የተወለዱት ምስራቅ ወለጋ ጅማ አርጆ አውራጃ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርጆ ከተማ በሚገኘው ቢተወደድ መኮንን ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን ነቀምት ከተማ ይገኝ በነበረው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኮምፕሬሄንሲቭ ትምህርት ቤት ገብተው 9ኛ እና 10ኛ ክፍልን ተከታትለዋል፡፡ የመምህራን ማሰልጠኛ የመግባት እድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጦር አካዳሚ ወታደራዊ መሰናዶ ትምህርት ቤት ለእጩ መኮንንነት በመመልመላቸው ምክንያት የመምህርነቱን ነገር ሳይቀጥሉበት ይቀራሉ፡፡ ሆኖም በወታደራዊ አካዳሚው የተሰጣቸውን ፈተና በማለፋቸው በ1962 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ሐረር ተላኩና 11ኛና 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በወታደራዊ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀቁ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናቸውን በጥሩ ውጤት አጠናቀው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጦር አካዳሚ ገብተው ለሶስት ዓመታት በመሰልጠን የምክትል መቶ አለቃነትን ማዕረግ አገኙ፡፡ የወታደራዊ ሥልጠናቸውን አጠናቀው እንደተመረቁ በዘጠነኛ ብርጌድ ውስጥ ታንከኛ ሆነው ተመደቡ፡፡
የዛሬው የዘመን እንግዳችን ሱማሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ካራማራ ላይ ከወገን ጦር ጋር በመሆን ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ በወቅቱ ታዲያ እስራኤል ተልከው ለአራት ወር ያህል ለታንክ ተዋጊነት ሰልጥነው በመመለስ ዳግም ጦሩን ተቀላቅለው ወራሪውን ኃይል የመመከት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ በተለይም ባቢሌ ግንባር የተመደቡት እኚሁ ሰው ከሌሎች የሰራዊቱ አባላት ጋር በመሆን የሶማሊያን ኃይል ድባቅ በመምታት አገራቸውን ነፃ ማውጣት ችለዋል፡፡ በድሉ ማግስትም በመንግሥት የትምህርት እድል አግኝተው ዩክሬን በመሄድ በወታደራዊ ፖለቲካ ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰሩ፡፡ ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ብዙም ሳይቆዩ ኤርትራ ተመድበው እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ሻቢያን ሲታገሉ ቆዩ፡፡
የደርግ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ ደግሞ ልክ እንደሌላው የሰራዊት አባላት በግፍ ከሚወዱት ሙያ ተሰናቱ፡፡ በዚህ ግን ተስፋ አልቆረጡም፤ በተለያዩ የግል ተቀማትና ኤጀንሲዎች ውስጥ በጥበቃነት በማገልገል ቤተሰባቸውን ማስተዳደር ቀጠሉ፡፡ በ1998 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በነበረው የፖለቲካ ግርግር ጋር ተያይዞ ‹‹የቅንጅት ደጋፊ ነህ›› በሚል በሕወሓት ሰዎች ለእስር ተዳረጉ፡፡ ለሃሰት ክሳቸው ይመች ዘንዳም በደህንነቶቻቸው አማካኝነት የቅንጅት ሰነድ ቤታቸው እንዲገባና በዚያም እንዲጠየቁ ተደረገ፡፡ ማዕከላዊ ውስጥ በሚገኝ ጨለማ ክፍል ውስጥ ለአራት ወራት ከታሰሩ በኋላ በወቅቱ የነበሩት ዳኛ በነፃ ለቀቋቸው፡፡ ሆኖም ዳግመኛ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲከሰሱ በማድረግ በእስር እንዲቆዩ ተደረገ፡፡
የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ሲሉ የደም ዋጋ ከመክፈል በዘለለ የሚጠየቁበት ወንጀል ባይገኝባቸውም ቅሉ ቀድሞ ከተከሰሱበት ርዕሰ ጉዳይ ነፃ ቢወጡም ቂመኛው የወያኔ መንግሥት ግን እሳቸውን ለማሰር አርፎ አልተኛላቸውም፡፡ ትውልዳቸው ከወለጋ በመሆኑ ብቻ ‹‹ከኦነግ ጋር ንክኪ አለህ›› በሚል ደግሞ ሁለተኛ ክስ ቀረበባቸው፡፡ ይሁንና ከጠንካራ ክርክር በኋላ በዋስ እንዲፈቱ ተደረገ፡፡ ከእሳቸው ጋር ታስረው የተፈቱ 17 ሰዎች ሀገር ጥለው ሲጠፉ እሳቸው ግን ‹‹ሀገሬን ጥዬ የትም አልሄድም›› ብለው ቆዩ፡፡ አሜሪካ ኤምባሲ በጥበቃነት ተቀጠሩ፡፡ሆኖም በኤምባሲ ከተቀጠሩ ሁለት ዓመት ያህል እንኳን ሳይሰሩ አሁንም በማያውቁት ነገር ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ፡፡ በቀጥታ ቃሊቲ ገብተውም ያለምንም ማስረጃና ፍርድ ለአራት ዓመታት ታሰሩ፡፡
የአገር ባለውለታው እኚሁ እንግዳችን ከእስር ከተፈቱ በኋላም ጥለውት የወጡት የአሜሪካ ኤምባሲ ሥራ ዳግም ማግኘት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ባንኮችና የግል ተቋማት በጥበቃ፤ በኦፕሬሽንና በአስተዳደር ዘርፍ እየተዘዋወሩ አገለገሉ፡፡እንዲሁም በጀነራል ዓለምሸት በተቋቋመው ሎያል ሴኪዩሪቱ በተባለ ድርጅት ውስጥ በኦፕሬሽን ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ
ወቅት ደግሞ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የቀድሞ ስርዓት አባላት የሚመራው አገር አድን ኮሚቴ ውስጥ ገብተው አባላቱን የማደራጀትና የማሰማራት ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ አሸባሪውን ኃይል መቀመቅ ለማውረድ በሚደረገው አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ዛሬም እንደቀድሞው ሁሉ የበኩላቸውን ለማበርከት ሌት ተቀን እየደከሙ ይገኛሉ፡፡ የዛሬው የዘመን እንግዳችን የቀድሞ ሰራዊት አደራጅ ግብረ ኃይል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሻለቃ ጀምበሬ ተሰማ ናቸው፡፡ ከእንግዳችን ጋር በተለያዩ የሕይወት ገጠመኞቻቸውና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በደርግ ዘመን ኢትዮጵያ የነበረችበትን ፈተና ብዙዎች አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያመሳስሉታል፤ ለምሳሌ ጦርነቱ ከሕወሓት ጋር መሆኑ፣ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት፣ ሴራው፣ ወዘተ፤ ከዚህ አንጻር እርስዎ ያለዎት ምልከታ ምን እንደሆነ ያስረዱንና ውይይታችን እንጀምር?
ሻለቃ ጀምበሬ፡- ልክ ነው፤ በብዙ መልኩ በደርግ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ሆኖም የደርግ መንግሥት ከወያኔ ባሻገር በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውስጥ የሚሰሩት አሻጥርና የተቃውሞ ትግል ችግሩን የከፋ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ በተለይም ኢህአፓና መኢሶን ያደርጉት የነበረው ፀረ ደርግ እንቅስቃሴ መንግሥትን ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ከቶት ነበር፡፡ በዚያን ወቅት እኔ በተለይ ነባሩ ታንከኛ ውስጥ ስለነበርኩኝ በሰራዊቱ ውስጥ ሳይቀር ሰርገው ገብተው የሚሰሩብን ሴራ በቀላሉ የሚገለፅ
አይደለም፡፡ ልክ አሁን በመላ ሀገሪቱ እንደሚታየው ሁሉ ሁሉም ዜጋ በኢትዮጵያዊነት ወኔ አገሩን ለማዳን ሲረባረብ ሰርጎ የገባው ኢህአፓ ያሰማራችው ኃይል ከወያኔ በላይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥርብን ነበር፡፡ የሚገርመው በዚያም ጊዜ የአባት ጦሮች እንዲጠሩ ተደርጎ ነበር፡፡ ባቢሌ ላይ እያጠቃን እያለን ከኋላ በኩል አዛዦች በኢህአፓ አባላት ይመቱ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ይህ ነገር በደህንነት ሰዎች ታወቀና የኢህአፓን ተላላኪዎች በታንከኛ ከበብናቸውና ረሽንናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የሱማሌን ወራሪ ኃይል ወደ መዋጋቱ የቀጠልነው፡፡
ልክ እንደአሁኑ የውስጥ ችግሮች ነበሩብን፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያዊ አንድነትና በተባበረ ክንድ ወራሪውን ለማሸነፍ ችለናል፡፡ አሁንም እኛ ከተባበርን ይህን ፀረ- ኢትዮጵያ ኃይል ድባቅ የማንመታበት ምክንያት የለም ባይ ነኝ፡፡ እርግጥ ነው ወያኔ ላለፉት 27 ዓመታት ህዝቡን አታሎ የተወሰነ ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ለእነሱ ተገዢ የሆኑትን እና ተላላኪዎችን በመጠቀም ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ግን ባለፉት ሶስት ዓመታት በተሰራ ሥራ ብቻ አይደለም፡፡
እንደሚታወቀው ወያኔ ስልጣን ላይ በወጣ ማግስት የመከላከያውን ከላይ እስከታች ያለውን መዋቅር በራሱ ታማኝ ሰዎች እንዲሞላ አደርጓል፡፡ የሚገርምሽ በመከላከያ ውስጥ ከነበረው አባል ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት የእነሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ወያኔ የቀድሞ ሰራዊትን ለማፍረስ ወደኋላ ያለችበት ቀን የለም፡፡ ደካማ የሆነ እና አሻንጉሊት የሆነ የክልል አስተዳደር በመመስረት የራሳቸውን ተላላኪዎች አስቀምጠው እንዳሻቸው ሲያተራምሱ ነበር የቆዩት፡፡ አሜሪካም ብትሆን በዚህ ሴራ ላይ ቀንደኛ ተባባሪ ነበረች፡፡ ወያኔ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ሙሉ ህዝቡን እንዳሻው ሲበድልና አገር ሲበዘብዝ አሜሪካ አንዳችም ነገር ስትናገር አልሰማንም፡፡ ምክንያቱም የወያኔ አሻንጉሊት መንግሥት ለእሷ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ምቹ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡም ቢሆን ለ27 ዓመታት ግፍ እየተፈፀመበት ቢቆይም የሚከስበት የፍትህ አደባባይ ባለመኖሩ በዝምታ ውስጥ ነበር የቆየው፡፡ ህዝቡ ምሬቱን ጎልቶ ያወጣው ግን ሕወሓቶች ሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ግፍ መፈፃማቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረጉት በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነገር
ነው፡፡ ሰው የሆነ ፍጡር በገዛ ወገኑ ሊፈፅም የማይችለውን ሁሉ በመፈፃማቸው ነው ማንነታቸው በገሃድ እንዲወጣ ያደረገው:: ህዝቡ በዚህ ደረጃ እነሱን ለማስወገድ የተነሳው::
እናም ከጠየቅሽኝ ጥያቄ አንፃር አንቺም እንዳልሽው ምዕራባውያኑ መንግሥቱ ኃይለማርያም በማውረድ ለእነሱ ተላላኪ የሆነው ወያኔን ለማምጣት ያደረጉትን ሙከራ አሁን በዐቢይ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈፀም መቋመጣቸው ግልፅ ነው:: ይህንን የሚያደርጉትም ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ ብቻ ነው እንጂ እውነታው ጠፍቷቸው አይደለም:: ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን በሙሉ ለመቆጣጠር የምታስችላቸው ቁልፍ ሀገር በመሆንዋ ይህንን ዓላማቸውን ለማስፈፀም ሲሉ ወያኔ በኢትዮጵያውን ላይ የሚፈፅመውን ግፍ ችላ በማለት የበለጠ አገሪቱ እንድትበተን ሲሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ ነው::
በመሰረቱ እነሱ የፈለጉትን ቢያስቡም ኢትዮጵያ ገናና የሆነ ታሪክ ያላት፤ ህዝቦቿም የአሸናፊነት ስነልቦና የተላበሱና ዛሬም ህልውናቸውን አሳልፈው የማይሰጡ ናቸው:: እኔ እንደሚገባኝ የአሜሪካኖቹ ዝምታ ይህች አይበገሬ ህዝብ ያላትን አገርን ለማበርከክ እና የእነሱን የበላይነት በዓለም ላይ ለማሳየት ስለሚሹ ነው:: በወያኔ ግፍ የተማረረው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ላይ የምዕራባውያን ሴራም ስለገባው ሀገሩን ለማዳን ቆርጦ ተነስቷል:: አሁን ላይ ወጣት አዋቂው ሁሉ የቀደመ የአንድነት ታሪኩን ለመመለስ ሲል የውስጥ እና የውጭ ጠላቱን እየተፋለመ ነው ያለው:: ደግሞም በአጭር ጊዜ ውስጥ የወያኔን ግብዓተ- መሬት እንደምንፈፅም አልጠራጠርም::
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያሉት ተፅዕኖ እስከመንግሥት ግልበጣ ይደርሳል ብለው አያምኑም?
ሻለቃ ጀምበሬ፡- በእኔ በኩል ምዕራባውያኑ የቱንም ያህል ቢጥሩ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ላይ የፈፀሙትን ነገር በዶክተር ዐቢይ ላይ መፈፀም አይችሉም:: እሱም ቢሆን ‹‹አንገቴ ይቀላ እንጂ ሀገሬን አሳልፌ አልሰጥም›› ብሎ እቅጩን ነግሯቸዋል:: ከአሁን በኋላ በምዕራባውያን የሚንበረከክ አሻንጉሊት መንግሥት ሊኖር አይችልም::ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሄ አሁንም ቢሆን ህብረታችንን አጠናክረን ይህንን ባንዳ ጠራርጎ ከምድረገፅ ማጥፋት ነው:: እርግጥ ነው፤ አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሰራዊት በችግር ጊዜ ድንገት የተደራጀ ነው:: ከልምድም አንፃር ብዙ የሚቀረው ሊሆን ይችላል:: ሆኖም አሁን በአጠቃላይ ሀገሩን ከጥቃት ሲከላከል የቆየው የቀድሞውም ሆነ የአሁኑ ሰራዊት በጋራ እየተሳተፈ በመሆኑ፤ ልምድም የሚቀሰምበት እድል በመኖሩ እንዳውም ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ጠንካራ ሰራዊት ለመፍጠር ያስችለናል የሚል እምነት ነው ያለኝ::ደግሞም ሀገሩን የሚወድና ከጥቃት የሚጠብቅ ወኔ ያለው ኃይል ለመፍጠር እኛ ተደራጅተን እየሰራን ነው ያለነው:: በሎጅስቲክና የአመራር አቅማችንን እያሳደግን በመጣን ቁጥር እንደቀድሞው በቀጠናው አስፈሪ የሆነ ኃይል እንፈጥራለን:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ በውስጣችን ያሉ አሁንም ለእነሱ ተላላኪ የሆኑ ግለሰቦችን የማጥራት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ::
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞ ሰራዊት በተለይም በወያኔ መንግሥት ብዙ ቢገፋም መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ያለምንም ማወላወል ድጋፍ ማድረጉ ምንን ያሳያል ይላሉ?
ሻለቃ ጀምበሬ፡– እውነት ለመናገር ያለፉት 27 ዓመታት ለቀድሞው ሰራዊት ያሳለፍነው ጊዜ በጣም ከባድ ነው:: ጡረታ ያላገኘ አለ:: በተለያየ ሁኔታ የገደሏቸው አሉ:: እኔ ራሴ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ለማለፍ ተገድጃለሁ:: ያ ሁሉ ችግር ደርሶበትም ቢሆን ሰራዊቱ አሁንም ለሀገሩ ህልውና መቀጠል ደሙን ለማፍሰስ ቆርጦ ተነስቷል:: ደመወዝም ሆነ ጥቅማ ጥቅም አይፈልግም:: የሚፈልገው ትጥቅ ብቻ ነው:: በተለይም ኦሮሚያ አካባቢ በርካታ የቀድሞ ሰራዊት ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ነው ያለው:: በራሳቸው ተደራጅተው እያሰለጠኑም ነው ያሉት:: ቁልፍ ቦታዎች ከተሰጡት ጠላትን ድባቅ የመምት ብቃት አሁን አለው::
አዲስ ዘመን፡- ባለፈው 27 ዓመታት የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአንድ ብሄር የበላይነት የነገሰበት የፖለቲካ ውግንና የነበረው መሆኑ ምን አስከትሏል ብለው ያምናሉ?
ሻለቃ ጀምበሬ፡– እንደሚታወቀው ወያኔዎች በኢትዮጵያ ላይ የአንድ ብሔር የበላይነት ለማንገስ ሲሉ መከላከያውን በዚያው መልኩ ነው ያደረጁት:: አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በመከላከያ ውስጥ ከላይ እስከታች ባለ ቦታ ላይ እነሱ ብቻ ነበሩ ፈላጭ ቆራጭ የነበሩት:: ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ ወያኔዎች በጣም ዘረኛ አስተሳሰብ ያላቸው ከመሆኑ የተነሳ አንድ በጣም የሚታወቅ የቀድሞ ጀነራል ለጉዳያቸው ፈልገውት ጠርተውት እንኳን ከነሙሉ ክብሩና ማዕረጉ ለመጥራት ከብዷቸው በስሙ ሲጠሩት ‹‹ምነው ማዕረጌን ተዋችሁት›› ቢላቸው‹‹ አንተ የእኛ ጓድ አይደለህም›› የሚል አሳፋሪ መልስ ነው የሰጡት:: እናም እነሱ ለይስሙላ ከሌላ ብሔር የመጣ አንድ ጀነራል ቢሾሙ እንኳን በገዛ ራሱ ላይ እንኳን የመወሰን መብት እንዳይኖረው አድርገው ነበር የሚያስቀምጡት::
በደርግም ሆነ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን እንዲህ አይነት ብሔርን መሰረት ያደረገ አድሏዊ አሰራር ፈፅሞ አልነበረም:: ብዙዎቻችን እንደምናውቀው በሁለቱም ስርዓቶች የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጣ ነው:: ስልጣንና ሹመት የሚያገኘው በችሎታው ተፈትኖ ሲያልፍ እንጂ በብሔሩ ምክንያት አይደለም:: በሰራዊቱ ውስጥም ቢሆን ከፍቅርና ከመከባበር ውጪ በብሔር ወይም በቋንቋ መከፋፈል አልነበረም:: ወያኔ ሲመጣ ግን በአንድ ጊዜ ያ ለዘመናት በሀገር ፍቅርና አንድነት መንፈስ የተገነባውን የሰራዊት ስነ-ልቦና የሚንድ ነገር ነው የተሰራው:: ይህ ደግሞ ሰራዊቱን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ምንያል እንደጎዳው በዓይናችን አይተነዋል::
በመሆኑም አሁንም የሚደራጀው ኃይል የሀገሩን ድንበር የሚከላከል እንጂ የማንም ፓርቲ ውግንና ሊኖረው አይገባም የሚል እምነት ነው ያለኝ:: ሕገመንግሥቱን የሚያስጠብቅ ድርጅት እንጂ ለአንድ ብሄር የበላይነት የቆመ ሊሆን አይገባውም:: በዓለም ላይ ቢሆን በሀገር እንጂ በፓርቲ የሚቋቋም ሰራዊት የለም:: አሁንም ቢሆን ከዚያ ነፃ የሆነ፤ በሀገር ፍቅር የታነፀ ሰራዊት መፍጠር ነው የሚገባን:: እነዚህ ሰዎች በብሄር ተደራጅተው ሌላውን ለማጥፋት ሲሉ ያደረጉትን ነገር ታሪክ የማይረሳው ነው:: በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሆነ ግልፅ ነው:: ስለዚህ የሚቋቋመው ሰራዊት የኢትዮጵያን ህዝብ እኩል የሚያይ ሊሆን ነው የሚገባው:: የቀድሞ ሰራዊት እርሾ ሆኖ ያሉ ስህተቶች እየታረሙ ትክክለኛ፤ ሀገር ወዳድ፤ ለሀገሩ ዘብ የሚቆም ሰራዊት መፍጠር ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይአሕመድ መዝመት የሰራዊቱን ሞራል ከመገንባት አኳያ ምንአይነት ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?
ሻለቃ ጀምበሬ፡– ጥሩ ሃሳብ ነው ያነሳሽው! መሪ ሁልጊዜም ቢሆን ፊት ሆኖ ነው መምራት የሚገባው የሚል እምነት አለኝ:: መሪ ፊት ሆኖ በመራበት የጦር ዓውዶች ሁሉ ድል አይጠፋም:: ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የእስራኤሎች ተሞክሮ ነው:: እስራኤል ብዙውን ጊዜ መሪዎቻቸው ናቸው ፊት የሚወጡት:: ‹‹አንድ ለሁሉ፤ ሁሉ ለአንድ›› የሚል አባባል አላቸው:: ህዝቡ ለመሪው ይሰለፋል፤ መሪውም ለህዝቡ ይቆማል:: አምስት ሚሊዮን የማይሞላው የእስራኤል ህዝብ 32 የአረብ ሀገራት ተሰልፎባቸው ሙሉ ለሙሉ ገትረው መከላከልና እንዳውም በማጥቃት የበላይነታቸውን ይዘዋል:: ይህ ሊሆን የቻለው አንድነታቸው ጠንካራ ስለሆነ ነው::
በእኛም ሀገር ቢሆን አብዛኞቹ መሪዎቻችን ከሰራዊቱ ጋር አብረው ተሰልፈው ጠላትን ድል ነስተዋል:: መንግስቱ ኃይለማርያም በየጊዜው በየጦር ሜዳው እየመጣ ለሰራዊቱ ሞራል ይሰጥ ነበር:: ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ቢሆኑ ሰራዊቱ በዘመናዊ መንገድ እንዲደራጅ ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል:: ያልተማሩት የወያኔ ሰዎች ግን ያንን ጠንካራ ተቋም አጠፉት:: መሪ ሁልጊዜ የአመራር ብቃቱን የሚያሳየውና ህዝቡንም ከጎኑ ማሰለፍ የሚችለው ከፊት ሲሆን ነው:: ለየትኛውም ነገር የቆረጠ መሪ መኖሩ ሲታወቅ ነው ህዝቡ ድጋፍን የሚሰጠው:: ዶክተር ዐቢይም ይህንን ተገንዝበው ከፊት ለመሰለፍ መቁረጣቸው በህዝቡ ዘንድ የነበራቸው ዓመኔታና ክብር እንዲጨምር ነው የሚያደርገው:: እንደምናየውም ከፊት ሆነው እየመሩ በመሆናቸው ነው አንፀባራቂ ድል እየተጎናፀፍን ያለነው::
አዲስ ዘመን፡- ከጦር ሜዳው ባሻገር ወያኔ በየቦታው ያሰማራቸው ተላላኪዎች የኢኮኖሚ አሻጥር እና መሰል ፀረ -ህዝብ ድርጊት እንዳይፈፅሙ በምን መልኩ መከላከል ይቻላል?
ሻለቃ ጀምበሬ፡– ልክ ነው፤ በየቦታው ያደራጇቸው ተላላኪዎች እንዳሏቸው አሁንም ግልፅ ነው:: እነዚህ ኃይሎች የጌቶቻቸውን ትዕዛዝ የሚጠብቁና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሀገር የማስረበሽ ሥራ ለመስራት ሙከራ ማድረጋቸው አይቀርም:: በመሆኑም መንግሥትና የፀጥታ ኃይሉ ብሎም ህዝቡ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አካባቢውን መጠበቅ አለበት ባይ ነኝ:: በእኔ እምነት በተለይ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው የደህንነት ኃይሉ ዋነኛ ሥራ ቢሆንም ህዝቡም በራሱ ተደራጅቶ አካባቢውና አገሩን ከጥፋት የሚጠብቅበት ሁኔታ መፈጠር አለበት:: ለዚህ ደግሞ ጊዜያዊ የሆነ ኮሚሽንም ቢቋቋም የተሻለ ነው ባይ ነኝ:: በዚህ ኮሚሽን ውስጥ ጦር ሜዳ ለመዝመት አቅማቸው ያልቻሉ የቀድሞ ሰራዊት አባላትን በማስገባት ህዝቡን እንዲያነቁ ማድረግ ያስፈልጋል:: እነዚህ ሰዎች እኮ ይህችን አገር ለማፍረስ ሲሉ የማይምሱት ጉድጓድ እንደሌለ አይተናል:: የእምነት ተቋማትን ሳይቀር ለሽብር አላማቸው ማስፈፀሚያ እስከማድረስ ደርሰዋል:: በቅርቡ እንደሰማነው በሬሳ ሳጥን መሳሪያ አስገብተው አገር ለማተራመስ ሙከራ አድርገው ነበር::
ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ይህች አገር እስከምትጠፋላቸው ድረስ የማይተኙልን መሆናቸውን አውቀን እኛም ቀን ከሌሊት ዘብ ልንቆም ይገባል፤ ጊዜ የሚሠጠውም ነገር አይደለም:: እርግጥ ነው የፀጥታ ኃይሉ ውስጥ ሰርገው ገብተው ብዙ አሻጥር እንደሚሰሩም ይታወቃል:: ስለዚህ ሁሉም ክልልና ድርጅት ራሱን ማጥራት ያስፈልገዋል:: በመከላከያ ውስጥ ራሱ ገብተው የታንክ መውጊያ እስከ መዝረፍና የወገን ኃይል እንዲጠቃ የተደረገበት ሁኔታም አለ:: በሁሉም መስኩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል:: ያንን የሚቆጣጠር አካል ግን ያስፈልጋል:: እኩይ ሥራ የሚሰራው ላይ ሌላውን ለማስተማር ያስችል ዘንድ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ::
ሻለቃ ጀምበሬ ፡- እኔም በዚህ ታሪካዊ ወቅት ተሞክሮዬንና ሃሳቤን እንዳካፍል እድሉን ስለሰጣችሁኝ ከልቤ አመሰግናለሁ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014