የወያኔ ወራሪ ኃይል በእውር ድንብር ከገባበት ከበባ ውስጥ መውጣት ሲሳነውና በተለያዩ ግንባሮች የተማመነበት ኃይልና ጉልበት ሲከዳው ከዓመት በፊት ወደ ነበረበት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ፊቱን የሚያዞርበት ጊዜው ላይ ደርሷል።
ለዚህም ባለፉት ዓመታት ሲያደርግ እንደነበረው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የኢትዮጵያ ነገሥታት የተዛባ ትርክትን በመቆስቆስ በግንባር የገጠመውን የሽንፈት አጀንዳ ለማስቀየር በዲጂታል ክንፉ ዳር ዳር እያለ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሕዝብም ተባብሮ በግንባር ያለውን ድል በአጭር ጊዜ እንዳሳካ ሁሉ የተፈጠረውን የአንድነት መንፈስ አጠንክሮ የሚቀጥልበትና ቀጣዩን የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ጆሮ ባለመስጠት የሚመክትበት ወቅት ላይ ይገኛል።
ፕሮፓጋንዳ ከየትኛውም ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የበለጠ ኃይል ያለውና ኢላማ ያደረገውን አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ሊያከሽፍና መልሶ ለራሱ አላማ መጠቀሚያ ሊያደርግ የሚችል መርዛማ መሣሪያ መሆኑን ተገንዝቦ፣ በተለይም በከፍተኛ ደረጃ በሶሻል ሚዲያ ለሚሰራጭ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆነው ወጣቱ ክፍል ከምን ጊዜውም በላይ ራሱን ማዘጋጀት የሚጠበቅበት ወቅት ላይ ይገኛል። ለዚህም የፕሮፓጋንዳ ምንነትና እንዴት ተፈጽሞ እንዴት ጉዳት እንደሚያስከትል ይጠፋዋል ተብሎ ባይታሰብም በዚህ ወቅት ማስታወሱና ራሱን ዝግጁ አድርጎ እንዲጠብቅ ማድረግ ተገቢ ነው።
‹‹በጥሩ ዘዴና ባለመታከት የሚቀርብ ፕሮፓጋንዳ መንግሥተ ሰማያትን ሲኦል አስመስሎ ማቅረብ፣ በተቃራኒው ደግሞ በጣም አስከፊ የሆነውን ኑሮ ገነት አስመስሎ ማቅረብ ይቻላል።›› ይላል የወያኔያዊ አስተሳሰብና ተግባር አባት የሆነው አዶልፍ ሂትለር። ውጤታማ ፕሮፓጋንዳ ማለት አንድን ኢላማ የተደረገበት የኅብረተሰብ ክፍል የያዘን አቋም አሊያም እውነት ነው ብሎ የተቀበለው ሀሳብ በፕሮፓጋንዲስቱ ጫና ያልመጣ መስሎ ሲሰማውና እራሱ አንፃራዊ ሁኔታዎችን መርምሮ የደረሰበት መደምደሚያ እንደሆነ ሲገምት ነው።
ይህን ዓይነት ‹‹ውጤታማ›› የፕሮፓጋንዳ ስትራቴጂ ለመተግበር ፕሮፓጋንዲስቱ በቅድሚያ የዚህን ኢላማ ያደረገበትን የኅብረተሰብ ክፍል ማንነትና ምንነት ያጠናል፤ ደካማና ጠንካራ ጎኑን ይፈትሻል፤ የመረጃ ምንጩን፣ መረጃውን የሚያገኝበትን መንገድና መረብ
ይመረምራል። ከዚህ ጥናት በኋላ በምን መልክ ምን መረጃ እንዴት ማቅረብ እንዳለበትና ለምን አላማ ይህ ሊሆን እንደሚችል ይለያል። በተለያየ መንገድ ማለትም በመጽሐፍ፣ በምርምር መልክ፣ በትምህርት፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ እናም በግለሰብ ደረጃ ፕሮፓጋንዳ ሊዛመት ይችላል።
የመገናኛ መሣሪያዎች ከህትመት ወደ ቴሌፎን፣ ከዚያም ወደ ራዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት እየተራቀቁ በሄዱ መጠን የአሳማኝ መልዕክቶች ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ተፋጥኗል። በመገናኛ ረገድ የተደረገው ይህ ሥር ነቀልና ፈጣን ለውጥ ሰዎች ከሁሉም አቅጣጫ በሚጎርፉ መረጃዎች እንዲጥለቀለቁ በማድረጉ የመረጃ መጨናነቅ ተፈጥሯል።
በዚህም ብዙ ሰዎች የሚደርሷቸውን መልዕክቶች ሳይመረምሩ ወይም ሳይጠረጥሩ ፈጠን ብለው በመቀበል ይህን መጨናነቅ ለማቅለል ሲሞክሩ ይስተዋላል። በተለይ ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንዲኖር የማይፈልጉት መሠሪ ፕሮፓጋንዲስቶች ይህን አቋራጭ መንገድ ይወዱታል።
ፕሮፓጋንዳ ስሜት በማነሳሳት፣ ስጋት በማሳደር፣ አሻሚ ትርጉም ባላቸው ቃላት በመጠቀምና የአመክንዮ ሕጎችን በማጣመም ምክንያታዊ አስተሳሰቦችን ያዳክማል። ታሪክ እንደሚመሰክረው እንደነዚህ ያሉ ዘዴዎች በጣም ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው አሉታዊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ረቂቅነትም ከዚህ የቆየ ጥናት የመነጨ ነው። አንድ ሰው የሚቀርብለትን መረጃ መጠየቅ ካልቻለ፣ በጥቅሉ እውነት ነው ብሎ ከተቀበለው ተሸንፏል ማለት ነው።
እርግጥ ነው ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ ንግድ እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ዘመን ለተራው የኅብረተሰብ ክፍል ሁሉንም መረጃ ለመመርመር የሚያስችል ማስረጃ ለማግኘትና ይህንንም መንገድ ለመከተል ጊዜም ገንዘብም ይጠይቃል። ነገር ግን መሠረታዊ የመጠየቅ ክህሎት ከዳበረ ጉዳዩን ከስር መሠረቱ መድረስ ባይቻል እንኳን በጥርጣሬ ለመመልከት ይረዳል።
ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ ሰው ውስን የሚያምነውን አቋም በጥቅሉ እንውሰድ፣ ይሄን አቋሙን እንዴትና በምን መረጃ ላይ ተመስርቶ ሊደግፍ ቻለ? ለያዘው አቋም እውነተኛ የሚላቸው የመረጃ ምንጮች ከየትና በምን መንገድ አገኛቸው? የእነዚህ የመረጃ ምንጮች የኋላ ታሪክ ምንድን ነው?
