
በትናንትናው ክፍል ሦስት እትማችን ሀገሪቱ ተግባራዊ እያደረገችው ያለው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ በተፅፅኖ ውስጥ የመጣ ሪፎርም እንጂ ኢትዮጵያዊ ሪፎርም አይደለም፤ በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ወደ አገልግሎቱ ያደላ፤ ለማኒፋክቸሪንግ እምብዛም ትኩረት የሰጠ አይደለም ለሚሉ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፤ በዛሬው እትማችን የቃለ መጠይቁን አራተኛ ክፍል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ኢቲቪ ፦ ቀደም ሲል ከግብርና አንጻር የተወሰነ ሃሳቦችን ሲያነሱልን ነበር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በተለይ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ አኳያ አንዱ የነፃነት ማረጋገጥ እሳቤ መሆኑ ይታወቃልና ይሄንንም በተደጋጋሚ ሲያነሱት እንሰማለን። ነፃነት በምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ አለበት የሚለውን ሃሳብ እና ከዛ አኳያ የሀገሪቱ የቆላማ አካባቢዎች ላይ በልማት ረገድ ተካታች በማድረግ መልኩ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምንድናቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ አንዱ የእይታ ለውጥ ያመጣንበት መንገድ የኢትዮጵያን መሬት ከጫፍ ጫፍ፣ የኢትዮጵያን ሰው ከጫፍ ጫፍ፣ የኢትዮጵያን እውቀት ከጫፍ ጫፍ መጠቀም አለብን፤ መደመር አለብን ያልነው እሱን ነው። ያልተደመረ አቅም፣ ያተደመረ እውቀት፣ ያተደመረ ሀብት፣ የምናስበውን ብልፅግና አያረጋግጥም መደመር አለበት። የምንደምረው ምንድነው? ለቆላ አካባቢዎች ያለን እይታ መቀየር አለበት። ቆላ ጠረፍ ብቻ አይደለም። ቆላ ችግር ብቻ አይደለም። ባይታይ ነው እንጂ ቆላ ውስጥ ሀብት አለ። ቆላ ውስጥ ለኢትዮጵያ ብልጽግና አጋዥ የሆኑ ጉልበቶች አሉ። እና ጠረፍ ነው ከሚል፣ ቆላ ነው፣ ችግር ነው ከሚል እይታ ወጥተን ለልማታችን ባለው አቅም ባለው ሳይዝ ግብዓት እንዲሆን መጠቀም አለብን። ሰውም መሬቱም ውሃውም የሚል የመደመር ዋነኛው እሳቤ ነው።
የቆላ ልማት ሀገሪቱን የማወቅ ሀብታችንን የማወቅ፣ አቅማችንን የማወቅ እና የመጠቀም ፍላጎታችን አካል ነው። የሀገሪቱን ሀብት በወጉ ሳናውቅ፤ አቅማችንን ሳናውቅ ያንን አሰናስለን መደመር ሳንችል የምናስበውን ብልፅግና አናረጋግጥም። ለምሳሌ፡- ቆላማ አካባቢዎች ካልነው አንዷን ብቻ እናንሳ ኦሞን ደቡብ ኦሞን አሁን ኢትዮጵያዊ እዛ አካባቢ ሄዶ የተኛውን መስክ፣ የተኛውን የውሃ ሳይዝ ቢያይ፣ በተለይ የሚያግዙን አካላትማ ያን ቢያዩ ሊከሱ ሁሉ ይችላሉ። ይሄን የሚያክል ነገር ይዛችሁ ነው ወይ ብለው። አሁን 145 ኪሎሜትር ካናል ደቡብ ኦሞ ሠርተናል። ካናል ሲባል ዝም ብላ ትንሽዬ ቦይ አይደለችም። ልክ እንደትልቅ ሪቨር እንደትልቅ ወንዝ የሚወርድ ትላልቅ የውሃ አቅም ያለው 145 ኪሎሜትር ካናል ተሠርቷል።
ውሃው ስላለ፣ መሬቱ ስላለ፣ ይሄን ማሽን ተጠቅመን ማልማት ከቻልን በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት፤ በምግብ ራስን መቻል ውስጥ የሚጫወተው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው። ሱማሌ እንደዛ ነው አፋር እንደዛ ነው። አሁን ቦረና ብትወስጂ ከውሃ ችግር በስተቀር የትኛውን ሜዳ ውሃ አድርሰንለት ብናርሰው እንኳን እኛ ሌላ ያበላል። ቆላ ማለት እነዚህ ናቸው። ቆላ ማለት አንደኛ ብዙውን ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ መሬት ማለት ነው። ወይናደጋውና ደጋው ተደምሮ ቆላውን አያክልም። በመሬት ስፋት በጣም ሰፊ ቦታ ነው ያለው። ቆላ ማለት ብዙ ሕዝብ የሌለበትና በማሽን ለማረስ የሚመች ቦታ ማለት ነው። ደጋና ወይናደጋው ተጣቧል እንደሚታወቀው። ቆላ ማለት በንጽጽር ሜዳማ ማለት ነው። ይሄኛው ለማሽን ብዙ አይመችም፤ ተራራ ስላለው ያኛው ሜዳማ ማለት ነው። ቆላ ማለት ሁሉም ወንዞቻችን በወይና ደጋውና ደጋው አካባቢ ዘንበው ወደታች ወርደው የሚገኙበት ቦታ ማለት ነው። እንጦጦ እኮ ዝናብ ከዘነበ ከ15፣ 20 ደቂቃ በኋላ ውሃ የለም። ውሃ ያለው እታች ነው ይወርዳል። ውሃ ያለበት፤ ያልታረሰ መሬት ያለበት፤ በማሽን ለመጠቀም አስቻይ ሁኔታ ያለበት፤ ኦፍኮርስ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና ድካም የሚጠይቀውን ስፍራ ሳናለማ የምግብ ሉዓላዊነት ብልፅግና የሚባል ጉዳይ በተሟላ መንገድ ሊመጣ አይችልም። በእርግጥ እኛ መሬቱን ብቻ ሳይሆ ን ሰውንም ደምረነዋል።
አጋር ተብሎ ሰከንደሪስ ተብሎ ሁለተኛ ዜጋ የተባለውን የለም አንተም እንደሌላው አንደኛ ዜጋ ነህ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ከማንም ያላነሰ ሚና አለህና መሐል ፖለቲካ ውስጥ ተጫወት ብለን አጋሩንም መሐል አስገብተን መሬቱንም በሚታሰቡ ፖሊሲዎችና እቅዶች የመሐሉ አካል አድርገነዋል። ብዙዎቻችን ከደጋ ወይናደጋ ስንመጣ እዛ አካባቢ ያለውን ነገር ብቻ ታሳቢ ስለምናደርግ ነው ሙሉ የሆነ እድገትና ልማት ልናመጣ ችግር የነበረብን እና ቆላውን መጠቀም፤ መሬቱን መጠቀም፤ ሰውን መጠቀም በከፍተኛ ደረጃ ፋይዳ አምጥቷል።
አሁን ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛዋ ስንዴ አምራች ናት እንላለን። ባይዘዌይ ይሄንን ጥያቄ ለማንሳት የሚሞክሩ ሰዎች አሉ። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛዋ ስንዴ አምራች ብቻ ሳትሆን ሁለተኛ አምራች ከሆነችው ግብፅ ሦስት እጥፍ ትበልጣለች። በድፍረት ነው ይሄንን የምናገረው፤ በሙሉ እምነት ነው የምናገረው፤ እውነት ስለሆነ። ስንጀምረው እናንሳለን፤ አሁን ሦስት እጥፍ ግብፅ ከምታመርተው እኛ እናመርታለን፤ ከፍተኛ የስንዴ ምርት አለ። ይሄን ለማጥላላት፣ ይሄን ለማራከስ፣ የለም ለማለት ሙከራዎች ሊደረጉ ይችላሉ። ግን ማንም ሰው ከዚህ ከዚች ከተማ 10፣ 15 ኪሎሜትር መንዳት ከጀመረ በኋላ የሚያየው ጉዳይ ነው። ከዚህ ወደሰሜን ሸዋ የሚጓዝ ሰው ከሱሉልታ ጀምሮ ባለው መንገድ ኦልዘዌይ ያየዋል ሌፍት ኤንድ ራይት ያየዋል። ምንም የተደበቀ ነገር አይደለም። ፋብሪካ እንኳን አይታይም፤ የታሸገ ቤት ውስጥ ነው የሚሠራው ይሄኛው እኮ ሜዳ ላይ ነው ያለው። በሁሉም ጫፍ ተንቀሳቅሰን እናያለን።
ሌላው ቅድም ባነሳሁልሽ ውስጥ የሚታየው ቴክኖሎጂን በሚመለከት እኔ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያክል መሬት እንደታረሰ በየአካባቢው ሄጄ ማየት አይጠበቅብኝም። በሳተላይት ኢሜጅ ሲስተሞች አሉ፤ ምን ያክል መሬት እንደታረሰ እናውቃለን እዚህ ሆነን። በዚያ መሬት ውስጥ ምን ያህል ሀርቨስት ሊገኝ እንደሚችል እንገምታለን። በሚያንሰው በሱፐርቪዥን በዳታ ይጨመራል። ቴክኖሎጂ እኮ አለ ዛሬ ችግር የለም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛዋ ስንዴ አምራች የሆነችበት ምክንያት ቆላ መጠቀም በመጀመራችን ነው። ለምሳሌ አንዱ የሚነሳው ኢትዮጵያ ስንዴ የምታመርት ከሆነ ለምን የዳቦ ዋጋ አልቀነሰም? ለምንስ ስንዴ ወደሀገር ውስጥ ይገባል? የሚሉ አንዳንዱ ጄንዊን ከሆነ እሳቤ የሚነሳ ጥያቄ አለ። አንዳንዱ ደግሞ የተሸፈነ አጀንዳ ያለው ጥያቄ አለ።
እኔ ኢትዮጵያ ስንዴ እያመረተች ያለች መሆኗን የማውቅበት አንድ ማስረጃ አለኝ። እኔ እንደሰው ቢሮ በገባሁ ዓመት በሁለት ሦስት ዓመት ድረስ በየዓመቱ ስንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚጎል ስምንት መቶ፣ ዘጠኝ መቶ፣ አንድ ቢሊዮን ዶላር አውጥተን ካልገዛን በስተቀር ምግብ ሀገር ውስጥ ያለው አይበቃም የሚል ጥያቄ ይቀርብልኝ ነበር። እኔ ግራ ቢያጋባኝም ጉዳዩ እፈርም ነበር ያ ጉዳይ እንዲፈጸም። ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ግን አንድ ብር አውጥቼ አላውቅም ለስንዴ። ከውጭ ስንዴ እንዲገባ አንድ ብር አውጥቼ ገዝቼ አላውቅም ሁለት ሦስት ዓመታት። ለዚያ ነው ደረቴን ነፍቼ ተመርቷል የምለው። ሄጄ ስለማየው ብቻ አይደለም። ገንዘብ ስለማላወጣበት።
ለምሳሌ ማዳበሪያ እስካሁን እናስገባለን፤ አላመረትንማ እስካሁን ብር ይጠየቃል። ስንዴ ግን ብር አይጠየቅም። ታዲያ አንተ ባትገዛም ስንዴ ሀገር ውስጥ ይገባል። ገባ ሲባል ዜና እንሰማለን የሚሉ ሰዎች ካሉ፤ አዎ ሊገባ ይችላል። ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኛ የተሸከመች ሀገር ነች። ኤክስ ዋይ የሚባል ሀገር ተነስቶ ለኢትዮጵያ ይሄን ያክል ረዳሁ የሚለው ለእኔ እኮ አይደለም የሚረዳው ስንዴ ጭኖ መጥቶ ለእነዛ ስደተኞች የሰጠውን ጭምር እኮ ነው ኢትዮጵያ የሚለው። እነዚያን ስደተኞች ዓለም መቀለብ አለበት የእኔ የግል ችግሬ አይደለም፤ ከተለያየ ሀገር የመጡ ናቸው። በክብር አስቀምጫለሁ፤ እያስተማርኳቸው ነው። እነሱን ለመቀለብ የምሰጥህ ስንዴ ነው ካለኝ በኋላ፤ ይሄን ያህል ስንዴ ሰጠሁ አይልም፤ ይሄን ያህል ቢሊዮን ረዳሁ ነው የሚለው። እየረዳም የራሱን ስንዴም እየላከ አትላክ ልለው አልችልም።
ለእኔ ብቻ የሚደረግ ጉዳይ አይደለም። እኔም አልረዳም ማለት አይደለም፤ ግን ዋናው ሰው እንዲገባው ነው። ለምን ለምን ፐርፐስ እንደሚመጣ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ ስንዴ አምራች ከሆነች ለምን ታዲያ ስንዴ እንዲገባ ፈቀደች፣ ለምን ታዲያ ስንዴ ተሸመተ ከውጭ የሚለው ሰው ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ የሆነ አየር መንገድ አላት። አንደኛ ብቻ ሳይሆን ከሁለተኛው በብዙ እጥፍ የላቀ አየር መንገድ አላት። ግን ተርኪሽ ኤር ዌይ ኢትዮጵያ ይገባል፣ ኤመሬትስ ይመጣል፣ የኳታር ኤርዌይ ይመጣል። አንደኛ አየር መንገድ ስላለን ለምን ሌላ አየር መንገድ እኛ ጋር ይመጣል ለምን አይከለከልም? የእኛ ደግሞ ይቅር ቡናን እንውሰድ። እኛ ቡና አንደኛ አምራች ነን፤ ቢሊየንስ ሸጥን እያልኩሽ ነው። ቡናን ኢምፖርት እናደርጋለን። ለማሽን ለምናምን ትናንሽ የሚታሸጉ ቡና መርጦ ሰው እኮ ኢምፖርት ያደርጋል ኢትዮጵያ ውስጥ። ፕሪፈረንስ ነው።
ይሄን አሁን ያለው የገበያ ሥርዓት መከልከል አይፈቅድልንም። ለምሳሌ አሜሪካ በመኪና ምርት በተለይ በኢቪስ ኤሌክትሪክ መኪና በሚባሉት ቴስላ የሚባለውን የምታመርት ሀገር ናት። በጣም ሰፋፊ መኪና ፋብሪካዎች አሏት። ግን ከአውሮፓም ከቻይና መኪና ምርት ይገባባታል። ለዚህ እኮ ነው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከውጭ የሚገባው መኪና ይሄን ያህል ታሪፍ የሚሉት እኮ ለዛ ነው። መኪና አላቸው። ሌላው ቀርቶ ኤሌክትሪክ መኪና ቴስላን በዚያ ልክ እያመረተ ቻይና የሚመረተው የኤሌክትሪክ መኪና አሜሪካ ይገባል። እኔ አምጥቼ እሸጥብሀለሁ፤ አንተ አታመጣብኝም ማለት አይቻልም። እኔም እሸጣለሁ እሱም ይሸጣል። ገዢው ሰው ግን ሁለት ነገር የትኛውን እንደሚገዛ ይወስናል።
አንደኛው የሠለጠነ የነቃ ማኅበረሰብ፣ የናሽናል ጥቅም የገባው፣ ብሔራዊ ጥቅም የገባው ማኅበረሰብ ሲሆን የሀገሩን ምርት ያስቀድማል። ሳይነገረው የሀገር ምርት መግዛት ፋይዳው ስለሚገባው በጠቅላላ ጥቅሙ ስለሚገባው የሀገር ምርት ያስቀድማል። ይህን በአውሮፓ ገበያ በቻይና ገበያ በደንብ እናየዋለን። የእኛም ሀገር ሰው እየነቃ ሲሄድ ውጭ ናፋቂነቱ የውጭ አድናቂነቱ እየቀነሰ ሲሄድ የራሱን ምርት ዋጋ ሰጥቶ ችግር እንኳን ቢኖርበት የእኔ ነው እያለ ይገዛዋል። አንዱ መንገድ እሱ ነው። ሁለተኛው በሀገር ውስጥ ምርት ሲትረፈረፍ ከውጭ ከመጣው ምርት በዋጋ ንጽጽር የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ነው። ያን ማድረግ ቀላል ነገር አይደለም። ለምሳሌ ስንዴ ሌላ ሀገር የሚመረተው፤ ቡናን እንውሰድ ስንዴን ትተን። ቡና ብራዚል በሄክታር በ120፣ 130 ታመርታለች በሄክታር።
እኔ በሄክታር 15 አመርታለሁ፤ ማክሲመም፤ ማክሲመም ነው እዛ ድረስ። በአንድ ሄክታር 15 የሚያመርተው ሰውዬና በአንድ ሄክታር መቶ ምናምን የሚያመርተው ሰውዬ ገበያ ሲወጡ እኩል አይሸጡም። ማሽነሪስ ያስፈልጋል፣ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል። ስንዴ ዩክሬን በሄክታር የምታገኘውን ግማሽ እኔ አላገኝም። ማሽነሪ ይፈልጋል፣ ስንዴ አመረትኩኝ እንጂ ገና ብዙ ሥራዎች ይጠበቅብናል። በአንድ ሄክታር መቶ ኩንታል የሚያገኝ ሰው፣ በአንድ ሄክታር 50 ኩንታል ከሚያገኝ ሰው ጋር ሲወዳደር ዘ ሴም ሳይዝ ባለው መሬት በጣም ብዙ ምርት ስላመረተ ባነሰ ዋጋ ይሸጣል። በዋጋ መወዳደር ሌላ ፈተና ነው ማለት ነው። ይሄ ጊዜ ይፈልጋል። ከዚያ ውጭ ኮንትሮባንዱ አለ፤ ደላላው አለ፤ የኢትዮጵያን ምርት ኢሌጋል በሆነ መንገድ ወደውጭ ሀገር መሸጥ የተለመደ ነው። ኮንትሮባንዱ፣ ደላላው፣ እኛ በሄክታር የምናመርተው ምርት ለመወዳደር ያለው ውስንነት የዓለም የገበያ ንግድ ሥርዓት በራሱ ደግሞ መከልከል ስለማይፈቅድ ሰው ደግሞ ነቅቶ ብሔራዊ ጥቅም ገብቶት የራሱን መርጦ ስለማይገዛ ሲደማመር የሚፈጠሩ ፈተናዎችና ችግሮች አሉ።
በፈለግነው ልክ ኢምፓክት ማድረግ እንቸገራለን። ለምሳሌ የዘመን መለወጫ፣ ገና፣ ፋሲካ፣ አረፋ ሲመጣ እኮ የእኔ ሥራ እኮ ነው። ልክ እንደመንግሥት ሥራ ኮሚቴ አቋቁሜ፣ ምርት ካለበት አስገዥቼ፣ አስጭኜ፣ እኮ ነው እዚህ እያስመጣሁ የማከፋፍለው፤ ሥራዬ ስንት ኪሎ ገባ፣ ስንት ገበያ ወጣ ሥራዬ እኮ እሱ ነው። በገና እለት ዋነኛ ሥራዬ እንቁላል ስንት ተሸጠ? ስጋ ስንት ተሸጠ? ነው እኔ ስጠይቅ የምውለው። ለምን? የገበያ ሥርዓቱ ዊክነስ ስላለበት ፈላጊው አለ፣ ምርቱ አለ፣ እዚህ መሐል ላይ ኢንተርቪን ካላደረግን በስተቀር ሰው ስለሚቸገር ግን የእኛ ሥራ መሆን ስለሚገባው አይደለም።
ብዙ ደላላና ብዙ አምታች ስላለ ደሃው እንዳጎዳ ለማድረግ ነው። እንደመንግሥት ቁጭ ብለን እንደሥራ የምንሠራው ማለት ነው። እነዚህን ጉዳዮች ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። እኛ ስላመረትን ኢምፖርት አናደርግም ማለት አይደለም። እኛ ስላመረትን በዋጋ ደግሞ እንወዳደራለን ማለትም አይደለም። ብዙ ፋክተሮች አብረውም የሚከተሉ ነገሮች አሉ። ይሄን እያረቅን እንሄዳለን። ማምረት እንደምንችል ገብቶናል። ስንዴ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ አንደኛ እንደሆንነው ሁሉ በሄክታር እያሰፋን እያሳደግን መሄድ እንዳለብን ገብቶናል።
ገንዘብ ይፈልጋል፣ ጊዜ ይፈልጋል፣ እውቀት ይፈልጋል እየሠራንበት ነው። የሠራንበትን በመካድ የጎደለንን መሙላት አንችልም። የሠራነውንና ያገኘነውን ውጤት እያደነቅን የጎደለውን እየሞላን እንሄዳለን። በዛ ዓይን ካልታየ በቀር አደገኛ ችግር ያመጣል። በጥቅሉ ቆላ ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም አላት። የከርሰ ምድር ውሃው የሰርፌስ ውሃው፣ በዝናብ የሚገኘው ውሃ ከፍተኛ መሆኑ፣ ያልታረሰ መሬት መሆኑ፣ ማዳበሪያ ያልነካው አፈር መሆኑ ተደማምሮ ምርታማነት የሚሳድግ ስለሆነ ቆላ ላይ አሁን ከሠራነው በላይ አበክረን መሥራት ይኖርብናል። ቆላ ላይ ስንሠራ ግን መሬቱ ላይ ብቻ አይደለም። ሰውንም ጭምር የሀገር ባለቤት መሆኑን አምነን እንደብልፅግና አቅፈን ነው። አንተ አጋር ነህ መሬትህ ግን የኛ ነው ማለት አንችልም። እሱም ባለቤት ነው፤ መሬቱም የእኛ ነው። በጋራ ስንለማ የምናስበውን ውጤት ልናመጣ እንችላለን። እና ኢንክሉሲቭ ነን፤ ተደማሪ ኃይል እናበዛለን፤ መደመር እናስባለን ስልን መሬትም ሰውም ውሃም፤ ጭንቅላትም፤ ሀብትም ነው የሚደመረው፤ በዚህ አግባብ ነው ቆላ ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው። ውጤቱም በዛ ልክ እየመጣ ያለው።
ኢቲቪ ፦ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከቆላማ ልማት ጋር በተገናኘ በተለይ ከቆላ አካባቢዎች ጋር ያነሳነው ጉዳይ አለ። ይህ አንዱ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ሥራዎች አካል ነው። ይህ ደግሞ ከተረጂነትም ጋር በቀጥታ ሊገናኝ የሚችል ጉዳይ እንደሆነ ታሳቢ ይደረጋል። ሌሎች በተለይም ካነሳናቸው ባሻገር ኢትዮጵያ ከተረጂነት ለመውጣት የምታደርጋቸው ጥረቶች ምንድናቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ ተረጂነት በተለይ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዘሞስት አሳፋሪው ነገር ነው። ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር ለራሷ አምርታ እራሷን ማብላት ተስኗት አንዳንዴ ከእሷም ካነሱ ሀገራት መለመኗ በጣም አሳፋሪ ነገር ነው። ከዚህ አሳፋሪ ይሄ ትውልድ ጨክኖ ኢትዮጵያን መገላገል አለበት። ልጆቻችን ግን ይህን ጉዳይ ከታሪክ ውጪ በተግባር ማየት የለባቸውም። እኛ ተረድተን ተረጂነትን ማውረስ የለብንም። እኛ ለምነን ልመናን ማሸጋገር የለብንም። እኛ ጋር መቆም አለበት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ተረጂነት ልክ እንደ ኢኮኖሚ በኢንፍሌሽን እንዳነሳነው በጣም አደገኛው ስብራት ነው። የሥነልቦና ስብራት ኢትዮጵውያን ከገጠመን ነገር አንዱ ከተረጂነት ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው። አሳፋሪ የሆነ ነገር ጌጥ ሆነልን፤ አሳፋሪ የሆነ ነገር ክብር ሆነልን። አሳፋሪ የሆነውን እና ደፍረን ልንተገብረው የሚገባውን ነገር በነፃነት የምንተገብረው በአደባባይ የምናደርገው ጉዳይ ሆነ።
ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የመጣው የባህል ለውጥ፤ የቫልዩስ የኢትዮጵያውያን እምነት መሸርሸር ልክ በጣም የሚያስፈራ ነው። በተደረገው ጥናት ያረጋገጥነው ለመረዳት በሴፍቲኔት ለመታቀፍ ሲሉ ጥሪታቸውን የሚሸጡ አሉ። በሬ ካለው ከብት ካለው፤ ከብት ካለው፤ ፍየል ካለው ደሃ ለመባል የሚሸጥ ሰው አለ። ይሄ በጣም የተረጋገጠ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሪታቸውን ሽጠው የለኝም እና በሴፍቲኔት ልኑር ብለው የወሰኑ ቤተሰቦች፣ ግለሰቦች አሉ። ከዚህ በላይ ስብራት የለም።
ባለኝ ጨምሬ ከልመና ልገላገል ሳይሆን ያለኝን ሽጬ በልመና ልኑር የሚል ነው። ልጅ እየቀያየሩ የሚለምኑ አሉ፤ እዚህ ከተማ ውስጥ እንደሚደረገው ተከራይተው ልጅ እንደሚለምኑት ጠዋት በሆነ ልጅ ይዘው ሄደው ስንዴ ወስደው፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ልጆች ቀይረው የሚለምኑ ሰዎች አሉ። ልጅ እየቀያየሩ ስንዴ የሚረዱ ሰዎች አሉ። በጥናት የተረጋገጠ ነው ይሄም።
አመራሩ ሳይቀር ወረዳ በታች ቀበሌ ያለው አመራር ሳይቀር ልክ እንደ ሥራ ማስኬጃ፤ እንደ በጀት የሌለውን ተረጂ ቆልሎ ርዳታውን ወስዶ ሽጦ ሥራ ማስኬጃ የሚያደርገው አለ። ምን ያክል የጉዳዩ አደገኛነት ማሳያ ከሆነች ብዬ ነው። ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ተቋም የሚያስተዳድረው አካልም ጭምር ማለት ነው። መሸማቀቅ የሚባለው ነገር ቀረ።
ጥናቱ እንደሚያመለክተው፤ በመጀመሪያ አካባቢ የሚረዱ ሰዎች ማታ ነጠላ ተሸፋፍነው ተደብቀው ርዳታ ይወስዱ ነበር። አሳፋሪ ስለነበረ ኋላ ላይ ሲነጋጋ ጀመሩ። አሁን ቀን ላይ ብቻ ሳይሆን ለምን ዘገየ ልክ እንደ ደመወዝ፤ ርዳታ ይምጣ እንጂ፤ ኪሎ ይጨመር እንጂ የሚለው ጉዳይ እንደ መብት በገሐድ የሚነገር፣ የሚሠራ ጉዳይ ሆነ።
አንዳንዱ አካባቢ በተለምዶ እኛ ሀገር አባት ለልጁ ሌላውን ሰው ልጅ ሲጠይቅ የሚጠየቁ ጥያቄዎች ነበሩ የሚታወቁ። ሥራ አለው ወይ፤ ባሕሪው ገቢው ይባላል። አንዳንድ ከባቢ በሴፍቲኔት ታቅፏል ወይ የሚልም ጥያቄ መመዘኛ ሆኗል። ሰው ልጁን ለመስጠት ባልየው በሴፍቲኔት የታቀፈ ከሆነ ሊሰጥ አልያ ደግሞ ሊከለክል ማለት ነው። በዚህ ደረጃ ነው ሥብራቱ፤ በዚህ ደረጃ ነው የባህል ውድቀቱ።
ይህንን ሥብራት ለመጠገን በትልቁ ማሰብ አለብን፤ ከተረጂነት መውጣት ብቻ ሳይሆን እረጂ መሆን አለብን እኛ የሚል ትልቅ ሃሳብ ካሰብን በኋላ ሕዝባችንን ነው ያወያየነው። ከቀበሌ ቀበሌ ሕዝብ አወያይተናል በዚህ ጉዳይ። የሚያስደስተው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰፋት ጉዳዩን ተገንዝቦ ሪስፖንድ ለማድረግ የሄደበት መንገድ በጣም ተስፋ ሰጪ ነው። እንፍጠን እንፍጠር እንሥራ ይብቃን ልመና የሚል የኢትዮጵያውያን የወል ድምፅ ነው። በውይይቱ ያረጋገጥነው የጋራ አቋማችንን ነው ይሄ የመንግሥት ብቻ አይደለም። ሕዝቡ ይጠላዋል ይህንን ነገር። ገባ ብለን ስናይ እውነት ለመናገር ልመና ርዳታ ኢትዮጵያ መርዝ ነው የሚያመጣባት። ከፋፋዩ ሃሳብ፤ ፖለቲካን የሚያተረማምሰው፣ ሕዝቡን የሚያወናብደው ርዳታ የሚባል ቆሻሻ ተግባር ነው። እሱ ውስጥ በጣም በጣም በርካታ ነገሮች ታጭቀው የሚመጡት። የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን መክረን እንዳንወስን የሚደርገን አንዱ ነገር ርዳታ የሚባለው ነው። የሚነገረን ብዙ ቢሊዮን ነው እኛ አናየውም በዛ ውስጥ ግን ሰው የፈለገውን ነገር በእኛ ውስጥ እንዲሠራ ያደርጋል እና መቆም ያለበት አደገኛ ስብራት፤ ለመልማት ለመለወጥ ያለንን ኢነርጂ የሚገታ አደገኛ መርዝ ነው። ይህንን ነገር ለመቅረፍ በመንግሥት ደረጃ በዚህ ቢሮ የተዋቀረ ቲም አለ። ርዳታን ማቆም አለብን፤ ተረጂን መቀነስ አለብን ብለን ጊዜ አስቀምጠናል። ቅድም በኤክስፖርት በጊዜ አነጻጽሬ አንስቼልሽ ነበር።
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ሌላው ማሳያ እና ኢትዮጵያውያን በአንክሮ ማስተዋል የሚገባቸው ከርዳታ ጋር ተያይዞ ያለ ጉዳይ ነው። በ2013 ትናንትና ኢትዮጵያ 27 ሚሊዮን ገደማ ተረጂ ነበራት። 27 ሚሊዮን ገደማ። በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብቻ ነው ተረጂ ያላት። 23 ሚሊዮኑ ነፃ ወጣ፤ 20 ሚሊዮን ተረጂ ነፃ ካወጣን በኋላ አንድ ሰው፤ አንደ ሥርዓት፤ አንድ ፓርቲ ባይኖርስ ምን ችግር አለበት፤ ከዚህ በላይ ድል አለ እንዴ። ዜሮ መሆን አለበት የማምነው ነገር ነው። ግን 20 ሚሊዮን ሰው ከእንደዚህ ያለ ስብራት ከማውጣት በላይ ድል ነፃ ለማውጣት በላይ ማንሰራራት ከየት ይመጣል።
ይሄ ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ያልነው እራሱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢንተርናሊ ዲስፕሌስድ የሆኑ ሰዎችን ይጨምራል። የተፈናቀሉ ሰዎች እነሱን ተወያይተን ቶሎ ወደ ቀያቸው መመለስ ብንችል ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ማለት ነው። መንግሥት ባስቀመጠው እቅድ፤ ሕዝባችን በነበረው መንገድ ድጋፉን ከቀጠለ፤ የኢትዮጵያ እና የርዳታ ጉዳይ ቢበዛ ሁለት ዓመት ነው ከዚያ በላይ አይቀጥልም። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ማክሲማም እናቆማለን ብለን እየሠራን ያለነው። ደግሞም እናሳካዋለን። 23 ያሳክን ሦስትና አራት አይከብደንም መቼም እናሳካዋለን።
በአንድ ጀንበር መሆን አይችልም ትልቅ ቁጥር ስለሆነ፤ 27 ሚሊዮን ማለት የብዙ ሀገር ፖፑሌሽን ማለት ነው። ትልቅ ቁጥር ነው፤ ከዛ ውስጥ 23 ያልነው እኛ ሰፈር ያሉትን ጎረቤቶች ደማምሮ የሚሆን ቁጥር ማለት ነው፤ ቀላል ነገር አይደለም። በሁለት ሦስት ዓመት ውስጥ ይህን የሚያክል ሰው ከተረጂነት ማውጣት የማንሰራራት መገለጫ ትልቁ ማሳያ ነው።
ግን ይሄ ጉዳይ በምን መጣ ነው? 23 ሚሊዮኑ እንዴት ተሳካልን? ስኬቱን ብቻ ሳይሆን የስኬቱን መንገድ ማየት ስለሚያስፈልግ። አንደኛው ዌዘር ነው። በዓመት ሁለቴ ማምረት ጀምረናል ክረምት ከበጋ እንደምታዩት ዝናብ ፈጣሪ ርስፖንድ አድርጓል ለልፋታችን። በግሪን ሌጋሲ ተከልን እግዚአብሔርም እረዳን ዝናብ የበጋም ስንዴም ከሞላ ጎደል በበቂ እያገኘን ነው። ይሄ እንዲቀጥል ሥራ ያስፈልጋል። የዘነበውን እንዳይባክን መቋጠር ያስፈልጋል፤ መገደብ ያስፈልጋል። ካናል ያስፈልጋል፤ ኢሪጌሽን ማስፋት ያስፈልጋል። ያ በየጊዜው ልንሠራበት የሚያስፈልገን ጉዳይ ነው። እካሁንም ያለው ጥረት ግን ዝናብ በእጅጉ አግዟል ፈጣሪ እረድቷል እዚህ ጋር።
ሁለተኛው ኢኒሼቲቮቻችን ናቸው። ለምሳሌ የሌማት ትሩፋት ስንጀምረው የዋዛ ይመስላል። ያመጣው ኢምፓክት ግን ዶሮ እንቁላል የሚባል ነገር የዓለም ሁሉ ስቃይ ነው የሆነው። ብዙ ልንሠራ የሚገባን ሴክተር ቢሆንም የሌማት ትሩፋትን ባንጀምር በዶሮ፣ በወተት፣ በሥጋ፣ በእንቁላል ሊፈጠር የሚችለው ቀውስ እየሠሩ ያሉ ሰዎች ይገባቸዋል። በነገራችን ላይ እዚህ እኮ ቢሾፍቱ ሞጆ ሲወጣ እየፈጠርን ያለነው የዶሮ ማምረቻ አቅም የሚገርም ነው። ትንሽ ነው መስፋት አለበት ግን የሚገርም ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ እኮ ነው ስለ ግራንድ ፓረንት ኢትዮጵያ ያወራችሁት። መቼ አውርተን እናውቃለን። ፓረንት ግራንድ ፓረንት ኖሮን ኢትዮጵያ ውስጥ ጫጩት አምርተን ማስፋት የሚል ሀሳብ እራሱንኮ ሌማት እኮ ነው ያመጣው፤ አልነበረንም። አሁን ግን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው ያለው። አሁንም ሥራ ይፈልጋል ያ ኢኒሼቲቭ እረድቷል። ብዙ ቤት እንቁላል ብዙ ቤት ዶሮ ገብቷል።
