የወታደሩ ትዝታዎች

ልጅነትን በጨረፍታ…

የአያት ልጅ ናቸው:: አስተዳደጋቸው ከእኩዮቻቸው ሁሉ ይለያል:: የልጅ ልጃቸውን በእጅጉ የሚወዱት አያቶቻቸው ለእሳቸው የማይሆኑት አልነበረም:: የጠየቁትን ያሟላሉ፣ የፈለጉትን ይሰጣሉ:: ይህ እውነት ለትንሹ ጸጋዬ መገርሳ የተለየ ዓለም ሆነ:: ተሞላቀው፣ ተደስተው ልጅነታቸውን አጣጣሙ::

ከጥቂት ግዜ በኋላ በደጋጎቹ አያቶች ቤት የሞት ጥላ አንዣበበ:: ሳይታሰብ ሁለቱ አዛውንቶች ተራ በተራ ሞት ነጠቃቸው፡ ይህ አጋጣሚ ለትንሹ ልጅ ፈተና ሆነ:: ከልጅነታቸው የወላጆቻውን ቤት የማያውቁት ፀጋዬ ጓዛቸውን ጠቅልለው ከተወለዱበት ቤት እንዲመለሱ ተገደዱ::

የነ ጸጋዬ አባት ሐይለኛ የሚባሉ አባወራ ናቸው:: ባሕሪያቸው ከብዙዎች አይገጥምም:: በየሰበቡ ቤተሰቡን መረበሽ፣ ማሳዘን መገለጫቸው ሆኖ ቆይቷል:: ይህ አይነቱ ሀቅ ለትንሹ ጸጋዬ ፍጹም አዲስና ያልተለመደ ነው:: የእሳቸው ልጅነት በዚህ መልክ አልተቃኘም:: ኑሯቸው በምቾት፣ ሕይወታቸው በቅንጦት ነው::

ከአያቶቻቸው ሞት በኋላ ከወላጆቻቸው ጋር መኖር ጀምረዋል:: እህት ወንድም በማግኘታቸው ቢደሰቱም የእናት አባታቸው ፍቅር ማጣት ያሳስባቸው ይዟል:: ሰላም አልባው ቤት ሁሌም በጭቅጭቅ ውሎ እያደረ ነው:: ይህ ችግር ቀን ሲቆጥር ከጫፍ ደረሰ:: የወላጆቻቸው ሰላም ማጣት ለውሳኔ አብቅቶ ነባሩ ትዳር በፍቺ ተቋጨ::

የፍቺው ጣጣ …

ከዚህ አጋጣሚ በኋላ የቤተሰቡ ኑሮ ስር እንደሌለው ዛፍ ሆነ:: እናት አባት ሲለያዩ ልጆች በየፊናው ተበተኑ:: ቤቱ ያለ አባወራ፣ ልጆች ያለ እናት ቀሩ:: ይህ ክፉ አጋጣሚ ለእንግዳው ጸጋዬ ፈታኝ ሆነባቸው:: ከአያቶቻቸው የወረሱት ፍቅር አሁን በቤታቸው አልተገኘም::

ትንሹ ልጅ ኑሯቸው እንደ ትናንቱ መልካም ሳይሆን ቢቀር ከልባቸው አዘኑ:: ጅምር ልጅነታቸው ተፈተነ:: የቤተሰቡ መበተን ያሳደረው ጫና በእሳቸው ጫንቃም አርፏል:: ሁሉን ከመቀበል በቀር ምርጫ አልነበራቸውም:: ክፉ ቀናትን ተሻግረው አፍላነት ላይ ሲደርሱ ግን በራሳቸው ሊወስኑ ግድ ሆነ:: አስራ ስድስተኛ ዓመታቸውን በደፈኑ ማግስት ልባቸው አርቆ አሰበ::

ውሳኔ…

ጸጋዬ ሎጋው ቁመታቸው፣ ከግዙፎች ጎራ አሰልፏቸዋል:: መልካም ቁመናቸው ሀያዎችን የተሻገሩ ይመስላል:: ይህ እውነት ውትድርናን ለሚያስቡት ጸጋዬ መልካም ሆኖ ነበር:: ዕድሜያቸውን ያልጠረጠሩ ቀጣሪዎች በሀያ ዓመት የዕድሜ ልየታ መርጠው ወደ ጦር ማሰልጠኛ መሯቸው::

በ1980 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት ጸጋዬና ውትድርና በወጉ ተዋወቁ:: በወቅቱ አጠራር ሸዋ ከሚባለው ክፍለሀገር ባሌ ጎባ ታጠቅ 4 ‹‹መስሎ›› ጦር ሰፈር የተገኙት ወጣት የሙያው ትክክለኛ ሰው ሆኑ:: ስልጠናውን በብቃት ካጠናቀቁ በኋላ ወደተመደቡበት ጦር ግንባር መዝመት ነበረባቸው:: ትግራይ መሬት ሽሬ ምድር ላይ::

ለከባዱ ፍልሚያ ወደሽሬ የተመመው የእሳቸው ክፍለ ጦር ቆይታውን አጠናቆ ወደ ደሴ ‹‹ ጢጣ ›› ጦር ሰፈር አመራ:: እሳቸው ያሉበት ጦር ዋንኛ ግዳጁ ማዘዣ ጣቢያውን መጠበቅ ነበር:: ሁለት ዓመታትን በክፍለጦሩ የቆዩት ወጣቱ ወታደር ለቀጣዩ ግዳጅ ራሳቸውን አዘጋጁ::

አስር አለቃ ፀጋዬ በውትድርና በቆዩባቸው ዓመታት ብዙ መንገዶች አልፈዋል:: ከጎናቸው የነበሩ ጓዶች በሞት ሲለዩ፣ ብዙሀን አካላቸውን ለጥይት ሲገብሩ ዓይናቸው አይቷል:: ለእሳቸው ዛሬ እንጂ ነገ ብርቃቸው ሆኖ አያውቅም:: አሁን ደግሞ ለቀጣዩ ግዳጅ በጓድ መሪነት እንዲዘጋጁ ተነግሯቸዋል::

በጦርሜዳ…

በ1983 ዓ.ም በነበረው ከባድ ውጊያ በርካቶች እንደቅጠል ረግፈዋል:: እንዲያም ሆኖ ጦርነቱ በበቃኝ አልቆመም:: በነባሩ ጦር ምትክ በ‹‹ሟሟያ›› መርህ አዲስ ጦር እንዲሰለፍ ሆኗል:: ከነዚህ ሟሟያዎች መሀል ጸጋዬ አንዱ ነበሩ:: በወቅቱ ከምክትል ጓድ መሪ እስከ ብርጌድ አዛዥ የተካተተበት አዲሱ ጦር በትኩስ ወኔ ተነሳስቶ ለግዳጅ ተሰማራ:: በየስፍራው የነበረው ውጊያ ብዙ ሕይወት አስከፈለ:: በአይበገሬነት የዘመተው ጦር እየጣለ ሲወድቅ ጸጋየም ለሁለት ግዜያት ቆስለው ተጎዱ::

በመጀመሪያው የወረራ ውጊያ ቀኝ እግራቸውን፣ ቀጥሎ ደግሞ ፊታቸው ላይ ጥይት ሰለባ አደረጋቸው:: ጦርነቱ አሁንም አላበቃም:: በየጫካው፣ በየሀይቁና ጋራ ተራራው ተጠናክሮ ቀጥሏል :: ሰፊ ግዜ፣ ክቡር ሕይወትና የደም መስዋዕትነት በተከፈለበት ጦርነት ወታደሮቹ እነ ፀጋዬ እንደ ቁስለኛ ተኝተው አላረፉም:: በዳግም ዘመቻ ሞራላቸውን ገንብተው ጦር ይዘው ተንቀሳቀሱ ::

ይህ ግዜ ለጸጋዬ ከመቼውም ይበልጥ ፈታኝና ከባድ ነበር:: አስርአለቃውን ለሶስተኛ ግዜ ያገኛቸው ጥይት እንደቀድሞ በወጉ ሽሮ አልዳነም:: ለዛሬው ማንነት አይሽሬ ጠባሳ ሆኖ አብሯቸው ዘለቀ:: ይህን የግንባር ውሎ ጸጋዬ የአሁን ያህል በቅርበት እየመዘዙ ያስታውሱታል::

