የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዘመኑን የማይዋጅ ከመሆኑ ባሻገር መንታ መንገድ ላይ ተቅበዝባዥ ሆኗል። የ”ልዕለ ኃያሏ” ዲፕሎማሲም ሆነ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የቁልቁለት መንገዱን ከተያያዘውም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሆኖታል። በእኛ የተጀመረ በእኛም የሚቋጭ አይደለም። ቀራጮች/ሪፐብሊካንስ/ አልያም ዴሞክራቶች መጡ ሔዱ ከተያያዘው የቁልቁለት መንገድ አያስቆሙቱም።
አገራችን ሰሞነኛውንም ሆነ መጪውን የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ፍርደ ገምድልነት ለማረቅና አሰላለፏን ከዚህ አንጻር ለመበየን ወይም ስትራቴጂካዊ እይታን ለመግለጥ የአሜሪካንን የውጭ ግንኙነት የቁልቁለት ጉዞ ከተጀመረበት አንስቶ መመልከት፣ መገምገምና መተንተን ግድ ይላል። በመነሻነት ቢያገለግል በሚል ቅንነት ይህን ስንክሳር በአለፍ ገደም በተከታታይ ክፍሎች ለመቃኘት እሞክራለሁ። የሳትሁት እውነት ቢኖር ለመታረም ፣ ይቅርታ ለመጠየቅ አላቅማማም።
ቀራጮች ነጩ ቤተ መንግሥት ሲገቡ ፖሊሲው በአዲሱ ወግ አጥባቂነት ፈለግ ይወሰድና ዴሞክራቶች በእግሩ ሲተኩ ደግሞ ቀኝ ኋላ ይዞርና በሊበራል ዓለም አቀፋዊነት ይመለሳል። በትራምፕም ሆነ በባይደን የታዘብነው ይሄን ነው። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው እንዲህ ባለ ውልውል ከመመናተሉ ባሻገር የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ አልያም ፕራግማቲስት አለመሆኑ ተደጋግሞ ይተቻል።
በአገራችንና በመንግሥታችን ላይ እያራመደችው ያለው ቁሞ ቀር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለዚህ ጥሩ እማኝ ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ባለፈው አዲስ ወግ ላይ እንደጠቆሙት አሜሪካና አጋሮቿ ዛሬም እንደ 83ቱ የመንግሥት ለውጥ(regime change) ለማምጣት ካርቦን ኮፒ የሆነ ሴራ እየጎነጎኑ ነው። ምንም እንኳ የአገራችን፣ የቀጣናውና የአህጉሩ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ፍጹም የተለያየ ቢሆንም አሜሪካ ዛሬም ያረጀ ያፈጀ የጨረተና ያረጠ ፖሊሲ የሙጥኝ እንዳለች ነው። ለዚህ ነው እንደ ማይክል ሒርሽ ያሉ አንዳንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉምቱዎችና ጸሐፊዎች ያለርህራሄ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሽፏል እስከማለት የደረሱት።
ቀራጮች የነጻ ገበያ አክራሪና የነጭ ወግ አጥባቂዎች ማለትም የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ደጅ ያልረገጡ ነጭ አሜሪካውያንና በተለምዶ አንድ በመቶ የሚባሉ ባለጠጎችን ማህበራዊ መሠረት ታሳቢ ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጫናን ይከተላል። የባለጠጋዎችን ግብር ይቀንሳል። እነሱን ታሳቢ ያደረገ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያደርጋል። ስደተኛን ይጠላል። አያበረታታም።
በ”አሜሪካ ትቅደም!” ስም የነጭ ወግ አጥባቂዎችን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስከበር ይተጋል። የገበያ ከለላ ይሰጣል። አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ድጎማ ያደርጋል። ሉዓላዊነትን እንደ መልካም አጋጣሚ ሳይሆን እንደስጋት ይቆጥራል። የመንግሥታቱን ድርጅት፤ የዓለም ባንክን፤ አለማቀፉን የገንዘብ ተቋም፤ የዓለም የንግድ ድርጅት፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳንን/ኔቶ/፤ የአውሮፓ ሕብረትን፤ ወዘተረፈ በጥርጣሬ ይመለከታል።
ጎልቶ የማይታየው ይህ የቀራጮች ፖሊሲ እድሜ ለትራምፕ አደባባይ ወጥቶ ተሰጥቷል። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ላለፉት 70ና ከዚያ በላይ ጊዜ በዓለም ላይ ለሰፈነው አንጻራዊ ሠላም በባለውለታነት የሚወደሱትን ኔቶንና የአውሮፓ ሕብረት አናንቋል። ያረጁና የጨረቱ ናቸው ሲል በሸንጎ መሀል አጣጥሏቸዋል፤ አዋርዷቸዋል። ከፓሪሱ አለማቀፍ የአየር ንብረት እና ከኢራኑ የጸረ ኒውክሌር ስምምነቶች አፈንግጧል።
አገሩ ለዓለም ጤና ድርጅት ታደርገው የነበረውን ድጋፍ አቋርጧል። የእንግሊዝን ከሕብረቱ የመነጠል ውሳኔ ሕዝብ ደግፎ ቆሟል። የአሜሪካንን ዓለም አቀፍ ሚና አቀዛቅዟል። በዚህ የተነሳ የተፈጠረውን ክፍተት በተለይ ቻይና እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅማበታለች። ራሽያም በእንግሊዝ መነጠል፤ በኔቶ መብጠልጠልና በአሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት ግንኙነት ንፋስ መግባቱ ጮቤ አስረግጧታል። የልብ ልብ እንዲሰማት አድርጓል።
አሜሪካ ስትለቅ ቻይና እግር በእግር ትተካለች። ከሁሉም በላይ ሽንፈቱ አልቀበልም በማለትና ደጋፊዎቹ እንደ አሜሪካ ዴሞክራሲ ቤተ መቅደስ የሚመለከውን ካፒቶል ሒል በማስወረርና በማስቀመጥ መፈንቅለ መንግሥት የማድረግ ያህል ሙከራ በማድረጉ አሜሪካውያንን ለዘመናት ሲመጻደቁበት የነበረውን ዴሞክራሲ አፈር ድሜ አብልቶታል። ቻይናና ራሽያ ድንቄም ዴሞክራሲ እያሉ እንዲሳለቁ ፤ ዴሞክራሲ አይሰራም እንዲሉ አደፋፍሯቸዋል። የልብ ልብ እንዲሰማቸው እና አሜሪካውያን እርስ በርስ እንዲከፋፈሉ አድርጓል።
የዴሞክራቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደግሞ በተቃራኒው በሊበራል ዓለም አቀፋዊነት ላይ መልሕቁን የጣለ ነው። ሉዓላዊነትን፣ ትብብርንና ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ለማስፋት የሚሰራ ነው። ከቀራጮች በተቃራኒው የመንግሥታቱን ድርጅት ጨምሮ ከፍ ብሎ ለተዘረዘሩ አለማቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማትና ስምምነቶች ተገዥ ነው። በአናቱ ነጻ ገበያን የሕግ የበላይነትን መልካም አስተዳደርን ሰብዓዊ መብትንና ዴሞክራሲን በፖሊሲ ማሳለጫነት ይጠቀማል።
ለዚህም ነው 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ከመግባታቸው የትራምፕን የውጭ ጉዳይና የአገር ቤት ውሳኔዎች መሻርና መቀልበስ የጀመሩት። የፖርቲው ማህበራዊ መሠረትም በተለምዶ 99 በመቶ የሚባለው በመካከለኛና በታችኛ መደብ የሚገኘው አሜሪካዊ ነው። የዩኒቨርሲቲ ደጅ ረጋጩ የፓርቲው አስኳልም ነው።