የበጋ እርሻ ቆላን ጨምሮ በጋ እርሻ ብዙ ችግር ቀርፏል ከዚህ አንጻር፤ ብዙ ቤተሰብ ከልመና እንዲገላገል አድርጓል። የጓሮ እርሻ፤ የጓሮ ጎመን፤ ሰላጣ የምንሠራው ነገር እዚህ ቤት እንኳን በሁለት ሳምንት ምን ያህል ሰው መጥቶ በወር ውስጥ የጓሮ አትክልት እንደሚካፍል ያው እናውቃለን። እናያለን ሁልጊዜ፤ በየቦታው የጓሮ እርሻ አግዟል፤ የከተማ እርሻ የከተማ መሬቶች ባዶ የነበሩ ወደ እርሻ መቀየራቸው አግዟል። እዚህ ጋር ቤተክርስቲያኖች ያጠሯቸው ቦታዎች፤ ዩኒቨርስቲዎች ያጠሯቸው ቦታዎች፤ ሀይስኩሎች ያጠሯቸው ቦታዎች፤ አንዳንድ የመንግሥት ኩባንያ ቢሮዎች ያጠሯቸው ቦታዎች እየታዩ በቨርቲክል ፋርሚንግ፤ በፕሪስን ፋርሚንግ፤ በዲፕ ኢሪጌሽን ታግዘው በጓሮ እርሻ፤ በከተማ እርሻ ማክሲማም ብንሠራባቸው ለምና ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡ።
አሁን በጣም የታጠረ ቦታ ሞልቷል መቼም ከተማ ውስጥ እንደሚታየው እሱ ሁሉ የወል ሀብት ስለሆነ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። ባለቤት መሆን ብቻ አይደለም፤ ባለቤቱ ማንም ይሁን ግን መጠቀም አለብን። ያ እየተሠራ መምጣቱ ጅማሮው ለቅድሙ ውጤት አግዟል። ሌላው ግን በጣም ያገዘን ዳታ ነው። ዳታ ማጥራት። አንዳንድ ቦታ እኮ የሌለ ሕዝብ፣ የሌለ ቤተሰብ፤ የሌለ ፖፕሌሽን፤ የሌለ ቁጥር ተመዝግቦ ነው ርዳታ የሚለመነው። ብዙ ስንዴ ለማግኘት ብዙ ቁጥር ማበራከት ወግ ስለነበር ማለት ነው። ዳታ አጠራን፣ ኢኒሸቲቮቻችን ሠሩ፤ ዌዘር ሰፖርት አደረገን፤ ሕዝባችን በአብዛኛው ወሰነ አይገባም ብሎ በዚህ ምክንያት አይገባም ብሎ በጣም በከፍተኛ ደረጃ በቁጥር አሽቆለቆለ። እንዴት ነው ሰስቴን የምናደርገው ይሄን ነገር። አንድ ዓመት ላይ 20 አንዴ 15 አንዴ 10 የሚባል የሚዋዥቅ ጉዳይ እንዳይሆን እንዴት ሰስቴን እናደርገዋለን የሚለው ደግሞ ወሳኝ ጥያቄ ነው።
ለዚህ አንደኛ ፈንድ አዋጅ ፓርላማ ነው ያለው በቅርቡ ይፀድቃል። በካቢኔ ፀድቋል። ፈንድ ከእያንዳንዱ ትራንዛክሽን ለዚህ ፐርፐዝ ሎካሊ ፈንድ እናሰባስባለን። ይሄንንም ኢትዮጵያውያን ማድረግ ይችላሉ። ሁለተኛ ክምችት ነው። ትልቁ የኢትዮጵያ ስብራት ምርት ባለባቸው በቂ የሆነ ስቶሬጅ የለም። ይመረታል ወይ ይበላል ወይ ይበላሻል። እያመረቱም የሚበላሽባቸው ቦታዎች በጣም ብዙ ናቸው። በቅርቡ እዚሁ ወደአፋር አካባቢ ሰዎች ጋር አዋሽ አለፍ ብሎ ሄደን ነበር። እናም መሬቱ በሙሉ ማንጎ እና ብርቱካን ፈሶ ለቃሚ አጥቶ አይተን ነበር። እዚህ አይተን አዝነናል። ግን በቃ እንደሱ ነው አንዳንድ ቦታ ይመረታል፤ ምርት የሚሰበስብ ሰው የለም፤ ከተማ ታጉሮ ነው ሥራ የለም የሚለው ምርቱና ፈላጊው አይገናኝም።
ክምችት ያስፈልጋል ምርቶቻችንን የምናቆይበት። ስንዴም ይሁን ጤፍም ይሁን በቆሎም ይሁን ከተመረተ በኋላ ሳይበላሽ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ ስቶሬጅ ያስፈልገናል።
ሦስተኛው የርዳታ ማስተባበሪያ የሚባለው ኮሚሽን እየለመነ የሚያከፋፍል ብቻ ሳይሆን የሚያርስ መሆን አለበት ነው ያልነው። በቆላም አካባቢዎች በዚህ ዓመት ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ አርሷል ኮሚሽኑ። የራሱ እርሻ አለው አርሶ ምግብ ይሰበስባል። ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከራሱ እርሻም ይሰበስባል። ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከራሱም እርሻ ድጋፍ ሰፖርት ያደርጋል ማለት ነው። ያን ማስፋት አለበት ሦስት አራት እጥፍ ማሳደግ አለበት። ቦታውም አለ፤ ውሃውም አለ፤ አቅሙን እያጎለበተ ማረስ አለበት። ከዚህ ውጪ ምላሽ የመስጠት የመንግሥት አቅም ተሻሽሏል። ለምሳሌ ሶማሌ ክልል እና ቦረና ድርቅ ሲያጋጥመን ሰው ሳይሞትብን ብዙም ርዳታ ሳናገኝ በራስ አቅም መከላከል የቻልንበት መንገድ ሪስፖንድ የማድረግ አቅማችን ስለጎለበተ ነው።
ድርቅ በሆነ ጊዜ ሊያጋጥም ይችላል። ድርቅ የትኛውም ዓለም ላይ የሚያጋጥም ነው። ድርቅ ሌላው ዓለም ላይ ኒውስ ነው። ሙቀት ጨመረ፤ ዝናብ ጠፋ ዜና ነው እንጂ ሰው አይገልም። እኛ ጋር ደግሞ ከዜናነት አልፎ የሰው ሕይወት እንዳይቀጥፍ ሪስፖንድ የማድረግ አቅማችንን ማሳደግ ያስፈልጋል። ይሄ እያደገ የመጣ አቅም ነው። ከእኛ ውጪ የኮሚኒቲ ሶሊዳሪቲ የኮሚኒቲ ሪስፖንድ በጣም የሚደንቅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ያለን ማጋራት፣ ማካፈል አዲስ እያደግንበት ያለ ባህል ሆኗል።
ማዕድ ማጋራት እኮ ቀላል ነገር አይደለም። ብዙ ሠራተኞች በማዕድ ማጋራት ጓዳቸውን እየሞሉ ከዓመት ዓመት ይኖራሉ እኮ። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሦስትና በአራት ወር የሚደረግላቸው የማዕድ ማጋራት ከፍተኛ ጠቀሜታ ነው ያለው። ብዙ ቦታ ይደረጋል፤ መመገቢያ ቦታ እያበጁ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በቀን አንዴና ሁለቴ አዛውንቶች፤ ትልልቅ ሰዎች የሚመገቡበት ስፍራ እየተመቻቸ እየመጣ ነው። ያም የማኅበረሰቡ ሪስፖንስ ሆቴሎች፣ ባለሀብቶች እያደረጉ ያሉት ድጋፍ ከፍተኛ ነው የሚጠይቁኝም ሰዎች አሉ። ምግብ ከሚደፋ ለምን አይሰጥም። መድፋት አንፈልግም የሚሉ እናትና አባቶች አሉ። ያም ሥርዓት የተበጀለት ሆቴሎች የተረፋቸውን ነገር ለእጅ አጠሮች ማገዝ የሚችሉበት መንገድ መስመር እየያዘ እየመጣ ነው ያለው።
ብዙ ሰዎች መደጋገፍን ባህል እያደረጉ ነው። ለብቻ መኖር ሳይሆን በጋራ መኖር እየተለመደ ነው። በግ ሥጋ ማካፈል እየተለመደ ነው። ከዚያ ባሻገር ግን የትምህርት ቤት ምገባ እጅ አጠር ሰዎች በምግብ ምክንያት ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ትምህርት ነፃ ነው ግን ምግብ ነፃ ስላልነበር መላክ የሚቸገሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች እኮ እንመግባለን አሁን። ቁርሳቸውን፤ ምሳቸውን ትምህርት ቤት እየበሉ ይማራሉ። አንዳንድ ድርጊታችን እኮ በጣም ሀብታም ሀገር ነው የምንመስለው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች በነፃ እየመገቡ ማስተማር ቀላል ነገር አይደለም። ልጆች ምግብ ስላጡ ትምህርት ቤት እንዲቀሩ መደረግ የለበትም። ይህ አቅም መጎልበት አለበት። ጅማሮው በጣም በጣም ተስፋ ሰጪ ነው።
እነዚህን ደምረን ነው እንግዲህ ወደ ኢትዮጵያ ኤድ ማደግ አለበት። ኢትዮጵያ ተረጂ ሳይሆን ረጂ መሆን አለባት፤ ፈንዱ ካደገ ክምችቱን ኢንቨስት ካደረግን ፕሮፐርሊ፤ ተቋሙ ማረስ ከጀመረ፤ የሚያመርተውን ምርት የሚያከማቸውን ነገር በዘላቂነት ሊያቆየው አይችልም። ያምርት ያከማች እና ገበያ ችግር አለ ሲባል፤ ኢንተርፊር አድርጎ መሐል ላይ ገብቶ ገበያ ያረጋጋል፤ ምርቱ ካለ። ገበያ ችግር ካለ ኤክስፖርት ያደርጋል። በገበያም በኤክስፖርትም ክፍተት ካልታየስ? ትርፍ ካለ የተቸገሩ ካሉ ያግዛል። ምክንያቱም ያ ማቆያ ቦታ ያ ስቶሬጅ ለሌላ ምርት ስለሚዘጋጅ ዝም ብሎ ማስቀመጥ አይቻልም። ወይ ይሸጣል፤ ወይ ይረዳል፤ ወይ ገበያ ይረጋጋበታል። እና ደግሞ አዲስ ምርት ይተካል ማለት ነው። ሌላውም ዓለም የሚያደርገው ይሄንን ነው።
በእኛ ሁኔታ ወደ እዚያ ማድረግ የሚያስችል፤ አቅም ስላለ ጅማሮ ውጤቱ ያንን ስለሚያመላክት ኢትዮጵያ ወደ አጋዥነት መሸጋገር አለባት። ትልቁ ሕልም እሱ ነው። አጋዥ የሚለውን ሕልም ለማሳካት ግን መጀመሪያ በትንሹ መጀመር ይፈልጋል፤ ቅድም እንዳነሳሁት። ባለፉት ሦስት ዓመታት 23 ሚሊዮን ተረጂን ነፃ ያወጣች ኢትዮጵያ እያደገች ነው ካልተባለ ማን ነው ታዲያ እያደገ ያለው? ባለፉት ሦስት ዓመታት 23 ሚሊዮን ተረጂን ነፃ ያወጣ መንግሥት ሀገሬ እያንሠራራች ነው ካላለ ማን ነው ታዲያ እያንሠራራች ነው የሚለው? የሚጨበጥ የሚዳሰስ ውጤት ነው። ያ ውጤት በእያንዳንዱ ሰው ቤት ውስጥ፤ በእኔ እና በአንቺ ቤት ውስጥ ላይታይ ይችላል። ምክንያቱም የእኛ ሕይወት ዘዬ እሱ አይደለም። የሚነካቸው ሰዎች ግን አሉ።
በዝምድና ባታውቂያቸው፤ በትውውቅ ባታው ቂያቸው በቅርበት ባታውቂያቸው አይመለከተኝም ማለት አትችይም። ለምን የጋራ ሕልም አለንና፤ ናሽናል ኢንተረስት አለን አልና የጋራ ሕልም ካለን የእነርሱ ኑሮ ዘዬ መቀየሩ ባንቺ ኑሮ ውስጥ ኢምፓክት አለው። ኑሯቸው ካልተቀየረ ሌባ ይሆናሉ። ገዳይ ይሆናሉ፤ ምናምን ይሆናሉ። ጥፋት ያመጣሉ ማለት ነው። እያንሰራራን ነው ስንል በኤክስፖርት ብቻ አይደለም።
በርዳታም የመጣው ውጤት ይበል ይቀጥል የሚያስብል አስደማሚ ውጤት ነው። የሚያኮራ ውጤት ነው። ይህንን የሠሩ የኢትዮጵያውያን እጆች በሙሉ የተባረኩ ናቸው። አሳፋሪውን ቀንበር ስላነሱልን አሳፋሪውን ቀንበር ለማንሳት የነበረን ጉጉት እንደሚሳካ ስላሳዩን። አርሶ አደሮቻችን ነጋዴዎቻችን ባለሀብቶቻችን እየጋገሩ የሚያበሉን እናቶቻችን እጃቸው የተባረከ ነው። መጠንከር አለበት ይሄ ሥራ መለመን የለብንም። ለማኝ ሀገር ሉዓላዊነት ብሎ ደረቱን ነፍቶ መናገር አይችልም። ያ እንዲቀየር የጀመርነው ሥራ አስደማሚ ነው። ኢትዮጵያ ከምታንሰራራበት ዘርፍ አንዱ ይሄ ነው። በውጤቱ እጅግ አድርገን ደስታ ይሰማናል። ውጤቱን ጠቅልለን እስክናሸንፍ ድረስ ግን፤ አይናችን እንዲያሸለብ አንፈቅድለትም ገና ነው። አሁንም ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ አለ። እሱ ዜሮ እስከሚሆን የሚያሸልብ ማንኛውም ሰው ያ ያሳከው ሊሸረሸር እንደሚችል ማወቅ አለበት። ዜሮ መሆን አለበት። ደግሞም እናደርገዋለን።
ኢቲቪ ፦ ወደሌላ ጉዳይ ልውሰድዎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ መንግሥትዎ ትኩረት ካደረገባቸውና ከሚሠራባቸው ጉዳዮች አንዱ የትርክት ግንባታ ነው። ለምንድነው በተለየ መልኩ የትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈለገው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ የትርክት ግንባታ ላይ ትኩረት መስጠት እንዴት እንዳስፈለገ ለምን እንዳስፈለገ እንዴት እንደሚሠራ ለማወቅ ራሱ ትርክትን በወጉ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ሰዎች ትርክት ችግር መሆኑን የሚገነዘቡት በብሔር በሃይማኖት ስለምንጨቃጨቅ ከፋፋይ ነገር ስለተነገረን በሚል ብቻ ነው። እሱ አንዱ ነው። እሱ ብቻ ግን አይደለም። ትርክት ማለት በየቀኑ ለልጃችን ምን እንነግረዋለን? እኛ ለራሳችን ምን እንነግረዋለን። ቅድም እንዳነሳሁት ትምህርት ቤት ስንሄድ የሚነገረን ምንድን ነው? እማትችል፤ እማታውቅ እማታከናወን፤ እማይሳካልን፣ ሰነፍ ወይም እገሌ ከእገሌ የምታንስ አይደለም? አይደለም? በየቀኑ የምንሰማው ይሄንን ነው። ያ አላስፈላጊ በውድድር፣ በአሸናፊና ተሸናፊ ሥነ ልቦና የተሞላው የየዕለት ውሏችን የትርክት ውጤት ነው።
ትምህርት ቤት ስንሄድ መምህራኖቻችን ይሄንን ያደርጋሉ። ሌላ የጋራ ቦታም ኳስ መጫወቻ ብንሄድ ጓደኞቻችን ቡል ያደርጉናል። ያሸማቅቀናል። ትርክት እኮ ነው። አንተ ሸፋፋ ነህ፤ አንተ አስቀያሚ ነህ የሚለው ጉዳይ ሁሉ ትርክት ነው። የሰውን ውስጣዊ ሥነ ልቦና እየሰበረው ስለሚሄድ ያ ሰው መጨረሻ ላይ ሙሉ ሆኖ ሙሉ እምነት ያለው እሳቤ ማሰብ ይቸገራል። እንደዚህ ያሉ በተናጠል አጥንት ሰባሪ ንግግሮች ቅስም ሰባሪ ንግግሮች ሕልውና አዋኪ ንግግሮች ተሰናስለው አደገኛ ጎርፍ የሚዘንብባቸው በሚዲያ ሲሆን ነው። አደገኛ ጎርፍ የሚሆኑት በስቴት በተቋም በተደራጀ ኃይል ደግሞ ሲሆን ነው። የአንተ ዘር አንደኛ ነው፤ የእሱ ዘር አይረባም። ያንተ እምነት እንደዚህ ነው የሱ እምነት አይረባም፤ ያንተ የትምህርት ዘርፍ አይረባም የእሱ እንደዚህ ነው የሚባል አማርኛ በጥፊ እንደመምታት በቦክስ እንደመምታት በጥይት እንደመምታት ስለማይታይ ነው እንጂ ውስጣችንን እያደቀቀ የሚሄድ ነገር ነው። አድቃቂ ነው።
ይሄ በብሔሩ ባያስብ በራሱ የማይተማመን በርካታ ሰው ፈጥሯል። በሃይማኖቱ ባይመካና በሃይማኖቱ ሰው ባይሳደብ በራሱ ሙሉ እምነት የማይተማመንና ከማድረግ ይልቅ በመታዘብ የሚያሳልፍ ሰው ፈጥሯል። ስብራቱ በጣም ሰፊ ነው። በትምህርት ሥርዓቱ መታየት አለበት። በሚዲያው መታየት አለበት። በእምነት ተቋማት ስብከት መታየት አለበት። በእያንዳንዱ ቀን የሚዘራው ስብከት ራሱ ኢነርጂ ፕሮቫይድ የሚያደርግ ነው ወይስ ያንን የሚያሳጣ ነው መታየት አለበት። ቤተሰብ ቤት ውስጥ የሚያወራው ወሬ መታየት አለበት። ጓደኞች አብረው ሲውሉ የሚያደርጉት ነገር መታየት አለበት። እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ተሰናስለው ነው እንግዲህ እንደሀገር ያለንን የተስተካከለ ትርክት የሚፈጥሩት።
ግለሰብ የሚሠራበት፤ ማኅበረሰብ የሚሠራበት፤ መሠረታዊው የስሪት ምሰሶ ትርክት ነው። ሰዎች ደሀ ናችሁ፤ ሰዎች ያደጋችሁ የበለፀጋችሁ ናችሁ የሚባለው ትርክት ነው። ሰላም ግጭት በቀዳሚነት (ፕራይመርሊ) ትርክት ነው። አንድ ምሳሌ ላንሳ በአንድ የአፍሪካ ሀገር ከዓመት በፊት በአንድ ዓመት ውስጥ ሰባ ሰባት ሺህ ሰዎች ጥቃት በሚያደርሱ አጥቂዎች አልቀዋል። በየቦታው በሰንጢ ሲገደሉ፤ በጥይት ሲገደሉ እንደኛ ጦርነት ሳይባል ግን በነፍሰ ገዳዮች (በመርደረሮች) ሞተዋል። ሰባ ሰባት ሺህ ሰዎች። አንድ ኢንቨስተር ያን ሀገር በንጽጽር ለኢንቨስትመንት ይሻላል ይመቻል ብሎ ሲቀበልና በትርክቱ ምክንያት ሲያስብና እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር ደግሞ ለኢንቨስትመንት አይመችም ብሎ በትርክት ምክንያት ሲያስብ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ (ፍሎ) ይጎዳል። አበዳሪዎች አናበድርም የሚሉት እኮ ግጭት አለባችሁ፤ ደሃ ናችሁ፤ አትከፍሉም ብለው እኮ ነው። እንጂ የኢትዮጵያ ዕዳ በንጽጽር እዚህ ግባ አይባልም።
አበዳሪዎች አናበድርም የሚሉት አትከፍሉም ብለው ነው እንጂ የኢትዮጵያ ዕዳ በንጽጽር ቢታይ እዚህ ግባ አይባልም። ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከአፍሪካ ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ ሦስተኛ፣ ተብለው የሚደረደሩ ሀገራት ያለባቸው ዕዳ እኛ ካለብን ዕዳ በአስር እና ሃያ ዕጥፍ ይበልጣል። ብዙ በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ያ ዕዳ ወደ እኛ ዕዳ ቢገባ፤ የእነሱ ዕዳ ወደ እኛ ቢገባ ምናልባት እኛ በብዙ እጥፍ ልንበልጣቸው እንችላለን። ዕዳ ቆልለውም ጭምር ነው አንደኛ የሚባሉት። ለምን እሳቤው (ፐርሰፕሽኑ) መክፈል ይችላሉ የሚል ነው። አንቺ መክፈል ትችያለሽ አንተ መክፈል አትችልም የሚል ትርክት ነው።
ትርክት ሲባል የማይነካው ዘውግ የለም። ፊልሞቻችን ተመልከቺ፣ ሙዚቃዎቻችንን ተመልከቺ ብዙ ነገሮቻችን መፈተሽ አለባቸው። እነዚያን ጉዳዮች መፈተሽ ስንችል ግለሰብ ላይ ማኅበረሰብ ላይ ለጋራ ግብ የሚቆም ትውልድ ላይ ትርክት አይተኬ ሚና ይጫወታል። አንድ የሰማሁትን እውነተኛ ታሪክ እንደ ምሳሌ ብጠቀም፤ ምናልባት የትርክትን ጉዳይ ሊገልፀው ይችላል። ምን ያክል ውሸት ምን ያክል የተደራጀ ነገር ሰው እንደሚያዛባ ለማየት ስለሚያግዝ። በአንድ ወቅት በሀገር ፍቅር ትያትር የአንድ ዘመን ትውልድ ነበር። ያ ትውልድ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰው አሁን በሕይወት አለ። ይህንን ስናገር፤ በዚህ ጉዳይ የተሳተፉ ሰዎች በሕይወት ስላሉ ምን እያልኩ እንደሆነ በደንብ ይገባቸዋል።
ሀገር ፍቅር ትያትር አንድ ሰው ኃላፊ ሆኖ ይሾማል። ያ የተሾመ ማናጀር እንደማንኛውም አመራር በእሱ ስር የሚሠሩ ሠራተኞች በሰዓት እንዲገቡና እንዲወጡ ዲስፕሊንድ እንዲሆኑ በሥርዓት ይፈልጋል። የትያትር ሠራተኞች ባሕሪ ደግሞ አንዳንዱ እያመሸ ይፅፋል። አንዳንዱ ሌላ ቦታ ይሠራል። የሥራ ባሕሪው በሰዓት የታጠረ አይደለም። ማታ አምሽተው ጠዋት በሰዓት ሊገቡ ይቸገራሉ። ያንን ነፃነት (ፍለክሰብሊቲ) ደግሞ ኃላፊው መስጠት አልወደደም። ጠዋት ሲገቡ ፈርም ፈርሚ 30 ደቂቃ አሳልፈሃል 40 ደቂቃ አሳልፈሻል በሚል ጭቅጭቅ ጀመረ። እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በሰዓት ግቡ በሰዓት ውጡ የሚለውን ነገር ማሳካት ፈለገ። እናም ሠራተኞች ተቸገሩ፤ እነሱ ማታ ሥራ አለባቸው ያመሻሉ። ከሰውየው ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም።
የትያትር ሠራተኞች ቀላል ሰዎችም አይደሉም። ጭንቅላታቸው ያስባል። የመፍጠር አቅማቸው ከባድ ነው። አንዳንዴ ለመልካም አንዳንዴ ለጥፋት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ለአንድ አፍታ ጥፋት መከሩ። ይህ ሰውዬ ይህንን ግትር አቋም ይዞ ሳያሳብድን በፊት ማሳበድ አለብን አሉ። ተመካከሩና ሥራ ተከፋፈሉ። አንተኛው እዚህ ጋር ጠብቀህ ይህን ትለዋለህ፤ አንቺኛዋ እዚህ ጋር ጠብቀሽ አንተኛው ብለው ሥራ ተከፋፈሉ። ኃላፊው ወደ ቢሮ ሲገባ አንደኛው ቢሮ በር ላይ ጠብቆት ጋሽዬ ምን ነክቶሃል፤ ምን ሆነሃል ሰሞኑን? ብቻህን እያወራህ እኮ ነው የምትሄደው ይለዋል አለቃውን። ‹‹ያምሃል እንዴ፤›› ብሎ ገባ።
ሥራ ቆይቶ በእረፍት ካፍቴሪያ ሲሄድ አንደኛዋ ጠጋ ብላ ወንድሜ ምን ነክቶሃል? ተው እንጂ ለልጆችህ አስብ ብቻህን እኮነው እያወራህ የምትሄደው አለችው። ‹‹ምን ነካሽ ሴትዮ›› ብሎ ጥሏት ተመለሰ። ከሰዓት አንዷ ጠብቃው ረሳኸኝ ዘነጋኸኝ እኔ እኮ ቤተሰብ ነኝ። አውቅሃለሁ፤ ዘመድ ነኝ። አንተ አጥፍተህኝ ነው። እና እዚህ ግቢ ውስጥ በስፋት የሚነገረው ብቻህን እያወራህ እንደምትሄድ ነው። እባክህን ብቻህን እያወራህ አትሂድ፤ ምን ነክቶሃል? አለችው። አሁን ሦስት ሆኑ፤ ቢሮ ገብቶ ማሰብ ጀመረ። ይሄ ነገር ምንድነው እያለ ሰዓት ደርሶ ከሥራ ወጥቶ ወደቤት ሲሄድ፤ አንዱ ጠበቀው። መንገድ ላይ ምን ነክቶሃል ብቻህን እኮ ነው? እያወራህ የምትሄደው አለው።
ከሰውየው ካለፈ በኋላ ይህ ግለሰብ እጁን እያወራጨ እያወራሁ ነው እንዴ የምሄደው ብሎ ተናገረ ድምፅ አወጣ፤ ድምፅ ካወጣ በኋላ ደግሞ አዩኝ እንዴ ብሎ ዞር አለ። በዛ ሂደት ውስጥ የእነሱ መጥፎ እሳቤና ፍላጎት በሰውየው ውስጥ እየሰረፀ ገባ ማለት ነው። እያመነ ሄደ። ይሄ እውነተኛ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገር ፍቅር የሆነ። ሰዎች ተደራጅተው ያልሆነውን ነገር ደጋግመው ነግረው፤ ያልሆነው ሰው እንደሆነ እንዲያስብ የሚያስገድድ ትርክት ማለት ነው። እየቆየ ሲሄድ ሰውየው ላይ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ማሰብ ነው።
በተደጋጋሚ ደግሞ የሚነገር አባባል አለ። አንድ አርሶ አደር በግ ሊሸጥ ከቤቱ በግ ተሸክሞ ይወጣል። እና ሰዎች ይመካከሩና ትንሽ ጉዞ እንደጀመረ አንደኛው ጋሽዬ ምን ነክቶህ ነው? ውሻ ተሸክመህ የምትሄደው? ይለዋል። ያምሐል እንዴ በግ ነው ብሎት ያልፋል። ትንሽ እልፍ እንዳለ አንደኛው ጋሽዬ ምን ነክቶሃል ውሻ እኮነው የተሸከምከው ይለዋል። ምን ነካህ በግ የእኔ በግ ነው ለገበያ ነው የማወጣው ይለዋል። ገበያ አካባቢ ሲቃረብ አንደኛውም ምን ሆነዋል ውሻ ተሸክመው የሚንቀሳቀሱት ይለዋል። ይህን ጊዜ ሰውየው ተደጋገመበትና የራሱን በግ ውሻ ነው ብሎ አውርዶ ጣለው። ያለንን እውነት የታጠቅነውን እውነት የምናውቀውን እውነት የሚያስጥል የድግግሞሽ ውሸት ሲፈጠር፤ የኛን ቁመና የኛን አቋም የኛን ቦታ የኛን ሁኔታ ይቀይረዋል። ለዚህ ነው ትርክት አደገኛ ነገር ነው፤ ግለሰብን ማኅበረሰብን ሊጎዳ ይችላል። ጥንቃቄ ያስፈልገዋል በተለይ ዘር ሃይማኖት እየተባለ በሚነገርበት ሀገር ውስጥ ደግሞ እንደዚህ አይነት ከፋፋይ ጉዳይ ካለ ጥፋት ያመጣል። መጫረስ ያመጣል፤ ሊገራ ሊታረም ይገባዋል የሚባለው።
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ንቅል ልሂቃን፤ ከፋፋይ የሆነ ትርክት እያሰረጹ፤ ትውልድ በትውልድ ላይ ሰው፤ በሰው ላይ ዜጋ በዜጋ ላይ ተባብሮ ልማትና ብልፅግናን እንዳያመጣ እርስ በርስ እንዲጠራጠር እንዲጠፋፋ መንገድ እየከፈቱ ነው። እነሱ የዜሮ ድምር ጨዋታቸውን በሕዝብ ላይ ሲያደርጉት ያን የሚገዛ ሰው ደግሞ እየተበራከተ ሲሄድ እርስ በርሳችን ሊያጠፋፋን ይችላል። ለዚህ ነው ልጆቻቸን ላይ ከመሠረቱ ከትምህርት ጀምሮ ከታችኛው ጀምሮ ልንሠራባቸው ይገባል። ሚዲያዎቻችን ድራማዎቻችን ፊልሞቻችን ፕሮጀክት የሚያደርጉት መሰብሰብን አንድነትን አብሮነትን መሆን አለበት። ያ ካልሆነ ጥፋት ያመጣል የምንለው።
ለምሳሌ በየሰፈሩ ኳስሜዳ እንሠራለን፤ ለምንድነው የምንሠራው፤ ሰብሰብ ብለው እንደ አብሮ አደግ፤ እንደ ጓደኛ የሚተያዩበት ባህል እየጠፋ ስለሆነ፤ እንዳይጠፋ እኮ ነው። የከተማ ልጆች የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደድሮው አይደለም እየቀነሰ መጥቷል። አብሮ አደጌ ነው፤ ወንድሜ ነው ብለው እንዲተሳሰቡ ለማድረግ ነው። በየቦታው አንፊ፣ የጋራ ስፖርት መሥሪያ፣ ፓርኮች እነዚህ ሁሉ ሰው ከቋንቋ ባሻገር፣ ከእምነት ባሻገር፣ ከፆታ ባሻገር፣ ከተወለደበት ሰፈር ባሻገር በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር አብሮ ወጥቶ ገብቶ ደስታን፤ አብሮ ወጥቶ ገብቶ መልካም እውቀትን ሊጋራ የሚያስችል ዓውድ መፍጠር አስፈላጊ ስለሆነ ነው።
ሚዲያዎቻችንም ከዛ አንጻር ከተገሩ፤ ሰዎቻችንም ከነቁ፤ ትርክት እየተገራ ከሄደ ብዙ ሀገራት ላይ እንደምናየው የተሰበሰበ ማኅበረሰብ መፍጠር ይቻላል። በብዙ ሀገራት የፖለቲካ ልዩነት አለ፤ በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ግን ሲያወላዱ አይታይም ፤ ብዙ ሀገራት ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነት ልዩነቶች አሉ፤ እንደእኛ ግን አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ፤ የሁሉ ነገር ትኩረት እና መነሻ መዳረሻ እሱ ብቻ ግን አይሆንም፤ ያንን ለመግራት ትርክት ያስፈልጋል።
ትርክቱ ደግሞ የሚሰበስበን፣ የሚያስማማን፣ የሚያቀራርበን ከልመና የሚያወጣን፣ ከድህነት የሚያወጣን፣ ከችግር የሚያወጣን፤ ተቋም እንድንገነባ የሚያደርገን እኔ ከአንቺ ጋር አንቺ ከእርሱ ጋር እርሱ ከእርሷ ጋር ለመኖር የሚያስችል ዓውድ የሚፈጥር፤ የተሳሳተ መረጃ፤ የተሳሳተ ወሬ ሆኖ ከሚከፋፍለን መልካሙን ነገር ዘርተን፣ መልካም ትውልድ መፍጠር አለብን የሚል እሳቤ ነው ያለው።
ትርክት ካልተገነባ በቀር ኤክስፖርቱ አይቀጥልም፣ ትርክት ካልተገነባ በቀር ቅድም ያነሳነው ለማኝነት አይጠፋም፣ ካልተገነባ በቀር ሉዓላዊነቷ የተከበረ፣ የገዘፈች ኢትዮጵያ መፍጠር አይቻልም። ኢትዮጵያ ገዝፋ ጸንታ ለልጆቻችን ማሸጋገር እንድንችል ቀናነት ያለበት፣ ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ፣ የጋራ አብሮነትን ታሳቢ ያደረገ፣ ክብራችንን/ዲግኒቲያችንን ያልደፈጠጠ፣ ያንንም ያከበረ የትርክት ሥርዓት መከተል ያስፈልጋል።
ያንን ካደረግን ነው የተሟላ ብልፅግና ልናረጋግጥ የምንችለው በሚል እሳቤ ነው ትርክት ላይ አበክረን የምንሠራው፣ ግን ዘርፉ ብዙ ነው በትምህርቱ፣ በጤናውም ፣ በሚዲያውም፣ በቲያትሩም፤ በሁሉም ዘርፍ ሊሠራ ሚገባው ሥራ እንደሆነ ደግሞ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።
ኢቲቪ ፦ እንዳሉት ትርክት ትውልድን የሚሻገር ጭምር ነውና ትውልድ ላይ ስናነሳ ተተኪነትንም አብረን የምናነሳው ጉዳይ ነው የሚሆነው፤ ምክንያቱም የፖለቲካ ሽግግር በዋናነት ተተኪ ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው እና አያይዘው እስኪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በተለይ የፖለቲካ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ተተኪዎችን በማፍራት ረገድ ወጣቶች ወደአመራር እንዲመጡ ምን ሥራዎች እየተከወኑ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ እስካሁን የገለጽኳቸው እያመጣናቸው ያሉ ውጤቶች በበቂ ደረጃ ተኪ አመራሮች ማፍራት ካልቻልን የአመራር መዛነፍ አለ፣ የጉዞ መደነቃቀፍ አለ፤ ውጤቱም ከግብ አይደርስም ማለት ነው። የአንድ አመራር መለኪያው በበቂ ተተኪዎች የማዘጋጀት እና የመፍጠር አቅሙም ጭምር ነው። ወጣቶችን ማዘጋጀት በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ በተግባር እኛ እናውቀዋለን።
ወጣት ሆነን ሃሳብ በምናነሳባቸው ጊዜዎች የሚደርሱብንን ኩርኩሞች እናውቃቸዋለን፤ ወጣት ውስጥ ያለ ኢነርጂ፣ ጉልበት ባላቸው፤ ብልሃት ባላቸው ሰዎች ቢታገዝ ምን አይነት ፍሬ እንደሚያፈራም እናውቃለን። በዚህ ምክንያት የወይፈኑን ጉልበት እና የበሬውን ብልሃት ደምረን ነው ያለውን መከራ ማረስ የምንፈልገው። መከራው መታረስ አለበት፣ መከራውን ለማረስ ጉልበት ያስፈልጋል ፤ መከራውን ለማረስ ግን ብልሃትም ያስፈልጋል። እነዚህን አቀናጅተን ነው የምናርሰው።
ይህንን ስናደርግ በብልፅግና እንደ ፓርቲ የወሰድነው በርከት ያሉ ወጣቶች በመንግሥትም በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥም ገብተው፤ መግባት በቂ ስላልሆነ፤ በየጊዜው ሠልጥነው ኢምፓወር ደግሞ ተደርገው ሥራ ተሰጥቷቸው እየተለማመዱ ተኪ ማፍራት አለብን የሚል ዝግጅት በስፋት እየሠራን ነው ያለ ነው። እኔ የምመራው ካቢኔ ከግማሽ በላይ ወጣት ነው።
ብዙዎቹ ትላንትና ዩኒቨርሲቲ የነበሩ፤ መጥተው በተለያየ ደረጃ ሠርተው፤ በተግባር ተምረው ዊስደም (ጥበብ) ካላቸው ሰዎች ጋር አብረው ሠርተው አሁን ትልልቅ ኃለፊነት ይዘው እየሠሩ ይገኛሉ። እዚህ ጋር ሁለት ችግር ነው ያለው። ብዙ ሰዎች ከፍተን ለማስገባት ሞክረናል ለምሳሌ አንቺ ከውጭ ስትመጪ፤ ከአሜሪካ ስትመጪ የመጀመሪያው ሃሳብሽ አመራር መዘጋጀት አለበት፤ እውቀት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፤ ወጣቶች ያስፈልጋሉ ትያለሽ ትክክል ነው፤ የመጣሽው ግን ራስሽን ሾመሽ ነው።
