ካባ በአገራችን እጅግ ልዩ ቦታ የሚሰጠው የልብስ ዓይነት ነው፡፡ የተለያየ ዓይነት ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያየ ትርጉምም አለው፡፡ ለአብነት ያህል ካባ የሚደረበው ስልጣን ሲሰጥ ፣ ዕውቀት ከፍ ሲል እንዲሁም የክብር ደረጃ ሲጨምር ነው። እንዲሁ በዋዛ የሚጎናጸፉት ዓይነት አይደለም፡፡ ካባ በተለያየ ህብረቀለም ያሸበረቀና በወርቀዘቦ የተንቆጠቆጠ ስለሆነም የክብር መገለጫነቱ ከሚባለው በላይ ከፍ ያለ ነው ቢባል አይበዛበትም፡፡
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ላይ እያነሳ ካልደረብኩላችሁ የሚለው ካባ፤ ሲደርቡት የሚያስከብር ወይም ደረጃን ከፍ የሚያስደርግ ሳይሆን በተቃራኒው የቆመ ነው፡፡ ልክ በአገራችን እንደሚደረገው ክብር ለሚሰጣቸው ሰዎች ትከሻቸው ላይ ሲደረብ ውበት የሚሆንና የሚመች ሳይሆን የሚኮሰኩስ ዓይነት ነው። ውበት ማጣቱ እና መኮስኮሱ ብቻ ሳይሆን ትከሻንም የሚያጎብጥ ነው፡፡
እርግጥ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ከራሱ ሀገር ፍላጎት በመነሳት እንዳሻው ማድረግ የሚችል ፈላጭ ቆራጭ እንደሆነ ቢታመንም ፤ ካልደረብኩላችሁ እያለ ለሚፎክርበት የካባ ስሪት ግን የብዙዎች ልፋትና ጥረት እንዳለበት መረዳቱ ተገቢ ነው፡፡ ካባው በተንኮል ሐር፣ በኩሸት ሱፍ፣ በሴራ በርኖስ እንዲሁም በአስመሳይነት ወርቀዘቦ ተውቦ ከግምጃ ቤቱ እንዲወጣ ከሚያግዙት ከዋንኞቹ ጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች መካከል ግምባር ቀደም ተጠቃሹ አሸባሪውና በግራ መጋባት ውስጥ የተቀመጠው ሕወሓት ነው፡፡
ይህ የግምጃ ቤቱ ካባ (በስውር እየተጣለብን ያለውና ሊጣልብን የተዘጋጀው ማዕቀብ) እንደነገርኳችሁ አይሞቅም፤ አይደላም፤ ኮስኳሽ ነው፡፡ ግምጃ ቤቱ ካልደረብኩላችሁ እያለ የሚፎክርበት ካባ በሰብዓዊ መብት ስም የተለበጠ፣ በዕርዳታ ስም የተሸሞነሞነ እንዲሁም በድጋፍ ስም የተንቆጠቆጠ በመሆኑ የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ ደግሞ ሳይታወቅ ጠልፎ እንዲጥለን እንዲሁም አንኮታኩቶ እንዲያስቀምጠን የታሰበ ነው፡፡
የማዕቀብ ካባውን ለመደረብ የሚደረገው ሩጫ በዋናነት በኢትዮጵያ ምድር ልማት እንዳያፋጠን ብሎም ሰላም እንዳይሰፍን ለማድረግ ነው፤ ይህንን ሴራ ዜጎቿ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ የማይገፋ ተራራ ብሎም የማይጠፋ ደማቅ አሻራ ሆኖ እያዛላቸው ነው እንጂ ቢሳካላቸው ግን የአሁኑ ጥረታቸው ያንን ደማቅ አሻራ ለመጋረድ ብሎም ለማጥፋት ከመናፈቅ የመነጨ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ቀዳሚ ትኩረቱ ኢትዮጵያን በማዳከም ምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ጀምሮ የአሜሪካ ግምጃ ቤት፣ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል በአሜሪካ ታዛቢነት የተካሄደውን እና ኢትዮጵያ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነትን የተቃወመችበትን ውይይት ሲመራ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ የሆኑት ስቴቨን ሙንሽን፣ አንዴ ሱዳን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ግብጽ እያቀኑ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲመክሩ መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡
ይህ ሁሉ ድካም ኢትዮጵያ ስለምን እጇን አልሰ ጠችምን የሚያሳብቅ ነው እንጂ አሜሪካ የምትጥለው ማዕቀብ እርሷ እንዲታሰብላት እንደምትፈልገው በቀጣናው ስትራቴጂያዊ ለውጥን ስለሚያስከትል አይደለም፡፡
አሜሪካ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት፣ ወታደራዊና የደኅንነት አባላት ላይ የቪዛ ዕቀባ ማድረጓም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የጉዞ ዕቀባ ውሳኔውም መሰረት ያደረገው በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ቢሆንም እውነታው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ እነርሱ የተቆረቆሩለት ወንበዴውና አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው ይቅር የሚያስብለው ጥቃት ወደጎን ተትቶ ሌላ ሌላውን አንስቶ መጣል አግባብነት የሌለው አካሄድ ነው። እርግጥ ነው ‹ስንተዋወቅ አንተዋወቅ› እንዲሉ እነርሱም ይህን አሳምረው የሚያውቁት ጉዳይ ነው፡፡
ሰበብ አስባብ እየፈጠሩ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እጃቸውን ለማስገባት ደፋ ቀና ሲሉ ቢሰነባብቱም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በተደጋጋሚ በውስጥ ጉዳዩ ጣልቃ በመግባት ተጽእኖ ለማሳደር የሚሹ መንግሥታትን ጫና ጨርሶ እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ኢትዮጵያውያኑም በተመሳሳይ ባገኟቸው መድረኮች ሆነ ምቹ መድረኮችን በመፍጠር ጭምር የኢትዮጵያን መንግሥት ሐሳብ ሲያራምዱ ቆይተዋል፡፡
በአገር ቤቱ ያሉ ዜጎችም ሆኑ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ እየተሴረ ስላለው ሴራ፣ ኢትዮጵያን ለመጉዳት እየተናፈሰ ስላለው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም አሸባሪው ሕወሓት እያካሄደ ስላለው ጭፍን ድርጊቱ ጭምር አሜሪካም ሆነች ጀሌዎቿ እያደረጉ ያለውን ጫና በመቃወም ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ሲገልጹት ቆይተዋል፡፡ ይህ የመንግሥትም ሆነ የዜጎች አካሄድ ያበሳጫት አሜሪካ ጉዳዩ የበለጠ እየወጠረችው ትገኛለች።
ለዚህም ነው አሜሪካ ፣ ምርቶቻቸውን ከቀረጥ እና ታሪፍ ነፃ በሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ ዕድል ከሰጠቻቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አገራችንን ከአገዋ ዕድል መንጥቃ ለታወጣት ውሳኔ ላይ የደረሰችው፡፡ እርሷ ግን ኢትዮጵያን ከዚህ ዕድል ውጪ ማድረጓ ምናልባት ሀገሪቱ ከጀመረችው የለውጥ ጉዞ ተንበርክካ ትመለሳለች በሚል ቀቢጸ ተስፋ ተሞልታ ይሆናል፡፡
የዚህ ዕድል ተጠቃሚ አለመሆን ኢትዮጵያ በንግዱ ዘርፍም ሆነ በሌላው አብቅቶላታል ማለት አይደለም። ሰሞኑ አዲስ አበቤዎች ባደረጉት የድጋፍ ሰልፍ ላይ የከተማዋ ከንቲባ ያሰሙትን አንድ ነጥብ ብቻ ማንሳቱ ማሳያ ይሆናል፡፡ ይኸውም ‹‹የዓደዋ ልጅ በአገዋ አይንበረከክም›› ሲሉ ነበር ከንቲባዋ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተው ያስተላለፉት መልዕክት፡፡ እርግጥ ነው ልክ እንደቀድሞዎች አባቶቻችን እና አያቶቻችን ታሪክ ለመሥራት የታደልን ትውልዶች መሆናችንን ለእኒህ አሜሪካኖች ማን በነገራቸው ?!
እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ አገራችን የማንከፍለው መስዋዕትነት አለመኖሩን ዓለም ያውቀዋል፡፡ የቀሩት ታሪኮቻችንም የዚሁ እውነታ ቅጂዎች ናቸው። አገር ለማፍረስ አስከ ሲኦል እወርዳለሁ ብሎ በአደባባይ ለፎከረ አሸባሪ ኃይል ሊኖረን የሚችለው ምላሽ ምን ሊመስል እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም።
ይህንን አሸባሪ ቡድን ለመታደግ በሰብዓዊነት ስም የሚደረግብንን ጣልቃ ገብነትም ሆነ እጅ ጥምዘዛ ሉዓላዊነታችንን እና ነፃነታችንን የሚጋፋ፤ አገራችንን የሚያሳጣ በመሆኑ በፍጹም የምንቀበለው አይሆንም፡፡ ይህንን ለማድረግም የቀደመው ታሪካችን አይፈቅድልንም። ለዚህም ነው በሰብዓዊነት ስም የሚጎነጎኑ ሴራዎችን እና በዚሁ የሴራ ድርና ማግ የተበጁ ካባዎችን አንደርብም ስንል በአንድ ድምፅ እምቢኝ! አሻፈረኝ! የምንለው፡፡
ቅድስት ሰለሞን
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2014 ዓ.ም