በአሁኑ ወቅት የሃራችንን ህልውና ለማስቀጠል ስማቸው ከፊት ከሚጠራው የሃገር መከላከያና የጸጥታ ዘርፍ አባላት ባሻገር ጋዜጠኞች፣ የታሪክ ምሁራንና ደራሲያን፣ ትልልቅ ፖለቲከኞች በአጠቃላይ ከእውነት ጋር የተቆራኙና ለሆዳቸው ያላደሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም የሌሎች ዓለማት ዜጎች ከሀገራችን ጎን በመቆም አኩሪ ሙያዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጀብዱን በመፈፀም ላይ ይገኛሉ።
በዚህ የእውነትን ማሳወቅ ትግላቸውም ከእኛ በላይ አፍ ሆነውልን የራሳቸውን ጥቅምና ሌሎች ነገሮቻቸውን ትተው ከመሟገት ጀምሮ ለሀገራችን የኢንተለጀንስ ተቋማት ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ ምስጢሮችን ወደ አደባባይ እያወጡ ታሪክ እየሠሩ ይገኛሉ። ለዚህም እንደ አገርና ህዝብ ትልቅ ምስጋና እንዲሁም አክብሮት አለን።
አሜሪካ ለአሸባሪው ሕወሓት ከተመረጠ መንግሥት ጋር እኩል ደረጃ እየሰጠች እንደውም አብዝታ እየወደደችና እየፈለገችው ነው:: ይህንን ሴራዋን ለማስፈጸም ደግሞ አገራችን ላይ ማዕቀብን ጨምሮ የተለያዩ ጫናዎች በማሳደር ከዓለም አቀፉ ንግድ (አገዋ) በመሰረዝ ለአሸባሪ ቡድኑ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ኢትዮጵያን የማዳከም ሥራዋን ቀጥላበታለች::
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያሉ ዜጎቿን ለቃችሁ ውጡ፣ የሽብር አደጋ እንዳይደርስባችሁ በማለት የበሬ ወለደ ወሬዋን በማውራትና ህዝብ እንደ ህዝብ እንዳይረጋጋ በማድረግ ስነ ልቦናዊ ጫናን ለማሳደር ጥረት እያደረገች ነው:: አሜሪካን ይህንን ታድርግ እንጂ ዜጎቿም ምን ሆንን ብለን ምን ሰምተን ነው በሰላም እየኖርን ካለንበት አገር ለቀን የምንወጣው ብለው ቁጭ ከማለታቸውም በላይ ጭራሽ ሌሎች ዜጎቿም በዚህን ወቅት ወደአገሪቱ በመግባት ላይ ናቸው::
ከእነዚህ ውትወታዋና የበሬ ወለደ የሐሰት ፕሮፓጋዳዋ ችላ ብለው ከአገራችን ጎን ለመቆም ከመጡት መካከል ደግሞ የአፍሪካ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ሎረንስ ፍሪማን አንዱ ናቸው:: ዘኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከእሳቸው ጋር ያረገውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ቆይታ፡፡
ዘኢትዮጵያን ሄራልድ፡- ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለመጀመሪያ ጊዜዎት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እውነታ በተለይም ከምዕራባውያኑ መንግሥታትና መገናኛ ብዙሃን አንጻር እንዴት ያዩታል?
ሎረንስ ፍሪማን፡- አይ አይደለም ወደ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ መጥቻለሁ የመጀመሪያዬም አይደለም:: አገሪቱንም በደንብ አውቃታለሁ:: እንደውም ላለፉት 10 እና 12 ዓመታት አጥንቼዋለሁ:: የአፍሪካ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮችን ለመተንተን ከተጓዝኩባቸው በርካታ የአፍሪካ አገራት የተሻለ ፖለቲካዊ መረጋጋት ሰላምና ደህንነት ያላት አገር ናት:: አሁን ላይ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃንና መሪዎች በተለይም አሜሪካና አውሮፓ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጀመሩት የስነ ልቦና ጦርነት ነው::
ለዚህ ይረዳቸው ዘንድ ደግሞ የተለያዩ የተዛቡ መረጃዎችን የመስጠት እንዲሁም የውሸት ዘገባዎችን በመሥራት ላይ ተጠምደው ነው ያሉት:: ይህንን ደግሞ ሆን ብለው የሚያደርጉት ነገር ነው፡፡ አሜሪካ ህዝቡን አሸብራ ለሽብር ቡድኑ መንገድ ለመክፈትና በዚህ ውስጥ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት እየሠራች ነው::
በአሁኑ ወቅት ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙሃን፣ አሜሪካ እና የተወሰኑ አውሮፓውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ በሐሰት ላይ የተመሰረተ የስነ[1]ልቦና ጦርነት ከፍተዋል፤ እነዚህ አገራት አቅደው በሐሰት መረጃ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብና ሕዝቡ እንዲወናበድ እያደረጉ ነው:: አዲስ አበባ ሰላም እንዳልሆነች አስመስለው በሲኤንኤን ይዘግባሉ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ወደ ኢትዮጵያ ዜጎች እንዳይመጡና እዚህ ያሉ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው እንዲወጡም እየወተወቱ ነው::
ውትወታውን ካልተቀበሉት አሜሪካዊያን አንዱ እኔ ነኝ:: በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ እኔ እነሱ የሚሉትን ጉትጎታ ሳልሰማ ወደኢትዮጵያ ለመምጣት ስሞክር ብዙ ሰዎች ተው ብለውኝ ነበር ፤ እኔ ግን ያለውን እውነታ ለመመልከት ብዬ ነው የመጣሁት፤ በአውሮፕላን ስመጣ ወንበሮቹ ሁሉ ሞልተዋል፣ የአዲስ አበባ አየር ማረፊያ የተለመደ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ተመለከትኩ ፤ከአውሮፕላን ወርጄ ከተማው ላይ ስንቀሳቀስም ከተማዋ ውስጥ ከሕፃናት ጀምሮ ሌሎች ሰዎችም በሰላም ወደሥራና ትምህርት ገበታቸው በሰላም ይዘዋወራሉ:: ሱቆችና መዝናኛ ስፍራዎችም ክፍት ሆነው ለተጠቃሚዎቻቸው አገልግሎትን ሲሰጡ ተመልክቻለሁ::
እዚህ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ ይህንን እውነታ በደንብ ያውቃል፤ ነገር ግን ሆነ ብሎ የውሸት መረጃን እያሰራጨ ስለመሆኑ ሊታውቅ ይገባል:: አሜሪካና አጋሮቿ የፖለቲካና የስነ ልቦና ጦርነት በመክፈት ኢትዮጵያን ለማዳከም አቅደው እየሠሩ ነው፤ ይህ ሊታወቅ ይገባል::
የአሜሪካ የወቅቱ አስተዳደሮች ሰዎች በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በእነሱ ይሁንታ እና ቁጥጥር ስር ማዋል ባለመቻላቸው፣ አገሪቱንም ሆነ ቀጠናውን ማተራመስን መርጠዋል:: ይህ ደግሞ እንደእኔ እብደት ነው::
ኢትዮጵያውያን በሕወሓት መራሹ የሽብር ቡድን የተደፈረውን ሉዓላዊነታቸውን በመሪያቸው አማካይነት ወደነበረበት ለማስመለስ እያደረጉት ያለው ጥረት በጣም ከፍተኛ ውጤት የሚያመጣ ከመሆኑም በላይ ምዕራባውያኑንም የሽንፈትን ጽዋ የሚያስጎነጭ ነው:: ዘኢትዮጵያን ሄራልድ፡- ለምን ይመስልዎታል እነዚህ አካላት በኢትዮጵያ ላይ የተጠናከረ ዘመቻን የከፈቱት ?
