ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገጠማትን የህልውና አደጋ በራሴ አቅም ቀልብሼ የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነቴን ላስከብር ባለች፤ የደከመች እንጂ የጠነከረች ኢትዮጵያን ማየት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ጫና በማድረግ የተቀናጀ ዘመቻ ከፍተውባታል።
በተለይ ማዕቀብን እስከ መጫን የደረሰው የአሜሪካን ጫና ለሰሚው ግራ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ ሌሎች ማስፈራሪያዎችን ይዞም እየመጣ ነው። አሜሪካንና አጋሮቿ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና የመንግሥትን እጅ ጠምዝዘው ወደ ድርድር ለማስገባት ብሎም ደካማና የእነሱ ጥገኛ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሆኑ በግልጽ እየታየ ያለ ሐቅ ነው። የተጠናከረ ጫና የሚያደርጉት በደካማ አገር ውስጥ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን ያለማስተናገድ ሞራል ያላቸው በመሆኑ ምዕራባውያኑ እንደማይሳካላቸው ዋል አደር ብለን የምናየው ነው።
ኢትዮጵያ ላይ የተዛቱት ዛቻዎች የተጣሉት ማዕቀቦች ሁሉ አገሪቱን ለጊዜው ያዳክሙ ይሆናል እንጂ ሕዝቦቿ በፍላጎታቸው የመረጡትን መንግሥት ግን የሚቀይር ሊሆን እንደማይችል እነሱም ያውቁታል ብዙዎችም የሚስማሙበት ነው።
በተለይ ሕዝቡ አሁን ላይ በአሜሪካንም ሆነ በአንዳንድ ምዕራባውያን አገራትና ተቋማቶቻቸው በኩል ኢትዮጵያ ላይ እየተቃጣ ያለው የማስፈራሪያ እንዲሁም የማዕቀብ መጣል የተጠናከረ ዘመቻ አሁን ላይ በቅጽበት የፈጠሩት ሳይሆን ከበፊቱም ጀምሮ ኢትዮጵያ ስጋታቸው እንደሆነች ገብቷቸው በጥናት በምርምር ሲሰሩበት የቆዩት ነው።
በዚህም እቅድ አንድ ወይም ሁለት ብለው በማስቀመጥ ቀን ሲጠብቁልን ኖረው አሁን የግብር አምሳላቸው ጁንታው ቡድን አገር ሲከዳ ተባባሪ ሆነው መነሳታቸው ቀድሞ በእቅድ የያዙትን ነገር ለማስፈጸም ጥሩ አጋጣሚን የማግኘታቸው ምክንያት ነው።
ይሁንን አሜሪካንና ምዕራባውያኑ ለረጅም ጊዜ ሲቋምጡለት የነበረውን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው የራሳቸውን ጥቅም የማስከበር ድብቅ ሴራ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ያሳቡበት ነው።
አሁን ላይ እነዚህ ኃይሎች በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ለመግባት የሞት የሽረት ትግል እያደረጉ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን በደማቸው ውስጥ ባለው የቅኝ አገዛዝን ያለማስተናገድ ወኔ ሙከራቸው ሁሉ እንደማይሳካ እያሳየን ነው። በሰብዓዊነትና በዴሞክራሲ ስም የምትምለው አሜሪካን በኃይል በገባችባቸው ሊቢያ ሶሪያ አፍጋኒስታንና ሌሎችም አገራት ፈራርሰው አሳዛኝ ሆኑ እንጂ ተገንብተው አሰፍነዋለሁ ያሉትን ዴሞክራሲ አስፍናላቸው የሰላምን አየር አላገኙም።
ታዲያ ነጻነታችንን አስከብረን በኖርን ሕዝቦች ላይ አሁን የገጠመንን ወቅታዊ ችግር ተንተርሶ ለመጡብን ኃይላት ፍላጎት ማስፈጸሚያነት እንዳናገለግል እንደ ቀደመው ወግ ባህላችን በአንድነት መነሳትና መቆም ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው። እኛም አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩ ያሉትን ተጽዕኖ አስመልክተን የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ከሆኑት ከአቶ እንዳለ ንጉሴ ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት ለአሸባሪው ሕወሓት እድሜ ለመጨመር በማሰብ ሁለንተናዊ ዘመቻን በኢትዮጵያ ላይ መክፈታቸውን እንዴት ያዩታል?
