የኑሮ ሁኔታ፣ በአቅራቢያ እና በዙሪያ ያሉ ሰዎችና ሁኔታዎች እንዲሁም ገጠመኞች የሰውን ልጅ እንደሚቀርጹ ይታወቃል። «ሰው ኑሮውን ይመስላል» መባሉም የአካባቢና የሁኔታዎች ድምር ውጤት መሆኑን ለማሳየት ነው። ሰውን አስቀደምኩ እንጂ እንስሳትም በጥቂቱ መሰልጠን(በተለይ የቤት እንስሳት) ይችላሉና ይህ እውነት ይመለከታቸዋል።
ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ ዘገባው ፈረስነቱን እንጂ ወይፈንነቱን ስለማታውቀው አስቶን አስነብቧል። ታሪኩ የሚጀምረው ከአምስት ዓመታት በፊት በፈረንሳይ በሚገኝ አንድ የእንስሳት ማርቢያ ውስጥ ነው። በትንሿ ማርቢያ አንዲት ላም ትወልዳለች፤ እምቦሳዋም ወንድ በመሆኑ አድጎ ለወተት ሳይሆን ለስጋ እንደሚሆን ይጠበቅ ነበር።
በዚያው ወቅት ደግሞ ሳቢን ራውዝ የተባለች የፈረስ ትርዒት አሰልጣኝ በሞት በተለያት ፈረሷ ምክንያት ሃዘን ላይ ወድቃ ነበር። ከ20 ዓመታት በላይ አብሯት የቆየው የህይወት ዘመን ጓደኛዋ ህልፈት ምክንያትም ከፈረስ ጋር ዝምድና ላይኖራት ከውሳኔ ደርሳ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለችም በገጠራማው የከብት እርባታ ጊዜዋን ማሳለፍ ትጀምራለች። በእርባታው ከሚገኙት ላሞች መካከልም በተለይ ነፍሰጡር የነበረችውን በልዩ ሁኔታ ትንከባከባት ነበር። ቀኗ ሲደርስም ላሚቷ አስቶን የሚል ስያሜ የተሰጠውን ጥጃ ትገላገላለች። ራውዝም እንደ ላሚቷ ሁሉ ከሚያምረው ጥጃ ጋርም ጓደኝነቷን ታጠናክራለች።
አስቶንም ቢሆን ራውዝ በገባች በወጣች ቁጥር ከስሯ የማይጠፋ ወዳጇ ሆነ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የእርባታው ባለቤት የሆነችው ሴት አስቶንን በመሸጥ ሌሎች ላሞችን የመግዛት ውሳኔ ላይ ትደርሳለች። ራውዝ ከለመደቻቸውና ከምትወዳቸው ወዳጆቿ ሊነጣጥላት በሚችለው ሃሳብ ደስተኛ ባለመሆኗ ምን ማድረግ እንደሚገባት ታስባለች።
ሃሳቧ ተሳክቶላትም አስቶንን እና እናቱን የግሏ ለማድረግ በቃች፤ አስቶን አንድ ዓመት ሲሆነውም ከማርቢያው በማስወጣት ወደራሷ ስፍራ ወሰደቻቸው። ራውዝ በወቅቱ ከአስቶን እና እናቱ ባሻገር ሳሚ የተባለ ፈረስ ስለነበራት፤ ሁለቱ እጅግ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ጓደኛሞች ሆኑ። በዚህም ይመስላል አስቶን ወይፈንነቱን ረስቶ የፈረስ ባህሪን መላበስ የጀመረው።
ራውዝ ወደ ቀደመ ስራዋ በመመለስም ፈረሷን በመሰናክል መዝለል እና ሌሎች ትርዒቶችን ታሰለጥነው ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ያልጠበቀችውን ነገር ከወይፈኑ ተመለከተች። ሁኔታውን ስትገልጽም «ለሳሚ አንዳንድ ስልጠናዎችን እሰጠው ነበር። ነገር ግን ስልጠናውን ወይፈኑም ይከታተለው ነበር፤ እናም እርሱንም ማሰልጠን ጀመርኩ። ሰው ተቀምጦበት መጋለብ ባይችልም ድምጼን ተከትሎ ግን የተለያዩ ነገሮችን ያደርግ ነበር። እያደገ ሲመጣም መጋለብን አስተማርኩት» ትላለች።
ወይፈኑን እንደፈረስ መጋለብ ለማስለመድ እንዲሁም ኮርቻውን በላዩ ላይ ለማስቀመጥ የነበረው ጥረት ከፍተኛ ቢሆንም፤ የራውዝ ትዕግስት ግን በሂደት 1ነጥብ3 ቶን የሚመዝነውን ወይፈን ሊገራው ችሏል። ከሶስት ዓመታት በፊትም ራውዝ ከአስቶን ጋር በመሆን በአቅራቢያዋ በሚገኝ ማሳያ ትርዒት ያቀርባሉ። በወቅቱም ወይፈን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረጉ ያልተለመደ በመሆኑ በመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆነ።
አሁን ግን ትርዒታቸው ከዚያም አልፎ በመላው የአውሮፓ ምድር የሚታይ ሆኗል። አስቶን አልፎ አልፎ ከአብሮ አደግ ጓደኛው ሳሚ ለረጅም ጊዜ ሲለይ ፍርሃት ቢጤ ቢሰማውም የሚያደርገው እንቅስቃሴ ግን ራውዝን የሚያስደስት ነው። ከተመልካቹም ከፍተኛ አድናቆት በጭብጨባ እንደሚቀርብለት ኦዲቲ ሴንትራል በተንቀሳቃሽ ምስል አስደግፎ አቅርቧል።
አስቶን በመሰናክሎች ላይ መዝለልን ጨምሮ እንደሚታዘዘው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ በደንብ ችሏል። ነገር ግን አሁንም መማር የሚገባው በርካታ ነገር መኖሩንም ራውዝ ትጠቁማለች። በአሁኑ ወቅት ከመላው ዓለም በማህበራዊ ድረገጾች እጅግ በርካታ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፤ በፌስቡክ 11ሺ በኢንስታግራም ደግሞ 3ሺ400ሰዎች ይከታተሉታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
ብርሃን ፈይሳ