
ሻሸመኔ ፡- በኦሮሚያ ክልል ምእራብ አርሲ ዞን ውሃ ካለባቸው አካባቢዎች ወደ ሌለባቸው በመውሰድ ስድስት ወረዳዎችን እና 72 ቀበሌዎችን ያስተሳሰረ የመጠጥ ውሃ ልማት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ነጌሶ አስታወቁ።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ስድስት ወረዳዎችን ያስተሳሰረው የሄበን ነጌሌ ሲራሮ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የሥራ ሂደት እና ውጤት በጋዜጠኞች እና በሚዲያ አመራሮች ከትናንት በስቲያ ተጎብኝቷል።
የኦሮሚያ ክልል ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮና የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባዘጋጁት የጉብኝት መርሃ ግብር ላይ የተገኙት አቶ ደስታ ነጌሶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ክልሉ በተለይም ከለውጡ ወዲህ ባሉት አምስትና ስድስት ዓመታት የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍና ውሃን ለማዳረስ አቅዶ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።በእዚህም የመጠጥ ውሃ እጥረት የነበረባቸው ወረዳዎችን እና የገጠር ቀበሌዎችን በማስተሳሰር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ፕሮጀክቱ ከኦሮሚያ ክልል ባሻገር በማእከላዊ ኢትዮጵያ የምትገኘውን የሀላባ ቁሊቶ ከተማንም የመጠጥ ውሃ ችግር የፈታ መሆኑን አቶ ደስታ ተናግረዋል።
የውሃ ልማቱ እንደ ሻላ፣ አጄ ፣ ሲራሮ፣ ሞቲ ቢምሾ ፣ ሰንቤታ ሻላ ፣ ሻኮ አርሲ ፣ ሻኮ አላባ የመሳሰሉ ቆላማ የገጠር ከተሞችን እና ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በዋናነት በወንዶ ገነት እና ነጌሌ አርሲ አካባቢ ከተቆፈሩት የውሃ ጉድጓዶችና ወራጅ ወንዝ የተገኘውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ረዥም ኪሎ ሜትር የሚዘልቅ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ተዘርግተውለት ወደ ቆላማ አካባቢዎች የደረሰ መሆኑ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉ አቶ ደስታ ተናግረዋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ ትስስሩ በክልሎች መካከልም ትብብርና መደጋገፍ እንደታየበት አመልክተው፤ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የተደረገው ንቅናቄ ልክ እንደ በጋ ስንዴ ሁሉ አዲስ ታሪክ የተመዘገበበት እንደሆነም አስረድተዋል።
አቶ ደስታ የውሃ አቅርቦትን እንደ መንገድና መብራት በከተሞችና በገጠር ቀበሌዎች የማስተሳሰሩ ጅምር የሚያበረታታ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ገና ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።
የኦሮሚያ ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን በቀለ (ኢ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በክልሉ የመጠጥ ውሃ ሽፋን እና ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ያደሩ ፕሮጀክቶችን የመጨረስ እና ያለቁ ፕሮጀክቶችን ወደ አገልግሎት የማስገባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የሄበን አርሲ ነጌሌ ሲራሮ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 28 የውሃ ጉድጓዶች (የውሃ መገኛዎች) ፣ ከ500 በላይ ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታ የተደረገለት መሆኑን ጠቁመው፤ 316 ቦኖዎችን የያዘ፣ ከ17 ሺህ በላይ የቤት ለቤት ደንበኞች ያሉት እንደሆነ አንስተው፤ ፕሮጀክቱ ስድስት ወረዳዎችን እና 72 ቀበሌዎችን ያስተሳሰረ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በዲዛይን ወቅት ያላካተታቸው አራት ያህል ቀበሌዎችም በማሻሻያ ሥራ የሚካተቱበት እድል እንዲፈጠር ከአማካሪ ድርጅቱና ከኮንትራክተሩ ጋር ንግግር የሚደረግ ስለመሆኑ አመልክተዋል።
የውሃ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የኢኮኖሚ አቅምቸውን እንዲያጎለብቱ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፈው የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፤ ከእዚህ አንጻር ቢሮው ክትትል እና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የመስክ ምልከታው የአገልግሎት ጥራትን ፣ ያደሩ ፕሮጀክቶች ፍጥነትን እንዲሁም የነገ ትልምን አቅጣጫ ለማስያዝ ያለመ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡
በምዕራብ አርሲ፣ አርሲ እና ባሌ ዞኖች የተሠሩትን የመጠጥ ውሃ መሠረተ ልማቶች የሥራ ሂደትና ውጤት አስመልክቶ የተዘጋጀው የመስክ ምልከታ ዛሬና ነገም የሚቀጥል እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም