ትንሳኤ (ፋሲካ) በኢትዮጵያ ውስጥ በድምቀት ከሚከበሩ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት በዓላት መካከል አንዱ ነው። በዓሉ ሀይማኖታዊ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በዓል የሚያከብሩበት ታላቅ በዓል ነው። በዓሉን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጥልቅ እምነትና ትውፊታዊ እሴት ታከብረዋለች።
የትንሳኤ በዓል በየዓመቱ የእምነቱ ተከታዮች የሆኑ ቤተሰቦች እና ማሕበረሰቦች ቀኑን በደስታ እና በፍፁም ፍቅር ለማክበር ልዩ ዝግጅት ያደርጋሉ። ትንሳኤ (ፋሲካ) ለኢትዮጵያውያን ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነቱ ባሻገርም ልዩ ትርጉም ያለው ነው። ለባሕላችን፣ ለማሕበረሰባችን እና ለአእምሮአችን መሰረት የሆኑ በርካታ እሴቶች የያዘ ነው። ከክብረ በዓሉ ብዙ ትምህርቶችን ማሕበረሰባችን ይማራል። በተለይ እነዚህ ትምህርቶች ለወጣቶች ስክነትን፣ ፅናትን፣ የሀይማኖት አስፈላጊነትን እንዲሁም ስነ ምግባርን የሚያላብሱ ናቸው።
ሃይማኖታዊ አስተምሮቱ እንደሚያሳየው ትንሳኤ (ፋሲካ) በዓል የሚከበረው ሁዳዴ ከተባለ ረጅም የጾም ጊዜ በኋላ ነው፤ ይህ ጾም ለ55 ቀናት ይቆያል። በዚህ ጊዜ የሀይማኖቱ ተከታዮች የሚበሉት ከዕፅዋት የተቀመሙ ምግቦችን ብቻ ነው። ለሰውነት ድሎትንና ተድላን ከሚሰጡ ስጋን፣ የወተት ተዋጽኦዎችን እና ሌሎች የእንስሳት ምርቶችን መቆጠብና የእምነቱን ሕግጋት መከተል ይኖርባቸዋል፤ እንደ አስተምሮቱ ጾም በምግብ ብቻ አይደለም። በተጨማሪም ልብንና አእምሮን ስለማጽዳት ጭምር ነው። በዚህ ምክንያት በሁዳዴ ሰዎች ከዘወትሩ በተለየ ይጸልያሉ፣ ሌሎችን ይረዳሉ እንዲሁም ከክፉ ተግባር እና ከእኩይ ድርጊት ይቆጠባሉ።
ሁዳዴ አብቅቶ ትንሳኤ (ፋሲካ) ሲሆን የክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳትን ምክንያት በማድረግ የደስታ ጊዜ ይሆናል። ነገር ግን በዓሉ ስጋ መብላት ወይም ቡና መጠጣት ብቻ አይደለም። በተከታታይ ቀናት በሚከበረው በዚህ ሀይማኖታዊ በዓል ፍቅርን፣ ይቅርታንና አንድነትን ምእመኑ የሚያስታውስበትና በበጎ ምግባር እራሱን የሚገልጥበት ነው።
ነገ በሚከበረው የትንሳኤ በዓል ላይ ኢትዮጵያውያን የእምነቱ ተከታዮች የሚያንፀባርቋቸው በጎ ምግባሮች ለሁሉም የሰው ለጆች በመሰረታዊነት የሚያስተምረው መልካም ነገር አለ። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንኑ በመገንዘብ በመጋቢ አዕምሮ አምድ ላይ ከዚህ እንደሚከተለው የበዓሉን ዋና ዋና እሴቶች በመግቢያችን እንዳመለከትነው በጥልቀት ይዳስሳል።
የትንሳኤ (የፋሲካ) ሃይማኖታዊ እሴት
ትንሳኤ (ፋሲካ) የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት እምብርት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት የተነሳበትን ቀን ነው። እንደ ክርስትና አስተምሮት ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን እንደገና ሕያው ሆኖ ተነስቷል። ይህ ሀይማኖታዊ አስተምሮት ከእምነትም በላይ ለሰው ልጆች የሚያስተምረው ጥልቅ እሴት እና የተስፋ ታሪክ አለ። ይህም ማለት የክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳት ሕይወት ከሞት የበለጠ ሀያልና አሸናፊ እንደሆነ ያስተምረናል። በተለይ መልካም ከክፉ እንደሚበልጥ ያሳየናል፤ ፍቅርም ከጥላቻ የበለጠ ጠንካራ እንደሆነ ያመላክተናል።
በትንሳኤ በዓል ላይ ከሚነገሩ ትምህርቶች መካከል ኢየሱስ ለዓለም ኃጢአት መሞቱን ነው። ይህ የሚያመላክተው ትልቁን ፍቅር ማሳየቱንና መስጠቱን ነው፤ የበደሉትን እንኳን ይቅር እንዳለ ነው። ለዚህ ነው ትንሳኤ (ፋሲካ) የእምነቱ ተከታይ ባንሆን እንኳን ሌሎችን እንድንወድ የሚያስታውስን የበጎነት ምሳሌ ክፋትን በመልካምነት የመቀየር ምልክት እንደሆነ የምንረዳው። ምንም እንኳን በሕይወታችን ላይ የበደሉንን ሰዎች ይቅር ማለት ከባድ ቢሆንም ይቅር እንድንባባል እና ያለፈውን እንድንተው ምሳሌ ይሆነናል። ወጣቶች ከዚህ ብዙ መማር ይችላሉ። በዘመናዊውና በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፍላጎታችንን በቁጣ ወይም በትዕግስት ማጣት ማንፀባረቅ ቀላል ነው። ትንሳኤ (ፋሲካ) ግን የተረጋጋን፣ ደግ እና ታጋሽ እንድንሆን ያስተምረናል። በእምነት እንድንጠነክር በተግባርም ጥሩ እንድንሆን ክርስቶስን ምሳሌ አድርጎ ያሳየናል። የትንሳኤ እሴት ዘርፈ ብዙ ነው። ከእነዚህ ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።
የፋሲካ ባሕላዊ እሴት
ኢትዮጵያውያን ከመላው የዓለም ክፍል በተለየ በርካታ ባሕሎችና ሀይማኖታዊ ክብረ በዓላት አሉን። እነዚህ በዓላት ከሌላው በተለየ ልዩ የሚያደርጋቸው እሴቶችም ይይዛሉ። ከዚህ ውስጥ ትንሳኤ (ፋሲካ) ይገኝበታል። ትንሳኤ ከኢትዮጵያ ባሕል ጋር በጣም የተቆራኘ ነው። ቤተሰብን እና ጎረቤትን አንድ ላይ ያጣምራል፤ ሰዎች ከሚወዷቸው ጋር ለመሆን ረጅም ርቀት ተጉዘው ለክብረ በዓላቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ይመጣሉ። በየመንደሩ ውስጥ ወይም በከተማ ውስጥ ሁሉም ሰው በዓሉን በድምቀት ያከብረዋል። ከትንሳኤ (ከፋሲካ) በዓል አስቀድሞ ሁሉም ቤተሰብ ቤቱን ያጸዳል። አዳዲስ ልብሶችን ይገዛሉ፤ ድፎ ዳቦ እንጀራ ይጋገራል፤ እንደ ዶሮ ወጥ ያሉ ልዩ ምግቦችን ይዘጋጃሉ፤ እንግዶችን ዘመድ ሊጠይቁ ይመጣሉ፤ ያላቸው ለአቅመ ደካሞች ማእድ ያካፍላሉ።
ይህ የኢትዮጵያውያን ባሕል እና የሀይማኖቱ ክፍል ነው። ማጋራት፣ መተሳሰብ እና መስጠት ሁሉም በሕይወት ዘመኑ ሊፈፅመውና ባሕሉ እንዳይጠፋ ሊጠብቀው የሚገባ እሴት ነው። ትንሳኤ (ፋሲካ) ሀብታሙም ድሀውም አብሮ የሚበላበት ጊዜ ነው፤ ሰዎች ልዩነታቸውን የሚረሱበት ጊዜ ነው። በዓሉ ከሰዎች ጋር በሰላም እንዴት መኖር እንደምንችል ያሳያል። በብዙ አካባቢዎች ሰዎች ጎረቤቶቻቸውን ወደ ቤታቸው ይጋብዛሉ። አብረው ተቀምጠው ቡና ይጠጣሉ፣ ያወራሉ። ይህ መተሳሰብን፣ አብሮነትን፣ ጓደኝነትን ይገነባል፤ በሰዎች መካከል ትስስር ይፈጥራል። በዓለማችን ላይ ብዙዎች ብቸኝነት በሚሰማቸውና በስነ ልቦና ችግር (ድባቴና ጭንቀት) በሚሰቃዩበት ጊዜ ይህን መሰል ባሕል እና አብሮነት መታደል ነው።
የፋሲካ ሥነ-ልቦናዊ ጥቅሞች
ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን ይህንን የምናውቀው? ትንሳኤ (ፋሲካ) የመሰሉ በዓላት ለአእምሮ ጤንነታችንም መጠበቅ ትልቅ ሚና አላቸው። በዚህ በሩጫ ዓለም ሕይወት በውጥረት የተሞላ ነው። ወጣቶች በትምህርት ቤት፣ በሥራ እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ጫና ይደርስባቸዋል። ብዙዎች ድካም፣ ጭንቀት ወይም ሀዘን ይሰማቸዋል። ትንሳኤን (ፋሲካ) የመሰሉ ሀይማኖታዊና ባሕላዊ ትርጉም ያላቸው በዓላት ግን እረፍት ይሰጡናል። ለማረፍ፣ ለማሰላሰል እና ከቤተሰባችን ጋር በደስታ ለመጨዋወት ጥሩ እድል ይሰጣል።
ይህ ብቻ አይደለም። ከትንሳኤ ቀን በፊት ያለው የሁዳዴ ረጅም ጾም ሰዎች ሰውነታቸውን እና አእምሯቸውን እንደገና እንዲያድሱ እድል የሚሰጥ ነው። ራስን መግዛትን እና ትኩረትን ማድረግን ያስተምራል። ይህ ከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ጠቀሜታ አለው።
በሁዳዴ ጊዜ የሚደረጉ ጸሎቶች ለልብም ሰላም ይሰጣሉ። ቁጣን፣ ፍርሃትን እና ጭንቀትን ለመቀነስ ይረዳሉ። ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ መዝሙሮችን መዘመር እና ሻማ ማብራት የተረጋጋ እና አስደሳች ስሜት ይፈጥራል። ጾሙን በስኬት ማጠናቀቅ የቻሉ ሰዎች ባገኙት ድል ፍፁም ሰላምና ደስታን ያገኛሉ። ከሁሉም በላይ ረጅሙን የፆም ግዜ በድል ማጠናቀቅና ትዕግስትን መለማመድ በምላሹ ለውስጣችን ሰላምና ጥሩ ውጤት ያስገኛል። በተለይ ይህ ሕይወታቸውን በበርካታ ፈተናና ፅናት የሚጠይቁ ተግዳሮቶች ለሚያሳልፉት ለወጣቶች ጠንካራ መልዕክት ነው። ሁዳዴን ድል ማድረግ በሕይወት ውስጥ ጥሩ ነገሮች ጊዜ እንደሚወስዱ ለመረዳት፤ ጠንክሮ መሥራት እና ትዕግስት ሁል ጊዜ ሽልማት እንዳለው ለማወቅ ያግዛል።
ትንሳኤ (ፋሲካ) ሚዛናዊነትን ያስተምራል። ከጾም በኋላ በጥንቃቄ እና በደስታ እንበላለን። ይህ የሚያሳየን ወደ ጽንፍ ሳንሄድ ሕይወትን እንዴት በደስታ መምራት እንደምንችል የሚያሳይ ነው። ከቤተሰብ ጋር መመገብ፣ መጨዋወት፣ መሳቅ እነዚህ ቀላል የሚመስሉ የደስታ ጊዜያት የውስጣችንን ሰላምና ስሜት ያሻሽላሉ፤ ጭንቀትን ይቀንሳሉ።
ትንሳኤ (ፋሲካ) እና የአንድነት ኃይል
ትንሳኤ እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ሕዝብ መሆናችንን ያስታውሰናል። ሀብታምም ሆኑ ድሆች፣ ወጣትም ሆኑ ሽማግሌዎች ሁሉም በአንድ ላይ በዓሉን ያከብራሉ። መለያየት በበዛበት በዚህ ዓለም ፋሲካ አንድነትን የሚያስተምር ታላቅ ትርጉምን የያዘ በዓል ነው። በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ መንደሮች እና ከተሞች ውስጥ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች አንዳቸው የሌላውን በዓላት ያከብራሉ፤ እንኳን አደረሳችሁ በመባባል ሰላምታ ይሰጣጣሉ። ይህ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ዋጋ ያለው ነው። ይህ የሰላም መንፈስ ለዓለም አብነት ነው። ለዚህ ነው ወጣቶች ሊጠብቁት የሚገባው። በዓሉ በፍቅር እና በሰላም በአብሮነት መኖር ከተቻለ ኢትዮጵያ ጠንካራ እንደምትሆን የሚያሳይ እሴት ነው።
ትንሳኤ (ፋሲካ) ፈተና የሚያበቃበት፣ ጦርነትን የምናቆምበት እና ሰላም የምንጀምርበት ጊዜ ነው። ከአንድ ሰው ጋር ችግር አጋጥሞን ከሆነ ይቅር ለማለት ጊዜው ትንሳኤ ነው። አንድ ሰው ቢጎዳህ፣ ቢያስቀይምህ ይቅር የምትልበት ጊዜው አሁን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገው ይህንኑ ነው።
ትንሳኤ- ኃላፊነትን ያበረታታል
በትንሳኤ (ፋሲካ) ወቅት ወጣቶች ኃላፊነትን መማር ይችላሉ። ቤተሰቡ ለቀኑ ሲዘጋጅ ሁሉም ሰው ይረዳዳል፤ ልጃገረዶች እና ወንዶች ልጆች ቤት ያፀዳሉ፣ ምግብ ያበስላሉ፣ ቤተሰቦቻቸውን ያገለግላሉ። ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ትምህርቱን ያዳምጣሉ። ይህ ስነ ምግባርና ተግሣጽን የሚሰሙ ወጣቶች ይፈጥራል። በተጨማሪም የዓላማ ፅናትን ይፈጥራል። በዚህ በ21ኛው ከፍለ ዘመን ብዙ ወጣቶች ከዓላማቸው የተሰናከሉ፣ የጠፉ ወይም የተሰላቹ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። በሀይማኖታዊ ክብረ በዓል፣ በጾም እና በባሕላዊ እሴቶች ላይ ሲሳተፉ ግን መሰል ስሜት ማስተናገድ ያቆማሉ፤ ጠቃሚ ዜጋ እንደሆኑ ይሰማቸዋል።
ትንሳኤን (ፋሲካን) ማክበር እቅድ እና ትዕግስትንም ያስተምራል። ጾም እቅድ ማውጣትን ይጠይቃል። ለበዓል ገንዘብ መቆጠብ ተግሣጽ ይጠይቃል። የበዓሉን ቀን በትዕግስት መጠበቅ ትዕግስትን ያስተምራል። እነዚህ ለሕይወት አስፈላጊ ክህሎቶች ናቸው።
ትንሳኤን (ፋሲካ) እንደ መስጠት ጊዜ
ፋሲካ ስጋ መብላት ብቻ አይደለም። ለተቸገሩም መስጠትም (ማካፈልም) ነው። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ለድሆች ምግብና ልብስ ይሰበስባሉ። ሰዎች የታመሙትን ይጎበኛሉ። ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች ገንዘብ ወይም ስጦታ ከወገናቸው ያገኛሉ። እነዚህ የደግነት ድርጊቶች ደስታን፣ ርህራሄን ይፈጥራሉ። ሌሎችን መርዳት ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል፤ ለሕይወት ትርጉም ይሰጣል። ወጣቶች ይህንን መማር አለባቸው። ለመርዳት ሀብታም መሆን አያስፈልግም። መልካም ቃል እንኳን በቂ ነው። የትንሳኤ (ፋሲካ) በዓል ይህን ልማድ ለመጀመር ጥሩ ጊዜ ነው። ዙሪያህን ተመልከት፤ ብቻውን የሆነ ሰው አለ? ምግብ ወይም ልብስ የሚያስፈልገው ሰው አለ? አረጋዊያን መጎብኘት ትችላለህ? እነዚህ ጥቃቅን የሚመስሉ መልካም ነገሮች አስፈላጊ ናቸው። ትንሳኤ ይህንን እንድናደርግ ያበረታታል።
ፋሲካ እና ማንነት
በፍጥነት በሚለዋወጠው በዚህ በ21ኛው ዓለም ብዙ ወጣቶች ማንነታቸውን እያጡ ነው። ቋንቋቸውን፣ ታሪካቸውን እና እምነታቸውን እየዘነጉ ነው። ትንሳኤ (ፋሲካ) ግን ማን እንደሆንን እንድናስታውስ ይረዳናል። በዓሉ አያሌ እሴቶችና የማንነታችን፣ የሀይማኖታችን መገለጫ የሆኑ የኢትዮጵያዊ መገለጫዎች አሉት። ከእናት አባቶቻችን እውቀትና ጥበብ፣ ከእሴቶቻችንን፣ ከመከባበር፣ ከታማኝነት፣ ከፍቅር እና ከታታሪነት ጋር ያዋድደናል። ትንሳኤ (ፋሲካ) ማንነትን ጠንካራ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ ነው። በማንነትህ የሚኮራበት እሴት፤ ኢትዮጵያ የበለፀገ እና ያማረ ባሕል እንዳላት ለዓለም የምታሳይበት ነው።
መልእክት ለወጣቶች
ትንሳኤ (ፋሲካ) የእምነቱ ተከታዮች ሃይማኖታዊ እሴት ወይም ባሕላዊ እሴት የያዘ ብቻ አይደለም። ትንሳኤ ማመን እንድንችል፣ ይቅር እንድንል፣ እንድንተባበር እና አንዳችን ለሌላችን እንድንጨነቅ የሚያስተምረን ሕያው ምስክር ነው። ጾሙ (ሁዳዴው) ትንሳኤ (በዓሉ) በሰላምና በዓላማ እንዴት መኖር እንዳለብን ያሳየናል። ወጣቶች እንደመሆናችሁ የነገ መሪዎች ናችሁ። ዛሬ የምትኖሩበት መንገድ የወደፊቱን ይቀርፃል። በእምነት፣ በፍቅር እና በመከባበር ከኖራችሁ ኢትዮጵያ በተስፋና በሚጨበጥ እድገት የተሞላች ትሆናለች።
ለዚህ ነው በመጨረሻ መልእክታችን ትንሳኤን (ፋሲካን) በምግብ ብቻ ሳይሆን በልባችሁ ጭምር አክብሩት የምንለው። ወጣቶች በመንፈስ፣ በጥንካሬ እና በልህቀት ለማደግ ይህንን በዓል ተምሳሌት አድርጉ። ለመማር፣ ለመውደድ እና ለመስጠት ትንሳኤ ተምሳሌት ይሁናችሁ። በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ ውስጥ የትንሳኤ (ፋሲካን) እሴቶች ያዙ። ባሕላችሁን አክብሩ፣ ሀገራችሁን ውደዱ፤ ወላጆቻችሁን አክብሩ፤ ጎረቤቶቻችሁን እርዱ። እንደየ እምነታችሁ ጸልዩ። የበደሏችሁን ይቅር በሉ። በመጨረሻም ሁልጊዜ በሰላም ለመኖር ይሞክሩ። ትንሳኤ በጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃን ነው። ያ ብርሃን በእናንተ ውስጥ ይብራ። ወደ ተሻለ ሕይወት ይመራችኋል። መልካም በዓል!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም