የእጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) «ዓድዋ» የተሰኘ ሙዚቃ ወደኋላ እየመለሰ ደግሞ ወደፊት እያደረሰ፤ ወዲህ ዛሬንም ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። የሙዚቃው ግጥም እያንዳንዱ ቃል ሕይወት እንዳለው ሆኖ ይናገረናል። ከዚሁ ሙዚቃ ግጥም መካከል፤ «…ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሲያከብር…» የምትለው ስንኝ እንደ ባለቅኔ የስንኝ ቋጠሮ ብዙ እውነት ተሸክማለች።
ዓድዋ፤ ኢትዮጵያውያን በአንድ ስም ተጠርተው ኢትዮጵያን ለመታደግ፤ ኢትዮጵያውያንን ለማዳን ሲሉ የተሰዉበት ድል ነው። ወዲህ እንመለስ፤ ዓለማችን በተለያየ ግብር የሚያልፉ ሰዎችን ታስተናግዳለች። የታደሉቱ «በደግነት… በፍቅር… በክብር» የተዋጉ ባለአገሮች፤ በተናጠል ስማቸው ሳይጠራ እንደ አንድ ሕዝብ ሲሞገሱ ይኖራሉ። ከራሳቸው በላይ ታላቅ ሥራን ሠርተውም ያልፋሉ። ከዛ ዝቅ ሲል ባለታሪኮችን አውቆ፤ ታሪክን ተረድቶ፤ ከታሪኩ ተምሮ ተካፋይ ለመሆን የሚተጉ ይገኛሉ። እነዚህ ስንት እንደተከፈለባቸው፣ ስንት ወጪ እንደ ወጣባቸው ያውቃሉና፤ ግብራቸው ታላቅ ነው። ከሁለቱም ያልሆኑስ? እነርሱ የት እንደሚመደቡ አናውቅም። እነሆ የዓድዋ ድል አንድ ሁለት ሦስት እያለ ተቆጥሮ 123ኛው ዓመት ላይ ደርሷል።
ያኔ የተዋጉና መስዋዕት የሆኑ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ ዛሬ ደግሞ ታሪክን ሊካፈሉ፣ በእውቀትና በጉልበት የአባቶችና እናቶችን ድካም በዘመን መካከል የሚጋሩ ልጆቻቸው ተገኝተዋል። በዘመን አቆጣጠራችን የካቲት 24 ቀን 2011ዓ.ም ላይ ነን፤ ዘንድሮ የዓድዋ ድል በዓል እንዴት ታሰበ? ምን ተወራ? ምን ተሠራ? ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ አካባቢዎች ከተደረጉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓላትና ኪነጥበባዊ ክዋኔዎች መካከል እጅግ ጥቂቱን ልናስቃኛችሁ ወደናል። በነገራችን ላይ፤ የዓድዋ ድል በዓል እስከ ሰባተኛው ዓመት ድረስ አልተከበረም ነበር። በ1895ዓ.ም ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ዓድዋ ሊከበር ነው ተባለ።
ይሄኔም እምዬ ምኒልክ አንድ መልዕክት አስተላልፈው እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ። መልዕክታቸውም ‹‹ድሉን ስናከበር ወይም ስናስብ በመታበይ አይደለ በትህትና ሊሆን ይገባል›› ሲሉ ያስተላለፉት ነው። እንዲህ አሉ «ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና እኔም ይኽንን በዓል እንዲህ አድርጌ ማክበሩ፤ እናንተንም ማድከሜ እግዚአብሔር በቸርነቱ ሰባት ዓመት ሙሉ በእረፍትና በጤና ስላኖረን ስለዚህ ነገር ማክበር ይገባል ብዬ ነው። እንጂ ለጥጋብና ለትዕቢት፣ ሠራዊት በዛ የጦር መሣሪያ በረከተ ለማለት አይደለም።…» ጉዞ ዓድዋ ጉዞ ዓድዋ እንደ ስሙ እስከ ዓድዋ የሚደረግ ጉዞ ነው። ይሁንና ይህኛው ጉዞ በእግር የሚደረግ እንጂ በተሽከርካሪ አልያም በበራሪ አውሮፕላን የሚከወን አለመሆኑ ለየት ያደርገዋል።
