በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል። የተፈጥሮ ጋዙ በቱቦ ወደ ጅቡቲ ተጓጉዞ እና በዚያው ተቀነባብሮ ለውጪ ገበያ ይቀርባል። ለዚህም የቱቦ ቀበራ ስራ ለማከናወን ስምምነት ተደርጓል። በጅቡቲም ማቀነባበሪያውን ለመገንባት በሚያስፈልገው ቦታ ላይም እንዲሁ ስምምነት ተደርሷል። ቱቦ የመቅበሩ ስራ በሶስት አመታት ውስጥ ተጠናቆ እአአ በ2021 የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ወጪ መላክ እንደሚጀመር የማእድንና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የነዳጅ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላም በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል። ከዶክተር ኳንግ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ቀጥሎ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተካሄደ ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ልማት አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ዶክተር ኳንግ – የጋዝ ልማቱ በሁለት መልኩ እየተካሄደ ነው። አንደኛ ቀደም ሲል የተገኘው ጋዝ አለ። ፖሊጂሲኢል የተባለው የቻይና ኩባንያ ይህን ቦታ ከተረከበ በኋላ ሌላ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አግኝቷል። እነዚህን ለማልማት እየተሠራ ነው። በሌሎች ተመሳሳይ አራት ብሎኮች ላይም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እየተካሄደ ነው ። በአጠቃላይ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱ ከስምንት እስከ አስር ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ይደርሳል። የተፈጥሮ ጋዙ ከኦጋዴ በቱቦ እስከ ጅቡቲ ተጓጉዞ ከተቀነባበረ በኋላ ወደ ውጪ ይላካል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ቅትም የጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ እየተዘረጋ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል። በጅቡቲ ለሚገነባው የጋዝ ማቀነባበሪያም የቦታ ስምምነት መደረጉንም ጠቁመዋል። እነዚህም ልማቱ እየተካሄደ ስለመሆኑ ሌሎች ማሳያዎች ናቸው። እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች መቼ ይጠናቀቃሉ?መቼስ ጋዝ ማምረቱ ይጀመራል ?
ዶክተር ኳንግ፡- የቱቦውን ዝርጋታ ለመጀመር የሚያስችሉ ስምምነቶችን እየተዋዋልን ነው። ቱቦው የሚዘረጋው በኢትዮጵያና ጅቡቲ እንደመሆኑ በሁለቱ ሀገሮች መካከል በዚህ በኩል የሚደረገውን ስምምነት በቅርቡ ተፈራርመናል ። ከዚህ በተጓዳኝ ሕጎች እየተዘጋጁም ነው። የቱቦ መቅበሩ እና ሌሎች ስራዎች በሦስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። ከዚህም እኤአ በ2021 የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ውጪ መላክ ይጀመራል።
አዲስ ዘመን ፡- ለኢትዮጵያ ምን ያህልየውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል?
ዶክተር ኳንግ ፡- ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው አጠቃላይ የገቢ መጠን በየአመቱ ይጨምራል። የተፈጥሮ ጋዙ መመረት ሲጀምር እስከ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እናገኛለን። ይህም ከአክሲዮናችንና ኩባንያው ከሚከፍለው የሮያሊቲ ክፍያ የሚገኝ ይሆናል። ሮያሊቲው ከአጠቃላይ ምርቱ እስከ ስምንት በመቶ ይደርሳል። ታክስ የመሬት ግብር እነዚህ ሁሉ ተካቶ ማለት ነው። የምርቱ መጠን እየጨመረ ሲሄድ ማምረት ከተጀመረ ከስድስት እና ሰባት ዓመት በኋላ የሚገኘው ገቢም በዓመት እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። ለአጠቃላይ ልማቱ በተለይ የተፈጥሮ ጋዝ ቱቦ መቅበሩ ስራና የማቀነባበሪያ ግንባታው 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋቸዋል። ይህም ኩባንያው በራሱ የሚያወጣው ነው።
አዲስ አበባ ፡-ነዳጅ የወጣባቸው ሀገሮች ተሞክሮ እንደሚያመለክተው፤ነዳጅ ለማውጣት፣ ለማጓጓዝ፣ ለመሸጥ፣ወዘተ ራሳቸውን የቻሉ ህጎች ያስፈልጋሉ። በኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ምን ተከናውኗል? ወይም ምን ለማከናወን ታስቧል?
