋል።
ለጣሊያን ምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያና ሶማሊያ ተመደበላት፡፡ ግን እንደሌሎቹ በቀላሉ አልተቀበለቻቸውምና በዓድዋ ድል ተመቱ፡፡ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ጥቁር ማሸነፍ እንደሚችል፣ ነጭ ደግሞ በመሳሪያ ብልጫ ቢኖረውም እንደሚረታ አሳዩ። ይህ ደግሞ ሌላው አፍሪካ እንዲነሳና ነጻነቱን እንዲያስከብር አደረገ። የኢትዮጵያ ፈርጥነት በዓለም አደባባይም ተንቦገቦገ። በዚህም ነጮች ኢትዮጵያን ወደመፍራቱ ገቡ።
ከዚህ በተጓዳኝም ጥርስ ነከሱባት፡፡ በዓድዋ መስመር አሁንም ሌላውን አፍሪካ እንዳታስተባብርባቸው ይፈራሉ፡፡ ምክንያቱም ይህም አሁን የሚደረገው ጦርነት የዳግም ዓድዋ ጉዞ ነው። ለዚህ መለያየት አንዱ የስኬታቸው ምንጭ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ ሆነዋል። በሚዲያዎቻቸው ጭምር የአገራችንን ስም ወደማጠልሸቱ ገብተዋል፡፡ እንደ ሕወሓት አይነት ቡድኖችን የተጠቀማቸው ምስጢርም ይህ ነው፡፡ ባንዳ የሆነ ቡድን ለእነርሱ ስኬት አስተማማኝ ክንድ ነው። እርሱ ሲያጠፋ ዝም የሚሉትና የሚደግፉትም ለዚህ ነው፡፡ ሕወሓትን ሲያጠምዱት መጀመሪያ እናንተ ልዩ ናችሁ፣ ተበድላችኋል፣ እንረዳችኋለን ወዘተ በማለት ነበር፡፡ ከዚያ እየሰበሰቡ ማሰልጠንና ኢትዮጵያ ጠል የሚሆኑበትን መስመር ዘረጉ፡፡ በሰለጠኑትና በተሰጣቸው ተልዕኮ መሠረትም እየሰሩ መሆኑን ተከታተሉ፡፡
27 ዓመታትም ያለፉት በዚህ መልኩ ነው፡፡ በሕወሓት ሎሌነት እኛ ጀግና የምንላቸውን ሰዎች ጥላሸት ቀብተዋል፤ ጀግና እንዳይኖረንም ሆነናል፡፡ እነርሱን ያሸማቀቁትን መሪዎች የብሔር ተጋፊ ናቸው በሚል ጥላቻ እንዲሰበክባቸውም አድርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ በብሔረሰብ መካከል ጭምር ቅራኔን ፈጥሯል፡፡ ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ምዕራባውያን በሕወሓት አማካኝነት ኢትዮጵያን ምሳሌ እንዳትሆን የሚተጉ ናቸው። ለአፍሪካ ምሳሌ እንዳትሆን በብርቱ ይፈልጋሉ፡፡
ሌሎች የአፍሪካ አገራት ያለምንም ማንገራገር የከርሰምድር ሀብታቸውን አሳልፈው የሚያስረክቡበትን መስመር ለመዘርጋት ደግሞ ቅድሚያ ኢትዮጵያን ማሸማቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም አገራችን በብዙ መልኩ የአፍሪካ ፈርጥ ነች፡፡ በጥቂቱም ቢሆን ፈረንጆቹን ማክበርና ከፍ ከፍ ማድረግ የተጀመረውም ለዚህ ነው፡፡ ይህንን ግን ያደረጉት ራሳቸው ሳይሆኑ በእኛው ባንዳዎች ተጠቅመው ነው፡፡ እነርሱ ቢያደርጉት መጡብን በሚል እንደምንነሳባቸውና አሁንም ድል እንደምናደርጋቸው ያውቃሉ፡፡
በተለይም አንድነታችን የቀድሞውን ቦታ ያዘ ማለት የሚገዙት አገር አይኖራቸውም፡፡ እናም እኛ ራሳችን በእኛ ላይ እንድንነሳ ሕወሓትን ላኩብን፡፡ ባንዳዎችንም ሰብስበው በአገራችን ላይ አዘመቷቸው፡፡ ዝምታቸውም የእኛ መስለው የራሳቸው ተላላኪ ስለሆኑ የመጣ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እንቢ ማለትና ማደግ ወይም ደግሞ እንደ ሕወሓት አይነት ባንዳዎች መጥፋት ነገ እንቢ የሚላቸውን ያበረክትባቸዋል፡፡
የራሱን እድል በራሱ መወሰን የሚችል ዜጋና አገርም ይፈጠርና ብቻቸውን ያስቀራቸዋል፤ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንን በማስተባበርና በጋራ በማደግ ኃያልነታቸውም ይቀማል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ያለንበት ጦርነት የዓድዋ በመሆኑ እንዳይደገም የተቻላቸውን ወደማድረጉ ገብተዋል፡፡ ሕወሓትና መሰል አገር አፍራሽ ኃይሎች የተዛመዱት ከዚህ ስሜታቸው በመነጨ ዓላማ ነው፡፡
ሕወሓትና መሰሎቹ አሁን ወደሥልጣን ለመመለስ ብቻ ሳይሆን ለመኖርም የሚረዳቸው አካልን ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደምዕራባውያኑ ያሉ አገራት ጠቃሚ ናቸው፡፡ እናም ትንሽነት የሚሰማውን አካል በማጀገንና በመደገፍ ከፍ እንዲል ይሠራሉ፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ አደጋ የደቀነው ሕወሓት ብቻ ሳይሆን የውጭ ኃይሎችም ጭምር ተቀናጅተው እንደሆነ ይታወቃል፤ ከዚህ አንጻር የውጭ ኃይሎች በተለይ አሜሪካና በእሷ የሚመሩት ጥቂት ምዕራባውያን በዚህ ልክ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የተነሱበት ምክንያት ምንድነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- እንደእኔ እምነት ሦስት ምክንያቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ከላይ የጠቀስነው በቀደመው ቁርሿቸው አሁንም ዳግመኛ ዓድዋ ይፈጠራል ብለው ይሰጋሉ፡፡ በዚህ ደግሞ ብዙ ነገራቸውን እንደሚያጡ ያምናሉ፡፡ መነሻ ምክንያታቸው ያስቀመጡት መንግሥት ድባቅ መመታቱና የሕዝቡ አንድነት መታየት ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ በር ናት፡፡ በዚህም ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የእድገት መሸጋገሪያም ትሆናለች፡፡ የአፍሪካ አገራት እርስ በእርስ ተሳስረው ለመሥራት እርሷን መያዝ አዋጪነቱ የበዛም ነውና እንደ ድፍረቱና ጀግንነቱ ከተጓዘ ያሰበው ላይ ይደርሳል ብለው ይሰጋሉ፡፡ በዚያ ላይ በተፈጥሮም ሆነ በሰው አቅም የተሻለች አገር ናት፡፡ ስለዚህም ተባብረው ለመሥራትና ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ዓይን ነች፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት አገራት አንዷ ናት። ለምሳሌ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ፈጣን መንገድ የላቸውም፡፡
ኢትዮጵያ ግን ከቻይና ጋር በመሥራቷ የፍጥነት መንገድም ሆነ ሌሎች ኢንዱስትሪዎችን አልምታለች። በተለይም ቻይና በዚህ መልኩ እየሰራች የምትቀጥል ከሆነ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ከቻይና ጋር አብረን እንሥራ የሚለውን ይደግፋሉ፡፡
ከቻይና ውጪ እንዳያዩም ይሆናሉ። በእርግጥ እንደ አሜሪካ አይነቶች ብዙ ዓመታት ግንኙነት ከእኛ ጋር ነበራቸው፡፡ ነገር ግን በምንፈልገው ልክና ዘላቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ አልሰሩልንም፡፡ ከቻይና ጋር ትብብር ከጀመርን ወዲህ ግን በአገራችን ላይ ያለውን ለውጥ ዓይናችን ይመሰክራል፡፡ ስለዚህም እንደ አገር ወዳጅ መስሎ ሊያጠፋን የሚሞክረውን ልንቀበለው አንችልም። ወዳጅነቱን በሥራና በመለወጥ ውስጥ የሚያኖረውን ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይደግፈዋል፡፡ ይህ መሆኑ ግን ለአንዳንድ ምዕራባውያን አልተዋጠላቸውም፡፡ ለዚህም ነው ጫናቸውን እያበረቱ ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ተስማምታ በዙሪያዋ ያሉት ወደቦችም መጠቀም ከጀመረች በቅርበት ሁሉም ያላቸውን ሀብት መጠቃቀምና እንደ አንድ አፍሪካዊ የፈለጋቸውን ማድረግ እንዲችሉ መፍትሄ ስለምትሰጥ ይህ የማስተባበር አቅሟ ያስፈራቸዋል፡፡ በዚህም ከጎረቤት አገራት ጋር ሳይቀር እንዳትስማማ ያደርጋሉ፡፡ ሌላው የልቦና ውቅራችን ከነጮቹ የምንስተካከል ነን የሚለው እይታችን መሠረቱ ቅኝ ያለመገዛታችን ምስጢር አሁንም ያስፈራቸዋል፡፡