ጉዞው በ2006 ዓ.ም በሰባት የሚዲያ እና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተቋቋመው ሲሆን አንድ ሺህ አስር ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናል። መነሻውንም ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ አድርጎ የዓድዋ ተራሮች ድረስ የሚያደርግ የእግር ጉዞ ነው። 2009 ዓ.ም በተካሄደው የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ነበር፤ ጉዞ ዓድዋ። በሽልማት ሥነሥርዓቱ ጊዜ የቀረበው የጉዞ ዓድዋ ታሪክ እንዲህ የሚል ቃል ይገኝበታል፤ «የመላው አፍሪካውያን ድል እስከ መባል የደረሰው ታላቁ የዓድው ድል፤ የግዝፈቱን ያህል ክብር እና መታወሻ ሥነ ሥርዓት ሳይኖረው እየተከታተለ ከመጣው ትውልድ ጋር የበዓሉ አከባበር ዐውድ እየወረደ ጭራሽ እየተዘነጋ እና እየደበዘዘ መሔድ ያሳሰባቸው የጉዞ ዓድዋ መሥራቾች፤ ትውልዱ ትኩረት ሰጥቶ የድሉን መንፈስ እንዲጋራ ለማድረግ ይህንን የጉዞ ሃሳብ አመንጭተዋል።» ጉዞው በእርግጥ ዝም ብሎ መጓዝ ብቻ አይደለም፤ የንባብና የማወቅ መንገድም ነው።
ተጓዦች በመንገዳቸውና ባረፉበት ቦታ መጻሕፍት ለውይይት ይቀርባሉ፤ በታሪክ ዙሪያ ይነጋገራሉ፤ ይማማራሉ። ባለፉባቸው መንገዶች እግራቸውን አጥበው በትህትና የሚቀበሏቸውም ብዙዎች ናቸው። ከዛ ባለፈም በረገጡት ቦታ ሁሉ ኢትዮጵያውያን የሠሩትን ታሪክና ገድል እያነበቡና እየጎበኙ ማለፋቸው ይህን ጉዞ ወደር የሌለው ያደርገዋል። ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ የተካሄደው ጉዞ ዓድዋ (ጉዞ ዓድዋ 6) ከታሪካዊቷ ከተማ ሐረር ተነስቷል። የዘንድሮው ጉዞ «ፍቅር ኢትዮጵያ» የሚል መሪ ሃሳብ ያለው እንደሆነም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ነበር። ታዲያ ጥር 7 ቀን 2011ዓ.ም የጀመረው ጉዞ ትናንት የካቲት 23 ቀን 2011ዓ.ም ዓድዋ ደርሷል። ተጓዦች በመንገዳቸው ብዙ ነገሮች ገጥመዋቸዋል፤ አንዳንዶቹ የሚነገሩ የተቀሩት በልባቸው የሚያኖሩት። ይሁንና ይህ በእግር የሚደረግ፣ አድካሚ ጉዞ ታሪክን በአካል የመጋራት ያህል የዛሬን ወጣቶች ከቀደሙት ጋር በመንፈስ የሚያገናኝ ነው።
ታሪክን – በምልሰት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ስር የሚገኘው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል በየ15 ቀኑ የጥበብ ውሎ ያደርጋል። ልክ እንደዛው ሁሉ ባሳለፍነው ሳምንት የካቲት 16 ቀን 2011ዓ.ም ዓድዋን አንድ አካል ያደረገ ተመሳሳይ የጥበብና የውይይት መድረክ ተዘጋጀቶ ነበር። በዛም ላይ ዓድዋን የተመለከተ ለውይይት መነሻሃሳብ ያቀረቡት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ነበሩ። ፕሮፌሰር አበባው «ዓድዋ፡ የዘመቻው መልካም አጋጣሚዎችና የድሉ ፈተናዎች» በሚል ርዕስ ነው መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት። የድሉ መልካም አጋጣሚዎች ይቆዩንና ስላነሷቸው ሦስት ፈታኝ ነገሮች እናንሳ። እንደ ታሪክ ባለሙያው ገለጻ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚይዝ ዘመን ነው። ለዚህም ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን ጠቅሰዋል። አንደኛው ከዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የኢትዮጵያን አንድነት ለማምጣትና ተከፋፍሎ የነበረውን መልሶ የተጠናከረ እንዲሁም የዘመነ አንድ አገር ለመፍጠር ብዙ ጥረት የተደረገበት መሆኑ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በእጅጉ የተፈተነበት ጊዜ መሆኑ ነው። ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ኢትዮጵያ ካደረገቻቸው ጦርነቶች ሁሉ በወቅቱ የነበረውን ትውልድ ብዙ ያስጨነቀ ብሎም ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ተንቀሳቅሳ የዘመተችበት ውጊያ ነው ይላሉ፤ ዓድዋ። ይጠይቃሉ፤ «በቀላሉ የተገኘ ነበር ወይ?» አልነበረም። ለዚህም ቢያንስ ሦስት ፈተናዎች እንደነበሩ ያነሳሉ። አንደኛው የዲፕሎማሲ ፈተና ነበር።
ይህም በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን በአንድ ወገን ጣልያን ሰው ማባበልና ማስከዳትን አንድ አማራጭ አድርጋ መውሰዷ ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ የውጫሌ ውል አስቀድሞም ሲፈረም ከአንቀጾቹ መካከል አንዱ እንዲሻሻል የሚፈልግ አገር አምስት ዓመታትን የግድ መጠበቅ እንዳለበት በውሉ ላይ መቀመጡ ነበር። ምን ቢበረታ ግን ይህን ችግር ተጋፍጠውታል። ሌላው የዓድዋ ፈታኝ ችግር የነበረው የስንቅ ነገር ነው። የዓድዋ ጦርነት ከሆነበት ወቅት በቀደመው ጊዜ ቢሆን ኖሮ ሠራዊትን ለማብላት ሁለት አማራጭ መንገድ ነበር። ይህም ሠራዊቱ አቋርጦ እንደሚሄደው አገር ይወሰናል።
