(ክፍል ሁለት)
ወዳጅ ሲበዛ ጠላት ይቀንሳል፤
በዚሁ ጋዜጣ የትናንትናው ዕትም ላይ ለተከታታይ ጽሑፎቼ የተዋስኩትን “የካሮትና ዱላ” ምሳሌያዊ የትመጣ፣ አስተሳሰቡንና ብሂሉ የተሸከመውን የፖለቲካዊ ሴራ መርህ በአጭሩ ለማሳየት ሞክሬያለሁ።ከመጋረጃ በስተጀርባ ያሉት የመርሁ ዋና ዋና አስፈጻሚ ተዋንያት እነማን እንደሆኑም ሁለቱን እንስት የአሜሪካ “ዱላ ወዝዋዥ” ሹመኞች ስም ጠቅሼ ለአብነት አስታውሼያለሁ።በሉዓላዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ ሲሸረብ የኖረው የተራቀቀ ሴራም ምን መልክ እንዳለው ለማሳየት ጥረት ተደርጓል።
እንደ ሀገሯ አውዳሚ የሱናሚ ሞገድ የዓለም ሀገራት በጤና ውለው እንዳያድሩ አመጽና ክፋት በመጎንጎንና በማስፈጸም እንቅልፍ አጥታ ስለምታድረው አሜሪካ ይሏት ሀገር በቀሩኝ ጥቂት ጉዳዮች ላይ መጠነኛ ዳሰሳ ላድርግ።በተለይም ከሀገሬ ጋር የነበራት “የረጅም ዘመናት የወዳጅነት” ትስስር ምን መልክ እንደነበረው “እነርሱ ቀልባቸውን እንዲያነቁ” አንባብያን ደግሞ እውነቱን እንዲረዱ በድርበቡ አንዳንድ ታሪካዊ ክስተቶችን አስታውሳለሁ።
የዛሬው ሴራቸው እየከሸፈ ያለውም እውነታችን አሸናፊ፣ ትምክህታችን ጽናታችን መሆኑን በግልጥ ቋንቋና “ባልተሽኮረመመ ድፍረት” አስረግጠን እንነግራቸዋለን። ወዳጅነቱን በጠላትነት ለውጠው ከብጤዎቻቸው ጋር ቢፈትኑንም “መከራችን” ብዙዎቹን ነባር ወዳጆቻችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ አብረውን እንዲቆሙ ምክንያት መሆኑንና አዳዲስ ደጋፊዎችም “አለንላችሁ!” ብለው ከጎናችን መቆማቸውን ሳንሸማቀቅ እናስረዳቸዋለን።“በፖለቲካ ፍጹም ጠላት፤ ፍጹምም ወዳጅ የለም!” በማለት ቀምረው ለዓለም የረጩትን መርህ መለስ ብለው እንዲያጤኑትም እንመክራለን።ይልቅዬ “ወዳጅ ሲበዛ የጠላት ጉልበት መሽመድመዱን” ቢገነዘቡት አይከፋ፡፡
ታሪክ እንዲህ ያስታወሰናል፤
የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት በይፋዊ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት መሠረት የተጣለው እ.ኤ.አ አቆጣጠር ዲሴምበር 27 ቀን 1903 ዓ.ም ሮበርት ስኪነር የተባሉ የአሜሪካ መንግሥት የልዑካን መሪ ከዳግማዊ አጤ ምኒልክ ጋር የንግድ ስምምነት ፊርማ በአዲስ አበባ ተገኝተው ከተፈራረሙና ከተግባቡ በኋላ ነበር።ከሦስት ዓመታት በኋላ ጁላይ 6 ቀን 1909 ዓ.ም ቆንስል ሆፍማን ፊሊፕ የሹመት ደብዳቤያቸውን በይፋ ካቀረቡ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ይበልጥ እየደመቀ መሄድ ጀመረ።ድምቀቱ ያለመደብዘዙን ከሚያመለክቱት ጉዳዮች መካከል የቀዳሚው የኤምባሲው መቀመጫ ጽ/ቤት ይገኝበት የነበረው አካባቢ (ከአንዋር መስጊድ ዝቅ ብሎ) ዛሬም ድረስ “አሜሪካ ግቢ” እየተባለ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዜጎች አፍ ሲጠራ መዋሉ ነው፡፡