አሁንም በዚህ ወኔ ውስጥ ሆነን ማንም እኔን ሊነካኝ አይችልም፣ በራሴ አቅም አለኝ፣ ራሴን የማስተዳድረው ሌላ በሾመልኝ መንግሥት ሳይሆን ራሴ በመረጥቁት ነው ማለታችንም ጫናውን ለመፍጠር መነሻ ሆኗቸዋል፡፡ ምክንያቱም እንደሚፈልጉት የምትሆንላቸው አገር አያገኙም፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጅቡቲ ሄደው እርቅ ማውረዳቸው፤ ኤርትራውያንንም እንዲሁ ከኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር እንዲገናኙ መፍቀዳቸው፤ ሱዳንንም ሰላሟ እንዲመለስ መሥራታቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ልብ ውስጥ እንድትቀመጥ አድርጓታል። ምስራቅ አፍሪካውያን ለመተሳሰራቸው መንገድ ጠርጓል፡፡ ስለዚህም ፍራቻቸው ገኖ ግንኙነቱን ለማሻከር መንግሥትን ወደማሸማቀቁ ገቡ፡፡ የውጭ ጉዞ ክልከላውም የጀመረው ከመሪዎች የመሆኑ ምስጢር ይህ ነው፡፡ እንደመንግሥት አምነን የመረጥነውን በተለያየ መንገድም ለማጠልሸት የሞከሩት ከምንም መነሻነት አይደለም፡፡ አገሪቱ ምርጫውን እንዳታካሂድ አንታዘብም አሉ።
እንዲያውም ምርጫው እንዳይካሄድም ብዙ አሴሩ፡፡ ሆኖም ሕዝቡ የሚፈልገውን ያውቃልና ምርጫውን ሰላማዊ አደረገው፡፡ በነቂስ ወጥቶም አሳፈራቸው፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ሳይቀሩ ለስኬቱ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አደረጉ፡፡ ቅድሚያ ለአገር የሚለው አስተሳሰብ በሁሉም ልብ ውስጥ ነበርና እነርሱ አንታዘብም ቢሉም እናንተም ጠርታችሁን የእናንተን አልታዘብንም፤ ለራሳችን አናንስም፤ የሕዝባችን እንጂ የእናንተን ቡራኬ አንፈልግም የሚል ምላሽ ሰጡም። በዚህም ምዕራባውያኑ ነገሩ አበሳጭቷቸው ነበርና መንገድ እየቀያየሩ ከሚያገኙት ተቋዋሚ ጋር እንዲሠሩ ሆነዋል፡፡ ሌላው የጫናቸውና የዝምታቸው ምንጭ ድህነቷ እየታወቀ እንደ ሕዳሴ ግድብ አይነት ትልልቅ ሥራዎችን ያለማንም እገዛ መሥራቷ ሌሎች የአፍሪካ አገራትንም የሚያነሳሳ መሆኑ ስለተሰማቸው ነው፡፡ ይቻላል የሚል መንፈስን እንዲሰንቁ ብርታት ይሆናቸዋል ብለው ሰግተዋል።
በተመሳሳይ እንቢ በማለት ውስጥ እየተራመድን ያለነው የእድገት ጉዞ ብዙ አስግቷቸዋል፡፡ ለምሳሌ ግድቡን እንዳትሞይ ስትባል መሙላቷ፤ ለማስፈራራት ደግሞ ግብጽን ጭምር ለምን በቦንብ አታጋይውም እየተባለ ሲነገር አለመስጋቷና ሞልታ ብቻ ሳይሆን ኃይል ለማመንጨትም እየተንደረደች መጓዟ ብዙ ችግር እንደሚፈጥርባቸው ያስባሉ፡፡ አመንጭታ የፈለገችውን በማድረግም እንደ ምታሳፍራቸው በምታደርገው የእድገት ጉዞ እየተረዱም ነው፡፡ በዚህም ልማቷንም ለማደናቀፍ የማይቆፍሩት ድንጋይ አይኖርም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ሕወሓት አገርን ለማተራመስ ከሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች አንዱ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ይታወቃል፤ ከዚህ አንጻር ሕብረተሰቡ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ሳይወናበድ አገሩን ለመከላከል ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- የመጀመሪያው ተግባራቸው በወሬ ማሸበርና ሰዎች ሥራ እንዳይሰሩ ማድረግ ነው። ይህንን አባቶች ሲገልጹትም “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ይሉታል፡፡ እናም በውሸት ወሬያቸው ብዙዎችን እያሸበሩ ጦርነቱን አራዝመዋል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። በእርግጥ ውስጠ ምስጢሩን ከዚህ በፊት አልተረዳነውም እንጂ ሕወሓት የውሸት ፕሮፓጋንዳው ዛሬ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ሥልጣን ላይ እያለ ጭምር ሲጠቀምበት የኖረ ነው፡፡ የሚመሩ አካላትም ሰይጣናዊነትን ከምዕራባውያን ተንኮል ስለተማሩት ጠንቅቀው ያውቁታል፤ ኖረውበታልም።
ሌላው ዜጋ ጭምር ይህንን እሳቤ ይዞት እንዲጓዝ እየሰራበትም ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያው አገር ሲያፈርስ ደም እያቃባ መሄዱ ነው፡፡ በቀለኛ ትውልድንም እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ሴራው በብዙ መንገድ ስለታወቀ ይቅርባይም አይኖርም ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ከኤርትራውያን ጋር ደም አቃብተውን ቢሄዱም ይቅር ተባብለናል፡፡ አሁንም ክልል እየከፈለ ያጠማመደንና ደም ያቃባንን ሕወሓት ድባቅ መተን ደሙን በምናውቀው ባህላችን እናደርቀዋለን፡፡
በውሸት ወሬ ሕዝቡ አሁን መሸሽን ምርጫው ሊያደርግ አይገባውም፡፡ ጦር ሰብቆ የመጣውን በዚያው ሊፋለመው ያስፈልጋል፡፡ ሲሰደድ ብዙ ነገሮች የሚገጥሙት ከመሆኑም በላይ የሕወሓት የፕሮፓጋንዳ ማስፈጸሚያ ይሆናል፡፡ አሸናፊነቱንም ያረጋግጥለታል፡፡ ስለሆነም በአለበት ሆኖ ጠላቱን ማሳፈር ይገባዋል፡፡
ሕወሓት በሚያደርገው የጥላቻ ወሬ ከመንግሥት ተቃራኒ መቆምንም ማስወገድ አለብን፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው መንግሥት በግለሰብ ደረጃ መረጥነውም አልመረጥነውም አብላጫውን ወንበር የያዘ ነው፡፡ መሪ የሌለው መኪና እንደማይሰራ ሁሉ መሪ የሌለው አገርም ሊኖር አይችልም፡፡ እናም ወሬውን ወደጎን በመተው ፈታኙን ጊዜ ከመንግሥታችን ጎን በመቆም መሻገር አለብን።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት በዚህ ወቅት በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ በቀጥታ የከፈተውን ጦርነትና በአገር ላይ የደቀነውን አደጋ ለመመከትስ በሕዝቡ በኩል ያለውን መነሳሳት እንዴት ያዩታል፤ ይህንን ኃይል ወደውጤት ለማድረስስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- እኛ እግዚአብሔር የሚወደን ሕዝቦች ነን በአገራዊው ምርጫ ሕዝብ የወደደውን እንዲያደርግ እድል ተሰጥቶታል፡፡ እኔም አምስት ሰዓት ሙሉ ተሰልፌ የመረጥኩት ሰላማዊ አካሄድ ስለነበረው ነው።ይሁን እንጂ ይህ እንዳይሆን ምዕራባውያን በተለያየ መልኩ ተዘጋጅተው እኛ የመረጥነውን መንግሥት ለማሸማቀቅ ሰርተዋል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥቱን ሳይሆን እኔን ነው የናቁኝ፡፡
እናም ይህንን ድፍረታቸውን ማፍረስና እነርሱ በሥራቸው እንዲያፍሩ ማድረግ የመጀመሪያ ሥራችን መሆን አለበት፡፡ በዚህ ምርጫ ሁለት መልዕክት እንዳስተላለፍንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው እኛ እንጂ እናንተ አይደላችሁም ባለቤቱ የእናንተ ይሁንታ መስጠት ለእኛ መንግሥት መመስረት አስፈላጊ አይደለም ብለንበታል፡፡ ሁለተኛው በተለያየ ሴራ ብዙ ችግሮች ቢፈጠሩም አሁንም ወቅታዊና ልዩ ልዩ ሕዝቡና መንግሥት አልተለያዩም፡፡ ራሳችሁን ተመልከቱ ለማለት ለተቃውሞ በአደባባይ ወጥተናል፡፡ እናም ጠላትንና ወዳጅን ሕዝብ በመለየቱ ለኢትዮጵያን ልዩ እድል ሲሆን፤ ለምዕራባውያን ሸር ደግሞ ክስረት ሆኗል፡፡ ስለዚህም አሁንም ይህ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ሌላው መደረግ ያለበት ነገር አሁን እንደመንግሥት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ መጠናከር ላይ ሲሆን፤ ከአንድ አካባቢ የተፈናቀሉትን በአንድ ቦታ ላይ ወስዶ ጥበቃ እየተደረገላቸው ማስፈሩና መደገፉ የሚበረታታ ነው፡፡
ለነገ ተስፋቸው ጥሩ ነገር የሚፈጥር ነው፡፡ ሕዝቡም ቢሆን እያደረገ ያለው ድጋፍና መረዳዳት ኢትዮጵያዊነት በፍጹም ልብ የሚገልጽ ነው፡፡ ከዘመቻው ጋር በተያያዘም እንዲሁ፡፡ አገር ከሌለ አይደለም መናገር መተንፈስ እንኳን አይኖርም። እናም የቻለው ሁሉ መዝመቱና ለአገሩ ነጻ መውጣት መታገሉ ይበል እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሕወሓትና ጀሌዎቹ በአገራችን ጉዳይ ላይ ትልቅ ችግር እንደሆኑ እሙን ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ እንደ ሜቴክ አይነት ተቋማትን የራሳቸው አስፈጻሚ አድርገው አገሪቱን በኢኮኖሚ ሲያዳሽቁ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻርም የለውጡ መንግሥት በእነዚህ ተቋማት ላይ ጠንካራ ሥራ አከናውኗል። አንዱ ቦርዶችን ቀይሮ የአገር መከታ የሚሆኑ ሰዎችን ማምጣት ሲሆን፤ እርስዎ አንዱ ንዎት፡፡ ለመሆኑ የተሰጥዎትን ኃላፊነት እንዴት እየተወጡ ነው፤ተቋማቱስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- የስኳር ኮርፖሬሽንና የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ብዙ መሥራትንና ለውጥን የሚፈልጉ አስቸጋሪ ቦታዎች ነበሩ፡፡ በዚህም ለውጥ የሚያመጣ ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ እናም የለውጡ መንግሥት ይህንን አድርጓል፡፡ ለውጥ ሲባል በብዙዎች ህሊና ውስጥ እንዳለው በፖለቲካ አስተሳሰብ ብቻ የሚሠራ እንዳልሆነም ተገንዝቦ በፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊነት የሌላቸውን የአመራር ቦታ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገር መሥራት እንዴት እንደሆነ ለማሳየት እድል ሰጥቷል፡፡
ብዙ ለውጦችም የመጣባቸው ለዚህ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ለማንም ክፍት አልነበሩም፡፡ የተቀመጠው አመራር የራሱ ቤት አድርጎ ስለሚያየው አይፈቀድም፤ ለአገርም እንዲያገለግል እድል አይሰጥም፡፡ ብዙ ምሁራንን የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ከውጭ አገር ድረስ መጥተው ጅምሩ ዳር ሳይደርስ ቀርቷል፡፡ አሁን ግን ነገሮች ተቀይረው የቦርድ አመራር በመሆኔ እኔ ከርቀትም ያየኋቸው ውስጥም ላይ ያለው ችግር እንዲታይ አድርገናል። ሁሉም በየበኩሉ ለአገሩ እንዲያበረክት ሆኗልም፡፡ እያንዳንዱ ነገሮች ቢፈተሹ ስህተት ለማግኘት አያስቸግርም፡፡ አሁን ግን ቦርዱ ብቻ ሳይሆን ሰራተኛውና ሌላው አመራር አብሮ ብዙ ነገሮችን በመለወጡ ብዙ ነገሮች ተፈተዋል፡፡ ነገሮች በቅደም ተከተል እየተከናወኑም ናቸው። እያንዳንዱ ሰው ኃላፊነቱ ምን ድረስ እንደሆነ ያውቃል።
ከዚያ ከወጣ የሚጠብቀውንም ይረዳል፡፡ ምክንያቱም በአዲስ አዋጅ ከስሙ ጀምሮ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ ብዙ መመሪያዎችም ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው፡፡ በስኳርም የሆነው ይኸው ነው፡፡ አዲስ ዘመን፡- አገር ካለችበት ችግር እንድትወጣ ምን ማድረግ አለባት? ፕሮፌሰር ዳንኤል፡- መጀመሪያ ኢኮኖሚዋን መገንባት ነው፡፡ ለዚህም አገር ውስጥ የምታከናውናቸውን የልማት ሥራዎች በፈተና ውስጥም ብትሆን ማጠናከር አለባት፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ገበያ የሚፈጥርላትን አማራጭ መመልከት ይኖርባታል፡፡ ለምሳሌ ጎረቤት አገራትን ማስጠጋትና ለጋራ ልማት ማበርታት ከምንም በላይ ያስፈልጋል፡፡
ምስራቅ አፍሪካ አብሮ የሚሠራበትን መንገድ ለመዘርጋት ከኢትዮጵያ በላይ እድል ያለው አካል የለም፡፡ ስለዚህም ያለውን ትልቅ ሀብት በእርስ በእርስ ትስስር ወደገበያ ማስገባት ያስፈልጋል። ነዳጅን ብቻ ብናይ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ ውስጥ ያለውንና ራሷ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ በመጠቀም ብዙ ለውጦችን ማምጣት ትችላለች። ምክንያቱም እንደ ሞንባሳ፣ ላሙ፣ አርጌሳ፣ ሞቃድሾ፣ ጅቡቲ፣ አሰብና ምጽዋ አይነት ወደቦች በዙሪያዋ ያሉ በመሆናቸው ድፍድፍ ከመላክ ይልቅ የነዳጁን ማጣሪያ በጋራ አቋቁሞ ለጋራ ተጠቃሚነት መሥራት ታስችላለች፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉም አገራት መድሃኒት፣ ማዳበሪያ፣ ፕላስቲክ ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ አልባሳት የመሳሰሉት ምርቶች እንዳይቸገሩ ያደርጋቸዋል፡፡
እናም ለዛሬው ኢኮኖሚያዊ ችግር መፍትሄ ይህ አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ሌላው ምዕራባውያን እንደሚሉት አሸባሪውና መንግሥት እኩል እንዳልሆኑ ማሳየት ነው፡፡ መቼም ቢሆን የአገር ጠላትና ወዳጅ አብሮ መጓዝ አይችልም፡፡ እነርሱም ይህንን ሃሳባቸውን አይተውትም፡፡ እናም አሁን የተደቀነብንን ጫና በተባበረ ክንድ ጦርነቱን በፍጥነት ጨርሰን ልማታችን ላይ ማተኮር አለብን፡፡ የዚህን ጊዜ ሳይወዱ በግዳቸው ይመጣሉ፤ መለማመጣቸውም አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ምንጊዜም አሸናፊ ተለማኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የቀደመ ታሪካቸውና የኖሩበት ስለሆነ በዚህ ማንም ጥርጥር ሊገባው አይገባም፡፡ የዓድዋን ድል እንደግመዋለን። በቅርቡ እናየዋለንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሃሳብ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፡፡
ፕሮፌሰር ዳንኤል፡ – እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4/2014