ከሞላ ጎደል በማህበራዊ ፍትሕና ዴሞክራሲ የሚያምን ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲ ደጅ የረገጡ ነጭ ሴቶች፣ ጥቁሮች፣ እስፓኒኮችና መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሌሎች አሜሪካውያን የፓርቲው ማህበራዊ መሠረቶች ናቸው። ዳሩ ግን በየራሳቸው አእማድ የቆሙ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች የታለመላቸውን ግብ ማሳካት እየተሳናቸው እንደሆነ ይተቻል። እኛም ከቻይናና ራሽያ ጋር የገባችበትን ቅርቃር፤ በቬትናም፣ በኢራን፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በሶማሊያ፣ በየመን፣ በፊሊፒንስ፣ በቬኒዞላ፣ ወዘተረፈ የቀራጮችም ሆነ የዴሞክራቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲከሽፍ ታዝበናል።
አንዳንድ ጉምቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቃውንት ቢቸግራቸው የ98 አመት የዕድሜ ባለጸጋ ወደ ሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደራሲ እስከ መባል ወደ ሚሞካሸው ሄነሪ ኪሲንጀር ዘመን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የታነጸ ዲፕሎማሲ ማማተር ጀምረዋል። የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ የቬትናምና የኢራን የውጭ ግንኙነት ቀውሶች ደራሲ በመባል ክፉኛ የሚተቸውን ኪሲንጀር እንደ ማሪያም መንገድ መወሳቱ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ያሳያል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመሠረቱ ተናግቷል በማለት ተጨማሪ ማሳያዎቻቸውን ያነሳሳሉ። በቀዝቃዛው ጦርነት ርዕዮተ ዓለምን ተከትሎ ያራምደው የነበረው የእመቃ ዲፕሎማሲ በዊልሰናዊያን የተስፋፊነት የተሳሳተ አባዜ ከቬትናም ጋር የተካሄደው ጦርነት የ50ሺ አሜሪካዊ ወታደሮች ያስገደለ፤ ከ70 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አክስሯል። ከሁሉም በላይ የሽንፈት ከል አከናንቦታል። የአሜሪካን ገጽታ ክፉኛ ጎድቶታል። እንዲሁም በድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት በአዲሱ የሬጋን “ሰይጣን”አገዛዞችን በኃይል የማስወገድ እርምጃ ከፍ ብሎ እንደተመለከተው ተሞክሮ ከሽፏል።
45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ደግሞ የ1950ዎቹንና 60ዎቹን “አሜሪካ ትቅደም!” ፖሊሲ አቧራውን አራግፎ ወደፊት ቢያመጣውም አሜሪካን ነጥሎ ብቻዋን በማስቀረት ከስሯል። ባሪ ጌዌን “The Inevitability of Tragedy” በተሰኘው የሄነሪ ኪሲንጀርና የዛን ዘመን የዲፕሎማሲ አካሄድ በሰነደበትና በተነተነበት ማለፊያ መጽሐፉ” በእርግጥ ሔነሪ ኪሲንጀርን ልትጠላውና ከይሲ ነው ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ልትረሳው አልያም ልተተው ግን አትችልም። ለዛውም በዚህ ጊዜ። እውነት ለመናገር የኪሲንጀር እሳቤም ሆነ ተፈጥሯዊ ወይም ደመነፍሱ ክፉኛ ያስፈልገናል። “በማለት የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚታደገው ኪሲንጀርና መንፈሱ ብቻ እንደሆነ ይነግረናል።
ቀራጮች የሚከተሉትም አዲሱ ወግ አጥባቂነት Neoconservative አልያም ዴሞክራቶች የሚያራምዱት ሊበራል አለማቀፋዊነት Liberal internationalism የአሜሪካን ዲፕሎማሲ ከገባበት ቅርቃር አያወጣውም። ለዚህ ነው ጌዌን በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ወደተቀረጸው የሔነሪ ኪሲንጀር የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንመለስ ሲል የሚወተውተው።