አቶ እንዳለ፦ አሜሪካን ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ያላት አገር ነች፡፡ ይህም ወዳጅነት ዝም ብሎ የሚቀያየር ሳይሆን ስትራቴጂክ የሆነ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ናቸው። ነገር ግን በተለይም አሁን ላይ አሜሪካን በአፍሪካ ሁኔታ ላይ ትክክለኛ ፖሊሲ የላትም። በተለይም አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር አፍሪካን እንዴት እንደሚመለከቱ በምን መልኩ መያዝ እንዳለባቸው የሚያመላክት ፖሊሲ የላቸውም። ፖሊሲ ማጣታቸው ደግሞ በግለሰቦች ፍላጎት እንዲመሩ አድርጓቸዋል። እነዛ ግለሰቦች እንዲሁም ሎቢዎች ደግሞ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው የመንግሥት አስተዳደር ጋር ግንኙነት የነበራቸው ናቸው።
በነገራችን ላይ የአሜሪካን መንግስት ምን ያህል ደካማ እንደሆነ የምናውቀው ባለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው እንዲከፋፈሉ እንዳይስማሙ በማድረግ ሲሰቃዩ ነበር፡፡ ነገር ግን አሜሪካን ግን ቡድኑ ስለተመቻት አገራችንንም እንደፈለገች ታሽከረክርበት ስለነበር የሕዝቡ ጉዳት ምንም ሳይመስላት እዚህ ደርሳለች። አሜሪካን ኢትዮጵያን እስካልያዘች ድረስ ብሔራዊ ፍላጎቷን ማሟላት አትችልም፡፡
በአንጻሩ ኢትዮጵያም በቴክኖሎጂ በንግድ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ አሜሪካን ታስፈልጋታለች። ይህም ቢሆን አሜሪካውያኑ ሥልጣኔው ባመጣው መሰረት ዘመናዊውን መሳ ለመሳ የሆነውን ፖሊሲ መጠቀም አልፈለጉም። እየተከተሉ ያሉት እንደ ጁንታው ዓይነት ቡድን ይዘው ሕዝቡን ቢፈልግ ያጥፋ ከፈለገ ያልማ ብለው እየቀጠሉ ነበር።
አጋጣሚ ሆኖ ያ ቡድን አሁንም ከባይደን አስተዳደር ውስጥ ተሸጉጧል፡፡ አሁን ላይ በአገሪቱ ጉዳይ ምንም ማድረግ ስላልቻሉ ኢትዮጵያውያን ያባረሩትን ወደ ጉድጓድ የሸኙትን ቡድን የመናፈቅ ነገር እየተስተዋለባቸው ነው። ይህ ግን በፍጹም ሊሆን የማይችል ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ከሌላው ማለትም ከዚህ ቀደም እንደ ፈለጉ ገብተው ካፈራረሷቸው አገራት ለየት ያለ ሁኔታ ላይ የምትገኝ ናት። የፈለጉትንም ማድረግ አይችሉም። ከዚህ አንጻር ስንወስደው የአሜሪካን ፖሊሲ ቆም ብሎ ማየት ያለበት ራሱን ነው።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፖሊሲ ዜጎችን መሰረት ያደረገ ጎረቤት አገሮችን የአፍሪካን ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስችል አዲስ ፖሊሲ ነው፡፡ እንደ ጁንታው ፖሊሲ አካባቢን በመረበሽ ላይ የተመሰረተ አይደለም። አሜሪካን ግን ከዚህ አንጻር እየሄደችበት ያለው መንገድ ኢትዮጵያውያንን የማያስደስት አፍሪካውያንን የሚያስከፋ ነው። ይህንን ላለመቀበል ትክክለኛው ነገር ኢትዮጵያ ጋር እንዳለ ላለመቀበል ገንዘብን መሰረት አድርገው አካባቢውን መዞር ይዛለች።