ለምሳሌ አገሩ የሚገብር ከሆነ አገሬው እንደየቤተሰቡ አቅም በየቤቱ የተወሰነ ሠራዊት ተመርቶ እንዲመገብ ይደረጋል። ቢቻልም ሠራዊቱ ከያረፈበት ቤት ለጉዞ ሲነሳ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን የሚሆን ስንቅ ይቋጠርለታል። ይህ ካልሆነ ሌላው አማራጭ ወራሪ መልቀቅ ነው። አገሬው ለሠራዊቱ እንቢኝ አልገብርም፤ አላበላም ካለ ምን አማራጭ አለ ነው ነገሩ። ታዲያ በዓድዋ ወቅት ግን ሁለቱንም ማድረግ አልተቻለም። ለምን ቢባል ከዓድዋ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን ድርቅ ማስተናገዷ ነው።
«በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉ፤ ከብቱን በሽታ ጨርሶታል፤ እህሉንም የአንበጣ መንጋ መትቶታል። ይህ ችግር በመጋፈጥ በኩል እቴጌ ጣይቱ የተወጡት ሚና ላቅ ያለ ነበር፤ እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገለጻ። እቴጌይቱ 16ሺህ ሰው በስራቸው ነበር፤ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የስንቁንና የጉዞውን ነገር የሚያቀላጥፍ ነበር። የቀለብ እጥረት ሠራዊቱን እንዳይበትን የጣይቱ ብልሃት አስፈልጓል፤ ጠቅሟልም። ንጉሡም ቀደም ብለው ይህን ችግር ስለተረዱ ከአዲስ አበባ ጭምር ያለው እህል ወደ አንድ ማዕከል እንዲሰበሰብ አዝዘው ነበርና ይህንን ችግር እንደምንም ተጋፍጠው አልፈውታል። ሦስተኛው ፈተና ጥይት ነበር አሉ – ፕሮፌሰር አበባው። የኢትዮጵያ ሠራዊት በቂ ጠመንጃ የነበረው ቢሆንም ጥይት ግን የለውም።
በኢትዮጵያ በኩል ጠመንጃ ቢገዛም እንኳ የጥይቱ ብዛት ትንሽ ነው። ይህ የጥይት እጥረት ሲታወቅ ራስ መኮንን ከሐረር ሆነው ጥይት በብዛት የሚገባበትን መንገድ እንዲፈጥሩ ተሞክሮ ነበር። በወቅቱ ፈረንሳዮች አንሸጥም ብለው፤ ኢንግሊዞችም ከለከሉና ችግሩየጸና ሆነ። ነገር ግን በራስ መፍትሄ አገኘ፤ ይህም በአንድ በኩል ጦርነቱ በአጭር ጊዜ መጠናቀቁ ጠቅሟል። ከዛም ባሻገር ጦርነቱ የቅልቅል ጦርነት መሆኑ እዚህ ላይ አግዟል። ታዲያ ግን በጥይት እጥረት ምክንያት ዒላማ የሌለው ተኩስ ተኩሶ ጥይት ማባከን ያስቀጣል የተባለበት ሁኔታም ነበር ይላሉ። የኢትዮጵያ መርፌ ሰውኛ ፕሮዳክሽን ቀደም ካሉ ጥቂት ዓመታት በፊት ጀምሮ የዓድዋን ድል በድምቀት የሚያስቡ ጥበባዊ ክዋኔዎችን ‹ክብረ ዓድዋ› በሚል ስያሜ ያደርጋል።
ተዋናይና የፊልም ባለሙያው ሚካኤል ሚልዩን በፊት መሪነት የሚያጋፍረው ይህ ሥራ፤ አውደ ርዕዮች፣ በእድሜና በእውቀት ሁሉንም አሳታፊ ተግባራት፣ በጥቅሉ ሳምንታዊ ፌስቲቫል የሚደረግበት ነው። ዘንድሮ ሰውኛ ፕሮዳክሽን፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ክብረ ዓድዋን አዘጋጅተዋል። «ዓድዋ የሰውነት ማህተም» ብውታል፤ መሪ ሃሳቡን። ከየካቲት 16 ቀን 2011ዓ.ም የጀመረው ይኸው መርሃ ግብር በሦስተኛው ቀን አንድ ዘጋቢ ፊልም በወመዘክር አዳራሽ ለእይታ አቅርቧል። ይህም «የሸዋ መርፌ» የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን፤ የዓድዋ ድልን በይበልጥ እቴጌ ጣይቱን መነሻ አድርጎ የቀረበ ነው።
ዘጋቢ ፊልሙን የደበበ እሸቱ ባለቤት ወይዘሮ አልማዝ አዘጋጅተውታል። የተሠራውም ከዓመታት በፊት ሲሆን በእለቱ የመጀመሪያ እይታው ነበር። በዚህ ዘጋቢ ፊልም የነገሥታቱ ታሪክ ግሩም በሆነ ሁኔታ ቀርቧል፤ እንደ ተክለጻድቅ መኩሪያ ያሉ ታሪክ አዋቂዎችም በቃለመጠይቅ የተሳተፉበት ነው። በቀረበው ዘጋቢ ፊልም ላይ ታዳሚያን አስተያየታቸውን አቀብለዋል፤ ውይይትም ተደርጓል። እቴጌ ጣይቱ እንዲሁም አጼ ምኒልክ ለአገር እድገትና ለውጥ፤ ዘመናዊነትና መሻሻል ዓይን የከፈቱ ናቸው። በንግሥናቸው ዘመን በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ዘለዓለም የሚወራ ታሪክ መሥራት የቻሉት እነርሱ ናቸው። በዘጋቢው ፊልም ውስጥም የእቴጌ ጣይቱ ሚና በዓድዋ ድልም ይሁን ቀጥሎ በመጣው የአገር ግንባታና ዘመናዊነት በጉልህ ታይቷል። ከአጼ ምኒልክ ኅልፈት በኋላም እቴጌይቱ ያሳለፉት ጊዜና የነበሩበት ሁናቴ ዛሬ የሆነ ያህል በዘጋቢ ፊልሙ በኩል በየተመለከተው ሰው ልቦና ጠልቋል። አገር የማይበቃው ሃውልት አሁን ያለንበትን ጊዜና ያለፈውን በዝርውና እንደመጣልን «አይ ጊዜ!» በሚል ቋንቋ ሳይሆን በጥልቀት እንመልከት። አሁን ላይ የገዛ አገራቸውን የዘረፉ ሌቦችን ሁሉ ለመቅጣት ፈታኝ መሆኑንና እስር ቤት ለማስገባት እንኳ አንድ ከተማ መገንባት ሊያስፈልግ እንደሚችል የሚነገርበት ጊዜ ነው። ይህም መነሻው እውነት ነው። ነገር ግን የዛሬን አያድርገውና ኢትዮጵያ በጀግኖቿ ብዛት ለሁሉም ሀውልት ቢቆምላቸው ስፍራው አይበቃም የሚባልላት ነች። ይህን ሃሳብ ያገኘሁት የቅርስ ጥናት ባለሙያ ከሆኑት ኃይለመኮት አግዘው ነው። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በየወሩ የሚያዘጋጀው ብሌን የኪነጥበብ ምሽት የየካቲት ወር መርሃ ግብር ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን ተካሂዷል።
እናም በዛ መድረክ ላይ አጭር ገለጻ ያቀረቡት አቶ ኃይለመለኮት፤ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር አንድ ሆነው ለአንድ ዓላማ ያቀኑበት መሆኑን ያስታውሳሉ። በዚህም ንግግራቸው በጊዜው የነበሩ መኳንንትና ሹማምንት እንዲሁም ገዢዎች፤ አጼ ምኒልክን የሚቃወሙና ቢችሉ ወርረው ድል ሊያደርጓቸው የሚፈልጉ ሁሉ ለአገራቸው ግን ታምነው ነበር። እዚህ ላይ ብዙ ጊዜ እንደማሳያ የሚነሱት የከፋ ንጉሥ የነበሩት ታቶ ጋኪ ሼሬቾ ናቸው። እኚህ ሰው ከምኒልክ ጋር ውጊያ ሊገጥሙ ነው መባሉን ኢንግሊዞች ይሰማሉ። ያገኙትን አጋጣሚ ለመጠቀምም ወደ ከፋው ንጉሥ መልዕክተኞችን ይልካሉ። መልዕክቱም «ከምኒልክ ጋረ ጦርነት ልትገጥም