
ራሄል ኤልሳ ትባላለች። የተወለደችው በአዲስ መልኩ በተዋቀረው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ውስጥ ቱሪሚ የምትባል ሥፍራ ነው። ቤተሰቦቿ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ይመደባሉ:: ዋናው የገቢ ምንጫቸው ግብርና ሲሆን፤ በተለይ የእርሻ ሥራና ሐመሮች በአብዛኛው የሚሰማሩበት የከብት እርባታ በተለየ ሁኔታ ኑሯቸውን ይደጉሙበታል።
የሐመሯ ቆንጆ ራሄል ልጅነቷን ያሳለፈችው በከባድ ፈተና ውስጥ ነው:: ሞቃታማውን የአየር ጠባይ ተጋፍጣ ከብቶቿን ውሃ ለማጠጣት፤ ለቤታቸው የሚሆን ውሃ ለመቅዳትም ርቃ መጓዝ ግዴታዋ ነበር:: ውሃ ለማግኘት በቀላሉ የማይቻልበት በርሀማው ሥፍራ አሸዋ መጫርንም ይጠይቃል:: እናም ራሄል ገና ባልጠነከረው ጉልበቷ ይህንን ታደርግ ነበር:: ከዚያም ባሻገር ለቤተሰቡ የማብሰያ እንጨት የመልቀም የሥራ ድርሻም አላት። በዚህ ልፋቷ አንድም ቀን ተማራ አታውቅም:: ይልቁንም ሥራ ያጠነከራት ልጅ አድርጓታልና ያንን ጊዜ ታመሰግነዋለች::
ቱርሚ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በጂንካ ከተማ ኔሪ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቷን የተከታተለችው ራሄል፤ ወደ ሆሳዕና በማምራት በሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከ10ኛ ክፍል የአዋላጅነት (ሚድ ዋይፈሪ) የትምህርት መስክ በዲፕሎማ መመረቅ ችላለች። በትምህርቷ በጣም ጎበዝና የደረጃ ተማሪ በመሆኗም በኮሌጁ በሰራተኛነት የመቅረትን እድል አግኝታለች። በኮሌጁ ውስጥ በማስተማር ሥራ ተሰማርታም ለአምስት ዓመታት አገልግላለች:: በኋላም ኮሌጁ ሌላ የትምህርት እድል የሰጣትና በዲላ ዩኒቨርሲቲ ገብታ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በጤና መኮንንነት ስትማር ቆይታ በኮሌጁ ተመልሳ ለሁለት ዓመት ያህል ማገልገል ችላለች::
ራሄል በትዳር ምክንያት ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን የሕክምና አገልግሎት የሥራ ሂደት አስተባባሪ በመሆን የተዛወረች ሲሆን፤ በዚያም ለስምንት ዓመት ያህል ሰርታለች። እንደ ዞን ጤና መምሪያ ማኔጅመንት አባልነቷ በጤናው ዘርፍ በርካታ ለውጦች እንዲመጡ አድርጋለች:: በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የጤና ትምህርት ክፍል እንዲጀመር አይነተኛ ሚናን ከተጫወቱት መካከል ግንባር ቀደ እንደነበረች ትናገራለች።
መልካም ሥራዎቿ ሌላኛውን የትምህርት እድል ያጎናጸፏት ራሄል፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት መስክ በቅዳሜና እሁድ መርሃግብር ተከታትላለች።
በአንድ ሥራ መርካት የማትችለው ራሄል፤ ከትምህርቷ ጎን ለጎን የእርሻ ሥራ ታከናውናለች:: እንዴት ቢሉ የምግብ ጤና ላይ መሥራት ማኅበረሰቡን ጤናማ ትውልድ ማድረግ ነው ብላ ስለምታምን ከጤና ሥራዋ በተጓዳኝ ከሥራ ሰዓት ውጪ ረጅም ጊዜዋን አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ተጠምዳ ታሳልፋለች:: ምርቷ ደግሞ ማኅበረሰቡ ዘንድ በዝቅተኛ ዋጋ እንዲደርስ ታደርጋለች።
በራሄል ትጋት የግብርናው ዘርፍ ተወዳጅ የሥራ መስክና በአካባቢው ዘንድ ያልተማሩ ብቻ ሳይሆኑ የተማሩ ሰዎች ጭምር የሚሰማሩበት ተደርጎ ተወስዷል። በዚያ ደግሞ ማኅበረሰቡ የራሱን መለያ ስም ‹‹ሪች ገበሬዋ›› በሚል ሰጥቷታል። በዚህ ስሟ ዛሬ ላይ እርሻ ሥራው በተጓዳኝ የአትክልትና ፍራፍሬ ጭማቂ መሸጫ ቤት ከፍታ በተጨማሪነት እየሠራች ትገኛለች። ከንግድ ሥራዋ ጎን ለጎንም በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬዎች ያላቸውን የጤና ጠቀሜታ ለደንበኞቿ ታስተምራለች። የሕብረተሰቡ አትክልትና ፍራፍሬ የመመገብ ባሕሉ እንዲያድግና እንዲሰፋ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲኖራቸው ጭምር ማድረግ ችላለች።
ለግብርና ሥራ በኢንቨስትመንት 86 ሄክታር መሬት ተረክባ ወደ እርሻ ሥራ የገባችው ራሄል፤ ትምህርት በቅዳሜና እሁድ መከታተል፤ የቢሮ ሥራዎች መበራከትና ከዚያ ሲወጡ ደግሞ የእርሻ ሥራውን ማስተዳደር በእጅጉ ስለከበዳትና ሙሉ መሬቱን ለማልማት የሚያስችል አቅም (ገንዘብ) ስላጠራት በወቅቱ ሙሉውን መሬት ወደ ሥራ አላስገባችም ነበር።
ባለቤቷ ከኮንስትራክሽኑ ሥራው የሚያገኘውን ገንዘብ በመጠቀም መጀመሪያ በተወሰነው መሬት ላይ ፓፓያን ማምረት ጀመረች:: ቀጥላም ወደ ሙዝ ሥራው ገባች:: ለአንዳንድ ወጪዎችና ለሠራተኞች ምግብ እንዲሆናት እንዲሁም በአካባቢው ላይ ጥሩ የገቢ ምንጭ እንዲሆኗት በማሰብ በቆሎና ማሽላን የመሳሰሉትን እህሎች ጎን ለጎን ማምረቱን ተያያዘችው:: ከዛም ቲማቲምና ሽንኩርት እንዲሁም ሀባብ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን ወደ ማምረቱም ገባች::
እነዚህን ሁሉ ምርቶች ለማምረት ዘሮችን፤ ችግኞችን ከተለያዩ ክልሎችና ከውጪ ሀገር ጭምር የምታስመጣው ራሄል፤ ለሥራዋ መፋጠን ስትል አዲስ የመግዛት አቅም ስላልነበራት አሮጌ የእርሻ ትራክተር በመግዛት ሥራዋን በጥረት ታከናውናለች:: አሁንም ገና አሮጌ ትራክተሯ አልተቀየረም:: ምክንያቱም ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል:: ይህ እንዳይሆን የአቅሟን ተጣጥራለች፤ ያላንኳኳችው የመንግሥት በር የለም:: እንደ መንግሥት በልማት ባንክ በኩል የብድር ስምምነቶች ተመቻችተዋል ብትባልም ሰባት ዓመታትን ሙሉ ሞክራ እንዳልተሳካላት ትናገራለች:: ፕሮፖዛል ጻፊ፤ 50ሺህ ብር ለሥራ ማስኬጃ ክፈይ ተብላ ብታደርገውም ለእርሷ ጠብ ያለ ነገር አለመኖሩን በምሬት ትገልጻለች:: እስከ አሁን ምንም ምላሽ ባታገኝም አሁንም ጥያቄ ከማንሳት ወደኋላ አላለችም:: በዚህ አጋጣሚም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ቢሰጠውና የሥራ ጥማቷን ማርካት ብትችል ደስ እንደሚላት ትናገራለች።
እንደ ሀገር በየቦታው ለማኅበረሰብ ለውጥ የሚሠሩ በርካታ ጠንካራ ሴቶች አሉ:: የሚደግፋቸውና ለሌሎች እንዲተርፉ የሚያደርጋቸው ግን እምብዛም ነው:: ስለዚህም መንግሥት የታችኛውን ክፍል ቢመለከተው ስትልም መልዕክቷን ታስተላልፋለች:: አሁን ላይ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች በመጠኑ እየታዩ እንደሆነም ግን አልሸሸገችም። በተለይም በስፋት ማምረት ላይ ለሚሠሩ ዜጎች ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው ትላለችም።
ወደ ሁለት ሚሊየን ብር ማንቀሳቀስ የሚያስችላትን የካፒታል እድል በራሷ የፈጠረችው ራሄል፤ በዚህ ሥራ ላይ ሌላው ፈተናዋ እንደነበር ያነሳችው የደረሱ ምርቶችን ወደ ገበያ አውጥቶ መሸጥን ነው። የመሰረተ ልማት ችግርና ከጂንካ ከተማ 54 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የእርሻ ቦታው ርቀት በቀላሉ ምርቷን ወደ ሌሎችም ሆነ የአካባቢው ገበያ ላይ እንዳታቀርብ እንቅፋት ፈጥሮባታል:: በርካታ ጊዜ የሰብል መበላሸትና መጥፋት ችግር አጋጥሟታልም:: ግን መቼም ቢሆን ለችግር እጅ መስጠትን አታውቅምና ለመፍትሄው መሯሯጥ ጀመረች::
ራሄል ምርጫዋን የእርሻ ሥራ ስታደርግ ዓላማ አድርጋ የተነሳችው አላት:: ይህም እርሻው የጤና ሥራውንም በተሻለ መልኩ የምታገለግልበት እንደሆነ ማመኗና ታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ለመድረስ የሚያስችላት ተግባር መሆኑን እርግጠኛ ስለሆነች ነው:: በዚህም ገበያዎች ምቹ ባልሆኑበት አጋጣሚ በየቤቱ እየዞረች አትክልትና ፍራፍሬዋን እንዲገዟት ማስታወቂያ ሰርታለች። ይህ ደግሞ የሞራል ጥያቄ ውስጥ ከቷት እንደነበርም አትረሳውም። በተለይም ተምሮ የተሻለ ሥራ ይዞ በዚህ ደረጃ እየወረዱ መነገዱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ነቀፌታን አምጥቶባትም ነበር። ግን ዓላማ ያለው ሰው በትንሽ ጫና አይወድቅምና ወደኋላ ማለትን ለራሷ አልፈቀደችም። ቀና ብሎ መራመድ እንደሚመጣ ታውቃለችና ነቀፌታዋን በውሸት ፈገግታ እየደለለች ትናንትን አሳልፈዋለች።
‹‹የሥራ ትንሽ የለውም ›› የሚል እምነት ያላት ባለታሪካችን፤ ለቆምንለት ሥራ ትኩረት የምንሰጥና ዝቅ ማለትን የማንፈራ ከሆነ ከፍታው ብዙ ጊዜ አይፈጅም ትላለች። ዝቅ ብሎ መሥራትን እንደ ነውር የምንቆጥርና መንግሥትን ቅጠረኝ በሚል የምናስጨንቅ ሰዎች፤ ሥራን መድፈር የምንፈራ ከሆንን ግን መቼም መለወጥ አንችልም። እናም ትናንት ዝንጥ ብለን ቢሮ ላይ የምንቀመጥ ከሆነ ዛሬን ለነገ የተሻለ እድል ስንል ቱታ መልበስን ልንወደው ይገባል በማለት ቀጣዩን የአሠራር ዘዴ ዘየደች:: ይህም ሙሉ ትኩረቷን የእርሻ ሥራው ላይ ያደረገችበትና፤ አማካኝ ቦታ ላይ ቤት ተከራይታ ገበያውን ሁሉ የተቆጣጠረችበት የሥራ አማራጭ ነው::
በትንንሽ ተሽከርካሪዎች የአካባቢውን ገበያ ለመቀላቀል የቻለችው ራሄል፤ በምትሠራቸው ተግባራት ብዙዎች ጥሩ ምላሾችን ይሰጧታል:: የተሻለ ገቢም ታገኝ ነበር:: ይህ እድል ለሌሎች የሥራ አማራጮች መንገድ የከፈተላት ሲሆን፤ በጁስና በመሳሰሉት መልኩ በቀጥታ የምትሠራበትን እድል የፈጠረላት ነው።
‹‹በጤናው ዘርፍ አሁን ሰዎችን በስፋት እያጠቃ ያለው የማይተላለፈው በሽታ ነው። ይህ ደግሞ በአመጋገብ ሥርዓት ብዙ ጊዜ ይታከማል። እኔም አሁን እያደረግሁ ያለሁት ይህንኑ ነው:: ከቅጥር ሥራ ራሴን በማውጣት ሌሎችም ሥራ እንዲያገኙ በማድረግ የተማርኩትን ትምህርት በማኀበረሰቡ ዘንድ ተፈጸሚ እንዲሆን እየታተርኩ ነው:: ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚጠቁ ሰዎች የበለጠ ተጠቃሚ እየሆኑ በመምጣታቸው ደግሞ ከሙያየ እንዳልራኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል›› የምትለው ራሄል፤ ማኅበረሰቡ እያንዳንዱን አትክልትና ፍራፍሬ ሲጠቀም ምን አይነት የጤና ጥቅሞች እንዳሉት እንዲረዳ ታደርጋለች:: ቤቷ ድረስ ሰዎች እየሄዱ ወደ ቤት ገዝተው በመውሰድ ጭምር ጤናቸውን ይጠብቃሉ::