አሁን ላይ ኢትዮጵያን እየተከተሉ አንዴ ሱዳን ጅቡቲ ኬንያ እየሄዱ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በራሱ ትልቅ ድክመት ነው። እንደ ኃያልነታቸው ይዘው መሄድ ያለባቸው የራሳቸውን ፖሊሲ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሱዳን ገቡ፤ ነገር ግን አገሪቱ የምትቆጠረው አሁን ላይ መንግሥት እንደሌላት ነው፡፡ ኬንያ ሄዱ ኬንያውያን ደግሞ ከዚህ ቀደም በምርጫ ምክንያት ያደረጓቸውን ስለሚያውቁ አይሰሟቸውም እንደውም ከአሜሪካን በላይ ኢትዮጵያ እንደምታስፈልጋቸው ያውቃሉ።
በመሆኑም አሁን የተለያዩ አፍሪካ አገሮች ላይ የሚሄዱት በኮሊኒያል አገዛዝ የተቀረጸው አዕምሯቸው እዛው ላይ ስላለና አፍሪካውያንን ከፋፍሎ በመግዛት የእነሱ መጠቀሚያ ለማድረግ ስለሚያስቡ ነው። ግን አይቀበሏቸውም። ኢትዮጵያውያንም ቢሆን በአሁኑ ወቅት አንድና ንቁ ናቸው፡፡ የራሳቸውን መንግሥት መርጠዋል፡፡ በዓለም ለይ ከአሜሪካን ውጪ በርካታ ወዳጅ አገራት አሉን፡፡ ይህ ሁሉ ሲወሰድ አሁን የሚያስቡትን መንገድ መተግበር አይችሉም።
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ግን አሜሪካን ከማዕቀብም ባሻገር አሁን ላይ ወታደራዊ ኃይሏን ሁሉ እንደምታሰማራ እየነገረችን ነው ፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ እንዳለ፦ አይ ይህማ ቅዠት ነው። ሲጀምር ማድረግ አትችልም። በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም ወታደራዊ ኃይሏን ባስገባችባት አፍጋኒስታን እንኳን ያወጣችው ወጪና የገበረችው የሰው ሕይወት ታውቃለች፡፡ በተመሳሳይ ሊቢያ ላይ ጋዳፊን ለመጣል ጥረት ቢያደርጉም አሁን ተመልሶ የመጣው የጋዳፊ ልጅ ነው። ሲሪያ ላይ እነሱ እናስወግደዋለን ያሉት መንግሥት እየጠነከረ ነው፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ትምህርት በመውሰድ አፍሪካ ላይ ደግሞ ነገሩ እንደሚብስ በመገመት እራሳቸውን ማስተካከል አለባቸው። ኢትዮጵያውያን ጁንታውን ለመምታት በሚታየው ልክ የተበረታቱት ፤ የአሜሪካንን ነገር በተለይም የውጭ ባንዳ አገራቸውን ሊያስተዳደር መምጣቱን ቢያውቁ በእጥፍ ሆነው እንደሚወጡ ምንም ጥርጥር የለውም። እንደውም ይህ አይነት ሃሳብ እንዳላቸው መናገራቸው ሕዝቡ የበለጠ እንዲጠነክር ዝግጁ እንዲሆን እያደረገው ነው። እኔ እንደውም ይህንን ነገር ሳስብ የተናገሩት የሚመስለኝ ብዙ ሳያስቡበት ነው ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አገራችን ላይ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ የለም። አገር ውስጥ ያለው ሕዝብ የራሱን መሪ መርጦ በአንድነት እየኖረ ነው። በውጪም ዓለም ያለውም ቢሆን በአገሩ ጉዳይ የሚደራደርበት ሁኔታ ላይ አይደለም፡፡ ሌሎች በአፍሪካ ኅብረት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ የዲፕሎማሲው ተዋንያንም ቢሆኑ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የያዘችው ጉዳይ ሐቅ ነው ብለው ከጎኗ እንደሚቆሙ በተግባር እያሳዩ ነው። ጅቡቲም እኔ አገር ሆኖ ሌሎችን መጉዳት አይቻልም ብላ መግለጫ ያወጣችው ወዲያውኑ ነው። በመሆኑም አሜሪካን ማስተካከል ያለባት ራሷን ነው።
አዲስ ዘመን፦እነሱ እራሳቸው ካዩ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን እኛ እንደ አገር ከዚህ ችግር ለመውጣት የሚጠበቅብን ነገር ምንድን ነው?
አቶ እንዳለ፦ ኢትዮጵያ የሚጠበቅባት አንድ መሆን ፐብሊክና የዜግነት ዲፕሎማሲዋን ማጠናከር ነው። እነሱ እኛን ይከተሉ። አሁን ለምሳሌ ናይጄሪያ ቢሄዱ ምንም የሚያመጡት ለውጥ የለም፤ ምክንያቱም ናይጄሪያ እንደኛ ተመሳሳይ ስቃይ ያለባት አገር ናት። ከቦኮሃራም ጋር ስትዋጋ አሜሪካን ወደኋላ ነው ያለችው ይህንን ደግሞ ዜጋው ያውቃል። ኬንያም እንዳልኩሽ ነው፤ በምርጫ ሰበብ እንደዛ ሲሆኑ የጠቀማቸውን ያውቃሉ። በመሆኑም አሁን ያለንበትን አቅጣጫ እያጠናከርን ከሄድን የውጭ ፖሊሲያችንን ከተገበርን አሜሪካን ልኳን አውቃ ወደኛ ሥር መምጣቷ አይቀርም። አሁን ባለው ሁኔታ ግን እንደዚህ ኢትዮጵያን ለማዳከም መዞሯ ምንም ሐቅ ያልያዘች መሆኗን አሳብቆባታል።
በጠቅላላው የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚፈታው በራሷ በዜጎቿ እንጂ በማንም አይደለም ፡፡ የዲፕሎማሲው ግንኙነት ባለቤቶች ዜጎቿ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሜሪካን በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እንዲሁም ከጁንታው ጋር በነበራት ወዳጅነት መሄዷ ኪሳራ ውስጥ ያስገባታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን እምነት ያሳጣታል። ስለዚህ ይህንን ማስተካከል አለባት። በነገርሽ ላይ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ አንድ ስለመሆናቸው በቀደም የነበረው የብራሰልሱ ሰላማዊ ሰልፍ ብቻውን በቂ ማስረጃ ነው። አሁን ማወናበድ አይቻልም።
አዲስ ዘመን ፦ አሜሪካ ኢትዮጵያውያን ላይ የስነ ልቦና ጉዳት ለማምጣት ለማሸበር ከምትጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ በመገናኛ ብዙኋኖቿ የምትለቃቸው የሐሰት ዜናዎች እንዲሁም ዜጎቿን ውጡ የማለት ሁኔታ ነውና ይህ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አቶ እንዳለ፦ እዚህ ላይ እንደውም በጣም ተሳስተዋል። አሁን እኮ ያለነው ዓለምን በሰከንዶች ውስጥ ማየት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ነው። እንዲህ አይነት ነጭ ፕሮፖጋንዳ ነጭ ውሸት ከሲ ኤን ኤን መስማት በጣም ይገርማል። ለነገሩ ይህ ሚዲያ ባለፉት ጊዜያትም ኢራቅ ላይ ተመሳሳይ ነገርን በማድረግ ምንም የሌለን መሣሪያ አለ በማለት ለዛ ሁሉ ፍዳ ዳርጓል። አሁን ላይ ግን ዓለም ሌላ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡
ይህንን ማውራታቸው እንደውም ሕዝባችን እንዲነቃ ድብቅ ፍላጎታቸውን እንዲረዳ አድርጎታል። በጣም የሚገርመው ደግሞ ትላንት ከተማውን ለቃችሁ ውጡ ብላ ዛሬ ደግሞ በጎን ዲፕሎማቶቻችን ይግቡ እያለች መጠየቋ ነው። ይህ በራሱ ምን ያህል በሁኔታው እንደተሳከሩ እውነትን ባለመያዝ ግራ እንደተጋቡ ቁልጭ አደርጎ የሚያሳይ ነው።
እኛ ደግሞ ምን ያህል የባይደን አስተዳደር ለጥቅሙ ሲል ነጭ ውሸት እንደሚዋሽ መረዳት አለብን። የአሜሪካን መንግሥት ሕዝብ የመረጠውን መሪ ማክበር ነበረበት ነገር ግን ከአሸባሪ ጋር ይሆናል። ይህንን ለማለት ደግሞ ምንም ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ መሠረት የለውም። በመሆኑም የአሜሪካን አካሄድ መልሳ የሚነጥላት እራሷን ነው። ግን የእነሱን ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት ምን ያህል እንደሚሄዱ ጥሩ ጥሩ ደላላዎች እንዳሏቸው ሚዲያቸው ለራሱ ክብር እንኳን የማያስብ መሆኑን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ እኛን እናዳክማለን ባሉ መጠን የራሳቸው ክብርን እያጡ መሆኑን ማወቅ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ነጭ ውሸት ተከትለው ከአገር በሚወጡ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ትምህርት እንዲቋረጥ በሚያደርጉ ኢንተርናሽናል ትምህርት ተቋማት ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ማድረግ ያለበት ምንድን ነው?
አቶ እንዳለ፦ መድኃኒቱ አሁን የጀመርነውን አንድነት አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡ ወጥቶም ይህ ልክ አይደለም ውሸት ነው፡፡ በአገሪቱ ላይ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም፡፡ መዲናዋም ሰላም ናት፡፡ ነገር ግን የራሳችሁን ሥራ ትታችሁ እኛን መከታተል ከፈለጋችሁ በርቱ ማለት መቻል አለብን። አሜሪካን በቀን ሶስት አራቴ ስለ ኢትዮጵያ መግለጫ ከማውጣት ተላቃ የራሷን ሥራ እንድትሰራ በሚገኘው አጋጣሚ ሁሉ መናገር ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያውያንም እነሱ አሉ ብለን ከመደናበር ወጥተን እንወጣለን ብለው የተነሱ ጉቦ የበሉ ዲፕሎማቶችን በመጡበት መንገድ መሸኘት ነው እንጂ መጨቃጨቅ አያስፈልግም። ምክንያቱም ነገ ለምነውን እንደሚመጡ ስለምናውቅ።
አዲስ ዘመን፦ አሜሪካን አሁን ላይ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች መረጃን እንዳያገኙ እያገደች ነው የሚል ነገር አለና እንደው ይህ ሁኔታ በዚህ ዘመን የሚጠበቅ ነገር ነው?
አቶ እንዳለ፦ አሜሪካን ለመረጃ ትልቅ ቦታ አለኝ የምትል አገር ናት። ይህንን ማድረግ ግልጽ የሆነ በሃሳብ የመሸነፏን በዲፕሎማሲ የመድከሟን ሁኔታ ቁልጭ አደርጎ ያሳየ ነው። ይህ ደግም እንደ ሁሉም ተጽዕኗቸው ሕዝቡ የበለጠ እንዲጠነክር ያደረገ ስለሆነ የሚጨንቅ ባይሆንም በራሳቸው ጊዜ ደግሞ ወደመስመር እንደሚገቡ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያ ግን እንደ ቻይናና ራሺያ የራሷን መንገድ ቀይሳ መዘጋጀትና መረጃ መለዋወጥን መቀጠል አለባት።
አዲስ ዘመን ፦ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች አሁን ላይ እያሳዩት ያሉት ገሸሽ የማለትና አያገባንም ዓይነት ነገር እንዴት ያዩታል?
አቶ እንዳለ፦ አሁን ላይ እነሱን መጠበቅ ብዙ የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዲሁም ሕዝቦቿን ለመጉዳትና የእሱን ተላላኪ መንግሥት ለማስቀመጥ የማይቆፍረው ነገር የለም። በመሆኑም ኢትዮጵያን በዚህም በዚያም በተጫኗት መጠን የበለጠ ጎልታ ብዙ ወዳጅ አግኝታ ትሄዳለች፡፡ እርዳታውም ቢሆን የምንችለውን ያህል በራሳችን አቅም ኋላም ሌሎች ለጋሽ አካላትን በማፈላለግ ለሕዝባችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደርሳለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን ፦ ኢትዮጵያ ግን ከዚህ ቀደም በነበረ ታሪኳ መሰል ጫናዎች አጋጥመዋት ነበር? እንዴትስ አለፈቻቸው?
አቶ እንዳለ፦ አለ! አሜሪካኖች እኮ በዚያድ ባሬ ጊዜ የገዛነውን መሣሪያ እንዳናስገባ ከልክለውናል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ሆነ በአድዋ ወረራ ጊዜ ከጎናችን አልነበሩም፤ ስትራቴጂክ ወዳጅነት ላይ እንጂ እኛ በተቸገርንበት ጊዜ ደርሰው ያደረጉልን ነገር የለም። በዚህ መልኩ ከችግር አውጥተውናል ብለን የምንናገርላቸው ታሪክም የላቸውም።
አዲስ ዘመን፦ እንግዲህ አሁን ላይ ከቻይና ከሶቭየት ኅብረትና ቱርክ ጋር ያለው ግኙኘት አለ፤ ከዚህም ባሻገር አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከፍ ያለ ነው፡፡ከዚህ አንጻር ይህንን እድል ለመጠቀም ምን መደረግ አለበት?
አቶ እንዳለ ፦ አሁን ላይ እኮ ኢትዮጵያ የአብዛኛውን የዓለም አገራት እምነት አግኝታለች። አፍሪካውያንም ከቀድሞም የነጻነት ተምሳሌታቸው ነበረች፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ይበልጥ በመሪዋ አማካይነት ምን ላይ እንዳለች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ከፍ ያለ ቦታና ግምት የሚሰጧት ሆናለች። በሌላ በኩል አፍሪካ ኅብረት ኢጋድም ቢሆን ከጎኗ ናቸው። በመሆኑም ይህንን ሁኔታ እያጠናከሩ መሄድ የተገኙትን እድሎች ሁሉ እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል።
ሌላው አሁን ላይ ያለብን ነገር በጋራ ለመሥራት መነጋገር መደማመጥ በጣም ወሳኝ ነው። እነሱ በሚፈጥሩት ነጭ ውሸት መርበትበትም ሆነ መፍራት ምን ልንሆን ይሆን ብሎ ግራ መጋባት አያስፈልግም። አሁን ላይ ኢትዮጵያ መሠረቷን እያሳመረች ነው። አንድነቷም ለብዙ ነገር መልስ እየሰጠ ነው። በሕዝቦቿ ይሁንታ መንግሥት መመስረቷም ቀላል የሚባል ነገር አይደለም። በመሆኑም ይህንን እያጠናከሩ መሄድ።
በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ልዩነቶች ቢኖሩን እንኳን በብሔራዊ ጥቅም ላይ ማንም መለያየት የለበትም። ስለዚህ ልዩነቶች ከብሔራዊ ጥቅሞች በመለስ መፈታት አለባቸው። መንግሥትና አገርን ለይቶ ማየት ይገባል:: የመጣው ደግሞ አገርን እበትናለሁ ያለ ኃይል ነውና ይህ እንደማይሆን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል። ቁርጥን በማወቅ ለሚሆነው ነገር መዘጋጀትና ወደ ማሸነፍ መሄድ ወሳኝ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ እንዳለ፦ እኔም አመሰግናለሁ::
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 30/2014