ኢትዮጵያውያን በዓል ላይ ሰብሰብ ብለውና ተጠራርተው መመገብን ይመርጣሉ:: የበዓሉ ማድመቂያ ተመራጭ ምግቦችም በአብዛኛው ቅባትና ቅመማ ቅመም የበዛባቸው ናቸው:: ከዚያም አለፍ ሲል ለምግብ መፈጨት አሊያም ለጨዋታ ድምቀት በሚል የአልኮል መጠጦችን ይቀርባሉ:: በዓል የሚከበረው በምግብና መጠጥ ነውና በጾም የቆየ ሆድ በምግብ ብዛት እንዲወጠር፤ በመጠጥ ብዛት እንዲጨነቅ ይገደዳል:: ይህ ደግሞ የአመጋገብ ሥርዓቱን ያዛባውና ለከፍተኛ የጤና እክል ይዳርጋል:: የተለያየ የጤና ጉዳቶችንም ያስከትላል።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ነገ የሚከበረው የትንሳኤ በዓል ደግሞ ለዚህ አይነት አመጋገብ ከፍተኛ እድልን የሚሰጥ በመሆኑ ሰዎች መጠንቀቅ ካልቻሉ ከአጭር ጊዜ እስከ ረጅም ጊዜ የሚዘልቁ የጤና ጉዳቶችን እንደሚያስተናግዱ የሥነምግብ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ::
አቶ ቤንኦን ጌታቸው በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የስነ ምግብ ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው በዓልና ጤናማ አመጋገብን በሚመለከት የተለያዩ ሀሳቦችን ይሰነዝራሉ:: ጤናማ አመጋገብ ምንድነው ከሚለው በመነሳትም ማብራሪያቸውን ይሰጣሉ:: ባለሙያው እንደሚሉት፤ ጤናማ አመጋገብ ማለት አንድ ትርጉም የለውም:: ሆኖም የዘርፉ ምሁራን የተስማሙበት ሰዎች ሰውነታቸውን የሚጎዱ ምግቦችን በመተው ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን መውሰድ ከጅምሩ ጤናማ ምግብን ወስደዋል ለማለት ያስችላል:: ከዚህ አንጻርም ገንቢ ምግቦችን፤ በሽታ ተከላካይ፤ ኃይል ሰጪና መሰል ሰውነታችንን ሊያበለጽጉ የሚችሉ ምግቦችን ስንመገብ ጤናችን በተለያየ መልኩ እንዲጠበቅ ስለሚያደርገው ጤናማ ምግቦችን እየወሰድን ነው እንላለን::
ይህ ነገር በበዓላት ወቅት እንዴት ተግባራዊ ይሆናል፤ እንዴትስ እየተገበርነው እንገኛለን ከተባለ በተለያየ መልከ ማየት ይቻላል:: በቅባት ብዛት፤ አብዝቶ ከመመገብ አንጻር፤ ቅመማቅመሞችን ከመጠቀም አኳያ፤ ከጾም ወደ ፍስክ የምንገባበትን ሁኔታ፤ የአልኮል መጠጦችን የአጠቃቀም ባሕላችንንና መሰል ነገሮችን ማንሳት ዝርዝር ጉዳዩን እንድንረዳው ያደርገናል:: እንደሚታወቀው ባሕላችን በዓል ሲሆን የምግብ ምርጫው የሚያዘነብለው በአብዛኛው ቅባት የበዛበት ምግብ ላይ ነው:: አብሮ የመብላቱ ባሕልም ስላለ ከአንዱ ቤት ሌላኛው ቤት ቢቀየርም ምግቡ አይለዋወጥም:: በዚህም ከፍተኛ የሆነ ቅባት የበዛባቸው ምግቦች እንመገብ ይሆናል:: ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክሎችን እንድናስተናግድ ያደርገናል:: ለአብነት የቅባት መብዛቱ የኮልስትሮን መጠንን በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል፤ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥን እድል ይጨምራል፤ ለልብ ሕመም፤ ለስኳርና ላላስፈላጊ ውፍረት ይዳርገናል:: የደም ዝውውር መስተጓጎል እንዲገጥመንም ያደርጋል።
በባሕላችን እንግዳ ወደ ቤታችን ከመጣ አብሮ መብላት አለያም መቅመስ እንዳለበት ያስገድደናል፤ ጎረቤት ተጠርተን ስንሄድም የግድ መቅመስ ያስፈልገናል። ቤት ውስጥም ቤተሰቡ ቁርስ መብላት አለበት ተብሎ ጥሪ እንኳን ቢኖር ትንሽ መቅመስ የግድ ይለናል። ይህ ሁሉ የአመጋገብ ግዴታ ደግሞ ምግብን መጥነን እንዳንወስድ ያደርገናል። በዚህም ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንጋለጣለን። በዚህ ወቅትም የሆድ፤ የጨጓራና መሰል አጣዳፊ በሽታዎች በስፋት በሰዎች ላይ ይከሰታሉ:: ይህ ሲሆን ደግሞ ሆስፒታሎችን ጭምር በከፍተኛ የሥራ ጫና ውስጥ ይገባሉ።
ሌላው አቶ ቤንኦን ያነሱት ጉዳይ በዓላትን ተመርኩዞ የምንጠቀማቸው ቅመማቅመሞችን የሚመለከተው ነው:: በበዓላት ወቅት አብዝተን ጥቅም ላይ የምናውላቸው ቅመማ ቅመሞች ናቸው:: ቅመሞች ሲዘጋጁ መጠናቸው ምን ያህል ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነው በሚል የተጠና አይደለም:: መጠቀም ያለባቸው ምን ያህል መጠን እንደሆነም አይገለጽም:: ምን አይነት የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ይከለከላሉ ወይም ይፈቀድላቸዋል፤ በየትኛው እድሜ ክልል ያሉት ቅመማ ቅመሞችን መመገብ የለባቸው የሚለውም የተለየ አይደለም::
ሌላው ደግሞ በፋብሪካ የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ ለብዙ ችግር ያጋልጣል:: በፋብሪካ የሚመረቱ የተለያየ ኬሚካል ጥቅም ላይ ይደረጋል:: ስለዚህም የጤና ጉዳቱ መጠን ሊገለጽና ሊታወቅ አይችልም:: ሆኖም በዋናነት ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸውን ከፍ እንደሚያደርገው በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ::
80 እና 90 በመቶ የጤና ችግር የሚከሰተው ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ የሚጠቁሙት ባለሙያው፤ በበዓላት ወቅት የሚያዘወተሩት ምግቦች ብቻ ሳይሆኑ የአልኮል መጠጦች ጭምር የጤና ጠንቅ መሆናቸውን ያነሳሉ:: ምግብን ይፈጫል በሚል፤ ሳቅና ጨዋታን ለመፍጠርና አብሮ ለመቆየት እንዲሁም ከበድ ያለ መጠጥን ማቅረብ እንደክብር መገለጫ ስለሚወሰድም በብዛት ጥቅም ላይ እናውላቸዋለን:: በዚህ ደግሞ ሰዎች ለከፍተኛ የልብና የሳንባ፤ የኩላሊትና የጉበት የጤና ችግር ይዳረጋሉ:: ስለዚህም በበዓላት ወቅት ለነገ ጤናማ ሕይወት መኖር ከተፈለገ አመጋገባችንን በብዙ መልኩ ማሻሻል እንደሚገባን ያስገነዝባሉ:: ጤናማ ምግቦች የሚባሉት ተፈጥሯዊ ምግቦች ብቻ መሆናቸውን ነው ጨምረው የገለጹት::
አቶ ቤንኦን በበዓላት ወቅት መደረግ አለባቸው የሚሏቸው ነገሮችን የዘረዘሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የሥጋና ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን አጠቃቀም መቀነስ ነው:: የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው የተቀቀለ ሥጋን አብዝቶ መመገብ ለካንሰር ያጋልጣል ይላል። ስለሆነም ሰዎች ሥጋን ጥሬውን ከመመገብ ይልቅ እሳት እንዲነካው፤ በጣምም እንዳይበስል ማድረግ ይኖርባቸዋል:: በተጨማሪም ከሥጋና ቅባታማ ከበዛባቸው ምግቦች ይልቅ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም ጥራጥሬዎችን ምርጫቸው ሊያደርጉ ይገባል:: ይህ ሲሆን ጤናቸው የበለጸገ፤ አካላዊ እድገታቸው የተመቻቸና አዕምሯዊ እድገታቸው ከፍ ያለ እንዲሆን ይረዳቸዋል ባይ ናቸው::
የበዓላት ወቅት ምግቦች ሲዘጋጁ ጤናማነትን በጠበቀ መልኩ ሊዘጋጁ ይገባል። ለአብነት ሥጋን ከጎመን ጋር፤ ስጋን ከሩዝና መሰል ሌሎች ምግቦች ጋር አቀላቅለን ብናዘጋጃቸው የተመጣጠነ የሚለውን ምግብ ማግኘት እንደምንችልም ያስረዳሉ። አክለውም ሰውነታችንን ከጾም በኋላ ቅባት የበዛበት (ጡሉላት) ምግቦችን ሳንወስድ ሆድን ማለማመድ ያስፈልጋል:: ለዚህም እንደ ተልባና መሰል ውስጣችንን ሊያለሰልሱ የሚችሉ ምግቦችን ቀድመን መመገብ አለብን። አንድ ሰው በቀን መመገብ ያለበት የተመጣጠነ ምግብ ከእድሜ፤ ከሚያደርገው ስፖርታዊ እንቅስቃሴና መሰል ነገሮች አንጻር የሚታይ በመሆኑ ይህንንም እያሰሉ መንቀሳቀስ የግድ ይላል:: ተላላፊም ሆኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በቀላሉ ለመከላከል፤ ጤናችንን አሻሽለን ምርታማ ለመሆን ያስችለን ዘንድ የስነ ምግብ ባለሙያዎችን ማማከርም እንደሚገባ ያስረዳሉ::
እንደ አቶ ቤንኦን ሁሉ አቶ እንዳሻው ሙላቴ የስነምግብ ባለሙያ ናቸው:: በዚህም የአመጋገብ ሁኔታችን በበዓላት ወቅት ምን መምሰል እንዳለበት ያብራራሉ:: በበዓላት ወቅት የሚዘወተረው የእንስሳት ተዋጽኦ በመሆኑ ሌሎችን የምግብ አይነቶች ማለትም የተመጣጠኑ ምግቦችን ሳናገኛቸው ቀናት ይቆጠራሉ:: በዚህም ሰዎች ለከፋ የጤና ችግር ይጋለጣሉ:: ለአብነት የሆድ ሕመም፤ ማቅለሽለሽ፤ ወደላይና ወደታች ማለት፣ የምግብ ፍላጎት መዘጋት፣ የጨጓራ፣ የአንጀትና የመሳሰሉ የጤና ችግሮች በዋናነት የሚከሰቱ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ::
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በባሕላችን በዓላቱ የሚደምቁት ቅባት በበዛባቸው ምግቦች፤ ጣፋጮችና በቅመማ ቅመም የተከሸኑ ሲሆኑ ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል:: ይህ ደግሞ በሰውነታችን ላይ በተለያየ መልክ ከባድ ጫና እንዲፈጠር ያደርጋል:: ድንገተኛ ሕመሞች ያጋልጣል። ምክንያቱም በስርዓተ ምግብ ሕግ የአመጋገብ ስርዓት ከተዛባ ድንገተኛም ሆነ የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮች ይከሰታሉ:: እንደ ሕጉ ከሆነ አብዝቶ መመገብ፤ የምግብ እጥረትና የማይታይ ረሃብ ወይም በማየት የማይታወቁ ነገር ግን በቂ ንጥረ ነገሮችን ሳናገኝ የምናልፍባቸው አጋጣሚዎች ለከፍተኛ ችግር ይዳርጉናል። እነዚህ ተግባራት ደግሞ በስፋት በበዓላት ወቅት እውን የሚሆኑ ናቸው::
በበዓላት ወቅት ሰብሰብ ብሎ መመገብ ልምድ ነው፤ ብትጠግቡም እኔ ቤት ሳትበላ መባባሉ የግድ ደግመን እንድንመገብ የሚያደርገን ነው፤ በጉርሻም ማጨናነቁ ሰዎች ፍቅራቸውን የሚገልጹበት አድርገው ይወስዱታል:: ይህ ደግሞ መጠናችንን ጠብቀን እንዳንመገብ ያደርገናል:: በተጨማሪም በቅባቱ መብዛት የተነሳ ሰውነታችን ለከባድ ጫና ይጋለጣል:: በዚህም ሳንወድ በግድ በአንጀት፤ በጨጓራና በሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች ላይ ቀላልና ከባድ የጤና ችግሮች እንድናስተናግድ ያደርገናልም ስለዚህ አመጋገባችን ጥንቃቄ የተሞላበት ይሁን ሲሉ ይመክሩናል::
በበዓላት ወቅት ስርዓተ ምግባችንን ከሚያዛቡት ነገሮች መካከል አንዱ ለረጅም ሰዓት ምግብ ሳይቀምሱ መቆየት እንደሆነም አቶ እንዳሻው ያነሳሉ:: በተለይ ሴቶችና እናቶች አካባቢ በስፋት የሚታይ ነው:: ቤተሰቡን ለመመገብ ሲባል በብዙ ይደክማሉ:: ምግብ ሲያዘጋጁም ሽታው የሚዘጋበት እድል አለ:: ስለዚህም ሰው በልቶ ሲጨርስ አሊያም ሥራ ሳይጠናቀቅ ከዚያም አለፍ ሲል አራበኝም በሚል ለረጅም ሰዓት ምግብ ሳያገኙ እንደቆዩ ይሆናሉ:: ይህ ደግሞ በርካታ የጤና ጉዳቶችን እንዲያስተናግዱ ያስገድዳቸዋል:: በተለይም በጊዜው በስፋት አሲድ የማመንጨት እድል ስለሚኖር ለጨጓራና ለስኳር በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል። በተመሳሳይ ቀደም ሲል እንደ ስኳርና ግፊት እንዲሁም የልብ ችግር ላለባቸው ሰዎችም በሽታውን የማባባሻ ምክንያት ተደርጎም እንደሚወሰድ ይናገራሉ::
አንድ ሰው ቢያንስ በቀን አመጋገቡ ውስጥ ስድስትና ከዚያ በላይ የሆኑ የተለያዩ ምግቦችን አመጣጥኖ መውሰድ ያስፈልጋል። ሆኖም በበዓላት ወቅት ይህ ሲሆን አይታይም። ይልቁንም ተከታታይነትን የማይጠብቁና ተመሳሳይነት ያላቸው በአንድ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ምግቦች ይዘወተራሉ የሚሉት አቶ እንዳሻው፤ ይህ ደግሞ ሰዎች በቀን ማግኘት ያለባቸውን የተመጣጠነ ምግብ እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል። ከዚያ በሻገርም በበዓላት ወቅት የምግብ አዘገጃጀታችን ሁኔታ የተዛባና በንጽህና የሚከወን ስላልሆነ ድንገተኛ የሚባሉ የጤና እክሎች ሰዎች እንዲያጋጥማቸው ይሆናሉ ሲሉም ያብራራሉ::
አቶ እንዳሻው እነዚህ ሁሉ ችግሮች መፍቻ መንገድ እንዳላቸው ይናገራሉ። አንዱ በበዓላት ወቅት ቅባትን መቀነስ፤ የተመጣጠኑ ምግቦችን ለመውሰድ መሞከርና በቂ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሁም ከአልኮል ይልቅ ውሃ በብዛት መጠጣት በዋናነት ጤናችንን የምንጠብቅባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ስለመሆናቸው ይገልጻሉ።
በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፤ አልኮል መጠጦች ሙሉ ለሙሉ ጥቅም የላቸውም። ይሁን እንጂ በዓል ነውና አቁሙ ለማለት ስለሚያስቸግር የተቀመጠለትን መጠን ማለፍ እንደማይገባ ጠቁመው፤ ይህ መጠን በሳምንት ከሁለት ብርጭቆ ያነሰ መሆኑን ያስረዳሉ። የቅባት መጠንም እንዲሁ ከሁለት እስከ ሦስት የሾርባ ማንኪያ ብቻ መሆን እንደሚገባውም ያስገነዝባሉ።
ሥጋና የሥጋ ተዋጽኦችን በሚመለከት ደግሞ ስንጠቀም በቀን በአማካኝ መውሰድ ያለብን 60 ግራም ብቻ እንደሆነ የስነምግብ ባለሙያው አቶ እንደሻው ይናገራሉ። ጣፋጭ ምግቦችም ከ30 ግራም መብለጥ እንደሌለባቸው ጭምር ይገልጻሉ። ስለሆነም ‹‹አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው›› እንዳለው ዘፋኙ እኛም አቅማችንን፤ መጠናችንን አውቀን እንመገብ የዚያን ጊዜ ጤናማ ሕይወታችንን እንመራለን በማለት ተሰናበትን::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም