ከሳምንቱ ቀናት በአምስቱ ከፀሐይ ጋር ቋሚ ቀጠሮ አለን፡፡ እርሷ ወደ ማደሪያዋ ማቆልቆል ስትጀምር ለአንድ ነገር እተጋለሁ፤ ከመኪናው መስኮት በኩል ያለውን መቀመጫ ለማግኘት። ምክንያቴ ማየት ነው፤ መንገዱን፣ ሰዎቹን፣ ሕንጻዎቹን፣ ግርግሩን፣…።
ከሚፈጥነው መኪና መስኮት የማየው የዓለምን ቅንጭብ ነው። ከፊቴ ያየሁት ዛፍ በሰከንዶች ውስጥ በመብራት ምሰሶ፣ ወጣቷ ከኋላዋ በሚያዘግሙ አዛውንት፣ አውቶቡሱ በሚከተለው የጭነት መኪና፣ ትልቁ ሕንጻ በሌላ ሕንጻ፣…፤ ጨርሼ የማየው ነገር አይኖርም። ሁሉም የቅምሻ ያህል ቅንጭብ ነው፤ እንዲህ መሆኑ ግን ከምንም ነገር በላይ ይጥመኛል።
ህይወታችንም የቅንጭቦች ጥርቅም እንደሆነች ይሰማኛል። አስቁመን የምናጣጥመው አልያም እስከሚበቃን የምንኖረው የህይወት ክፍል የለንም። አንዱ በሌላ ይተካል፤ ሌላውም ለሌላ ቦታውን ይተዋል። ከማህጸን በመውጣታችን የምናስከትለው ለቅሶ ከእናታችን ዕቅፍ ስንገባ በፍስኃ ይተካል።
ብዙም አንቆይም ዳዴ ለማለት ከሙቀቱ እወጣለን፣ «ወፌ ቆመች» ከመባላችን መኮላተፍ፣ ዓይተው ሳይጠግቡን ደግሞ ወዲያ ወዲህ መሯሯጥ፣ ልጅነታችንም ዕድሜ አይኖረውም ራሱን ወደ ወጣትነት ያሳድጋል፣ በዚያው ፍጥነት ደግሞ ጉልምስና ይተካል፣… ቅንጭብ ህይወታችን ተጠራቅሞ ዕድሜ ይባልና መድረሻችን ከመቃብር ይሆናል።
ህይወት መንገድ የመሆኗ ቅኔ የተፈታልኝ፤ የምሳፈርበት መኪና ወደፊት ሲስፈነጠር የቀደመንን ሁሉ ወደሁዋላ እየተውነው በሄድንበት ጊዜ ነው። ህይወት ጎዳና ናት፤ ዕድሜ በተባለ መንኩራኩር ተሳፍረን የምናልፍባት። የቀደመውን ሸኝታ አዲሱን የምትቀበል።
ከመንገድ ዳር ከተነጠፈ ሸራ ወደ ተደረደሩ ዕቃዎች አጎንብሰው ከሻጭ የሚከራከሩ ገዢዎች፤ ተስማምተው የግላቸው ያደርጉት ይሆን? አልፏቸው ከቆመው አውቶቡስ ደርሰው ትኬት ለመቁረጥ የሚሮጡት ባልቴት፤ ከቦርሳቸው የሚንጠባጠቡትን ሳንቲሞች ሊያነሱ አጎነበሱ ወይስ አውቶቡሱን መረጡ? ከሻይ ቤት ደጃፍ የተቀመጡትን ሰዎች ምጽዋት እንዲጥሉላቸው የሚማጸኑት የኔቢጤ አገኙ ወይስ አጡ? ከጎረምሶች ጋር ለታክሲ የሚጋፉት አዛውንት ገቡ ወይስ ተረፉ? እጇን አሁንም አሁንም የምታወናጭፈው ወጣትስ ጓደኛዋን ጥላው ሄደች ወይስ ተስማሙ?