ማይክል ሒርሽ “WELCOME To Kissinger’s World” በሚል ርዕስ በፎሪን ፖሊሲ መጽሔት ባለፈው አመት ባስነበበን ወግ፤ የኮሮና ወረርሽኝ የትራምፕን “አሜሪካ ትቅደም!” የሚለውን የተነጣይነት አጀንዳ ለማጉላት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። የንግድ ወኪሉ ሮበርት ሊቲዘር ቻይና በምትከተለው አደገኛ የንግድና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ አሜሪካ በውጭ የሚገኙ ፋብሪካዎቿንና ኩባንያዎቿን ወደ አገር ቤት መመለስ ያስፈልጋታል ሲል የትራምፕን የተነጣይነት ፖሊሲ ያቀነቅናል።
ትራምፕ በዚህ አያበቃም። ሳይሳካለት ቀረ እንጂ የቻይናን የኢኮኖሚ እድገት ግስጋሴን ለመገዳደር የሚችል የተለያዩ አገራትን ግንባር ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ዴሞክራቶች ይህን የትራምፕ ገዳዳ አቋም በገደምዳሜ ከመደገፍ አልፈው በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት የነበረውን አይነት ትንቅንቅ እስከመቆስቆስ ደርሰዋል።
የዚያን ጊዜው እጩ የዛሬው ዴሞክራት ፕሬዝዳንት ባይደን በተደጋጋሚ የቻይናውን ፕሬዝዳንት ዢ ዥንፒግ ከማድነቅ አልፈህ ፊት ትሰጥ ነበር በማለት በምርጫው ክርክር ወቅት ይከስ ነበር። ዴሞክራቶች ከዚህ አልፈውም በእነሱ ሊበራል አለማቀፋዊነት መርህ መሠረት የተቋቋሙ እንደ የዓለም ንግድ ድርጅት ያሉ ተቋማትን የቻይና መጠቀሚያ እየሆኑ ነው በማለት ማብጠልጠል መጀመራቸው፤ ሳያንስ ቻይና የአሜሪካውያንን የሥራ ዕድል እየተሻማች ነው በሚል መክሰሳቸውን ሒርሽ ያትታል።
“WELCOME Back To Kissinger’s World” በሚል ርዕስ በፎሪን ፖሊሲ መጽሔት ባስነበበን ማለፊያ መጣጥፍ፤ ደግነቱ ይላል ማይክል ሒሽ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የተመሠረተው ነጻው አለማቀፍ ሥርዓትና የትበብር መንፈስ እየተፍገመገመም ቢሆን ዛሬ ላይ ደርሷል። ወደፊትም ይቀጥላል። የመንግሥታቱ ድርጅት፣ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ፣ የዓለም ባንክ ፣ የዓለም ንግድ ድርጅትና ሌሎች ተቋማት ለአለማቀፍ ትብብርና ሠላም የዋሉትን ውለታ ያነሳሳል። ሆኖም ዋሽንግተን፣ ቻይናና ራሽያ የየራሳቸውን አመለካከትና ስውር አጀንዳ አስርገው ለማስገባት የሚያደርጉት ትንቅንቅ እነዚህን ተቋማት ሽባ እያደረጓቸው ነው።
በጸጥታው ምክር ቤት እስራኤልን በተመለከቱ በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠሩ የወሳኔ ሀሳቦች በአሜሪካ ወይም በአጋሮቿ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ውድቅ ይሆናሉ። እንዲሁም ቻይናና ራሽያ የሚያቀርቧቸውን የውሳኔ ሀሳቦች አሜሪካና አጋሮቿ እግር በእግር እየተከታተሉ ውድቅ ያደርጉታል። አሜሪካና ምዕራባውያን አገራችንን በሚመለከት ያቀረቧቸው ደርዘን የውሳኔ ሀሳቦች እንዴት ውድቅ እንደተደረጉ ያጤኑአል። እነቻይናም እንደዚሁ እያደረጉ የጸጥታው ምክር ቤት የመቧቀሻ መድረክ በማድረግ ሽባ እያደረጉት ነው። መተማመን ቀርቷል። መጠራጠር ነግሷል ።
በእነዚህ ኃይሎች መካከል እየተፈጠረ ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቶ የቀዝቃዛውን ጦርነት ራስ ምታት /ሀንጎበር/ እየቀሰቀሰ ነው። አሜሪካና ምዕራባውያን በአንድ ወገን ቻይናና ራሽያ በሌላ ወገን ሆነው አፍሪካን፣ እስያንና ላቲን አሜሪካን ግዳይ የመጣያ መስክ እያደረጓቸው ነው። አሜሪካና ጭፍራዎቿ በአገራችን ላይ እየተከተሉት ያለው ፍርደ ገምድልነትና ጫና የዚህ እውነታ ማሳያ ነው። ደግነቱ ይላል ሒሽ ወደ ተነሳበት ነጥብ ሲመለስ፤ በርዕዮተ ዓለም ተከፋፍሎ መቧቀሱ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋር ላይመለስ ተሸኝቷል። ዛሬ ኮሚኒዝም አልያም ካፒታሊዝም በሚል ጎራ ለይቶ መጠዛጠዝ የለም።
ባለፈው ክፍለ ዘመን ንጉሳዊ፣ አምባገነናዊ፣ ፋሽስታዊና ኮሚኒስታዊ አገዛዞች በዓለም ላይ ያስከትሉትን ጥፋትና ምስቅልቅል ተመልክተናልና ዛሬም ይላል ማይክል ሒሽ፣ ዴሞክራሲ በጽንፈኝነት፣ በተጠመዘዘ መረጃና እንደ ራሽያ ባሉ አገራት ደባ እየተፈተነ ከፍ ሲልም አይሰራም እየተባለ እየተብጠለጠለ ነው። ካፒታሊዝም ራሱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ስለአልቻለ የሰው ልጅ ጥያቄ እያነሳበት ነው። ይህ የተወዛገበ የአገር ቤት ፖለቲካ ነው እንግዲህ አወዛጋቢ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይዞ ብቅ ያለው። አንድ ጊዜ “አሜሪካ ትቅደም !”ሌላ ጊዜ “አሜሪካ ተመልሳለች!” እያለ የሚወራከበው። ከእኔ ጋር ካልሆናችሁ ከጠላቶቼ ጋር ናችሁ እያለ ጥርስ የሚያፋጨው ።
ለዚህ ነው የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ጥፋት ከቻይና ጋር መተባበራቸው ሆኖ የተገኘው። አገራችን ላይ የተከፈተው የሚዲያ፣ የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የዚህ ቅጥያ ነው። ከቻይናና ከራሽያ ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት የአሜሪካና የምዕራባውያን ስጋት በማድረግ ግንኙነቱን ለመቀልበስ ከፍ ያለ ጥረት እየተደረገ ያለው። ኢትዮጵያን ከፍ ሲልም አፍሪካን የማንበርከክና በምትኩ ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚ መንግሥት ለመትከል የሚባዘነውም ፤ ወዳጆቻችሁንም ሆነ ጠላቶቻችሁን እኛ ነን የምንመርጥላችሁ ከሚል ቁሞ ቀር ፖሊሲ የመነጨ ነው። ብዙዎቹ ፈቅደውና መርጠው እየተከተሉት ያለው አለማቀፍ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ በውድቀት ቁልቁለት ላይ ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ የተደረሰው በዚህ ነው ይላል ማይክል ሒሽ።
የአሜሪካ ክብርና ኃይል እንዲህ እንደዛሬው ተዳክሞ አያውቅም ይላል ሒሽ ፤ በተለይ የአንድ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆኖ የቀረው የትራምፕ አሜሪካ “እሴቶቼ” የምትላቸውን ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና ነጻነት ችላ ብሎ ከአምባገነኖች ጎን መቆሙ ሳያንስ አድናቂያቸው መሆኑ፤ እንደ መንግሥታቱ ድርጅትና ኔቶ ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ማጣጣሉ እና ዛሬ ድረስ ለማመን በሚቸግር ሁኔታ አሜሪካ ኮቪድ 19ን መከላከልና መቆጣጠር ተስኗት በወረርሽኙ ሕንድንና ብራዚልን አስከትላ በመያዝና በመሞት 1ኛ መሆኗ ዓለም ስለ አሜሪካ የነበረው አመለካከት እንደገና እንዲያጤን አስገድዷል።
“የጥቁር ሕይወት ይገደናል !”(Black Lives Matter)የሚለውን ተቃውሞና የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ አስመልክቶ ትራምፕ ያራምደው የነበረ የተለሳለሰና እርስ በርስ የሚጣረስ አቋም በአሜሪካውያን ዘንድ በተለይ በጥቁሮችና በሌሎች ህዳጣን ጥርስ እንዲነከስበትና እንዲናቅ አድርጎታል። ቻይናም የጆርጅ ፍሎይደን ነገር እየጠቀሰች አሜሪካን ስለሰብዓዊ መብት የዓለማችን ቃፊር የመሆን የቅስም ልዕለና የለሽም አረፈሽ ተቀመጭ እያለቻት ነው።
ከሁሉም በላይ የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ትራምፕ አልቀበልም ማለቱና የባይደንን አሸናፊነት አምኖ ሽንፈቱን አለማመኑ ይባስ ብሎ ደጋፊዎቹ ካፒቶል ሒለን ወረው ተነጠቀ ያለውን ድምጻቸውን እንዲያስመልሱ በተደጋጋሚ ወትውቶ የተፈጠረው ሁከት የዓለምን ሕዝብ ያስደነገጠ ነበር።
ክስተቱ የሰው ዘር በሙሉ ስለአሜሪካ የነበረውን በጎ ገጽታ እንደገና እንዲመረምር አስገድዶታል። ይህ የአሜሪካ የቁልቁለት መንገድ በጆርጅ ደብሊው ቡሽ የተጀመረ ነው። ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ልዕለ ኃያልነቷ ጉልበትም ሞገስም እየራቀው ይገኛል። ከጥንታዊው የሮማ አገዛዝ በላይ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት የነበረው የድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት የአሜሪካ ተጽዕኖ እየሟሸሸ መሆኑን የታዋቂው የየል ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ፓል ኬኔዲ ይስማማል። ኬኔዲ አያይዞ አሜሪካ አለማቀፍ የጸረ ሽብር ዘመቻውን የመራችበት አግባብና ሳትቋጭ እንደ ብላቴና በፊት በውጥን ያስቀረችበትን ማመንታት ሌላው የድክመቷ መባቻ አድርጎ ያሳያል።
የከሸፈው የጸረ ሽብር ዓለም አቀፍ ዘመቻ ገጽታዋን ከማጠልሸቱ ባሻገር ኢኮኖሚዋን ክፉኛ ጎድቶታል። የኒውዮርክ የሽርክና ገበያ እንዲወድቅ፤ ኢኮኖሚው እንዲንኮታኮት አድርጓል። ቻይና አጋጣሚውን ተጠቅማ እድገቷን ለማፋጠን ተጠቅማበታለች። ይህ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይና የዲፕሎማሲ የቁልቁለት ጉዞ የሐንስ ሞርጌንታው ደቀ መዝሙር የሔነሪ ኪሲንጀርን በነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲን ዳግም እንድንተገብር ያስታውሳል ይላል ሒሽ። የዓለማችንን ጅኦፖለቲካ ወቅታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ያስገባ ዲፕሎማሲ።
የሐንስ ንድፈ ሀሳብ የኪሲንጀር የዲፕሎማሲ ዋልታና ማገር የሆነውን በነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን መሠረት ያደረገ ነው። የቻይናን ተጽዕኖና ቀጣይ እጣ ፈንታ ከግምት ያስገባ ዲፕሎማሲ ያሻል ይላል። ቤሪ ጌዌኒ”The Inevitability of Tragedy” በተሰኘውና የሔኔሪ ኪሲንጀርን ሕይወትና የዲፕሎማሲ ፍልስፍና በገመገመበት መጽሐፍ ቻይናን የዘነጋ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሳሎን ውስጥ ያለን ዳይናሶር አላየሁም እንደማለት ነው ይላል።
ቤሪ ጌዌን ከፍ ሲል በተጠቀሰው መጽሐፍ በዓለም ላይ ሠላምና መረጋጋት እውን እንዲሆን የተበላሸውን የቻይናንና የአሜሪካን ግንኙነት ማስተካከል ያሻል ቢልም መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከዚህ ጋር የሚቃረን ነው። ሰሞኑን ባይደንና ዥን ያደረጉት የእስካይፕ ውይይት ያለ ውጤት የተቋጨው ለዚህ ነው። ትራምፕ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቻይናን ከማጠልሸት አልፎ በቻይና ላይ ተደራራቢ ቀረጥ በመጣል የዓለም የንግድ ድርጅት መርሆዎችን ጥሷል።
የኮሮና ቫይረስን የቻይና ቫይረስ እያለ በመጥራት ለሕዝበኝነት የፖለቲካ ፍጆታ አውሎታል። ዓለም ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ እንዲል፤ ጆ ባይደን ቻይና ምሳችንን እየበላች ነው ብሎ አርፎታል። ለአሜሪካ የሚገባውን ሲሳይ ቻይና በሕገ ወጥ መንገድ እየተጠቀመች ነው ለማለት መሆኑ ነው። የትራምፕም ሆነ የባይደን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሬት ላይ ባለ እውነታ የማይመራ ለመሆኑ ጥሩ አብነት ነው።
ለዚህ ነው ጌዌን አሜሪካ በ1970ዎቹ ማለትም በቬትናም ቀውስ፣ በአሜሪካ የእርስ በርስ ሁከቱ፣ ዋተርጌት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የሸመታ መቀዛቀዝና የሥራ አጦች ቁጥር መጨመር፣ ወዘተረፈ. ቀውሶች በተከሰቱበት ጊዜ እንደ መውጫና የማርያም መንገድ ሆኖ ያገለገለው የሔነሪ ኪሲንጀር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው መፍትሔው የሚለው። ዛሬም አሜሪካ ለምትገኝበት ቀውስ መዳኛው ወቅታዊውን ጂኦ ፖለቲክስ፣ የኃይልና የሥልጣኔ አሰላለፍን ታሳቢ ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነው። በዚህ ስብራት ነው እንግዲህ አገራችንን ጨምሮ አሜሪካ በዓለማችን ላይ እያራመደች ያለችውን ሸውራራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለመገምገምና ለመተንተን አበክሮ መዘጋጀት የሚገባው።
ከድህረ 2ኛው የዓለም ጦርነት አንስቶ በኋላም የቀዝቃዛውን ጦርነት በአሸናፊነት ለደመደመችው አሜሪካ ልዕለ ኅያልነቷን የሚገዳደር እንደ ቻይና ያለ ኃይል ሲመጣ መቀበል ይቸግራል። ይህን አለማቀፍ ነባራዊ ሁኔታ አምና ለመቀበል ዝግጁና ፈቃደኛ አለመሆኗ ነው እንግዲህ አሁን ለምትገኝበት ቅርቃር የዳረጋት። ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ እንደ ሱዛን ራይስ ያሉ የባይደን አስተዳደር ሰዎች ተጽዕኖ በመቀጠል አሜሪካ በአገራችን ላይ ጥርሷን እንድትነክስ ያደረገው ከቻይና ጋር የመሠረተችው ጥብቅ ወዳጅነት ነው። በመላው ዓለም ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታዋን በቻይና መነጠቋ ፤ በአፍሪካ በቀይ ባህርና በአባይ ተፋሰስ ላይ የነበራት የበላይነት ቋፍ ላይ መሆኑ የቆሰለ አንበሳ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ሙሌት አጠናቀቀች ማለት የአጋሯ የግብጽ ጅኦ ፖለቲካዊ ስፍራ አደጋ ይደቀንባታል ብላ ስለምታምን ኢትዮጵያን ማዋከብ የዲፕሎማሲዋ አካል አድርጋዋለች። በተፋሰሱ የኢትዮጵያ የበላይ ሆኖ መውጣት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግብጽ ከአሜሪካና ከእስራኤል ተጽዕኖ ይልቅ በኢትዮጵያው ተጽኖ ስር ልትወድቅ ትችላለች ብላ ስለምትሰጋ ከግብጽ ጋር በመቆም የእስራኤል ጥቅም ማስቀጠል መርጣለች። ይሄን ስታደርግ ግን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የማልማትና የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላት ጠፍቷት አይደለም። ሒሽ አሜሪካ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር ተናጥባለች የሚለውም ይሄንን ነው።
#በቃ !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2014