ኢትዮጵያ የጸረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠልም ጽህፈት ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል ፎረም ማቋቋሙን አስታውቋል።
በዘርፉ ያለው ፍላጎትና የችግሩ ውስብስብነት እያደገ ይገኛል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጸረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት እና ሌሎች ተቋማት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ አልተቻለም። በመሆኑም የስፖርት ባለሙያዎችን ተሳትፎ ማሳደግና የበኩላቸውን ርብርብ እንዲያደርጉ ለማስቻል፤ ቋሚ የጸረ-አበረታች ቅመሞች ፎረም ማቋቋምና ወደ ተግባር እንዲሸጋገር ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል።
በአገሪቷ በሚካሄደው የጸረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ የስፖርት ባለሙያዎችና ማናጀሮች፤ በባለቤትነት እንዲሁም በኃላፊነት ችግሩን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል ቋሚ ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ ፎረሙ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ መሆኑን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን በድረ ገጹ አስነብቧል።
የፎረሙ ዋና ተግባርም፤ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ዘላቂ በሆነ መንገድ መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ በየጊዜው ስትራቴጂዎችን በመንደፍና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበሩ ማስቻል ነው። በየደረጃው ያለውን ግንዛቤ ማጎልበት እና የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀምም ይሁን በሌላ መንገድ የሚፈጸሙ የህግ ጥሰቶችን መቀነስ እና ንጹህ ስፖርትንም ማስፋት የፎረሙ ዓላማ ነው።
በጸረ-አበረታች ቅመም ፎረም ማቋቋሚያ ደንብ መሰረትም፤ የአመራሮች ምርጫ ተካሂዷል። በዚህም ዶክተር ይልማ በርታ የፎረሙ ሰብሳቢ፣ አቶ ንጉሴ ጌቻሞ ምክትል ሰብሳቢ፣ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ፀሀፊ፣ ወይዘሮ ብርቱካን ቀፀላ እና ወይዘሮ ኬሪያ ሁሴን አባል በመሆንም ተመርጠዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጸረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ፤ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ከአሸናፊነት ፍላጎት ጋር በተያያዘ ከትክክለኛው መንገድ ውጭ ኃይል ሰጭ ቅመሞችና ዘዴዎች በተለያዩ መንገድ በመውሰድ እና በመጠቀም ተገቢ ያልሆነ ውጤት የማስመዝገብ ዝንባሌዎች መፈጠራ ቸውን ገልጸዋል። ባለፉት ጊዜያትም በተለያዩ ስፖርቶች የማጭበርበር ስልቱ እጅግ እየረቀቀ እንደመጣና ስፖርተኞችን ጨምሮ ያለ አግባብ ውጤት የማስመዝገብ ችግሮች ጎልተው መስተዋላቸውንም ጠቅሰዋል።
የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው፤ የጋራ ቅንጅታዊ አሰራርን በማስፈንና የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በጋራ በመከላከልና በመቆጣጠር ሀገሪቷ በስፖርቱ መስክ ማግኘት የሚገባትን ጥቅምና የተገነባውን መልካም ገጽታ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
ብርሃን ፈይሳ