መቃብር ባልገባም በለቅሶ በዋይታ እርግጥ ነው ሞቻለሁ የፈነዳሁ ለታ ይላል አሉ ስታሊን ገብረክርስቶስ የሰው ልክ የማያውቅ፤ ሰው የሠራውን ጀብድ ዓይቶና ሰምቶ ከማድነቅ ይልቅ በተቃራኒው ለመስማት በሚሰቀጥጥ መልኩ የሚያሽሟጥጠው ስታሊን ሽልማት አለኝ ብሏል::
አይ መፈንዳት! ይሔ ሰው በኋላ ለመፀፀት የማይመችበት ደረጃ ላይ ሳይደርስ አልቀረም:: በእርግጥ ይህ ሰው ገና ያልበሰለና በብዙ መልኩ ኋላቀር የሆነ አስተሳሰብ ያለው እንጭጭ በመሆኑ ስለሱ ማንሳቱ ብዙም ጠቃሚ ባይሆንም ነገሩ አስቂኝ ስለሆነ ነው ነገሩን ለማንሳት መፈለጌ:: አሁን አሁን ሰዎች ሲሰሙት የሚያፍሩበት እና የሚሸማቀቁበት ሰው መሆኑን አለማወቁ እየታየ ነው::
ያው አምሮብኛል ብሎ ይለፈልፋል:: ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ እንደሚባለው ስለእርሱ ምን እንደሚነገር የማያውቀው ስታሊን አደባባይ ወጥቶ የመሃይም ጥግ ላይ እንደሚገኝ እያሳየ ነው::
ጆሮውን የደፈነ እና አይኑን የጨፈነ፤ ደንቆሮ ስታሊን በእርግጥ በአደባባይ ሽልማት አለኝ ማለቱ አያስደንቅም:: ሚዲያም በዚህ ልክ መጫወቻ መሆኑ የሚያስገርም ነው:: ለዘመናት መጥፎ ጓደኞቹ የለመዱት ማታለያን ጉርሻ እያሉ በአስተሳሰብ ድሃ የሆኑ ሰዎች አገር ሲያስከዱ ለሚሰጡት የማታለያ ገንዘብ መጠሪያው ጉርሻ ነው::
ልዩነቱ በፊት በድብቅ ነበር፤ አሁን ግን በግልፅ አገሩን ለሚከዳ መደለያውን ጉርሻ እንሰጣለን እያሉ ነው:: የሕወሓት አመራሮች እና በትግራይ ሚዲያ ሃውስ (ቲ ኤም ኤች) ላይ ከአቅሙ በላይ በአማርኛ ይሁን በትግሬኛ በማይለይ አንደበት የሚለፈልፈው ስታሊን፤ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያሉበትን ለጠቆመ የትግራይ አመራሮች 10 ሚሊየን እንሸልማለን ብለዋል:: እኛ ደግሞ 11 ሚሊየን ብር እንሸልማለን::›› ሲል በአደባባይ ተሰምቷል:: በእውነት ይህን ሰው ሆኖ መገኘት ቀርቶ፤ የዚህ ሰው የቤተሰብ አካል መሆን ወይም ይህን ሰው ማወቅ እጅግ ያማል::
አሸማቃቂው ስታሊንን ጨምሮ ጉርሻ እንሰጣለን ባዮቹ የትግራይ ሕዝብ ጠላቶች ቀልባቸውን ሰብሰብ አድርገው ጉርሻውን ለሕዝባቸው በርሃብ እየተጎዳ ላለው ወገናቸው ቢሰጡት ጥሩ ነበር:: ጠቅላይ ሚኒስትሩማ በአደባባይ ያሉበት እየታየ ነው:: እንግዲህ ውጭ አገር ሆኖ በምድረ አሜሪካ ያለው ስታሊን ልብ ካለው ከቻለ እና ከደፈረ ወደ አገራቸው ገብተው እንደዘመቱት ኢትዮጵያውያን መሳሪያ አንስቶ አገራቸውን ከሚወጉ የምድር ጉዶች ጋር ተደምሮ ይምጣ::
ይህ ሁሉ መጊያጊያጥ ለመላላጥ ይባል አይደል:: ይህ ሁሉ ትዕቢት የሚተነፍስበት መንገድ አጭር ይሆን ነበር:: አቤት አቤት ግርማ ሞገስ፤ የስታሊን ግርማ ሞገስ ያስደንቃል:: እውነት የሃቅ ምግብ አጥግቦት ተደስቶ ተነፋፍቶ አምሮበት ይሆን እንዴ? በትግራይ ሚዲያ ሃውስ (ቲ ኤም ኤች) ላይ ተሽቀርቅሮ መቅረቡን ይቀጥል ይሆን? አይመስለኝም::
ነገሩ እንደፊኛ በአየር ተሞልተው የተነፉት የኢትዮጵያ ነቀርሶች ሲተነፍሱ ስታሊን ባለበት ምድር ላይ አካሉ ባይፈርስም መንፈሱ ይሞታል:: ስታሊን ተሸቀርቅሮ ከሚቀርብበት (ቲ ኤም ኤች) ላይ መሠወሩ አይቀርም:: ንፍቅ ያለን ስታሊን እና የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የነጮች ተላላኪ ሆነው እያገለገሉ ያሉት ሰዎች በአካልም በመንፈስም የሚፈርሱበት ጊዜ ብቻ ነው::
ነገሩ አሁን መቀመቅ የመውረጃቸው ጊዜ ቀረብ ብሏል:: ከስታሊን በተጨማሪ ክህደት ለሚፈፅም አገሩን አሳልፎ ለሚሰጥ መደለያ ማዘጋጀቱን በአደባባይ ሲለፍፍ አድናቂዎች መኖራቸው ደግሞ ያስቃል፤ ማሳቅ ብቻ አይደለም ያስደንቃል::
‹‹ወይ አለማፈር!›› ሰው እንዴት በአደባባይ አገር ለሚከዳ ሽልማት አዘጋጅቻለሁ ብሎ የሚለፍፍ ሰውን ያደንቃል? አድናቂ ነን ባዮቹ በአደባባይ መደገፋቸው ያስገርማል:: ሰው እንዲህ እንዴት ሊወርድ እንደሚችል ማሰብ በራሱ በጣም ይከብዳል:: ነገር ግን እነስታሊን ገብረሥላሴ እና አጠቃላይ የአስተሳሰቡ ደጋፊዎች ወርደው ተዋርደው እየታዩ ነው::
በተቃራኒው ትዕግስት ውቂያኖስን ያደርቃል እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን ለእነስታሊን ትዕግስታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ:: እነስታሊን ደግሞ በተቃራኒው የታገሰ ሕዝብ ላይ እያሾፉ መቀለዳቸውን አሁንም ቀጥለዋል::
አሁን እየተሸነፉ በሞት አፋፍ ላይ ሆነውም እነስታሊን ፍንድት ብለዋል:: በስተሽምግልና መፈንዳት እንዴት እንደሚያስጠላ ፍንዳታ ሽማግሌዎችን ያየ ያውቀዋል:: የመውጊያውን ብረት የረገጡት እነስታሊን መውጊያው ሳይሆን የሚጎዳው እነርሱ ተሰነጣጥቀው ፈርሰው ፈራርሰው ኢትዮጵያ ላይ እንዲደርስ የተመኙት ሁሉ በእነርሱ ሕይወት ላይ ደርሶ ወደ ሲኦል እንደሚንደረደሩ አልተጠራጠሩም::
ሰው ቢሆኑ እና ማሰብ ቢችሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉበትን ለጠቆመ የ11 ሚሊየን ብር ሽልማት ከሚያዘጋጁ የተራበውን የትግራይ ሕዝብ በደገፉ ነበር:: ነገሩ ስታሊንን ጨምሮ የሕወሓት አመራሮች ማሰቢያቸውን የተነጠቁት ከማደጋቸው በፊት በሕፃንነታቸው ነው:: ከዚህ አንፃር የትግራይ ሕዝብ እየተራበ ዐቢይ የዘመተበትን አቅጣጫ ለጠቆመ እንሸልማለን ማለታቸው አያስደንቅም:: ነገሩ እፉኝት የእፉኝት ልጅ ሃሳቡ የተለየ ነው:: እፉኚት የተሰኘው እባብ በቀላሉ አይሞትም አሉ::ክፉ እና መርዛማ እባብ በመሆኑ ለመንደፍ ምክንያት የለውም::
ዓላማው ማንንም መርዞ መግደል ብቻ ነው:: እንደነእስታሊን እና እንደሕወሓት አመራሮች ማለት ነው:: እፉኚት ከመሞቱ በፊት ብዙ ይሰቃያል:: የእነስታሊን ነገርም ተመሳሳይ ነው:: ዓላማቸው መግደል እና ማውደም ብቻ ነው:: አሟሟታቸውም ቀላል አይሆንም:: ግፍ ገፍቶ የትኛው ጫፍ ላይ እንደሚያደርስ አይታወቅም::
ከልብ ሞልቶ የተረፈውን አፍ ይናገራል:: እንደሚባለው ልባቸው ውስጥ ያለው ጠቅላይ ሚኒስትሩን መግደል፤ ኢትዮጵያውያንን መጨረስ እና አገር ማፍረስ ነው:: ለነገሩ ስታሊን “እኔ በሕይወቴ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ቆሜ ከማየት በላይ የሚያስደስተኝ ነገር የለም” ብሎ የለ፤ ግን እንዳማረህ ይቀራል፤ ከዚህ ይልቅ አንተና መሰሎችህ በቁማችሁ ስትፈርሱ ቆመን እያየን ነው:: ስለዚህ ዘወትር በልባቸው ሞልቶ በአፋቸው ያለውን ይለፈልፋሉ::
ሕዝብን እንጨርሳልን፤ መሪውን ገድለን አገር እናፈርሳለን ይላሉ:: ወይ አገር ማፍረስ! ነገሩ ለእነስታሊን ይህ አስተሳሰብ ትክክለኛ ሃሳብ ሆኖ ተገልጦላቸው ይሆን እንዴ? በእርግጠኝነት አገር ማፍረስ እና ሞራልን መሸጥ ልማዳቸው በመሆኑ ለሌላው ትክክል የሆነው ለእነርሱ ስህተት ለሌላው ስህተት የሆነው ደግሞ ለእነርሱ ትክክል ሳይሆን አይቀርም::
ኢትዮጵያውያን ከሃይለኛ ይሻላል ትዕግስተኛ ብለው ታግሰው እንጂ ካለማስተዋል ሃይልን መጠቀም ብቻ አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ የትህነግ ሃይሎች በየትኛውም ግንባር ሃይል ተጠቅመው አሸንፈው አንዲት ስንዝር ባልተራመዱ ነበር:: አስተዋዩ ሕዝብ መንግሥት እንደታገሰው እርሱም ታግሶ ትዕዛዝ ተቀብሎ እንደፈለጉ እንዲፋንኑ ባይፈቅድላቸው ኖሮ እነስታሊንም የሚለፈልፉበትን ዕድል አያገኙም ነበር:: ነገሩ እነርሱ የሚሉትን አያጡም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ነው::
በሥራ የተገኘ ትንሹ ይበቃል ብሎ የሚያምን ሕዝብ ነው:: በእርግጥ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው አልፎ አልፎ በጉርሻ የሚታለል ሰነፍ አይጠፋም:: ቀድሞ የደርጋዊ ሥርዓት መንግሥት አገዛዝ በነበረበት ዘመን ባለማወቅ አንዳንዱ ደግሞ አውቆ በጉርሻ ተታሎ የአገሩን ጦር አሳልፎ ለሕወሓት ሰጥቶ ነበር:: አሁን ግን ይህ በፍፁም ሊሆን አይችልም:: አሳልፎ ለመስጠት ያሰበ ካለ ነቅቶ የሚከታተለው እልፍ በመሆኑ ሳያስብ ከጀርባ ይደፋል:: የማታለያ ጉርሻው ሕልም ይሆንበታል::
ስለዚህ አሳሳቾቹ እነስታሊን የምታገኙት ምንም ነገር የሌለ በመሆኑ አትድከሙ:: ለነገሩ እነስታሊን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉበትን ለጠቆመ በደንብ አድርገን ሽልማቱን እናበረክታለን ቢሉም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሱ በአደባባይ በአገሪቱ ቴሌቪዥን የት እንዳለ እያሳየ ነው:: ስታሊን እንዳለው ትህነጎች እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩን መማረክ አሁን ተራ ወታደር መማረክ የሚችሉበት ሰዓት አይደለም::
የስታሊን አስተሳሰብ አፍቃሪዎች ለርካሽ ዓላማ የተሰለፉ ምስኪን ዘማቾች አሁን ራሳቸው እጃቸውን እየሰጡ ነው:: በየግንባሩ ሁሉም ተከበዋል:: መውጫ አጥተው እየተፍጨረጨሩ እየተንፈራፈሩ ነው:: ስለዚህ ስታሊን ከዛሬ ጀምሮ ማሰብ ከጀመረ ወገኖቹን ይምከር:: የፍፃሜው ዘመን መሲሆች! በትግራይ ሚዲያ ሃውስ (ቲ ኤም ኤች) ላይ ብቅ ያለው ሰው መሳይ ሰይጣኑ ስታሊን ከአፉ የሚወጡት ቃላቶች ሲሰሙ ብረት ሲፋፋቅ የሚሰማ አይነት የመሰቅጠጥ ስሜት በመላ ሰውነት የሚረጭ ቢሆንም ስታሊን ብቻ ሳይሆን የትግራይ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮም አሁን ላይ ብዙዎች የበለጠ ከማለቃቸው በፊት ‹‹የትግራይ ሠራዊት ከአሁን በኋላ እጅ ስጥ እና ራስህን አድን›› ቢሏቸው መልካም ነበር::
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ነን ባዮች እነሸኔም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በመደረሱ ቢዘገይም አሁንም በፍጥነት ነቅተው እጃቸውን ሰጥተው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁ ቢመከሩ ይሻላል:: ለነገሩ ከስታሊን መልካም ነገር አይጠበቅም:: እንደው መላ የሚለው ቢያገኝ ጥሩ ነበር:: ባልሆነ በሆነው አፍንጫውን አሹሎ ስስ ከንፈሩን አሞጥሙጦ የመንደር ሥራ ከሚሠራ ሰው የሠራውን አይቶ ቢያደንቅ ይሻል ነበር::
ይልቅ በተቃራኒው በማሽሟጠጥ ከሚጠመድ በተቃራኒው ወገኖቹን አሁን ይበቃናል ቢላቸው መልካም ነበር:: አሁን የኢትዮጵያ ጠላቶች እስከ ወዲያኛው የሚገረሰሱበት ጊዜ ደርሷል:: አሜሪካ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅማ የኢትዮጵያን መንግሥት ለማዳከም ብትታትርም፤ ልሒቃን ነን ባዮቹ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅና ጭፍሮቹ ጠላት ኢትዮጵያን እንዲያፈርስ ለማገዝ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ዲፕሎማቶች ጋር መንግሥት ለመሆን ቢዶልቱም አሁን ተስፋቸው ጨልሟል::
ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ መንግሥት ሆኖ የሚመራውም ሕዝቡ የመረጠው ብቻ እንደሚሆን አያጠያይቅም:: ክፉ ሰባኪዎች አሁን ላይ ካለፈው ድርጊታቸው ታርመው ወደ ትክክለኛው መንገድ ቢመጡ መልካም ነው:: እርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን ብዙ ተበድለናል:: ነገር ግን ቢያንስ አሁን ቢያንስ ዛሬ ቢበቃ ይሻላል:: በየማህበራዊ ሚዲያው የሚለፈልፈውም ሆነ በተለያየ መልኩ በሴራ የተጠመደው ዛሬ ላይ ከዚህ ተግባሩ መታቀብ አለበት::
በተቃራኒው ወገኑን ለማዳን ለመምከር እና እውነቱን ለመንገር ከሞከረ የሕሊና ኪሳራ ቢያጋጥመውም ቢያንስ በሕይወት ለመቆየት ይታደላል:: ስለዚህ እነትህነግ ዛሬ ከእንቅልፋቸው ባንነው ወደ እውነተኛው ሕዝብን ሁሉ ወደሚያስማማው የሠላም መንገድ መምጣት አለባቸው:: አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለበትን ለጠቆመ 11 ሚሊየን ብር እንሰጣለን ከሚለው ከንቱ ቅዠት ይልቅ መንግሥት የሰጣቸውን እድል ተጠቅመው ተከታዮቻቸው ከእልቂት የሚድኑበትን መንገድ ቢከተሉ የተሻለ ነው:: በራሳቸው በኩል ምን ያህል እየተዳከሙ ሕዝባቸውም እያለቀ መሆኑን አጋልጠው ሁሉም እጁን እንዲሰጥ ቢያበረታቱ መልካም ነው::
በስታሊን የበሬ ወለደ ዜና እና በዘግናኝ የማሽሟጠጥ ሥራ መሳቀቅ እና አንገት ደፍቶ አንዳንዴም ባላዋቂነቱ መሳቅ ይብቃ! ያለበለዚያ ያው እውነት ለእውነተኞች ታደላለች፤ የግፍ ፅዋ ሞልቷል እና መፀፀት ካልተቻለ መትረፍ አይታሰብም:: ከአንድ አመት በፊት በእብሪት በትእቢት እስከ አሁን የቀጠለው ጥጋብ ዞሮ መውረድ ቢጀምርም ቆይቶ ወደ ጥልቅ ጉድጓድ መቀመቅ መግባቱ አይቀርም:: የዛን ጊዜ አሁን በስታሊን ንግግር ብንሸማቀቅም፤ የትህነግ ተዋጊዎች ግፍ ቢያንገፈግፈንም በወደቀ ሬሳ ላይ እየተሳለቅን ራሳችንን አናዋርድም::
ለጊዜው አሁንም ካልገባው እስከሚገባው ለስታሊን ቂቂቂ እያለ እያላገጠ እንዲቆይ ፈቅደንለታል:: እኛ ግን የእርሱን ብልግና አንደግመውም:: እንደስታሊን በስሜት ጨለማ ውስጥ የባዘንን ማንነታችንን አናረክሰውም፤ እኛ የሚታየን ብርሃን ነው:: የምንራመደው አይተን እና ተጠንቅቀን ነው:: እንደእነስታሊን የታሪክ አተላ አንሆንም:: የግፋቸው ጥግ ትከሻችንን አጉብጦ ለማስኬድ ቢያስገድደንም ከጉልበታችን ሸብረክ ሳንል ያሰብነውን መፈፀማችን አይቀርም::
ብዙ በመታገስ ቢዘገይም የሚሉት የማያጡት እነስታሊንን አሁን እያስደነገጥናቸው ነው:: ድንጋጤያቸው ይቀጥላል:: ማሽሟጠጣቸው ይቀንሳል:: ምናልባት አንድ ቀን የኢትዮጵያ እውነት ገብቷቸው እነርሱም የሚመለሱበት ቀን ይመጣል:: ያው ተስፋ ላለመቁረጥ ይህንን ብለን አብቅተናል:: ሠላም፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ኀዳር 23 / 2014