ሎረንስ ፍሪማን፡- ይህ እንግዲህ የሚያሳየው ምዕራባውያን ምን ያህል በታመመ አስተሳሰብ ውስጥ እንዳሉ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልሂቃን አሉ፣ እኔ ኦሊጋርኪ ብዬ ነው የምጠራቸው(ጥቂቶች ብቻ የደለቡበት የኢኮኖሚ ሁኔታ ማለት ነው)።
እነዚህ አካላት ሁሉንም ነገር መቆጣጠር እንዳለባቸው ያምናሉ፤ እና እነሱ እንደሚፈልጉት ያልሄደን ነገር ሁሉ የተገደበ ዓለም ነው ብለው ያምናሉ፤ ከዚህ የተነሳ ደግሞ የሕይወት ዋና ዓላማቸው መሆን ነው፤ ከዚህ የተነሳ በእነሱ ፍላጎትና አስተሳሳብ ባልሄደ አካል ላይ ሁሉ የሚያደርሱት ጫና የሚታይ ነው:: እንደ ምሳሌ በቻይና ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መመልከት በቂ ነው።
በመሆኑም የጂኦ ፖለቲካል አስተሳሰባቸው ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ በእነሱ ቁጥጥር ስር እንዳልሆኑ ነው የሚያዩት። እናም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ብጥብጥ እና ጦርነት መፍጠርን ይመርጣሉ፡፡ ምክንያቱም እነሱ ራሳቸው ስላልተቆጣጠሩት። ይህ ለእኔ የእብደት ዓይነት ነው። ሰዎች በዚህ መንገድ ማሰብ በጣም ከባድ ነው። እኔም ይህንን ለ50 ዓመታት አጥንቻለሁ።
ከጥናቴ ተነስቼም ለመናገር ስሞክር ችግሩ በባይደን አስተዳደር ውስጥ እነዚህን መሰል ሰዎች መኖራቸው ነው። ፕሬዚዳንት ባይደንን ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የሚችለውን የአገዛዝ ለውጥ ወደ አለመረጋጋት ለመሳብ እየሞከረ ነው። ምን ያህል አብሮ እንደሚሄድ አላውቅም። ምክንያቱም ፕሬዚዳንት ኦባማ ሊቢያን መረጋጋት እንዳሳጣት ሁሉ መንግሥታቸው የረዥም ጊዜ አጋርን ያለመረጋጋት እንዲኖረው ይፈልግ እንደሆነ አላውቅም።
አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አገራቸውን ከጎሳ እንቅስቃሴና ተገንጣይ ቡድን ለማላቀቅና በወታደራዊ ኃይል መንግሥትን ለመጣል የሚያደርገውን ጥረት መፍቀድ ባለመቻላቸው የተከሰተ ጫና ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዓመት በሰኔ እና በመስከረም ወር በተደረጉ ሁለት ምርጫዎች ተመርጠዋል። ከ43 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ድምፅ ሰጥቷቸዋል። ያ በፕሬዚዳንት ባይደን እውቅና ተሰጥቶት አያውቅም።
በስቴት ዲፓርትመንት ወይም በዩኤስ ኮንግረስ፣ እንዲሁም በአውሮፓ ውስጥ ያለ ማንኛውም አካል ለጉዳዩ እውቅና አልሰጠም:: ምክንያቱም ዕውቅና መስጠት ስለማይፈልጉ ነው:: ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ 43 ሚሊዮን ሕዝብ የወጣበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደነበር መቀበል አይፈልጉም።
የባይደን አስተዳደር በሀገሪቱ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ አመራር እንዲኖር አይፈልግም። ስለዚህ ለምርጫ እውቅና ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ነገር ግን በምርጫው ወቅት የአፍሪካ ህብረት እዚህ ነበር። እናም ፍትሐዊ ምርጫ ነበር ብሏል።
ይህም ቢሆን ግን የኔ መንግሥት ቀና ነገር ተናግሮ አያውቅም፤ መንግሥትን ለመጣል የሚሞክረውን ወያኔን እንደ አንድ የተመረጠ መንግሥት እኩል ፓርቲ አድርገው ይቆጥሩታል። በዚህ ከቀጠለ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ችግር ውስጥ ይወድቃሉ:: ምክንያቱም እንደምታውቁት አፍሪካ በመቶዎች በሚቆጠሩ ጎሳዎች ተሞልታለች።
አሜሪካን ከተመረጠ መንግሥት እኩል ለሕወሓት ደረጃ ከሰጠች፣ ናይጄሪያ ላይ የሠራችውን ተመሳሳይ የቢያፍራ ጦርነት እንዲቀጣጠል በማድረግ ኢትዮጵያንም የመበጣጠስ ህልሟን ለማሳካት ትጥራለች። በመሆኑም ለዚህ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል:: ዘኢትዮጵያን ሄራልድ፡- ለምንድነው አሜሪካ በምርጫ ለተመረጠው መንግሥት እውቅና ከመስጠት የተቆጠበችው?
ሎረንስ ፍሪማን፡- በምርጫው ወቅት ስድስት የሚሆኑ አሜሪካውያን ታዛቢዎች እዚህ ነበሩ። 65 ያህል ሰዎች የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ነበሩ፤ ስለዚህ ወደ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በመዞር ምርጫውን ማየት አልቻሉም። ችግሩ ይህንን ያሉት የባይደን አስተዳደር ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው:: እነዚህ በፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ውስጥ ያሉ ሰዎች ደግሞ ከሕወሓት ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። እናም በኢትዮጵያ ላይ እንዲህ ዓይነት ቁጥጥር እንዲኖር ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ መሆን አልቻለም::
እንደ ሴክሬተሪ ብሊንከን፣ ጋይል ስሚዝ፣ ሳማንታ ፓወር፣ ሊንዳ ቶማስ፣ ግሪንፊልድ፣ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ጥፋት እየተስተዋለ እነሱ የሚፈልጉት ነገር ብቻ ስለሆነ የሚያዩትና የሚሰሙት 7 ሚሊዮን ተፈናቃዮች በአፋርና በአማራ ክልል መኖራቸውን ቸል ብለዋል:: ይህ ቁጥር ምናልባትም በትግራይ ከሚሰቃዩት እጅግ ይበልጣል። ነገር ግን መልሳቸው ዝም ሆኗል::
አሁን ላይ ግን ምንም ይሁን ምን መንግሥት ይህንን ጦርነት መፍታት አለበት፣ ወያኔ መንግሥትን መጣል አንችልም ብሎ አምኗል። ኢትዮጵያዉያን ላለፉት 10 ዓመታት ሲኖሩበት የነበረው የኢኮኖሚ እድገት ተዳክሟል፡፡ ሀገሪቱን የመገንባትና ሥራ መሥራት አለብን። በአገሪቱ ላይ መሰል ችግሮች እንዳትይከሰቱም መፍትሔው ለሁሉም ሰው የሚሆን የኢኮኖሚ ሀብት ማሳደግ ነው። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የየራሳቸውን ክልል ፈላጭ ቆራጭ ፖሊሲ መፍጠር ሳይሆን እንደ አንድ የኢትዮጵያ ዜጋ መሆን፤ መሥራትና መለወጥ የግድ ያስፈልጋል::
እዚህ ላይ ልል የምችለው ነገር ቢኖር በአገሪቱ ውስጥ የቡድን ዜጋ መኖር የለበትም፤ እናም ቡድኖቹን ማቆየት ፤ የተመረጠ መንግሥት ማክበር መታዘዝና ተረዳድቶ ለማደግ መሞከር ይገባል። ነገር ግን መንግሥትን ካልወደዱ በሚቀጥለው ምርጫ ላይ መቀየር ብቸኛው አማራጭ ነው::
ግን ጦርነት ማወጅ እና የአዲሱ የሽግግር መንግሥት አካል ለመሆን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ አይደለም። ዘኢትዮጵያን ሄራልድ፡- ዴሞክራቶች ዴሞክራሲን በዓለም ላይ ለማስፋት እንሠራለን ይላሉ። ታዲያ የተመረጠውን መንግሥት ለመጣል የሚደረገው ሙከራ ከራሳቸው መርህ ጋር አይቃረንም? ሎረንስ ፍሪማን፡- እንግዲህ አንድ ነገር መገንዘብ ያለብን ፣ ለዴሞክራሲ ያላቸው አመለካከት የዴሞክራሲን የበላይነት እየተጫነ መሆኑን ነው። በነገራችን ላይ አሜሪካን ቀጥተኛ ዴሞክራት አገር አይደለችም:: ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እንጂ።
ለምሳሌ እኛ ፕሬዚዳንታችንን የምንመርጠው ጥበበኛ እና አስተዋይ ሰዎችን በመምረጥ ሲሆን፤ እነሱም ምርጫ ኮሌጅ ይባላሉ። እኛ ንፁሕ ዴሞክራሲያዊ አገር አይደለንም፣ ያለፉት ምርጫዎች እንዳሳዩት፡፡ ነገር ግን ፀሐፊ ብሊንከን እና ሌሎች ዴሞክራሲ እንፈልጋለን ሲሉ፣ ምን ማለታቸው ነው፤ ፍላጎታቸውን በሌሎች ሀገራት ላይ መጫን ይፈልጋሉ እንዴ ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል።
ለእኔ ዴሞክራሲ ምርጫ ብቻ አይደለም፡፡ እውነተኛው ዴሞክራሲ የተማረ፣ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ያለው እና በአገሪቱ ፖሊሲዎች ላይ መወያየት የሚችል ዜጋ መኖሩን ማረጋገጥ ነው። ዴሞክራሲ ማለት ዜጎች በወደፊቷ ሀገር ጉዳይ ላይ መወያየት ሲችሉ ማየት ማለት ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ መብራት፣ ምግብ፣ በቂ መኖሪያ ቤት፣ ልጆቻችን ተምረው ማንበብ ሲችሉ፣ የሚታሰብ ነገር ሲኖር ነው::
ይህን ማድረግ ከተቻለ እርስ በእርሳችሁ ተገናኝታችሁ የተለያዩ የከተማ ማዘጋጃ ቤት ስብሰባዎችና መድረኮች፣ ላይ ትወያያላችሁ፡ ፡ እኔም ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ መሄድ አለባት ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን እንደ ብሄር ሳይሆን እንደ አንድ ዜጋ ስለ ሀገራችሁ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ክርክር ማድረግ አለባችሁ። ለኔ ይህ ዴሞክራሲ ነው። ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ግን ልማት ሊኖር ይገባል።
መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት መጠበቅ ዴሞክራሲ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ መብራት፣ ምግብ፣ የሰዎችን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ መሰረተ ልማቶች መገኘት የሰው ልጆች መብቶች ናቸው። እናም እኔ የማምነው ኢትዮጵያ ይህን ያህል ዓመታት እነዚህን ተግባራት ለመፈጸም ስትሞክር ቆይታለች። እና ወደዚያ ኮርስ መመለስ አለባችሁ:: እናም ከክልላዊ ብሄርተኝነት ወጥታችሁ ሁሉም የጋራ ጥቅም ሆኖ ለሀገሩ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አንድ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያዊነት ዜግነት መንገድ መሄድ አለበት። የሚያስፈልገው ይህ ነው።
ዘኢትዮጵያን ሄራልድ፡- የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን የሚጠላ ቡድን እየደገፈ መሆኑን አብዛኛው አሜሪካዊ ያውቃል?
ሎረንስ ፍሪማን፡- በፖለቲካ ውስጥ ለ 50 ዓመታት ያህል ተካፍያለሁ፣ ግማሽ ክፍለ ዘመን ማለት ነው። ችግሩ አማካዩ አሜሪካዊ ዜጋ ራሱን ችሎ የማያስብ እና እኛን የሚያሳስቡን የዓለም ሁኔታዎች የሚያሳስቡት አይደለም።
አሜሪካን ላይ የነበረው የቀደመ ባህልና ራዕይ ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ውስጥ ቀንሷል። አሁን የመረጥናቸው ባለሥልጣኖቻችን ከሕዝባችን የተውጣጡ ናቸው፣ እና በአሜሪካን ውስጥ የመረጥናቸው ባለሥልጣኖቻችን በቂ መረጃ የላቸውም። ስለ አፍሪካ የሚያውቁት በጣም ጥቂት ነው።
ስለ ኢትዮጵያም ትንሽ ያውቃሉ። ሴኔተሮቹ እና የምክር ቤቱ ተወካዮች እንደ እኔ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ላይ ገለልተኛ የሆነ ዕውቀት ስለሌላቸው በጣም በቀላሉ ይገለበጣሉ። ለምሳሌ ሚዲያዎች ልክ እንደ ሲኤንኤን የአሜሪካንን እና የተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ውሳኔ እንዲያወጡ ማሳመን እና በሲኤንኤን የተደራጀ መረጃን መስጠት አስበውበት የተነሱት ነው::
ስለዚህ ሚዲያ ሁሉም የሚቀበለው የውጭ ፖሊሲ ሆኗል። ፀሐፊው ስቴት ብሊንከን የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማፅዳት እና የዘር ማጥፋት ወንጀልን ሲጠቅስ ለሰብዓዊ ርህራሄ ዋና ቃላቶች ሲሆኑ ያገኛቸው ከዜና ሚዲያ ዘገባዎች እንጂ መሬት ላይ ካለው መረጃ አይደለም። እና በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉት “የሰብዓዊ ቀውስ ጣልቃ ለመግባት” የሚለውን ጥያቄ ፣ R2Pን የመጠበቅ ኃላፊነት ይባላል፡፡
በጆርጅ ሶሮስ ኦፕን ሶሳይቲ እና በለንደን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር አንድ ላይ ተሰብስበዋል። በ 1990 ዎቹ መጨረሻ የአሜሪካ ጦር በኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ ሊገባ በሚችልበት ሁኔታ ላይ አሁን በመገናኛ ብዙኃን ላይ ውይይት ተደርጓል። አሁን ተንሳፈፈ። የኢትዮጵያ ህዝብ እየተሰቃየ ነው ሲሉ ጣልቃ መግባት አለብን አሉ። ያ ምክንያት ይሆናል።
እናም በዚህ ሆን ተብሎ የተሳሳቱ መረጃዎችን የማታለል ዘመቻ ሰዎች እያደረጉ ነው። እናም የአሜሪካ ዜጋ እና የአሜሪካ ኮንግረስ በትክክል እየሆነ ስላለው ነገር አያውቁም። ከመገናኛ ብዙኃን በሚመጣ የቡድን አስተሳሰብ ብቻ ይሳባሉ። ሚዲያው ዓላማ የለውም። ለእውነት ፍላጎት የላቸውም። በዚህ ፖሊሲ ወደፊት እንዲራመዱ ሰዎችን ለማሳመን የ ኦሊጋርኪ ክንድ አካል ናቸው። ትልቅ መጠን ያለው የባይደን አስተዳደር ክፍል ለጂኦ – ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ቁርጠኛ ነው።
ስለ ኢትዮጵያዊያን ደኅንነት ፍላጎት የላቸውም። እነሱ ቢሆኑ ኖሮ ላለፉት 30 ዓመታት ራሳቸውን ለልማት አሳልፈው ይሰጡ ነበር። በጣም ከባድ ነው፣ አፍሪካውያን ይህንን ሊረዱት ይገባል። ነገር ግን ሀገሬ አፍሪካን ለማሳደግ፣ የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ቁርጠኝነት የላትም። በተቃራኒው ቻይናውያን የአፍሪካ አገራት እንዲያድጉ ራሳቸውን እንዲችሉ ጥረት እያደረጉ ነው። ነገር ግን አሜሪካን ይህንን አላደረገችም::
ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ምንም ሚና አልነበራትም፡፡ ምናልባትም በ 1960ዎቹ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከሞቱ በኋላ ለአፍሪካ ልማት እራሳችንን አልሰጠንም ተብሎ ነበር። እንደ የጂኦፖለቲካዊ አስተሳሰብ አካል ስለ ልማት አይጨነቁም፡፡ ልማት ቢያሳስባቸው ኖሮ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 6 ሺ 200 ሜጋ ዋት የሚያመርት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን ልማት በማሳየቱ አዎንታዊ ሙገሳን በሰጡ ነበር።
ለዚያ ተግባር መንግሥትን አለማሞገሳቸውና አለማመስገናቸው የልማት ፍላጎት እንደሌላቸው ማሳያ ነው። በአፍሪካ ቀንድ ያለው አቅም ትልቅ ነው። ሱዳን ውስጥ የተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶችን በማጥናት ብዙ ዓመታትን አሳልፌያለሁ፣ ሱዳን ከመበታተኗ በፊት በአህጉሪቱ ካሉት ሁሉ ያልታረሰ ሰፊ የእርሻ ቦታ ነበራት።
በትክክል ያ መሬት ለልማት ውሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሱዳን መላውን አህጉር መመገብ ትችል ነበር። ነገር ግን ይህንን ማድረግ አልተቻለም። አሜሪካንም ሱዳን በዚህ መሬቷ ላይ እንድትለማ ፍላጎት አልነበራትም። በተመሳሳይ አሜሪካ ኢትዮጵያን የማልማት ዓላማ የላትም። ስለዚህ ሌሎች አጋሮችን መፈለግ አለባችሁ:: ለምሳሌ ቻይና ለኢኮኖሚ ልማት አስተማማኝ አጋር አገር ናት፣ ሌሎች አገሮች ወይም አጋሮች፣ የአፍሪካ አገሮችም ቢሆኑ አንድ ላይ መሰባሰብና መሥራት አለባችሁ።
እዚህ ላይ ግን ኢትዮጵያ ራሷን ከአሜሪካ አስተዳደር እንድታርቅ እየጠቆምኩ አይደለም። እኔ ከአሜሪካ የዘለለ ህይወት እንዳለ እየጠቆምኩ ነው፤ እና አዎንታዊ ግንኙነት ስንል ኢትዮጵያ በምዕራቡ ዓለም ጂኦፖለቲካል አስተሳሰብ ታግታ ልትኖር አይገባም እያልኩ ነው። ምዕራባውያን መርዳት ካልፈለጉ ወደፊት የምትሄድባቸውን ሌሎች መንገዶችን ታገኛላችሁ ነው ለማለት የፈለኩት።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ማድረግ ያለባችሁ የሚያስከትሉትን አደጋ ከስር ከስር እየተከታተላችሁ ለሁሉም ሰው በሚገባ መልኩ መግለጽና መምታት ያስፈልጋል። ስለዚህ እኛ የአፍሪካ አገሮች፣ ላቲን አሜሪካ፣ አፍሪካውያን አሜሪካውያን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሁሉም ማንቂያውን እየሰሙ መሆኑንም ማረጋገጥ አለባችሁ።
በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ የለም። ጣልቃ አትግቡ እና የአፍሪካ ሀገራት ችግሮቻቸውን በራሳቸው እዲፈቱ አትከልክሉ፤ ህጋዊ መንግሥትን እናስወግዳለን በማለት በተግባር የሚንቀሳቀስ ቡድንን ህጋዊ አታድርጉ ማለት ይገባል።
ዘኢትዮጵያን ሄራልድ፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
ሎረንስ ፍሪማን፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኀዳር 23 / 2014