የወደቁትን አንሱ የነዳያን ማኅበር መስራች አቶ ስንታየሁ አበጀ ይባላሉ ትውልዳቸው በደቡብ ጎንደር አካባቢ ነው። እናታቸው ገና በስድስት ዓመታቸው ያረፉ ሲሆን በርካታ ህመሞችም ነበሩባቸው። በ1981 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ የመጨረሻውን ፈውስ በሐመረ ኖህ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት በጸበል እስኪያገኙ ድረስ ያልሞከሩት ህክምና አልነበራቸውም። ማኅበሩን ለመመስረት ያበቃቸውን አጋጣሚ የተከሰተበት ግን የሚከተለው ጉዳይ ነበር። አቶ ስንታየሁ በተለያዩ ጊዜያት የጤና መታወክ እክል ገጥሟቸው የሚያውቁ ቢሆንም በ1989ዓ.ም የገጠማቸው ግን ከፋ ያለ ነበር። የገጠማቸው ህመም አካላቸውን ማንቀሳቀስ የማይችሉ ፓራላይዝድ አድርጓቸው ነበር። በወቅቱ በቅርብ የሚደግፋቸው ዘመድም ሆነ ወዳጅ ስላልነበራቸውና ወደየትም ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ሰው እስኪጸየፋቸው ድረስ በከፋ ስቃይ ውስጥ ነበሩ።
እናም ነግቶ በጠባ ወይ አልፈወስከኝ ወይ ከጎኔ የሚቆም ረዳት አልቸርከኝ እያሉ ፈጣሪያቸውን ያማርሩ ነበር። አንድ ቀን ግን አንተስ በቁመናህ ምን ሰራህ የሚል ምላሽ በሰመመን ወስጥ እያሉ ይደርሳቸዋል። ለካ ከዛ በፊት እኔም እንደኔ ራሳቸውን ችለው መብላት መጠጣት መጸዳዳት መንቀሳቀስ የማይችሉ ብዙዎችን እያየሁ ሳልፍ ቆይቼያለሁ። የሚረዳቸውም አላየሁም ነበር ብለው ራሳቸውን ይወቅሳሉ። በዚህም ፈጣሪዬ ጤናዬን መልሰህ የአስራ አምስት ቀን አድሜ ስጠኝና የተራቡትን አብልቼ የተጠሙትን አጠጥቼ የታረዙትን አልብሼ የተኙትን አገላብጬ የሞቱትን ቀብሬ ልለፍ ብለው እንደስለት ይናገራሉ። በወቅቱ እንኳን መንቀሳቀስ በሥርዓት መገላበጥ ለማይችሉት አቶ ስንታየሁ አስራ አምስት ቀን ብዙ ነበር።
የፈጣሪ ነገር ሆኖ በዛው ወቅት ጤናቸው በጸበል ለመስተካከል ይበቃል። ነገር ግን እሳቸው ለፈጣሪያቸው የገቡትን ቃል ለመጠበቅ ሥራውን ቢጀምሩም ነገሩ ሁሉ እንዲህ አልጋ በአልጋ ሳይሆንላቸው ይቀራል። የሚኖሩት እንጦጦ ሐመረ ኖህ ኪዳነምረት አካባቢ በመሆኑ በርካታ ድጋፍ የሚሹ አረጋውያን በአካባቢው ነበሩ። እናም በእሳቸው አቅም በቀላሉ የሚገፋ አልሆን ይላቸዋል። ምን አልባት የኔ ሃሳብ ተጋሪ ባገኝ ብለው ረዳት ቢፈልጉም የአካባቢው ነዋሪዎች የእሳቸውን ሁኔታ ያውቁ ስለነበር «ራስ ሳይጠና ጉተና፤ ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት» እያሉ ይቀልዱባቸዋል። እሳቸው ግን የአቅማቸውን በማድረግ ሥራቸውን ይቀጥላሉ። አንድ ቀን ግን የግድ ሰው ያስፈልጋቸውና በመንገድ ያገኟቸውን ወጣቶች ድጋፍ ሲጠይቁ ሰርተህ ብላ ብለው ያቧርሯቸዋል።
ለጊዜው ሸሽተው ቢሄዱም ተስፋ ባለመቁረጥ ሌሎች አስራ አራት ዓመት የሚሆናቸውን ሁለት ልጆች አግኝተው በድጋሚ ትብብር ሲጠይቁ ልጆቹ ፈቃደኛ ይሆኑላቸውና ሥራ ይጀምራሉ። ይህም ሆኖ ሄደን ማየት አለብን ብለው ልጆቹን ያዩና አብረው ለመስራት ይስማማሉ። አቶ ስንታየሁ ግን ቀጠል አድርገው ሶስት ነገሮችን ለመሥራት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ይነግሯቸዋል።
