አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት ‹‹ከአማራ ህዝብ ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ ፤ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ…›› በሚል ዓላማ ጦርነት ከፍቷል። ይህ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የአሸባሪው ቡድን እንቅስቃሴ ከቡድኑ ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ የፈጸመው ኦነግ ሸኔ እንዲሁም ሚዜና አጃቢ የሆኑት የውስጥና የውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚሳተፉበት ድግስ ነው።
በዚህ የቡድኑ ወረራ ምክንያት በርካቶች ሕይወታ ቸውን አጥተዋል። ወልደው ከብደው ከኖሩበት፣ ሀብት ንብረት ካፈሩበት ቀያቸው ተፈናቅለዋል። የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ሁሉ ወድሟል። አገር ላይ ታሪክ እንዳይኖር መረጃና ማስረጃዎችን ማቃጠልና መዝረፍ፤ የሚዘርፈውን ዘርፎ ያልቻለውን አውድሞ መሄድ አሸባሪው ቡድን ሲሠራቸው የነበሩ አሁንም እጁን ያልሰበሰበባቸው የእኩይ ሥራው መገለጫዎቹ ናቸው።
አሸባሪው ሕወሓት ቀድሞም በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ለአንዱ ብሄር ሌላ ተቀጥላ ተቀናቃኝ በመፍጠር ትንንሽ ልዩነቶችን በመልቀምና አንዱን በአንዱ ላይ ባላንጣ አድርጎ በመሥራት አብሮ የኖረው፣ ተጋብቶ ወልዶና ወግ ማዕረግ አይቶ በፍቅር ይኖር የነበረውን ዘመድና ጎረቤት ሳይቀር በጥርጣሬ እንዲተያዩ ሲያደርግና ሲሠራ ከርሟል።
ዛሬ እዚህም እዚያም የሚሰሙ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ያልሆኑ ምልክቶች ሁሉ ያኔ የተቀበሩ ቦምቦች ናቸው። ዛሬም የቀበራቸው ቦምቦች በተላላኪ ባንዳዎቹ አማካኝነት እያፈነዳ ነው። በቅርቡ በደሴ የታየውም ይሄው ነው።
አሸባሪው ሕወሓት የሽብር ተግባሩን አጠናክሮ የቀጠለው ሌሎች ጋሻ ጃግሬዎቹን ከኋላው አስከትሎ ነው። ዛሬ እነአሜሪካና አንዳንድ ምዕራባውያን የሚያደርጉት እያንዳንዱ ሥራ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለመ ነው። እንደነ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን ፣ የመን… ሁሉ አገር አልባ የማድረግ ፍላጎት ነው።
የዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን የእነ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስ እና ሌሎቹም ሐሰተኛ፣ የተዛቡና የተጋነኑ በሬ ወለደ ዓይነት ዘገባዎችም የዚሁ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ነው። ምዕራባውያን በግልጽ ጦር ባያዘምቱብንም የጦር መሪ ሆነው በሳተላይት ፣ሲያሻቸውም መልዕክተኛና ተዋጊ ሰው በመላክ፣ የማቴሪያል ድጋፍ በመስጠትና አሸባሪውን በመደገፍ በግንባር ቀደምትነት እየወጉን ይገኛሉ።
ሕዝቡን በስነ ልቡና በማሸበር ጦርነቱን በበላይነት እየመሩ ናቸው። መሪዎችን በተለያየ መልኩ በማስፈራራትና በማስጨነቅ፤ ልዩ ልዩ ማዕቀቦች በመጣል፣ ‹‹የውጭ ሀገር ዜጎች ውጡ … የበረራ አቬሽኑ ስጋት ላይ ነው›› የሚሉና ሌሎች የሽብር ማስፈራሪያዎችን እያሰሙ ነው፡፡ ነገር ግን የሚሰማቸው ሕዝብም ሆነ ከአቋሙ ፍንክች የሚል መሪ አላገኙም። እነሱ ግን አሸባሪውን ቡድን ተሸክመው ለማምጣት ዛሬም ትግሉን ቀጥለዋል፤ የሽብር ወሬ በመንዛት እጃችንን ሊጠመዝዙ የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያውያን ‹‹ለራሳችን የውስጥ ጉዳይ ራሳችን በቂ ነን። ከዚያም አለፍ ሲል የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካ ይፈታል፤ ተውን፤ ልቀቁን፤ እኛ አሻንጉሊት አይደለንም፤ አሻንጉሊትም መሆን አንፈልግም፡፡ ብልጥ ከሌላው ሞኝ ከራሱ ይማራል፤ እኛ ደግሞ ዓይናቸው እያየ ከነበሩበት ከፍታ ወርደው በጣልቃ ገቦቹ የውጪ ኃይላት ሲፈራርሱ ያየናቸውን አገራት ዓይተን ተምረናል። ስለዚህ ለራሳችን ጉዳይ ራሳችን በቂ ነን›› ብለናል፡፡ ምዕራባውያን ግን ይህን አቋማችንን አልተቀበሉትም።
‹‹ለምን›› ብሎ መጠየቅ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል። መልሱም የሚገኘው ለምን ብሎ ከመጠየቅ ሲሆን፤ በዚህም ምዕራባውያን በአገራችን ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብተው አሸባሪዎችን እየደገፉና ምን እየሠሩ እንደሆነ ማየት እንችላለን።
በአገራችን ላይ የሚደረገውን ይህን ሁሉ ሴራ ግን ‹‹ለምን›› ብለን ስንጠይቅ ሌሎች አገሮችን እንዴት አድርገው እንደበታተኑ እንድናይ ያደርጋል። ‹‹ለምን›› ብለን ስንጠይቅ ለ27 ዓመታት ሞግዚት መንግሥት አስቀምጠው የአገራችንን ሕዝቦች በዘር ከፋፍለው አንዱ ላንዱ ስጋው ሳይሆን ስጋት እንዳደረጉት ማየት እንችላለን። ‹‹ለምን›› ብለን ስንጠይቅ ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዳይጠነክርና የነበረው የጀግንነት ስማችን እንዲጎድፍ ከመፈለግ መሆኑን እንረዳለን።
‹‹ለምን›› ብለን ስንጠይቅ ‹‹ቅኝ ተገዢነትን በዓድዋ ድል ያስቀረች አገር ኢትዮጵያ በቀጣይ ደግሞ ፓን አፍሪካኒዝምን ታጠናክራለች። ታዛዥ ሳይሆን ጠንካራና ተገዳዳሪ፣ ጡንቻዋ የፈረጠመ አፍሪካ እውን ትሆናለች፤ ስለሆነም ከዚሁ ከጅምሩ መቅጨት አለብን›› ብለው መነሳታቸውን እንድናይና ብዙ ነገሮችን አርቀን እንድንመረምር ያደርገናል። ይህ ዓይነት የጥንካሬ፣ የአንድነትና፣ የሉዓላዊነት አስተሳሰብ ለእነዚህ ኃያላን አገራት ምቾት አይሰጣቸውም፤ አልሰጣቸውምም። ዛሬም ፍላጎታቸው አፍሪካን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ቁጥጥር ስር ማድረግ ነው።
የአፍሪካ መሪዎች ለእነአሜሪካ ጋሻ ጃግሬዎች ታዛዦች፤ ሕዝቡም የእነርሱ አገልጋይ እንዲሆን ማድረግ ነው። ፍላጎታቸው የአፍሪካውያንን ሀብት በቀላሉ መዝረፍና ሕዝቡንም ማንበርከክ ነው። ዛሬ የሚታየውን የኢትዮጵያ አንድነት፣ ጥንካሬና የመበልጸግ ፍላጎት ነገ እንዳይጎለብት ማኮላሸት ነው። ‹‹አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው›› እንዲሉ አያያዛችን አልተመቻቸውም።
እኔ ያልኩትን ካልፈጸማችሁ የሚል ቂም የያዘው የአሜሪካ መንግሥት ‹‹ሕዝብን የማይጎዳ ማዕቀብ›› በባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ሲናገር ነበር፡፡ የተወሰደው ዕርምጃ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያን ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካን እንዲልኩ ከሚያግዘው የአጎዋ (AGOA) ን መርሐ ግብር እንደምትሰርዝ አሳውቃለች፡፡ ይህ ውሳኔ በርካታ ኢትዮጵያውያንንና የሚተዳደሩበትን ዘርፍ የሚጎዳ ነው፡፡ ይሄ እጅ መጠምዘዣ ኢኮኖሚውን ማስጎንበሻ አንዱ መንገድ አይደለም እንዴ? ይሄንን ዕቅዳቸውን ማሳካት የሚችሉት ደግሞ በየአገራቱ ታዛዥና በቀላሉ እጃቸውን የሚጠመዘዙ መንግሥታትን ማስቀመጥ ሲችሉ ነው፡፡
ተላላኪ የሆነና ሕዝብን ጨቁኖ የሚገዛ መንግሥት መመስረት ሲችሉ ነው። ስለሆነም ይህን ለማሳካት ለእነሱ የሚታዘዝና ዘርፎ የሚያዘርፋቸው አሻንጉሊት መንግሥት ማስቀመጥ ይፈልጋሉ። አሸባሪው ሕወሓት በ1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን ሲመጣ በምን መንገድ እንደገባ፣ ምን እንደሠራና እነሱንም እንዴት አድርጎ እንደሚያገለግል ያውቃልና ተሳክቶለት ቆይቷል። አሁን ግን ጊዜው ተቀይሯል። ሕዝብና መንግሥት ክፉና ደጉን አገናዝቧል።
ከሌሎች አገራትም ተምረናል። እናም ለአሸባሪው ሕወሓትና ለተላላኪው ሸኔ በግልጽና መናገር ያስፈልጋል፡- አታስቡ፤ እነ አሜሪካ ባሉት ሳይሆን ወሳኞቹ የኢትዮጵያ ዜጎችና መንግሥት ናቸው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ በሚበጀበው መልኩ አገራችንን ከመፍረስ ሕዝባችንን ከስደት እንጠብቃለን። አንድነታችንን አጠናክረን ለአገራችን ህልውና ዘብ እንቆማለን። ይሄንንም ከአገር ውስጥ እስከ ዲያስፖራው ወደ ጦር ግንባር በመዝመት፣ በገንዘብና በሞራል በመደገፍ ፤ የተቃውሞ ድምፁን በአደባባይ በማሰማት ደጀን በመሆን ጭምር አስመስክረናል።
አሁንም ለአገራችን ጠበቃና ዘብ ሆነን እንቀጥላለን። የሚያሳዝነው ግን አሸባሪው ሕወሓት ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ቀንደኛ ጠላቶች ጋር አብሮና ተባብሮ በአገር ላይ የሚፈጽመው ታሪክ የማይረሳው ደባ ነው። ታሪኩን በጥቁር መዝገብ እያሰፈረ ነው። በባንዳነቱ ትውልዱ የሚኮራበትን ሳይሆን አፍሮ የሚሸማቀቅበትን ታሪኩን እያሰፈረ ነው። ይሄን ሁሉ ሴራና ግፍ የሚፈጽመው አሸባሪው ሕወሓት አሁን ደግሞ ለዘረፍኩትና ላወደምኩት ሀብትና ንብረት፣ ለጨፈጨፍኳቸው ንጹሐን፣ ለደፈ ርኳቸው ሴቶች፣ አረጋውያን እና መነኩሴዎች፤ ላጎደፍኩት ቤተ እምነቶች፤ ላጠፋሁት ታሪክ ‹‹ካሳ እጠይቃለሁ›› ሲል ተደመጠ። እውነት ነው ለዚህ ተግባሩ ይግባኝ የማይጠየቅበት የፍትህ ካሳ ይገባዋል¡ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የታሪክ አተላነቱን የሚገልጽ ታሪክ ሊጻፍለት ይገባል። ልክ ነው የአሸባሪው ካሳ ይሄ ነው።
ለፈጸመው ምናልባትም በዓለም ላይ ተሰምቶ ለማያውቀው በአገርና ወገን ላይ ለፈጸመው ጭካኔው ካሳ ይገባዋል። ‹‹ልብ እንቅርት ይመኛል›› ማለት ለዚህ ዓይነቱ ነገር ነው።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4/2014