ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት ለመቀልበስ የመጨረሻ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች:: ለዚህ ደግሞ ከመሪዋ ጀምሮ ወደግንባር በመዝመት ጦርነቱን በድል ለመፈፀም ከጫፍ ደርሳለች::
በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ወደግንባር መዝመት ተከትሎ መላ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር በመነቃነቅ የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳዩ ነው:: ለዚህም ከሰሞኑ የተገኙ ድሎች ቡድኑ የመጨረሻ መቀበሪያው ወቅት ላይ መደረሱን አመላካች ናቸው።
እኔ ከሞትክ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ትፍረስ በሚል ቡድኑ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን የዘመናት ምኞት እውን ለማድረግ በሕዝብና በአገር ላይ ጦርነት አውጇል።
ከመንግሥትነት ወደ ተራ አሸባሪነት በመቀየርም ኢትዮጵያዊ ባልሆነ መንገድ ለአገር በታሪክ ያልታየ ባንዳ ሆኗል። በአሜሪካ እና ግብረ አበሮቿ ድጋፍ ከተንቤን በበረሃ ተንፏቆ ሰሜን ሸዋ የደረሰው አሸባሪው ትህነግ አሁን አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ ነው። አብዛኛው ሠራዊቱ ምትና ቁስለኛ እየሆነ፤ ብዛት ያለውም ነፍሱን ለማትረፍ መሳሪያውን አስቀምጦ እጁን ከፍ እያደረገ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰሞኑን ከግንባር ባስተላለፉት መልእክት፤ “በአጠረ ጊዜና በአነስተኛ መሥዋዕትነት የኢትዮጵያ ድል ይረጋገጣል” ሲሉ የድሉን ግስጋሴ የሚገታ አለመሆኑን አረጋግጠዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መውረድን ተከትሎ በተከታታይ እየተመዘገቡ የሚገኙት ተከታታይ ድሎች ለመላ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የሞራል እና የአሸናፊነት ወኔን አላብሰዋል። በጠላት መንደርም ከፍተኛ መረበሽና መደናገጥን መፍጠሩ በግልጽ እየታየ ነው::
በተለይ አሸባሪውን ሕወሓት ከፊት በማሰለፍ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፍተኛ ሁኔታ ሲሯሯጡ የነበሩት አሜሪካና ሸሪኮቿ የሰሞኑ የኢትዮጵያውያን አስፈሪ ምት በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጧቸዋል:: የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መውረድ የድሉን ማርሽ የሚቀይር ስለመሆኑ ቀድመው ሳይረዱ የቀሩም አይመስልም።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ግንባር መግባት ተከትሎ ሲያሰሙት የነበረው ጫጫታ ይሄንኑ ከመፍራት የመነጨ እንደሚሆን ለማሰብ አይቸግርም። የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወደ ግንባር መዝመትን ለማጣጣል የመሞከራቸው ሚስጥርም ይኸው ስጋታቸው እንደነበረ ለመገመት የሚከብድ አይደለም። የምእራቡ ዓለም ዋና ዋና የሚባሉ የመገናኛ ብዙኃኖች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ግንባር መዝመት ለማሽሟጠጥ ማንም አልቀደማቸውም።
‘የሠላም ኖቤል ተሸላሚው ወደ ግንባር ዘመተ’ በሚል ስላቅ በተሞላበት መልኩ የዜና ማጠንጠኛቸው ሲያደርጉ በጤናቸው አልነበረም። የዘነጉት ነገር የእኛ መሪ ሠላም ይወዳል፤ ሠላምን ፍለጋ ጦርነትን ተጸይፎ እንደ ፈሪ ተፎክሮበታል፤ እንደ ደካማ ተቆጥሯል፡፡ ከሠላም ወዳድና ከታጋሽ ሕዝብ መሪ የሚጠበቀውን አድርጓል፡፡
እንደ ቀደሙት የኢትዮጵያ መሪዎች ዶክተር ዐቢይ ከጦርነት ይልቅ ሠላምን ፍለጋ ብዙ መንገድ ሄዷል፡፡ በእርግጥ የሠላም ኖቤል መሸለም አገር አደጋ ውስጥ ስትገባ፤ የአገርህን ጥቅም የሚነካ ነገር ሲመጣ “ሠላማዊ” እንድትባል እጅህን አጣጥፈህ ቁጭ ማለትን የሚጠይቅ አይደለም። ከሆነ ስለ ሠላም ያለን አስተሳሰብ ሙሉ ያልሆነና ሰለ ሠላም የሚከፈል መስዋእትነትን የዘነጋ ነው።
የሠላም ኖቬል ሽልማቱ እንደ ጎርቫቾቭ እየተሞገስክ ታላቅ አገርህ ስትፈራርስ ተቀመጥ የሚል መመሪያ በውስጡ የተሸከመ ከሆነ ሽልማቱ ከጅምሮ ኢትዮጵያንና መሪዎቿዋን በአግባቡ ያለማወቅ ችግር ነበረበት ማለት ነው። ይህ እንደማይሆን አምናለሁ፤ በሸላሚዎቹም ከፍ ያለ መተማመን አለኝ።
ስለ ኢትዮጵያ ጨለምተኛ የሆኑ የምእራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃኖች በያዙት ጥቁር የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መሪዋ ሳይቀር ዘምቶ ዋጋ ከፍሎ አገርን ለማስቀጠል እየተደረገ ያለውን ተጋድሎ ማሳነስ መርጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አገር ለማቆየት የሚደረገውን የሕልውና ትግል መቀላቀላቸው ጥፋት አድርገው ለማሳየት ሞክረዋል።
በአገር አፍራሾች ፊት ስህተት የመሰለው የጠቅላይ ሚኒስቴሩ መዝመት ግን በሚመሩት ሕዝብ እና በሕዝቡ ታሪክ ፊት ትልቅ ክብር ተችሮታል። የዶክተር ዐቢይ ውሳኔ የኢትዮጵውያን መሪዎች የቆየ ፤ ዛሬ በአዲስ መንፈስ እየታደሰ ያለ አገራዊ እውነታ ስለመሆኑ ያለማወቅ ችግር ነው። የኖቤል ተሸላሚ መሆን አገርን ለማፍረስ ጠላት ሲመጣ መመከት ይከለክላል ? ማለት ፍጹም ጅልነት ነው።
ያለ አዋቂ ሳሚ እንደሚባለው አይነት ነው። ለዚህ እውነት ለትችት ለፈጠኑት ምዕራባዊያን አንዳንድ ነገር ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛል ። እ.አ.አ 2011 የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚደንት ኦባማ የሠላም ኖቤል ሽልማት ወስደዋል።
ኦባማ በሽልማት ሥነ[1]ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ “የዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ የሕይወት ትግል ቀጥተኛ ውጤት ሆኖ ከፊታችሁ እንደ ቆመ ሰው፣ አመጽ የማያጣቅስ ሠላማዊ ንቅናቄ ስላለው የሞራል ጉልበት ሕያው ምስክር ነኝ። በጋንዲና በኪንግ እምነት ውስጥ ደካማነት፣ መፋዘዝም ሆነ ነሆለልነት እንደሌለ አውቃለሁ።
“ነገር ግን አገሩን ለመጠበቅና ለመከላከል ቃለ-መሃላ እንደፈጸመ የአገር መሪ፣ በእነሱ [ኪንግና ጋንዲ] ተምሳሌት ብቻ ልመራ አልችልም። ዓለምን የምጋፈጣት እንደ አመጣጧ ነው፣ እናም በአሜሪካ ሕዝብ ላይ አደጋ ተደቅኖ እያየሁ እጄን አጣጥፌ ልቀመጥ አልችልም። በፍጹም እንዳትስቱ ፥ ክፋት በዓለም ላይ አለ።
“አመጽ የማያጣቅስ ሠላማዊ ንቅናቄ የሂትለርን ጦር ሊገታው አይችልም ነበር። ድርድር የአልቃኢዳ መሪዎች የጦር መሣሪያቸውን እንዲያወርዱ ሊያሳምናቸው አይችልም። የሃይል አማራጭ አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ነው ማለት ጨለምተኝነትን ማቀንቀን አይደለም፤ ይልቁንስ ለታሪክ፣ ለሰው ልጅ ኢ-ፍጹማዊነት፣ እንዲሁም ለምክንያታዊነት ውስንነቶች እውቅና መስጠት ነው”ብለዋል፡፡
የኖቤል ተሸላሚው ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ በ2011 ሊቢያን ሲወሩና በዘመናዊ ጦር ሲደበድቡ በወቅቱም ከልካይም ሆነ ገላማጭ አልነበረም። ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት ለመምራት እና አገርን አድኖ ሠላም ለማምጣት መዝመቱ ምኑ ጋር ይሆን ወንጀሉ ? እንጃ ። የምዕራባዊያኑ አሸማቃቂ ዘገባ ብሎም፣ የአሜሪካን ዛቻ ጆሮ ያልሰጡት ዶክተር ዐቢይ ፤ ወደ ግንባር መዝመት ተከትሎ የድሉ ማርሽ ሲቀየር ታዝበናል።
የአሜሪካ እና ግብረ አበሮቿ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የመዝመት መረጃ እንደተሰማ ግራ በሚያጋባ መልኩ ለምን ጫጫታ እንዳሰሙ ግልጽ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት በኢትዮጵያ ላይ በሚጋልቡት የሽብር ፈረስ የከፈቱብን የውክልና ጦርነት በሽንፈት እና በውርደት የሚጠናቀቅበትን ጊዜ ያሳጥረዋል። በዚህም የሚጋልቡት ሽብርተኛው ፈረስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቅበር የሚያስችል መነሳሳት ፈጥሯል፤ በተጨባጭም እየታየ ያለው ይሄው ነው።
የኖቤል ተሸላሚ መሆን የአገር ሉዓላዊነትን ሲደፈር መሪ ቆሞ ማየት እንደሌለበት የኦባማ ተሞክሮ በቂ ማሳያ ነው። ይህ አይነቱ ተግባር በኢትዮጵያ ሲሆን እንደ ጥፋት የታየበት መነጽር ነውር ነው – ዓለም አቀፍ ነውር። እዚህ ጋር “ጦርነት ወደ ሠላም መሸጋገሪያ አንድ መንገድ ነው” የምትለውን ጣፋጭ አባባል በማስተዋል፤ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ መዝመት የመጨረሻው ግብ ሠላም ማስፈን እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል እላለሁ። እንዲህ አይነቱ ክስተት ደግሞ ለኢትዮጵያዊያን የቆየ ባህልና የመሪዎቿ የአገር ፍቅር ጽናት ማሳያ ነው።
እንዲህ አይነቱ ክስተት ደግሞ ለኢትዮጵያዊያን የቆየ ባህልና የመሪዎቿ የአገር ፍቅር ጽናት ማሳያ ነው።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ኀዳር 23 / 2014