ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዓመቱ ከሚያካሂዳቸውና በጉጉት ከሚጠበቁ ትልልቅ ውድድሮች መካከል አንዱ የዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ነው። በተያዘው ወር መጨረሻ የሚካሄደው ውድድሩ ከወዲሁ ተጠባቂ ሲሆን፤ ማህበሩ በድረገጹ ላይ በርቀቱ ስኬታማ የሆኑና በውድድሩም ተጽእኖ ፈጣሪ እንደሚሆኑ የሚጠበቁትን ሀገራት ዘርዝሯል። ከአምስቱ ቀዳሚ ሀገራት መካከልም አንዷ ኢትዮጵያ ሆናለች።
በረጅም ርቀት አትሌቲክስ ስኬታማ ከሆኑት የዓለም ሀገራት ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ በዚህ ዝርዝር ባስመዘገበችው ውጤት ተጠቃሽ ስትሆን፤ የምትቀድማት ብቸኛዋ ሀገር ጎረቤቷ ኬንያ መሆኗም ነው በዘገባው የተጠቆመው። ዘገባው እአአ በ2004ዓ.ም በብራሰልስ አዘጋጅነት የተካሄደውን ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከተሳትፎዎቿ መካከል እጅግ የደመቀችበት መሆኑን አንስቶ፤ በተለይ ስኬታማ የሆኑትን አትሌቶችን ስምም ጠቅሷል።
43 ዓመታትን ያስቆጠረው የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር እአአ በ1973 በቤልጂየም የተጀመረ ውድድር ነው። ውድድሩ እአአ እስከ 2011 ድረስ በየዓመቱ ሳይቆራረጥ ሲካሄድ ቢቆይም ከ2013 ጀምሮ ግን በየሁለት ዓመቱ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይ ባላት ተሳትፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ውጤት ያስመዘገበችው እአአ በ1981 ሲሆን፤ ሞሃመድ ከድር ባጠለቀው የብር ሜዳሊያ ነው። በቀጣዩ ዓመትም አትሌቱ ሰዓቱን በማሻሻል ጭምር አሸናፊ በመሆን ኢትዮጵያን በመድረኩ ከወርቅ ሜዳሊያ ጋር ሊያወዳጃት ችሏል።
አትሌት በቀለ ደበሌ እአአ በ1983 አሸናፊ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወዳጆ ቡልቲ የነሃስ ሜዳሊያ አጥልቋል። እአአ 1986 አበበ መኮንን የብር ሜዳሊያ ባለቤት ከሆነ በኋላ፤ ፊጣ ባይሳ የነሃስ ሜዳሊያ እስኪያገኝ፤ ለአምስት ዓመታት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አልታዩም ነበር።
እአአ 1994 በሃንጋሪዋ ቡዳፔስት በተካሄደው ውድድርም ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ለመጀመሪያ ጊዜ የነሃስ ሜዳሊያ በማጥለቅ ስሙን በታሪክ አስጽፏል። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ጥቂት አትሌቶች የብርና የነሃስ ሜዳሊያዎችን ቢያገኙም የወርቅ ሜዳሊያው በበላይነት የተያዘው በኬንያውያን አትሌቶች ነው። ኬንያዊው ፖል ቴርጋት ለአምስት ዓመታት በተከታታይ በማሸነፍም ታሪካዊ አትሌት ነው።
እአአ ከ2012 ጀምሮ ግን የበላይነቱ ከኬንያዊው አትሌት ወደ ኢትዮጵያዊው ወጣት የተሸጋገረበት ነበር። እስካሁንም በመድረኩ አቻ ያልተገኘለት ቀነኒሳ በቀለ ለአምስት ጊዜያት በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት እረፍት በኋላ በድጋሚ ወርቅ በማጥለቅ በ12 ኪሎ ሜትር ውድድር የስድስት ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን ወርቃማ ታሪኩን አስመዝግቧል። ቀነኒሳ በዚህ ውድድር አጭር ርቀትም ስኬታማ ሲሆን፤ አምስት የወርቅና አንድ የብር በአጠቃላይ ስድስት ሜዳሊያዎችን የግሉ በማድረግም ባለ ክብረወሰን ነው።
እአአ በ2004 በብራሰልስ በተካሄደው ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ፣ ገብረእግዚአብር ገብረማርያም እና ስለሺ ስህን በሰከንዶች ልዩነት ተቀዳድመው ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ የወሰዱበት ውድድር እስካሁንም እጅግ ስኬታማው ነው። አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም አንድ የወርቅ ሁለት ብር ሜዳሊያዎችን ሲያስመዘግብ (በአዋቂዎች ዘርፍ)፤ ስለሺ ስህን አንድ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ከመድረኩ አግኝቷል። አትሌት ኢማና መርጋ እአአ በ2011 እና 2013 የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን፤ ሙክታር እድሪስና አባዲ ሃዲስ ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች ናቸው።
በሴቶች በኩል ኢትዮጵያ ከሜዳሊያ የተወዳጀችው በኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ሲሆን፤ ለሶስት ተከታታይ ዓመታትም ድሉ የኢትዮጵያውያን ነበር። እአአ በ1995 እና 1997 በደራርቱ በ1996 ደግሞ በጌጤ ዋሚ የወርቅ ሜዳሊያው ተወስዷል። ሁለቱ አትሌቶች በየዓመቱ እየተፈራረቁ የቆዩ ሲሆን፤ በተለይ አትሌት ጌጤ ዋሚ ሁለት የወርቅ፣ ሁለት የነሃስ እና ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ስኬታማ አትሌት ናት።
ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ መሪማ ደንቦባ፣ እጅጋየሁ ዲባባ፣ መሰለች መልካሙ እና መስታወት ቱፋም ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች ሲሆኑ፤ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ሶስት ወርቅ እና አንድ ብር በማግኘት ከስኬታማ አትሌቶች መካከል ትመደባለች። ጥሩነሽ በአጭር ርቀትም አንድ የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ ያገኘች አትሌት ናት። አትሌት ህይወት አለሙ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ በላይነሽ ኦልጂራ እና ነጻነት ጉደታም በቅርብ ዓመታት የሀገራቸውን ስም ማስጠራት የቻሉ አትሌቶች ናቸው።
በተመሳሳይ በአዋቂ ወንድና ሴት በቡድን ውጤትም ኢትዮጵያ የተሻለ ታሪክ ያላት ሲሆን፤ በወንዶች 10 የወርቅ፣ 13 የብር እና 7 የነሃስ ሜዳሊያዎችም ተመዝግበዋል። በሴቶች ደግሞ 11 የወርቅ፣ 12 የብር እና 1 የነሃስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል። ከዚህ ባሻገር በርካታ አትሌቶች በወጣቶች፣ በአጭር ርቀት ሀገር አቋራጭ እንዲሁም በየርቀቱ በቡድን የሜዳሊያ ባለቤቶች ሆነዋል።
ማህበሩ ከኢትዮጵያ ባሻገር በዘርፉ ስኬታማ የሆኑትን ሀገራት አንስቷል። ኬንያ ለሶስት አስርት ዓመታት በስኬታማነት የቆየች ሀገር ስትሆን፤ በተለይ ከ2010 ወዲህ በርካታ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ላይ ያለች ሀገር መሆኗም ተጠቁሟል። በወንዶች በኩል ኒውዝላንድ እና አሜሪካ ሲጠቀሱ በሴቶች ደግሞ ፖርቹጋል ትጠቀሳለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
ብርሃን ፈይሳ