ዶክተር ኳንግ ፡- በጣም የቆየ የነዳጅ ሥራዎች የመቆጣጠሪያ አዋጅ አለ። ህጉ መሻሻል አለበት ብለን ስላመንን ለማርቀቅ ቡድን አቋቁመናል። ቡድኑ የተቋቋመው ከውጪ እና ከመሥሪያ ቤቱ በተውጣጡ አማካሪዎች ነው። ለዚሁ ብለን በቀጠርናቸው አማካሪዎችም እየሠራን ነው።
ይህም አጠቃላይ የነዳጅ ፍለጋውን በቀጣይ ደግሞ የነዳጅ ልማቱን በደንብ የተሳለጠ እንዲሆን ያደርጋል የሚል እምነት አለን ። ከነዳጅ ወይም ከተፈጥሮ ሀብት የሚገኘውን ገቢ ተጠያቂነትና ግልፅነት በተሞላበት መንገድ መከፋፈል ካልተቻለ ችግር ይፈጠራል። ነዳጅ በወጣባቸው አንዳንድ ሀገሮችም ችግሩ ሲያጋጥም ታይቷል። የሚወጣው አዋጅ ይህ ሁሉ እንዳይከሰት እንዲሁም ቢከሰት እንኳ ለመፍታት ያስችላል።ሌላው ደግሞ ሌሎች የሀገራችን ሕጎች አሉ።
በተለይ በማዕከላዊ መንግሥትና በክልሎች መካከል የሀብት ክፍፍል ይደረጋል። ይህን በደንብ ተከትሎ መሄድ ያስፈልጋል። የተፈጥሮ ጋዝ ልማቱ ለአካባቢው ህዝብ የተለየ ጥቅም የሚያስገኝበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። እስካሁን ከኩባንያዎች ጋር ድርድር በምናደርግበት ጊዜ በዓመት የተወሰነ በጀት ለአካባቢው ህዝብ እንዲያስቀምጡ /ያስቀመጥነው መቶኛ የለም/ የሚያስችል አሰራር አልዘረጋንም። በቀጣይ በሚወጣው ፖሊሲና ሕግ የተወሰነ መቶኛ ለአካባቢው ህዝብ የሚቀመጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንሰራለን ።
አዲስ ዘመን ፡- ለልማቱ ተባባሪ እንዲሆን በተለይ ነዳጅ በሚወጣባቸው አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ለማካሄድ ምን ታስቧል?
ዶክተር ኳንግ ፡- አዎ ፤ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ለአካባቢው ህዝብ ምን እየተሠራ ስለመሆኑ ማሳወቅ ያስፈልጋል።ነዳጁ መቼ ነው የሚወጣው የተፈጥሮ ጋዙ መቼ ለገበያ ይቀርባል? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይገባል። ከዚህ አኳያ ከክልሉ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል። የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ በሚደረግበት አካባቢ በመሄድ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ነዳጅ እንዴት ነው የሚፈለገው? ፍለጋውስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል ?ከወጣስ በኋላ እንዴት ይለማል? ሀብቱስ በምን መልኩ ጥቅም ላይ ይውላል ? ይሄን ሁሉ ለህዝቡ የምናስገነዝብበት ፕሮግራም አብረን በጋራ ለመንደፍ ከክልሉ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል ።
አዲስ ዘመን ፡-የተፈጥሮ ጋዝ ምርቱ ለውጭ ገበያ ነው የሚቀርበው። ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውልበት ሁኔታ ለምን አልተፈጠረም?
ዶክተር ኳንግ ፡- የተፈጥሮ ጋዝ በውጪው አለም በአብዛኛው ለኃይል ማመንጫ ነው የሚያገለግለው፤ኤሌክትሪሲቲ ይመረትበታል። እኛ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ከተፈጥሮ ሀብት የምንጠቀመው በአብዛኛው በውሃ ነው። ስለዚህ የተፈጥሮ ጋዙን በጥሬው የምንጠቀምበት ሁኔታ ላይኖር ይችላል። ከዚህ አኳያ በተደረገ ጥናት በተፈጥሮ ጋዙ ይበልጥ የምንጠቀመው ለውጪ ገበያ ስናውለው መሆኑ ተለይቷል። ይህ ሲባል ግን በሀገር ውስጥየምንጠቀምበት አግባብ የለም ማለት አይደለም። በኢትዮጵያና በሞሮኮ በአክሲዮን በድሬዳዋ እንደሚገነባ ለሚጠበቀው የማዳበሪያ ፋብሪካ በግብአትነት ያገለግላል።
ለዚህም ኩባንያው የተፈጥሮ ጋዙን እንዲያቀርብ ባለፈው ሳምንት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል። ሌላው እያሰብን ያለው ኩባንያው ጅቡቲ እንደሚገነባው ግዙፍ አይነት ባይሆንም መለስተኛ የጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በአካባቢው እንዲገነባ ነው። ጅቡቲ የሚገነባው በአመት ሶስት ሚሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ የሚያቀነባብር ነው። ይሄኛው ግን ግማሽ ሚሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የሚያቀነባብር ይሆናል። ከተቀነባበረ በሁዋላም በመኪና ወደ ጅቡቲ ይጓጓዛል ማለት ነው። ይህን በመኪና ብቻ ለማጓጓዝ በርካታ ልዩ ተሽከርካሪዎች ያስፈልጋሉ። በአካባቢው ከተፈጥሮ ጋዙ በተጓዳኝ ፈሳሽ ነዳጅም ተገኝቷል። የዚህንም መጠን ለማወቅ የሙከራ ማምረት ስራ ተጀምሯል። ስራው አሁንም ቀጥሏል። በዚህ ላይ ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት የሚፈጅ ሙከራ እናደርጋለን ። የፈሳሽ ነዳጁ መጠን ከታወቀ በኋላ እንዴት እናልማው የሚለውን ኩባንያው ያቀርባል። እኛም ኩባንያው የሚያቀርበው ሀሳብ አጥጋቢ ከሆነ እናፀድቃለን። ከዚህም አንጻር በሀገር ውስጥም የምንሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን ፡- የተፈጥሮ ጋዙ በቱቦ ተጓጉዞ እና ጅቡቲ ውስጥ ተቀነባብሮ ለውጪ ገበያ ይቀርባል። ይህም ከጋዙ ሦስት ሀገሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያመለክታል። ተጠቃሚነቱ በምን መልኩ የሚፈጸም ይሆናል?