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እ.ኤ.አ ከ1954 – 1973 ለስድስት ያህል ጊዜያት በኦፊሴል የሥራ ጉብኝት አሜሪካንን በተደጋጋሚ ሲጎበኙ ከየትኞቹም የዓለም መሪዎች ይልቅ በከፍተኛ ክብርና ሞገስ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር።ፕሬዚዳንት ኬኔዲ በተገደሉበት ዓመት በ1963 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ አሜሪካን የሄዱት በወዳጃቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ነበር።ሦስተኛውን ኦፊሴላዊ ጉብኝት አድርገው ከተመለሱ አንድ ወር ብቻ ቆይተው ዳግም መመለሳቸው የወዳጅነታቸው ጥግ ምን ያህል የጠነከረ እንደነበር ጥሩ ማሳያ ነው።በእኛውስ ዘመን ቢሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የሚገኘው የኬኔዲ ላይብረሪ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ተማሪዎች በየዓመቱ እየተጎበኘ ዕውቀት እየተቀሰመበት አይደል።በአካዳሚያ ዙሪያ ያለን የቆየ ወዳጅነት ስፋቱ የጠለቀ ነው፡፡
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከ1994 – 2002 ለሦስት ያህል ጊዜያት (ሁለቴ ለሥራ ጉብኝት፤ አንዴ ከበርካታ አፍሪካዊያን መሪዎች ጋር በፕሬዚዳንት ክሊንተን የራት ግብዣ ላይ) ተገኝተው ነበር።ከደርጉ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር ግን አሜሪካና ኢትዮጵያ ዐይንና ናጫ ስለነበሩ ከወቅቱ መሪዎች ጋር እንኳንም በአንድ ጠረጴዛ ተገናኝተው “ቡና ሊገባበዙ” ቀርቶ በደግ እንኳን እንደማይፈላለጉ ብዙ ታሪካዊ አጋጣሚዎችን በመጠቃቀስ ማስታወስ ይቻላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአሜሪካ የተገኙት ከየትኛውም የሀገራችን መሪዎች ይልቅ የሰላም ዘንባባ እያውለበለቡ ነበር።በዚያ ምድር የሚኖሩ የኢትዮጵያን ልጆች ለማቀራረብና ወደ ሀገራቸው ገብተው በምድራቸውና በሕዝባቸው መካከል እንዳሻቸው ሠርተውና ከብረው እንዲኖሩ፣ ካሻቸውም ያለምንም መሳቀቅ ወለል ብሎ በተከፈተላቸው የሀገሪቱ በር ዘመድ አዝማድ ጠይቀውም ሆነ ጎብኝተው መመለስ እንደሚችሉ “ኑ! ከአዲሱ መንግሥት ጋር ተባብረን እንስራ!” የሚል መልእክት ለማድረስ ነበር። ድልድዩን ጠግነው፤ ጎዳናውን ለማስፋት።
ይህን መሰሉ ከመቶ ሃያ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት ብዙ መደጋገፎችና ብዙ ተግባራት የተከናወኑበት እንደነበር ለመተንተን የጋዜጣው የገጽ ውሱንነት ገድቦን እንጂ በተከታታይ ቅጾች የሚሰነድ ታሪክ ማስታወስ በተቻለ ነበር።የዛሬ መሪዎቿ እየናዱ ያለው ይህንን ግንኙነት ነው።በእርዳታና በልማት ስም የሚወረውሩልንን “ካሮት” ከታሪካዊ ፋይዳ አስበልጠው ማየታቸውም የሀገሪቱ የወቅቱ መሪዎች ምን ያህል የተንሸዋረረ አመለካከት እንዳላቸው ጥሩ ማሳያ ነው።
ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸው የግንኙነት መርህ “በዱላቸው ጥንካሬ ብቻ እንደሚወሰን” እያሰቡ መቃዠታቸውም ገና እንቅልፋቸውን ያልጨረሱ ፖለቲከኞችና ሹመኞች በሥልጣን ኮርቻ ላይ ወጥተው የመፈናጠጥን ዕድል ስላገኙ ይመስላል።ከአሁን ቀደም ለተደረገልን ድጋፍም ሆነ በጎነት የማናመሰግን አደራ በል እንዳልሆንን በተገቢው መንገድና መድረክ ተደጋግሞ ተገልጾላቸዋል።የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ንፋስ እንዲገባው እንደማይፈልጉም አጽንኦት ተሰጥቶ ተረጋግጦላቸዋል።ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ከአሜሪካ መንግሥትና ሕዝብ ጋር በፍጹም ለመቆራረጥ ሳይሆን በመከባበርና ተደጋግፎ ለመጓዝ ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውን በብዙ ማስረጃዎች ማስረገጥ ይቻላል፡፡
እንደ አንድ ታላቅ ሉዓላዊ መንግሥትና ሕዝብ የምንጠይቀው አንድና አንድ ጉዳይ ብቻ ነው። “ከካሮታቸው” ቆንጥረው ሊሰጡን የሚፈልጉትን እርዳታና ድጋፍ “በዱላቸው” እያስፈራሩ አይፎክሩ። የአጎዋን ፕሮግራም ወይንም የልማትና የአጋርነት ድጋፋቸው ተጠቃሚ ለመሆን የምንፈልገው በ“እንካ በእንካ (win win)” መርህ መሠረት እንጂ እኛ ለማኝ እነሱ ተለማኝ በመሆን እንዳልሆነ ሊገነዘቡት ይገባል።
ቢቻል ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር አብረውም ሆነ አሲረው ሉዓላዊነታችንን ባይዳፈሩ እንመክራለን።የእኛኑ እኩያን “የእንግዴ ልጆች” በግላጭ እያሰባሰቡም ሆነ በድብቅ እያሴሩ ለጥፋት ተልዕኮ ባያሰማሯቸው መልካም ነው።ከጥሮ ግሮ ነዋሪዎቻቸው የሚሰበስቡትን ታክስና ግብር ለአመጽ ማስፋፊያ፣ ለሴረኞች ጥፋት፣ ለሆድ አደር ሚዲያዎች እየረጩ ሰላምም እንቅልፍም እንዳይነሱን “በሕግ አምላክ!” በማለት እንሞግታቸዋለን።ዘመናዊነትንና ሥልጣኔን ለእርሷ ብቻ፤ “ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ”ን መርህ ለግሏ እንደሆነ እየቆጠረች ያለችው አሜሪካና መሪዎቿ ምን ያህል ከዘመኑ አስተሳሰብ በንግግር እንጂ በተግባር እየራቁ እንዳሉ እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለምም እየታዘባቸው እንደሆነ ያውቁት ይሆን ?
ከግል ማስታወሻ ትዝታዎቼ፤
እ.ኤ.አ ኖቬምበር 7 ቀን 2000 ዓ.ም በመላው አሜሪካ የተጧጧፈው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ በአጋጣሚ በዚህቺው ሀገር የሚኒሶታ ክፍለ ግዛት ተማሪ ስለነበርኩ የትዕይንቱ የዓይን ምስክር ለመሆን ዕድሉ አጋጥሞኝ ነበር።በዲሞክራቱ ተወዳዳሪ በሚ/ር አል ጎር እና በሪፐብሊካኑ ሚ/ር ጆርጅ ቡሽ መካከል የነበረው ከፍተኛ ትንቅንቅ አሸናፊው ማን ሊሆን እንደሚችል ለመተንበይ እንኳ ፈታኝ ነበር፡፡
በተለይም የእኔ መኖሪያ በነበረው የመንትያ ከተሞች ክፍለ ግዛት ውስጥ የታየው እልህ አስጨራሽ ፉክክር የጋለ እንደነበር በሚገባ አስታውሳለሁ።የዲሞክራሲው ጡዘት በከረረበት በዚህ ወቅት እጅግ ያስገረመኝ ጉዳይ በዚያ ክፍለ ግዛት ነዋሪ የነበሩት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን (ዜግነት ይኑራቸውም አይኑራቸው) ለዲሞክራቱ አል ጎር ያሳዩ የነበረው ድጋፍ ነበር።በታክሲ ማሽከርከር ሥራ ላይ የተሠማሩ ወገኖቻችን በሙሉ የክፍለ ግዛቱን መራጮች በነፃ ለማጓጓዝ ተስማምተው ሙሉ ቀን መኪኖቻቸውን ለአገልግሎት አሰማርተው አውለው ነበር።በተለያዩ ሙያ ላይ የተሰማሩትም እንዲሁ በቅስቀሳም ሆነ በገንዘብ አሰባሰብ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም፡፡
ለእኔ መሰሉ አዲስ መጤ ኢትዮጵያዊ በተለየ ሁኔታ ለዲሞክራቱ ዕጩ የተደረገው ያን ዓይነት ልባዊ ድጋፍ ግርታን መፍጠር ብቻም ሳይሆን “ዕንቆቅልሽ” እንደነበር አስታውሳለሁ።ለምን ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ለዲሞክራቶች ድል ያን ያህል ዋጋ ሊከፍሉ ፈቀዱ? ኢትዮጵያዊያን ብቻም ሳይሆኑ የበርካታ ሀገራት “ዲያስፖራዎችም” ለምን ልባቸው ለተወዳዳሪው እጩ ፕሬዚዳንት አል ጎር ሊያደላ ቻለ? ምክንያቱን ዘልቆ ለማወቅ አዋቂዎችን በመጠየቅና የሁለቱን አውራ ፓርቲዎች የፖለቲካና የፖሊሲ ልዩነት መመርመር የጀመርኩት ከዚያን ዕለት በኋላ ነበር፡፡
አንዱ የአህያ ውርንጭላ ሌላኛው የዝሆንን ምስል መለያቸው በማድረግ ሲፋተጉ የኖሩት ሁለቱ ፓርቲዎች በተካረሩ የፖሊሲ አተገባበሮች ላይ የጎሉ ልዩነቶችን በማንጸባረቅ ነው።አንደኛው የታክስ አከፋፈሉ እንደ ዜጎቹ የገቢ መጠን ከፍና ዝቅ ይበል ሲል ሌላኛው ፓርቲ ባለገንዘቦቹን ሀብታሞች አታበሳጩብኝ በማለት ጫናው ደሃው ላይ እንዲወድቅ ይታገላል።አንደኛው ፓርቲ ማሕበራዊ ተራክቦውና ተጠቃሚነቱ በብዙኃን ስብስብ ላይ ይሁን ሲሉ ሌላኛው “እንዴት ሲደረግ ፍትሕና ርትዑ በግለሰቦች መብትና ግዴታ ላይ መንጠልጠል አለበት” እያለ ይሞግታል።አንደኛው ፓርቲ በመጻተኞችና በባዕዳን የውጭ ዜጎች ላይ ለስለስ ያለ አቋም ሲይዝ አንደኛው ምን ሲደረግ “ባዕድና ጨለማ አንድ ናቸው አይታመኑም” በሚል መርህ መጤዎች ላይ ጫና ያሳርፋሉ።ዝርዝሩ ብዙ ነው።
ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ወደ ዴሞክራቶች እንዲያዘነብሉ ያደረጋቸው በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን ይሻላል ብለው በመረጡትና “ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ” በሚለው የሀገራቸው ብሂል መሠረት እንደሆነ ለመገንዘብ ችያለሁ።እውነትም እንደተረባረቡት በዚያ የሚኒሶታ ክፍለ ግዛት ዴሞክራቱ አልጎር በማሸነፋቸው የእኔዎቹ ዘመዶች ሌሊቱን ሙሉ ሲጨፍሩ ማንጋታቸውን አስታውሳለሁ።ካልተሳሳትኩ በስተቀር እኔንም ሳያሳትፉኝ አልቀሩም፡፡
የሀገሬ ልጆች ለዲሞክራቶች ያላቸው ወገንተኝነት ተሸርሽሮ አልቆ ወደ ሪፐብሊካኑ ፊታቸውን ያዞሩት የወቅቱ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ለምድራቸው ሕመም ጥዝጣዜውን ስላበዙባት እንደሆነ በተግባር በማረጋገጣቸው ነው።ማረጋገጫውም በቅርቡ በተደረገው የቨርጂኒያ ክፍለ ግዛት ምርጫ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን በዘመቻ ወጥተው ዲሞክራቱን ቴሪ ማክአውሊፍ ከውድድር ውጭ አድርገው ሪፐብሊካኑ ግሌን ዮንግኪን መንበረ ሥልጣኑን እንዲቆጣጠሩ ማድረጋቸው በአድናቆት እየተገለጸላቸው ነው።ይህ ውጤት በነገው የአሜሪካ የፖለቲካ አካሄድ ላይ ሊኖረው የሚገባው ተጽእኖ ምን ያህል ሊበረታታ እንዲሚችል ጥሩ ማሳያ ነው። ልብ ያለው ልብ ያድርግ!
አሜሪካ በመስከረም አሥራ አንዱ ጥቃት የአሸባሪዎች መከራ በዘነበባት ዕለት ይህ ጸሐፊ በዚያው ምድር ስለነበረ ከአሜሪካና ከወዳጆቹ ጋር አብሮ የእምባ መዋጮ በማድረግ ልባዊ ሀዘኑን ለመግለጽ ችሎ ነበር።አሜሪካ በንዴት ጦፋ በአጥፊዎቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ስትጣደፍም “ተገቢ ነው!” በማለት አቋሙን ገልጾ ነበር።ያቺ ለራሷ ክብር ስትጋደል የኖረችው አሜሪካ ይሏት ሀገር ዛሬ የእኔይቱ ሀገር በአሸባሪዎች ተደፍራ የግፍ ዓይነት ሲዘንብባት “ከደም አፍሳሾቹ የዲያቢሎስ ውላጆች ከትህነግ ትርፍራፊዎች” ጋር አባሪ ተባባሪ ሆና “ማንን ፈርቼ” በሚል ድፍረት ፊት ለፊት ስትደግፋቸው ማስተዋል በእነርሱ ቋንቋ ትዝብት ውረሱ “Shame on you!” ብለን የምናልፍ ብቻ እንዳይመስላቸው ቢያውቁት አይከፋም።
“ተደራደሩ፣ ጊዜያዊ መንግሥት፣ ቅብጥርሴ!” የሚሉትን ጉትጎታ ቢያቆሙ የሚሻል ብቻ ሳይሆን በግዴታም ጭምር ከዚህ መሰሪ ሴራ እንዲታቀቡ ደግመን ደጋግመን እንገልጽላቸዋለን።ግድ ካሉንም ሃሳባቸውን የምናጤነው እነርሱ አሸባሪዎች ብለው በዝርዝራቸው ውስጥ ከያዟቸው ከአልቃይዳ፣ ከአይ.ኤስ.አይ.ኤስ ቡድን (ባንግላዲሽ፣ ፊልፒንስ፣ ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት)፣ ከአራካት ሳውድ ሚዝር፣ ከኢስላሚክ ሪቮሊዩሽን ጋርድ፣ ከኢዝቦላ ሙጃሂዲን፣ ከቦኩ ሀራምና መሰል በርካታ ቡድኖች ጋር እርቅ ፈጽመው ሲጨባበጡ ስናይ ነው።ያለበዚያ ክብራችን “ከካሮታቸው”፣ የሉዓላዊነታችን ብርታትም “ከማስፈራሪያ ዱላቸው” እንደሚበልጥ ሊገነዘቡት ይገባል።“ይብቃ! No More!” እያሉ ዜጎቻችንና ወዳጆቻችን በመላው ዓለም ድምጻቸውን እያስተጋቡ ያሉትም እውነታችን ግድ ስላለንና ስላላቸው ነው።የኢትዮጵያ እውነት ያሸንፋል
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2014