ይህ የያዘውን አቋም ከሌላው ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ካለው መሠረታዊ አቋም በምን መልኩ ይቃረናል ወይንስ ይታረቃል? ይሄን ፕሮፓጋንዳ በግልጽም በሽፋንም የሚያቀብሉት አካላት የወሰደውን አቋም ተከትሎ ምን እንዲያደርግ ነው የሚፈልጉት? አንድ ሰው ይሄንና መሰል ነጥቦችን መጠየቅና መመርመር ከቻለ ዓይኑን እየተገለጠና እየሆነ ያለውን እየተረዳ ይሄዳል።
የሚባለውና በመሬት ላይ ያለውን ነገር አነፃፅሮ እየሆነ ያለውን እውነታ መለየቱ ላይ ነውና ቁም ነገሩ። ሰላም አሰፍናለሁ ያለ ሁሉ የሰላም ዘብ ላይሆን ይችላል፤ የዴሞክራሲ ማማ ነኝ የሚል አገርና መንግሥት ሁሉ የሚለውና እየሆነ ያለው የተለያየ ነገር ሊሆን ይችላል፤ አንድነታችሁን ላስጠብቅ የሚል ሁሉ የበለጠ ሊበትነን ይችላል። አሊያም ነፃነት አመጣለሁ ወይንም አመጣሁ ያለ ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የባርነት ቀንበር ሊያጠልቅ እያመቻቸ ሊሆን ይችላል።
ነፍሱን ለመታደግ እርዳታ የሚያስፈልገው ሕዝብና መንግሥት የቁስና የገንዘብ እርዳታ ለጋሽ ነኝ እያለ አገርን ሊዘርፍ ሲዳዳ የሚያምነው ካለ ችግር ነው። እኔ በትክክል ምንድን ነው የምፈልገው? ይሄ ፍላጎት እንዴትና ከየት መጣ? ፍላጎትና ተግባር እንዴት ይግባባል? ይሄን መመርመር እንጂ ጠበቃ ነኝ ያለ ሁሉ ለክስ እያመቻቸ እንዳይሆን መጠንቀቅ ዘመናዊነት ነው። ፕሮፓጋንዳ ሁሉ መጥፎ አላማ አለው ሊባል ባይችልም እንዲህ ኢትዮጵያ ላይ እንደተቃጣው ያለ እንደ ምስጥ ውስጣችንን ሰርስሮ ለመጣል የደረሰ አደገኛ ነገር የለም።
እጅግ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ በአጠቃላይ በህልውናችን የመጣና ሳናውቀው የህልውናችን ማጥፊያ መሣሪያና ሰለባ መሆናችን ነው። የፕሮፓጋንዲስት አላማ ታውቆም ሆነ ሳይታወቅ እንድንከተለውና ለፈለገው ግብ መሳካት መሣሪያ እንድንሆን ማድረግ ነው። ከዚያ በኋላ እኛ ላይ ስለሚፈጠር ተፅዕኖ ኃላፊነት አይወስድም። ይሄንን የቆየ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለመቋቋም የግድ ተቋማዊ በሆነ መንገድ የካውንተር ፕሮፓጋንዳና ኢንዶክትሬኔሽን ማዕከል በግልጽም ሆነ በሽፋን አገሪቱ ማቋቋም ያስፈልጋታል።
ምክንያቱም በግለሰብ ደረጃ ይሄን ሁሉ ከብረት የከበደ የፕሮፓጋንዳ ናዳ ተቋቁሞና ተከላክሎ መቆም አይቻልምና። ለጊዜው ግን አፍንጫችን ስር ያለውን የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ከዚህ በፊት ያደረሰብንን መከፋፈልና የደቀነብንን አደጋ በማስተዋል ‹‹ከዚህ በኋላ በቃ›› ልንለውና ጆሮ ልንነፍገው ይገባል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 29/2014