እንኳን ለ123ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሰን። ጊዜ እየተዟዟረ መልካችንን በገዛ መስታወታችን እያሳየን ነው። እንደምታውቁት ደግሞ ይህን ሰሞነ ዘመን ከአዲስ ዓመት በዓል ውጪ የምንስማማበት የጋራ ነገር ቸግሮናል። ሳይኖር ቀርቶ ነው ወይ? አይመስለኝም። ቤታችን በአንድ ወገን አለን የምንለውን የአንድነት ምልክት የሚፍቁ፤ በአንጻሩ ደግሞ ሊገነቡ በሚታገሉ መካከል ትንቅንቅ የሚታይባት ሆናለች።
«ጠላታችን ድህነት ነው… ጠላታችን የገዛ አስተሳሰባችን ነው… ጠላታችን ማኅበራዊ ሚድያ ነው…» ወዘተ፤ ሌላው ቢቀር በጋራ አንድ ጠላት ላይ ተስማምተን አናውቅም። ሰው እንዴት በዓድዋ ድል የተለያየ ሃሳብ ይይዛል። በአፄ ሚኒሊክ የሚመራው አርበኛ የዋለው ውለታ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ያኮራል፣ በዓለም የሰው ልጆች ታሪክ በደማቅ ቀለም ተፅፏል፡፡
ታዲያ እኛ እንዴት ይሄን መቀበል አቃተን? እንዴትስ ከመሬቷ አፈር ላይ ተዘርቶ የበቀ ለፍሬዋን በምታበላን አገር እንደራደራለን። «የእኛ» በምንለው ችግር ተስማምተንና ችግሩ ላይ ዘምተን ድል እስክናደርግ ድረስ፤ እንዲህ በአባቶቻቸን ድል መታሰቢያ «እንኳን አደረሰን» ብንባባል አይሻልም? እዚች ጋር አንዲት ነገር ልንገራችሁ! እንዲህ ነው፤ ትላናትና «አንዳንድ አካላት» ንእንኳን አደረሰን ስል ነበር። «እንኳን አደረሳችሁ» የሚል ሰው ራሱንእንዳራቀ ይቆጠራል ብዬ ነው፤ በጣም ቤተሰባዊ ሳደርገው «እንኳን ለ123ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ አደረሰን» ነው ያልኩት። ከታች አንድ አስተያየት አየሁ፤ «አደረሰን ያልሽው እነማንን ነው?» ብለው ጠየቁኝ።
ጉድ ፈላብን! «እኔ እንኳ ሁላችንንም በሕይወት ያለነውን የሰው ልጆች ጉዳዩ ውስጥ አካትቼ «እኛ» በሚለው ቃል መሰብሰቤ ነው።» ብዬ በጨዋነት መልስ ሰጠሁኝ። «እና ስለእኛ ይመለከትሻል?» ብለውኝ እርፍ። ወዳጄ! ለጸብ ምክንያት የሚፈልግ አንዳንድ አካል አለ፤ ዝም አልኩኛ! ለካ ማለት የነበረብኝ «እንኳን አደረሰንአደረሳችሁ- አደረሳቸው» ነው። እንዲህ ሲሆን የሚመለከተው ሁሉ የየራሱን ይወስዳል ማለት ነው። እኔ የምለው ግን! ቃላት ከትፈንና ሰንጥቀን፤ ፈልጠንና ቆርጠን ለመከራከር ምክንያት በመፈለግ እስከመቼ እንዘልቅ ይሆን? ብቻ ግን እኔ ያው በመረጥኩት ሄጃለሁ፤ «እንኳ ንአደረሰን» ብያለሁ።
ነገር አበዛሁ! እየውላችሁ ሰሞኑን በአእምሮዬ ሁለት ሃሳብ እንዲሁ ሲመላለስ ነበር። አንደኛ እኛ በእምዬ ምኒልክ ዘመን ተገኝተን ቢሆን ኖሮ ወይም ደግሞ ምኒልክ በእኛ ዘመን መጥተው ጦርነቱ አሁን ቢካሄድስ? ይለኛል፤ ሃሳቤ። በእርግጥ አንዱን ሃሳቤን ይዞ ለመሄድ እንዲያስችለን እኛ ወደ ኋላ ተመልሰን ብንገኝ ሳይሻል አይቀርም።
እምዬ ምኒልክ መጥተው ስንት ጉዳችንን ያዩብናል? ደግሞስ «ምነው ልጆቼ! ጦብያን ምን አስነካችኋት?» ቢሉን ምን መልስ አለን? ነገሩን እንደ ፊልም በምልሰት ተመልከቱት፤ ያኔ የነበረው ሁሉ እንዳለ ሆኖ የዛሬ ሰዎች ብቻ በያዝነው ስብእና እና ስነልቦና ወደ1888ዓ.ም ብንሄድ ወይም ብንመለስ ብሎ እንደማሰብ ነው። እናሸንፍ ነበር? ማሸነፉስ ይቅር እንደ ውም ከመንቀዥቀዧችን የተነሳ ከጦርነት ስልት ወጥተን ያለ ግዜው ውጊያውን ጀምረነው ድል ተነስተን ኢትዮጵያዬን አንገት እናስደፋት ነበር። ለምን? ችኩል ነና! እንቸኩላለን።
ለመውደድም ለመጥላትም እንቸኩላለን፤ ተስፋ ለማድረግም ተስፋ ለመቁረጥም እንቸኩላለን፤ ለመጀመርም ለማቋረጥም እንቸኩላለን፤ ለማዘንም ደስ ለመሰኘትም እንቸኩላለን፣ ለማድነቅም ለመኮነንም እንቸኩላለን፤ ለመመረቅም ለመስደብ ምእንቸኩላለን፤ ለመሄድም ለመመለስም እንቸኩላለን… ብቻ ከማን እንደወረስነው እንጃ እንጂ ችኩልነት የሚባል ጸባይ ይታይብናል።
«ኢትዮጵያ አገሬ ንገሪን አናስብ፤ መች ነው የሚገጥም ደግ መሪ ከሕዝብ።» እላለሁ አንዳንዴ። በእርግጥ ደግ መሪና ሕዝብ በእምዬ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ገጥመው ነበር መሰለኝ። በተረፈ ግን አንዳንዴ ከመሪ ምንም ሳይጎድል በችኩልነታችን ብቻ ብዙ ኪሳራ አምጥተናል፤ እናመጣለንም። ዓድዋ ዘመን ላይ ተመልሰን ቢሆን ኖሮ የሚሆነው ከዚህ ጋር አንድ ነው።
መቸኮል ሰው ያደርጋል ወይ? ካልን፤ ወተት ሳይረጋ ቂቤ ይወጣዋል ወይ? ወደሚለው ጥያቄ እናቀናለን። ወተት በሳይንስ በተብራራ ነገር ግን በተፈጥሮ ተረጋግቶ ሲቀመጥ የሚያስገኘው ትርፍ የላቀ ይሆናል። ወተት ሲንቦጫቦጭ ቢኖር ምን ዋጋ አለው? ምንም። የተወሰነ ጊዜ ሰጥቶ ከረጋ በኋላ ግን ቂቤም በሉት ዓይብ…ትርፉ ብዙ ነው።
ጾም መያዣ ላይ ሆነንማ ይህ እንዴት ይጠፋናል! መረጋጋት ማለት ሰው እንደ ሰው ሆኖ፤ አእምሮውን ተጠቅሞና አስቦ፤ ልቡን ተገልግሎበትና አመዛዝኖ መንቀሳቀስ ማለት ነው። መረጋጋት ጸጋ ነው ብንለውስ ያንሳል? እኛ ግን «ነገ ዐይንህ ይበራልሃል ቢሉት ዛሬን እንዴት አድሬ አለ» እንደሚባል ለትባለታሪክ፤ የዐይን አብሪውን ትዕግስት ሁላ የምንፈታተን ነን። እንደው ዓድዋ ይቆየንና፤ በየመንገዳችን ባዶ አውቶብስ ለመሳፈር አስር ሰዎች ሲጋፉ አይታችሁ አታውቁም? «ኧረ አውቶብሱ ሰፊ ነው ለሁላችንም ይበቃል!» እየተባለ እንኳ የማይሰማ ብዙ ነው፤ ከሚጋፉት አስሩ ሰዎች መካከል ነው እንግዲህ የምላችሁ።
ፈርዶብን እንዲህ ሆንን መሰለኝ፤ በቃ! ልክ መልካም ነገር ሲመጣ ጸባያችን ሁሉ ይከፋና ችኩል እንሆናለን። የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል እንላለን፤ ግን እስኪወለድ መታገስ አንችልም። እጅግ ብዙ ተራራ ገፍተንና መከራ አልፈን ተሻግረናል፤ የአንዲት ማለዳ ድንግዝግዝ ብርሃንን እስከፀሐይ መውጣት መታገስ ግን አንችልም። እና ምን አለፋችሁ! እምዬ ምኒልክ ከሌላ አገር ሕዝብ አስመጥተውም ቢሆን ይዋጉ ነበር እንጂ እኛን ይዞ ድል የሚታሰብ አይመስለኝም። ጠቢቡ ሶሎሞን ልጄን «ሰው ሁን!» ሲል፤ እንግዲህ ሰው ሆኖ ከመፈጠር የሚልቅ ሰው መሆን አለማለት ነው። ልክ የዓድዋ ዘመን ሰዎች ሆነው እንደተገኙት ዓይነት ሰውነት ማለት ነው። እነርሱ በሰውነታቸው ሰው ሆነው የወጡት ቸኩለው አይደለም፤ እና ወዳጄ! ረጋ ብንል ያዋጣልም። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011
በሊድያተስፋዬ