ዶክተር ኳንግ ፡- ማየት ያለብን የጋዝ ምርቱ ዋና ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መሆናቸውን ነው። ቡና በጅቡቲ በኩል ወደ ውጪ እንደምንልከው የተፈጥሮ ጋዙንም እንልካለን። ስለዚህ ከዛ ለጅቡቲ የምንከፍለው የትራንዚት ወይም የማስተላለፊያ ኪራይ ነው። እኛና ኩባንያው የምርት ስምምነት አለን። በዚህ መሠረት አንደኛ 15% ሼር ዲቪደንድ ይኖረናል። ከዚያም ከሮያሊቲ እናገኛለን ።
አዲስ ዘመን፡- በአካባቢው የነዳጅ ድፍድፍ እየወጣ መሆኑም ይታወቃል። ከዚህ ምን ያህል ተጠቃሚ እየሆንን ነው?ለሙከራ በቀን 400 በርሜል እየተመረተ ነው። ይህ መጠን አልጨመረም ወይ ? ይህስ መጠንከነዳጅ አምራች ሀገሮች የቀን ምርት ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነውና በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?
ዶክተር ኳንግ ፡-አሁን ነዳጅ የማውጣት ሙከራ ነው እየተደረገ ያለው፤ነዳጅ ማውጣት ግን አይደለም። ስለዚህ መጠኑ እንዲጨምር አይጠበቅም። ነዳጁ ምን ያህል ግፊት አለው የሚለውን ለማወቅ ነው እየተሰራ ያለው። ይህን መነሻ በማድረግ መጠኑ ምን ያህል ነው የሚለውን ለማወቅ እየተሰራ ነው ። አንዳንዱ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ እንዲወጣ እየተደረገ ነው ። በፓምፕ የሚደረግ የማውጣት ስራም አለ። ለሙከራ እየወጣ ያለው የነዳጅ ድፍድፍ በጣም ትንሽ ነው ።
450 በርሜል በጣም ትንሽ ነው ። ሌሎች ሀገሮች በቀን ወደ 40ሺ እና 50 ሺ በርሜል ነው የሚያመርቱት። ከአንድ ቢሊዮን እስከ 4 ቢሊዮን በርሜል በቀን የሚያመርቱም አሉ። እኛ ሙከራ እያደረግን ነው። መውጣት ስላለበት ነው እንዲወጣ እየተደረገ ያለው። ይህን አይነቱን ምርት በርካታ ሀገሮች ያቃጥሉታል ። ወይም ያፈሱታል። ቢቃጠል አካባቢ ይበከላል። እኛ ሀገር ለብርጭቆ እና ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲሸጥ ይፈቀዳል። ኩባንያውም ለፋብሪካዎቹ እየሸጠ የሚገኘውን ጥቅምም በውሉ መሠረት እንከፋፈላለን።
አዲስ ዘመን፡- ፍለጋና ልማቱ በሚካሄድበት አካባቢ የፀጥታ ችግሮች እንዳይከሰቱ እና የልማት እንቅስቃሴው እንዳይጓተት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር ኳንግ ፡-አካባቢው ላይ ኩባንያው፣ መከላከያ ኃይል እና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች እንደዚሁም የአካባቢው ህዝብ አብረው እየሰሩ ናቸው ። ቢያንስ በሳምንት አንዴ እየተገናኙ ይመክራሉ። እስካሁንም ችግር ያልተፈጠረው በዚህ መልኩ በመሰራቱ ነው።
አዲስ ዘመን፡-የተፈጥሮ ጋዙም ሆነ ነዳጅ በሚወጣበት ስፍራ ላይ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ተደርጓልን ? ዶክተር ኳንግ ፡- ፍለጋውም ልማቱም ከመጀመራቸው በፊት አንዱ መካሄድ ያለበት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ነው። የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እየተደረገ በኛ እንዲጸድቅ ይደረጋል። የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሳይደረግ ሥራ የሚጀመርበት ሁኔታ የለም። ስራው ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ ሁኔታ እየተካሄደ ስለመሆኑ በመስክ ምልከታም በደንብ አረጋግጠናል። ይሄን ያህል አካባቢውን የሚበክል ነገር የለም። በእርግጥ ግንዛቤ የሌላቸው አንዳንድ ወገኖች የሚያነሱት ነገር አለ።
እነዚህ ወገኖች አካባቢው ነዳጅ እየተፈለገበት ስለሆነ የከብቶች ግጦሽ ስፍራ ይጎዳል ይላሉ። ይህን አይነት ችግር ስላለመኖሩ በመስክም ምልከታ አይተናል። ፍለጋ በሚካሄድበት ጊዜ ሲሲሚክ መረጃ ለመሰብሰብ የሚደረግ እንቅስቃሴ ይኖራል፡ ፤መረጃው ከተወሰደ በሁዋላ ይሰመራል። ነዳጅ የሚፈለግበት ወይም የሚቆፈርበት ቦታልክ ትንሽ ነው ። አንዳንድ ጊዜ እስከ 5ሺ ስኩዌር ሜትር ይደርሳል። ከዛ ውጪ ያለው በሙሉ ነፃ ነው ። ስለዚህ ከብቶች የአካባቢውን ሣር እንዳይግጡ የሚከለክል ነገር የለም ። ይሄ ነዳጅ እንደሌላ ማዕድን አይደለም። ነዳጅ የሚፈለገው በመሬት ሥር ስለሆነ ከመሬት ላይ ያለው ሰው እየተጠቀመበት እንደሆነ ህዝቡ እንዲገነዘበው ግንዛቤ እንዲያገኝ እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን ፡- ልማቱ ለምን ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ታስቧል?
ዶክተር ኳንግ ፡- አጠቃላይ በግንባታው ወቅት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ይፈጠራል። በአሁኑ ጊዜም በተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋና ልማቱ እስከ አንድ ሺ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ተፈጥሯል። የስራ እድሉ ይሄ ብቻ አይደለም የሚሆነው። በተጓዳኝ የሚፈጠሩ የስራ እድሎችም አሉ። ኩባንያው ከአካባቢው የሚጠቀመው አገልግሎት እንዲሁም ለእነዚህ አገልግሎቶች ዕቃ የሚያቀርቡ ይኖራሉ። በአካባቢው የትራንስፓርት አገልግሎት የሚሰጡም ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ኩባንያው የሚያስፈልጉትን ምርቶችና አገልግሎቶች በቅድሚያ ከሀገር ውስጥ እንዲጠቀም ፣ምርቶቹና አገልግሎቶቹ በሀገር ውስጥ የማይገኙ ሲሆን ብቻ ከውጭ እንዲያስገባ የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል። ለዚህም ጥራት ያላቸው ምርትና አገልግሎቶችን ማቅረብ ይገባል። ስለዚህ በቀጥይ የሚቀጥሯቸው ሰራተኞች በብዙ ሺህ ይሆናሉ። ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩም በአካባቢው ብዙ የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን ፡- የቴክኖጂ ሽግግር ለማድረግ እና የባለሙያዎች ሥልጠና ለመስጠት ምን ታስቧል?
ዶክተር ኳንግ ፡- ልማቱ እስካሁን የተወሰኑ የስራ እድሎችን አስገኝቷል። እየሰፋ እንደሚሄድ ይጠበቃል። ኩባንያው ከቴክኖሎጂ እውቀትና ሽግግር አንጻር ሰራተኞችን እንዲያሰለጥን እየሰራን ነው። ኩባንያው በየአመቱ ለሥልጠና የሚከፍለው ብር አለ። ሥልጠናው የሚኒስቴሩ ባለሙያዎች ዐቅም የሚገነባበት ነው። ይህም አንዱ የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር የሚደርግበት መንገድ ነው። ልማቱ እየተጠናከረ በሚሄድበት ጊዜ የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግሩም እየተጠናከረ ይሄዳል። አዲስ ዘመን ፡- ላደረጉልን ትብብር እናመስግናለን ። ዶክተር ኳንግ ፡- እኔም አመስግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