ዝግጅት ላይ እንዳለህ ሰምተናል፤ የሚያስፈልግህን የጦር መሣሪያና ሌሎችም ነገሮች በመላከ ድጋፍ እናደርግልሃለን…» ይላል። ታቶ ጋኪ ሼሬቾ ታዲያ እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጡ፤ «አሁን የሚደረገው ጦርነት የወንድማማቾችነውና የእናንተ እርዳታ አያሻኝም…» አሉ። እኚህ ሰው ለአገራቸው እንደታመኑ ቆይተዋል። አጼ ምኒልክ ወደ ዓድዋ በዘመቱ ጊዜ አገር እንዲጠብቁ ያሏቸው ነገሥታትም ንጉሡ የሉም ብለው ያሻቸውን አላደረጉም፤ ይልቁንም ታምነው አገራቸውን ጠብቀዋል።
ዓድዋን ባወሳው በዚህ ብሌን ኪነጥበባዊ ምሽት ላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተፈሪ ዓለሙና ዓለማየሁ ታደሰ ግጥሞችን አቅርበዋል፤ የሙዚቃ ተመራማሪው ሰርጸ ፍሬስብሐት በጊዜው ስለነበረው ሙዚቃና የሙዚቃ ኃይል አንስቷል፤ ወጎች ቀርበዋል፤ ሙዚቃም ነበር። የዋዜማ ቴአትር ተፈሪ ዓለሙ፣ ሶሎሞን ዓለሙ ፈለቀ፣ ተስፋዬ ገብረሃና፣ ሚካኤል ሚልዮን፣ ዓለማየሁ ፈንታዬ መዓዛ ታከለ እና ሌሎችም በርካታ አንጋፋ እንዲሁም አዳዲስ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፣ በዋዜማ ሙዚቃዊ ቴአትር። ቴአትሩ አንጋፎች የተሳተፉበት በመሆኑ ብቻ ሳይሆነ በቀረበበት ትርዒትና ባስተላለፈው መልዕክት ልዩ ነበር። ከደራሼ የመጣ የባህል ሙዚቃ ቡድን ደግሞ ትርዒቱን ይበልጥ ማራኪና አስደሳች አድርጎታል። የቴአትሩ ታሪክ ይቅርታ ማድረግን ያሳያል። ይልቁንም ከዓድዋ ድል ማግስት አጼ ምኒልክ ለተማረኩ የጣልያን ወታደሮች ያሳዩትን ይቅርታና ርህራሄ ቁልጭ አድርጎ የሚያወሳ ነው።
ወንድሟ በውጊያው መካከል የተገደለባት ሴት፤ የወንድሟን ገዳይ ጣልያናዊ ወታደር ለመበቀል በምታሳየው ፍላጎት ወደ ጡዘት የሚደርሰው ታሪኩ፤ በብዙ ምክርና ተግሳጽ፤ ጸሎትና ልመና ይቅርታ ስታደርግለት ያሳያል። በዛ ያበቃል፤ ያ ጣለያናዊ ወታደር መልሶ በጥፋት ውስጥ ይገኛል፤ በዚያች ይቅርታ ባደረገችለት ሴት ላይ በደል ፈጸመ ተብሎ ይነገራል። «ይገደል!» ሲሉም ብዙዎች ይፈርዱበታል። ይሁንና ንጉሡ ግን የዛ ሰው እናትም ሀዘን ይገባታል፤ ህመሟ ይሰማኛል ብለው በይቅርታ ወደ አገሩ እንዲላክ ያደርጋሉ። ሙዚቃዊ ቴአትሩ ይህንን ነው በሙዚቃ፣ በፉከራና ሽለላ፣ በበገናና በጆሮ ገብ ሳቢ ድምጾች አጅቦ ለታዳሚው ያቀረበው። የኪነጥበብ ኃይል ምንም የማያሻማ ሆኖ፤ እንዲህ ታሪካዊ ሁነቶች ጋር ሲደመር ደግሞ የአገር ታሪክ በተመልካችና አድማጭ ልቦና ቀርተው ሁሉም ስለአገሩ ግድ እንዲለው ያደርጋል። በትናንትና የነበረውን ይቅርታና ፍቅር፤ ጥንካሬና እምነት ብቻ ሳይሆን ዛሬም የሚያስፈልገውን የሰውነት ትልቅነት ቴአትሩ ያመለክታል። «ብጌ» ብጌ ይሉታል፤ ብጋራ እንደማለት ነው።
የአባቶችን ድል፣ ድካማቸውንና ጉዟቸውን፣ ደስታቸውንና ስሜታቸውን ሁሉ ስለመጋራት ነው። የዚህኛውም መርሃ ግብር አዘጋጅ በዋናነት በሰውኛ ፕሮዳክሽን ነው። ይህም የ«ክብር ዓድዋ» ዝግጅት አንድ አካል ሲሆን ዘንድሮ የሚዘጋጀው ለሦስተኛ ጊዜ ነው። ይህ መርሃ ግብር ምንድን ነው? ከአራዳ ጊዮርጊስ ከምኒልክ አደባባይ የሚጀምር ጉዞ። የዓድዋ ድል እንደሚታወቀው ውጊያ ከተከናወነበት ዓድዋ ባሻገር መሃል አዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ በድምቀት ታስቦ ይውላል። ታዲያ «ብጋራ» ብሎ ለጉዞ የወጣ ሁሉ ጉዞውን የሚጀምረው ከአብዛኛው ሕዝብ ጋር በጋራ በስፍራው ያለው ክዋኔ ላይ ከተሳተፈ በኋላ ነው። ከዛ እንደተነሱ ሽለላና ፉከራ፣ ቀረርቶ እየተሰማ፤ የተለያዩ ትርዒቶች እየቀረቡ እስከ ዓድዋ ድልድይ ድረስ ጉዞ ተደርጓል።
እንደውም «እምዬ ምኒልክ የማያውቁትን ነገር ይዛችሁ አትምጡ» ይባላል። ተሳታፊው ከአለባበስ ጀምሮ አጊያጊያጥ፣ የሚይዘው እቃና ሁለንተናው የጥንቱን ለመምሰል የቀረበ ነው። በቀደመው የባህላዊ አለባበስ ሥርዓት ደምቆና ተውቦ፤ እንደ ቀደሙት አርበኞች ባለ ሥርዓት ይራመዳል። ያምራል! ይደምቃል! ሳያስቡት ወደኋላ መልሶ ይወስድና፤ «እንዲህ ነበር እንዴ?» እንድትሉ ያስገድዳል። ዓድዋ ድልድይ ላይ ጉዞው ሲጠናቀቅ ባለአራት እግር ጎማ መኪናዎች በቻሉት አቅም ተሳታፊውን ይዘው ወደ እንጦጦ ይገሰግሳሉ፤ ወደ ምኒልክ ቤተመንግሥት። ግብር የሚቀርበው እዛ ነው። ስንቅ የያዘ ስንቁን ያቀብላል፤ በጋራ መቋደስ። ትናንትናም ይህ ሆኗል፤ እጅግ ማራኪና አይረሴ በሆነ ሁኔታም ተደርጓል። ካየነው ያላየነው ይልቃል ከላይ የተነሱት ገጹ ፈቅዶ የሚይዘውና በቅርበት የታዘብነው ነው። እንጂ ካየነው ያላየነውና ያላነሳነው እንደሚልቅ ግልጽ ነው። የዓድዋን አባቶች ለማሰብና ለማስታወስ ዘንድሮ የተጀመረው «ጎፈሬ ነኝ» እንቅስቃሴ አንዱ ነው። ይህም የቻለ ሁሉ ጸጉሩን አጎፍሮ የታየበትና የተወዳደረበት ነው። ከዛ ስንሻገር በትናንትናው እለት የአገራቸውን ባንዲራ ለብሰውና ደምቀው፤ «ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም…እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውድም» እያሉ ከተማዋን ያደመቁ ስፍር ቁጥር የላቸውም። 123ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በሚመጡት ቀናትም በተለያዩ መርሃ ግብራት እንደሚታሰብ ይጠበቃል። ከምንም በላይ ግን መታሰቢያው «ጠፋ» የሚባለውን የአገር ፍቅር ስሜት «የት ነህ?» ብሎ የሚጠራ ዓይነት ነው። እናብቃ! «ለሁሉም ጊዜ አለው!» እንዲል፤ ጥበብ አገልግሎቷ የታየበት፤ አባቶችም እምነትና እውነታቸው በትውልድ ልብ እንደገባ የታየበት ነው። ይበል ይሁን! የዓመት ሰው ይበለን ከማለት ውጪ ምን እንላለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011
በሊድያ ተስፋዬ