በአዋጅ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!!!” አልተባለም እንጂ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ከሆነ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል። በተለይ የአገር መከላከያ ሰራዊታችን ከተከዳና ከተካደበት፤ ከጀርባውም ከተመታበት ከጥቅምት 24 /2013 ዓ.ም ጀምሮ የሁሉም ሰው አምስቱም የስሜት ህዋሳት ከዚሁ ካልተፈለገ፤ ነገር ግን ደግሞ የህልውና ጥያቄን ካስከተለው ሕወሓት ወለድ ጦርነት ጋር በቅርብ የተሳሰረ ከመሆኑ አኳያ፣ በይፋ ባይታወጅም “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!!!” አልነበረም ማለት አይደለም፤ ነበር።
ይህ በሕግ የማስከበር ዘመቻ የተጀመረው የ”ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!!!” ሕዝባዊ አቋምና መርህ በመከላከያ ብቻ ሳይወሰን ወደ ሕዝብም በመውረድ የሕልውና ዘመቻ ወደ መሆን ከመሸጋገሩም በላይ የአገሪቱ መሪዎችም ወደ ግንባር እንዲተሙ ሁሉ አስገድዷል። በዚሁ መሰረትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት ባለሥልጣናትና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደ ጦር ግንባር ያቀኑ ዘንድ ግድ ብሏል።
የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሁለት ሳምንት የጦር ግንባር፣ የአመራርና የአዋጊ ተዋጊነት ቆይታቸው ምን ምን ተግባራትን አከናወኑ፣ ምንስ ውጤት ተገኘ? ወዘተ የሚለውን በተጨመቀ መልኩ፣ በአንድ በማሰባሰብ ለታሪክ ማብቃት ፤ በእግረ መንገድም “እንኳን በሰላም፤ በድል ተመለሱ” ለማለት ነው። እንደሚታወሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በማቅናት የጦርነቱን ሂደት በመምራት መሳተፍ መጀመራቸው ከተገለጸ ከቀናት በኋላ የመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ግንባሮች በወሰደው እርምጃ በሕወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ስፍራዎችን ማስለቀቅ መቻሉ በበቂ ሁኔታ ተዘግቧል። ከምእራባውያኑና ተባባሪዎቻቸው ሚዲያዎች በስተቀር ሌላው ከዐቢይና እውነቱ ጎን ቆሞ ጉዳዩን አብራርቶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቀጥታ፣ የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት ወታደራዊ ጉዳዮችን በመከታተል በሽብር ኃይሉ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ የጀመሩት በሕወሓት ኃይሎች ጥቅምት 24/2013 በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መሆኑ ይታወቃል። በዛው መሰረትም፣ በፌዴራል መንግሥቱ እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል በተለያዩ ግንባሮች ጦርነት ተካሂዶ የፌዴራሉ መንግሥት ሠራዊት፣ ዋና ከተማዋ መቀሌን ጨምሮ፣ የተለያዩ የትግራይ ከተሞችን በሦስት ሳምንት ውስጥ መቆጣጠር እንደቻለም አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ፣ ጉዳዩ በዚሁ እልባት ሊያገኝ አልቻለም። የሽብር ቡድኑ ከባእዳን ጋር በመወዳጀቱ ምክንያት ብቻ ተመልሶ ለማንሰራራትና እንደገና ወደ ጥፋት ተግባሩ በመመለስ ከአጎራባች ክልሎችም አልፎ አጠቃላይ የአገሪቱ ራስ ምታት ለመሆን በቅቷል። በፌዴራል መንግሥት በደል እየደረሰበት እንደሆነ በማስመሰል መንግሥትን ሲያሳቅል፣ መንግሥት ክልሉን ጥሎለት ወጥቷል። ከተወሰኑ ወዳጅ አገራት በስተቀር፣ ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብም በምዕራባዊያን የሀሰት መረጃ በመወናበዱ ምክንያት የፌዴራል መንግሥትን መንግሥታዊ ተግባር እስከ መርሳትና የሽብር ቡድኑን እስከ መደገፍ ድረስ የዘለቀ አስተያየቱን ሲሰጥ ቆይቷል።
ይህ ሁሉ ሲሆን የዐቢይ አስተዳደር ከዚህ በመለስ ሊባል በማይችል ትእግስት ችግሩንና የችግሩ ባለቤቶችን ሲያስታምም ኖሯል። ሁሉም ነገር የራሱ ወሰንና ድንበር አለውና ሁሉም አልቆ፤ የመንግሥት ትእግስትም ተሟጥጦ ወደ “ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” ተገባ። ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን አጠቃላይ የጦር ሜዳ፣ የፖለቲካ ሁኔታና አስተዳደራዊ ተግባራት በየወቅቱ ይወጡ በነበሩ ዜና ዘገባዎች ብዙ የተባለሲሆን፤ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በሁለት ሳምንቱ የዐቢይ የጦር ሜዳ ውሎና አመራር ላይ ብቻ ያተኩራል። ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱን ጥምር የፀጥታ ሃይሎች በመምራት ወደ ጦር ግንባር ከሄዱ ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ ጽሕፈት ቤታቸው በድል ተመልሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግንባር በቆዩባቸው ሳምንታት ውስጥ “ምን ምን ወታደራዊ ተግባራት ተፈፀሙ፤ ምን ውጤት፣ ድልስ ተገኘ?” ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ ከራሳቸው አንደበት የእለት ተእለት ወታደራዊ ውሎን አስመልክተው ሲሰጡ ከነበሩትና የሕዝቡን የድል ዜና ጥም ሲቆርጡበት ከነበረው መግለጫዎቻቸው ስንረዳ ቆይተናል። ከእነዛ ወታደራዊና የድል ዜናዎች መካከልም፤ “በተካሄደው ዘመቻ በጠላት እጅ የነበሩት ዋና ዋና ቦታዎች ማለትም ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ባቲን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎች በወገን ጦር እጅ ገብተዋል” የሚለው አንዱ ነበር።
“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት የኢትዮጵያውያንን የቆየ ጀግንነትና ማንነት የሚያሳይ የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው” የተባለለት ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ የግንባር ውሎ የተለያዩ አካባቢዎችን በኃይል በመውረር የኃይማኖት ቦታዎችን ሲያረክስ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ሳይቀር ሲያቃጥል፣ ታሪካዊ ቦታዎችን ሲያወድምና ሲያፈራርስ ወዘተ የቆየውን ሕወሓት ከተሸሸገበት እያወጣ አይቀጡ ቅጣት ሲቀጣና ስፍራዎቹን ወደ ነበሩበት ሰላማዊ ሁኔታ ሲመልስ ነው የከረመው።
የዚህ ማስረጃው ደግሞ እንደ ደረሱ፣ “ወታደራዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው የተባለውን የሰሜን ወሎ ዞን ተራራማውን ስፍራ ጋሸናን በአጠረ ጊዜ እንቆጣጠረዋለን” በማለት መግለፃቸው ፤ እንዳሉት ሁሉ ቃል በገቢር እንዲሉ ያሉትን ማድረጋቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲመሩት የነበረው ጥምር የፀጥታ ኃይል (መከላከያ፣ የአማራና አፋር ልዩ ኃይሎች፣ ፋኖ፣ የአካባቢ ሚሊሻ …) በሽብር ቡድኑ የተያዙና ነፃ ያልወጡ አካባቢዎችን እያሰሰ ነፃ ሲያወጣ የቆየ ሲሆን፤ ሸዋ፣ ጋሸና፣ ወረኢሉ … በዚሁ ዘመቻና ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አዋጊነት ነፃ የወጡ አካባቢዎች ናቸው።
በመሆኑም ይመስላል ከጌትነት እንየው (“በላይ የወንዶች ቁና”) ቋንቋ በመዋስ “ዐቢይ የወንዶች ቁና” ባዮች ብቅ ብቅ እያሉ ያሉት። በዚህ፣ በ”ዘመቻ ሕብረ ብሄራዊ አንድነት” ዘመቻ ማሕበራዊ ተቋማትን ሲያፈራርስና ሲያወድም፣ የግልና መንግሥትን ሀብትና ንብረት ሲዘርፍ፣ ንፁሃን የየአካባቢው ነዋሪዎችን በጅምላ ሲረሽን፣ ሴቶችን (እናቶችና መነኩሴዎች ሳይቀሩ) ሲደፍር፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕፃናትን ሲያሰቃይና ሲገድል፣ ለጦርነት ሲማግድ፣ በሰው ልጅ ላይ ተፈፅመው የማያውቁ እጅግ አስከፊ ድርጊቶችን ሁሉ ያለ ርህራሄ ሲፈፅም የነበረው የሽብር ሃይል ተደምስሶ አካባቢዎች ነፃ ወጥተዋልና ከመንበራቸው ወርደው በደ ጦር ግንባር በማምራት ድል በድል ያደረጉንን ጠቅላይ ሚኒስትር እናመሰግናቸዋለን የሚለው ከግለሰብና የአንድ አካባቢ ማሕበረሰብ ቋንቋነት በዘለለ የሕዝብ ሆኖ እየተሰማ ይገኛል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ግንባር መሄድ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን እፎይ ያሰኛት እራሳቸውን፣ በማያውቁት ጉዳይና በጥቂት ግለሰቦች ምክንያት ለጦርነት የተዳረጉትን የሕወሓት ጀሌዎችንም ጭምር ሲሆን፣ ለዚህም “ዝም ብላችሁ በማታውቁት ምክንያት ከምታልቁ ለመከላከያ ሰራዊት እጃችሁን ስጡ” በማለት ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ጀሌዎቹ እጃቸውን ከፍ አድርገው በመስጠት ላይ መሆናቸው በቂ ማሳያ ነውና የዐቢይ ወደ ጦር ግንባር ማቅናት ጥቅሙ የጋራ፣ የሁላችንም እንደነበር ጥሩ ማሳያ ነው። ዐቢይ “የክፍለ ዘመኑ ጀግና” ቢባሉ ምናልባት ቢያንስ እንጂ አይበዛባቸውም ስንል ፍርዱን ለታሪክ በመተው ነው። ይህ በ“ዘመቻ ሕብረ ብሄራዊ አንድነት” መርህ የታጀበውና በዐቢይ አሕመድ የሚመራው ተዋጊ ኃይል ገና ስራውን አንድ ብሎ ሲጀምር ድል መጎናፀፍ የጀመረው የሽብር ቡድኑ በጋሸና ግንባር (ህዳር 21 ቀን፣ ጠዋት ላይ ነው ምሽጉ የተደረመሰው) በዶዘር አርቆ የቆፈረውን ምሽግ በማፍረስና ያከማቸውን ያለ የሌለ የሰው ኃይሉንና የጦር መሳሪያውን በመማውደም ፤ በግንባሩ ውጊያም የጠላት ጦር እምሽክ ከማለቱም በላይ ኢትዮጵያ እነ አስር አለቃ ጌቱ ፈይሳ (ታንከኛ)ን የመሳሰሉ ጀግኖችን ያፈራችበት ነውና የዐቢይ የውጊያ አመራርና ሲደነቅ ከዚህ ሁሉ አኳያ ነው ፣ አሁንም “ብራቮ!!!” እንላለን። ሌላው የዐቢይን የግንባር ውሎ ለየትና ተደናቂ የሚያደርገው “ተከተለኝ” በማለት ወደ ግንባር ማቅናቱና የተከታዩ አይነት (ከየሙያ ዘርፉ) እና ብዛቱ ነው። የዐቢይን “ተከተለኝ” ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ግለሰቦች፣ በአገር ውስጥን በውጭ የሚኖሩ፣ የቀድሞው ሰራዊት አባላት፣ አርቲስቶች፣ ባለ ሀብቶች፣ አትሌቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች ወዘተ ወደ ጦር ግንባር ያቀኑ ሲሆን፤ ይህም የጥንቱን ፋሺስት ሞሶሎኒን ለመደምሰስ የተደረገውን ክተት ከማስታወሱም በላይ ያንን የጀግንነት እሴት ማስቀጠሉና የሽብር ኃይሉን በቀላሉ ለመደምሰስ ማስቻሉ ሌላው የዘመቻው ትሩፋት ነውና አሁንም በወቅቱ የጣሊያን ዩኒቨርሲቲዎች ማሕበረሰብ አባላት “ብራቮ ሚኒሊክ!!! ብራቮ … ብራቮ …” እንዳሉት ሁሉ እኛም “ብራቮ ዐቢይ!!! ብራቮ … ብራቮ …” እንላለን። (እሳቸውን በመደገፍ፣ ምእራባውያኑን በመቃወም በትውልደ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም የተካሄዱ ምድር አንቀጥቅጥ ሰልፎችን ለሌላ ጊዜ እናቆያቸው በሚል እዚህ አልጠቀስናቸውም።) “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር መዝመትና ጦሩን መምራት የአገርን አንድነት ለማጠናከር የተወሰደ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት”ን የመወጣት አንዱና ቀዳሚው አካል መሆኑ የተነገረለት የዶ/ር ዐቢይ ወደ ግንባር ማቅናት የውጊያ አመራር መስጠት ለበርካታ እቅዶች በአጭር መቀጨት ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ በእነ ቢቢሲ “አማጽያኑ ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ በመሻገር ወደ አዲስ አበባ በሚያደርጉት ግስጋሴ የሚያቆማቸው ኃይል እንደሌለ” ማስታወቃቸው የተነገረላቸው የሽብር ቡድኑና ጀሌዎቹ ይህንኑ እጣ ፋንታ መጎንጨታቸው ነውና የጠ/ ሚኒስትሩ አዋጊነት ተገቢነትና አዋጪነት ነበረው ማለት በመሆኑ አሁንም “ብራቮ ዐቢይ!!!” ያስብላል ፤ ብለናል። “ኢትዮጵያ የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ ታሪክ አደራ አለብን”፤ “ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ”፤ “አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን”፤ “ይህ ትግል ልጆቻችን አገር እንዲኖራቸው የሚደረግ ትግል ነው። ልጆቻችን ክብርና ነጻነትን ለብሰው፣ በዓለም አደባባይ በኩራት ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚደረግ ትግል ነው”፤ “….. ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ”፤ “እያንዳንዱ የብልፅግና አመራር እራሱ ተሰውቶ ኢትዮጵያን ለማዳን ተዘጋጅቷል” በማለት ነበር በእለተ ማክሰኞ (ህዳር 22 2014 ዓ.ም) ወደ ጦር ግንባር ያመሩት ጠቅላይ አዛዡ “የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላምና ልማት ነው። ወደ’ዚህ ጦርነት የገባነው ተገድደን ነው። ማሸነፋችን ግን አይቀሬ ነው”፤ “የምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆም ኢትዮጵያን ማየት ነው።” የሚሉና የመሳሰሉትን የቁርጥ ቀን መልእክቶች ከጦር ሜዳ በማስተላለፍ የጠላትን አንጀት ሲያቃጥሉና ልብ ሲያቆስሉ፤ እንዲሁም የሕዝብና የሠራዊቱን ሞራል ሲገነቡ መሰንበታቸውም ሌላውና ተጠቃሽ የሞራል ልእልናቸው ማሳያ በመሆኑ እዚህ ሊጠቀስ ይገባዋል እንላለን። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምንም እንኳን “ውረድ እንውረድ ….” (በሚለው የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ፍልስፍና መሠረት) ብለው ወደ ዋናው ጦር ግንባር ቢያቀኑም ከወደ እነ ጌታቸው በኩል እንኳን እሚወርድ ቀርቶ ብቅ ብሎ በመስኮት እንኳን የሚያይ ሊኖር ባለመቻሉ ዐቢይ በድል ሊመለሱ በቅተዋልና “ኢትዮጵያ አሸንፋለች!!!” የሚለው መሬት ይይዝ ዘንድ ማሳያ እሰይ ይሁን ብለናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከቦታው በቴሌቪዥን በአማርኛ እና በኦሮምኛ በሰጡት አጭር መግለጫ ሠራዊቱ በአፋር ክልል ካሳጊታ የተባለውን ስፍራ መቆጣጠሩን፤ ቡርቃ እና ጭፍራን ደግሞ እንደሚቆጣጠሩ (ወዲያውኑ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በዐቢይ የሚመራው ሠራዊት ቡርቃን እና በባቲ ከተማ ዙሪያ ያሉ ተራሮችን መቆጣጠራቸውን እንዲሁም በአፋር በኩል ጪፍቱን፣ የጭፍራ ከተማንና አካባቢውን መያዙን አመልክቷል) የማይረሳ ሲሆን፤ ይህ ድልም እየገሰገሰ እየገሰገሰ ሄዶ ሄዶ፣ መጥቶ መጥቶ፤ በመጨረሻም ሰኞ፣ ህዳር 27፣ ማታ ደሴ፣ ባቲ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴ …. በሠራዊታችን ቁጥጥር ስር መግባታቸውን አበሰሩ።
ካዛም፣ ከአንድ ቀን በኋላ፣ ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ተመለሱ ፤ መግለጫም ሰጡ። (ሙሉ ቃሉን ከፅህፈት ቤታቸው ድረ-ገፅ ይመለከቷል።) ጥቅምት 24/2013 ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት (‘በውጭ ኃይሎች ሴራ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁር ሕዝቦች ላይ ሁሉ አዲስ የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን ያለመ” ጦርነት ነው እንዳሉት) ለስምንት ወራት ተካሂዶ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከክልሉ መውጣቱን ካሳወቀ በኋላ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች መስፋፋቱን የገፋበት ይህ የሽብር ቡድን ዓላማው አንድና አንድ ብቻ ሲሆን እሱም “ኢትዮጵያን ማፍረስ” በመሆኑ ከብዙዎች ጋር በማይታረቅ መልኩ እንዲጋጭ፣ ጥርስም እንዲነከስበት አድርጎታል።
ይህም ለዚህ፣ ዛሬ ላለበት እጣ ፈንታው አድርጎታል። ሌላውና “የውጭ ኃይሎች ከውስጥ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ጥቃት ለመመከት” (እሳቸው ወደ ግንባር ሲያቀኑ እንዳሉት) የጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር መዝመት፤ ዘምቶም ለሳንምንታት እዛው ግንባር መቆየት ለብዙዎች “የማይታሰብ” ብቻ ሳይሆን የህልም እንጀራ ነው፤ በህልም ሲደረግ፤ ሲያደርጉት የሚያዩት።
በተለይ አፍሪካ ውስጥ ከወንበር ላይ ተነስቶ ወደ ጦር ሜዳ ቀርቶ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባን እንኳን ጀምሮ ለመጨረስ ስጋቱ ቀላል አይደለም፤ አቋርጠው የሚሄዱ ሁሉ እንዳሉ ይታወቃል።
በተለይ በዐቢይ አስተዳደር ውስጥ ያለው የባለሥልጣናት አመለካከት የተከፋፈለ ነው፤ አማራው የዐቢይን ሥልጣን መያዝ አይፈልገውም ወዘተን ለመሳሰሉ አሉባልታዎች ቀጥተኛ ምላሽን የሰጠ ሲሆን፤ የዐቢይ የግንባር ቆይታ ከሠራዊቱና ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ማለፉም፤ ዐቢይን ሕዝቡ አይወደውም፤ በሕዝብ የተመረጠ መሪ አይደለም”ና በሽግግር መንግሥት ልንተካው ይገባል በማለት ለሥልጣን የቋመጠውን ቡድን እስኪገባው ድረስ ያስተማረ ሆኖ አልፏልና የዐቢይ ወደ ግንባር መዝመት ትርጓሜና አንድምታው ብዙ ነው።
ባጠቃላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ በእሳቸው የሚመራውን የመጀመሪያውን ዙር ውጊያ አጠናቅቀው በድል ተመልሰዋል። ጽ/ቤታቸው እንደ ገቡ እንደ ሰጡት መግለጫ ከሆነ ሁለተኛው ዙር የሚቀጥላል እሱም መሆን፣ መደረግ ባለበት ጊዜ የሚደረግ ይሆናል። በድጋሚ እንላለን፤ ጉሮ ወሸባዬ ወሸባ ዐቢይ ድል አድርጎ ሲገባ። ኢትዮጵያ አሸንፋለች!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4/2014