አንቺ የመጣሽው የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ለመሆን፤ የውጭ ጉዳይ ለመሆን ነው ወይም መከላከያ ለመሆን ነው፤ ወስነሻል፤ ያ የወሰንሽው ነገር ካልተሰጠሽ ማገልገል ውስጥሽ ስለሌለ አኩርፈሽ ነው የምትሄጂው። ብዙዎች አኩርፈው የሄዱት በዚህ ነው። ራሳቸውን ሹመው ከመጡበት ቦታ ውጪ ማገልገል ያለ አይመስላቸውም። ወረድ ብሎ ለማገልገል ብዙ ሰው ዝግጁ አይደለም፤ ወረድ ብለን ካላገለገልን ደግሞ መንግሥት ምን እንደሆነ የመንግሥት ሲስተም ምን እንደሆነ አናውቃቸውም። ታች ነው ብዙ ጣጣ ያለው፤ እርሱን እያየን ስንሄድ ነው መፍትሔ አፍላቂ የምንሆነው።
ያንን በማይጥስ መንገድ የ60ዎቹ ትውልዶች፤ በደርግም፤ በኢሕአዴግም እስከ ብልፅግና መጀመሪያ አካባቢ፤ ከሞላ ጎደል የኢትዮጵያ ፖለቲካ አድራጊ ፈጣሪ ሠሪዎች የ60ው ትውልድ ነው። በ60ዎቹ ያሉ ትውልዶች ናቸው አጀንዳ ፈጣሪም ሠሪም፤ ይሄ ጉዳይ ምን ውጤት እንዳመጣ ደግሞ አይተነዋል። በሁለቱም መንግሥታት ዘመን አይተነዋል። ስለዚህ አሁን ደረጃ በደረጃ ጥበብን ሳናጣ ተኪ ኃይል ሀገር የሚያሸጋግር ኃይል መፍጠር አለብን በሚል በታቀደ መንገድ ነው እየሠራን ያለነው።
በእርግጠኝነት ከእኛ የተሻለ ውጤት የሚያመጡ ሰዎች እየተፈጠሩ እንዳሉ ይሰማኛል። አመራር ሲፈጠር መጀመሪያ ሰውየው መወሰን አለበት፤ ሕልም ከሌለው ስለተማረ ብቻ፤ ትጋት ከሌለው፤ ስለተማረ ብቻ ማለፍ በሚገባው መንገድ ማለፍ ካልፈቀደ፤ ስለተማረ ብቻ በቂ መሪ ሊወጣው አይችልም። መሪነት የእውቀት ብቻ አይደለም የክህሎት እና የጥበብ ጭምር ነው።
ያ ክህሎት እና ጥበብ ደግሞ የሚገኘው ወጥቶ በመውረድ ነው ከታች ጀምሮ አመለካከቱ የቀና፣ ለማገልገል የተዘጋጀ ስርቆት የሚጠየፍ፤ በልፋት በጥራት ውጤት የሚያመጣ በድካም ውስጥ እያበጠ እያደገ እንደሚሄድ የሚያምን፣ ሳይደክም አልጋ በአልጋ የሆነ ነገር እንደሌለ የሚያስብ ከሆነ በጣም በርካታ ወጣት ሊሠሩ የሚችሉ ወጣቶች ያሉበት መንግሥት እና ፓርቲ ነው። በእርግጠኝነት ብዙ ሰዎች ዕድል እያገኙ ኢምፓወር እየተደረጉ፤ እያበላሹ እየተገሰጹ፣ እየተመከሩ፣ እየሠለጠኑ ስለሆነ፤ ኢትዮጵያ ወደፊት የመሪ ጉዳይ ብዙ ያሳስባታል ብዬ አልሰጋም ።
ኢቲቪ ፦ ወደሌላ ጉዳያችን ሻገር እንበል እስኪ በተለይ የውጪ ግንኙነታችንን እስኪ እንፈትሽ ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት አዳዲስ ጉዳዮች የሰማንበት ነበር በውጭ ግንኙነቱ ሒደት እና በዲፕሎማሲው እና በውጭ ግንኙነት ረገድ ባለፉት ሰባት ዓመታት እንደመንግሥት ያሳኳቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ በውጭ ያለውን ግንኙነት በቅጡ ለመረዳት እና ለማወቅ መጀመሪያ ዓለም ያለችበትን ነገር መገንዘብ ያስፈልጋል። ዓለም በከፍተኛ መወናበድ ውስጥ ነው ያለችው፤ ምንም ነገር የሚጨበጥ የሚዳሰስ የለም ፍሉድ ነው። በየቀኑ የሚወጡ ዜናዎች የዓለምን ነገር በተሟላ ለመተንበይ የሚያግዙ አይደሉም። ብዙ አዳዲስ ዜናዎች፤ ዛሬ ፍቅር ነገ ጸብ፤ ዛሬ ኅብረት ነገ መበተን የሚታይበት ዓለም ነው።
በሽታው፤ ጦርነቱ ተደማምሮ አጠቃላይ የዓለም እድገት ካለፉት አስርት ዓመታት በንጽጽር ቀንሷል። አጠቃላይ የዓለም እድገት ቀንሷል፤ ራሱ ፍሎዲቲው ያለው ችግር እድገት እንዲቀንስ አድርጓል። በዓለም ላይ በሁሉም ዓለም ማለት ይቻላል በንጽጽር ግሽበት ጨምሯል። ድሮ ከነበረው ግሽበት የኑሮ ውድነት ጨምሯል።
በሁሉም ዓለም ማለት ይቻላል አቅርቦት ሠንሠለት ተመቷል፤ የንግድ ሥርዓት ተጎድቷል። የመርከብ ንግድ እንኳን ብናይ በዘንድሮው ዓመት 40 በመቶ ቀንሷል ። ግማሹ ግጭት ነው፣ ግማሹ ታሪፍ ነው፣ ግማሹ ምክንያት አለው ግን ቀንሷል ። በዓለም ላይ የብድር ጫና በጣም ከፍ ብሏል፤ መንግሥታት ያለባቸውን ብድር ለመክፈል ተችግረዋል፤ ብዙዎቹ።
አብዛኛው የአፍሪካ ሀገርን ብድርን የሚቋቋመው ከዚህ ተበድሮ እዚህ እየከፈለ ነው። ጫናው በጣም ከፍተኛ ነው የበጀት ጉድለት በዓለም ደረጃ በጣም አድጓል። የበጀት ጉድለት የለባቸውም የሚባሉ ሀገራት በጣም ጥቂት ናቸው፤ አብዛኛው በጀት ጉድለት የሚያስተናግድ ሀገር ነው። ምን ማለት ነው የራሱ ጉድለት ስላለበት ያንቺን ጉድለት አያይልሽም ማለት ነው።
ግጭቶች ግጭት ከዚህ ቀደም አፍሪካ ላይ እንደ ባህል እንደ ወግ እንደ ልማድ ተወስዶ ነበር። በየጊዜው የሚሰማ ጉዳይ ነው፤ እኛ ተወልደን ካደግን ጀምሮ ግን በምዕራቡ ዓለም ግጭት አልሰማንም፤ አሁን በምዕራቡ ዓለም ግጭት አለ። ግጭት በሆነ አሕጉር ውስጥ ታጥሮ የቀረ ጉዳይ አይደለም ሁሉም ጋር የሚታይ ጉዳይ ሆኗል።
ይሄ ነው የዓለም ሁኔታ ግጭት ያለበት፤ እድገት የሌለበት፤ ኢንፍሌሽን የበዛበት፤ በጀት ጉድለቱ፣ ዕዳው፤ ግንኙነቱ፣ የንግድ ሥርዓቱ የተረበሸ ዓለም ነው። እኛ ከዚያ በፊት እንከተለው የነበረው አፕሮች ዘርፈ ብዙ ነው። ጠቅለል አድርጎ ሲነሳ ግን ስሪ ፒ ይባላል። አንደኛ ፖለቲካል ነው፣ እኛ እና ኤክስ እኛ እና ዋይ ያለን ግንኙነት ፖለቲካል ነው። ሁለተኛው ፕሮሰስ (ሂደት) ነው። ጽፌ ነበር መልሶልኛል፣ ደውሎ ነበር ደውሎልኛል፣ አግኝቼው ነበር አግኝቶኛል፣ ጎብኝቶኝ ነበር ጎብኝቼዋለሁ ዓይነት ሂደት ነው። ሦስተኛው ፕሮቶኮል ነው። ውክልና ነው፤ ዩኤን ጋር አልተገኘንም፤ እንትን ጋር አልተገኘንም፤ እንትን ጋር አልተናገርንም ነው። ሄደንም፣ አግኝተንም፣ ተናግረንም፣ ለኢትዮጵያ ምን አመጣን የሚል ነገር የለውም።
አውትካም ሌቭል ኢቫሉዌት (በውጤት ደረጃ አይመዝንም) አያደርግም ሂደት ነው። ፖለቲካል ብቻ ከሆነ እና ቢዝነሱ ከሌለ፤ ፕሮሰስ ብቻ ከሆነ እና አውትካም ሌቭል (በውጤት ደረጃ)፣ የማይታይ ከሆነ፣ ፕሮቶኮል ብቻ ከሆነ እና ሀገር የምትገለጸው በፕሮቶኮል ብቻ ከሆነ ውጤት የለውም፤ መቀየር አለበት ።
ይሄ ዓውድ መቀየር አለበት፤ እያንዳንዷ ነገር ከብሔራዊ ጥቅም አንጻር መመዘን አለባት የሚል ውሳኔ ነበርን፤ ፖሊሲያችንን ቀይረናል፤ ጎረቤት ላይ የሚያተኩር፤ የንግድ ሥርዓት የሚያሰፋ፤ ወዳጅ የሚያበራክት እንዲሆን አድርገን ለመሥራት በአራት ኤ ነው የከፈልነው። የመጀመሪያው ኤ አክቲቭ ነው ያልነው።
አክቲቭ ማለት ዓለም እየተወናበደ ነው ያለው፤ የነቃ ግን ደግሞ ገለልተኛ መሆን የማይስት ዲፕሎማሲ፤ መንቃት አለበት፤ ንቁ ሆኖ መከታተል አለበት። በየቀኑ ስለሚወነባበድ አንድ ቀን ብንዘናጋ ያልፈናል። ነቅተን መጠበቅ አለብን፤ ግን ደግሞ ገለልተኛ መሆን አለብን ተለጣፊ መሆን የለብንም፤ ንቁ ገለልተኛ የሚለው አክቲቫል ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ኦልተርኔቲቭ ማበራከት፤ አለብን ኤክስ ወዳጃችን ስለሆነ በቃ ሳይሆን ከየአሕጉሩ፤ ከየመንደሩ ሳንንቅ፣ ሳናራክስ የልብ ወዳጆች፤ የኢትዮጵያ ወዳጆች ማፍራት አለብን። በጥቅሉ ያለው እንደተጠበቀ ሆኖ። ግን በየቦታው ምስጢር የሚያጋሩን ችግር የሚጋሩን፣ ደስታ የሚጋሩን፤ ሁነኛ ወዳጆች እንደ ሀገር እንደመንግሥት እየፈጠርን መሄድ አለብን። ያ ያለው ውጤት በብዙ ስላየነው።
ሦስተኛው ገቢር ነበብ መሆን አለበት። አዳፕቲቭ መሆን አለበት ብዙ የሚቀያየር ነገር ስላለ ስታስቲክ በሆነ መንገድ አንዴ ያሰብነውን እቅድ ፍላጎት በዘላቂነት ልናሳካው አንችልም። ገቢር ነበብ መሆን አለብን ስንል አዳፕቲቭ መሆን አለብን ስንል ከርዕዮተ ዓለም እስረኛ የፀዳ መሆን አለበት። ከሆነ እሳቤ የፀዳ መሆን አለበት። ለምሳሌ ሚድል ኢስት አያስፈልጉንም እነርሱ እንዲህ ስለሆኑ አንልም።
ከእነርሱም የንግድ ትስስር አምጥተን ውጤት የምናመጣ ከሆነ እንወዳጃቸዋለን፤ ከዓረቡ በዓለም ወዳጅ ስለሆንን እስራኤል አታስፈልገንም አንልም፤ እስራኤልም ወዳጃችን ናት፣ ታስፈልገናለች፤ ዓረቡም ያስፈልገናል። እነርሱ መካከል ያለ ቁርሾ ካለ ከቻልን እናስታርቃለን፤ ካልቻልን ግን ገለልተኞች ነን በአንዱ አንታጠርም።
ገቢር ነበብ የሚለው ምንድነው፤ ከዚኛው የምናገኘውን ከዚህኛው ስለማናገኝ ይሄኛው ያለው ኩዋሊቲ ይሄኛው የለውም፤ እኛ ፕራግማቲክ ነን፣ የምናገኘውን ነገር በሚለይ መንገድ ነው የምንሄደው። የመጨረሻው ግን አጀንዳ ነው። ዓለም ዲፕሎማሲው በአብዛኛው አጀንዳ ተቀባይ ነው፤ ኩክ ይደረጋል ይነገራል፤ በድግግም ይሰበካል እሱ ነው አጀንዳው ።
ኢትዮጵያ አጀንዳ ተቀባይ ከመሆን ወጥታ አስፈላጊ በሆነ ጉዳይ አጀንዳ ሰጪ መሆን አለባት። የሰው አጀንዳ ብቻ ኢንተርቴን የምናደርግ መሆን የለብንም ። በዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያስፈልጉን ጉዳዮች ለመሳተፍ አሰርቲቭ በሆነ መንገድ ቦልድ በሆነ መንገድ ዲማንድ ማድረግ አለብን። ምንም የምንሽኮረመምበት ምክንያት የለም። ትልቅ ሀገር ነውም፤ ምንም ጥያቄ የለውም ከዓለም 11 ትላልቅ ሕዝብ ካላቸው ሀገሮች አንዱ ነው ኢትዮጵያ ነች።
የሺህ ዓመታት ታሪክ ያለው ሀገር ነው ኢትዮጵያ ቢበረታ እና መባላቱን ቢያቆም መብላት ብቻ ሳሆን ማብላት የሚችል ሀገር ነው ኢትዮጵያ፤ በምን ሂሳብ ነው አራክሰው እንዲያዩ የምንፈቅድላቸው፤ ደግሞ አራክሰው ያዩናል እንጂ በዛ ልክ የጎደለ ጓዳችን አይሆኑልንም። ይሄን እንደሀገር ማስተናገድ የለብንም የሚሉ አቋሞች ወስደን፤ በአራቱ ኤ ከፍለን፣ አክቲቭ መሆን አለብን፣ ኦልተርኔቲቭ ማበራከት አለብን፣ አዳፕቲቭ መሆን አለብን፣ አጀንዳ መፍጠር አለብን፤ ዲፕሎማሲያችን አሰርቲቭ መሆን አለበት ቦልድ መሆን አለበት፤ ወዳጅን የለየ መሆን አለበት ብለን ነው የጀመርነው።
በዚህ ነው እንግዲህ በርከት ያሉ ስትራቴጂክ አጋር (allwaither) የሚባሉ ወዳጆች በንግግር ብቻ ሳይሆን በፍርርም ደረጃ የደረስነው፣ በከፍታም በዝቅታም ፤ በሙቀትም በቅዝቃዜም አብረን እንቆማለን የሚል ነው ( allwaither) ማለት በከፍታም በዝቅታም በሙቀትም በቅዝቃዜም አብረን እንቆማለን የሚል ነው ኦልዌዘር ማለት። በዚያ ሌቭል አፍርተናል ወዳጆች። በብዙ መድረኮች ለሸምጋይነት የምንፈለግ ሆነናል። ይህ አንዳንድ አጉራ ዘለል አማተር ፖለቲከኞች እንደሚያወሩት ሳይሆን ኢትዮጵያ የተከበረች አገር ናት፤ በዓለም መድረክ ላይ። በዚያው ልክ በብዙ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንድትሳተፍ የምትፈለግ ሀገር ናት። የብሪክስ አባል ሀገር ናት፡ የብሪክስ አባል የሆንነው ዝም ብሎ በዋዛ አይደለም፤ ቅድም ባልኩት መንገድ ነው።
እኛ ደቡብ አፍሪካ ስንሄድ፤ የብሪክስ አባል እንደምንሆን ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት አንድም የብሪክስ አባላት አልወሰኑም። ኢትዮጵያን አለማስገባት ያለውን ጉዳት ካስገነዘብን በኋላ ከሚድ ናይት በኋላ ነው ኢትዮጵያ ገብታ ጠዋት የታወጀው ማለት ነው። ከገባች በኋላስ ዝም ብላ አባል አይደለችም። አጀንዳ ያላት ሀገር ናት ኢትዮጵያ። በቅርቡ ብራዚል ላይ የሚኒስትሮች ስብሰባ ነበር ብሪክስን በሚመለከት እዛ ውስጥ ጠንከር ያሉ ሀሳቦች ካላቸው እና እባካችሁ ይሄን ጉዳይ ብትተዉልን፣ ብታናግሩልን ከሚባሉ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
እኔ አልሄድኩም የሄደው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነው ግን ጠንከር ያለ አቋም ስለነበረን ወደ እኔ ሽምግልና የሚልኩ ሰዎች አሉ በዚህ ጉዳይ ብትለሳለሱ፣ ይሄን ብትተዉ፣ ይሄን ብትፈጥሩ የሚሉ ሀገራት ልከውለኛል። ዝም ብሎ አባል አይደለንም አጀንዳ ያለን አጀንዳችንን አሰርቲቭ በሆነ መንገድ የምናነሳ፣ አርጊው የምናደርግ፣ ፍላጎቶቻችንን ለማሳካት የምንጥር ሆነን ነው የተገኘነው።
ከዚያ በተረፈ ግን ኢትዮጵያውያን ቢማሩ፤ የወደፊት አመራሮች ቢማሩ፤ ትላንትና በብዙ ሚስ አድርገናል ብዬ ከማስብበት ነገር አንዱ የልብ ወዳጆች ማፍራት አለመቻል ነው። ዝም ብሎ ለፕሮቶኮል ተገናኝቶ የተከበሩ፣ የተከበሩ መባባል እና ወዳጅ ማፍራት ለየቅል ነው። ዛሬ እኛ በሁሉም አሕጉራት የልብ ወዳጆች አሉን። ምስጢር የሚያጋሩን፣ ትሬንድ ከእኛ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ካዩ ሰው ልከው ይሄ ጉዳይ አለ አስተውላችኋል ወይ የሚሉን፣ መረጃ የሚሰጡን፣ በችግር የሚደግፉን፣ በትጥቅ የሚደግፉን፣ በሥልጠና የሚደግፉን የልብ ወዳጆች አሉን። እንደዚህ ዓይነት ወዳጅነት ሲፈጠር ዲፕሎማሲው ናሽናል ኢንተረስትን እየጠበቀ እና እያረጋገጠ እንዲሄድ በእጅጉ ያግዛል። እና ባለፉት ሰባት ዓመታት በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በሩቅ ምስራቅ፣ በሰሜን አሜሪካ ጠንካራ ወዳጆች የፈጠርንበት፣ የምናምናቸው፣ የሚያምኑን፣ የምናውቃቸው፣ የሚያውቁን፣ የምንረዳቸው፣ የሚረዱን ሰዎች የተፈጠሩበት፤ ከብዙዎቹ ጋር በሳምንት ሁለት ሦስቴ እንደቅርብ የሥራ ጓደኛሞች የምንነጋገርበት፣ የምንጻጻፍበት፣ ምስጢር የምንጋራበት፣ ችግርን የምንጋራበት፣ ሃሳብ የምንጋራበት እጅግ የተሻለ እና ያደገ የዲፕሎማቲክ ዓውድ ተፈጥሯል። ይሄ ግን ከብዙ ጉዳይ ጋር ይያያዛል።
ልመናን ሳናቋርጥ ምንም ወዳጅ ብንፈጥር የኤክስፖርት አቅማችን አድጎ ዕዳ መክፈልን ችግር ሳናደርግ፤ ምንም ወዳጅ ብንፈጥር አይዘልቅምና እድገቱን እያረጋገጥን ልመና እያቋረጥን ዕዳችንን በደንብ ከፍለን ከዕዳ ጣጣ ወጥተን ይሄ አሁን የያዝንውን አቋም ከያዝን ግን የኢትዮጵያ የወደፊት የዲፕሎማሲ መድረክ ምንም ጥርጥር የለውም በልኳ ይሆናል። እስካሁን ከልኳ በጣም የወረደ ነው። በመላላክ የሠራናቸው ሥራዎች አሉ፣ ግን እንደሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ ቆመን የሠራናቸው ሥራዎች ውስን ናቸው። ከመላላክ የወጣ፣ አጀንዳ ከመቀበል የወጣ የራሱን አጀንዳ ይዞ በማያስፈልግ ጉዳይ ኖ በሚያስፈልግ ጉዳይ ላይ ደግሞ የስ ብሎ የሚሄድ ቁመና እየፈጠርን ነው ያለነው። በዚህ መንገድ ነው ዲፕሎማሲን እኔ የምገመግመው።
ኢቲቪ ፦ እርሶ እንደመሪ የመሪ ዲፕሎማሲ ላይ በጣም ጠንካራ እንቅስቃሴ እንዳለዎት በብዙ መልኩ ይገለፃል። ከዛ ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ለምሳሌ የፋይናንስ መዋቅርን በመሞገት የአፍሪካ ኅብረት የዩኤን ተሳትፎን በመሞገት ረገድ በመሪነት የሚወጧቸው ሂደቶች አሉ። ምን ያህል ዲፕሎማሲው ደግፎዎታል? የእርስዎን ተሳትፎ እዛ ላይ ማየት የሚያስፈልግ ስለመሰለኝ ነው ይህንን ጥያቄ ያነሳሁት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ ቅድም እንዳነሳሁት ነው ተቋም ስብራታችን ነው። ተቋም መገንባት አለብን። በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ውስጥ ልምድ ያካበቱ፤ ዊዝደም ያላቸው ሰዎች አሉ። ምንም ጥያቄ የለውም። ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ልምድ ያላቸው ሰዎች አሉ። ያ ልምድ ግን መገራት አለበት። ከፖለቲካ፣ ከፕሮሰስ፣ ከፕሮቶኮል ወጥቶ ፍሬአማ እንዲሆን መገራት አለበት። እንደተቋም እውነት ለመናገር ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ አንዱ መስክ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።
አሁን ሪፎርም ጀምረናል፣ ወጣት አመራሮች አምጥተናል። በርከት ያለ ወጣት፣ መቶ ገደማ ወጣት ከዩኒቨርስቲ አወዳድረን አስገብተናል፣ ሥልጠና እየሰጠን ነው። በተለያየ ዓለም ሥልጠና እየሰጠን ነው። በአረብኛ፣ በቻይንኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በተለያየ ቋንቋ የሚሠሩ ወጣቶች እያበራከትን ነው። በሚቀጥሉት ሁለት ሦስት ዓመታት ተቋሙ የምንፈልገውን ቅርጽ እና ቁመና እንደሚይዝ ይታመናል። እስካሁን ባለው ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ አሮጌ አቁማዳ አዲሱን ወይን ለመሸከም ያለው ዝግጁነት የተቸገረ ከሆነ በነበረው መንገድ የሚጓዝ ከሆነ ተቋሙ አለ፤ ፍላጎቱ አለ፤ ግን የሚከወነው ነገር ውስን ሊሆን ይችላል። አሁን ለውጥ ተጀምሯል። ውጤቱ በአንድ ጀምበር የሚታይ ባይሆንም በእርግጠኝነት በሚቀጥሉት ዓመታት ውጪ ጉዳይ ጠንካራ ኢንስቲትዩሽን እንደሚሆን እምነት አለ።
እኔን በሚመለከት እኔ ያው ፍላጎት፣ ግብ፣ የማስበውን ነገር አነጣጥሬ ነው የምሠራው ማንኛውንም ነገር። እርሻ ላይ ስንዴ ከፈለኩ ስንዴ ላይ ነው የምሠራው። ከተማ ላይ ኮሪዶር ከፈለኩ ኮሪዶር ነው የምሠራው። ዲፕሎማሲውም እንደዚሁ ነው። ዝም ብሎ በገፍ በጅምላ የሚባል እንቅስቃሴ እምብዛም አልደግፍም። ውጤት ማግኘቴን አረጋግጬ ነው የምንቀሳቀሰው። በዚያ መንገድ ከሞላ ጎደል የተሳካ ቆይታ ነበረኝ፣ ብዙ ተምሬበታለሁ፣ ብዙ ወዳጅ አፍርቼበታለሁ፣ ብዙ ስለዓለም ተገንዝቤበታለሁ፣ ገና ብዙ መማር የሚገባኝ ነገር እንዳለ አውቃለሁ። እኔም ጓደኞቼም ተጋግዘን የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ወደሚቀጥለው ደረጃ እንደምናሸጋግር ሙሉ እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም