ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የሐሰት ውንጀላና ዘመቻ ቀጥለውበታል።የሰሞኑ ተረኛ አጀንዳቸው ደግሞ ‹‹የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹ወደ ጦር ግንባር እዘምታለሁ› አሉ›› የሚለው ጫጫታ ነው።በእርግጥ ይህ የመገናኛ ብዙኃኑ ወሬ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ሲነገርና ሲፃፍ እንደነበረ አይካድም።ሰሞኑን የተፈጠሩት አዳዲስ ክስተቶች ደግሞ ጫጫታው እንዲበረታ ተጨማሪ ምክንያቶች ሆነዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኅዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም ” … ጥቁር ሕዝቦች የራሳችን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ክብር እንዳይኖረን ሆን ተብሎ የሚደረግ አንገት የማስደፋት ትግል ነው። ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተ ዘመቻ፣ ኢትዮጵያን በማንበርከክ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የአሸናፊነት አርአያ እንዳያገኙ የተከፈተ ዘመቻ መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ስትሉ፣ በፓን አፍሪካ መንፈስ፣ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ … ጊዜው አገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።
ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ። ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ።የእኛ መዝመት የሚፈጥረውን ክፍተት ከግንባር የቀሩት በሙሉ አቅማቸው ሸፍነው ይሠራሉ።በግንባር ያልተሰለፉ የክልልና የፌደራል አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ አቅማቸው ይከውናሉ …›› በማለት ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ወዳጆች መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መልዕክት ባስተላለፉ ማግሥት ከአሸባሪው ሕወሓትና ጀሌዎቹ ጋር የሚደረገውን ፍልሚያ ለመምራት በውጊያ ግንባር ተሰልፈዋል፤ ተከታታይ ድሎች እየተመዘገቡና እየተበሰሩም ነው።የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ተከትሎ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ‹‹የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹ወደ ጦር ግንባር እዘምታለሁ› አሉ … ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት ተቀብለው ዛሬ ግን ጦርነት የሚመሩ ሰው ሆኑ … ›› የሚለውን ጩኸታቸውን እያቀለጡት ነው።
ካለፉት ወራት የመገናኛ ብዙኃኑ ውንጀላ አንፃር ሰሞነኛው ጫጫታም ብዙም የሚያስገርም አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የ2019 የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ‹‹ሰላምና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማስፈን፣ በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረው የድንበር ውዝግብ እልባት እንዲያገኝ ለወሰዱት ወሳኝ እርምጃ›› እውቅና በመስጠት እንደሆነ ይታወሳል።ልብ በሉ! የኖቤል ኮሚቴው (Norwegian Nobel Committee) ሽልማቱን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያበረከተላቸው ሰላምን ለማስፈን ባደረጉት ጥረት ነው።
ይህንን የሽልማቱን ምክንያት ይዘን የመገናኛ ብዙሃኑን ውንጀላና ጩኸት እንፈትሽ። ጠቅላይ ሚኒትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ‹‹ … ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ።
ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ …›› ብለው ጦር ሜዳ ላይ ለመሰለፍ የተገደዱት ጠብ ፈላጊና ሰላምን የማይፈልጉ ሆነው አይደለም። ወደ ጦር ግንባር ያቀኑት ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ለመፋለምና ሰላምን ለማስፈን ነው።
ጦር ሜዳ የወረዱት ውጊያ እየተመለከቱ ለመዝናናት ሳይሆን ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ መሄድ ካለብን እንሄዳለን›› ብሎ በአደባባይ የተናገረን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ ነው። ይህ ድርጊታቸው በሰላም ፈላጊነት የሚያስ መሰግናቸው እንጂ በጠብ አጫሪነት የሚስከስሳቸው አልነበረም።ያደረጉት ነገርም ከተሸለሙት የሰላም ኖቤል ሽልማት ጋር የሚጣረስ አይደለም።
ትናንት ‹‹ሰላምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሸባሪዎችን መፋለማቸው ሌላ የሰላም ኖቤል ሽልማት ያሸልማቸዋል! ለማስፈን ጥረት አድርገዋል›› ተብለው የተሸለሙ ሰው ዛሬም ሰላምን ለማስፈን እርምጃ መውሰዳቸው ሌላ ሽልማት ያሸልማቸዋል እንጂ በጠብ ጫሪነት አያስከስሳቸውም። እዚህ ላይ ‹‹አንዳንድ ጊዜ ጦርነት አስገዳጅ ቢሆንም ከጦርነቱ በፊት ውይይትንና ድርድርን በአማራጭነት መጠቀም አይቻልም ነበር?›› ብለው ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ።
እነዚህ ወገኖች ሕወሓት ‹‹አልደራደርም! ጦርነቱ እኮ አልቋል፤ከማን ጋር ነው የምደራደረው?›› የሚል የእብሪት መልስ እንደሰጠስ ሰምተዋል? የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የ2009 ዓ.ም (እ.አ.አ) የሰላም ኖቤል ሽልማትን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር ‹‹ … As someone who stands here as a direct consequence of Dr. King’s life work, I am living testimony to the moral force of non-violence. I know there’s nothing weak — nothing passive — nothing naïve — in the creed and lives of Gandhi and King. But as a head of state sworn to protect and defend my nation, I cannot be guided by their examples alone. I face the world as it is, and cannot stand idle in the face of threats to the American people. For make no mistake: Evil does exist in the world. A non-violent movement could not have halted Hitler’s armies. Negotiations cannot convince al Qaeda’s leaders to lay down their arms. To say that force may sometimes be necessary is not a call to cynicism — it is a recognition of history; the imperfections of man and the limits of reason. …›› ትርጉም፡- ‹‹ …የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒዬር የሕይወት ትግል ቀጥተኛ ውጤት ሆኖ ከፊታችሁ እንደቆመ ሰው፣ በአመጽ ያልታጀበ ትግል ስላለው የሞራል ጉልበት እኔ ሕያው ምስክር ነኝ። በማህተመ ጋንዲና በማርቲን ሉተር ኪንግ እምነትና ተግባር ውስጥ ደካማነትና መፋዘዝ እንደሌለም አውቃለሁ። ነገር ግን አገሩን ለመጠበቅና ለመከላከል ቃለ-መሃላ እንደፈጸመ አንድ የአገር መሪ፣ በእነሱ [በኪንግና በጋንዲ] ተምሳሌት ብቻ ልመራና ልጓዝ አልችልም።
ዓለምን የምጋፈጣትና የምረዳት እንደ አመጣጧ ነው፤ እናም በአሜሪካ ሕዝብ ላይ አደጋ ተደቅኖ ዕያየሁ እጄን አጣጥፌ ልቀመጥ አልችልም። በፍጹም እንዳትሳሳቱ፣ ክፋት በዓለም ላይ አለ። አመጽ የሌለበት ንቅናቄ የሂትለርን ጦር ሊገታው አይችልም ነበር።
ድርድር የአልቃይዳ መሪዎች መሣሪያቸውን እንዲያወርዱ ሊያሳምናቸው አይችልም። ‹የኃይል አማራጭ አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ነው› ማለት ጨለምተኝነትን ማቀንቀን አይደለም፤ ይልቁንስ ለታሪክ፣ ለሰው ልጅ ኢ-ፍጹማዊነት፣ እንዲሁም ለምክንያታዊነት ውስንነቶች እውቅና መስጠት ነው … ›› ኦባማ በዚሁ ንግግራቸው ጦርነት አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ የተናገሩት ስህተት አይደለም። በአደባባይ በግልጽ ‹‹አልደራደርም፤ አገር አፈርሳለሁ›› ከሚል አካል ጋር ከጦርነት በስተቀር በምን መግባባት ይቻላል ? አንዳንድ ጦርነቶች አስገዳጅና አማራጭ አልባ ናቸው።ኧረ ለመሆኑ ‹‹አልደራደርም፤ አገር አፈርሳለሁ›› ብሎ የተነሳን ቡድን መፋለምና አገርን ማዳን ነውርና ወንጀል የሚሆነው እንዴት ነው ?።
የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊው ባራክ ኦባማ በሊቢያና በሶሪያ ላይ ጦርነት አውጀው አገራቱን ሲያፈራርሱ ግን ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን ‹‹አላየንም፤ አልሰማንም›› ብለዋል።[በእርግጥ ሰው እንዳይታዘበን ብለው ይሁን በሌላ ምክንያት ባይታወቅም የአሜሪካ የጦር ሄሊኮፕተሮች ሊቢያን ሲደበድቡ አንድሪው ኖርዝ የተባለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በወቅቱ ‹‹Libya፡ Obama’s Step from Nobel Winner to Warrior›› የሚል ጽሑፍ ጽፎ ነበር።] ምን ይሄ ብቻ? ኦባማ ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ አሜሪካ በአፍጋኒስታን ያላት ጦር በሦስት እጥፍ እንዲጨምር ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒትስር ሜናሄም ቤጊን ከግብጹ ፕሬዝደንት አንዋር ሳዳት ጋር እ.አ.አ. በ1978 ዓ.ም የሰላም ኖቤል ሽልማትን በጋራ አሸናፊ ከሆኑ ከአራት ዓመታት በኋላ (እ.አ.አ. በ1982 ዓ.ም) ጠቅላይ ሚኒትስር ቤጊን ከሊባኖስ ጋር ጦርነት ገጥመው ነበር።እ.አ.አ በ1990 ዓ.ም የሽልማቱ አሸናፊ የነበሩት የሶቭየት ኅብረቱ ሚካሂል ጎርባቼቭ ከሽልማቱ በኋላ ከባልቲክ የነፃነት ተዋጊዎች ጋር ፍልሚያ ውስጥ ገብተው እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል።
የእስራኤሎቹ ይስሃቅ ራቢን እና ሺሞን ፔሬዝ የሰላም ኖቤል ሽልማትን አሸንፈው ከፍልስጤም ‹‹የነፃነት ታጋዮች›› ጋር መዋጋታቸውንም እንዳንዘነጋ። ለነገሩ እነዚህ ምን ያስገርማሉ? በቺሊ ሕጋዊው የዶክተር ሳልቫዶር አሌንዴ መንግሥት እንዲገለበጥ ያደረጉትና ለአርጀንቲና አምባገነን መንግሥት ድጋፍ የነበራቸው እጅግ አወዛጋቢው የአሜሪካ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ አልፍሬድ ኪሲንጀርም የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሲሆኑ የምዕራብ መገናኛ ብዙኃን ‹‹የሰላም ሰው›› ብለው ያሞገሱ ጉደኛ ተቋማት ናቸው።
ከዚህም አልፈን እንነጋገር ከተባለ እኮ ሽልማቱ በስሙ የተሰየመለት ዋናው ሰውዬ አልፍሬድ ኖቤልም እኮ ‹‹የሞት ነጋዴ›› (Merchant of Death) የሚል መጠሪያ አለው። ሄንሪ ኪሲንጀር የቬትናም ጦርነት እንዲያበቃ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ‹‹የሰላም ሰው›› ተብለው ሲሸለሙ ሕጋዊውን የቺሊን መንግሥት ሲገለብጡ ግን ዝም ተብለው ታልፈዋል።በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረው የድንበር ውዝግብ እልባት እንዲያገኝ በወሰዱት ወሳኝ እርምጃ ምክንያት የተሸለሙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አሸባሪዎችን ለመደምሰስ ሲፋለሙ ደግሞ ‹‹ጠብ ጫሪ›› ብሎ መፈረጅ የለየለት ኢ-ፍትሐዊነት ነው።
እነዚህ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ የጦር ኃይሏን ለማጠናከር የምትወስዳቸውን እርምጃዎችንም እንደጠብ አጫሪ ድርጊት ይመለከቷቸዋል።ፖለቲካዊ ትኩሳቱ እጅግ የጋለ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ (Horn of Africa) ቀጣና የምትገኘው ኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሏን ብታጠናክር ጥፋቷ ምንድን ነው? ደግሞስ ‹‹ሰላም ከፈለግክ ለጦርነት ተዘጋጅ›› አይደል የሚባለው?! እውነት ነው፤ ሰላም የሚፈልግ አካል ለጦርነት መዘጋጀት አለበት።
አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ኃያላን አገራት ለጦርነት ስለተዘጋጁ (የመከላከያ ኃይላቸውን አጠንክረው ስለገነቡ) ማንም እየተነሳ ‹‹ላፍርሳችሁ፣ ልደብድባችሁ …›› እያለ አይዘባበትባቸውም።የመከላከያ ኃይልን ማጠናከር የሚያስፈልገው ለሌሎች ጡንቻን ለማሳየት ብቻም ሳይሆን ሰላም አግኝቶ ትኩረትን ወደ ልማትና ወደ ሌሎች ዘርፎች ለማዞር ነው።
ለጦርነት መዘጋጀት ማለት ‹‹ኑ ግጠሙኝ!›› እያሉ መደንፋትና ሌሎችን መተናኮል አይደለም፤ ‹‹ጠንካራ የጦር ኃይል ስላለኝ እኔን ለመተናኮስ እንዳታስቡ›› የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ሌሎቹ ልካቸውን አውቀው እንዲቀመጡና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ሕይወት እንዲኖር ማድረግ (ምቹ ሁኔታ መፍጠር) ማለት ነው። አቅሙን የገነባ አገር ከውስጥም ከውጭም ጠላት ስለማይደፍረው ለረጅም ጊዜ ሰላም ሆኖ ይዘልቃል፤ ጠላት ገፍቶ ከመጣም ጠንካራ አቅም የገነባው አካል ያን ጠንካራ አቅሙን ተጠቅሞ ጦርነቱን በፍጥነት ስለሚያጠናቅቀው የሰላም መደፍረሱ ለረጅም ጊዜ አይቆይም፤ የሰላም ሁኔታው በፍጥነት ወደነበረበት ይመለሳል።
‹‹ሰላም ከፈለግክ ለጦርነት ተዘጋጅ›› ማለት ይህ ነው፤ሌላ ትርጉም የለውም! ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት ተቀብለው ዛሬ ግን ጦርነትን የሚመሩ ሰው ሆኑ›› የሚለው የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ተራ ውንጀላ ነው።
አንድ መሪ አገሩን ከመጠበቅ የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሌለው እነዚህ ሚዲያዎች ዘንግተውታል (ማስታወስ አልፈለጉም) ማለት ነው።የማንኛውም የአገር መሪ የመጀመሪያውና ዋነኛው ኃላፊነቱ የአገሩን ህልውና (ሰላምና ፀጥታ) መስጠበቅ ነው። የሰላም ኖቤል ሽልማት አገርን ለአሸባሪ አሳልፎ ለመስጠት የሚፈፀም ስምምነት አይደለም።
በአጠቃላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከአሸባሪዎች ጋር ለመፋለም ወደ ጦር ግንባር መሄዳቸው ‹‹ኢትዮጵያን በማፍረስ የአፍሪካን ብሎም የዓለምን ሰላም አደጋ ላይ የመጣል ዓላማ ያላቸውን አሸባሪ ቡድኖችን በመደምሰስ ለዓለም አቀፍ ሰላም መስፈን ላበረከቱት ግሩም አስተዋፅኦ›› የሚል ሌላ የሰላም ኖቤል ሽልማት ያሸልማቸዋል እንጂ በጠብ ጫሪነት አያስወቅሳቸውም!::
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ኅዳር 29/2014