አንደኛ የወደቁትን ማንሳት ሁለተኛ የሞቱትን መቅበር ሶስተኛም የተቸገረን መርዳትን ሰዎችን በማስተማር ማንቃት መሆኑን ይነግሯቸዋል። ከዛን ጊዜም አንስቶ እነዚህ ካሳሁን ከበደና፤ ንጉሴ ሀብታሙ የተባሉ ወጣቶች፤ በዛን ኤች አይ ቪ ከምንም በላይ በሚያስፈራበት ወቅት የወደቁትን እያነሱ፤ ቁስላቸውን እያከሙ፤ ልብሳቸውን ወንዝ አውርደው ያጥቡ ነበር። በዚህ ሁኔታ ካለምንም ጥሪት በመልካም እሳቤ ብቻ የተጀመረው ስራ በ1993 ዓ.ም ሶስት ሕጋዊ ፈቃድ በማግኘት ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅቷል።
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሀረገወይን ሃይሌ ማኅበሩን የተቀላቀሉት በ1992ዓ.ም በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ነበር። በ1993 ዓ.ም ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ያለውን የማኅበሩን እንቅስቃሴ እንደሚከተለው አስቃኝተውናል። ማኅበሩ በብዙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ካለፈ በኋላ ጥቅምት ሃያ አንድ ቀን 1993ዓ.ም ከሚመለከተው አካል እውቅና ለማግኘት ይበቃል። ችግረተኞቹ ይሰበሰቡ የነበሩት በቤተክርስቲያኒቷ አካባቢና በመቃብር ቤት ይኖሩ የነበሩት ናቸው። ለማእከሉ አብዛኛውን ድጋፍ ያደርጉ የነበሩትም እንጦጦ ሀመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስትያን ይሳለሙ የነበሩ ምእመናን ናቸው።
በተለይ ነሀሴና የካቲት አስራ ስድስት ዓመታዊ በአል ስለነበር ጥሩ ድጋፍ ይሰበሰብ ነበር። የሚገኘውም ገቢ በአብዛኛው ከጥቂት ሰው ብዙ ገንዘብ ሳይሆን ከብዙ ሰው በትንንሹ የሚሰጥ ብዙ ገንዘብ ነበር። ከእነዚህም መካከል እንጨት ለቅመው የሚተዳደሩ እናቶች፤ የኔ ቢጤዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ድጋፉ ይደረግ የነበረው ደግሞ በቤተክርስቲያኒቷ አንድ ባለሀብት ሰርተውት በነበረና ረዥም ዓመታትን ባስቆጠረ መጠለያ ውስጥ ነበር። ቀድሞ መጠለያው ለነዳያኑ መዋያ ብቻ የነበረ ቢሆንም ማኅበሩ ማደሪያም እድርጎ ሲጠቀምበት ይቆያል። ነገር ግን ሕጋዊ አውቅና ባገኙበት ዓመት ቤተክርስቲያኒቷ ቦታውን ለልማት ስለፈለገችው መልቀቅ የግድ ሆነ።
ነገር ግን አባላቱ ምንም ገቢ ባይኖራቸውም በድፍረት ከአንድ ግለሰብ ሶስት ክፍል ቤት እዛው አካባቢ በ120 ብር ይከራያሉ። ቤቱ ዛሬም ድረስ አስራ ሁለት ሺ ብር እየተከፈለበት እያገለገለ ይገኛል። በዚህ ሁኔታ ቆይተው በ2000 ዓ.ም የነበሩት የቀበሌ አመራሮች ደግሞ ስራቸውን አይተው አንድ የቀበሌ ቤት ይሰጧቸዋል። ከዚህ ወቅት አንስቶ ማሕበሩ በቦርድ መተዳደር ጀምሮ ነበር። ባጠቃለይም ለቢሮና ለእቃ ማስቀመጫ በዝቅተኛ ሂሳብ ከተከሯዩዋት ጋር ሶስቱን ክፍል ይዘው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ።
ከዚህ በኋላ ደግሞ በቀበሌው በኩል አንዲት የመንግሥት እርሻ ወስጥ ትሰራ የነበረችና ከቤቷ የተገለለች መንቀሳቀስ የማትችል ሴት የነበረችበትን እሷንም እንዲንከባከቡ ተደርጎ ይጨመርላቸዋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሌላ ወንዝ ዳር የነበረ ቤት በከፊል በመፍረሱ ነዋሪዎቹ ወደ ሌላ ተዛውረው የቆሻሸ ማከማቻ ሆኖ የተቀመጠ ነበር። ቀበሌውም ይህንን ቤት አጽድተው እንዲጠቀሙ እንዲፈቀድላቸው ያደርጋል። ፈቃዱን ካገኙ በኋላ ለማስገንባት ሕብረተሰቡን ማስተባበር ሲጀምሩም አንድ ኢንጂነር ቤቱን አድሰው ጣጣውን ጨርሰው ያስረክቧቸዋል።
በዚህ ሁኔታ ስራቸውን እያስፋፉ ቢሄዱም የትራንስፖርት ችግር አገልግሎታቸውን ይፈታተን ነበር። አረጋውያኑ አብዛኛዎቹ የጤና እክል የነበረባቸው በመሆኑ ለህክምና ማመላለሱ እጅግ አስቸጋሪ ነበር። በተጨማሪ የተጠናከረ አገልግሎት ለብዙዎች ለመስጠት ሕንጻ መገንቢያ ቦታ ለማግኘትም መንቀሳቀሳቸችውን ይቀጥላሉ። መኪናውን በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በመሄድ ለማግኘት ቢሞክሩም ያልተሳካላቸው በመሆኑ እንደለመዱት ሕብረተሰቡን ወደ ማስተባበር ይዞራሉ። በዚህ ወቅትም በተመሳሳይ ከጥቂት ሰዎች ብዙ ብር ሳይሆን ከብዙ ሰዎች ጥቂት ጥቂት ብር አግኝተው በ2001 ዓ.ም አንድ ተሽከርካሪ ለመግዛት ይበቃሉ።
ከዚህ ቀጥሎ የነበሩት ቤቶችም በተደራጀ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት የሚያበቁ ስላልነበሩ አንድ ሕንጻ ውስጥ ለመሰብሰብ የራሳቸው ቦታ ለማግኘት መንቀሳቀሱን ይቀጥላሉ። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አቶ ኩማ ደመቅሳ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት በ2004 ዓ.ም የካቲት አስራ ሰድስት ቀን ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ ሃያ አምስት ካሬ ሜትር ቦታ ከሊዝ ነጻ ካርታው በአዲስ አበባ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ስር ሆኖ ይሰጣቸዋል።
አባላቱ ወደ ወደ ቀጣይ ስራቸው በማምራት ሕንጻ ለማሰራት መሰረቱ እንዲጣል ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች እንዲኖሩ ለማድረግ በማሰብ አምስት ወር ቢሞክሩም የተለያዩ ምክንያቶች እየፈጠሩ የተጋበዙት በሙሉ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ። ከቦርዱ ጋር በመነጋጋርም አንድ አባባ መኮንን ብሩ የተባሉ ከንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ጀምሮ የነበሩ አርበኛ አባቶችን ወክለው፤ አንዲት ሃምሳ ዓመት በቤት ሰራተኝነት ያገለገሉ እማማ ማሚቴ ገብረማርያም የሚባሉ እናት እናቶችን ወክለው፤ እንዲሁም ደምለው አስማማው የተባለ አካል ጉዳተኛ ወጣትን እንዲወክል ተደርጎ የክብር እንግዳ በማድረግ ጥር ሃያ አምስት ቀን 2005 ዓ.ም የሕንጻውን የመሰረት ድንጋይ ያስቀምጣሉ። ከዚህ በኋላ ከመንግሥት በኩል ያለው ነገር በሙሉ ተጠናቆ የካቲት 2006 ዓ.ም የሕንጻው ግንባታ ተጀመረ። በወቅቱ ማሕበሩ ቦታውን ሲረከብ የነበረው አንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺ ብር ብቻ ሲሆን ስምንት መቶ ሺ ለፕሮጀክት፤ አምስት መቶ ሺ ለግንባታ መነሻ ተደርጎ ነበር።
ከዚህ በኋላ የተሰበሰበውን ጨምሮ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ይዘው ሰላሳ ሁለት ሚሊዮን ብር በወቅቱ ግምት የሚጨርሰውን ሥራ ፈጣሪንና ሕዝባቸውን ከፊት በማስቀደም ይጀምሩታል። ሰውም ይህንን ሲመለከት ጠንካራ ትበብር በአይነትም በገንዘብም ድጋፍ እያደረገ በ2008 ዓ.ም ሕንጻው በከፊል ለመጠናቀቅ በቃ። በተመሳሰይ ወቅት እንጦጦ ሐመረ ኖህ ቤተክርስቲያን ስር የነበረውና አርባ አረጋውያን የነበሩበት ቤት በመንገድ ግንባታ ምክንያት እንዲፈርስ ተደረገ።
አባላቱ ሕንጻው ሳይጠናቀቅ ላለመግባት በነበራቸው ፍላጎት ቤት ሲያፈላልጉ ቢቆዩም ለአንድ ቤት እስከ ሃምሳ ሺ በመጠየቃቸው በሚያዚያ ወር 2008ዓ.ም ባላለቀው ሕንጻ ስራቸውን ለመቀጠል ይገደዳሉ። በዚህ ሁኔታ አልፎም ታህሳስ ሃያ አንድ ቀን 2010 ዓ.ም ሕንጻው ሙሉ ለሙሉ ለመጠናቀቅ ይበቃል። ሕንጻው ለአረጋውያኑና ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚያገለግል የጤና ክሊኒክ ደረጃውን የጠበቀ የዊልቸር መወጣጫ (ራምፕ) በእያንዳንዱ ወለል ሻወርና መጸዳጃ ቤት ባጠቃላይ አንድ ዘመናዊ የአረጋውያን መጦሪያ ሊኖረው የሚገባውን በሙሉ ያካተተ ነው።
«ማኅበሩ እንደ መርህ ኢትዮጵያውያን፤ ለኢትዮጵያውያን በሚል እሳቤ ያምናል፤ ይህም በመሆኑ በዋናነት ድጋፉን የሚያገኘው ከኢትዮጵያውያን ሲሆን ከእነዚህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ከሚገኙት ነው»። ያሉን ደግሞ የማኅበሩ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ገብረስላሴ ናቸው። አቶ ግርማ የማኅበሩን አሁናዊ እንቅስቃሴ አስመልክተው እንዳብራሩልን በማእከሉ የምግብ የልብስ የመጠለያ የሥነ ልቦና የፊዚዮ ቴራፒና ከቤተሰብ የማቀላቀል አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
ማኅበሩ በመስከረም አንድ ቀን 1990 ዓ.ም ከተመሰረተበት ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጉዞ 983 ወንዶችና 1017 ሴቶች በአጠቃላይ 3017 ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ከእነዚህ ውስጥ 241 ሰዎች ድነው 4 ሰዎች በድርጅቱ ውስጥ ተቀጣሪ ሠራተኛ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በተለያየ የሥራ መስክ ተሰማርተው እራሳቸውን በመርዳት ላይ ይገኛሉ። የፈጣሪ ነገር ሆኖ 265 ሰዎች ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በያሉበት በተለያዩ ጊዜያት የምግብ፣ የአልባሳት፣ የንጽህና እቃዎችና የሕክምና ድጋፍ ያገኙም ቁጥራቸው ከ1000 በላይ ተጠቃሚዎች አሉ።
በቀጣይም አረጋውያንን በማእከል በመርዳት ችግሩ የሚቀረፍ ባለመሆኑ የአረጋውያን እንክብካቤ ሙያ ሥልጠና ለመስጠት ከኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ፈቃድ አግኝቶ አንድ መቶ ሺ ብር በማውጣት የኮርስ ቀረጻ እየተከናወነ ይገኛል።
ሠልጣኞች የሶስስት ወር ሥልጠና ወስደው ከማእከሉ ተመርቀው ሲወጡ በድርጅቶች ብቻ ሳይሆን በየቤቱ ቤተሰብ እየከፈላቸውም ሆነ በድጋፍ አድራጊዎች አረጋውያንን መንከባከብ ይሰራሉ። ከዚሁ ጋር በተያየዘ ማኅበሩ ባለው ክፍት ቦታ ሁለተኛ ሕንጻ ግንባታ አከናውኖ በአገሪቱ የመጀመሪያውን ለአረጋውያን ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል ለማቋቋም እቅድም አለው። ለዚህ ደግሞ በርካታ በጎ ፈቃድ ሀኪሞች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል። ለቀጣይ ዘላቂ የገቢ ማስገኛ እንዲኖር ከትምህርት ቤቱ በተጓዳኝ የዳቦ ምርት፤ ሽመና ለመስራት እቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል።
«መልካም ሥራ የክፉ ቀን ስንቅ ነው» በሚል መሪ ቃል እየተንቀሳቀሰ ያለው ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት 200 በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ወደ ጎዳና እንዳይወጡ 100 የደሃ ደሃ በተመላላሽ በቀን አንድ ጊዜ የምሳ አገልግሎት የሚሰጣቸውና በተለያዩ በዓላት ጊዜ የምግብና የንጽኅና መጠበቂያ ድጋፍ እንዲሁም የጤና ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ የነጻ ሕክምና የሚያገኙ ተጠቃሚዎች አሉ።
መንግሥት ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ለመስራት በጀመረው እንቅስቃሴ ሃያ አምስት አረጋውያን ከጎዳና በማንሳት እየተደገፉ ይገኛሉ። በቅርቡም ከሀልፕ ኤይድ ኢንተርናሽናል ጋር በተደረገ ስምምነት ለዘጠኝ ወር ሃያ ስምንት ሰዎች የቀጥታ 427 ብር የገንዘብና የሕክም ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። ለዚህም ከስልሳ አራት በላይ ሠራተኞች በማክሉ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
በተጨማሪ በአረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ ሰጪነት ከሚሰሩ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር በተፈጠረው ህብረት ድርጅቱ ዓመታዊ የንብረት ቆጠራ በሚያደርግበት ወቅት ተረፍ ያለ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ካለን፤ በአጋጣሚ በርከት ያሉ በተለይም የአልባሳት ድጋፍ ሲገኝ ለኅብረቱ አባላት እንዲሁም ለሌሎች አረጋውያን ማኅበራት እያካፈለ ይገኛል። በተጨማሪ ለዓባይ ግድብ፣ በተለያየ የተፈጥሮና የድንገተኛ አደጋዎች ለችግር ለተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2014