ጅምሩን ከማየት ውጪ የምጨርሰው ታሪክ እንዳይኖር መኪናው ይዞን ይበራል፤ ከጠጅ ቤቱ እስክንደርስ ይህ ሁሉ ቅንጭብ ህይወት ነውና እኔን ይጥመኛል። ከመንገዳችን እኩሌታ፤ ከድልድዩ አጠገብ ወንዙን በፍርሐት የምታይ የምትመስለው ጠጅ ቤት የድሆች መናኸሪያ እንድትሆን የተቀለሰች ይመስለኛል።
ቢበሉም ባይበሉም የምታጠግባቸው ብቸኛዋ አሳቢያቸው ሆናለች፤ በደቃቃ ሳንቲም ብርሌያቸውን ጨብጠው ማጣታቸውን ይዘነጋሉ። ጀምበር ማቆልቆል ስትጀምር ይሰባሰባሉ፤ ስናልፋቸው የውስጣቸውን ጉዳት ረስተው እየተሳሳቁ ነው። ሰማያዊ ቀለም ያለውን መኪናችንን ይለዩታል፤ ስንደርስ እጅ ይነሱናል።
ልምድ አድርገውታል ግማሾቹ ተቀምጠው የተቀሩት ቆመው እጃቸውን ያውለበልባሉ። የቀን ተቀን ልምዳቸው በመሆኑ ከዚያች ስፍራ ስንደርስ ተሳፋሪው ሁሉ ለዚህ ትዕይንት ይሰናዳል፤ በአድራጎታቸውም ይሳሳቃሉ።
እኔ ግን ሁሌም ቆጠራ ላይ ነኝ፤ ስናልፋቸው ከተውለበለቡልን እጆች መካከል የቷ እንዳለፈች አስባለሁ። በቋፍ ያለ ኑሯቸው ከወንዙ አፋፍ እንደተቀለሰችው ጠጅ ቤት ህይወታቸውን ከቋፍ አድርሶታል። ስናልፋቸው ጎድለው በሚጠብቁን እጆች የሚተኩት ሌሎቹ እጆችም የሚያጣጥሙት የጠጁን ቅንጭብ ነው። አንዱ ዕለት በሌላኛው ሲተካ መዳፎቻቸው ሲላሉ ክንዶቻቸውም ሲረግቡ አስተውያለሁ።
ህይወታቸው በየቀኑ እየተሸረሸረ እንደሚገኝ ይሰማኛል። ወደ አንድ ጎን ካዘመመው አቋቋማቸው፣ ከማበጠሪያ መለየቱን ከሚያሳብቀው ጸጉራቸው፣ ከበለዘው ፊታቸው፣ ከቆቡ ለመላቀቅ ከሚታገል ዓይናቸው፣ ፈገግ ሲሉ ከሚሸበሸበው የጉንጭ ቆዳቸው፣ በከፊል ከወላለቀውና ከተሸራረፈው ጥርሳቸው፣ ጭንቅላታቸውን መሸከም አቅቶት ወዲያ ወዲህ ከሚዋልል አንገታቸው፣ እንደነገሩ በአዳፋና አሮጌ ልብስ ከተሸፈነው የገረጣ ሰውነታቸው፣ ሚዛኑን መጠበቅ አቅቶት ከሚወዘወዝ ቄጤማ እግራቸው ስር በየቀኑ የሚናድ መንገድ ይታየኛል።
የህይወት ፍቺና ትርጉሟ የገባኝ ሳልፍ ባለፉ ሰዎች ነው። እነርሱ ጋር እኛ በመኪና ስናልፍ ወደሁዋላ እንደምንተወው ዓይነት ሳይሆን፤ እያደር መንገዱ ወደ እነርሱ የሚቀርብ ይሆንብኛል። መሄጃቸውን የማያውቁ ተሳፋሪዎች ናቸውና እኔ የማጣጥመውን ያህል የቅንጭብ ህይወት ጣዕም አያውቁትም። መንገዳችን ለየቅል ነው፤ እኛ ልንመለስ ስናልፋቸው እነርሱ ደግሞ ዘላቂዎች ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
ብርሃን ፈይሳ