
የጎልማሶች ትምህርት በኢትዮጵያ የትምህርት ሂደት ውስጥ ረጅም ታሪክ አለው ። ትምህርቱ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ በተለያዩ የአቅርቦት ስልቶች ሲሰጥ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። በትምህርት ዘርፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ስልት ነበር ፡፡
በኢትዮጵያ በዚህ ስልት ተምረው አውሮፕላን አብራሪ፣ የሕክምና ዶክተር፣ መምህር፣ ኢንጂነር፣ በመንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ የደረሱ… ዜጎች ስለመኖራቸው መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡
በ2015 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት መርሐ ግብር የበጎ ፈቃደኛ አመቻቾች የአገልግሎት አሰጣጥ ማንዋል እንደሚያመለክተው፤ ትምህርቱ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት እየተሰጠው፤ አንዳንዴም እየደበዘዘ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች እዚህ የደረሱ ዜጎችን ጭምር በማፍራት ሲተገበር ቆይቷል። ሆኖም እየደበዘዘ መተግበሩ እና ዘላቂና ወጥ አለመሆኑ የተፈለገውን ያህል የጎልማሳውን ፍላጎት ማርካት አለመቻሉንም ይጠቅሳል።
በትምህርት ሚኒስቴር የጎልማሶች እና መደበኛ ያልሆኑ ትምህርት ፕሮግራሞች መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዮሴፍ አበራ እንደተናገሩት ፤ ተደራሽነቱን ለማስፋት ከለውጡ ወዲህ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት አተገባበር ተከልሷል። የአንድ ዓመት የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት እንዲሆንም ተደርጓል። ትምህርቱ የማንበብ፤ የመፃፍ እና የማስላት ክህሎቶችን ከሌሎች ሙያዊ እና የገቢ ማመንጫ ሥራዎች ጋር የተቀናጀ ነው። አሁን እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ያለችበትን 52 በመቶ የተማረ ሰው ምጣኔ ከፍ ከማድረግ በዘለለ በእያንዳንዱ ጎልማሳ አኗኗር፤ ብሎም በሀገር እድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት በሚያመጣ መልኩ የተቃኘ ነው። ይሄም የብዙ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ ከተወሰደ በኋላ ነው ወደ ትግበራ የተገባው።
በደቡብ ምስራቅ እሲያ የምትገኘው ባንግላዴሽ፤ ኩባ፤ ቻይና፤ ግብጽ ፤ቱርክ ተሞክሮ ከተወሰደባቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ። በተለይ ኩባ የመሠረተ ትምህርት በሀገር ደረጃ ያወጀችው እ.እ.አ ከ1961 ጀምሮ ነው። ከዚህ ጀምሮም በመንግሥት ድጋፍ ስታከናውን ቆይታለች። የትምህርቱ ዓላማም የዜጎችን፤ የማንበብ፤ የመፃፍ የማስላት ክህሎት ማሳደግ ነው። በዘመቻው ብዙ መምህራን በበጎ ፈቃደኝነት፤ አመቻችነት፤ ተንቀሳቅሰዋል። በተለይም የሴት ወጣት በጎ ፈቃደኛ አመቻቾች በገጠሩ ክፍል በመግባት፤ አብሮም ከኅብረተሰቡ ጋር በመኖር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ኩባ መርሐ ግብሩን በጀመረችበት ዓመት በበጎ ፈቃደኞች 707ሺህ ዜጎቿን ማንበብ፤ መፃፍና ማስላት አስችላለች ሲሉ ተሞክሮውን ዋቢ አድርገው አቶ ዮሴፍ ያነሳሉ፡፡
የውጭ ተሞክሮን አስመልክተው በ1960ዎቹ እስከ 1970ዎቹ የሰላም ጓዶች (Peace corps) ለሀገራችን ያበረከቱት አስተዋጽኦ የሚዘነጋ እንዳልሆነም ይናገራሉ። የሰላም ጓዶች በሀገራችን በጎ ፈቃደኛ አስተማሪ በመሆን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጡ ስለመቆየታቸውም ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ዮሴፍ የአንድ ዓመቱን የጎልማሶች ትምህርት በበጎ ፈቃድ ስልት ተደራሽ በሆነ መልኩ ለመተግበር ከኢትዮጵያም ተሞክሮ ተወስዷል። በ1967 ዓ.ም በአዋጅ የተደነገገው የዕድገት በሕብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ዋናው ነው። በተጨማሪም ከ1971 እስከ 1981 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ሌላው እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
አቶ ዮሴፍ እንደሚናገሩት፤ በእነዚህ ወቅቶች ከፍተኛ ዘመቻ ተካሂዷል። በዘመቻው የዩኒቨርሲቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ መምህራን፤ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት፤ የተማሩ እና በጡረታ የተገለሉ ግለሰቦች፤ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባላት ፣ በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል። እንዲሁም የተማሩ የፋብሪካ እና የግብርና ሠራተኞች ተካፍለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችና ጎልማሶችም በዚሁ ዘመቻ ተምረው የማንበብ፤ የመፃፍ፤ የማስላት ክህሎት ማዳበር ችለዋል። በዚህ ውጤትም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ ተሸላሚ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡
እንደ ትምህርት ሚኒስቴር አዲሱ አመራር ከመጣ በኋላ በ2015 ዓ.ም ይሄን የሀገር ውስጥና የውጭ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስልት መሠረት ያደረገ ተሞክሮ በመውሰድ እየተተገበረ ይገኛል ይላሉ፡፡
“የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩ የራሱ ዓላማ አለው” የሚሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ፤ በጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት ወጥ የሆነ የበጎ ፈቃደኛ አመቻቾች የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋትን ስለመሰነቁም ያነሳሉ። የወጣቶች እና የጎልማሶች የማንበብ፤ የመፃፍ እና የማስላት ምጣኔን ማሳደግን ማዕከል ስለማድረጉም ያወሳሉ።
በጎ ፈቃደኝነትን አስመልክተውም የሚሰጠውን ትርጉም ሲያስረዱ “አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን በሚፈለገው የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ለማኅበረሰቡ እድገት፤ ልማት እና ደህንነት ዕውቀቱን፤ ጉልበቱን እና ጊዜውን በነፃ ለመስጠት የሚያሳየው ፍላጎት እና ተነሳሽነት ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
“በጎ ፈቃደኝነት ለማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ እድገት መፋጠን መሠረታዊ ሚና ይጫወታል” ይላሉ። እንዲሁም በተሰማሩበት የአገልግሎት ዘርፍ ወጪን መቀነስ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ መቀራረብን ፤ ቀናነትና አንድነትን በመፍጠር የሚጫወተው ሚና ቀዳሚ ነው። ሀገራዊ ፍቅርን በማሳደግና ሌሎችንም ዋና ዋና ለውጦችን በማምጣት ትልቅ አበርክቶ አላቸው።
አቶ ዮሴፍ በጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት በጎ ፈቃደኛ አመቻቾችን ማሳተፍ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያስረዳሉ። የትምህርት ዕድል ያላገኙ ወጣቶችን እና ጎልማሶች በጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት መርሐ ግብር በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ማስቻሉ አንዱ ነው። ወጣቶች እና ጎልማሶችን የማንበብ፤ መፃፍና ማስላት፤ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ማድረግም ሌላው ነው። ለኅብረተሰቡ መቆርቆር እና የሀገር ፍቅር ስሜትን እንደሚያጎለብትም ያነሳሉ። በዜጎች መካከል የመተሳሰብ እና የአንድነት ስሜት እንዲጎለብት እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለመደ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ የሚያበረከት መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሀገር የሚወጣውን ወጪ በብርቱ የሚቀንስ ስለመሆኑም ይናገራሉ።
አቶ ዮሴፍ እንዳሉት፣ ከለውጡ በኋላ የአንድ ዓመት የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት መርሐ ግብር በአዲስ እየተተገበረ ይገኛል። የውጭና የሀገር ውስጥ በተለይም የኩባ ተሞክሮችን በመቀመር እንደ ሀገር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲተገበርም በውጭ የተገኙ ተሞክሮዎችን በሀገር ውስጥ ለማስገኘት ስለመቻሉም አንስተዋል። በአንድ ዓመት የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት መርሐ ግብር በ2016 ዓ.ም ሦስት ወር ያልሞላ የክረምት ጊዜያት 140 የአሰልጣኝና የሰልጣኝ ሞጅሎች በማዘጋጀት ከ500 ሺ ጎልማሶች በላይ ማንበብ፤ መፃፍ፤ ማስላት እንዲችሉ ተደርጓል። በዚህም 16 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ሌሎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ይሄ የአንድ ዓመት መርሐ ግብር በአዲስ በተጀመረበት በ2015 ዓ.ም መርሐ ግብሩን በውጤታማነት እና በተሳለጠ ሁኔታ በዘላቂነት ተደራሽ በሆነ መልኩ ለመተግበር የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት ፕሮግራም መርሐ ግብር የበጎ ፈቃደኛ አመቻቾች የአገልግሎት አሰጣጥ ማንዋል በትምህርት ሚኒስቴር መዘጋጀቱን ይናገራሉ ፡፡
የጎልማሶች እና መደበኛ ያልሆኑ ትምህርት ፕሮግራሞች በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ስር እንደመሆኑ ማንዋሉ በቅርቡ የወጣውን የአጠቃላይ ትምህርት ሕግ ተከትሎ መዘጋጀቱንም አስታውሰዋል። በማንዋሉ የበጎ ፈቃዱ አመቻቾች ተለይተው ተቀምጠዋል። የትምህርት ሚኒስቴር አንዱ ሲሆን የክልል ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በአመቻችነት ከተለዩት መካከል ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም የዞን ክልል ከተማ ትምህርት መምሪያ ፤ የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት፤ የቀበሌ ትምህርትና ሥልጠና ቦርድ የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ጣቢያ እና የበጎ ፈቃደኞችም በአመቻችነት ተካትተዋል። አመቻቾቹም የየራሳቸው ተግባርና ኃላፊነት እንዳላቸውም አቶ ዮሴፍ ጠቅሰዋል፡፡
የበጎ ፈቃደኞቹ አመቻቾች ምልመላ እና ተሳትፎ የራስ ተነሳሽነትን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑም ይገልፃሉ። በነፃ አገልግሎት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ የሚደረገው ልየታም ይሄን ታሳቢ አድርጎ የሚከናወን ነው ይላሉ። ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት መርሐ ግብር የበጎ ፈቃደኛ አመቻቾችን በቴሌቪዥን፤ ሬዲዮ፤ ጋዜጦች፤ ድረ ገጽ እና የማስታወቂያ ሰሌዳዎች በመጠቀም መልምሎ ለማሳተፍ መሠራቱን ነው የተናገሩት። በዚህም መሠረት በ2016 ዓ.ም በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፤ ከደባል ሱስ የፀዱ፤ ለማህበረሰባቸው አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ፤ ለሥራው ፍላጎት እና ተነሳሽነት ያላቸው 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ እና ከዚህ በላይ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ከ16ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን መመልመል ተችሏል፡፡
እነዚህም ከማህበረሰብ ሙያ እና የሥራ ተዋጽኦ አንጻር ሲቃኙ በአካባቢው የሚገኙ የትምህርት ቤት መምህራን፤ የተማሩ እና በጡረታ የተገለሉ ግለሰቦች፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች በተጨማሪም የአካባቢው ተወላጆች፤ ታዋቂ ግለሰቦች የሚገኙበት ስለመሆኑ ነው ያስረዱት። 12ኛ ክፍል ጨርሰው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚጠባበቁ ተማሪዎች ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር ብለዋል። ባለፈው የትምህርት ዘመን ክረምት ላይ ብቻ በሁሉም የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ከ500ሺህ በላይ ጎልማሶችን ማስተማር መቻሉንም ሳያስታውሱ አላለፉም።
ዘንድሮም ማንዋሉ ላይ በመመሥረት ምልመላው በተመሳሳይ መልኩ እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። 20 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን ለመመልመል ታቅዷል። በእነዚህ በጎ ፈቃደኞችም ሦስት ወር በማይሞላ የክረምት የእረፍት ወራት ብቻ ከ700 ሺህ በላይ ጎልማሶችን ማንበብ፤ መጻፍ እና ማስላት ለማስቻል ታስቧል። ማንዋሉ ታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ በሀገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም ክልሎች መርሐ ግብሩ በአዲስ መተግበር ከመጀመሩ ቀደም ብሎ መሠራጨቱንና አሁንም እየተሠራ ያለውም በዚሁ መሠረት መሆኑን ያብራራሉ።
ማንዋሉ መርሐ ግብሩን ለመተግበር የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ከዚህ ከፍ ያለ ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑን መሪ ሥራ አስፈፃሚው ይናገራሉ። አሁንም መርሐ ግብሩን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ሌሎች ደንቦችን የማዘጋጀት ዕቅድ አለ፡፡
እንደሳቸው ገለፃ በቀጣይ የሚዘጋጁት ደንቦችም ቢሆኑ ልክ እንደማንዋሉ ኢትዮጵያ በተማረ የሰው ኃይል ምጣኔ አሁን ላይ ያለችበትን 52 በመቶ የጎልማሶች ትምህርት ተደራሽነትን የበለጠ በማስፋት ማሳደግ ላይ ያጠነጠኑ ናቸው። በተለይ ለበጎ ፈቃደኛ አመቻቾች ተግባር እና ኃላፊነት የበለጠ ትኩረት ይሰጣሉ። ምክንያቱም አመቻቾቹ ተግባርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግ መርሐ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል። ከዚሁ ጋር አያይዘውም በጎ ፈቃደኞቹ አገልግሎት የሚሰጡበትን ጊዜ በስምምነት ውል ማረጋገጥ በዚሁም መሠረት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
በተጨማሪም ከሚመለከታቸው የቀበሌ አመራር እና የጎልማሶች ትምህርት አስተባባሪዎች ጋር በመሆን ተሳታፊ ጎልማሶች ወደ መማሪያ ጣቢያ ለማምጣት መቀስቀስ ፤ መመዝገብ መርሐ ግብርም ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። የመርሐ ግብሩ ተሳታፊ ወጣቶች እና ጎልማሶችን አሳታፊ ሊያደርግ የሚችል በድርጊት መርሐ ግብር የታቀደ የትምህርት ዕቅድ ያመቻቻሉ። ከዚህ በተጨማሪም የመማማሪያ ጣቢያው አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዲሟሉለት በኅብረተሰብ ተሳትፎ እና ባለቤትነት እንዲጎለብቱ ግንዛቤ ያስጨብጣሉ።
መሠረታዊ የማንበብ፤ የመፃፍ እና የማስላት ክህሎቶችን ከሌሎች ሙያዊ እና የገቢ ማመንጫ ሥራዎች ጋር በማቀናጀት የማመቻቸትም ተግባር ያከናውናሉ። ተሳታፊ ጎልማሶችን በተከታታይ የምዘና ዘዴ ይመዝናሉ። የትምህርት አቀባበል ችግር ላለባቸው ተሳታፊዎች ክትትል እና ድጋፍ ያደርጋሉ። ኃላፊው እንደሚሉት አንድነትን፤ ማህበራዊ መስተጋብርን፤ የሌሎች አካባቢዎች ባሕል፤ አኗኗር ዘይቤና መልካ ምድር መቃኘት እንዲችሉና ሀገራቸውን በሚገባ እንዲያውቁ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ተግባሩን ማከናወንም ከበጎ ፈቃደኞቹ ይጠበቃል። እየተዘጋጀ ባለው ደንብም ተቀምጧል። ሆኖም በዘንድሮ ክረምት ይሄን ወደ መሬት አውርዶ መተግበር ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ስለሆነ አይተገበርም ብለዋል። ከጤና፤ ከግብርና፤ ከቴሌኮሙኒኬሽንና ከሌሎች ዘርፎች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራቱ ረገድ ግን እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም