
ቻይና 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ህዝብ በመያዝ በዓለማችን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ሀገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በኢኮኖሚ እድገት፣ በቴክኖሎጂ፣ በመሰረተልማት፣ በትምህርት ፣በህክምናና በበርካታ ዘርፎችም ስማቸው ቀድመው ከሚነሱ ሀገራት አንዷ ናት።
የዛሬይቷ የስልጣኔ እና የሀያልነት ምሳሌ ከ 50 እና 60 አመታት በፊት ግን ታሪኳ ሌላ ነበር። ያኔ ቅንጦት ብሎ ነገር አይታሰብም፣ እለታዊ ጉርሳቸውን በአግባቡ የማይመገቡት ዜጎችም እልፍ ነበሩ። በአጠቃላይ የድህነት ጥግ ተምሳሌት ነበረች።
ለዜጎቿ እንኳንስ የቅንጦት ህይወት ቀርቶ የእለት ጉርሳቸውን ማግኘት በከበዳቸው ሰአት ታዲያ “ድህነትን በሁሉም መልኩ በሁሉም ቦታ አስወግድ” በሚል መሪ ሀሳብ በወቅቱ የነበረው የኮሚኒስት ፓርቲ የድህነት ቅነሳ ንቅናቄን በራስ አቅም ማካሄድ ጀመረ፡፡
ከንቅናቄው ውስጥም (1953-1957)የመጀመርያው የአምስት ዓመት ብሔራዊ ኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ በማዘጋጀት ተግባራዊ ተደረገ፡፡ በዚህም በሀገሪቱ የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በዋነኝነት የሚጠቀሱ መስኮች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ሁሉንም ቻይናውያን ለመመገብ ግብርና ማልማት በሚል መሪ እቅድ በተለይም መሬትን ለገበሬዎች በመስጠት ከፍተኛ ምርት እንዲገኝ በማድረግ ዛሬ ላይ እራስን በምግብ ለመቻልና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡
በወቅቱ የያዘቻቸውን የቻይናን የፈጠራ አቅም ፣ የሀገር ውስጥ ገበያ ስርዓትን ለማሳደግ እና ለድሆች የሀብት ክፍፍል ግቦችንም ማሳካት ችላለች፡፡
ታዲያ ዛሬ ላይ ቻይና ከራስዋ አልፋ እርዳታ ለሚሹ ሀገራት እጆቿን በመዘርጋት እና በጋራ በመስራት ቀዳሚ ሀገር ናት፡፡
ከአፍሪካ ጋር ረዥም አመታት ያስቆጠረ ግንኙነት ያላት ሲሆን በቻይና እና በአፍሪካ መካከል የህዝብ ለህዝብ ፣የባህል ልውውጥን እና የሚዲያ ትብብርን ለማጠናከር በቅርቡ ከአፍሪካ ሀገራት ለተውጣጡ ጋዜጠኞች የልምድ ልውውጥ መርሃግብር ተካሂዶ ነበር።
በቻይና በቻይና የዓለም አቀፍ ጥናትና ከፍተኛ ማሰልጠኛ ተቋም (CICG) በተዘጋጀው ሴሚናር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ጋዜጠኞች የቻይናን ታሪክ እና ባህል የመቃኘት እድል ነበራቸው። እኔም የዚሁ አካል ስለነበርኩ ትዝብቴን በመጠኑ ላጋራችሁ ወደድኩ።
ሴሚናሩ በቻይና መቀመጫ በሆነችው የቤጂንግ ከተማ የተጀመረ ሲሆን አጫጭር ገለጻዎችና የውይይት መድረኮችን ያካተተ ነው፡፡ በዚህም ቻይና ከነበረችበት ድህነት ለመውጣት ስላካሄደችው እርምጃና የኮሚኒስት ፓርቲ መሪዎች ቆራጥነት በስፋት የተብራራበት ነበር፡፡
በተጨማሪም ስለ ቻይና አመራር አስተዳደር ጽንሰ-ሀሳቦች ፣የቻይና ወደ ዘመናዊነት የሄደችበት መንገድ እና ስለ ቻይና-አፍሪካ ማህበረሰብ የወደፊት የልማት ትብብር እና ድጋፍ ዙሪያ ሰፌ ገለጻ ተገርጓል።
በተጨማሪም ስልጠናው የተለያዩ የቻይና ግዛቶችን በመጎብኘት የታጀበ ሲሆን ጉዟችንንም የጀመርነው ከቻይና ታላቁ ግንብ ነው፡፡
ታላቁ የቻይና ግንብ በሰሜን ቻይና ውስጥ ከ 5500 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ጥንታዊ ግንብ ነው፡፡
ታላቁ የቻይና ግንብ ለመገንባት ሁለት ሺህ ዓመታት ፈጅቷል፣ ዛሬ ላይ የቻይና ጥንታዊ ስልጣኔ ምልክት፤ በዓለም ላይ በጣም ታዋቂ መዳረሻዎች አንዱና ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ ከዓለም ሰባት አስደናቂ ነገሮች አንዱ ተደርጎም ይወሰዳል።
በቦታው ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከህጻን እስከ አዛውንት የሆኑ ጉብኝዎች ይታያሉ። በአብዛኛው የሚገኙት ከተለያዩ የቻይና አካባቢዎች የመጡ ጎብኚዎች ሲሆኑ ከአፍሪካም በርከት ያሉ ጎብኚዎች ይስተዋላሉ።
ግንቡ እንኳን ተጉዘው ታይቶ የማያልቅ በመሆኑ የምንችለውን ያህል ርቀት በመጓዝ ተመልሰን ወደማደሪያችን አቀናን፡፡
ቀጣዩ ጉብኝት የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ኤግዚቢሽን ሲሆን አዳራሹ የፓርቲውን ምዕተ-አመት የረዥም ጊዜ ጉዞን በስፋት የሚያሳይ ድንቅ ቦታ ነው።
ኤግዚቢሽኑ በውስጡ ቁልፍ ታሪካዊ ክንውኖችንና ስኬቶችን በቅርሶች፣ ታሪካዊ ሰነዶች እና ዘመኑን በዋጁ የቴክኖሎጂ አቀራረቦችና ምስሎች አጉልቶ ያሣያል፡፡ ይህም ለተመልካች ግርምትን የሚያጭር ሲሆን ቻይና ታሪክ ከመስራት ባለፈ ታሪክን ለትውልድ ብሎም ለሌላው አለም ለማሳየት የሰጠችውን ትልቅ ቦታ ያሣየ ነው፡፡
ሙዚየሙ ከታሪክ መዛግብት ባለፈም ሃሳቦችን እና እምነቶችን ለማጠናከር ብሎም ለቀጣይ ትውልድ ካለፈው ጋር ተጨባጭ ግንኙነት በማቅረብ ለወደፊት እድገትና ስልጣኔ መድረክ ሆኖ ያገለግላል።
ሌላው መዳረሻ የነበረው በአለም ላይ ትልቁ እና ጥንታዊው አምልኮ ቦታ የሆነው “ቴልፕል ኦፍ ሄቨን” ሲሆን ጥንታዊ ንጉሠ ነገሥቱ በየክረምቱ የአምልኮ እና ጥሩ ምርት ለማግኘት በጸሎት ለመጸለይ ይመጡ የነበረበት ቦታ ነው፡፡
በነገስታቱ ዘመን ተራ ሰዎች እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ለጎብኚዎች ክፍት ሲሆን ቀኑን ሙሉ ሊዝናኑበት ይችላሉ።
ቦታው ላይ የጠዋት እንቅስቃሴ የሚሰሩ አዛውንቶችን ጨምሮ ፣ ካራቴና የጥንቱን ማርሻል አርት በመጠቀም በሰይፍ መዋጋት የሚማሩ ወጣቶች እንዲሁም ባህላዊ ውዝዋዜን የሚለማመዱ ቻይናውያን ይታያሉ፡፡
ለሀገሪቱ የግብርና ምርቶች በስፋት ለማምረት የሚያስችሉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚሰሩበት የቻይና የግብርና ሳይንስ አካዳሚ ሌላው መዳረሻ ነበር፡፡
በዚህም በተለይም ‹ፒዮኒ › ተብሎ የሚጠራው ሀገር በቀል አበባ ለአለም ገበያ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በጥናትና ምርምር በመታገዝ አበባው ላይ ዕሴት በመጨመር ለምግብና መጠጥነት እንዲሁም የውበት መጠበቂያ ድረስ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ይነገራል።
በተጨማሪም በአካባቢው ጥበቃ ስራ አፈሯንና ወንዞቿን በሚገባ በመንከባከብ ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ብሎም ምርታማነት እንዲጨምር ተደርጓል፡፡
በጥንት ዘመን ለጽሑፍ አገልግሎት ሲውሉ የነበሩ የቀርከሃ ቁሳቁሶችን የያዘ ሙዚየም ሌላው የጉብኝቱ መዳረሻ ነበር፡፡ ቀርከሃ በቻይና ውስጥ ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ለጽህፈት መሳሪያነት አገልግሏል።
ቀርከሃዎቹን በመጠቀምም መልእክቶችን ከመለዋወጥ ጀምሮ ግብር፣የቤተሰብ ምዝገባ እና የመሳሰሉት ህጋዊ ሰነዶችን ለመመዝገብ ይጠቀሙበት ነበር፡፡
እነዚህ የቀርከሀ የጽሑፍ ቁሳቁሶች የሰው ልጅ ስልጣኔ ውጤቶች ናቸው፡፡ ሙዚየሙም ቻይናውያን የጥንት ሥልጣኔን የሚያሣይና ለሰው ልጅ ስልጣኔ እና ማህበራዊ እድገት ያበረከተውን ትልቅ አስተዋፅኦ በጥልቅ የሚሣይ ነው፡፡
በተጨማሪም ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ የጥናትና ምርምር ተቋም፣ የአርኪዎሎጂ ስፍራዎች፣ፓርክ፣የሚዲያ ተቋማት፣የኤክስፓርት ወደብና የኢንቨስትመንት ድርጅቶች፣ የቻይናውያን ታሪክና ባህል የሚሣዩ ሙዚየሞችና ጥንታዊ መንደሮች የጉብኝቱ አካል ነበሩ፡፡
ከቤጂንግ ከተማ በተጨማሪ በሁናን ግዛት የቻንግሻ ከተማ እና የዩያንግ ጉብኝቶች ተካሂዷል።በስተደቡብ-መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል የምትገኘው ሁናን ከተማ የቻይናን ጥንታዊነት ከዘመናዊነት ጋር አጣምራ የያዘች ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት ናት፡፡ በሻይ ምርቷም ትታወቃለች።
በአጠቃላይ ጉብኝቱ በቤጂንግ፥ በሻንግሻና በዩያንግ ከተሞች የተካሄድ ሲሆን በጉብኝቱ ከማብራሪያ ጋር ተደምሮ ታላቋን ቻይና በትንሽ ጊዜያት ውስጥ ለመረዳት ያስቻለ ነበር፡፡
በሲሚናሩ ከጎበኘናቸውና በስልጠና ካገኘናቸው ታሪኮችና እውቀቶች ጎን ለጎን በመብራት ያሸበረቁ የቻይና ህንጻዎችና ጎዳናዎች ቀልብን ሳቢ ሆነው አግኝተናቸዋል። በተለይም ታዳጊ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ለመጣ ሰው ሀገሩ ወደፊት እንደዚህ እንድትመስል መመኘቱ አይቀርም፡፡
በቻይና ይበልጥ ከሚያስገርሙ ነገሮች ውስጥ በተለይም በዋና ከተማዋ ቤጂንግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ቢኖርባትም ረጋ ያለች ከተማ ናት፡፡ በመንደገዶች ላይ ከሚታዩት ተሽከርካሪዎች በይበልጥ የአብዛኛው ሰው መጓጓዣ ብስክሌትና ስኩተር ነው፡፡
የብስክሌትና ስኩተር እንቅስቃሴን ሊመጥን በሚችል መልኩም መንገድ ተሰርቷል፡፡ የከተማዋን የቆየ ስልጣኔ የሚያንጸባርቁ ረዥም አመት ያቆጠሩ ዛፎችና አረንጓዴ ቦታዎች የከተማዋን ውብና ጽዱነት አጉልተው ያሣያሉ፡፡
ይህንንም ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት በስፋት የሰራችው የአረንጓዴ ልማት፣ የመኪናና የሳይክል መንገድ መሰረተልማት የማስፋፋት ስራ ከቻይና ጋር ያመሳስላታል፡፡
ቻይናውያን ምግብ ጨዋማ ፣የሚያቃጥል፣ በቅመማ ቅመም የተለወሰ፣ ጣፋጭ እና መራራ ጣዕም ያላቸው ባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁ ምግቦች አሏቸው፡፡ የቻይና ብሔራዊ ምግብ ተብሎ የሚጠራው ዳክዬ ምግብም በየሄድንበት ከምናገኛቸው ምግቦች ውስጥ ዋናው ነው፡፡
በተለይም ኢትዮጵያዊያን የመጣንበት እምነትና ወግ ባይፈቅድም የአሳማ ሥጋ ፣የተጠበሰ ዳክዬ ፣ሽሪንፕስ፣ የእርግብ ስጋን ጨምሮ የባህር ውስጥ እንስሳት በተለያየ መልኩ ክሽን ተደርገው ይቀርባሉ፡፡
በምግቡ ውስጥ የተካተቱ ዕፅዋት እና ቅመማ ቅመሞች እያንዳንዱን ምግብና የሾርባ ዓይነቶች ይበልጥ ጣፋጭ ያደርጉታል፡፡
ሳይነሳ የማያልፈው ሀቅ ታዲያ የቻይናዊያን የስራ ፍቅርና ታታሪነት ነው፡፡ ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ ለስራ ክብር በመስጠት የበለጠ ለመለወጥ ይተጋሉ፡፡ ይህንንም በሀገራችን የምናያቸው ቻይናዊያን ምስክር ናቸው፡፡
በተለያዩ አማራጮች ከሚታየውና በወሬ ከሚሰማው ባለፈ ማየት ማመን ነው እንዲሉ በዚህ ስልጠና በተለይም አፍሪካዊያን በርካታ እውቀቶችና የልምድ ልውውጦችን ያገኙበት ነው፡፡
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ቅድሚያ ለህዝብ የተሻለ ህይወትና አገልግሎት መስጠት አላማ አድርጎ በመስራቱም ህዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ተቀናጅተው ይሰራሉ፡፡
በዚህም በራስ መንገድና በራስ አቅም ማደግ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ስትሆን ይህም አፍሪካ ከቻይና ልትወስዳቸው ከሚገቡ መልካም ተሞክሮዎች አንዱ ነው፡፡
በህዝቦች መካከል ከመከፋፈል ይልቅ ግንኙነቶችን በመገንባት ለጋራ ዓላማ መሳካት በቁርጠኝነት መስራት፣ጠንካራና ቆራጥ አመራር ብሎም በግል እና በመንግስት ሴክተሮች መካከል መተባበር ለሀገር እድገትና ብልጽግና ያለው ሚና አይተኬ ስለመሆኑ ያመላክታል፡፡
ምግብና መጠለያ፣ የመኖሪ ቤት፣ ትምህርትና የጤና አገልግሎት የመሳሰሉ አገልሎቶችን ለሁሉም በሁሉም የሀገሩ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ፣የውጭ አቅርቦቶች ላይ እሴት በመጨመር ገቢን ማሳደግ ከብዙ ጥቂቶቹ ልምዶች ናቸው፡፡
ልክ እንደ ቻይና ልማትና እድገትን ለማፋጠን ለሚፈልጉ ታዳጊ ሀገራት ያላቸውን የተፈጥሮና የሰው ሀብት በአግባቡ በመጠቀም በራስ አቅም እራስን መቻል ብሎም ለሌሎች መድረስ እንደሚቻል ልንማር ይገባል፡፡ ሀገራትም ለችግሮች ጥበብ እና መፍትሄ መስጠትን ከቻይና የተሳካ ልምድ መውሰድ ይችላሉ።
ሌላው በህዝብና በሀገራት መካከል ጥሩ ወዳጅነቶችን ማጠናከርና በችግር ጊዜ ቀድሞ ደራሽ መሆኗም በአለም ላይ መልካም ግንኙነት ሀገራት ውስጥ ተጠቃሽ ያደርጋታል፡፡
“በፍጥነት መሄድ ከፈለግህ ብቻህን ሂድ፣ ሩቅ መሄድ ከፈለግክ በጋራ ሄድ ” የሚለው አባባልም ቻይና ከራሷ እድገት ባለፈ አብሮ ማደግን የምትደግፍ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ አጋርነትን ማጎልበት እንደሚገባ ሀገራችን ብሎም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊማሩት የሚገባ ልምድ ነው፡፡
የጋዜጠኞቹ ስልጠና የተካሄደው በአለም አቀፍ ደረጃ በሚከበረው በላብአደሮች ቀን ( ሜይዴይ ) ሰሞን ሲሆን በቻይና ቀኑ ለአምስት ቀናት ይከበራል፡፡ በሳምንቱ አምስት የስራ ቀናት ዝግ በመሆናቸውም የሚባክን ጊዜና ስራን ለማካካስ እሁድ ቀን የስራ ቀን ተደርጎ ነበር፡፡
በአጠቃላይ ሲሚናሩ ለ20 ቀናት የተካሄደ ሲሆን ተሳታፊ ሰልጣኖችም ከአሰልጣኞችና አስጎብኚዎች ብሎም በተለያዩ አጋጣሚዎች ካገኟቸው ቻይናዊያን ጋር ጥሩ ወዳጅነት ያፈሩበት ነው፡፡
ቻይና እና አፍሪካ ለረዥም አመታት በሰላም እና በልማት ላይ ወዳጅት አላቸው፡፡ ለአፍሪካ ሚዲያ ባለሙያዎች የተሰጠው ስልጠናም ቻይናን የበለጠ ለመረዳት እና በቻይና እና በአፍሪካ መካከል የጋራ መግባባት ፣ መተማመን እና መደጋገፍ ድልድይ ይሆናል ።
በተጨማሪም የአፍሪካ ሀገራ ትልቅ ትምህርት በመውሰድ እርዳታ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ እራሳቸውን እንዲያበቁ ልምድ የሚቀስሙበት ነው፡፡
የቻይና የዓለም አቀፍ ጥናትና ከፍተኛ ማሰልጠኛ ተቋም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሃን ሊኪያንግ በስልጠነው መዝዝጊ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም፤ ሴሚናሩ ከአፍሪካ ለመጡ ጋዜጠኞች የጥንቷና የአሁና ቻይና ባህልና ታሪክ እንዲተዋወቁ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአካል ተገናኝቶ ልምድና ተሞክሮ ከመለዋወጠጥ ባለፈ ስለቻይና ትክክለኛ አመለካከት ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ጋዜጠኞች ወደ መጡበት ሲመለሱ በሚሠሯቸው ዘገባዎች ያዩትን፣ የሰሙትን እና ያሰቡትን ለሀገሮቻቸው ለማካፈል ግንኙነትና እና ትብብርን ለማጠናከር ስለ ቻይና የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በማህሌት ብዙነህ