ሕፃን ናሆም በልስቲ
ፍልቅልቅ ነው፤ ላየው ሁሉ የሚያጓጓ አስተዋይ:: አንዳንዴ የሚጠቀማቸው ቃላቶች ያስገርማሉ:: ከእናቱ እና ከቤተሰቡ እንዲሁም ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ያለው ግንኙነት አስደሳች ነው:: ሁሉም ይወደዋል:: አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅፅል ስም አውጥተውለታል:: የዘጠኝ ዓመቱ ናሆም በቃና ተከታታይ ፊልም እጅግ ተወዳጅ ሆኖ ከተሳለው የሕፃን ገፀባህሪ ከዶሩክ ጋር አመሳስለው በዚያው ሥም ይጠሩታል::
የአካባቢው ሰዎች ከዕድሜው በላይ ፍጥነቱ እና አስተዋይነቱ እያስገረማቸው ይሳሱለታል:: በተለይ እናቱ ናሆምን ስታይ እጅግ ትጓጓለች:: እርሱም በበኩሉ ገና በዘጠኝ ዓመቱ ስለእናቱ ያስባል:: ለእናቱ ያለው ፍቅር የተለየ ነው:: ስሞ አይጠግባትም:: እርሷ ናሆም ታመመ ከተባለ ትኩሳት ሲይዘው እንኳ ብርክ ይይዛታል:: አብዝታ ትሳሳለታለች፤ ትሰስተዋለች:: ያዘዘውን ሁሉ ታደርግለታለች:: ናሆም ጠይቆ አባቱ አቶ በልስቲም ሆነ እናቱ ወይዘሮ ወይንሸት ከበደ የሚከለክሉት ምንም ነገር የለም:: ነገሩ ናሆም (ዶሩክ) አስተዋይ በመሆኑ እንደሕፃን ደጋግሞ ጥያቄ አያበዛም::
የቤት ሠራተኛዋ
ወይዘሮ ወይንሸት ከበደ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች የሚወደደው የፋሲካ ፆምን በትጋት ለማከናወን ፈልጋለች:: ፆም ፀሎቷን እና ስግደቷን እንደመሻቷ ለመፈፀም አቅም ያስፈልጋታል:: ዓቅሟን በቤት ሥራ ላይ ካዋለች የፆሙን ጊዜ እንደፍላጎቷ ላያልፍ ነው:: የክርስትና እምነት ተከታይ ሆና ለዚያውም የዓብይ ፆምን በደንብ ከቤተሰብ ጋር እየፆመች እና እየፀለየች አለማሳለፍ ያስከፋል:: ስለዚህ እንደተለመደው የቤት ሠራተኛ ለመቅጠር አሰበች:: ቢያንስ የቤት ውስጥ ሥራውን ድካሟን የምትጋራላት የቤት ሠራተኛ በየትኛውም መንገድ ለማግኘት አቅዳለች::
በፆም ጊዜ ተባለ እንጂ ወትሮም ቢሆን ያለቤት ሠራተኛ ድጋፍ ለብቻ ለራሷ እና ለሦስት ልጆቿ እንዲሁም ለልጆቿ አባት የሚመገቡትን መሥራት፤ ዕቃ ማጠብ፣ ትልቅ ቤት እና ጊቢ ማፅዳት እጅግ ከባድ ነው:: ስለዚህ ድጋፍ ለማግኘት ‹‹የቤት ሠራተኛን መቅጠር የግድ ነው›› ብላ በቡራዩ ከታ ቢቂልቱ ጎጥ ከእነቤተሰቧ በአንድ ጊቢ የምትኖርዋ ወይንሸት ሰዎች ሠራተኛ በዘመድ እንዲያፈላልጉላት ብትጠይቅም ያገኘላት አልነበረም::
ፆሙም በመቃረቡ ድሮም ቢሆን በዘመድ ሲጠፋ በደላላ የቤት ሠራተኛ ወደምታገኝበት አዲሱ ገበያ አካባቢ አቀናች:: የካቲት 20 ቀን 2013 ዓ.ም በደላላው ቤት የተገኘችዋ ልጅ ቀልጣፋ የሥራ ልምድ ያላት ለወይዘሮ ወይንሸት የምትመች ዓይነት ነበረች:: እንደተለመደው የቤት ሠራተኛዋ ተያዥ አቀረበች:: የቤት ሠራተኛዋ እና ወይዘሮ ወይንሸት በውል ተስማሙ:: ወይዘሮ ወይንሸት አላመነታችም፣ ቀጥታ ወደ ቤቷ ይዛት ሔደች::
የቤት ሠራተኛዋ ከተቀጠረችበት ቀን ጀምሮ ጎልቶ የሚታይ መጥፎ ባሕሪ የላትም:: ነገር ግን በተደጋጋሚ በስልክ ታወራለች:: አንዳንዴ በተደጋጋሚ ስልክ ማውራቷ ሥራዋ ላይ ተፅዕኖ እስከመፍጠር ይደርሳል:: ወይዘሮ ወይንሸት ልጅቷን ‹‹ እባክሽ ስልክ ቀንሺ አንዳንዴ ሥራሽን እስከመርሳት እያደረሠሽ ነው::›› ትላታለች:: ወይዘሮዋ በልጅቷ የስልክ ጥሪ መብዛት ትንሽ ቅር ብትሰኝም ኃይለ ቃል አልተናገረችም:: ነገር ግን ካልሆነ ፆሙ ተጠናቆ በዓል ሲያልፍ ሌላ ሠራተኛ እፈልጋለሁ ብላ በውስጧ አስባለች:: ለጊዜው ‹‹ማሚ›› እያለች እየተለማመጠች የምትኖረዋ ሠራተኛ እንዳይከፋት በሚል ምንም ሳትባል ኑሮዋን ቀጠለች:: ቀን ቀንን እየወለደ ሔደ::
ጥቁሩ ቀን
ፆሙ እየተገባደደ ሰሞነ ሕማማት ሊጀመር በመሆኑ ለፋሲካ በዓል የሚሆን በግ በየቤቱ ይጮሃል:: ናሆም (ዶሩክ) ከሆሳዕና በፊት በዕለተ ቅዳሜ ጎረቤት በግ ተገዝቶ ስላየ ለወላጆቹ በግ እንዲገዛለት ጥያቄ አቀረበ:: የተሰጠው መልስ ደስታው ወደር እንዲያጣ አደረገው:: ‹‹ፋሲካ እስከሚደርስ መጠበቅ አለብህ›› አለመባሉ እጅግ አስፈነጠዘው:: ወላጆቹ አብዝተው ይወዱታልና ከበዓሉ ቀደም ቢልም ናሆም ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በግ ገዙ:: አንዳንዴ ነገረ ሥራው እንዳዋቂ፤ መልሶ ሕፃን ነውና እንደሕፃን ይሆናል:: በጉን ከጊቢ ውጪ ይዞ እየወጣ ሣር ያበላል፤ ለበጉ ውሃ ያጠጣዋል፤ አንዳንዴም ከበጉ ጋር ይላፋል::
ሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2013 ዓ.ም በሆሳዕና ማግስት ሰሞነ ህማማት ተጀምሯል:: ናሆም (ዶሩክ) ገና በዘጠኝ ዓመቱ የዐቢይ ፆም ይፆማል:: እስከ ስምንት ሰዓት ተኩል ሰግዶ ከቤተሰቦቹ ጋር ምሳውን በላ:: ዕለቱ ንፋስ የቀላቀለ ካፊያ ነበረው:: እናት ወይዘሮ ወይንሸት ግን አብራ ምሳ አልበላችም፤ ረዘም አድርጋ ፆማ እና ሰግዳ አመሻሽ ላይ ለመመገብ አስባለች::
ወይዘሮ ወይንሸት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ለመስገድ ስለፈለገች ወደ ቤተክርስቲያን ልትሔድ ተነሳች:: አባት አቶ በልስቲ ‹‹ነገ ትሔጃለሽ አሁን ቤት ሁኚ›› አሉ:: መለስ ብለው አባት አቶ በልስቲ ከቤት ፀጉራቸውን ለመስተካከል እና ለሌላም ጉዳይ መውጣት እንደሚፈልጉ ገለጹ:: ናሆም (ዶሩክ) እና ወይዘሮ ወይንሸት የቤቱን አባወራ ለመሸኘት ተነሱ:: ወይዘሮ ወይንሸት ከቤት ወጥታ አቶ በልስቲን መኪና ከፍታ ስትሸኝ ናሆም አባቱን ‹‹ቻዎ!›› እያለ ስልክ ይዞ ቪዲዮ ሲቀርፅ ነበር:: ናሆም አባት ወደ መኪና ሲገቡ በር ሲከፈት እና ሲወጡ ቪዲዮ ቀረፆ ይዟል::
ወይዘሮ ወይንሸት ወደ ፀሎት ቤት አቀናች:: ናሆም ግን ወላጆቹ አጥብቆ የፈለገውን በግ ገዝተውለታልና ከበጉ ጋር ለመጫወት ጓጉቷል:: ለእናቱ በጉን ውጪ አውጥቶ ሣር ለማብላት እንደሚፈልግ ተናገረ፤ ፍቃድ ጠየቀ:: ‹‹ካፊያ ስላለ ብርድ ይመታሃል፤ በኋላ ወደ ማታ አብረን ወጥተን ሣር ታበላለህ::›› አለችው:: ወይዘሮ ወይንሸት ይህን መልስ ሰጥታ ወደ ፀሎት ቤት ስትገባ፤ ናሆም በጊቢው ውስጥ መቦረቁን ቀጠለ::
ያቺን ሰዓት
ወይዘሮ ወይንሸት ፀሎት ቤት ሆና የሚንጓጓ ነገር ትሰማለች:: ፀሎት አቋርጣ ሠራተኛዋ ባኞ ቤት የወደቀች ስለመሰላት ‹‹ምንሆነሽ ነው?›› ብላ ትጠይቃለች:: ሠራተኛዋ‹‹ የሻወር ቤት ሻታፍ ወደቀ›› በማለት መልስ ትሰጣለች:: ወይዘሮ ወይንሸት በድጋሚ ከትንሽ ቆይታ በኋላ የሠራተኛዋን ድምፅ ትሰማለች:: ‹‹ወይኔ ወይኔ ዛሬ ምን ዓይነት ቀን ነው?›› ትላለች:: ወይዘሮ ወይንሸት ደንግጣ በድጋሚ ‹‹ምንድን ነው?›› ብላ ትጠይቃለች:: ሠራተኛዋ ‹‹ኮሪደሩን ሳፀዳ ሙሉ ውሃ ተደፋብኝ›› ትላለች:: ወይዘሮ ወይንሸት ፀሎቷን አቋርጣ ‹‹በቃ! በመወልወያ አንሺው::›› ትላታለች::
ወይዘሮ ወይንሸት እየሠገደች በፀሎት ቤቱ ውስጥ ሳይታሰባት ብዙ ቆየች:: መጨረሻ ላይ የቤት ሠራተኛዋ ‹‹ማሚ ናሆሜ፤ ማሚ ናሆሜ›› ብላ ስትጮህ ወይዘሮ ወይንሸት በድንጋጤ ከፀሎት ቤት ወጥታ ድምፅ ወደ ሰማችበት አቅጣጫ ሮጠች:: ከውጪ ሲመጣ መሃል ላይ ያረፈውን ትልቁን ቤት ሲያልፉ ወደ ሰርቪስ ቤት መሔጃው ቀጭኑ መንገድ ላይ ሠራተኛዋ እግሯን ዘርግታ ተቀምጣ የናሆምን ጭንቅላት እጇ ላይ አድርጋ አንገቷን ወደ ግንቡ አዘንብላ ትጮኻለች::
ወይዘሮ ወይንሸት ሮጣ ደርሳ ልጇን ስታየው መልኩ ጥቁር ብሏል:: ነፍስ ያለው አይመስልም:: ‹‹ናሆሜ›› እያለች ብትጮህም መልስ አልሰጣትም:: ዓይኑ ፈጥጧል:: ‹‹ምንድን ነው? ምን ሆኖ ነው?›› በማለት ወይዘሮ ወይንሸት ሠራተኛዋን ጠየቀች:: የቤት ሠራተኛዋ የልብስ ማስጫ ገመድ ላይ የተንጠለጠለውን ስከርቭ እያሳየች ‹‹ በዛ ላይ ራሱን ሰቅሎ ታነቀ›› አለቻት:: ‹‹ ምን? እንዴት? ልጄ ይህንን አያርግም? ይህንን ነገር ለሰው አላወራም፤ አንቺም እንዲህ አትበይ›› ብላ ልጇን መደባበስ ጀመረች:: ናሆም ቀዝቅዟል፤ ምላሷ እየተሳሰረ ደጋግማ ብትጠራውም አይሰማም:: ልጁን ሠራተኛዋ ላይ ትታ ከጊቢ ውጪ እደጅ ወጥታ ‹ኡኡኡ…›› እያለች ጩኸቷን አቀለጠችው:: ጎረቤት ተሰበሰበ::
ሕፃን ናሆምን የማዳን ሩጫ
ጎረቤቶች የሚወዱትን፤ ቀልጣፋውን፤ አስተዋዩን ናሆምን ይዘው እየተሯሯጡ ወደ ግሩም ሆስፒታል አቀኑ:: ሆስፒታሉ ምርመራ አደረገ:: ሆኖም የሆስፒታሉ ዶክተር ‹‹ይዛችሁ የመጣችሁት አየር አጥቶ ታፍኖ ህይወቱ ያለፈ ሕፃን ልጅ ነው›› አለ:: ከጥቂት ሰዓታት በፊት ጤነኛ፤ ምግብ በአግባቡ የተመገበ ተጫዋች ልጅ በድንገት ህይወቱ አልፏል ተባለ::
የግሩም ሆስፒታል መረጃ እንደሚያመለክተው ናሆም ሆስፒታል ሲደርስ ምንም ዓይነት ቅፅበታዊ የሳንባ እንቅስቃሴ አልነበረውም፤ ምንም ዓይነት የልብ ምት አልነበረውም:: በዚህ ምክንያት በሕይወት የመኖር ምልክት ያልታየበት ነበር:: ቀደም ሲል ሕፃን ናሆም ምንም ዓይነት የታወቀ ለሞት የሚያበቃ ህመም አልነበረበትም:: ወደ ሆስፒታል ሲመጣ በአፉ ላይ ወደ ውጪ አስመልሶት እንደነበር የሚያመለክት ፍንጭ ተገኝቷል:: ሆስፒታሉ ለሞት ያበቃው ከባድ የአየር መተላለፊያ ቱቦ በመዘጋቱ የተነሳ የተከሰተ የመተንፈሻ አካል ሥራ ማቆም የላይኛው የዓየር መተላለፊያ ቱቦ መዘጋት መሆኑን ጠቆመ::
የሕፃና ናሆም ሥርዓተ ቀብር
እናት ወይዘሮ ወይንሸት አበደች፤ የምትይዝ የምትጨብጠው ጠፋት:: ጎረቤት አባት ቤተዘመድ ሁሉም እዬዬ አለ:: የበዓል የደስታ መንፈስ በኀዘን ተተካ:: ወይዘሮ ወይንሸት ኀዘኑን መሸከም ከብዷታል:: ራሷን ለማረጋጋት ተቸግራለች:: ጎረቤቶች እና ዘመድ አዝማድ የሕፃን ናሆም የቀብር ስነስርዓት በክብር እንዲከናወን የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ:: ቀብሩ ተፈፀመ::
ሁሉም በታላቅ ኀዘን ውስጥ በትካዜ ተዋጠ:: የእነናሆም ቤት ብቻ ሳይሆን የነናሆም ሰፈር ሳይቀር በአስቀያሚ የኀዘን ጨለማ ተዋጠ:: እናት እና አባቶች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናት ጎደኞቹ እና የዕድሜ እኩዮቹ እንዲሁም የታላላቅ ወንድሞቹ ጓደኞች በአጠቃላይ የአካባቢው ነዋሪ ሁሉም አዘነ::
ድንኳን ተደኩኖ የኀዘን ደራሾች እየተስተናገዱ ሲወጡ የሚያስተናግዱት ጎረቤቶች ወደ ሰርቪስ ቤትም ሆነ ወደ ዋናው ቤት ጎራ እያሉ ሲንጎዳጎዱ፤ የሠራተኛዋ ሁኔታ አላማራቸውም:: አንዳንዴ መፍዘዟ፤ ለመሔድ የምትፈልግ መምሰሏ ጥርጣሬ ውስጥ ከተታቸው:: በተለይ በደህና የዋለ ልጅ በእርሷ እጅ ላይ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱ አጠራጠራቸው::
አጠገቧ ግቢው ውስጥ እያለች ልጇ የሞተባት እናት ግን ቀልቧን በመሳቷ መጠራጠር አልቻለችም:: ምንም እንኳ ልጇ በሠራተኛዋ እጅ ላይ ሕይወቱ አልፎ ብታገኘውም በፍፁም ጉዳዩን ከሠራተኛዋ ጋር ባለማገናኘቷ የአስክሬን ምርመራ ሳይደረግ ቀብሩ ተፈፅሟል::
ከሠልስት በኋላ የጎረቤት ምክር
ወይዘሮ ወይንሸትን ጎረቤቶቿ በተወሰነ መልኩ ስለመጠራጠራቸው ፍንጭ ሲሰጧት አጥብቃ ማሰብ ጀመረች:: የቤት ሠራተኛዋ ‹‹ታንቆ አገኘሁት›› ያለችበት የልብስ ማስጫ ገመድ ለመሬት ቅርብ መሆኑ ትዝ አላት:: የናሆም ቀብር በተፈፀመ በሦስተኛው ቀን ለሊት ድንገት ተነስታ የቤት ሠራተኛዋን ጠርታ ጠየቀቻት:: ‹‹ናሆምን በትክክል ያገኘሽው እንዴት ሆኖ የት ነው?›› ስትላት መልሷ ተመሳሳይ ነበር:: በስከርቭ ተሰቅሎ ማግኘቷን ደገመችላት::
አሁንም ወይዘሮ ወይንሸት ትንሽ ብትጠራ ጠርም ገመዱ አጭር በመሆኑ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ተሰቅሎ ሊሞትበት የማያስችል መሆኑን አላረጋገጠችም:: ከናሆም ሕይወት መጥፋት ጋር የቤት ሠራተኛዋን ሊያገናኛት የሚችል ነገር ይኖራል ብላ አሁንም መገመት አልቻለችም:: ስለዚህ ያለምንም ጥርጣሬ የአስክሬን ምርመራ ሳይደረግ ናሆም በክብር መቀበሩ አልቆረቆራትም::
ወይዘሮ ወይንሸት የተወሰነ መረጋጋት ስትችል ‹‹ልጅቷ የተለያዩ ምልክቶችን እያሳየች ነው:: ናሆም ሕይወቱ ሲያልፍ ቤት የነበራችሁት አንቺ እና እርሷ ናችሁ፤ ስለዚህ ፖሊስ ጣቢያ አብራችሁ ቃል ስጡ›› ያሏትን ጎረቤቶቿን ምክር ተቀብላ ሰልስት ካለፈ በኋላ ወይዘሮ ወይንሸት ሠራተኛዋን ይዛ ቃል ለመስጠት ፖሊስ ጣቢያ ሄዱ::
ፖሊሶች ቃል ሲቀበሉ እግረ መንገዳቸውን ብዙ ምርመራ አደረጉ:: ሠራተኛዋ ያየሽውን ተናገሪ ተባለች:: የልብስ ማስጫ ገመድ ላይ በስከርብ ተንጠልጥሎ እንዳገኘችው ተናገረች:: ወይዘሮ ወይንሸትም በሠራተኛዋ እጅ ላይ እንዳገኘችው ተናገረች:: ፖሊሶቹ ለሠራተኛዋ ‹‹የልብስ ማስጫ ገመድ ላይ የተንጠለጠለ ስከርቭ ሰው አያንቅም:: እንዴት ታነቀ ትያለሽ?›› ብለው በጥያቄ ማጣደፍ ጀመሩ::
ወይዘሮ ወይንሸት ቀድሞም ‹‹ገመዱ ይበጠሳል እንጂ እንዴት ሰው ያንቃል? የገመዱ ርቀትም ናሆምን ለማንጠልጠል የሚያስችል አይደለም:: ይህ ነገር ልክ አይደለም:: እውነቱን ንገሪኝ›› የሚል ጥያቄ አቅርባ ‹‹አይ እንደተናገርኩት ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥታ ነበር:: ፖሊሶቹ እንደወይዘሮ ወይንሸት ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረቡ:: ‹‹እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል?›› ብለው እንድታምን ጎተጎቷት:: አሁን ሃሳብ ቀየረች:: ‹‹እኔ ነኝ ታንቆ ነው ያልኩት:: ይህንን ምክንያት ፈጥሬ ያመጣሁት ማሚ ትቆጣለች ብዬ እንጂ ከግንብ ላይ ሲንጠለጠል ወድቆ አረፋ ደፈቀው፤ ከዚያ ሞተ::›› አለች::
በዚህ ጊዜ ፖሊሶቹ ስለተጠራጠሩ የበለጠ ምርመራ ማካሔድ ጀመሩ:: ቤተሰቡ የማያውቃቸው መታወቂያ ያላቸው በአጋጣሚ በፖሊስ ጣቢው የተገኙ ሰዎች ባሉበት ማንም ሳያስገድዳት ከምትሰጠው የተምታታ ምላሽ በመነሳት ያለምንም የኃይል ጫና እርሷ መግደሏን እንድታምን ተጠየቀች:: በመጨረሻም አመነች:: በግ እየፈታ ሲያስቸግራት ተደብቃ በለበሰው ስከርቭ ለብዙ ደቂቃ ስታንቀው ሕይወቱ መጥፋቱን ተናገረች:: ይህንን የዕምነት ቃል ስትናገር የተገኙ ሰዎች እንደምስክር ተቆጠሩ::
የአስክሬን ምርመራ
እነወይዘሮ ወይንሸት ፍፁም ባለመጠራጠራቸው አስክሬኑ ሳይመረመር ተቀብሯል:: የቤት ሠራተኛዋ በስከርቩ አንቃው እንደነበር ማመኗን ተከትሎ ክስ ተመሠረተ:: በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቡራዩ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ትዕዛዝ አስተላለፈ:: ፖሊስ እና ሽማግሌ ባለበት የሕፃኑ ልጅ ሬሳ በክብር ወጥቶ ተመርምሮ በክብር ወደ ቀብር ቦታ እንዲመለስ ታዘዘ::
ሆስፒታሉ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሕፃን ናሆም ከተቀበረበት ቦታ፣ ጉድጓድ እና ሳጥን ጀምሮ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሉ ተመርምሮ መረጃ ተያዘ:: በመጨረሻም ሕይወቱ ያለፈበት ምክንያት በአንገቱ ላይ የኃይል ግፊት ጫና በመድረሱ መሆኑን ያመለክታል:: የፍርድ ቤት ክርክር ቀጠለ:: ምስክሮች መሰከሩ:: የህክምና ማስረጃ ቀረበ::
የፍርድ አሰጣጥ
ፍርድ ቤቱ ሲያከራክር ቆይቶ ሕፃን ናሆም ባረፈበት ጊዜ ከመቀበሩ በፊት ሆስፒታል ሄዶ የነበረው ማስረጃ፤ የአስክሬን ምርመራ እንዲሁም ባመነች ጊዜ የነበረ የሰው ምስክር እና የእርሷ ገድያለሁ ብላ ማመኗ በሙሉ ተጠናቀረ:: ነገር ግን ተጠርጥራ ከታሠረች በኋላ ፍርድ ቤት ስትቀርብ መልሳ መግደሏን ብትክድም መግደሏ ተረጋግጦ የሁለት ዓመት ከሦስት ወር ፍርድ ተሰጠ::
የወንጀል ህጉ
የወንጀል ሕጉ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን በሚመለከት ማንም ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት በማናቸውም ዓይነት መሣሪያ ወይም ዘዴ ሰው የገደለ ከሆነ ነፍሰ ገዳይ ይባላል ይላል:: አስቦ ወይም በቸልተኝነት ሰውን በመግደል ጥፋተኛ የሆነ ሰው ላይ የሚጣለው ቅጣት እንደአገዳደሉ ቀላልነትና ከባድነት በሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ይወሰናል:: አስቦ ወይም በቸልተኝነት የገደለ ሁሉ የሚጠየቀው ሕጋዊ በሆኑ የፍርድ ሒደቶች እና ውሳኔዎች መሠረት ብቻ እንደሆነ አስቀምጧል::
በወንጀል ህጉ ከባድ የሰው ግድያን በሚመለከት በአንቀፅ 539 ላይ እንደተቀመጠው ማንም ሰው ሰውን ለመግደል አስቀድሞ የነበረው ሃሳብ ወይም ምክንያት ለመግደል የተጠቀመበት መሳሪያ ወይም ዘዴ፣ የአገዳደሉ ሁኔታ ወይም ግድያው የተፈፀመበት ሁኔታ የሚያከብድ በጭካኔ ነውረኛ ወይም አደገኛ በሆነ መንገድ መግደል ሰውን ለመግደል ወይም የውንብድና ወንጀል ለመፈፀም የተደራጀ የወንበዴ ቡድን አባል በመሆን ወይም ሌላ ወንጀል ለመፈፀም እንዲመቸው ወይንም የተፈፀመ ወንጀል እንዳይገለጽ ለማድረግ ሲል አስቦ ሰውን የገደለ እንደሆነ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል ይላል:: ክሱ የቀረበው በቅድሚያ በዚሁ ወንጀል የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶበት ቅጣቱ በመፈፀም ላይ እንዳለ ከሆነ በሞት እንደሚቀጣ አስቀምጧል::
ተራ የሆነ የሰው ግድያን የሚያመለክተው አንቀፅ 540 ላይ ደግሞ ማንም ሰው አገዳደሉ በአንቀፅ 539 ላይ የተገለጸውን ያህል ከባድ ወይም በአንቀፅ 541 ላይ የተመለከተውን ያህል ቀላል ባልሆነ ሁኔታ አስቦ ሌላ ሰውን የገደለ ከሆነ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ አስቀምጧል::
የሆነ የሰው ግድያ ቅጣትን ያካተተው አንቀፅ 541 ላይ ደግሞ እንደተመላከተው ማንም ሰው የአስገዳጅ ሁኔታን ወሰን በመተላለፍ በአንቀፅ 75 ወይም ህጋዊ መከላከልን ከመጠን በማሳለፍ አንቀፅ 78 ላይ ከፍ ባለ ደም በሚያፈላ ምክንያት ወይም ባልጠበቀው ህሊናን በሚያውክ ምክንያት ወይም በከፍተኛ ስሜት ወይም በብርቱ ዝንባሌ የተነሳሳ ሆኖ ፤ በአዕምሮ ግምት ይህን ለማድረግ በሚያደርሱ እና በከፊል ይቅርታን በሚያሰጡ ሁኔታዎች አስቦ ሌላውን ሰው የገደለ እንደሆነ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚቀጣ አስቀምጧል::
የኦሮሚያ ልዩ ዞን ፍርድ ቤት በየትኛው አንቀፅ ተመስርቶ ፍርዱን እንደሰጠ ለአንባቢ እንተወው:: ወይዘሮ ወይንሸት የልጁ ሕፃን መሆን እና ድርጊቱን የፈፀመችውን ሴት ለመከላከል የማይችል መሆኑ ታሳቢ ሳይደረግ፣ የአገዳደል ሁኔታው እና ግድያው በግፍ የተፈፀመ ሆኖ ሳለ ለግድያው የሁለት ዓመት ከሦስት ወር ብቻ ፍርድ መሰጠቱ ምን ያህል አግባብ ነው የሚለው የእኛም ጥያቄ ነው::
የወላጅ እናት የፍረዱኝ ቃል
እምባዋ ማቋረጫ የለውም:: ጉንጯን ሳይነካ እየተንከባለለ በአራት ማዕዘን ወደ መሬት ከሚፈስ እንባ ጋር “ከገደለችው የበለጠ ፍርዱ ልጄን ገድሎብኛል:: ከዚያን ቀን ጀምሮ ታምሜያለሁ:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የልጄ አምላክ ይፍረደኝ:: ፍርድ ተጓድሎብኛል:: ሠራተኛዋ የ22 ዓመት ሴት ራሱን መከላከል የማይችል የዘጠኝ ዓመት ልጅ ላይ የግፍ ግድያ ፈፅማለች:: ለዚህ ፍርዱ 2 ዓመት ከ3 ወር ብቻ መሆኑ ያሳምማል:: በምን ምክንያት ይህ ፍርድ እንደተሰጠ አልገባኝም” ትላለች::
አቃቤ ሕግም ክስ የመሰረተው ሆን ተብሎ የተፈፀመ ከባድ የግድያ ወንጀል ብሎ ነው:: የህክምና ማስረጃ መጥቶ፤ የአስክሬን ምርመራ ቀርቦ ስታምን የነበሩ ሰዎች መስክረው ከረሜላ እንደሠረቀ ሌባ ሁለት ዓመት ከሦስት ወር ብቻ መፈረዱ አስደንጋጭ ሆኖብኛል:: ሕዝብ መንግሥት አለ ብሎ እንዳያስብ የሚያደርግ ፍርድ መፈረዱ አሳምሞኛል:: ይህንን ሕዝብ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ::
ልጁ ነፃ ልጅ ነው:: ከዕድሜው በላይ ብዙ ነገሮቹን ያውቃል:: ያለፈው ሕዳር 7 ገና አስር ዓመት ይሆነው ነበር:: ነገር ግን በአጭር ተቀጨ:: ተንጠልጥሎ ከነበር በእርሷ አቅም መውረድ አይችልም:: በተጨማሪ ልጁ ራሱን ለመስቀል የሚያበቃው ችግር ቤት ውስጥ የለም፤ በፍቅር በሰላም በሚኖር ቤተሰብ ውስጥ የሚገኝ ልጅ ነው:: ካልገደለችው መለቀቅ ነበረባት:: ከገደለች ደግሞ ተገቢው ፍርድ መሰጠት አለበት::
ነገ መቀጣጫ የሚሆን ፍርድ መሰጠት ሲገባው አልሆነም:: ሠራተኛዋ የገደለችው ናሆምን ብቻ አይደለም:: መላ ቤተሰቤን ነው:: እኔ ከራሴ አልፎ ለመላ ቤተሰቤ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች የምሆን ሰው ነበርኩኝ:: ዓላማዬ ትልቅ እና ብዙ ነበር:: አሁን ስጋዬ ቢራመድም ሞራሌ፣ መንፈሴ ሞቷል:: በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ሳይቀር በናሆም መሞት ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ፍርድ መሰጠቱ የስነልቦና ጫና አድርሶባቸዋል::›› ትላለች::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 22/2014