የመጨረሻው ፍልሚያ…

1983 ዓ.ም:: ሰሜንሸዋ ጣርማበር ግንባር:: መንዝ መዘዞ የደረሱት ተዋጊዎች አንዳቸው ዋሻውን ለመያዝ፣ አንዳቸው ደግሞ ላለማስነጠቅ መሞላሸቅ ጀምረዋል:: የመጨረሻው የሞት ሽረት ትግል፣ የብዙሀን መስዋዕትነትና ድል፣ አይበገሬነት የታየበት ከባድ ግዜ:: በስፍራው የቆሙት ሁሉ ለአፍታ ትንፋሽ ያገኙ አይመስልም:: ጦርነቱ በእጅጉ ፍሟል:: በጓድ መሪነት ጦር ይዘው የቀደሙት አስር አለቃ ግዳጃቸውን በብቃት ለመወጣት መሀል ውጊያ ውስጥ ናቸው::

ለሊት አስራ አንድ ሰዓት የጀመረው ጦርነት ሰማይ ምድሩን እያስጨነቀ ነው:: የጥይት፣ የከባድ ጦር መሳሪያ ሀያል ድምጽ ተራራውን እያለፈ ፣ ጨለማውን በብልጭታ ይሰነጥቃል:: ማለዳውን ጸሀይ እንዳኮረፈች በደም ተሸፍና ብቅ አለች:: ማዶ ለማዶ በግንባር የተፋጠጡት ተዋጊዎች ነፍጣቸውን አልጣሉም::

ውጊያው ከቀድሞው በላቀ ተጧጡፎ ቀጥሏል:: በየአፍታው እልፍ ነፍሶች ስለ ዓላማ ጽናታቸው በክብር መውደቅ፣ መርገፍ ይዘዋል:: በድንገት ተመተው የወደቁትን የጦሩን የሻለቃ አዛዥ ሞት ተከትሎ ጸጋዬ ቦታውን ተክተው መንቀሳቀስ ነበረባቸው:: በፍጥነት አሰሉና የታሰበውን አደረጉ::

ቁስለኛው …

ግንቦት 8 ቀን 1983 ዓ.ም:: አሁን የሻለቃ አዛዡ ቦታ በአስር አለቃ ጸጋዬ ተተክቷል:: ጸጋዬ ከውጊያ ያደረ ክንዳቸው ፈጽሞ አልዛለም:: ከፊት፣ ከኋላ ትዕዛዝ እየሰጡ ጦራቸውን ማዋጋት ያዙ:: አሁንም በላያቸው የሚያሽካካው ከባድ መሳሪያ መሬቱን የገመሰው ያህል ያርበደብዳል:: ጸጋዬ ዓላማቸውን አልሳቱም:: ጦሩን እየመሩ ወደፊት ገሰገሱ:: ይህ ጀግንነት ግን ብዙ አልቆየም:: እሳቸውም እንደሻለቃው አዛዥ ተመተው ቆሰሉ::

የጸጋዬን ተመቶ መቁሰል ያዩ አግላይ ቡድኖች ከወደቁበት አንስተው በፍጥነት ቦታቸውን ተኩ:: ፀጋዬ ክፉኛ የተመታው ጎናቸው ያለማቋረጥ እየደማ ነው:: ከዚህ ቀድሞ ለሁለት ግዜ ቆስለዋል:: በአሁኑ ግን አካላቸው በወጉ እየተንቀሳቀሰ አይደለም:: በቂና ተገቢ ሕክምና ያላገኙት በርካታ ቁስለኞች በከባድ ስቃይ ውስጥ ናቸው::

ግዜው የተሟላ ሕክምና ለመስጠት የሚያመች አልሆነም:: የአንድ ወገን ጦር መሸነፍ በሌላው ሥር ለመሆን አስገድዷልና ሁኔታዎች ሁሉ ከፍተዋል:: እንደነገሩ የመጀመሪያ እርዳታ ያገኙት ቁስለኞች ከስፍራው ተንቀሳቅሰዋል:: በወጉ ያልዳኑት ጸጋዬ አሁን ደብረዘይት ጀግኖች አምባ ናቸው:: እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ጓዶቻቸው ጦርነት የተወላቸውን ክፉ ጠባሳ ጋር ዳግም ተገናኝተዋል::

የነሀሴ ወር ዝናብ ጠዋት ማታ መውረዱን ቀጥሏል:: የስፍራውን ሙቀት አልፎ የሚመጣው የክረምት አየር የስፍራውን እንግዶች እየጎበኘ ነው:: በዚህ ስፍራ ያሉ ነፍሶች ስሜታቸው እኩል ነው:: ስለዓላማቸው አካላቸውን ሰጥተዋል:: ዓይናቸውን ገብረዋል:: ሁሉም ግን ስለከፈሉት ክቡር መስዋዕትነት ሽልማታቸው የሀገር ፍቅር ነው:: ዛሬ በሕይወት መቆማቸውን ሲያሥቡ ከጎናቸው የተሰው ጓዶቻቸውን አይዘነጉም::

በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አምባ ግቢ መልከ ብዙ ገጽታዎች በአንድ ውለው ያድራሉ:: የሁሉም ማሰሪያ ገመድ ስለሀገር የተከፈለ ድንቅ መስዋዕትነት ሆኖ ተመዝግቧል:: አሁን በመላው አገሪቱ አዲስ የለውጥ ግዜ ተተክቷል:: እንዲህ መሆኑ በተቃራኒው ለነበሩ ሀይሎች ተጽእኖው ከባድ ነው::

ጸጋዬ በራሻውያን የሕክምና ባለሙዎች ያገኙት ክትትል ቁስላቸውን አጥግጓል:: ሽንጣቸውን ጥሶ ጎናቸውን የነካው ጉዳት ግን እምብዛም ተስፋ አልታየበትም:: ቁስለኛው ወታደር ያለፉትን የጦር ሜዳ ውሎዎች ያስታውሳሉ:: ሁለቴም ሲቆስሉ በቆይታ ብዛት ድነው መነሳት ችለዋል::

ዛሬም እንደትናንቱ ተስፋ ያልቆረጡት ፀጋዬ ቆሞ መሄዳቸውን እየናፈቁ ነው:: ውሎ አድሮ ቀናት በቀናት፣ ወራትም በወራት ተተኩ:: ጸጋዬ የናፈቁት ዕለት አልደረሰም:: ‹‹ቆሜ እራመዳለሁ፤ ተነስቼ እሮጣለሁ ››ያሉበት ምኞት ዕውን አልሆነም:: አሁንም ከአልጋ ሳይነሱ፣ ቆመው ሳይሄዱ መሽቶ ይነጋል:: የአንድ ቀን አጋጣሚ ጸጋዬ ከወገባቸው በታች ያለ አካላቸው እንደማይንቀሳቀስ አሳወቃቸው:: ይህን በተረዱ ግዜ ተስፈኛው ወታደር ቀናቸው ድቅድቅ ጨለማ ሆነባቸው:: ሕይወት፣ ኑሮና ዕቅዳቸው ተዛባ:: ባጋጠማቸው ሁሉ እጅግ ያዘኑት ወታደር ወጣትነታቸው እንደተበላ ባወቁ ግዜ ተስፋቸውን በግል ውሳኔያቸው ሻሩት::

ተስፋ መቁረጥ…

አሁን ጸጋዬ ነገን እያሰቡ አይደለም:: ‹‹ምን ዋጋ አለኝ›› ይሉት ስሜት ከሰውነት አውጥቶ ክፉ ያሳስባቸው ይዟል:: ከእንግዲህ ቆመው እንደማይሄዱ ሲገባቸው በሰው እጅ መውደቁ ያሳስባቸው ጀመር:: ይህ እውነት ደግሞ በዚህ ስሜት ብቻ አልቆመም:: በተስፋ መቁረጥ ራሳቸውን ለማጥፋት ብዙ ሞከሩ::

አንድ ቀን ጸጋዬ የተላጠ ኤሌክትሪክ ጨብጠው ለመሞት ሞከሩ:: አጋጣሚ አልተሳካምና ጥረታቸው ከሸፈ:: እንደገና በሌላ ዕቅድ ተመለሱ:: ለአስራአምስት ቀናት ከምግብ ርቀው ራሳቸውን ቀጡ:: አሁንም ያሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ሕይወታቸው ተረፈ::

ጸጋዬ ደጋግመው ያደረጉት ራስን የመግደል ሙከራ እየከሸፈ ግዚያት ተቆጠሩ:: እንዲህ በሆነ ጥቂት ግዚያት በኋላ በጀግኖች አምባ የሆነው አጋጣሚ ሁኔታውን ሊለውጠው አስገደደ:: በአምባው ግቢ በቁስለኝነት አርፈው የነበሩ ወታደሮች ስፍራውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዙ:: እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ጓዶቻቸው የተባሉትን ከመፈጸም ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም::

አዲስ አበባ መካኒሳ አካባቢ በሚገኘው የአካል ጉዳተኞች ተሀድሶ ማዕከል በደረሱ ግዜ የነበረው ሁኔታ አስደንጋጭና አሳዘኝ ነበር:: በውቅቱ ቦታው ለብዙሀን አመቺ አልሆነም:: ከባድ ብርድ፣ የምግብ ችግርና እንግልት ያገኛቸው ቁስለኞች በየቀኑ ይሞቱ፣ ይሰቃዩ ነበር:: በብዙ መልክ የሚገለጸው የግቢው ችግር ያለአንዳች መፍትሔና ሕክምና ነፍሳቸውን አክርሞት ቆየ:: በብዙ ችግሮች መሀል የተመላለሱት የሀገር ባለውለታዎች ቀናትን አልፈው ሌለ አዲስ ቀን እስኪነጋ ጠበቁ::

ዓመታትን በትዝታና መተሳሳብ ያለፉት የጦር ጉዳተኞች አንዳንዴ በትውስታ መለስ ብለው ትናንትን ይቃኙታል:: ዛሬ ባሉበት እውነት እየተከፉ ቢያዝኑም በሕይወት መኖራቸው ብቻ ተስፋ ይሰጣቸዋል:: ጸጋዬና የትግል ጓዶቻቸው ዛሬ ረጅሙን የዕድሜ ግዚያቸውን በማዕከሉ ኖረው አሳልፈዋል::

ዛሬን…

ዛሬ ጸጋዬ ብዙ መከራዎችን አልፈው በሕይወት ኖረዋል:: የሚንቀሳቀሱበት ዌልቸር የማንነታቸው መገለጫ ነው:: አንዳንዴ በውቅቱ በቂ ሕክምና ያለማግኘታቸው ለጉዳት እንዳበቃቸው ያስቡና ይተክዛሉ:: መልሰው ደግሞ በሕይወት መኖራቸውን እያሰቡ ‹‹ተመስገን:: ይላሉ::

አሁን በበሰለ ዕድሜያቸው ሁሉን ሲያስቡት ሞት ያለ ቀን እንደማትመጣ ይገባቸዋል:: ለውትድርና የተዳረጉበት የቤተሰባቸው መለያየት ብዙ እንዳስከፈላቸው ያውቃሉ:: የእናት አባታቸውን በሕይወት መኖር ሲያስቡት ደግሞ ፈቃዱን ለፈጣሪ ሰጥተው በሆነው ሁሉ ምስጋናን ይቸራሉ:: ዛሬ ጸጋዬን ካሉበት ደርሰው የሚጠይቋቸው ቤተሰቦች ብዙ ናቸው::

ወታደሩ ጸጋዬ ከምንም በላይ ለእናት ሀገራቸው የሚሰጡት ግምት ይለያል:: እሳቸውና መሰል ጓዶቻቸው ስለ ኢትዮጵያ ደም አፍስሰው፣ አጥንት ከስክሰዋል:: ክቡር ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡም በርካቶች ናቸው:: ይህ የሆነው ደግሞ ለኢትዮጵያ በክብር መቆም ሲባል ነው:: ዛሬም ቢሆን ጸጋዬ ውድ ሀገራቸው ሰላሟ ሲሸረፍ ክብሯ ሲነካ በእጅጉ ያማቸዋል::

ስለሀገር…

ጸጋዬ አካላቸው ተጎድቶ በዊልቸር ከዋሉ በኋላ በርካታ የታሪክ መጽሀፍትን አንብበዋል:: ሁሉም በሚባል መልኩ ስለሀገር የሚያወሳ ነው:: በእሳቸው ዕምነት በትውልድ ቅብብሎሽ አደራዋ ተጠብቆ የቆየችው ሀገር ዛሬም እንደትናንቱ ጸንታ ልትቆም ግድ ይላል::

የውጭ ሀይሎች ፍላጎት ስረ መሰረቱ የሩቅ ነውና ሁሉም ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ ቢፈታ ምኞታቸው ነው:: አስር አለቃ ጸጋዬ ስለሀገራቸው ሲወሳ ስሜታቸው ይለያል፤ አንደበታቸው ይሰላል:: ብዙ ሆነው ራሳቸውን የሰውላት ሀገር በእሳቸውና በመሰሎቻቸው ትግል ታሪኳ ቀጥሏል:: ከጦርነት የሚገኘው ትርፍ ግን ሞትና የእሳቸውን መሰል ጉዳት ስለመሆኑ ደግሞ አድምቀው ያሰምሩበታል:: አስር አለቃ ጸጋዬ::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You