ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የሴቶች ጨዋታ የፊታችን ሀሙስ በጅግጅጋ ከተማ ይጀመራል። «ስፖርት ለሴቶች ሁለንተናዊ ለውጥ» በሚል ለሚካሄደው ውድድር ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑም ተገልጿል።
የሴቶች ስፖርት ተሳትፎን ዓላማ ያደረገው ይህ ውድድር በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፤ በሴቶች እየተመራ ሴቶች እርስ በእርሳቸው ይፎካከሩበታል። በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደውን ውድድር የማስተናገድ ተራውን የወሰደው የጅግጅጋ ከተማ፤ በየደረጃው የተቋቋመው የዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴ መሰናዶውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በጋራ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።
«ስፖርት ለሴቶች ሁለንተናዊ ለውጥ» በሚል የሚካሄደው ውድድር ለአስር ቀናት የሚካሄድም ነው። ሴቶች የሚሳተፉባቸው በርካታ የስፖርት እንቅስቃሴ መድረኮች ቢኖሩም ብቻቸውን የሚወዳደሩበትና የሚመሩትን ተጨማሪ መርሀ ግብር መዘርጋት በማስፈለጉ ዕቅድ ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚቀጥልም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ ገልጸዋል።
ሶስተኛው የሴቶች ጨዋታ የተሳካ እንዲሆንም ሁሉም ክልሎች የውስጥ ውድድሮቻቸውን አከናውነዋል። በዚህም መሰረት በውድድሩ ላይ ክልሎቻቸውን ወክለው 2ሺ500 ሴት ስፖርተኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ኮሚሽኑ በድረገጹ ጠቁሟል። ውድድሩን በ10 የስፖርት ዓይነቶች ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸው እና በገንዘብና በስልጠና ድጋፍ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዳዊት አስፋው ናቸው።
መንግስት ህብረተሰቡ በየደረጃው ተሳታፊ እና ተጠቃሚ የሚሆንባቸውን ስፖርቶች ለማስፋትና ለማሳደግ የሚያደርጋቸውን እንቅሴዎች እንደ ሚያጠናክርም በመግለጫው ተመልክቷል። በዚህም መሰረታዊ የኢትዮጵያ ስፖርት ችግሮች በጥናት እየተለዩ የሚፈቱባቸውን አቅጣጫዎች በማስቀመጥ በመስራቱ በርካታ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። ሆኖም ከሀገሪቷ ህዝብ ቁጥር አኳያ በተለይ ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶችን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን ማከናወን ገና በጅምር ላይ ነው።
ስለሆነም የሴቶች ስፖርት ተሳትፎን ዓላማ ያደረገው ይህ ጨዋታ በርካታ ልምዶችና ተሞክሮች የሚገኝበት መድረክ እንደመሆኑ፤ ህብረተሰቡ ከጎናቸው በመሆን ስፖርታዊ ጨዋነትን ባሰፈነ መልኩ በማበረታታት ጨዋታው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ሚናውን መወጣት እንዳለበትም ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ባልቻ ጠቁመዋል።
የመጀመሪያው መላ የሴቶች ጨዋታ በ2007 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ አስተናጋጅነት የተካሄደ ሲሆን፤ ዘጠኙም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቮሊቦል፣ ጠረዼዛ ቴኒስ፣ ቼስ፣ ዳርት እንዲሁም በፓራሊምፒክ ተሳትፈው ነበር።
ሁለተኛው መላ የሴቶች ጨዋታ በ2009 ዓ.ም በሀረሪ ክልል አስተናጋጅነት ሀረር ከተማ የተካሄደ ሲሆን፤ ሶስተኛው ውድድር በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት በጅጅጋ ከተማ ከየካቲት 28- መጋቢት 08/2011 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ይሆናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
ብርሃን ፈይሳ