የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከአስር ዓመት በፊት ሪፖርት አውጥቶ ነበር። ሪፖርቱ በተለያዩ ዓለምአቀፍ የስፖርት መድረኮች ስፖርተኞች በዘርና በቆዳ ቀለማቸው መገለል የተለመደ እንደሆነ ያትታል። ይህ እውነታ አሁን ላይ አደጉ በምንላቸው አገራት ስፖርት ላይ እንኳን ነቀርሳ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች እንመለከታለን። በተለይም እንደ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና አውሮፓ የመሳሰሉ አገራት ላይ ጥቁር ስፖርተኞች አሁንም ድረስ በዘረኝነት ሲዘለፉ፤ ሲንቋሸሹና ዝቅ ተደርገው የሚታዩባቸው አጋጣሚዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ከዘር፤ ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ነፃ መሆን የሚገባው ስፖርት ላይ መጥፎ አሻራ እያሳረፈ ይገኛል።
ጥቁሮች አሁን ላይ በየትኛውም ዓለምአቀፍ መድረክ ተፎካካሪ ሆነዋል። ከዚህ ባሻገር በትልቅ ደረጃ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ለማሳየት በርካታ ጥቁር ከዋክብት ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠዋል። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን አትሌቶች በዚህ ረገድ ያዩት ፈተና ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።
አፍሪካውያንም ቢሆኑ በርካታ መከራዎችን ተጋፍጠው ለታላቅ ክብር በመብቃት ለአሁኖቹ አትሌቶች ፋና ወጊ ሆነው እኩልነትን ማንፀባረቃቸው አይካድም። ለዚህም ታሪካዊውን ኢትዮጵያዊ የማራቶን ኮከብ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በትልቁ የሚነሳ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያውያን በስፖርቱ ብቻም ሳይሆን በአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና የመዓዘን ድንጋይ ሆነዋል። የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነው የአድዋ ድል የሚዘከርበት የካቲት ወር በመላው ዓለምም የጥቁር ህዝቦች መታሰቢያ ሆኖ ይከበራል። በስፖርቱ ዓለም ለእኩልነት የታገሉ ቁንጮ አትሌቶችም በዚህ ወር ሳይዘከሩ አይታለፉም።
በእርግጥ በስፖርት መድረክ ዘረኝነትን የታገሉ፤ እኩልነትን ያንፀባረቁና በድላቸው የጥቁር ህዝቦችን አንገት ያቀኑ በርካታ ጥቁር ከዋክብቶችን መኖራቸው አይካድም። ከነዚህ ከዋክብት ግን ተፅዕኗቸው ከፍተኛ የነበረ፤ ድላቸው በርካታ ትርጉም የነበረውና በትልቅ ደረጃ የሚነሱትን ሦስት ጀግኖች ብቻ እንመልከት።
አበበ ቢቂላ
1928 ፋሺስት ጣሊያን በአምባገነኑ ቤኒቶ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ወረረ፤ ምስጋና ለማይዘነጉት ጀግኖቹ አርበኞቻችን ይግባና ሞሶሎኒና ግብረ አበሮቹ ብዙም ሳይደላደሉ በቅሌት ተባረሩ። ከሃያ አራት ዓመታት በኋላ ታላቁ አበበ ቢቂላ ሮምን በባዶ እግሩ ወሮ ዓለምን ጉድ አሰኘ፤ የምን ጊዜም የማራቶን ንጉሱ የአፍሪካውያን ኩራትና የነፃነት ተምሳሌት ሆነ። እንዲሁም የመጀመሪያው ጥቁር የማራቶን ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ በጥቁሮቹ ጀግኖች መታሰቢያ ወር የካቲት የጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙንና ሀገሩን አሳረፈ። ከሃምሳ አምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ዋዜማ በሮም ኦሊምፒክ የፈፀመው ታሪካዊ ጀብድ በመላው ዓለም ያሉ ጥቁር አትሌቶችን በእጅጉ ያኮራና ያነሳሳ ሆነ። ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም አስራ ሰባተኛው የሮም ኦሊምፒያድ በታላቋ ሮም ጎዳናዎች አንድ ተዓምር ታየ። በርካቶች አይናቸውን ለማመን ተቸገሩ፤ በአምባገነኑ ሞሶሎኒ አገር በበርካታ ነጮች መሃል አንድ ጥቁር በባዶ እግሩ ተከሰተ።
የጥቁር ህዝቦች ተዓምርን ለመቀበል የሚተናነቃቸው ዘረኝነትን በደማቸው ያሰረፁ ነጮች እንዴት ይህ ሊሆን እንደቻለ ግራ ተጋቡ። አፍሪካውያንን ያኮራ ኢትዮጵያውያንን ከልብ ያስፈነጠዘ ታሪካዊ ድል። የአራት ዓመት ታዳጊ ሆኖ እናት አገሩ ኢትዮጵያ በጣሊያን ፋሺስት ስትወረር መጥፎውን ጊዜ ገና ባልጎለበተ የህፃን አዕምሮው የሚያስታውሰው አበበ ቢቂላ ሃያ ስድስት ዓመታት ጠብቆ ታላቁን የሮም ጎዳና በባዶ እግሩ ወሮ ታሪክ ሰራ። ከአራት ዓመት በኋላም1956ዓ.ም በድጋሜ ጫማ አጥልቆ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሸንፎ ጥቁሮች በማይደፈረው ርቀት አሁን ላይ ቁንጮ እንዲሆኑ መሰረቱን አኖረ።
እርሱ በከፈተው በሮም ቁጥር ስፍር የሌላቸው የማራቶን አትሌቶች ለዘመናት ርቀቱን የግላቸው አድርገው አሁንም ድረስ ዘልቀዋል።
ጄሴ ኦውንስ
ታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ እንደ 1936ቱ በዘረኝነት የተጨማለቀበትን ወቅት ማስታወስ ከባድ ነው። ገና ከጅምሩ አይሁዶችንና ጥቁሮችን ከኦሊምፒኩ ለማግለል እንዲሁም የነጮችን የበላይነት አስተሳሰብ የመደገፍ አባዜ የተጠናወተው ዘረኛው የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር ውድድሩ በአገሩ ጀርመን እንደሚካሄድ ካወቀበት ጊዜ አንስቶ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ይህ ኦሊምፒክ ብዙ ተቃውሞ ቢገጥመውም ከውድድሩ ራሳቸውን ያገለሉና እንዳይሳተፉ የተደረጉ አይሁዳውያን ነበሩ። በውድድሩ የተሳተፉትም ቢሆኑ በሂትለር ትዕዛዝ የተገለለ የመለማመጃ ሜዳና የውድድር ቁሳቁስ እንዲጠቀሙ ተደርገዋል። ጥቁሮችም በዚህ ኦሊምፒክ ተመሳሳይ እጣ ፋንታ የገጠማቸው ሲሆን የበታች እንደሆኑ ለማሳየት ያልተደረገ ጥረት አልነበረም። ይህን ጥረት ሁሉ ውድቅ አድርጎ የሂትለርን ቆሽት ያሳረረ አንድ ክስተት ግን በጥቁሩ አሜሪካዊ አትሌት ጄሴ ኦውንስ ተፈፀመ።
ኦውንስ በዚህ የበርሊን ኦሊምፒክ በመቶ፣ በሁለት መቶ፣ በረጅም ዝላይና አራት በመቶ የዱላ ቅብብል ውድድሮች አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጠራርጎ በመውሰድ ጥቁሮች አንገታቸውን ያቀኑበት ነጮች ደግሞ የተሸማቀቁበትና ለመቀበል ያቃራቸውን ድል አጣጣመ። ይህ አልዋጥለት ያለው ሂትለር ግን በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ኦውንስን ላለመጨበጥና ለድሉም እውቅና ላለመስጠት ራሱን አሳምኖ ስቴድየሙን በድንፋታ ለቆ ወጣ። የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልትም ቢሆኑ ለኦውንስ ድል እውቅና ሳይሰጡት ቀርተዋል። ኦውንስ ይህ ገድሉ በዘረኛ ነጮች እውቅና ይነፈገው እንጂ ነጮች ወደዱም ጠሉም ከጥቁሮች እኩል እንደሆኑ ልቦናቸው እንዲያምን አስገድዷቸዋል። በአንድ አገር ውድድሮች የነጭና የጥቁር ተብሎ ተከፍሎ በሚካሄድባት አሜሪካም በወቅቱ የኦውንስ ድል ትልቅ ትርጉም ነበረው።
በዚህም ኋላ ላይ እኤአ 1976 የአሜሪካውያን ትልቁ ሽልማት የሆነውን የነፃነት ሜዳሊያ ሊሸለም በቅቷል። ኦውንስ ህይወቱን በሙሉም የጥቁሮች መብት እንዲከበር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥብቅና ከመቆም ባሻገር የእሱን ፋና ተክለው ለመጡ ጥቁር አትሌቶች ሁሉ ትልቅ የመንፈስ ብርታት በመሆንከጎናቸው ሲቆምና ሲሟገት ኖሯል።
መሐመድ አሊ
የምን ጊዜም የቦክስ ስፖርት ንጉሱ መሐመድ አሊ የዓለም የቦክስ ቻምፒዮንና ታላቅ የቡጢ ተፋላሚ ብቻ አልነበረም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፤ የጥቁር ህዝቦች ሰንደቅ፤ በመላው ዓለም በስፖርትና በታላቅ ሰብዕና ተምሳሌትም ጭምር ነው። ብዙዎች ቦክስ ስፖርት ሳይሆን የጥጋበኞች ድብድብ አድርገው ከመሳል አስተሳሰብ አውጥቶ የቦክስን ስፖርት ጥበባዊ ገፅታ በማላበስ ተወዳጅና አሁን ላይ በዓለማችን በአንድ ጊዜ በርካታ ሚሊየን ዶላሮች የሚያሳቅፍ ግንባር ቀደም ስፖርት እንዲሆን ተፅዕኖውን አሳርፏል።
መሐመድ የትውልድ ስሙ ካሴስ ክሌይ ቢሆንም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ባሮችን ነፃ ለማውጣት በታገሉ ታላቅ ሰው መታሰቢያነት የወጣለት ስም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ከሆነ በኋላ በማግስቱ ስሙን ለመቀየር ወሰነ። የነፃነት ታጋዩን ማልኮለም ኤክስ ከጎኑ አድርጎ በሰጠው መግለጫ «ዘ ኔሽን ኦፍ ኢስላም» የተባለውን ተቋም መቀላቀሉን በማሳወቅ የባርያ ስም ይለው የነበረውን ካሴስ ክሌይ በመቀየር በቀድሞ ስሙ ላለመጠራት ወሰነ። በወቅቱ «ኔሽን ኦፍ ኢስላምን» ይመራ የነበረው ኤልጅያህ መሃመድ እኤአ በ1964 ላይ መሐመድ አሊ የሚለውን ስም ካወጣለት በኋላ እሱን በማፅደቅ እስከ ህይወት ዘመኑ መጨረሻ ተጠራበት።
ታሪካዊው ኢትዮጵያዊ አትሌት አበበ ቢቂላ በ1960 የሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ለጥቁር ህዝቦች የመጀመሪያውን የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ መሐመድ አሊም በቦክስ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቆ ነበር። ሁለቱ ታሪካዊ የጥቁር ህዝቦች ከዋክብት ፊርማቸውን ተለዋውጠዋል። ይሁንና መሐመድ አሊ ይህን የወርቅ ሜዳልያውን ለአገሩ ከማበርከት ይልቅ በሊውስ ቪል ግዛት በሚገኘው የኦሃዮ ወንዝ ጨምሮታል። ሜዳልያውን ለአሜሪካና ለትውልድ ከተማው ሊውስ ቪል ቢቀዳጅም በርገር የመግዛት እንኳን መብት ባለመኖሩ ተቃውሞውን ለመግለፅ ነበር ይህን ርምጃ የወሰደው። በ1996 አገሩ አሜሪካ ባስተናገደችው የአትላንታ ኦሊምፒክ ችቦውን እንዲለኩስ ከመደረጉ ባሻገር ወንዝ የጨመረው የወርቅ ሜዳልያ ምትክ ሌላ ሜዳሊያ በአንገቱ ተጠልቆለታል።
በ1970 የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሽልማት የተቀበለው መሐመድ አሊ፤ የዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት ተምሳሌት ሆኖ ያውቃል። የተባበሩት መንግስታት የሰላም መልዕክተኛ ሆኖ እኤአ ከ1998 እስከ 2008 በታዳጊ አገራት በመዘዋወር አገልግሏል። ታላቁን የደቡብ አፍሪካ ነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር እንደተፈቱ በአካል ተገኝቶ ደስታውን ለመግለፅ መሐመድን የቀደመው አልነበረም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
በቦጋለ አበበ