አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ ካርታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ ይደረጋሉ

– የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን አብሮ የመሥራት ስምምነት ተፈራርሟል

አዲስ አበባ፡- የቱሪዝም ዘርፉ ከልማዳዊ አሠራር ወጥቶ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በስፔስ ሳይንስ እና በጂኦስፓሻል ለዓለም ተደራሽ መሆን እንደሚገባው ተገለጸ።የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ትናንት ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር አብሮ የመሥራት ስምምነት ተፈራርሟል።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቤተልሔም ንጉሤ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎቿን እያሰፋች ስለሆነ ዘመናዊ የቱሪዝም ካርታዎች ያስፈልጋሉ።አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ ካርታ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ ይሆናሉ።ለእዚህም የሞባይል መተግበሪያዎች ተዘጋጅተዋል።

ኢንስቲትዩቱ ይህን ሥራ ለመሥራት ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።የመግባቢያ ስምምነቱ ከሌሎች ክልሎች ጋርም ይቀጥላል ብለዋል።

እንደ ኢንጂነር ቤተልሔም ገለጻ፤ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከሚሠራባቸው ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው።ተቋሙ ለቱሪዝም ግብዓት የሚሆኑ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።የኢትዮጵያን የቱሪዝም ካርታ፣ የአማራ ክልልን እና የአዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ ካርታ ሠርቷል።“ቪዚት ኢትዮጵያ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ለቱሪዝም ሚኒስቴር አስረክቧል።“ጎ ቱር” የተሰኘ ድረ ገጽ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የጋሞ እና ደቡብ ኦሞ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።ኢንስቲትዩቱ የቱሪዝም ቦታዎችን የሚያሳይ አዲስ ስካነር መግዛቱንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ቱሪዝም ቀድሞ በነበረው አሠራር ብቻ ተገድቦ የሚቆይ ሳይሆን ከስፔስ ሳይንስ ጋር አብሮ የሚያድግ ነው።ቱሪዝም ከመሬት ውስጥ ውሃ እስከ ሕዋ ድረስ ያለው ሀብት ነው።በተለመደው መንገድ የሚታዩትን ብቻ ሳይሆን በስፔስ ሳይንስ እና በጂኦስፓሻል ምርምር የተደገፈ መሆን ይገባዋል ነው ያሉት።

ለእዚህም የቱሪዝም ተቋማት ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር አብሮ መሥራት ስለሚያስፈልግ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

እንደ አቶ ነጋ ገለጻ፤ የስፔስ ሳይንስ ራሱን የቻለ ቱሪዝም ከመሆኑም ባሻገር የቱሪዝም ዘርፉ በቴክኖሎጂ የታገዘ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን ያደርጋል።በቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ የሚኖረውን የአየር ሁኔታ የትንበያ መረጃ እንዲቀመጥ ያደርጋል።በየትኞቹ አካባቢዎች ምን እንደሚገኝ እና በየጊዜው ምን የተቀየረ ነገር እንዳለ መረጃው በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ይታወቃል።ዘመኑ የቴክኖሎጂ ስለሆነ ጎብኚዎችም ካርታ ይፈልጋሉ።በልማዳዊ መንገድ ይደረግ የነበረውን የአቅጣጫ ጥቆማ ዘመናዊ በማድረግ ጎብኚዎች ልዩ የሆኑ ሰፈሮችን ጭምር በቀላሉ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትን ሲጎበኙ፤ ኢንስቲትዩቱ ከከርሰ ምድር እስከ ስፔስ ድረስ የሚሸፍን የመረጃ ሥርዓት የገነባ መሆኑን አንስተው፤ የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ምን ላይ እንዳለ እና የመሬታችንን ሀብት እንድንለይ አስችሎናል ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁኑ ሰዓት ድረስ ያለው መረጃ በእዚህ ተቋም አማካኝነት ተመዝግቦ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መሬቶችን እያንዳንዳቸው በመለየት መሬቱ የማን ነው? በቦታው ላይ ምን እየተከናወነ ነው? የሚለውን ለመለየት እንዲሁም በመሸጥ በመለወጥ ሂደት ውስጥ ያለውን አሠራር መንግሥት እንዲያውቀው ተቋሙ የሠራው ሥራ ትልቅ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱን በጎበኙበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You