
ግብር የሀገር ምሶሶ ነው። ስንዴ ሰጥተን ፍላጎታችንን እንጫንባችሁ ለሚሉን ሀገራት መልስ መስጫ ቁልፍ ከዜጎች ግብር መሰብሰብ ነው። ሀገር በኢኮኖሚ አድጋ ዜጎች ከተለያዩ አማራጮች የሚያገኙትን ገቢ በታማኝነት ለሀገራቸው ሲገብሩ፤ ከተጽእኖ ተላቃ ሌሎች ላይ ተጽእኖ የምታደርስ ሀገር ዜጎች ለመሆን የበኩላቸውን ጡብ እያዋጡ ነው። አለፍ ሲልም በየስብሰባ መድረኩና በግሩፕ ውይይቶች የሚነሱ የመንገድ ይሠራልን፣ የጤና ተቋማት ይስፋፉልንና መሰል ጥያቄዎችን መመለስ ያስችላል።
በሀራችን የገቢ ግብር አሰባሰብ ለረዥም ጊዜ ሥርዓት ተዘርግቶለት ሲተገበር የቆየ ቢሆንም በዋናነት ደሞዝተኛው ላይ ያተኮረ የገቢ አሰባሰብ ሂደት ነበር። ይህንን ለመቀየር ያሰበና ሀገሪቷ የምትሰበስበውን የገቢ መጠን የሚጨምር የመካከለኛ ዘመን የገቢ ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ በዘርፉ ለውጥ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ከ2017 እስከ 2020 ዓ.ም ተግባራዊ በሚደረገው ስትራቴጂ ከዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ከግብርና ቀረጥ የሚገኘውን የገቢ ድርሻ በየዓመቱ በአንድ በመቶኛ ለማሳደግ ታስቧል። እንዲሁም በስትራቴጂው የማጠናቀቂያ ዘመን ከዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ከሚገኘው ገቢ ከግብርና ቀረጥ የሚገኘውን ገቢ ድርሻ ወደ 11 በመቶ ከፍ ለማድረግ ታስቧል።
የታቀደው እቅድ ከወጣ ከዘጠኝ ዓመት በላይ ባስቆጠረው የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ማስፈጸም እንደማይቻል ግልጽ ነው። በዋናነት የመንግሥትን ገቢ ለማሻሻልና የታክስን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችልና በየደረጃው በርካታ ምክክሮች የተደረጉበት አዲስ አዋጅ ተዘጋጅቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።
አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ሰባት ዓላማዎች ያሉት ሲሆን ለዛሬ ጽሁፋችን የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ዋነኛ ዓላማዎች ናቸው ብሎ የለያቸውን ሁለት ዓላማዎች እንቃኛለን። እነሱም ዝቅተኛ ገቢ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል የሚያርፍበትን የግብር ጫና መቀነስና የግብር መሠረትን ማስፋት ናቸው።
አዲስ በጸደቀው አዋጅ ምንም እንኳን አነስተኛ ቢሆንም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያለው የግብር ጫና እንዲቀንስ ተደርጓል። ሥራ ላይ በነበረው አዋጅ ከግብር ነጻ ይደረግ የነበረው ደሞዝተኛ እስከ 600 ብር የነበረ ሲሆን፤ ከ601 ብር እስከ 1650 ብር የሚከፈላቸው ዜጎች የገቢያቸውን 10 በመቶ ግብር ይከፍሉ ነበር። በአዲሱ አዋጅ እስከ ሁለት ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ የሚያገኙ ዜጎች ከግብር ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ሆኖም የግብር መነሻ የነበረው 10 በመቶ ጠፍቶ የገቢ ግብር የሚጀምረው ከ15 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል። በአንጻራዊነት የነበረው በርካታ የግብር እርከን ቢቀጥል ለደሞዝተኛው የተሻለ ይሆን ነበር። የገቢ ግብር ጣሪያው አሁንም 35 በመቶ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ነገር ግን በተቀየረው አዋጅ ከ 10,900 ብር በላይ ወርሃዊ ደሞዝ የሚያገኝ ዜጋ የደሞዙን 35 በመቶ ይቆረጥበት ነበር። አሁን በተሻሻለው አሠራር ይህ ከ 14 ሺህ ብር በላይ በሚያገኙ ዜጎች ላይ ወደመፈጸም ተቀይሯል። በመሆኑም በአዲሱ አዋጅ የተደነገጉ ድንጋጌዎች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የሕረተሰብ ክፍሎች የግብር ጫናን በተወሰነ መልኩም ቢሆን መቀነስ ያስችላሉ።
አዋጁን ማሻሻል ካስፈለገበት ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ ተብሎ የተለየው የግብር መሠረትን ማስፋት ነው። በሀገራችን በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችም ሆነ ሰዎች ኑሮን ለማሸነፍ በሚያደርጉት መፍጨርጨሮች የገቢ አይነቶች እየበዙ ነው። ያም ቢሆን አብዛኛው የገቢ ግብር ይቆረጥ የነበረው ከደሞዝተኛው ነው። ይህም በሀገራችን የአብዛኛው ተቀጣሪ ደሞዝ ከእጅ ወደአፍ ቢሆንም ግብር የሀገር ዋልታ ነውና ሲቆረጥበት ቆይቷል።
በተቃራኒው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለማችን በርካታ ተጠቃሚ እያገኙ ያሉት የማህበራዊ ሚዲያዎች አዲስ የገቢ አማራጭ እየሆኑ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ለሚያዘጋጁ ድርጅቶች የማህበራዊ ሚዲያዎቹ ክፍያ የሚፈጽሙበት ሁኔታ አለ። ከዚህ ውጭም ከተመልካች ስጦታ የሚያገኙበት ሁኔታ አለ። በዚህ አይነት ሁኔታም በርካታ ሠዎች ከተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ ተከታዮቻቸው በሚጎርፍላቸው ስጦታ በአንዴ ወደ ሚሊየነርነት ተርታ ሲሸጋገሩ ታዝበናል።
በእዚህ ሂደት የተመልካችን ስጦታ ለማግኘት በርካቶች ስድድብን አማራጭ አድርገው አዳዲስ ስድቦችን እየፈበረኩ ሲሳደቡ ማየት የሀገራችን የማህበራዊ ሚዲያ አሳዛኝ እውነታ ከሆነ ቆይቷል። በእዚህ ሂደት በርካታ የውሸት መረጃዎችና የሥም ማጥፋቶች ቢኖሩም በሽልማት ከሚያገኙት ረብጣ ብርና የማህበራዊ ሚዲያዎቹ ከሚፈጽሙላቸው ክፍያ በተጨማሪ ከማስታወቂያ ከፍተኛ ክፍያ እያገኙ ነው። በዚህም በርካታ ታዳጊዎች የገዙትን ቤትና መኪና እያሳዩ ኑሮ አልሞላ ብሎት ለሚዳክረው ደሞዝተኛ እንቁልልጭ ሲሉት ቆይተዋል።
ታዲያ ተገላቢጦሹ እዚህ ጋር ነው። ደሞዝተኛው ምንም እንኳን አገልጋይ፣ ለረዥም ሰዓት የሚሠራና የሚደክም ቢሆንም የሚያገኘው ገቢ አነስተኛ ነው። ሆኖም ሀገር ያለዜጎች አስተዋጽኦ አታድግምና ካገኛት ብር ላይ ለሀገሩ የድርሻውን እያበረከተ ቆይቷል። በተቃራኒው በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ከሽልማት፣ ከማስታወቂያ፣ ከሚዲያው ክፍያ ከሚያገኙት አለፍ ሲልም የብራንድ አምባሳደር ወደ መሆንና በዚህም ከፍተኛ ክፍያ ወደማግኘት ተሸጋግረዋል።
የዜጎች በተለያዩ አማራጮች ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚያስደስት ነገር ነው። ሆኖም ሁሉም ዜጋ መብቱን እንደሚጠይቀው ሁሉ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል። ነገር ግን ከዚህ ቀደም የነበረው የገቢ ግብር አዋጅ ከዲጅታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢን ታሳቢ ያደረገ አልነበረም። አዲስ በጸደቀው አዋጅ ግን ይህንን ክፍተት የሚሞላና ግብር የሚሰበሰብበትን አድማስ የሚያሰፋ ነው። በዚህም የዲጅታል ገቢ ፈጠራ ከዩቲዩብ፣ ከማህበራዊ ሚዲያ፣ በኢንተርኔት ከሚሰራጭ መረጃ (ፖድካስቲንግ) በኢንተርኔት ከሚፈጸም ግብይት፣ ከስፖንሰርሽፕና ከመሳሰሉት የሚገኝ ገቢ ላይ ግብር መሰብሰብ ያስችላል።
የዲጅታል ሥራው በመደበኛነት የሚከናወን ከሆነ የሚገኘው ገቢ በንግድ ሥራ ገቢ ስር የሚያርፍ በመሆኑ የንግድ ሥራ ገቢ ግብር ይከፈልበታል። ሥራው በንግድ ሥራ ገቢ ስር ለመቆጠር የማያስችል ከሆነ ሌሎች ገቢዎች በሚለው ምድብ ተካቶ ከጠቅላላ ገቢው ላይ 15 በመቶ ግብር የሚከፈልበት አሠራር ተቀምጧል። ይህንን ለመቆጣጠር ያስችል ዘንድም ለዲጅታል ይዘት አመንጪዎች ክፍያ የሚያመቻቹ ለዲጅታል ይዘት አመንጪ የከፈሉትን ገንዘብ የሚያሳይ ሪፖርት ለታክሱ ባለስልጣን የመላክ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ይህ አዋጅ ሲተገበር የግብር አድማሱ ስለሚሰፋ የታቀደውን ገቢ ማግኘት ያስችላል። ከዜጎች የሚሰበሰበው የገቢ ግብር መጠን በጨመረ ቁጥር የተጓደሉ የዜጎች ፍላጎትን ለማሟላት መንግሥት አንድ ርምጃ ወደ ፊት መራመድ ያስችለዋል። በሂደት አሁን አነስተኛ ተብሎ የተቀመጠውን የመንግሥት ደሞዝተኛን ደሞዝ ወደማሻሻልና መሰል ጉዳዮች ለመግባት ከግብር በቂ ብር መሰብሰብ ይገባል።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ከትዝታ ማስታወሻ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም