በመዲናዋ 15 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃቸውን ተነጠቁ

-11 ሆቴሎች ባለ አምስት ኮከብ ደረጃን አገኙ

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ዳግም በተደረገ የሆቴሎች ምዘና 15 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃቸው መነጠቁን ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ 11 ሆቴሎች ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ማግኘታቸውም ተጠቁሟል፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቱሪስት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታሪኩ ደምሴ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች ደረጃ ትናንት ይፋ ሲደረግ እንደተናገሩት፤ በ2017 ዓ.ም በሆቴሎች ላይ በተደረገው ዳግም ምዘና አገልግሎት ያቆሙ፤ በሌላ አገልግሎት ዘርፍ የተሠማሩ እና በምዘና ወቅት ተባባሪ ያልሆኑ 15 ሆቴሎች በተቀመጠው መመሪያ መሠረት የኮከብ ደረጃቸው ሊነጠቅ ችሏል፡፡

በምዘና ወቅት ዲሚትሪ፣ ሲዮናት፣ ክራውን፣ አምባሳደር፣ ፓራማውንት፣ በሻሌ፣ ሐራምቤ፣ አስትራ ሆቴሎች አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ገልጸው፤ እንዲሁም 22 የሚገኘው እስቴይ ኢዚ ሆቴል፣ ሞዛይክ ፣ናርዳን፣ ሊ ማስተር ሆቴሎች የአገልግሎት ዘርፍ የቀየሩ በመሆናቸው የኮከብ ደረጃቸው መነጠቁን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ዋቢ ሸበሌ እና ደሳለኝ ሆቴል ለምዘና ተባባሪ ባለመሆናቸው እንዲሁም ሲያቲን ሆቴል የስያሜ እና የባለቤትነት ለውጥ ያደረገ በመሆኑ የኮከብ ደረጃቸው ሊነጠቅ ችሏል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በደረጃ ምዘናው ከውጭ ገጽታ ጀምሮ 12 መስፈርቶች በማስቀመጥ 92 ሆቴሎች ላይ ምዘና የተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ይፋ የተደረገው የ40 ሆቴሎች ደረጃ ነው ብለዋል ፡፡

ደረጃቸው ይፋ ከሆነ 40 ሆቴሎች 34 ሆቴሎች ዳግም ምዘና የተደረገላቸው እንደሆኑ ገልጸው፤ ስድስት አዳዲስ ሆቴሎች ወደ ኮከብ ደረጃ የገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በምዘናው መሠረት እስከ 30 በመቶ የተቀመጠውን መስፈርት ያሟሉ ሆቴሎች በኮከብ ደረጃ ውስጥ መካተታቸውን በመግለጽ፤ ከ90 በመቶ በላይ መስፈርቱን ያሟሉ ሆቴሎች ባለ አምስት ኮከብ ያገኙ ናቸው ብለዋል፡፡ የኮከብ ደረጃ ያገኙ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃቸው በሕጉ መሠረት ለሦስት ዓመት እንደሚያገለግል አስታውቀው፤ነገር ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ  በሚያደርገው ደንገተኛ እና መደበኛ ክትትል ሆቴሎቹ ከደረጃ በታች አገልግሎት መስጠታቸው ከተረጋገጠ በማንኛውም ጊዜ የኮከብ ደረጃቸው የሚነጠቅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ዳግም ምዘና ለተደረገላቸው ሆቴሎች ከምዘና በፊት ከአዲስ አበባ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን የድጋፍ እና የቁጥጥር ሥራ እንደተደረገላቸው የተናገሩት አቶ ታሪኩ፤ በተደረገው ድጋፍ መሠረት ሆቴሎቹ ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲያሟሉ በቂ ጊዜ የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዳግም ክትትል ሥራው በተቀመጠው አሠራር መሠረት እንዲከናወን ከክልል የተውጣጡ ባለሙያዎችን በማደራጀት መከናወኑን በመግለጽ፤ የምዘና ሥራውን ፍትሐዊ ለማድረግ ስድስት የሙያና የሆቴል ዘርፍ ማህበራት በታዛቢነት እንዲሳተፉ መድረጉን ጠቁመዋል፡፡ በምዘናው ላይ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሆቴሎች በሚኒስቴሩ የተዋቀረ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አሠራር የተዘረጋ በመሆኑ ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡

በኦሮሚያ፣ ሲዳማ እና በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ሆቴሎች ምዘና የተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀጣይ ባሉት ጊዜያት ይፋ እንደሚደረግም አመልክተዋል፡፡ ከሆቴሎች በተጨማሪ የሎጆች እና ሬስቶራንቶች ምዘና ስለተጠናቀቀ በቀጣይ ደረጃቸው ይፋ ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You