እውነት ትቀጥናለች እንጂ አትበጠስም። የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት አንዴ በታሪክ መዝገብ ላይ ታትሟል። ይህ ትልቅ እውነት መቼም ሆነ መቼ ከዓለም የታሪክ ማህደር ላይ በፍፁም መፋቅ አይቻልም፡ ይህን ታሪክ ለመፋቅ በከንቱ የሚተጉ ብዙዎችም ትጋታቸው ከንቱ መሆኑን ዛሬም እንደ ትናንቱ የሚረዱበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
ታሪኳን ለመፋቅ ያሰቡት ተሸናፊዎች የኢትዮጵያን ስም ለማጥፋት ቆርጠው ተነስተዋል። የእነርሱ ትጋት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ፈርሳ ወይም በማይመጥናት መልኩ ኖራ እንድታልፍ ነው። ሁለቱም የጠላቶቻችን አማራጮች በምንም መልኩ ኢትዮጵያ እውን አይሆኑም። ምክንያቱም የጠላቶቻችንን ሴራ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተረድተውታል፤ ተረድተነዋል።
ኢትዮጵያ ከመፍረሷ በፊት ሕዝቦቿ አስቀድመን ነቅተናል። ስለዚህ ከአሁን በኋላ ምንም ዓይነት ጥረት ቢደረግ የኢትዮጵያ ሥም መቼም ሆነ መቼ ከምድረ ገፅ ሊጠፋ አይችልም። ይልቁኑ ከምንጊዜውም በላይ በርሃብ ሳይሆን በጥጋብ፤ በድህነት ሳይሆን በብልፅግና፤ በትንሽነት ሳይሆን በትልቅነት ስሟ የሚጠራበት ጊዜ ደርሷል።
ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ እንደምታድግ፣ እንደምትለማ እና እንደምትበለፅግ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የአንዳንዶችን ሴራ አስመልክቶ መንቃታቸውን ለማረጋገጥ ጥናት አያስፈልግም። በአገሪቱ በዕልህ ከጫፍ ጫፍ ኢትዮጵያ አትፈርስም በማለት ለመዝመት የተነሳሳውን ኢትዮጵያዊ ማየት ብቻ በቂ ነው። ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ከህይወት መስዋእትነት ጀምሮ የሚያስፈልገውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው የተናገሩ ብቻ ሳይሆን ይህንንም በተግባር የፈፀሙትን አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል።
ኢትዮጵያ አትፈርስም በሚል ወኔ ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ ሰልፍ በመውጣት አገር አፍራሾችን የመቃወም ወኔን ከማየት ባሻር፤ ባሳለፍነው እሁድ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ብሔር እና ሐይማኖት ሳይለይ ምድር እስኪጨንቃት የተካሔደው ሰልፍ ላይ የነበረው ህዝብ፤ ከእንባ ጋር ዕልሁን ሲገልፅ ያሰማ የነበረው ድምፅን ማዳመጥ እና ሁኔታውን ማየት ብቻ በቂ ነው።
አሁን የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላቶች የፈለጋቸውን ያህል ተባበረው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢታትሩም በዘይት የተጠበሰ ዓሳ ውሃ ውስጥ ገብቶ ነፍስ እንደማይዘራው ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ያሴሩት ሴራ በፍፁም የማይሳካ መሆኑን ማረጋገጥ ችለዋል። ኢትዮጵያን በማፍረስ የአሸናፊነት ታሪኳን ከማጥፋት በተጨማሪ ሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች ያላቸው አካላት በተለያየ መልኩ ፕሮፖጋንዳ በመስራት ሊከፋፍሉን ጥረት ቢያደርጉም ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን በማሳየት ላይ ነን።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገሪቱን በኢኮኖሚ ለማዳከም ጥረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያውያን ግድግዳ ላይ እንደሚመታ ሚስማር እየጠነከርን እንሔዳለን እንጂ አንሰበርም። ይልቁኑ ጦርነቱን በድል ካጠናቀቅን በኋላ ፊታችንን ወደ ዕድገት ጎዳና በማዞር እልሃችንን በሥራ ላይ በመወጣት ዓለምን የሚያስደንቅ ብልፅግና ላይ መድረሳችን አይቀርም። በእርግጥ አሁን ይህንን እንደምናደርገው የኢትዮጵያ ጠላቶች እያወቁ ናቸው።
የአገር ውስጥ ጠላቶች ድጋፍ በማግኘታቸው ኢትዮጵያውያንን ለማዳከም ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችሉ ተረድተው በሌላ በኩል ከኢትዮጵያውያን ፍቃድ ውጪ ሌላ መንግሥት ለማስቀመጥ ቢያስቡም በፍፁም ሊሳካ አይችልም። ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ አናት ላይ የሚቀመጠው በሕዝብ ፈቃድ ያገኘ አካል ብቻ ነው።
ኢትዮጵያውያን ልምዳችን ነፃነት ነው። ለእዚህ ዛሬም ሆነ ወደ ፊት መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ ነን። ቀድሞ ባላሰብነው እና ባልተረዳነው ሁኔታ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ለሚታዘዝ መንግሥት ታዘናል። አሁን ግን ምስጢሩ በሙሉ ገሃድ ወጥቷል። አሁን ያለው መንግሥት ከውጪ በሚመጣ ፖሊሲ ኢትዮጵያውያን እንደማይመራ አረጋግጧል። ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እና ሃብት ጋር የተጣጣመ ፖሊሲ አውጥቶ በራሱ መንገድ ኢትዮጵያን እንደሚያሳድጋት ነግሮናል። ለዚህም ኢትዮጵያውያን ፍቃዳችንን ሰጥተነዋል።
ይህ ያልተመቻቸው የውጭ ጠላቶች የአሸንጉሊት መንግሥት ለማስቀመጥ የሚያደርጉትን ጥረት ለኛ ለኢትዮጵውያን ትርጉም ያለው ጉዳይ አይደለም። አሁን ላይ እንደቀደመው ዘመን በኢትዮጵያ ላይ የወደዱትን እና የሚመቻቸውን የአሸንጉሊት መንግሥት ለማቋቋም የሚችሉበት ሁኔታ የለም። የሽብር ቡድኖችን በመደገፍ መንግሥትን ለማዳከም የሚያደርጉት ጥረታቸው በመላው ህዝባችን የጋራ ክንድ መክሰሙ አይቀርም። ለዚህም መላው ህዝባችን በገንዘቡ፣ በእውቀቱ እና በጉልበት ሀገሩን ለመታደግ እያደረገ ያለው ርብርብ የዚሁ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ እልኸኞች ናቸው። እልሃቸውን የሚያስተነፍሱት ደግሞ የኢትዮጵያን ህልውና በማረጋገጥ ነው። እልሃቸውን ካላስተነፈሱ አይተኙም። አሁን የውጭ ጠላቶች መጠቀሚያ ዕቃ ሆኖ አገር እያወደመ ህዝብ እየገደለ እንደፊጋ በሬ እየበጠበጠ ያለ ሰው መሰል ዕቃ የተሰበሰበበት ቡድን የእጁን ማግኘቱ አይቀርም።
በእርግጠኝነት የዚህ ቡድን አባላት ውሎ አድሮ አሁን በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈፀሙ ካለው አስነዋሪ ተግባር አንፃር የሚጠየቁትም ሆነ የታሪክ ተወቃሽ የሚሆኑት በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ይሆናል። ፍርድ ቤት የሚቀርቡት በዘር ማጥፋት በዓለም አደባባይ ላይ እንደሚሆን አልጠራጠርም።
በእርግጠኝነት ቡድኑ ብቻ አይደለም በማማከርም ሆነ በተለያየ መንገድ የሚዲያ ዘመቻ በማካሔድ ለጥፋት ሃይሉ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ አጋር ሆነው እያገለገሉ ያሉ አካሎችም ቆይተው ያሰቡት ሳይሆን ሲቀር፤ እውነቱ ሲገለፅ እንደቀደሙት የኢትዮጵያ ጠላቶች በጦርነት ሲሸነፉም ሆነ ኢትዮጵያ የጊዜውን ፈተና ተቋቁማ ስታልፍ አንገታቸውን መድፋታቸው አይቀርም።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፤ የዓድዋ ብቻ ሳይሆን የዚህ ዘመን የድል ታሪኳ በወርቅ ብዕር ይፃፋል። ጦርነቱም ሆነ መከራው፤ ችግሩም ሆነ ርሃቡ ታሪክ ሆኖ ያልፈል። ኢትዮጵያውያን የሚሰደዱ ሳይሆኑ አሁን በድህነት ላይ ሆናም ስደተኞችን እንደምትቀበለው የብልፅግና ማማን ስትቆናጠጠ ደግሞ ዓለም ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ለመሰደድ የሚመኝበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። እርሷም ከልጆቿ አልፋ ተርፋ ብዙዎችን ታቅፋለች። ሰላም!
ፌኔት ኤልያስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2014