የቤት እንስሳት እንደአፈጣጠራቸው ባህሪያቸውም ይለያያሉ፡፡ የሚሰጡትም አገልግሎትም እንዲሁ ይለያያል፡፡ ለአብነትም በጥቂት ሀጋራት ካልሆነ በስተቀር አህያ በአብዛኛው ለጭነት አገልግሎት እንጂ ለምግብነት አይውልም፡፡ በሬ በተለይ በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ለእርሻ ስራ የሚጠቀም ሲሆን፣ ስጋውም ለምግብነት ያገለግላል። የበሬው ቆዳና ሌሎች ተረፈ ምርቶችም ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች ይውላሉ፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን በሬ ሌላ የሚሰጠው አገልግሎት የለም፡፡ በፈረንሳይ ሀገር በአነስተኛ የከብቶች እርባታ ማዕከል የተወለደው አስቶን የተሰኘው ጥጃ ሲያድግ ልክ እንደ ሌሎቹ በሬዎች ሁሉ ታርዶ ስጋው ለምግብነት እንዲውል የታሰበ ቢሆንም፣ ምስጋና ለአንዲት ፈረስ አስልጣኝ ከእርድ ተርፏል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ ፅፏል፡፡
በሬው ከሌሎች በሬዎች በተለየ መልኩ ከእርድ ያመለጠበት ሁኔታ ግን ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ሳቢን ሩዋስ የተሰኘችው በፈረንሳይ የስትራሰበርግ ግዛት ነዋሪ ከሃያ ዓመታት በላይ አብሯት ከቆየው ፈረስ ከተለያየች ወዲህ የእርሱን ምትክ ሳታገኝ ትኖራለች፡፡
በዚህ ፋንታም በምንትኖርበት አካባቢ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ አነስተኛ የከብቶች እርባታ ማዕከል በሚገኙ ላሞች ላይ አይኗን ትጥላለች፡ ፡ ከላሞቹ መካከል አንዷ እርጉዝ ነበረች፡፡ ከዚች ላም ጋር ያላት ቅርርብም በተለየ መልኩ በየጊዜው እየጨመረ ይመጣል፡፡ በዚህ የተነሳም ላሚቱ ገና እርጉዝ እያለች ጥጃው የእርሷን ድምፅ ይሰማ እንደነበር ታምናለች፡፡ ጥጃው ከተወለደ በኋላ እርሷ በሄደችበት ሁሉ ሲከታላትየቆየበትን ሁኔታም ለዚህ እንደ ማረጋገጫ ታቀርባለች፡፡
የጥጃው ባለቤት ገበሬ በእርባታ ማእከሉ ጥጃው እንዲቆይ ፍላጎት ስለነበረው ኤም 309 የሚል ስም ሰጥቶት ከሶስት ወር በኋላ ለማረድ ያቅዳል፡፡ የትናንቱ ጥጃ አድጎ በሬ ይሆናል፡፡ የእርድ ጊዜውም ይቃረባል፡፡ በዚህ መሃል ታዲያ ፈረስ አሰልጣኟ ሳቢን በሬው አይታረድም በማለት አሻፈረኝ ትላለች፡፡ ገበሬው በሬውን ለእርድ እንዳይሸጠውም መታገል ትጀምራለች፡፡ በዚህም ተሳክቷላትም በሬውን በመውሰድ የራሷ ታደርጋቸዋለች፡፡ ሳቢን ቀስበቀስ ልክ የዝላይ ትርኢት እንደሚያሳይ ፈረስ በሬውም እንዲዘል ማለማመድ ትጀምራለች፡፡ አስተን ብላ ስም ያወጣችለት በሬ አብዛኛውን ጊዜውን ከእርሷ ጋር ማሳለፍ ይጀምራል፡፡
ልምምዱንም ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡ 1ነጥብ 3 ቶን ክብደት የሚመዝነውን በሬ እየጋለቡ እንደፈረስ እንዲዘል ማለማመድ አስቸጋሪ ቢሆንም የበሬው ልምምዱን ቶሎ የመቀበል ችሎታና የፈረስ አሰልጣኟ ሳትታክት ማለማመዷ ታክሎበት በሬውን ልክ እንደፈረስ የዝላይ ትርኢት ማሳያ ማድረግ ተችሏል፡፡
በሬው ልክ እንደፈረስ ኮርቻ ተስርቶለት በጀርባው ላይ ቁጭ ብሎ ለመጋለብ አንድ ዓመት ያህል የፈጀ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ልክ እንደፈረስ የዝላይ ትርኢት ማሳየት ጀምሯል፡፡ አስተንና ሳቢን በአካባቢው ከሶስት ዓመት በፊት ትርኢት ማሳየት የጀመሩ ሲሆን፣ ዜናው እንደ ሰደድ እሳት በመሰራጨቱ ዛሬ ሁለቱ ለዝላይ ትርኢት ጥቂት በማይባሉ የአውሮፓ ሃገራት እየተዘዋወሩ ትርኢታቸውን ማሳየት መጀመራቸውን ፅሁፉ አስነብቧል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
በአስናቀ ፀጋዬ