አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት፤ ጠንካራ መሪ እንዲወጣባት አይፈልጉም። እንግሊዞች አጼ ቴዎድሮስን የወጉት ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ማዕከላዊ መንግሥት ለመመስረት የጀመሩትን እንቅስቃሴ ለማምከን እንደሆነ አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ያስረዱናል። አሜሪካ በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግሥትን በአሻጥርና በተጽዕኖ ከስልጣን አስወግዳ የራሷን አሻንጉሊት መንግሥት ያስቀመጠችበት ምስጢርም ይሄው ነው።
አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዶ በመረጠው መንግሥት መተዳደር ሲጀምርና ኢትዮጵያ ተስፋዋ ሲለመልም አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት መሪዎች እውነታውን በዝምታ ለማየት አልወደዱም።
ከፍ ባለ የህዝብ ትግልና መስዋእትነት ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ ሀይሉ እውነተኛ የፌደራሊስት ሥርዓት በመገንባት በእኩልነት፣ በመፈቃቀርና በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከፍ ያለ አላማ አንግቦ ወደ አደባባይ ብቅ ካለ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው።
ግቡም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማምጣት፤ ህዝቦችን ከድህነት፣ ከተረጂነትና ከጠባቂነት አውጥቶ የበለጸገች ሀገር መፍጠር ነው። እርግጥ ነው እድገትና ብልጽግና ሲታሰብ ከዓለም ሀገራት ጋር በትብብር መሥራት ይጠበቃል። ለዚህም የለውጡ መንግሥት ስልጣን በጨበጠ ማግስት ከአጎራባችና ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን በማጠናከር ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል።
መንግሥት ከጎረቤትና ከተቀሩት የዓለማችን ሀገራት ጋር በትብብር ለመሥራት የነበረው ቁርጠኛነት በተጨባጭ ትርጉም ያለው ውጤት የተመዘገበበት ነው። የኢትዮ -ኤርትራ የሰላም ስምምነት፤ በኢትዮጲያ፣ በሶማሊያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው አካባቢያዊ ህብረት ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው።
የለውጥ ሀይሉ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተው የውጪ ፖሊሲው፤ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም አሳልፎ የመስጠት ፍላጎት ያለው አይደለም። የውጭ ጣልቃ ገብነትንም የመቀበል ክፍተት የለበትም፤ ኢትዮጵያ በራሷ ምህዋር ላይ አንድትሽከረከር ይፈልጋል።
ሰጥቶ በመቀበል መርህ ያምናል። ሰጥቶ በመቀበል መርሁ የመረዳዳት እንጂ የሀገርን ጥቅምና ክብር አሳልፎ የመስጠት አጀንዳ የለውም። ታዲያ ይህ የለውጡ መንግሥት አካሄድ ለእጅ አዙር ቀኝ ገዢዎች ምቹ ሁኔታ ባለመፍጠሩ ለምን ውሃ ቀጠነ የሚል ሰበባሰበብ እየደረደሩ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምእራብ ሀገራት መንግሥታት በሀገሪቱ ላይ ጫና በመፍጠር ላይ ናቸው።
እነዚህ ሀገራት የኢትዮጵያ አካሄድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትንም ከእጃችን ያስወጣብናል የሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል። ለዚህም ሲሉ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጣውን የለውጥ መንግሥት አስወግደው የሚጋልቧቸውን ፈረሶች ለማስቀመጥ እንቅልፍ ካጡ ውለው አድረዋል ።
ከፕሬዚዳንት እስከ ሹማምንት፣ ከጋዜጠኛ እስከ አክቲቪስት የተለያዩ የጦር አውድማዎችን በመክፈት እየተንቀሳቀሱ ነው። የእርዳታ ክልከላና ማእቀብ ማድረጋቸው ሳያንስ በሸብርተኝነት ለተፈረጀውና የእብሪት ጦርነት አውጆ የህዝባችንን የእለት ተእለት ህይወትና የነገ ተስፋ እየተገዳደረ ያለውን ሕወሓትን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ በመርዳት ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ገናና ስም ያላት ሀገር ነች።
የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር ህዝቦች ነጮችን ጦርነት ገጥመው ያሸነፉበትን ታሪክ ያስመዘገበች፤ የራሷ ፊደል ያላት፤ ለማንም ተንበርክካ የማታውቅ፤ በተለያዩ ጊዜያት የመጡባትን ወራሪ ጠላቶች አሳፍራ የመለሰች ሀገር ነች።
ጥቃት የማይወዱና በባርነት ከመኖር ይልቅ ከጠላት ጋር ተፋልመው የክብር ሞትን የሚመርጡ ህዝቦች ያሏት፤ ለአፍሪካውያን የነጻነት ፋና ወጊ፤ ለፓን አፍሪካኒዝም መመስረት እርሾ የጣለች፤ በአፍሪካ አህጉርም ይሁን በአፍሪካ ቀንድ ተጽእኖ ፈጣሪ፤ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፤ የአምባሳደሮችና የዲፕሎማቶች መናኸሪያ፣ ተስማሚ የአየር ጸባይ፣ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሀብት፤ የዓለምን ትኩረት የሚስብ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ያላት ጭምር ነች።
ይችን የጥቁር ህዝቦች ምልክትና ኩራት የሆነችን ሀገር ማንበርከክና በቁጥጥር ስር ማዋል ለአሜሪካና ለአንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት አፍሪካን ሙሉ አንደመቆጣጠር ነው። በሀገሪቱ ላይ የተከፈተውም ሁለንተናዊ ዘመቻ የብርሃን ጭላንጭል ማየት የጀመረችውን ሀገር ወደ ነበረችበት ጭለማ በመድፈቅ አፍሪካ ቀና እንዳትል ማድረግ ነው።
የተከፈተብን ዘመቻ የኢትዮጵያን ተስፋ የማጨለም፤ የህዝቦቿን የተባበረ ክንድ የማዛል፤ አንድነታቸውን የማዳከምና ገናና ታሪኳን ዝቅ የማድረግ፤ የሚፈልጉትን አሻንጉሊት መንግሥት አስቀምጦ በእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ ስር የወደቀች ኢትዮጵያን የመፍጠር ነው። ኢትዮጵያን በማንበርከክ ሌሎች አፍሪካውያንንም ተስፋ ቢስ የማድረግ ነው።
መንግሥት የያዘው የልማት፣ የእድገትና የብልጽግና አቅጣጫ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚጋባ ነው።
ይህ ደግሞ ነገዎቻቸውን በአፍሪካ ላይ ተስፋ ላደረጉ ሀይሎች ምን ማለት እንደሆነ ለመገመት የሚከብድ አይደለም። ‹‹ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም›› እንዲሉ የኢትዮጵያን ጅማሮ ማምከን ለነዚህ ሀይሎች ምን ትርጉም እንደሚኖረው ለማሰብ አያስቸግርም። በኢትዮጵያ በህዝብ የተመረጠን መንግሥት አስወግደው የራሳቸውን ተላላኪ መንግሥት ለመሰየም የሚሯሯጡትም ለዚሁ ነው።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከስልጣን መወገዱ አንገብግቧቸው መልሰው ሊያነግሱት የሚሞክሩትም እንደፈለጉ የሚጋልቡት በመሆኑ ነው። እንደፈለጉ የሚጋልቡት አሻንጉሊት መንግሥት ሲያገኙ ትውልድ መጥቶ ትውልድ በሄደ ቁጥር የእርዳታ ስንዴ፣ ብድርና የገንዘብ እርዳታ እየተመጸወተ የሚኖር ህዝብ ይፈጥርላቸዋል፤ የሚወረወርለትን ቁራሽ እየጠበቀ የሚኖር ህዝብ ደግሞ አድርግ የተባለውን ይፈጽማል እንጂ ለምን? የሚል ጥያቄ አያነሳም።
ቢያነሳም የአሻንጉሊት መንግሥታት ዋንኛ ተልእኮም ይህንኑ ጥያቄ ማፈን ነው። የመቶ ሚሊዮን ህዝብን ፍላጎትና ምርጫ ወደ ጎን ብለው የኢትዮጵያን ህዝብ ሲዘርፍና ሲያስለቅስ ከነበረ አሸባሪ ቡድን ጋር የመተባበራቸው ምስጢር ከዚህ ውጭ አይሆንም። ይህ ባይሆን ኖሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባ የወጋ፣ ንጹኋንን የጨፈጨፈ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የሃይማት ተቋማትን ያወደመ ቡድንን ባልደገፉ ነበር።
ለነገሩ አሸባሪው ሕወሓት እና አሜሪካ ተወራራሽ ባህሪ እንዳላቸው ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል። አሜሪካ ዓለምን መግዛት፤ ዓለምን መቆጣጠር ትፈልጋለች። ከእኔ በላይ ማንም የለም ትላለች፤ በመሆኑም በተለያዩ ሀገራት እጇን እያስገባች ስሪተ መንግሥታቸው እርሷ በምትፈልገው መንገድ እንዲሆን ጫና ታደርጋለች። የአሸባሪው ሕወሓትም ባህሪ እንዲሁ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከእኔ በላይ ማንም የለም የሚል ነው። መቀሌ ተቀምጦ እጁ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል ይደርሳል፤ ለጥቅሙ ሲል ብሄርን ከብሄር ያጋጫል፤ የሰዎች እልቂት የንብረት መውደም ግድ አይሰጠውም።
ሁለቱም እውነትና ዲሞክራሲን በወሬ ካልሆነ በስተቀር በተግባር አያውቋቸውም። ተቀናቃኛችን ነው በሚሉት አካል ላይ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዙ ነጥብ በማስጣል ተሰሚነት ለማግኘት የሚጥሩ ናቸው። ያልሆነውን ሆነ፤ የሆነውን አልሆነም በሚል አይኔን ግንባር ያድርገው እያሉ የሚምሉ ናቸው።
ሰላም እያደፈረሱ ጣታቸውን ወደ ሌሎች መጠቆም ተክነውበታል። በጥቅም እየደለሉ ሌሎችንም ከጎናቸው ማሰለፍ ያውቁበታል፤ ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ›› እንደሚባለው ጩኸትን ቀምቶ በማስተጋባት የሚወዳደራቸው የለም። አሜሪካ ‹‹ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲኦል መግባትም ካለብን እንገባለን›› ብሎ ከተነሳ ቡድን ጋር መተባበሯ ኢትዮጵያን ለማዳን ሳይሆን ለማፍረስ ወስና እየተንቀሳቀሰች ስለመሆኑዋ መሳያ ነው።
ለዚህም ነው አሸባሪ ቡድኑ በሶስት ሳምንት ህግ የማስከበር ርምጃ ትቢያ ከሆነ በኋላ በአሜሪካና በግብረአበሮቿ እርዳታ አንዲያንሰራራ የተደረገው። ወገን፤ አሁን ያለንበት ወቅት የመጪዋ ኢትዮጵያ እጣፈንታ የሚወሰንበት ነው። የውስጥ አረሞቻችንን በመንቀልና ኢትዮጵያን ከቀኝ ገዢዎች መንጋጋ በመመንጨቅ በራሷ ምህዋር ላይ እንደትቆም ማድረግ፤ ካልሆነም በጨለማ ውስጥ እየዳከርን መኖር የሚሉትን አማራጮች የያዘ ነው።
ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከባትን ሉዓላዊት ሀገር አስከብሮ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለበት። ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ኩራት፤ የነጻነት ሰንደቅ እንድትሆን አባቶቻችን የህይወት ዋጋ ከፍለዋል። ከአባቶቻችንን የወረስነው ድልን እንጂ ሽንፈትን አይደለም።
በወሬም በጦርነትም የማንፈታ ትውልዶች መሆናችንን ለማሳየት መዘጋጀት ይኖርብናል። ነገ አሜሪካና አጋሮቿ የሀገራችንን ድንበር ዘልቀው ጦርነት ሊከፍቱብን ቢያስቡ በቬትናም፤ በሶማሌያና በአፍጋኒስታን የገጠማቸውን ውርደት አከናንበን እንልካቸዋለን እንጂ አንገዛላቸውም። ሥነ ልቦናችንን ለዳግም ድል እናዘጋጅ።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ኀዳር 27 / 2014