ራሄል የመንግሥት ቅጥር ላይም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሥራ ላይ ገብታ በከፍተኛ ክፍያ ራሷን ብቻ መጥቀም የምትችልበት የትምህርት ዝግጅቷም ሆነ የሥራ ልምዷ ይመሰክራል። ሆኖም ይህንን ማድረግ ለእርሷ ራስ ወዳድነት እንደሆነ ይሰማታል። ስለሆነም ማኅበረሰቡን ታች ወርዳ ማገልገልን መርጣለች:: በዚህ ደግሞ አሁን ላይ ብዙዎችን ከጤና ችግራቸው ታድጋለች:: ገበያውን በማረጋጋት ዙሪያ የራሷን አሻራ አሳርፋለች:: በሥራ እድል በመፍጠርም ቢሆን ለብዙዎች ተስፋ ሆናለች:: ለምሳሌ፡‹- በእርሻ ቦታዋ ላይ መጀመሪያ አካባቢ ወደ ሥራ ስትገባ ከአራት የማይበልጡ ሠራተኞች ቢኖሯትም አሁን ላይ 20 ቋሚ ሠራተኞችና 45 የሚሆኑ የኮንትራት ሠራተኞችን ቀጥራ ታሠራለች። በጁስ ቤቷ ውስጥ ደግሞ 12 የሚደርሱ ሠራተኞችን የሥራ እድል ፈጥራላቸዋለች።
ራሄል ሠራተኞቿን ልክ እንደ ልጆቿ የምታይ እንስት ናት:: ብዙ ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ ስለምታውቅ ምንም እንኳን ምግባቸውን የሚያገኙት ከዚያው ቢሆንም ደሞዛቸውን ስትከፍላቸው ከምግቡ ውጪ ነው:: በዚህ ደግሞ ‹‹ለሠራተኞቼ ብቻ ሳይሆን ለእነርሱ ቤተሰቦች ጭምር መትረፍ ችያለሁ፤ ለልጆቼም ተምሳሌት የመሆን እድልን አግኝቻለሁ። ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል እያሳየኋቸው ነው። በአገልግሎቴ ጤናማ ማኅበረሰብን ማፍራት ችያለሁ›› የሚል አመለካከት ፈጥሮላታል።
‹‹ፍራቻ አቅምን ይቀንሳል፤ ጥገኝነትን ያበዛል፤ ውድቀትን ያፋጥናል። በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድፍረት ግን ከምንፈልገው ስኬት ላይ ያደርሰናል›› የሚል አቋም ያላት ራሄል፤ ሰዎች ማንኛውንም ሥራ ሲያስቡ ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል። ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ደግሞ ደፋር መሆን የግድ ይላል። ድፍረት ደግሞ በእውቀት መደገፍ ይኖርበታል። በጭፍን ደፋር መሆን ከፍርሃት አይተናነስም። አወዳደቃችንን በከፍተኛ ሁኔታ የከፋ ያደርገዋል ብላም ታምናለች። በዚህም ሰፊውን ሽፋን ይዘው ሥራውን የሚያከናውኑላትን ሴት ሠራተኞች በዚ ልክ ለመቅረጽ ትሞክራለች:: በቀጣይም የምታስበው ከእርሷ በታች ሆነው የሚሠሩ ሳይሆን ከእርሷ እኩል ሆነው አብረዋት የሚሠሩ ሴቶችን በብዛት መፍጠር ላይ ነው።
ራሄልን የመሰሉ ብርቱና ጠንካራ፤ በሥራ ደከመኝ የማያውቁ ሴቶችን ማፍራት ሕልሟ ነው። በዚህም ማታ እስከ አምስት ሰዓት ተኩል፤ ጠዋት ደግሞ 11 ሰዓት ላይ ቤቷን በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጡ ታበረታታቸዋለች። ሌሎችም ጠንካራ ሠራተኛ እንዲሆኑ እንዲህ ስትል ትመክራለች:: ‹‹አሁን ያለንበት ጊዜ በሕይወት ለመቆየት አብዝቶ መሥራትን ይሻል። የኑሮ ውድነቱን ተቋቁሞ ነገ ላይ ለመድረስ በተገደበ ጊዜ ሳይሆን በአልተገደበው ሙሉ ቀን ሁሉ መትጋትን የግድ ይላል። ስለሆነም ሁሉም ሰው በተሰማራበት ሁሉ ያለመታከት ለነገ የተሻለ ሕይወትና ሀገር መታተር ይኖርበታል›› በማለት ሀሳቧን ትቋጫለች።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም